የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ቤተ መቅደሱ እንደገና ጸዳ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ኢየሱስ የገንዘብ መንዛሪዎቹን ጠረጴዛ ገለባበጠ

      ምዕራፍ 103

      ቤተ መቅደሱ እንደገና ጸዳ

      ማቴዎስ 21:12, 13, 18, 19 ማርቆስ 11:12-18 ሉቃስ 19:45-48 ዮሐንስ 12:20-27

      • ኢየሱስ አንዲት የበለስ ዛፍ ረገመ፤ ቤተ መቅደሱንም አጸዳ

      • ብዙዎች ሕይወት እንዲያገኙ ኢየሱስ መሞት አለበት

      ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከኢያሪኮ ከመጡ ወዲህ በቢታንያ ሦስት ቀን አድረዋል። ሰኞ፣ ኒሳን 10 ገና በጠዋቱ ወደ ኢየሩሳሌም ጉዞ ጀመሩ። ኢየሱስ ርቦታል። ስለዚህ አንዲት የበለስ ዛፍ ሲመለከት ወደ እሷ ሄደ። ዛፏ ፍሬ ይኖራት ይሆን?

      መጋቢት እየተገባደደ ነው፤ በለስ ደግሞ ከሰኔ በፊት አይደርስም። ያም ቢሆን ዛፏ ከወቅቱ ቀደም ብላ ቅጠል አውጥታለች። በመሆኑም ኢየሱስ አስቀድማ አፍርታ ሊሆን እንደሚችል አስቧል። ሆኖም ዛፏ ላይ አንድም ፍሬ አላገኘም። ዛፏ ቅጠል በማውጣቷ ታሳስታለች። ኢየሱስ “ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት። (ማርቆስ 11:14) የበለስ ዛፏም ወዲያውኑ መድረቅ ጀመረች፤ ይህ ምን ትርጉም እንዳለው ነገ ጠዋት ግልጽ ይሆናል።

      ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ኢየሩሳሌም ደረሱ። ኢየሱስ ትናንት ከሰዓት በኋላ ቤተ መቅደሱን ቃኝቶ ነበር፤ ዛሬም ወደዚያው ሄደ። አሁን ግን በመመልከት ብቻ ሳይወሰን፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በ30 ዓ.ም. በተከበረው የፋሲካ በዓል ላይ የወሰደውን እርምጃ ደገመው። (ዮሐንስ 2:14-16) በዚህ ወቅት ኢየሱስ “በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን” ሰዎች አስወጣ። “የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎችም ገለባበጠ።” (ማርቆስ 11:15) ዕቃ የተሸከመ ማንኛውም ሰው አቋራጭ ለማግኘት ሲል በቤተ መቅደሱ ግቢ አልፎ እንዳይሄድ ከለከለ።

      ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ገንዘብ በሚመነዝሩትና እንስሳት በሚሸጡት ሰዎች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ የወሰደው ለምንድን ነው? እንዲህ አለ፦ “‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈም? እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት።” (ማርቆስ 11:17) ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች፣ ዘራፊዎች ብሎ የጠራቸው ለመሥዋዕት የሚሆኑ እንስሳትን ከእነሱ ከመግዛት ሌላ አማራጭ የሌላቸውን ሰዎች በጣም ውድ ዋጋ ስለሚያስከፍሏቸው ነው። ኢየሱስ እንዲህ ዓይነቱን ንግድ እንደ ዘረፋ ወይም ሌብነት ተመልክቶታል።

      የካህናት አለቆችና ጸሐፍት እንዲሁም የሕዝቡ መሪዎች ኢየሱስ ያደረገውን መስማታቸው አልቀረም፤ በመሆኑም እሱን ለማስገደል እንደገና መንገድ መፈለግ ጀመሩ። ይሁንና አንድ ችግር አጋጠማቸው። እነዚህ ሰዎች፣ ሕዝቡ ሁሉ እሱን ለመስማት እየጎረፈ በመሆኑ እንዴት ሊያስገድሉት እንደሚችሉ ግራ ገባቸው።

      ከአይሁዳውያን በተጨማሪ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎችም በፋሲካ በዓል ላይ ለመገኘት መጥተዋል። ከእነዚህም መካከል ለበዓሉ የመጡ ግሪካውያን ይገኙበታል። እነሱም ወደ ፊልጶስ ቀረቡና ኢየሱስን ሊያዩ እንደሚፈልጉ ነገሩት፤ ሰዎቹ ወደ ፊልጶስ የመጡት የግሪክኛ ስም ስላለው ይሆናል። ፊልጶስ፣ ሰዎቹን ከኢየሱስ ጋር ማገናኘቱ ተገቢ መሆኑን ለማረጋገጥ ሳይሆን አይቀርም ጉዳዩን ለእንድርያስ ነገረው። ከዚያም ሁለቱ ሐዋርያት ይህን በተመለከተ ኢየሱስን አነጋገሩት፤ በዚህ ወቅትም ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ያለ ይመስላል።

      ኢየሱስ ከጥቂት ቀናት በኋላ እንደሚሞት ያውቃል፤ በመሆኑም እሱን ማየት የሚፈልጉ ሰዎችን ለማስተናገድ ወይም ማንነቱን ለማሳወቅ አሁን ጊዜው አይደለም። የሚከተለውን ምሳሌ በመናገር ለሁለቱ ሐዋርያት መልስ ሰጣቸው፦ “የሰው ልጅ ክብር የሚያገኝበት ሰዓት ደርሷል። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ አንዲት የስንዴ ዘር መሬት ላይ ወድቃ ካልሞተች አንድ ዘር ብቻ ሆና ትቀራለች፤ ከሞተች ግን ብዙ ፍሬ ታፈራለች።”—ዮሐንስ 12:23, 24

      አንዲት የስንዴ ዘር ያን ያህል ዋጋ ያላት አትመስል ይሆናል። መሬት ላይ ተዘርታ ‘ከሞተች’ ግን ትበቅላለች፤ ውሎ አድሮም ብዙ የስንዴ ዘሮችን የያዘ ዛላ ታፈራለች። በተመሳሳይም ኢየሱስ ፍጹም የሆነ አንድ ሰው ነው። ይሁንና ለአምላክ ታማኝ ሆኖ ከሞተ፣ ልክ እንደ እሱ የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚያሳዩ በርካታ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ ይከፍታል። በመሆኑም ኢየሱስ “ሕይወቱን የሚወድ ሁሉ ያጠፋታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ሁሉ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል” በማለት ተናገረ።—ዮሐንስ 12:25

      ኢየሱስ ስለ ራሱ ብቻ እየተናገረ አይደለም፤ ምክንያቱም ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “እኔን ሊያገለግል የሚፈልግ ቢኖር ይከተለኝ፤ እኔ ባለሁበት አገልጋዬም በዚያ ይሆናል። የሚያገለግለኝንም ሁሉ አብ ያከብረዋል።” (ዮሐንስ 12:26) ይህ እንዴት ያለ ግሩም ወሮታ ነው! አብ የሚያከብራቸው ሰዎች በአምላክ መንግሥት ከክርስቶስ ጋር አብረው ይገዛሉ።

      ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀውን ከፍተኛ ሥቃይና አሠቃቂ ሞት በማሰብ እንዲህ አለ፦ “አሁን ተጨንቄአለሁ፤ እንግዲህ ምን ማለት እችላለሁ? አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ።” ኢየሱስ ይህን ሲል የአምላክን ፈቃድ መፈጸም እንደማይፈልግ መግለጹ አይደለም። “የመጣሁት ለዚህ ሰዓት ነው” በማለት ተናገረ። (ዮሐንስ 12:27) ኢየሱስ መሥዋዕት ሆኖ መሞትን ጨምሮ የአምላክን ዓላማ ለመፈጸም ተስማምቷል።

      • የበለስ ወቅት ባይደርስም ኢየሱስ በለስ እንደሚያገኝ የጠበቀው ለምንድን ነው?

      • ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚሸጡትን ሰዎች “ዘራፊዎች” ብሎ መጥራቱ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

      • ኢየሱስ ከስንዴ ዘር ጋር ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው? ከፊቱ ስለሚጠብቀው ሥቃይና ሞትስ ምን ተሰማው?

  • አይሁዳውያን የአምላክን ድምፅ ሰምተው ያምኑ ይሆን?
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” አለ፤ በአቅራቢያው የቆሙ አይሁዳውያን የአምላክን ድምፅ ሰሙ

      ምዕራፍ 104

      አይሁዳውያን የአምላክን ድምፅ ሰምተው ያምኑ ይሆን?

      ዮሐንስ 12:28-50

      • ብዙዎች የአምላክን ድምፅ ሰሙ

      • ለፍርድ መሠረት የሚሆነው ነገር

      ሰኞ፣ ኒሳን 10 ገና አልተገባደደም፤ ኢየሱስ አሁንም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሲሆን የሚሞትበት ጊዜ እየቀረበ መሆኑን ተናገረ። በአምላክ ስም ላይ የሚደርሰው ነቀፋ ስላሳሰበው “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” አለ። በዚህ ጊዜ “ስሜን አክብሬዋለሁ፤ ደግሞም አከብረዋለሁ” የሚል ታላቅ ድምፅ ከሰማይ ተሰማ።—ዮሐንስ 12:27, 28

      በቦታው ቆሞ የነበረው ሕዝብ ግራ ተጋባ። አንዳንዶች የተሰማው ድምፅ ነጎድጓድ እንደሆነ አሰቡ። ሌሎች ደግሞ “መልአክ አናገረው” አሉ። (ዮሐንስ 12:29) ይሁንና የተናገረው ይሖዋ ነው! ደግሞም ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ ሰዎች የአምላክን ድምፅ ሲሰሙ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

      ከሦስት ዓመት ተኩል በፊት ኢየሱስ በተጠመቀበት ጊዜ አምላክ “በእሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ስለ ኢየሱስ ሲናገር መጥምቁ ዮሐንስ ሰምቶ ነበር። ከዚያም በ32 ዓ.ም. የፋሲካ በዓል ከተከበረ በኋላ ኢየሱስ በያዕቆብ፣ በዮሐንስና በጴጥሮስ ፊት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ተለወጠ። እነዚህ ሦስት ሰዎች፣ አምላክ “በጣም የምደሰትበት፣ የምወደው ልጄ ይህ ነው። እሱን ስሙት” ብሎ ሲናገር አዳምጠዋል። (ማቴዎስ 3:17፤ 17:5) አሁን ለሦስተኛ ጊዜ ይሖዋ፣ ብዙዎች ሊሰሙ በሚችሉበት መንገድ ተናገረ!

      ኢየሱስ “ይህ ድምፅ የተሰማው ለእኔ ሳይሆን ለእናንተ ሲባል ነው” አለ። (ዮሐንስ 12:30) የአምላክ ድምፅ መሰማቱ፣ ኢየሱስ በእርግጥም የአምላክ ልጅና አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ መሆኑን ያረጋግጣል።

      ኢየሱስ በታማኝነት ያሳለፈው ሕይወት የሰው ልጆች እንዴት መኖር እንዳለባቸው አርዓያ ከመሆኑም ሌላ የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ መጥፋት እንደሚገባው የሚያረጋግጥ ነው። ኢየሱስ “ይህ ዓለም የሚፈረድበት ጊዜ አሁን ነው፤ የዚህ ዓለም ገዢ አሁን ይባረራል” አለ። እየቀረበ ያለው የኢየሱስ ሞት፣ ድል እንጂ ሽንፈት አይደለም። እንዴት? ኢየሱስ “እኔ ግን ከምድር ወደ ላይ ከፍ ከተደረግኩ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ወደ ራሴ እስባለሁ” በማለት የተናገረው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል። (ዮሐንስ 12:31, 32) ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ በመሞት ሌሎችን ወደ ራሱ ይስባል፤ በሌላ አባባል የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ ይከፍትላቸዋል።

      ኢየሱስ ‘ወደ ላይ ከፍ እንደሚደረግ’ ሲናገር ሕዝቡ እንዲህ አሉ፦ “ክርስቶስ ለዘላለም እንደሚኖር ከሕጉ ሰምተናል። ታዲያ አንተ የሰው ልጅ ከፍ ማለት አለበት እንዴት ትላለህ? ይህ የሰው ልጅ ማን ነው?” (ዮሐንስ 12:34) አብዛኞቹ ሰዎች የራሱን የአምላክን ድምፅ መስማትን ጨምሮ ብዙ ማስረጃዎችን የተመለከቱ ቢሆንም ኢየሱስ እውነተኛው የሰው ልጅ ማለትም ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን አላመኑም።

      ኢየሱስ ከዚህ ቀደም እንዳደረገው ሁሉ አሁንም “እኔ . . . ብርሃን ነኝ” በማለት ተናገረ። (ዮሐንስ 8:12፤ 9:5) ከዚያም ሕዝቡን እንዲህ ሲል አሳሰባቸው፦ “ብርሃኑ ለጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር ይቆያል። ጨለማ እንዳይውጣችሁ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃን ሂዱ፤ . . . የብርሃን ልጆች እንድትሆኑ ብርሃኑ እያለላችሁ በብርሃኑ እመኑ።” (ዮሐንስ 12:35, 36) ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ አካባቢውን ለቆ ሄደ፤ ምክንያቱም የሚሞተው ኒሳን 10 አይደለም። ‘ወደ ላይ ከፍ የሚደረገው’ ወይም በእንጨት ላይ የሚቸነከረው ኒሳን 14 በፋሲካ በዓል ላይ ነው።—ገላትያ 3:13

      ኢየሱስ ያከናወነውን አገልግሎት መለስ ብለን ስንመለከት አይሁዶች በእሱ አለማመናቸው አስቀድሞ የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም እንዳደረገ ግልጽ ይሆንልናል። ሕዝቡ ተመልሰው እንዳይፈወሱ፣ ዓይናቸው እንደሚታወርና ልባቸው እንደሚደነድን ኢሳይያስ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳይያስ 6:10፤ ዮሐንስ 12:40) በእርግጥም አብዛኞቹ አይሁዳውያን፣ ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት አዳኛቸውና የሕይወት መንገድ መሆኑን የሚያሳየውን ማስረጃ ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል።

      ኒቆዲሞስ፣ የአርማትያሱ ዮሴፍና ሌሎች በርካታ ገዢዎች በኢየሱስ ‘አምነዋል።’ ሆኖም እነዚህ ሰዎች እምነት እንዳላቸው ያሳዩ ይሆን? ወይስ ከምኩራብ እንዳይባረሩ በመፍራት ወይም ‘ከሰው የሚገኘውን ክብር በመውደድ’ እምነታቸውን ከመግለጽ ወደኋላ ይላሉ?—ዮሐንስ 12:42, 43

      ኢየሱስ በእሱ ማመን ምንን እንደሚጨምር ሲገልጽ “በእኔ የሚያምን ሁሉ በእኔ ብቻ ሳይሆን በላከኝም ጭምር ያምናል፤ እኔን የሚያይ ሁሉ የላከኝንም ያያል” አለ። ኢየሱስ የአምላክን መመሪያ በመከተል የሚያውጀው እውነት በጣም አስፈላጊ በመሆኑ እንዲህ አለ፦ “እኔን የሚንቀውንና ቃሌን የማይቀበለውን ሁሉ የሚፈርድበት አለ። በመጨረሻው ቀን የሚፈርድበት የተናገርኩት ቃል ነው።”—ዮሐንስ 12:44, 45, 48

      ከዚያም ኢየሱስ እንዲህ ሲል ደመደመ፦ “እኔ የተናገርኩት በራሴ ተነሳስቼ አይደለምና፤ ከዚህ ይልቅ ምን እንደምልና ምን እንደምናገር ያዘዘኝ የላከኝ አብ ራሱ ነው። ደግሞም የእሱ ትእዛዝ የዘላለም ሕይወት እንደሚያስገኝ አውቃለሁ።” (ዮሐንስ 12:49, 50) ኢየሱስ በቅርቡ፣ በእሱ ለሚያምኑ ሁሉ ሕይወቱን መሥዋዕት አድርጎ እንደሚሰጥ ያውቃል።—ሮም 5:8, 9

      • ከኢየሱስ ጋር በተያያዘ የአምላክ ድምፅ በየትኞቹ ሦስት ጊዜያት ተሰምቷል?

      • በኢየሱስ ያመኑት ገዢዎች እነማን ናቸው? በእሱ እንደሚያምኑ በግልጽ ያልተናገሩት ለምን ሊሆን ይችላል?

      • “በመጨረሻው ቀን” ሰዎች የሚፈረድባቸው በምን መሠረት ነው?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ