የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በበለስ ዛፍ ተጠቅሞ ስለ እምነት ማስተማር
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ፍሬ የሌላት የበለስ ዛፍ እንደደረቀች አስተዋሉ

      ምዕራፍ 105

      በበለስ ዛፍ ተጠቅሞ ስለ እምነት ማስተማር

      ማቴዎስ 21:19-27 ማርቆስ 11:19-33 ሉቃስ 20:1-8

      • የደረቀችው የበለስ ዛፍ—ስለ እምነት አስተማረ

      • በኢየሱስ ሥልጣን ላይ ጥያቄ ተነሳ

      ኢየሱስ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ከኢየሩሳሌም ወጥቶ በደብረ ዘይት ተራራ ምሥራቃዊ አቀበት ላይ ወደምትገኘው ወደ ቢታንያ ተመለሰ። የሚያድረው ወዳጆቹ በሆኑት በአልዓዛር፣ በማርያምና በማርታ ቤት ሳይሆን አይቀርም።

      አሁን ኒሳን 11 ማለዳ ነው። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም እንደገና መጓዝ ጀመሩ፤ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ለመጨረሻ ጊዜ የሄደው በዚህ ዕለት ነው። እንዲሁም ፋሲካን ከማክበሩ፣ የሞቱን መታሰቢያ በዓል ከማቋቋሙና ሸንጎ ፊት ቀርቦ ከመገደሉ በፊት አገልግሎቱን ያከናወነበት የመጨረሻ ቀን ነው።

      ከቢታንያ በመነሳት በደብረ ዘይት ተራራ አልፈው ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ እያለ ኢየሱስ ትናንት ጠዋት የረገማትን ዛፍ ጴጥሮስ ተመለከተ። ጴጥሮስ “ረቢ፣ ተመልከት! የረገምካት የበለስ ዛፍ ደርቃለች” አለው።—ማርቆስ 11:21

      ይሁንና ኢየሱስ ዛፏ እንድትደርቅ ያደረገው ለምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ ብሎ በተናገረ ጊዜ ምክንያቱን ገልጿል፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ እኔ በበለስ ዛፏ ላይ ያደረግኩትን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት እንኳ ይሆንላችኋል። እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ታገኛላችሁ።” (ማቴዎስ 21:21, 22) ይህን ሲል እምነት ተራራን እንደሚያንቀሳቅስ ከዚህ በፊት የተናገረውን ሐሳብ መድገሙ ነው።—ማቴዎስ 17:20

      ስለዚህ ኢየሱስ ዛፏ እንድትደርቅ በማድረግ፣ ሐዋርያቱ በአምላክ ማመን እንዳለባቸው የሚያስገነዝብ ሠርቶ ማሳያ አቀረበላቸው። “በጸሎት የምትጠይቁትንና የምትለምኑትን ነገር ሁሉ እንዳገኛችሁት አድርጋችሁ እመኑ፤ ደግሞም ታገኙታላችሁ” አላቸው። (ማርቆስ 11:24) ይህ ለሁሉም የኢየሱስ ተከታዮች የሚሆን እንዴት ያለ ጠቃሚ ትምህርት ነው! በተለይ ደግሞ ሐዋርያቱ በቅርቡ ከሚያጋጥሟቸው ከባድ ፈተናዎች አንጻር ይህን ማለቱ ተገቢ ነው! ሆኖም የበለስ ዛፏ መድረቅ ከእምነት ጋር የሚያያዝበት ሌላም መንገድ አለ።

      እንደዚህች የበለስ ዛፍ ሁሉ የእስራኤል ብሔርም አሳሳች መልክ አለው። ሕዝቡ ከአምላክ ጋር በቃል ኪዳን ተዛምዷል፤ እንዲሁም ሕጉን የሚጠብቅ ይመስላል። ይሁንና ብሔሩ በአጠቃላይ እምነት የለሽና መልካም ፍሬ የማያፈራ መሆኑ ታይቷል። ሌላው ቀርቶ የአምላክን ልጅ እንኳ ለመቀበል አሻፈረኝ ብሏል! በመሆኑም ኢየሱስ ፍሬያማ ያልሆነችው የበለስ ዛፍ እንድትደርቅ ማድረጉ፣ ፍሬ የማያፈራውና እምነተ ቢስ የሆነው የዚህ ብሔር የመጨረሻ ዕጣ ምን እንደሆነ ያሳያል።

      ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ገቡ። ኢየሱስ እንደ ልማዱ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ ማስተማር ጀመረ። የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎች “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን ነገሮች እንድታደርግስ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” አሉት። ይህን ያሉት ከአንድ ቀን በፊት ገንዘብ መንዛሪዎቹ ላይ የወሰደውን እርምጃ በአእምሯቸው ይዘው ሳይሆን አይቀርም።—ማርቆስ 11:28

      ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰ፦ “አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ። እናንተም መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። ዮሐንስ የማጥመቅ ሥልጣን ያገኘው ከአምላክ ነው ወይስ ከሰው? መልሱልኝ።” አሁን ተቃዋሚዎቹ ፈተና ገጠማቸው። ካህናቱና ሽማግሌዎቹ ምን ብለው እንደሚመልሱለት ይማከሩ ጀመር፦ “‘ከአምላክ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ ደፍረን ‘ከሰው ነው’ ብንልስ? ሰዎቹ ሁሉ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ያዩት ስለነበር ሕዝቡን ፈሩ።”—ማርቆስ 11:29-32

      የኢየሱስ ተቃዋሚዎች አጥጋቢ መልስ መስጠት አልቻሉም። በመሆኑም “አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።—ማርቆስ 11:33

      • ኒሳን 11⁠ን ለየት የሚያደርገው ምንድን ነው?

      • ኢየሱስ የበለስ ዛፏን በማድረቅ ምን አስተማረ?

      • ኢየሱስ የፈጸማቸውን ነገሮች ያከናወነው በምን ሥልጣን እንደሆነ ጥያቄ ያቀረቡለትን ሰዎች ግራ ያጋባቸው እንዴት ነው?

  • ስለ ወይን እርሻ የተነገሩ ሁለት ምሳሌዎች
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ገበሬዎቹ የወይን እርሻውን ባለቤት ልጅ ሲገድሉት

      ምዕራፍ 106

      ስለ ወይን እርሻ የተነገሩ ሁለት ምሳሌዎች

      ማቴዎስ 21:28-46 ማርቆስ 12:1-12 ሉቃስ 20:9-19

      • ስለ ሁለት ልጆች የተነገረ ምሳሌ

      • ስለ ወይን እርሻ ገበሬዎች የተነገረ ምሳሌ

      ኢየሱስ የፈጸማቸውን ነገሮች የሚያከናውነው በምን ሥልጣን እንደሆነ ቤተ መቅደሱ ውስጥ እያለ ለጠየቁት የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ግራ የሚያጋባ መልስ ሰጥቷቸዋል። ኢየሱስ የሰጠው መልስ አፋቸውን አስያዛቸው። ከዚያም እውነተኛ ማንነታቸውን የሚያጋልጥ ምሳሌ ተናገረ።

      ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ወደ መጀመሪያው ልጁ ሄዶ ‘ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ወደ ወይኑ እርሻ ሄደህ ሥራ’ አለው። ልጁም መልሶ ‘አልሄድም’ አለው፤ በኋላ ግን ጸጸተውና ሄደ። ሁለተኛውንም ቀርቦ እንደዚሁ አለው። ልጁም መልሶ ‘እሺ አባዬ፣ እሄዳለሁ’ አለው፤ ግን አልሄደም። ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” (ማቴዎስ 21:28-31) መልሱ ግልጽ ነው፤ በኋላ ላይ የአባቱን ፈቃድ ያደረገው የመጀመሪያው ልጅ ነው።

      ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች ወደ አምላክ መንግሥት በመግባት ረገድ ይቀድሟችኋል።” ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች አምላክን ለማገልገል በመጀመሪያ ፈቃደኞች አልነበሩም። ይሁንና እንደ መጀመሪያው ልጅ በኋላ ላይ ንስሐ የገቡ ሲሆን አሁን እያገለገሉት ነው። በሌላ በኩል ግን የሃይማኖት መሪዎቹ እንደ ሁለተኛው ልጅ ናቸው፤ አምላክን እናገለግላለን ቢሉም ተግባራቸው ሌላ ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “[መጥምቁ] ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ መጣ፤ እናንተ ግን አላመናችሁትም። ይሁን እንጂ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች አመኑት፤ እናንተ ይህን አይታችሁም እንኳ ጸጸት ተሰምቷችሁ እሱን ለማመን አልፈለጋችሁም።”—ማቴዎስ 21:31, 32

      ኢየሱስ በመቀጠል ሌላም ምሳሌ ተናገረ። በዚህ ምሳሌ ላይ የሃይማኖት መሪዎቹ ጥፋት አምላክን አለማገልገላቸው ብቻ እንዳልሆነ አመልክቷል። እነዚህ ሰዎች ክፉ ናቸው። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “አንድ ሰው የወይን እርሻ አለማ፤ ዙሪያውንም አጠረው፤ ጉድጓድ ቆፍሮም የወይን መጭመቂያ አዘጋጀ፤ ማማም ሠራለት፤ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ። ወቅቱ ሲደርስ ከወይኑ ፍሬ ድርሻውን ከገበሬዎቹ እንዲያመጣለት አንድ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ። እነሱ ግን ይዘው ደበደቡት፤ ባዶ እጁንም ሰደዱት። በድጋሚ ሌላ ባሪያ ወደ እነሱ ላከ፤ እሱንም ራሱን ፈነከቱት፤ ደግሞም አዋረዱት። ሌላም ባሪያ ላከ፤ እሱን ደግሞ ገደሉት፤ ሌሎች ብዙዎችንም ላከ፤ አንዳንዶቹን ደበደቡ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ ገደሉ።”—ማርቆስ 12:1-5

      ኢየሱስን የሚያዳምጡት ሰዎች ምሳሌውን ይረዱ ይሆን? ኢሳይያስ የተናገረውን የሚከተለውን ውግዘት አዘል ሐሳብ ያስታውሱ ይሆናል፦ “የሠራዊት ጌታ የይሖዋ የወይን እርሻ የእስራኤል ቤት ነውና፤ የይሁዳ ሰዎች እሱ ይወደው የነበረው የአትክልት ቦታ ናቸው። ፍትሕን ሲጠብቅ እነሆ፣ ግፍ ይፈጸማል።” (ኢሳይያስ 5:7) የኢየሱስ ምሳሌም ከዚህ ጋር ይመሳሰላል። ባለ ርስቱ ይሖዋ ሲሆን የወይን እርሻው ደግሞ የአምላክ ሕግ እንደ አጥር ከለላ የሆነለት የእስራኤል ብሔር ነው። ይሖዋ፣ ሕዝቡን ለማስተማርና መልካም ፍሬ እንዲያፈሩ ለመርዳት ነቢያት ልኳል።

      ይሁንና “ገበሬዎቹ” ወደ እነሱ ከተላኩት “ባሪያዎች” አንዳንዶቹን አሠቃዩአቸው፤ ሌሎቹንም ገደሏቸው። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “[የወይን እርሻው ባለቤት] የቀረው የሚወደው ልጁ ነበር። ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት በመጨረሻ እሱን ላከው። እነዚያ ገበሬዎች ግን እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው። ኑ እንግደለው፤ ርስቱም የእኛ ይሆናል’ ተባባሉ። ስለዚህ ይዘው ገደሉት።”—ማርቆስ 12:6-8

      ኢየሱስ “እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ምን የሚያደርግ ይመስላችኋል?” በማለት ጠየቀ። (ማርቆስ 12:9) የሃይማኖት መሪዎቹም እንዲህ አሉ፦ “ክፉዎች ስለሆኑ ከባድ ጥፋት ያደርስባቸዋል፤ ከዚያም የወይን እርሻውን፣ ፍሬውን በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል።”—ማቴዎስ 21:41

      ይህን ሲናገሩ ሳያውቁት የፈረዱት በራሳቸው ላይ ነው፤ ምክንያቱም የይሖዋ “የወይን እርሻ” የሆነውን የእስራኤልን ብሔር ከሚያስተዳድሩት “ገበሬዎች” መካከል እነሱም ይገኙበታል። ይሖዋ ከእነዚህ ገበሬዎች ከሚጠብቃቸው ፍሬዎች አንዱ፣ በልጁ ማለትም በመሲሑ ማመን ሲሆን ይህን መጠበቁም ተገቢ ነው። ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹን ትኩር ብሎ በመመልከት እንዲህ አለ፦ “እንዲህ የሚለውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል አላነበባችሁም? ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማዕዘን ራስ ድንጋይ ሆነ። ይህ የይሖዋ ሥራ ነው፤ ለዓይናችንም ድንቅ ነው።’” (ማርቆስ 12:10, 11) ከዚያም ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል የምላችሁ ለዚህ ነው” በማለት ነጥቡን ግልጽ አደረገ።—ማቴዎስ 21:43

      “በዚህ ጊዜ ጸሐፍትና የካህናት አለቆች ይህን ምሳሌ የተናገረው እነሱን አስቦ እንደሆነ” ተረዱ። (ሉቃስ 20:19) ስለዚህ ሕጋዊ ‘ወራሽ’ የሆነውን ኢየሱስን ለመግደል ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቆርጠው ተነሱ። ይሁንና ሕዝቡ እንደ ነቢይ ስለሚያየው ሕዝቡን ፈሩ፤ በመሆኑም በዚህ ወቅት ሊገድሉት አልሞከሩም።

      • በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሱት ሁለት ልጆች እነማንን ያመለክታሉ?

      • በሁለተኛው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው “ባለ ርስት” እና “የወይን እርሻ” እንዲሁም “ገበሬዎቹ፣” “ባሪያዎቹ” እና “ወራሹ” እነማንን ያመለክታሉ?

      • “ገበሬዎቹ” ወደፊት ምን ያጋጥማቸዋል?

  • ንጉሡ ታዳሚዎችን ወደ ሠርግ ድግስ ጠራ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ንጉሡ የሠርግ ልብስ ያልለበሰውን ሰው ከሠርጉ ግብዣ ሲያስወጣው

      ምዕራፍ 107

      ንጉሡ ታዳሚዎችን ወደ ሠርግ ድግስ ጠራ

      ማቴዎስ 22:1-14

      • የሠርጉ ድግስ ምሳሌ

      ኢየሱስ፣ አገልግሎቱ እየተገባደደ ባለበት በዚህ ወቅት ጸሐፍትንና የካህናት አለቆችን ለማጋለጥ ምሳሌዎችን መናገሩን ቀጠለ። በመሆኑም ሊገድሉት ፈለጉ። (ሉቃስ 20:19) ሆኖም ኢየሱስ እነሱን ማጋለጡን አላቆመም። እንዲያውም ሌላ ምሳሌ ነገራቸው፦

      “መንግሥተ ሰማያት ለልጁ ሠርግ ከደገሰ ንጉሥ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ንጉሡም ወደ ሠርጉ የተጋበዙትን እንዲጠሩ ባሪያዎቹን ላከ፤ ተጋባዦቹ ግን ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም።” (ማቴዎስ 22:2, 3) ኢየሱስ ምሳሌውን የጀመረው ስለ “መንግሥተ ሰማያት” በመናገር ነው። በመሆኑም “ንጉሡ” ይሖዋ አምላክን እንደሚያመለክት ማሰቡ ምክንያታዊ ነው። የንጉሡ ልጅና ወደ ሠርጉ ድግስ የተጋበዙትስ? የንጉሡ ልጅ፣ ምሳሌውን እየተናገረ ያለው የይሖዋ ልጅ ኢየሱስ እንደሆነና ወደ ድግሱ የተጠሩት ደግሞ ከልጁ ጋር ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡትን ሰዎች እንደሚያመለክቱ መገንዘብ አይከብድም።

      ወደ ሠርጉ ድግስ እንዲመጡ መጀመሪያ የተጋበዙት እነማን ናቸው? ኢየሱስና ሐዋርያቱ ስለ መንግሥቱ ሲሰብኩ የቆዩት ለእነማን ነው? ለአይሁዳውያን ነው። (ማቴዎስ 10:6, 7፤ 15:24) ይህ ብሔር በ1513 ዓ.ዓ. የሕጉን ቃል ኪዳን ተቀበለ፤ በመሆኑም “የካህናት መንግሥት” የመሆን አጋጣሚ መጀመሪያ የተከፈተው ለዚህ ብሔር ነው። (ዘፀአት 19:5-8) ይሁንና ብሔሩ ወደ ‘ሠርጉ ድግስ’ የተጠራው መቼ ነው? ማስረጃዎቹ እንደሚጠቁሙት ይህ ግብዣ የቀረበው ኢየሱስ ስለ መንግሥተ ሰማያት መስበክ በጀመረበት ጊዜ ማለትም በ29 ዓ.ም. ነው።

      ለመሆኑ አብዛኞቹ እስራኤላውያን ለግብዣው ምን ምላሽ ሰጡ? ኢየሱስ እንደተናገረው ወደ ሠርጉ “ለመምጣት ፈቃደኛ አልሆኑም።” ከሃይማኖት መሪዎቹም ሆነ ከሕዝቡ መካከል ብዙዎቹ፣ ኢየሱስን መሲሕና አምላክ የመረጠው ንጉሥ አድርገው አልተቀበሉትም።

      ይሁንና ኢየሱስ፣ አይሁዳውያን ሌላ አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “[ንጉሡ] በድጋሚ ሌሎች ባሪያዎች ልኮ ‘ተጋባዦቹን “የምሳ ግብዣ አዘጋጅቻለሁ፤ ሰንጋዎቼና የሰቡት ፍሪዳዎቼ ታርደዋል፤ ሁሉም ነገር ዝግጁ ነው። ወደ ሠርጉ ኑ” በሏቸው’ አለ። እነሱ ግን ግብዣውን ችላ በማለት አንዱ ወደ እርሻው፣ ሌላው ወደ ንግዱ ሄደ፤ ሌሎቹ ደግሞ ባሪያዎቹን ይዘው ካንገላቷቸው በኋላ ገደሏቸው።” (ማቴዎስ 22:4-6) ይህ ምሳሌ የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመ በኋላ የሚፈጸመውን ሁኔታ ያመለክታል። በዚያ ወቅት አይሁዳውያን ወደ መንግሥቱ የመግባት አጋጣሚ የተከፈተላቸው ቢሆንም ብዙዎቹ ግብዣውን አልተቀበሉም፤ እንዲያውም ‘የንጉሡን ባሪያዎች’ አንገላቷቸው።—የሐዋርያት ሥራ 4:13-18፤ 7:54, 58

      ታዲያ ይህ በብሔሩ ላይ ምን ያስከትላል? ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ንጉሡም እጅግ ተቆጣ፤ ወታደሮቹንም ልኮ እነዚያን ነፍሰ ገዳዮች ገደለ እንዲሁም ከተማቸውን አቃጠለ።” (ማቴዎስ 22:7) አይሁዳውያን ይህ የደረሰባቸው በ70 ዓ.ም. “ከተማቸውን” ኢየሩሳሌምን ሮማውያን ባጠፏት ጊዜ ነው።

      ይሁንና ይህ ብሔር የንጉሡን ጥሪ ስላልተቀበለ ሌላ ማንም አይጋበዝም ማለት ነው? ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ ይህ እንዳልሆነ ያሳያል። ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ከዚያም [ንጉሡ] ባሪያዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ሠርጉ ተደግሷል፤ የተጋበዙት ግን የሚገባቸው ሆነው አልተገኙም። ስለዚህ በየአውራ ጎዳናው ሂዱና ያገኛችሁትን ሰው ሁሉ ወደ ሠርጉ ጥሩ።’ በዚህ መሠረት ባሪያዎቹ ወደ አውራ ጎዳናዎች ሄደው ክፉውንም ጥሩውንም፣ ያገኙትን ሰው ሁሉ ሰበሰቡ፤ የሠርጉ አዳራሽም በተጋባዦች ተሞላ።”—ማቴዎስ 22:8-10

      ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ፣ አሕዛብን ይኸውም በትውልድ አይሁዳዊ ያልሆኑ እንዲሁም ወደ ይሁዲነት ያልተለወጡ ሰዎችን እውነተኛ ክርስቲያኖች እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። የሮም ሠራዊት አለቃ የሆነው ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ በ36 ዓ.ም. የአምላክን መንፈስ በመቀበላቸው ኢየሱስ የጠቀሰውን መንግሥተ ሰማያት ለመውረስ አጋጣሚ ተከፈተላቸው።—የሐዋርያት ሥራ 10:1, 34-48

      ወደ ግብዣው ከመጡት መካከል ‘በንጉሡ’ ዘንድ ተቀባይነት የማያገኙ እንደሚኖሩ ኢየሱስ ጠቁሟል። እንዲህ አለ፦ “ንጉሡ እንግዶቹን ለማየት ሲገባ የሠርግ ልብስ ያልለበሰ አንድ ሰው አየ። በዚህ ጊዜ ‘ወዳጄ ሆይ፣ የሠርግ ልብስ ሳትለብስ እንዴት እዚህ ልትገባ ቻልክ?’ አለው። ሰውየውም የሚለው ጠፋው። ከዚያም ንጉሡ አገልጋዮቹን ‘እጁንና እግሩን አስራችሁ በውጭ ወዳለው ጨለማ ጣሉት። እዚያም ሆኖ ያለቅሳል፤ ጥርሱንም ያፋጫል’ አላቸው። የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች ናቸውና።”—ማቴዎስ 22:11-14

      ኢየሱስን የሚያዳምጡት የሃይማኖት መሪዎች እሱ የተናገረውን ነገር ትርጉምም ሆነ አንድምታ ሙሉ በሙሉ ላይረዱ ይችላሉ። ያም ቢሆን በተናገረው ነገር ቅር የተሰኙ ከመሆኑም ሌላ እንዲህ እያሳፈራቸው ካለው ሰው ለመገላገል ይበልጥ ተነሳሱ።

      • ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ “ንጉሡ፣” “ልጁ” እና ወደ ሠርጉ ድግስ መጀመሪያ የተጋበዙት እነማን ናቸው?

      • አይሁዳውያን መጀመሪያ ላይ የተጋበዙት መቼ ነው? በኋላስ እነማን ተጋበዙ?

      • የተጠሩት ብዙዎች፣ የተመረጡት ግን ጥቂቶች መሆናቸው ምን ይጠቁማል?

  • ኢየሱስን ለማጥመድ የተጠነሰሰው ሴራ ከሸፈ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ኢየሱስ ለግብር የሚከፈለውን ሳንቲም እያሳየ ፈሪሳውያን ላቀረቡለት የተንኮል ጥያቄ መልስ ሲሰጥ

      ምዕራፍ 108

      ኢየሱስን ለማጥመድ የተጠነሰሰው ሴራ ከሸፈ

      ማቴዎስ 22:15-40 ማርቆስ 12:13-34 ሉቃስ 20:20-40

      • የቄሳር የሆነውን ለቄሳር

      • ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች ያገባሉ?

      • ከሁሉ የሚበልጡት ትእዛዛት

      የኢየሱስ ጠላቶች የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች ተበሳጭተዋል። ኢየሱስ ክፋታቸውን የሚያጋልጡ ምሳሌዎች ተናግሮ መጨረሱ ነው። በዚህ ጊዜ ፈሪሳውያን እሱን ለማጥመድ ሴራ ጠነሰሱ። እሱን ለሮም አገረ ገዢ አሳልፈው ለመስጠት የሚያስችላቸው ነገር እንዲናገር ለማድረግ የሞከሩ ሲሆን ለደቀ መዝሙሮቻቸው ገንዘብ በመክፈል እሱን እንዲያጠምዱ ላኳቸው።—ሉቃስ 6:7

      እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፦ “መምህር፣ አንተ ትክክለኛውን ነገር እንደምትናገርና እንደምታስተምር እንዲሁም እንደማታዳላ፣ ከዚህ ይልቅ የአምላክን መንገድ በእውነት እንደምታስተምር እናውቃለን፦ ለመሆኑ ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባናል ወይስ አይገባንም?” (ሉቃስ 20:21, 22) ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ግብዞችና ተንኮለኞች መሆናቸውን ስለሚያውቅ በሽንገላቸው አልተታለለም። ‘ግብር መክፈል ተገቢ አይደለም’ ብሎ ቢመልስ ‘በሮም መንግሥት ላይ ዓመፅ አነሳስተሃል’ ተብሎ ሊወነጀል ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ‘ግብር መክፈል ተገቢ ነው’ ቢል በሮም ቀንበር ሥር በመውደቃቸው የተማረሩት አይሁዳውያን በተሳሳተ መንገድ ሊረዱትና በእሱ ላይ ሊነሱ ይችላሉ። ታዲያ ኢየሱስ ምን ብሎ ይመልስ ይሆን?

      “እናንተ ግብዞች፣ ለምን ትፈትኑኛላችሁ? እስቲ ለግብር የሚከፈለውን ሳንቲም አሳዩኝ” አላቸው። እነሱም አንድ ዲናር አመጡለት። ኢየሱስ “ይህ ምስልና የተቀረጸው ጽሑፍ የማን ነው?” አላቸው። እነሱም “የቄሳር” አሉ። በዚህ ጊዜ “እንግዲያው የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” በማለት ጥበብ የተንጸባረቀበት መመሪያ ሰጣቸው።—ማቴዎስ 22:18-21

      ሰዎቹ ኢየሱስ በሰጠው መልስ ተደነቁ። ማስተዋል ለታከለበት ንግግሩ ምላሽ መስጠት ስላልቻሉ ትተውት ሄዱ። ይሁንና ቀኑ ገና አላበቃም፤ ሰዎቹም እሱን ለማጥመድ መሞከራቸውን አላቆሙም። ፈሪሳውያን ያደረጉት ጥረት አልተሳካም፤ ከዚያም ሌሎች የሃይማኖት መሪዎች ወደ ኢየሱስ መጡ።

      በትንሣኤ የማያምኑት ሰዱቃውያን፣ ከትንሣኤና ከዋርሳ ጋብቻ ጋር በተያያዘ ጥያቄ አነሱ፦ “መምህር፣ ሙሴ ‘አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ቢሞት ወንድሙ የሟቹን ሚስት ማግባትና ለወንድሙ ዘር መተካት አለበት’ ብሏል። በእኛ ዘንድ ሰባት ወንድማማቾች ነበሩ። የመጀመሪያው ሚስት አግብቶ ልጅ ሳይወልድ በመሞቱ ወንድሙ የሟቹን ሚስት አገባ። ሁለተኛውም ሆነ ሦስተኛው እስከ ሰባተኛው ድረስ ልጅ ሳይወልዱ ሞቱ። በመጨረሻም ሴትየዋ ሞተች። እንግዲህ ሁሉም ስላገቧት በትንሣኤ ከሰባቱ ለየትኛው ሚስት ትሆናለች?”—ማቴዎስ 22:24-28

      ኢየሱስ፣ ሰዱቃውያን የሚያምኑባቸውን የሙሴን መጻሕፍት በመጥቀስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እናንተ የምትሳሳቱት ቅዱሳን መጻሕፍትንም ሆነ የአምላክን ኃይል ባለማወቃችሁ አይደለም? ከሞት በሚነሱበት ጊዜ ወንዶችም አያገቡም ሴቶችም አይዳሩም፤ ከዚህ ይልቅ በሰማያት እንዳሉ መላእክት ይሆናሉ። ስለ ሙታን መነሳት ግን በሙሴ መጽሐፍ፣ ስለ ቁጥቋጦው በሚገልጸው ታሪክ ላይ አምላክ ሙሴን ‘እኔ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ እንዳለው አላነበባችሁም? እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም። እናንተ እጅግ ተሳስታችኋል።” (ማርቆስ 12:24-27፤ ዘፀአት 3:1-6) ሕዝቡ በኢየሱስ መልስ በጣም ተደነቁ።

      ኢየሱስ ፈሪሳውያንንም ሆነ ሰዱቃውያንን ዝም አሰኝቷቸዋል፤ በመሆኑም ተቃዋሚዎቹ የሆኑት እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች እንደገና ሊፈትኑት ግንባር ፈጥረው ወደ እሱ መጡ። አንድ ጸሐፊ “መምህር፣ ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” ሲል ጠየቀው።—ማቴዎስ 22:36

      ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “የመጀመሪያው ይህ ነው፦ ‘እስራኤል ሆይ ስማ፤ ይሖዋ አምላካችን አንድ ይሖዋ ነው፤ አንተም አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህ፣ በሙሉ አእምሮህና በሙሉ ኃይልህ ውደድ።’ ሁለተኛው ደግሞ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ የሚል ነው። ከእነዚህ የሚበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለም።”—ማርቆስ 12:29-31

      ጸሐፊው የኢየሱስን መልስ ሲሰማ እንዲህ አለው፦ “መምህር፣ የተናገርከው እውነት ነው፤ ‘እሱ አንድ ነው፤ ከእሱ ሌላ አምላክ የለም’፤ እሱን በሙሉ ልብ፣ በሙሉ አእምሮና በሙሉ ኃይል መውደድ እንዲሁም ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ፣ ሙሉ በሙሉ ከሚቃጠል መባና ከመሥዋዕት ሁሉ እጅግ ይበልጣል።” ኢየሱስ፣ ጸሐፊው በማስተዋል እንደመለሰ ሲመለከት “አንተ ከአምላክ መንግሥት የራቅክ አይደለህም” አለው።—ማርቆስ 12:32-34

      ኢየሱስ ለሦስት ቀናት (ኒሳን 9, 10 እና 11) በቤተ መቅደሱ ሲያስተምር ቆይቷል። እንደዚህ ጸሐፊ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ደስ እያላቸው አዳምጠውታል። የሃይማኖት መሪዎቹ ግን እንዲህ አልተሰማቸውም፤ እነሱ ‘ከዚህ በኋላ ሊጠይቁት አልደፈሩም።’

      • ፈሪሳውያን ኢየሱስን ለማጥመድ ምን ሙከራ አደረጉ? ውጤቱስ ምን ሆነ?

      • ኢየሱስ ሰዱቃውያን እሱን ለማጥመድ ያደረጉትን ጥረት ያከሸፈው እንዴት ነው?

      • ኢየሱስ ለጸሐፊው በሰጠው መልስ ላይ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ የገለጸው ነገር ምንድን ነው?

  • ተቃዋሚዎቹን አወገዘ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹ የሆኑትን የሃይማኖት መሪዎች አጋለጠ

      ምዕራፍ 109

      ተቃዋሚዎቹን አወገዘ

      ማቴዎስ 22:41–23:24 ማርቆስ 12:35-40 ሉቃስ 20:41-47

      • ክርስቶስ የማን ልጅ ነው?

      • ኢየሱስ የተቃዋሚዎቹን ግብዝነት አጋለጠ

      የኢየሱስ ተቃዋሚ የሆኑት የሃይማኖት መሪዎች፣ እሱን ተቀባይነት ለማሳጣትም ሆነ እሱን በማጥመድ ለሮማውያን አሳልፈው ለመስጠት ያደረጉት ጥረት አልተሳካም። (ሉቃስ 20:20) ዕለቱ ኒሳን 11 ሲሆን ኢየሱስ አሁንም ያለው በቤተ መቅደሱ ነው፤ በዚህ ጊዜ በተራው ጥያቄዎችን በማንሳት እውነተኛ ማንነቱን እንዲያውቁ አደረገ። ቅድሚያውን በመውሰድ “ስለ መሲሑ ምን ትላላችሁ? የማን ልጅ ነው?” ሲል ጠየቃቸው። (ማቴዎስ 22:42) መሲሑ ወይም ክርስቶስ ከዳዊት የዘር ሐረግ እንደሚመጣ በሰፊው ይታወቃል። እነሱም ይህን መልስ ሰጡ።—ማቴዎስ 9:27፤ 12:23፤ ዮሐንስ 7:42

      በዚህ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፦ “ታዲያ ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ እንዴት ጌታ ብሎ ይጠራዋል? ምክንያቱም ዳዊት ‘ይሖዋ ጌታዬን፦ “ጠላቶችህን ከእግርህ በታች እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ” አለው’ ሲል ተናግሯል። ታዲያ ዳዊት ጌታ ብሎ ከጠራው እንዴት ልጁ ይሆናል?”—ማቴዎስ 22:43-45

      ፈሪሳውያን ምንም መልስ አልሰጡም፤ ምክንያቱም እነሱ የሚጠብቁት ከሮማውያን አገዛዝ ነፃ ሊያወጣቸው የሚችል የዳዊት ዘር የሆነ ሰው እንደሚመጣ ነው። ኢየሱስ ግን በመዝሙር 110:1, 2 ላይ ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ በመጥቀስ መሲሑ ከሰብዓዊ ገዢ የበለጠ ሚና እንደሚኖረው ገለጸ። መሲሑ የዳዊት ጌታ ሲሆን በአምላክ ቀኝ ከተቀመጠ በኋላ በሥልጣኑ መጠቀም ይጀምራል። ኢየሱስ የሰጠው መልስ ተቃዋሚዎቹን ጸጥ አሰኛቸው።

      ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ብዙ ሰዎች ኢየሱስን እያዳመጡት ነው። አሁን ኢየሱስ ጸሐፍትንና ፈሪሳውያንን አስመልክቶ ማስጠንቀቂያ ሰጠ። እነዚህ ሰዎች የአምላክን ሕግ ለማስተማር “በገዛ ሥልጣናቸው የሙሴን ቦታ ወስደዋል።” ኢየሱስ አድማጮቹን “የሚነግሯችሁን ነገር ሁሉ አድርጉ፤ ጠብቁትም፤ ሆኖም የሚናገሩትን በተግባር ስለማያውሉ እነሱ የሚያደርጉትን አታድርጉ” በማለት አስጠነቀቀ።—ማቴዎስ 23:2, 3

      ቀጥሎም ኢየሱስ ግብዝነታቸውን የሚያሳይ ምሳሌ ሲጠቅስ “ትልቅ ክታብ ያስራሉ” አለ። አንዳንድ አይሁዳውያን የሕጉን የተወሰኑ ክፍሎች የያዘ ትንሽ ማኅደር በግንባራቸው ወይም በግራ ክንዳቸው ላይ ያስራሉ። ፈሪሳውያን ግን ለሕጉ የሚቀኑ መስለው ለመታየት ሲሉ ትልቅ ክታብ ያስራሉ። ከዚህም ሌላ ‘የልብሳቸውን ዘርፍ ያስረዝማሉ።’ እስራኤላውያን በልብሳቸው ጫፍ ላይ ዘርፍ እንዲያደርጉ ታዘዋል፤ ይሁንና ፈሪሳውያን የልብሳቸውን ዘርፍ በጣም ያስረዝሙታል። (ዘኁልቁ 15:38-40) ይህን ሁሉ የሚያደርጉት “በሰዎች ለመታየት ብለው ነው።”—ማቴዎስ 23:5

      የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም እንኳ ከፍ ያለ ቦታ የማግኘት ፍላጎት ሊያድርባቸው ይችላል፤ በመሆኑም የሚከተለውን ምክር ሰጣቸው፦ “መምህራችሁ አንድ ስለሆነ ረቢ ተብላችሁ አትጠሩ፤ እናንተ ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ። በተጨማሪም አባታችሁ አንድ እሱም በሰማይ ያለው ብቻ ስለሆነ በምድር ላይ ማንንም አባት ብላችሁ አትጥሩ። እንዲሁም መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ ስለሆነ መሪ ተብላችሁ አትጠሩ።” ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ ለራሳቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? ምን ማድረግስ ይኖርባቸዋል? ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ከመካከላችሁ ታላቅ የሆነው የእናንተ አገልጋይ መሆን ይገባዋል። ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል።”—ማቴዎስ 23:8-12

      ኢየሱስ በመቀጠል ግብዝ የሆኑትን ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የሚያወግዝ ነገር በተከታታይ ተናገረ፦ “እናንተ ግብዞች ጸሐፍትና ፈሪሳውያን፣ ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳይገቡ በሩን ስለምትዘጉ ወዮላችሁ! እናንተ ራሳችሁ አትገቡም፤ ለመግባት የሚመጡትንም እንዳይገቡ ትከለክላላችሁ።”—ማቴዎስ 23:13

      ፈሪሳውያን፣ ይሖዋ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸውን ነገሮች አቅልለው ስለሚመለከቱ ኢየሱስ አወገዛቸው፤ ይህ አስተሳሰባቸው ለእነሱ እንደሚመቻቸው በሚያወጧቸው ደንቦች ላይ ተንጸባርቋል። ለምሳሌ ያህል “አንድ ሰው በቤተ መቅደሱ ቢምል ምንም አይደለም፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ባለው ወርቅ ቢምል ግን መሐላውን የመጠበቅ ግዴታ አለበት” ይላሉ። እንዲህ ማለታቸው፣ ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንደማይችሉ ያሳያል፤ ምክንያቱም የይሖዋ የአምልኮ ቦታ ከሆነው ቤተ መቅደስ ይልቅ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለውን ወርቅ ከፍ አድርገው ተመልክተዋል። በመሆኑም “በሕጉ ውስጥ የሚገኙትን እንደ ፍትሕ፣ ምሕረትና ታማኝነት ያሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች” ችላ ብለዋል።—ማቴዎስ 23:16, 23፤ ሉቃስ 11:42

      ኢየሱስ እነዚህን ፈሪሳውያን “እናንተ ዕውር መሪዎች! ትንኝን አጥልላችሁ ታወጣላችሁ፤ ግመልን ግን ትውጣላችሁ!” ብሏቸዋል። (ማቴዎስ 23:24) ፈሪሳውያን ከሚጠጡት ወይን ውስጥ ትንኝን አጥልለው የሚያወጡት በሕጉ መሠረት ርኩስ ስለሆነች ነው። ሆኖም በሕጉ ውስጥ ያሉትን የበለጠ ክብደት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ችላ ማለታቸው ርኩስ የሆነውንና ከትንኝ እጅግ የሚበልጠውን ግመል ከመዋጥ የሚተናነስ አይደለም።—ዘሌዋውያን 11:4, 21-24

      • ዳዊት በመዝሙር 110 ላይ ስለተናገረው ሐሳብ ኢየሱስ ፈሪሳውያንን በጠየቃቸው ጊዜ ዝም ያሉት ለምንድን ነው?

      • ፈሪሳውያን ትላልቅ ክታቦች የሚያስሩትና የልብሳቸውን ዘርፍ የሚያስረዝሙት ለምንድን ነው?

      • ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ምክር ሰጠ?

  • ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ያሳለፈው የመጨረሻ ቀን
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ኢየሱስ አንዲት ድሃ መበለት በቤተ መቅደሱ የመዋጮ ሣጥን ውስጥ ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች ስትከት ተመለከተ

      ምዕራፍ 110

      ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ያሳለፈው የመጨረሻ ቀን

      ማቴዎስ 23:25–24:2 ማርቆስ 12:41–13:2 ሉቃስ 21:1-6

      • ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹን እንደገና አወገዘ

      • ቤተ መቅደሱ ይጠፋል

      • አንዲት ድሃ መበለት ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች መዋጮ አደረገች

      ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ባሳለፈው የመጨረሻ ቀን የጸሐፍትንና የፈሪሳውያንን ግብዝነት ማጋለጡን የቀጠለ ሲሆን ፊት ለፊት “ግብዞች” በማለት ጠራቸው። በምሳሌያዊ አነጋገር በመጠቀም እንዲህ አለ፦ “ጽዋውንና ሳህኑን ከውጭ በኩል ታጸዳላችሁ፤ ውስጡ ግን ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት የሞላበት ነው። አንተ ዕውር ፈሪሳዊ፣ በመጀመሪያ ጽዋውንና ሳህኑን ከውስጥ በኩል አጽዳ፤ ከዚያ በኋላ ከውጭ በኩልም ንጹሕ ይሆናል።” (ማቴዎስ 23:25, 26) ፈሪሳውያን፣ ሕጉ ርኩስ ስለሆኑ ነገሮች የሚሰጠውን መመሪያ ምንም ሳያዛንፉ የሚከተሉና ከውጭ ለሚታዩ ነገሮች ጥንቃቄ የሚያደርጉ ቢሆንም ውስጣዊ ማንነታቸውን ችላ ብለዋል፤ እንዲሁም ምሳሌያዊ ልባቸውን አላጸዱም።

      ለነቢያት መቃብሮች መሥራታቸውና መቃብሮቹን ማስጌጣቸውም ግብዝነታቸውን ያሳያል። ሆኖም ኢየሱስ እንደገለጸው “የነቢያት ገዳዮች ልጆች” ናቸው። (ማቴዎስ 23:31) ኢየሱስን ለመግደል የሚያደርጉት ጥረት ለዚህ ማስረጃ ነው።—ዮሐንስ 5:18፤ 7:1, 25

      ቀጥሎም ኢየሱስ፣ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ንስሐ ካልገቡ ምን እንደሚያጋጥማቸው ሲገልጽ “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች፣ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?” አላቸው። (ማቴዎስ 23:33) በአቅራቢያው ያለው የሂኖም ሸለቆ (ገሃነም) ቆሻሻ የሚቃጠልበት ስፍራ ነው፤ በመሆኑም ኢየሱስ ይህን ማለቱ ክፉ የሆኑት ጸሐፍትና ፈሪሳውያን የሚደርስባቸውን ዘላለማዊ ጥፋት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

      የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ‘ነቢያት፣ ጥበበኞችና የሕዝብ አስተማሪዎች’ በመሆን እሱን ወክለው ይናገራሉ። ታዲያ ሰዎች እንዴት ይቀበሏቸው ይሆን? ኢየሱስ የሃይማኖት መሪዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “[ከደቀ መዛሙርቴ] መካከል አንዳንዶቹን ትገድላላችሁ እንዲሁም በእንጨት ላይ ትሰቅላላችሁ፤ አንዳንዶቹን ደግሞ በምኩራቦቻችሁ ትገርፋላችሁ፤ ከከተማ ወደ ከተማም ታሳድዷቸዋላችሁ፤ በዚህም ምክንያት ከጻድቁ ከአቤል ደም ጀምሮ . . . እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ በምድር ላይ ለፈሰሰው የጻድቃን ደም ሁሉ ተጠያቂ ትሆናላችሁ።” ከዚያም “እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ በዚህ ትውልድ ላይ ይደርሳሉ” በማለት አስጠነቀቀ። (ማቴዎስ 23:34-36) በ70 ዓ.ም. የሮማውያን ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ሲያጠፋና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዳውያን ሲያልቁ ኢየሱስ የተናገረው ነገር ፍጻሜውን አግኝቷል።

      ኢየሱስ ይህን አሰቃቂ ሁኔታ ሲያስበው በጣም ተጨነቀ። በመሆኑም በሐዘን እንዲህ አለ፦ “ኢየሩሳሌም፣ ኢየሩሳሌም፣ ነቢያትን የምትገድል! ወደ እሷ የተላኩትንም በድንጋይ የምትወግር! ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፎቿ ሥር እንደምትሰበስብ እኔም ልጆችሽን ለመሰብሰብ ስንት ጊዜ ፈለግኩ! እናንተ ግን አልፈለጋችሁም። እነሆ፣ ቤታችሁ ለእናንተ የተተወ ይሆናል።” (ማቴዎስ 23:37, 38) ይህን ሲል የሰሙት ሰዎች ስለ የትኛው ‘ቤት’ እየተናገረ እንዳለ ግራ ተጋብተው ይሆናል። በኢየሩሳሌም ስላለውና አምላክ የሚጠብቀው ስለሚመስለው አስደናቂ ቤተ መቅደስ መናገሩ ይሆን?

      ኢየሱስ አክሎም “እላችኋለሁ፣ ‘በይሖዋ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!’ እስክትሉ ድረስ ከእንግዲህ ወዲህ ፈጽሞ አታዩኝም” አላቸው። (ማቴዎስ 23:39) ይህን ሲል በመዝሙር 118:26 ላይ የሚገኘውን “በይሖዋ ስም የሚመጣው የተባረከ ነው፤ በይሖዋ ቤት ሆነን እንባርካችኋለን” የሚለውን ትንቢት መጥቀሱ ነው። ይህ ቤተ መቅደስ ከጠፋ በኋላ በአምላክ ስም ወደዚህ ቦታ የሚመጣ ሰው እንደማይኖር ግልጽ ነው።

      ከዚህ ቀጥሎ ኢየሱስ፣ የመለከት ቅርጽ ያላቸው የመዋጮ ሣጥኖች ወደሚቀመጡበት የቤተ መቅደሱ ክፍል ሄደ። ሕዝቡ የሚሰጡትን ገንዘብ በሣጥኑ አናት ላይ ባለው ትንሽ ቀዳዳ ማስገባት ይችላሉ። ኢየሱስ የተለያዩ አይሁዳውያን ይህን ሲያደርጉ ተመለከተ፤ ሀብታሞቹ “ብዙ ሳንቲሞች” መባ አድርገው እየከተቱ ነው። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ አንዲት ድሃ መበለት “በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች” ስትከት ተመለከተ። (ማርቆስ 12:41, 42) አምላክ በዚህች መበለት ስጦታ ምን ያህል እንደሚደሰት ኢየሱስ ያውቃል።

      በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱን ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ በመዋጮ ሣጥኖቹ ውስጥ ገንዘብ ከጨመሩት ሁሉ የበለጠ የሰጠችው ይህች ድሃ መበለት ነች።” ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ኢየሱስ “ሁሉም የሰጡት ከትርፋቸው ነውና፤ እሷ ግን በድሃ አቅሟ ያላትን ሁሉ፣ መተዳደሪያዋን በጠቅላላ ሰጥታለች” በማለት አብራራ። (ማርቆስ 12:43, 44) የዚህች ሴት አስተሳሰብም ሆነ ድርጊት ከሃይማኖት መሪዎቹ ምንኛ የተለየ ነው!

      ኒሳን 11 እየተገባደደ ሲሄድ ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ቤተ መቅደሱን ለቆ ወጣ። በዚህ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ “መምህር፣ እንዴት ያሉ ግሩም ድንጋዮችና ሕንጻዎች እንደሆኑ ተመልከት!” አለው። (ማርቆስ 13:1) በእርግጥም ቤተ መቅደሱ ከተገነባባቸው ድንጋዮች መካከል አንዳንዶቹ በጣም ትላልቅ በመሆናቸው ቤተ መቅደሱ ጠንካራና የማይፈርስ እንዲመስል አድርገውታል። በመሆኑም ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት መመለሱ ግራ የሚያጋባ ይመስላል፦ “እነዚህን ታላላቅ ሕንጻዎች ታያለህ? ይህ ሁሉ ሳይፈርስ እንዲህ ድንጋይ በድንጋይ ላይ እንደተነባበረ ከቶ አይኖርም።”—ማርቆስ 13:2

      ኢየሱስ ይህን ከተናገረ በኋላ ከሐዋርያቱ ጋር የቄድሮንን ሸለቆ አቋርጦ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጣ። ጴጥሮስ፣ እንድርያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ አጠገቡ ናቸው። ከተራራው ላይ ሆነው አስደናቂውን ቤተ መቅደስ ቁልቁል መመልከት ይችላሉ።

      • ኢየሱስ ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ቤተ መቅደሱ በሄደበት ወቅት ምን አከናወነ?

      • ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ወደፊት ምን እንደሚሆን ተናገረ?

      • ኢየሱስ መበለቷ ከሀብታሞቹ የበለጠ መዋጮ እንዳደረገች የተናገረው ለምንድን ነው?

  • ሐዋርያቱ ምልክት እንዲሰጣቸው ኢየሱስን ጠየቁት
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ኢየሱስ አራት ሐዋርያቱ ላነሱት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ

      ምዕራፍ 111

      ሐዋርያቱ ምልክት እንዲሰጣቸው ኢየሱስን ጠየቁት

      ማቴዎስ 24:3-51 ማርቆስ 13:3-37 ሉቃስ 21:7-38

      • አራት ደቀ መዛሙርት ምልክት ጠየቁ

      • ምልክቱ በመጀመሪያው መቶ ዘመንና ከዚያ በኋላ የሚኖረው ፍጻሜ

      • ምንጊዜም ንቁ መሆን አለብን

      ዕለቱ ማክሰኞ ከቀትር በኋላ ሲሆን ኒሳን 11 እየተገባደደ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ በሥራ ተወጥሮ ያሳለፈው ጊዜም ሊያበቃ ተቃርቧል። ኢየሱስ ቀን ቀን በቤተ መቅደስ ሲያስተምር እየዋለ ማታ ደግሞ ከከተማዋ ውጭ ያድራል። ሕዝቡ ልዩ ትኩረት የሰጡት ሲሆን “በቤተ መቅደስ እሱን ለመስማት በማለዳ ወደ እሱ” ሲመጡ ሰንብተዋል። (ሉቃስ 21:37, 38) ይህ ሁሉ አልፎ አሁን ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ከጴጥሮስ፣ ከእንድርያስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ተቀምጧል።

      እነዚህ አራት ሐዋርያት ወደ እሱ የመጡት ብቻውን ሊያናግሩት ነው። ኢየሱስ የቤተ መቅደሱ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተነባብሮ እንደማይቀር ስለተናገረ ጉዳዩ አሳስቧቸዋል። ይሁንና ያሳሰባቸው ሌላም ነገር አለ። ቀደም ሲል ኢየሱስ፣ “የሰው ልጅ ይመጣል ብላችሁ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ” ብሏቸው ነበር። (ሉቃስ 12:40) በተጨማሪም ‘የሰው ልጅ ስለሚገለጥበት ቀን’ ተናግሯል። (ሉቃስ 17:30) እነዚህ ሐሳቦች አሁን ቤተ መቅደሱን አስመልክቶ ከተናገረው ነገር ጋር የተያያዙ ናቸው? ሐዋርያቱ ይህን ለማወቅ ከፍተኛ ጉጉት አድሮባቸዋል። በመሆኑም “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” አሉት።—ማቴዎስ 24:3

      ይህን ያሉት በቅርብ ርቀት የሚታያቸው ቤተ መቅደስ የሚጠፋበትን ጊዜ በአእምሯቸው ይዘው ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የሰው ልጅ ስለሚገኝበት ጊዜ ጠይቀውታል። ደቀ መዛሙርቱ “ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ለመመለስ” ስለተጓዘ “አንድ መስፍን” ኢየሱስ የተናገረውን ምሳሌ ያስታውሱ ይሆናል። (ሉቃስ 19:11, 12) ከዚህም ሌላ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ለማወቅ ፈልገዋል።

      ኢየሱስ የሰጠው ዝርዝር ሐሳቦችን የያዘ መልስ፣ በወቅቱ ያለው የአይሁድ ሥርዓትና ቤተ መቅደሱ የሚጠፋበትን ጊዜ የሚጠቁም ምልክት ያካተተ ነው። ምልክቱ ግን በዚህ ብቻ አይወሰንም። ይህ ምልክት፣ ወደፊት ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ ላይ የሚኖሩ ክርስቲያኖች የእሱን ‘መገኘት’ እንዲገነዘቡና በምድር ላይ ያለው ሥርዓት የሚደመደምበትን ጊዜ መቅረብ እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል።

      ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሐዋርያቱ የኢየሱስ ትንቢት ሲፈጸም ይመለከታሉ። በእርግጥም ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገራቸው በርካታ ነገሮች እነሱ በሕይወት እያሉ መፈጸም ጀመሩ። በመሆኑም ከ37 ዓመታት በኋላ ማለትም በ70 ዓ.ም. የሚኖሩ ንቁ የሆኑ ክርስቲያኖች፣ የአይሁድ ሥርዓትና ቤተ መቅደሱ የሚጠፉበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ ሁኔታው እንግዳ አልሆነባቸውም። ይሁን እንጂ ክርስቶስ ከተናገራቸው ትንቢቶች መካከል እስከ 70 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ፍጻሜያቸውን ያገኙት ሁሉም አይደሉም። ታዲያ ወደፊት፣ ኢየሱስ በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱን የሚጠቁም ምን ነገር ይፈጸማል? ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የተናገረው ነገር መልሱን ይሰጠናል።

      ኢየሱስ “ጦርነትና የጦርነት ወሬ” እንደሚሰማ እንዲሁም “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንግሥት ላይ” እንደሚነሳ ተነበየ። (ማቴዎስ 24:6, 7) በተጨማሪም “ታላላቅ የምድር ነውጦች ይከሰታሉ፤ በተለያየ ስፍራም የምግብ እጥረትና ቸነፈር ይሆናል” አለ። (ሉቃስ 21:11) ኢየሱስ “ሰዎች ይይዟችኋል፤ ስደት ያደርሱባችኋል” በማለት ደቀ መዛሙርቱን አስጠነቀቃቸው። (ሉቃስ 21:12) ሐሰተኛ ነቢያት ይነሳሉ፤ ብዙዎችንም ያሳስታሉ። ክፋት እየበዛ ይሄዳል፤ እንዲሁም የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል። ከዚህም ሌላ ኢየሱስ “የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተናገረ።—ማቴዎስ 24:14

      ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ኢየሩሳሌም በሮማውያን ከመጥፋቷ በፊትና በምትጠፋበት ወቅት በተወሰነ ደረጃ የተፈጸመ ቢሆንም ምልክቱ ከዚያ በኋላ ታላቅ ፍጻሜ ይኖረው ይሆን? ኢየሱስ የተናገረው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ትንቢት በዘመናችን ዋነኛ ፍጻሜውን እያገኘ እንደሆነ የሚጠቁመውን ማስረጃስ እየተመለከትክ ነው?

      ኢየሱስ፣ መገኘቱን እንደሚጠቁም የሰጠው ምልክት አንዱ ገጽታ “ጥፋት የሚያመጣው ‘ርኩስ ነገር’” መታየቱ ነው። (ማቴዎስ 24:15) በ66 ዓ.ም. የጣዖት አርማ ወይም ምልክት የያዘው የሮም “ጦር ሠራዊት” ሲመጣ ይህ “ርኩስ ነገር” ታይቷል። ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ከበው የግንቡን የተወሰነ ክፍል ማፍረስ ጀመሩ። (ሉቃስ 21:20) በመሆኑም ይህ “ርኩስ ነገር” መቆም በሌለበት ቦታ ማለትም አይሁዳውያን ‘እንደተቀደሰ’ በሚቆጥሩት ስፍራ ቆመ።

      ኢየሱስ ቀጥሎም “ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል” አለ። በ70 ዓ.ም. ሮማውያን ኢየሩሳሌምን አጠፉ። በአይሁዳውያን ‘ቅድስት ከተማ’ እና በቤተ መቅደሱ ላይ የደረሰው ይህ ጥፋት በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነ ታላቅ መከራ ሆኗል። (ማቴዎስ 4:5፤ 24:21) ይህ ጥፋት ኢየሩሳሌምም ሆነች የአይሁድ ሕዝብ ከዚያ ቀደም ካጋጠማቸው ሁሉ የባሰ ነው፤ አይሁዳውያን ለበርካታ ዘመናት ሲከተሉት የነበረው የተደራጀ የአምልኮ ሥርዓት እንዲያበቃ አድርጓል። ከዚህ አንጻር፣ የኢየሱስ ትንቢት ከጊዜ በኋላ የሚኖረው ታላቅ ፍጻሜ እጅግ የከፋ እንደሚሆን ግልጽ ነው።

      ትንቢቱ በሚፈጸምበት ጊዜ መረጋጋት

      ኢየሱስ፣ በመንግሥቱ ሥልጣን መገኘቱንና የዚህን ሥርዓት መደምደሚያ ስለሚጠቁመው ምልክት ከሐዋርያቱ ጋር ያደረገው ውይይት ገና አልተቋጨም። አሁን ደግሞ “ሐሰተኛ ክርስቶሶችና ሐሰተኛ ነቢያት” እንዳያታልሏቸው ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። እነዚህ ሰዎች “ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ” ለማሳት እንደሚሞክሩ ተናገረ። (ማቴዎስ 24:24) ሆኖም እነዚህ የተመረጡ ሰዎች አይታለሉም። ሐሰተኛ ክርስቶሶች በዓይን ይታያሉ። በአንጻሩ ግን ኢየሱስ በሥልጣኑ የሚገኘው በማይታይ ሁኔታ ነው።

      ኢየሱስ አሁን ባለንበት ሥርዓት መጨረሻ ላይ ስለሚኖረው ታላቅ መከራ ሲናገር “ፀሐይ ትጨልማለች፤ ጨረቃም ብርሃኗን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይላትም ይናወጣሉ” አለ። (ማቴዎስ 24:29) ይህን አስፈሪ ሐሳብ የሰሙት ሐዋርያት ምን እንደሚፈጸም በትክክል ባያውቁም ሁኔታው አስደንጋጭ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

      እነዚህ አስፈሪ ክስተቶች ሰዎች ምን እንዲሰማቸው ያደርጋሉ? ኢየሱስ “የሰማያት ኃይላት ስለሚናወጡ ሰዎች ከፍርሃትና በዓለም ላይ የሚመጡትን ነገሮች ከመጠበቅ የተነሳ ይዝለፈለፋሉ” አለ። (ሉቃስ 21:26) በእርግጥም ኢየሱስ በሰው ልጅ ታሪክ ታይቶ የማያውቅ የጨለማ ጊዜ እንደሚመጣ እየገለጸ ነው።

      ሆኖም ኢየሱስ፣ የሰው ልጅ “በኃይልና በታላቅ ክብር” በሚመጣበት ጊዜ የሚያዝኑት ሁሉም ሰዎች እንዳልሆኑ ለሐዋርያቱ በግልጽ የነገራቸው መሆኑ የሚያበረታታ ነው። (ማቴዎስ 24:30) “ለተመረጡት ሲባል” አምላክ ጣልቃ እንደሚገባ ኢየሱስ ቀደም ሲል ገልጿል። (ማቴዎስ 24:22) ታዲያ እነዚያ ታማኝ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ የገለጻቸው አስደንጋጭ ክንውኖች ሲፈጸሙ ምን ሊያደርጉ ይገባል? ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እነዚህ ነገሮች መከሰት ሲጀምሩ መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ” የሚል ማበረታቻ ሰጣቸው።—ሉቃስ 21:28

      ይሁንና ኢየሱስ በተነበየው በዚያ ዘመን የሚኖሩ ደቀ መዛሙርቱ መጨረሻው መቅረቡን ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው? ኢየሱስ ስለ በለስ ዛፍ የሚገልጽ ምሳሌ ሰጠ፦ “ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ። በተመሳሳይ እናንተም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደደረሰ እርግጠኞች ሁኑ። እውነት እላችኋለሁ፣ እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ ይህ ትውልድ ፈጽሞ አያልፍም።”—ማቴዎስ 24:32-34

      ከዚህ አንጻር፣ ደቀ መዛሙርቱ የምልክቱ የተለያዩ ገጽታዎች በመፈጸም ላይ መሆናቸውን ሲመለከቱ መጨረሻው መቅረቡን ሊገነዘቡ ይገባል። ኢየሱስ ታላላቅ ነገሮች በሚከናወኑበት በዚያ ጊዜ ለሚኖሩት ደቀ መዛሙርቱ የሚከተለውን ምክር ሰጠ፦

      “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም። በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል። ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም፤ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል።” (ማቴዎስ 24:36-39) ኢየሱስ፣ የሰው ልጅ ከሚገኝበት ጊዜ ጋር ያወዳደረው ክንውን ይኸውም በኖኅ ዘመን የመጣው የጥፋት ውኃ መላውን ዓለም ያዳረሰ ነው።

      በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆነው ኢየሱስን እያዳመጡ ያሉት ሐዋርያት ንቁ የመሆንን አስፈላጊነት እንደሚገነዘቡ ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከልክ በላይ በመብላትና በመጠጣት እንዲሁም ስለ ኑሮ በመጨነቅ ልባችሁ ሸክም እንዳይበዛበት ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፤ አለዚያ ያ ቀን ድንገት ሳታስቡት እንደ ወጥመድ ይመጣባችኋል። ይህ በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ ይደርስባቸዋልና። እንግዲያው መፈጸማቸው ከማይቀረው ከእነዚህ ሁሉ ነገሮች ማምለጥና በሰው ልጅ ፊት መቆም እንድትችሉ ሁልጊዜ ምልጃ እያቀረባችሁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።”—ሉቃስ 21:34-36

      ኢየሱስ፣ የተናገረው ትንቢት በተወሰነ ዘመን ወይም አካባቢ ላይ ብቻ የሚፈጸም እንዳልሆነ በድጋሚ እየጠቆመ ነው። እየተናገረ ያለው ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በኋላ ስለሚፈጸሙና ኢየሩሳሌምን ወይም የአይሁድን ብሔር ብቻ ስለሚነኩ ክንውኖች አይደለም። ከዚህ ይልቅ “በመላው ምድር በሚኖሩ ሁሉ ላይ” ስለሚደርሱ ክንውኖች መግለጹ ነው።

      ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ምንጊዜም ንቁና ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ተናገረ። ይህን ማስጠንቀቂያ ጠበቅ አድርጎ ለመግለጽም ሌላ ምሳሌ ተጠቀመ፦ “ይህን እወቁ፦ አንድ ሰው ሌባ በየትኛው ክፍለ ሌሊት እንደሚመጣ ቢያውቅ ኖሮ ነቅቶ በጠበቀና ቤቱ እንዳይደፈር በተከላከለ ነበር። ስለዚህ እናንተም የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ።”—ማቴዎስ 24:43, 44

      ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ምክንያት እንዳለም ቀጥሎ ገለጸ። እሱ የተናገረው ትንቢት በሚፈጸምበት ወቅት ንቁ የሆነና በሥራ የተጠመደ “ባሪያ” እንደሚኖር አረጋገጠላቸው። ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ በቀላሉ በአእምሯቸው ሊስሉት የሚችሉ ሁኔታ ጠቀሰ፦ “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው? ጌታው በሚመጣበት ጊዜ እንዲህ ሲያደርግ ካገኘው ያ ባሪያ ደስተኛ ነው! እውነት እላችኋለሁ፣ ጌታው በንብረቱ ሁሉ ላይ ይሾመዋል።” ይሁንና ያ “ባሪያ” ክፉ ቢሆንና ሌሎችን ቢበድል ጌታው “ከባድ ቅጣት ይቀጣዋል።”—ማቴዎስ 24:45-51፤ ከሉቃስ 12:45, 46 ጋር አወዳድር።

      ኢየሱስ ይህን ሲል ግን የተወሰኑ ተከታዮቹ እንደ ክፉ ባሪያ ዓይነት ዝንባሌ እንደሚኖራቸው መግለጹ አይደለም። ታዲያ ለደቀ መዛሙርቱ ሊያስተላልፍ የፈለገው ትምህርት ምንድን ነው? ምንጊዜም ንቁ እንዲሆኑና በሥራ እንዲጠመዱ ይጠብቅባቸዋል፤ ይህንንም ቀጥሎ በሚናገረው ምሳሌ ላይ ግልጽ ያደርገዋል።

      • ሐዋርያቱ ወደፊት ስለሚከናወኑ ነገሮች ጥያቄ እንዲያነሱ የገፋፋቸው ምንድን ነው? ሌላስ ምን ነገር በአእምሯቸው ይዘው ሊሆን ይችላል?

      • የኢየሱስ ትንቢት መፈጸም የጀመረው መቼ ነው? እንዴትስ?

      • ለክርስቶስ መገኘት ምልክት የሚሆኑ አንዳንድ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?

      • “ርኩስ ነገር” የሚታየው እንዴት ነው? ከዚያስ በኋላ የትኞቹ ነገሮች ይፈጸማሉ?

      • ሰዎች የኢየሱስን ትንቢት ፍጻሜ ሲመለከቱ ምን ይሰማቸዋል?

      • ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ መጨረሻው መቅረቡን ማስተዋል እንዲችሉ ምን ምሳሌ ሰጠ?

      • ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት የሚፈጸመው በመላው ዓለም ላይ እንደሆነ የሚጠቁመው ምንድን ነው?

      • ኢየሱስ የሥርዓቱ መደምደሚያ በተቃረበበት ወቅት ለሚኖሩ ደቀ መዛሙርቱ ምን ምክር ሰጠ?

  • ንቁ ስለ መሆን የተሰጠ ትምህርት—ደናግሉ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • አምስቱ ልባም ደናግል መብራቶቻቸውን አብርተው

      ምዕራፍ 112

      ንቁ ስለ መሆን የተሰጠ ትምህርት—ደናግሉ

      ማቴዎስ 25:1-13

      • ኢየሱስ የአሥሩን ደናግል ምሳሌ ተናገረ

      ኢየሱስ፣ ከመገኘቱና ከሥርዓቱ መደምደሚያ ምልክት ጋር በተያያዘ ሐዋርያቱ ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ቆይቷል። አሁንም ተጨማሪ ምሳሌ በመጠቀም ጥበብ ያዘለ ምክር ሰጣቸው። የምልክቱን ፍጻሜ ኢየሱስ በሥልጣኑ በሚገኝበት ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ ሰዎች ይመለከቱታል።

      ኢየሱስ ምሳሌውን ሲጀምር እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማያት መብራታቸውን ይዘው ሙሽራውን ሊቀበሉ ከወጡ አሥር ደናግል ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አምስቱ ሞኞች፣ አምስቱ ደግሞ ልባሞች ነበሩ።”—ማቴዎስ 25:1, 2

      ኢየሱስ፣ መንግሥተ ሰማያትን ከሚወርሱት ደቀ መዛሙርቱ ግማሾቹ ሞኞች ግማሾቹ ደግሞ ልባሞች እንደሆኑ እየተናገረ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከመንግሥተ ሰማያት ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ደቀ መዝሙር ንቁ መሆኑ አሊያም ትኩረቱ መከፋፈሉ በራሱ ምርጫ ላይ የተመካ መሆኑን እየገለጸ ነው። ሆኖም ኢየሱስ፣ እያንዳንዱ የእሱ አገልጋይ ታማኝነቱን መጠበቅና የአባቱን በረከት ማግኘት እንደሚችል እርግጠኛ ነው።

      በምሳሌው ላይ አሥሩም ደናግል ሙሽራውን ለመቀበልና ሠርጉን ለማጀብ ወጥተዋል። ሙሽራው ሲደርስ ደናግሉ መብራታቸውን አብርተው አካባቢውን ያደምቃሉ፤ ሙሽራው ሙሽራይቱን ወደተዘጋጀላት ቤት ሲያመጣት መብራታቸውን ማብራታቸው ለእሱ ያላቸውን አክብሮት ያሳያል። ታዲያ በምሳሌው ላይ የተገለጹት ደናግል ምን አጋጠማቸው?

      ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ሞኞቹ መብራታቸውን ቢይዙም መጠባበቂያ ዘይት አልያዙም ነበር፤ ልባሞቹ ግን ከመብራታቸው ጋር በዕቃ ዘይት ይዘው ነበር። ሙሽራው በዘገየ ጊዜ ሁሉም እንቅልፍ ተጫጫናቸውና ተኙ።” (ማቴዎስ 25:3-5) ሙሽራው እንደተጠበቀው ቶሎ አልመጣም። ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ ይመስላል፤ በዚህ ጊዜ ደናግሉ እንቅልፍ ጣላቸው። ሐዋርያቱ፣ ኢየሱስ ወደ ሩቅ አገር ስለሄደና “ከጊዜ በኋላ ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ” ስለመጣ አንድ መስፍን የነገራቸውን ምሳሌ ያስታውሱ ይሆናል።—ሉቃስ 19:11-15

      ኢየሱስ ስለ አሥሩ ደናግል በተናገረው ምሳሌ ላይ ሙሽራው በመጣበት ወቅት ምን እንደተከናወነ ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “እኩለ ሌሊት ላይ ‘ሙሽራው እየመጣ ነው፤ ወጥታችሁ ተቀበሉት!’ የሚል ጫጫታ ተሰማ።” (ማቴዎስ 25:6) ለመሆኑ ደናግሉ ዝግጁና ንቁ ሆነው ጠብቀውታል?

      ኢየሱስ ቀጥሎ እንዲህ አለ፦ “በዚህ ጊዜ ደናግሉ ሁሉ ተነስተው መብራቶቻቸውን አዘጋጁ። ሞኞቹ ደናግል ልባሞቹን ‘መብራታችን ሊጠፋብን ስለሆነ ከያዛችሁት ዘይት ላይ ስጡን’ አሏቸው። ልባሞቹም ‘ለእናንተ ከሰጠናችሁ ለእኛም ለእናንተም ላይበቃን ስለሚችል ወደ ሻጮች ሄዳችሁ ለራሳችሁ የተወሰነ ዘይት ብትገዙ ይሻላል’ ብለው መለሱላቸው።”—ማቴዎስ 25:7-9

      ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው አምስቱ ሞኝ ደናግል የሙሽራውን መምጣት ንቁና ዝግጁ ሆነው አልጠበቁም። ለመብራታቸው በቂ ዘይት ስላልያዙ ሄደው መግዛት አለባቸው። ኢየሱስ የተፈጸመውን ሁኔታ እንዲህ ሲል ገለጸ፦ “ሊገዙ ሄደው ሳሉም ሙሽራው ደረሰ። ተዘጋጅተው የነበሩት ደናግልም ወደ ሠርጉ ድግስ ገቡ፤ በሩም ተዘጋ። በኋላም የቀሩት ደናግል መጥተው ‘ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ ክፈትልን!’ አሉ። እሱ ግን ‘እውነቴን ነው የምላችሁ፣ አላውቃችሁም’ አላቸው።” (ማቴዎስ 25:10-12) ዝግጁና ንቁ ሆኖ አለመጠበቅ ያስከተለው መዘዝ ምንኛ አሳዛኝ ነው!

      ሐዋርያቱ በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሙሽራ ኢየሱስን እንደሚያመለክት መረዳት ይችላሉ። ከዚህ ቀደም ኢየሱስ ራሱን ከሙሽራ ጋር አመሳስሏል። (ሉቃስ 5:34, 35) ልባሞቹ ደናግልስ ማንን ያመለክታሉ? ኢየሱስ፣ መንግሥት ስለሚወርሰው “ትንሽ መንጋ” ሲናገር “ወገባችሁን ታጠቁ፤ መብራታችሁንም አብሩ” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 12:32, 35) በመሆኑም ስለ ደናግሉ በሚገልጸው በዚህ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ እንደ እነሱ ስላሉ ታማኝ ደቀ መዛሙርት እየተናገረ እንደሆነ ሐዋርያቱ መገንዘብ ይችላሉ። ታዲያ ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ተጠቅሞ ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምንድን ነው?

      ነጥቡን ምንም በማያሻማ መንገድ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል። “እንግዲህ ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት ምሳሌውን ደመደመ።—ማቴዎስ 25:13

      ኢየሱስ ከእሱ መገኘት ጋር በተያያዘ ታማኝ ተከታዮቹ ‘ዘወትር ነቅተው መጠበቅ’ እንደሚያስፈልጋቸው እያሳሰበ እንደሆነ ግልጽ ነው። ኢየሱስ መምጣቱ አይቀርም፤ በመሆኑም ተከታዮቹ ውድ ለሆነው ተስፋቸው ትኩረት ሳይሰጡ ቀርተው ሽልማታቸውን እንዳያጡ እንደ አምስቱ ልባም ደናግል ዝግጁና ንቁ ሆነው መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል።

      • ንቁና ዝግጁ ከመሆን ጋር በተያያዘ አምስቱ ልባም ደናግል ከአምስቱ ሞኝ ደናግል የሚለዩት እንዴት ነው?

      • ሙሽራው ማንን ያመለክታል? ደናግሉስ?

      • ኢየሱስ ስለ አሥሩ ደናግል በሚገልጸው ምሳሌ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምንድን ነው?

  • ትጉ ስለ መሆን የተሰጠ ትምህርት—ታላንቱ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • አንድ ባሪያ በከረጢት የተቋጠረ ገንዘብ መሬት ውስጥ ሲቀብር

      ምዕራፍ 113

      ትጉ ስለ መሆን የተሰጠ ትምህርት—ታላንቱ

      ማቴዎስ 25:14-30

      • ኢየሱስ የታላንቱን ምሳሌ ተናገረ

      ኢየሱስ ከአራት ሐዋርያቱ ጋር በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነው፤ እዚያው እያሉ ሌላ ምሳሌ ነገራቸው። ከጥቂት ቀናት በፊት በኢያሪኮ እያለ፣ መንግሥቱ የሚመጣው ወደፊት እንደሆነ ለማመልከት የምናኑን ምሳሌ ተናግሮ ነበር። አሁን የተናገረው ምሳሌ ከምናኑ ምሳሌ ጋር የሚያመሳስለው ብዙ ነገር አለ። ይህ ምሳሌ፣ ስለ መገኘቱና ስለ ሥርዓቱ መደምደሚያ ለቀረበለት ጥያቄ የሰጠው መልስ ክፍል ነው። ደቀ መዛሙርቱ በአደራ የሰጣቸውን ሥራ በትጋት ማከናወን እንዳለባቸው ያጎላል።

      ኢየሱስ ምሳሌውን ሲጀምር እንዲህ አለ፦ “መንግሥተ ሰማያት ባሪያዎቹን ጠርቶ ንብረቱን ለእነሱ በአደራ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ከተነሳ ሰው ጋር ይመሳሰላል።” (ማቴዎስ 25:14) ቀደም ሲል ኢየሱስ፣ ራሱን “ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ለመመለስ” ወደ ሌላ አገር ከተጓዘ ሰው ጋር ስላመሳሰለ ሐዋርያቱ አሁን በሚናገረው ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው “ሰው” እሱ እንደሆነ በቀላሉ ማስተዋል ይችላሉ።—ሉቃስ 19:12

      በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሰው ወደ ሌላ አገር ከመጓዙ በፊት ውድ ንብረቱን ለባሪያዎቹ በአደራ ሰጣቸው። ኢየሱስ ለሦስት ዓመት ተኩል ባከናወነው አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገው የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበክ ላይ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱንም ለዚህ ሥራ አሠልጥኗቸዋል። እንዲሠሩ ያሠለጠናቸውን ሥራ እንደሚያከናውኑ በመተማመን አሁን ትቷቸው ሊሄድ ነው።—ማቴዎስ 10:7፤ ሉቃስ 10:1, 8, 9፤ ከዮሐንስ 4:38 እና 14:12 ጋር አወዳድር።

      በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው ሰው ንብረቱን ያከፋፈለው እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው፣ ለአንዱ አምስት ታላንት፣ ለሌላው ሁለት፣ ለሌላው ደግሞ አንድ በመስጠት ወደ ሌላ አገር ሄደ።” (ማቴዎስ 25:15) እነዚህ ባሪያዎች በአደራ የተሰጣቸውን ንብረት ምን ያደርጉታል? ጌታቸው ትርፍ እንዲያገኝ ሲሉ የተሰጣቸውን ታላንት ተጠቅመው በትጋት ይሠሩ ይሆን? ኢየሱስ ሐዋርያቱን እንዲህ አላቸው፦

      “አምስት ታላንት የተቀበለው ሰው ወዲያው ሄዶ ነገደበትና ሌላ አምስት ታላንት አተረፈ። በተመሳሳይም ሁለት ታላንት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ። አንድ ታላንት ብቻ የተቀበለው ባሪያ ግን ሄዶ መሬት ቆፈረና ጌታው የሰጠውን ገንዘብ ቀበረ።” (ማቴዎስ 25:16-18) ታዲያ ጌታቸው ሲመለስ ምን ያደርጋል?

      ኢየሱስ በመቀጠል “ከረጅም ጊዜ በኋላ የእነዚያ ባሪያዎች ጌታ መጥቶ ሒሳቡን ከባሪያዎቹ ጋር ተሳሰበ” አለ። (ማቴዎስ 25:19) የመጀመሪያዎቹ ሁለት ባሪያዎች ‘እንደ ችሎታቸው’ ይኸውም አቅማቸው የፈቀደውን ያህል ሠርተዋል። ሁለቱም ባሪያዎች በአደራ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ትጉ፣ ታታሪና ውጤታማ ሆነዋል። አምስት ታላንትም ሆነ ሁለት ታላንት የተሰጠው ባሪያ የተቀበለውን እጥፍ አድርጓል። (በወቅቱ አንድ ሠራተኛ አንድ ታላንት ለማግኘት 19 ዓመት ገደማ መሥራት ነበረበት።) ጌታው እያንዳንዱን ባሪያ እንደሚከተለው በማለት አመሰገነ፦ “ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ።”—ማቴዎስ 25:21

      1. አንድ ባሪያ በከረጢት የተቋጠረ ገንዘብ መሬት ውስጥ ሲቀብር፤ 2. ይኸው ባሪያ በውጭ ወዳለው ጨለማ ሲጣል

      አንድ ታላንት የተቀበለው ባሪያ ሁኔታ ግን የተለየ ነው። ይህ ባሪያ እንዲህ አለ፦ “ጌታ ሆይ፣ አንተ ያልዘራኸውን የምታጭድ፣ ያልደከምክበትንም እህል የምትሰበስብ ኃይለኛ ሰው መሆንህን አውቃለሁ። ስለዚህ ፈራሁ፤ ሄጄም ታላንትህን መሬት ውስጥ ቀበርኩት። ገንዘብህ ይኸውልህ።” (ማቴዎስ 25:24, 25) ይህ ባሪያ፣ ታላንቱን ገንዘብ ለዋጮች ጋ በማስቀመጥ ጌታው የተወሰነ ትርፍ እንዲያገኝ እንኳ አላደረገም። በእርግጥም የጌታውን ጥቅም የሚነካ ነገር ፈጽሟል።

      ጌታው ይህን ግለሰብ “ክፉና ሰነፍ ባሪያ” ብሎ መጥራቱ የተገባ ነው። ያለው ንብረት ከእሱ ተወሰደና በትጋት ለመሥራት ፈቃደኛ ለሆነው ባሪያ ተሰጠ። ጌታው የሚመራበትን ደንብ ሲገልጽ “ላለው ሁሉ ይጨመርለታል፤ ደግሞም ይትረፈረፍለታል። የሌለው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል” አለ።—ማቴዎስ 25:26, 29

      የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሲሰብኩ

      የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ምሳሌ ጨምሮ ሊያስቡበት የሚገባ ብዙ ነገር አለ። ኢየሱስ በአደራ የሰጣቸው ነገር ይኸውም ደቀ መዛሙርት የማድረግ ውድ መብት ከፍ ተደርጎ ሊታይ እንደሚገባ መገንዘብ ይችላሉ። ደግሞም ይህን ኃላፊነት በትጋት እንዲወጡ ይጠብቅባቸዋል። ኢየሱስ፣ የሰጣቸውን የስብከት ሥራ ሁሉም በእኩል መጠን ማከናወን እንዳለባቸው አያስብም። በምሳሌው ላይ እንደተገለጸው “እያንዳንዱ እንደ ችሎታው” ይኸውም አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይኖርበታል። ያም ቢሆን አንድ ባሪያ “ሰነፍ” ቢሆንና የጌታውን ንብረት ለማብዛት የተቻለውን ያህል ባይጥር ኢየሱስ በእሱ ፈጽሞ ደስ አይሰኝም።

      ሐዋርያቱ “ላለው ሁሉ ይጨመርለታል” የሚለውን ማረጋገጫ ሲሰሙ ምንኛ ተደስተው ይሆን!

      • ስለ ታላንቱ በተነገረው ምሳሌ ላይ በጌታው የተመሰለው ማን ነው? በባሪያዎቹስ?

      • ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ምን ትምህርት ሰጠ?

  • ክርስቶስ በመንግሥቱ በበጎችና በፍየሎች ላይ ይፈርዳል
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች የኢየሱስን ፍርድ እየተጠባበቁ ወደ ሰማይ ሲመለከቱ

      ምዕራፍ 114

      ክርስቶስ በመንግሥቱ በበጎችና በፍየሎች ላይ ይፈርዳል

      ማቴዎስ 25:31-46

      • ኢየሱስ የበጎቹንና የፍየሎቹን ምሳሌ ተናገረ

      ኢየሱስ አሁንም በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ነው፤ ስለ አሥሩ ደናግልና ስለ ታላንቱ የሚገልጹትን ምሳሌዎች ተናግሮ መጨረሱ ነው። ሐዋርያቱ ስለ መገኘቱና ስለ ሥርዓቱ መደምደሚያ ምልክት ላቀረቡለት ጥያቄ የሰጠውን መልስ እንዴት ይደመድመው ይሆን? ስለ በጎችና ፍየሎች የሚገልጽ የመጨረሻ ምሳሌ ተናገረ።

      ኢየሱስ “የሰው ልጅ ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ በክብራማ ዙፋኑ ላይ ይቀመጣል” በማለት የምሳሌውን መቼት ገለጸ። (ማቴዎስ 25:31) በምሳሌው ላይ ጉልህ ሚና የሚጫወተው እሱ ራሱ እንደሆነ በግልጽ ጠቁሟል። ኢየሱስ፣ ራሱን “የሰው ልጅ” በማለት በተደጋጋሚ ጠርቷል።—ማቴዎስ 8:20፤ 9:6፤ 20:18, 28

      ኢየሱስ በክብራማው ዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ታማኝ ሰዎችን በጎች እንደሆኑ ሲፈርድላቸው

      ይህ ምሳሌ ፍጻሜውን የሚያገኘው መቼ ነው? ኢየሱስ “ከመላእክቱ ሁሉ ጋር በክብሩ ሲመጣ” እንዲሁም “በክብራማ ዙፋኑ ላይ” ሲቀመጥ ነው። የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር “በኃይልና በታላቅ ክብር በሰማይ ደመና” እንደሚመጣ ኢየሱስ ቀደም ሲል ተናግሯል። ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ‘ከመከራው በኋላ ወዲያውኑ’ ነው። (ማቴዎስ 24:29-31፤ ማርቆስ 13:26, 27፤ ሉቃስ 21:27) እንግዲያው ይህ ምሳሌ ፍጻሜውን የሚያገኘው ወደፊት ኢየሱስ በክብሩ ሲመጣ ነው። በዚያ ወቅት ምን ያደርጋል?

      ኢየሱስ ‘የሰው ልጅ ሲመጣ ሕዝቦች ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ’ አለ፤ ከዚያም “እረኛ በጎቹን ከፍየሎቹ እንደሚለይ ሁሉ እሱም ሰዎችን አንዱን ከሌላው ይለያል። በጎቹን በቀኙ፣ ፍየሎቹን ግን በግራው ያደርጋቸዋል” በማለት ተናገረ።—ማቴዎስ 25:31-33

      የንጉሡን ሞገስ ያገኙትን በጎች በተመለከተ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከዚያም ንጉሡ በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።’” (ማቴዎስ 25:34) በጎቹ የንጉሡን ሞገስ የሚያገኙት ለምንድን ነው?

      ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ “ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል። እንግዳ ሆኜ አስተናግዳችሁኛል፤ ታርዤ አልብሳችሁኛል። ታምሜ አስታማችሁኛል። ታስሬ ጠይቃችሁኛል።” “ጻድቃን” የተባሉት እነዚህ በጎች ከላይ የተጠቀሱትን መልካም ነገሮች ለንጉሡ ያደረጉለት በምን መንገድ እንደሆነ ሲጠይቁ ንጉሡ “ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት ሁሉ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ይቆጠራል” በማለት መለሰላቸው። (ማቴዎስ 25:35, 36, 40, 46) በሰማይ የታመሙ ወይም የተራቡ ስለሌሉ በጎቹ እነዚህን መልካም ነገሮች የሚያደርጉት በሰማይ አይደለም። እነዚህን ነገሮች ያደረጉት በምድር ላሉት የክርስቶስ ወንድሞች መሆን አለበት።

      ታማኝ ያልሆኑ ሰዎች ፍየሎች እንደሆኑ ተፈርዶባቸው

      ንጉሡ በስተ ግራው ያደረጋቸው ፍየሎችስ ዕጣ ምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ከዚያም [ንጉሡ] በግራው ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፦ ‘እናንተ የተረገማችሁ፣ ከእኔ ራቁ፤ ለዲያብሎስና ለመላእክቱ ወደተዘጋጀው ዘላለማዊ እሳት ሂዱ። ምክንያቱም ተርቤ አላበላችሁኝም፤ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝም። እንግዳ ሆኜ አላስተናገዳችሁኝም፤ ታርዤ አላለበሳችሁኝም፤ ታምሜና ታስሬ አልጠየቃችሁኝም።’” (ማቴዎስ 25:41-43) ፍየሎቹ እንዲህ ዓይነት ፍርድ የተበየነባቸው በምድር ያሉትን የክርስቶስ ወንድሞች በደግነት መያዝ ሲገባቸው እንዲህ ስላላደረጉ ነው።

      ሐዋርያቱ ወደፊት የሚከናወነው ይህ ፍርድ የማይለወጥና ዘላለማዊ እንደሆነ ይገነዘባሉ። ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “[ንጉሡም] መልሶ ‘እውነት እላችኋለሁ፣ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ይህን ሳታደርጉ መቅረታችሁ ለእኔ እንዳላደረጋችሁት ይቆጠራል’ ይላቸዋል። እነዚህ ወደ ዘላለም ጥፋት ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።”—ማቴዎስ 25:45, 46

      ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ጥያቄ የሰጠው ምላሽ ተከታዮቹ ሊያስቡባቸው የሚገቡ ብዙ ነጥቦችን ይዟል፤ ይህ ትምህርት ዝንባሌያቸውንና ተግባራቸውን እንዲመረምሩ ሊያደርጋቸው ይገባል።

      • ኢየሱስ፣ ስለ በጎችና ፍየሎች በተናገረው ምሳሌ ላይ “ንጉሡ” ማን ነው? ምሳሌው ፍጻሜውን የሚያገኘውስ መቼ ነው?

      • በጎቹ የኢየሱስን ሞገስ እንዳገኙ ተደርጎ የተፈረደላቸው ለምንድን ነው?

      • አንዳንዶች ፍየል እንደሆኑ ተደርገው እንዲፈረድባቸው መሠረት የሆነው ነገር ምንድን ነው? የበጎቹና የፍየሎቹ የወደፊት ዕጣስ ምንድን ነው?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ