የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ባዶ መቃብር—ኢየሱስ ሕያው ሆነ!
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ሴቶቹ የኢየሱስን መቃብር ባዶ በማግኘታቸው ደንግጠው

      ምዕራፍ 134

      ባዶ መቃብር—ኢየሱስ ሕያው ሆነ!

      ማቴዎስ 28:3-15 ማርቆስ 16:5-8 ሉቃስ 24:4-12 ዮሐንስ 20:2-18

      • ኢየሱስ ከሞት ተነሳ

      • የኢየሱስ መቃብር ጋ ያጋጠሙ ነገሮች

      • ኢየሱስ ለተለያዩ ሴቶች ተገለጠ

      ሴቶቹ መቃብሩን ባዶ ሆኖ ሲያገኙት ምንኛ ደንግጠው ይሆን! መግደላዊቷ ማርያም “ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር” ይኸውም ወደ ሐዋርያው ዮሐንስ እየሮጠች ሄደች። (ዮሐንስ 20:2) መቃብሩ ቦታ የቀሩት ሌሎቹ ሴቶች ግን አንድ መልአክ አዩ። በመቃብሩ ውስጥ ደግሞ “ነጭ ልብስ የለበሰ” ሌላ መልአክ አለ።—ማርቆስ 16:5

      ከመላእክቱ አንዱ እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ፤ በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ኢየሱስን እየፈለጋችሁ እንደሆነ አውቃለሁ። አስቀድሞ እንደተናገረው ከሞት ስለተነሳ እዚህ የለም። ኑና አስከሬኑ አርፎበት የነበረውን ስፍራ እዩ። ስለሆነም ፈጥናችሁ ሂዱና ለደቀ መዛሙርቱ ከሞት እንደተነሳ ንገሯቸው፤ ‘እነሆ፣ ቀድሟችሁ ወደ ገሊላ ይሄዳል። . . .’ በሏቸው።” (ማቴዎስ 28:5-7) ስለዚህ ሴቶቹ “በአድናቆት ተውጠው በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ” ዜናውን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ።—ማርቆስ 16:8

      በዚህ ጊዜ ማርያም፣ ጴጥሮስንና ዮሐንስን አግኝታቸዋለች። ትንፋሿ እየተቆራረጠ “ጌታን ከመቃብሩ ውስጥ ወስደውታል፤ የት እንዳኖሩትም አናውቅም” አለቻቸው። (ዮሐንስ 20:2) ጴጥሮስና ዮሐንስም ይህን ሲሰሙ ወዲያውኑ መሮጥ ጀመሩ። ዮሐንስ ፈጣን በመሆኑ መቃብሩ ጋ ቀድሞ ደረሰ። ዮሐንስ ጎንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ሲመለከት የበፍታ ጨርቆቹን አየ፤ ወደ ውስጥ ግን አልገባም።

      ጴጥሮስ ግን መቃብሩ ጋ ሲደርስ ሰተት ብሎ ወደ ውስጥ ገባ። በዚያም የበፍታ ጨርቆቹንና የኢየሱስ ራስ የተሸፈነበትን ጨርቅ ተመለከተ። በዚህ ጊዜ ዮሐንስም ወደ ውስጥ ገባ፤ ማርያም የነገረችውንም አመነ። ኢየሱስ አስቀድሞ የነገራቸው ቢሆንም አንዳቸውም ከሞት እንደተነሳ አልገባቸውም። (ማቴዎስ 16:21) በነገሩ ግራ ተጋብተው ወደ ቤት ተመለሱ። ወደ መቃብሩ ቦታ ተመልሳ የመጣችው ማርያም ግን እዚያው ቆየች።

      ይህ በእንዲህ እንዳለ ሌሎቹ ሴቶች ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ለደቀ መዛሙርቱ ለመንገር እየሮጡ ሄዱ። መንገድ ላይ እያሉ ኢየሱስ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነሱም እግሩ ላይ ወድቀው “ሰገዱለት።” ከዚያም ኢየሱስ “አትፍሩ! ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሯቸው፤ እዚያም ያዩኛል” አላቸው።—ማቴዎስ 28:9, 10

      ቀደም ሲል የምድር መናወጥ ሲከሰትና መላእክቱ ሲገለጡ መቃብሩ ጋ የነበሩት ወታደሮች ‘ተንቀጥቅጠው፣ እንደ በድን ሆነው’ ነበር። ድንጋጤያቸው ለቀቅ ሲያደርጋቸው “ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ ለካህናት አለቆቹ ነገሯቸው።” የካህናት አለቆቹም ከአይሁድ ሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ተማከሩ። ከዚያም ወታደሮቹ ጉዳዩን በሚስጥር እንዲይዙትና “ሌሊት ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው አስከሬኑን ሰረቁት” ብለው እንዲናገሩ ለማድረግ ጉቦ ሊሰጧቸው ወሰኑ።—ማቴዎስ 28:4, 11, 13

      ሮማውያን ወታደሮች በጥበቃ ሥራ ላይ እያሉ ካንቀላፉ በሞት ሊቀጡ ይችላሉ፤ በመሆኑም ካህናቱ “አትጨነቁ፤ ወሬው [ስለ መተኛታቸው የሚናገሩት ውሸት] ወደ አገረ ገዢው ጆሮ ከደረሰ ሁኔታውን እናስረዳዋለን” ብለው ቃል ገቡላቸው። (ማቴዎስ 28:14) ወታደሮቹ ጉቦውን ተቀብለው ካህናቱ እንዳሏቸው አደረጉ። በዚህም ምክንያት የኢየሱስ አስከሬን እንደተሰረቀ የሚገልጸው የሐሰት ወሬ በአይሁዳውያን መካከል በስፋት ተሰራጨ።

      በዚህ ወቅት መግደላዊቷ ማርያም መቃብሩ አጠገብ ሆና እያለቀሰች ነው። ወደ መቃብሩ ውስጥ ለማየት ጎንበስ ስትል ነጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት አየች! የኢየሱስ አስከሬን አርፎበት በነበረው ቦታ አንዱ በራስጌው ሌላው በግርጌው ተቀምጠዋል። እነሱም “አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ?” ብለው ጠየቋት። ማርያምም “ጌታዬን ወስደውታል፤ የት እንዳደረጉትም አላውቅም” በማለት መለሰች። ከዚያም ዞር ስትል አንድ ሰው አየች። እሱም መላእክቱ ያቀረቡላትን ጥያቄ ከጠየቃት በኋላ አክሎ “የምትፈልጊው ማንን ነው?” አላት። እሷም አትክልተኛው ስለመሰላት “ጌታዬ፣ አንተ ከዚህ ወስደኸው ከሆነ የት እንዳደረግከው ንገረኝ፤ እኔም እወስደዋለሁ” አለችው።—ዮሐንስ 20:13-15

      ማርያም እያነጋገረች ያለችው ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ነው፤ በዚያ ወቅት ግን ይህን አልተገነዘበችም። ይሁንና ኢየሱስ “ማርያም!” ሲላት አወቀችው፤ ማንነቱን ያወቀችው ሌላ ጊዜ በሚያናግራት መንገድ ስለጠራት ነው። በዚህ ጊዜ በደስታ “ራቦኒ!” አለችው (ትርጉሙም “መምህር!” ማለት ነው)። ማርያም ወደ ሰማይ ሊያርግ እንደሆነ ስለተሰማት ያዘችው። በመሆኑም ኢየሱስ እንዲህ አላት፦ “ጥብቅ አድርገሽ አትያዥኝ፤ ገና ወደ አባቴ አላረግኩምና። ይልቁንስ ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ ‘ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ላርግ ነው’ ብለሽ ንገሪያቸው።”—ዮሐንስ 20:16, 17

      በዚህ ጊዜ ማርያም፣ ሐዋርያት ከሌሎች ደቀ መዛሙርት ጋር ወደተሰበሰቡበት ቦታ እየሮጠች ሄደች። ከዚያም “ጌታን አየሁት!” አለቻቸው፤ እሷ የተናገረችው ነገር ቀደም ሲል ከሌሎቹ ሴቶች የሰሙትን የሚያጠናክር ነው። (ዮሐንስ 20:18) ይሁን እንጂ ደቀ መዛሙርቱ፣ ሴቶቹ ‘እንዲሁ የሚቀባጥሩ መሰላቸው።’—ሉቃስ 24:11

      • መግደላዊቷ ማርያም መቃብሩን ባዶ ሆኖ ካገኘችው በኋላ ምን አደረገች? ሌሎቹ ሴቶችስ ምን አጋጠማቸው?

      • ጴጥሮስና ዮሐንስ መቃብሩ ባዶ ሆኖ ሲያገኙት ምን ተሰማቸው?

      • ሌሎቹ ሴቶች ወደ ደቀ መዛሙርቱ እየሄዱ ሳለ ማንን አገኙ? መግደላዊቷ ማርያም ወደ መቃብሩ ቦታ ከተመለሰች በኋላ ምን አጋጠማት?

      • ደቀ መዛሙርቱ የሴቶቹን ወሬ ሲሰሙ ምን አሰቡ?

  • ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለብዙዎች ተገለጠ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
    • ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለቶማስ ሲገለጥ

      ምዕራፍ 135

      ከሞት የተነሳው ኢየሱስ ለብዙዎች ተገለጠ

      ሉቃስ 24:13-49 ዮሐንስ 20:19-29

      • ኢየሱስ ወደ ኤማሁስ በሚወስደው መንገድ ላይ ተገለጠ

      • ቅዱሳን መጻሕፍትን ለደቀ መዛሙርቱ በተደጋጋሚ ጊዜ ገለጠላቸው

      • የቶማስ ጥርጣሬ ተወገደ

      ዕለቱ እሁድ፣ ኒሳን 16 ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ በሐዘን ተውጠዋል። መቃብሩ ባዶ መሆኑ ምን ትርጉም እንዳለው አልገባቸውም። (ማቴዎስ 28:9, 10፤ ሉቃስ 24:11) በዚያው ቀን ወደ በኋላ ላይ ቀለዮጳና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር ከኢየሩሳሌም 11 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ ወደምትገኘው ወደ ኤማሁስ መጓዝ ጀመሩ።

      ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ስለተፈጸመው ነገር እየተነጋገሩ ነው። በዚህ መሃል አንድ የማያውቁት ሰው አብሯቸው መሄድ ጀመረ። እሱም “እየተጓዛችሁ እንዲህ እርስ በርስ የምትወያዩበት ጉዳይ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቃቸው። ቀለዮጳም መልሶ “በኢየሩሳሌም ውስጥ ለብቻህ የምትኖር እንግዳ ሰው ነህ እንዴ? ሰሞኑን በዚያ የተፈጸመውን ነገር አታውቅም ማለት ነው?” አለው። ሰውየውም “ምን ተፈጸመ?” ብሎ ጠየቃቸው።—ሉቃስ 24:17-19

      እነሱም “ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር በተያያዘ የተፈጸመው ነገር ነዋ!” አሉት። አክለውም “እኛ ግን ይህ ሰው እስራኤልን ነፃ ያወጣል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር” በማለት ተናገሩ።—ሉቃስ 24:19-21

      ቀለዮጳና ጓደኛው በዚያ ዕለት የተፈጸሙትን ነገሮች ተረኩለት። ወደ ኢየሱስ መቃብር የሄዱ አንዳንድ ሴቶች መቃብሩን ባዶ እንዳገኙት እንዲሁም ተአምራዊ ነገር እንደተመለከቱ ይኸውም መላእክት ተገልጠው ኢየሱስ ሕያው መሆኑን እንደነገሯቸው ገለጹለት። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ ሌሎችም ወደ መቃብሩ እንደሄዱና ‘ሴቶቹ እንደተናገሩት ሆኖ እንዳገኙት’ ገለጹ።—ሉቃስ 24:24

      ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የተፈጸሙት ነገሮች ግራ እንዳጋቧቸው ግልጽ ነው። አብሯቸው እየተጓዘ ያለው ሰው፣ እንዲያዝኑ ያደረጋቸውን የተሳሳተ አመለካከታቸውን ፊት ለፊት በማረም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ማስተዋል የጎደላችሁና ነቢያት የተናገሩትን ሁሉ ከማመን ልባችሁ የዘገየ! ክርስቶስ እነዚህን መከራዎች መቀበልና ክብር ማግኘት አይገባውም?” (ሉቃስ 24:25, 26) ከዚያም ስለ ክርስቶስ የሚናገሩ በርካታ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎችን በሚገባ አብራራላቸው።

      በመጨረሻ ሦስቱ ሰዎች ወደ ኤማሁስ ተቃረቡ። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ይበልጥ እንዲያስረዳቸው ስለፈለጉ “ቀኑ እየተገባደደና ምሽቱ እየተቃረበ ስለሆነ እኛ ጋ እደር” ብለው አጥብቀው ለመኑት። ግለሰቡም እነሱ ጋ ለማደር ተስማማ። ከዚያም ምግብ መብላት ጀመሩ። ግለሰቡ ዳቦውን አንስቶ ጸሎት ካቀረበ በኋላ ቆርሶ ሲሰጣቸው ማን መሆኑን አወቁ፤ እሱ ግን ከአጠገባቸው ተሰወረ። (ሉቃስ 24:29-31) ኢየሱስ ሕያው መሆኑን አሁን እርግጠኞች ሆነዋል!

      ሁለቱ ደቀ መዛሙርት በጣም ተደስተው “በመንገድ ላይ ሲያነጋግረንና ቅዱሳን መጻሕፍትን በሚገባ ሲገልጥልን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረም?” ተባባሉ። (ሉቃስ 24:32) ወዲያውኑ ተነስተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ፤ በዚያም ሐዋርያቱንና ሌሎች ደቀ መዛሙርትን አገኙ። ቀለዮጳና ጓደኛው ገና ከመናገራቸው በፊት ሌሎቹ “ጌታ በእርግጥ ተነስቷል፤ ለስምዖንም ተገልጦለታል!” አሉ። (ሉቃስ 24:34) ከዚያም ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ ለእነሱ እንዴት እንደተገለጠላቸው ተረኩ። እነሱም ኢየሱስን አይተውታል።

      በዚህ መሃል ኢየሱስ ባሉበት ክፍል ውስጥ ድንገት ሲገለጥ ሁሉም በጣም ደነገጡ። ይህ ለማመን የሚከብድ ነው፤ ምክንያቱም አይሁዳውያንን ፈርተው በሮቹን ቆልፈዋቸዋል። ያም ቢሆን ኢየሱስ በመካከላቸው ቆመ። ከዚያም “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። እነሱ ግን ተረበሹ። በአንድ ወቅት ተሰምቷቸው እንደነበረው ሁሉ አሁንም “መንፈስ ያዩ መሰላቸው።”—ሉቃስ 24:36, 37፤ ማቴዎስ 14:25-27

      ኢየሱስ፣ ምትሃት ወይም በአእምሯቸው የፈጠሩት ነገር ሳይሆን ሥጋዊ አካል ያለው መሆኑን እርግጠኞች እንዲሆኑ ሲል እጆቹንና እግሮቹን በማሳየት እንዲህ አላቸው፦ “ለምን ትረበሻላችሁ? ለምንስ በልባችሁ ውስጥ ጥርጣሬ ያድራል? እኔ ራሴ መሆኔን እንድታውቁ እጆቼንና እግሮቼን ተመልከቱ፤ ደግሞም ዳስሳችሁኝ እዩ፤ መንፈስ በእኔ ላይ እንደምታዩት ሥጋና አጥንት የለውምና።” (ሉቃስ 24:36-39) ደቀ መዛሙርቱ በጣም የተደሰቱና የተደነቁ ቢሆንም ነገሩን ለማመን አመነቱ።

      ኢየሱስ እውን መሆኑን እንዲያስተውሉ ይበልጥ ለመርዳት ሲል “የሚበላ ነገር አላችሁ?” ብሎ ጠየቃቸው። የተጠበሰ ቁራሽ ዓሣ ሲሰጡት ተቀብሎ በላው። ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “ከእናንተ ጋር በነበርኩበት ጊዜ [ከመሞቴ በፊት] ‘በሙሴ ሕግ፣ በነቢያትና በመዝሙራት ስለ እኔ የተጻፉት ነገሮች ሁሉ መፈጸም አለባቸው’ ብዬ የነገርኳችሁ ቃሌ ይህ ነው።”—ሉቃስ 24:41-44

      ኢየሱስ፣ ለቀለዮጳና ለጓደኛው በቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፈውን በሚገባ አብራርቶላቸዋል፤ አሁን ደግሞ ለተሰበሰቡት ሁሉ ይህን አደረገ። እንዲህ አላቸው፦ “እንደሚከተለው ተብሎ ተጽፏል፤ ክርስቶስ መከራ ይቀበላል፤ በሦስተኛውም ቀን ከሞት ይነሳል፤ በስሙም የኃጢአት ይቅርታ የሚያስገኝ ንስሐ ከኢየሩሳሌም አንስቶ ለብሔራት ሁሉ ይሰበካል። እናንተም ለእነዚህ ነገሮች ምሥክር ትሆናላችሁ።”—ሉቃስ 24:46-48

      ምክንያቱ ባይታወቅም ሐዋርያው ቶማስ በዚያ አልተገኘም። በቀጣዮቹ ቀናት፣ ሌሎቹ በደስታ ፈንድቀው “ጌታን አየነው!” አሉት። ቶማስ ግን “በእጆቹ ላይ ምስማሮቹ የተቸነከሩበትን ምልክት ካላየሁ እንዲሁም ጣቴን ምስማሮቹ በነበሩበት ቦታ ካላስገባሁና እጄን በጎኑ ካላስገባሁ ፈጽሞ አላምንም” አላቸው።—ዮሐንስ 20:25

      ከስምንት ቀን በኋላ ደቀ መዛሙርቱ እንደገና የተሰባሰቡ ሲሆን በሮቹን ቆልፈዋቸዋል፤ አሁን ግን ቶማስም በቦታው አለ። ኢየሱስ ሥጋ ለብሶ በመካከላቸው ተገለጠና “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው። ከዚያም ቶማስን “ጣትህን እዚህ ክተት፤ እጆቼንም ተመልከት፤ እጅህንም አምጣና በጎኔ አስገባ። መጠራጠርህን ተውና እመን” አለው። ቶማስም መልሶ “ጌታዬ፣ አምላኬ!” አለ። (ዮሐንስ 20:26-28) ኢየሱስ ሕያውና ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር እንዲሁም የይሖዋ አምላክ ወኪል እንደሆነ ቶማስ አሁን እርግጠኛ ሆነ።

      በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ስላየኸኝ አመንክ? ሳያዩ የሚያምኑ ደስተኞች ናቸው” አለው።—ዮሐንስ 20:29

      • ሁለት ደቀ መዛሙርት ወደ ኤማሁስ እየተጓዙ ሳለ አንድ ሰው ምን ጥያቄዎች አቀረበላቸው?

      • የደቀ መዛሙርቱ ልብ እንደ እሳት እንዲቃጠል ያደረገው ምንድን ነው?

      • ቀለዮጳና ጓደኛው ወደ ኢየሩሳሌም ሲመለሱ ምን አስደሳች ወሬ ሰሙ? ከዚያስ ምን ተፈጸመ?

      • ቶማስ፣ ኢየሱስ ሕያው መሆኑን መጨረሻ ላይ ያመነው እንዴት ነው?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ