-
በመጨረሻው ፋሲካ ላይ ትሕትናን ማስተማርኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 116
በመጨረሻው ፋሲካ ላይ ትሕትናን ማስተማር
ማቴዎስ 26:20 ማርቆስ 14:17 ሉቃስ 22:14-18 ዮሐንስ 13:1-17
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የመጨረሻውን ፋሲካ በላ
የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ትምህርት ሰጠ
ጴጥሮስና ዮሐንስ፣ ኢየሱስ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት ለፋሲካ ዝግጅት ለማድረግ ቀደም ብለው ኢየሩሳሌም ገብተዋል። ትንሽ ቆየት ብሎ ኢየሱስና ሌሎቹ አሥር ሐዋርያት ወደዚያ ሄዱ። ጊዜው ከቀትር በኋላ ሲሆን ኢየሱስና አብረውት ያሉት ሰዎች ከደብረ ዘይት ተራራ ሲወርዱ ፀሐይዋ በምዕራብ አቅጣጫ እየጠለቀች ነው። ኢየሱስ ሞቶ ከመነሳቱ በፊት ከዚህ ተራራ ላይ ሆኖ በቀን አካባቢውን የሚመለከተው ለመጨረሻ ጊዜ ነው።
ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስና አብረውት ያሉት ሐዋርያት ወደ ከተማዋ ደረሱና ፋሲካን ወደሚበሉበት ቤት አመሩ። ከዚያም ደረጃዎቹን ወጥተው ወደ ሰፊው ሰገነት ገቡ። ብቻቸውን ሆነው ለሚያከብሩት የፋሲካ በዓል የሚያስፈልጉት ዝግጅቶች ሁሉ ተደርገዋል። ኢየሱስ “መከራ ከመቀበሌ በፊት ይህን ፋሲካ አብሬያችሁ ለመብላት በጣም ስመኝ ነበር” ስላለ ይህን በዓል በጉጉት ሲጠባበቀው ቆይቷል።—ሉቃስ 22:15
በፋሲካ በዓል ላይ የወይን ጠጅ የያዙ ጥቂት ጽዋዎችን የመቀባበል ልማድ ከበርካታ ዓመታት በፊት ተጀምሮ ነበር። በበዓሉ ላይ ኢየሱስ አንደኛውን ጽዋ ተቀብሎ አምላክን ካመሰገነ በኋላ እንዲህ አለ፦ “እንኩ፣ ይህን ጽዋ እየተቀባበላችሁ ጠጡ፤ እላችኋለሁና፣ ከአሁን ጀምሮ የአምላክ መንግሥት እስኪመጣ ድረስ ከዚህ ወይን ዳግመኛ አልጠጣም።” (ሉቃስ 22:17, 18) ኢየሱስ ይህን ማለቱ የሚሞትበት ጊዜ መቅረቡን በግልጽ ያሳያል።
ፋሲካን እየበሉ ሳለ አንድ ያልተለመደ ነገር ተከናወነ። ኢየሱስ ተነስቶ መደረቢያውን ካስቀመጠ በኋላ ፎጣ ወስዶ ወገቡ ላይ አሸረጠ። ከዚያም በአቅራቢያው በሚገኝ የመታጠቢያ ዕቃ ውስጥ ውኃ ጨመረ። በአብዛኛው የእንግዶች እግር እንዲታጠብ ዝግጅት የሚያደርገው ጋባዡ ነው፤ ምናልባትም አንድ አገልጋዩ እግራቸውን እንዲያጥብ ያደርግ ይሆናል። (ሉቃስ 7:44) ይሁንና በቦታው ጋባዥ ስለሌለ ኢየሱስ ይህን አገልግሎት ራሱ አከናወነ። ከሐዋርያቱ መካከል አንዳቸው እንዲህ ማድረግ ይችሉ ነበር፤ ሆኖም ማናቸውም ይህን አላደረጉም። ይህ የሆነው በመካከላቸው ያለው ፉክክር ስላልጠፋ ይሆን? ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ኢየሱስ እግራቸውን ማጠብ ሲጀምር አፈሩ።
ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ወደ እሱ ሲመጣ “በፍጹም እግሬን አታጥብም” ሲል ተቃወመ። ኢየሱስም “ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ምንም ድርሻ አይኖርህም” ሲል መለሰለት። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በስሜታዊነት “ጌታ ሆይ፣ እግሬን ብቻ ሳይሆን እጄንና ራሴንም እጠበኝ” አለው። ኢየሱስ በሰጠው መልስ ምንኛ ተገርሞ ይሆን! ኢየሱስ እንዲህ አለው፦ “ገላውን የታጠበ ሁለመናው ንጹሕ በመሆኑ ከእግሩ በስተቀር መታጠብ አያስፈልገውም። እናንተ ንጹሐን ናችሁ፤ ሁላችሁም ግን አይደላችሁም።”—ዮሐንስ 13:8-10
ኢየሱስ የአስቆሮቱ ይሁዳን ጨምሮ የ12ቱንም እግር አጠበ። መደረቢያውን ለብሶ ዳግመኛ በማዕድ ከተቀመጠ በኋላ እንዲህ ብሎ ጠየቃቸው፦ “ምን እንዳደረግኩላችሁ አስተዋላችሁ? እናንተ ‘መምህር’ እና ‘ጌታ’ ብላችሁ ትጠሩኛላችሁ፤ እንደዚያ ስለሆንኩም እንዲህ ብላችሁ መጥራታችሁ ትክክል ነው። ስለዚህ እኔ ጌታና መምህር ሆኜ ሳለሁ እግራችሁን ካጠብኩ እናንተም እርስ በርሳችሁ እግራችሁን ልትተጣጠቡ ይገባችኋል። እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ። እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ባሪያ ከጌታው አይበልጥም፤ የተላከም ከላከው አይበልጥም። እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ።”—ዮሐንስ 13:12-17
ትሕትና በተግባር የታየበት እንዴት ያለ ግሩም ትምህርት ነው! የኢየሱስ ተከታዮች ከፍ ተደርገው ሊታዩና ሊገለገሉ እንደሚገባ በማሰብ ቀዳሚውን ቦታ ለማግኘት መጣር የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ የተወላቸውን ምሳሌ መከተል ይገባቸዋል፤ ይህን የሚያደርጉት እግር የማጠብን ሃይማኖታዊ ሥርዓት በመፈጸም ሳይሆን በትሕትና እንዲሁም ያለአድልዎ ለማገልገል ፈቃደኛ በመሆን ነው።
-
-
የጌታ ራትኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 117
የጌታ ራት
ማቴዎስ 26:21-29 ማርቆስ 14:18-25 ሉቃስ 22:19-23 ዮሐንስ 13:18-30
ይሁዳ ከሃዲ መሆኑ ተገለጸ
ኢየሱስ የመታሰቢያ በዓል አቋቋመ
በዚህ ምሽት ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር በማጠብ ስለ ትሕትና አስተምሯቸዋል። ፋሲካን ከበሉ በኋላ ሳይሆን አይቀርም ኢየሱስ፣ ዳዊት የተናገረውን ትንቢት በመጥቀስ እንዲህ አለ፦ “ከእኔ ጋር ሰላም የነበረው፣ እምነት የጣልኩበትና ከማዕዴ ይበላ የነበረ ሰው ተረከዙን በእኔ ላይ አነሳ።” ኢየሱስ አክሎም “ከእናንተ አንዱ አሳልፎ ይሰጠኛል” ሲል በግልጽ ተናገረ።—መዝሙር 41:9፤ ዮሐንስ 13:18, 21
ሐዋርያቱ እርስ በርስ ተያዩ፤ ከዚያም እያንዳንዳቸው “ጌታ ሆይ፣ እኔ እሆን?” ይሉት ጀመር። የአስቆሮቱ ይሁዳ እንኳ ይህን ጥያቄ አቀረበ። ጴጥሮስ፣ ይህ ግለሰብ ማን እንደሆነ እንዲያጣራ በማዕዱ ላይ ከኢየሱስ አጠገብ የተቀመጠውን ዮሐንስን ጠየቀው። እሱም ወደ ኢየሱስ ደረት ጠጋ ብሎ “ጌታ ሆይ፣ ማን ነው?” አለው።—ማቴዎስ 26:22፤ ዮሐንስ 13:25
ኢየሱስም “ይህን የማጠቅሰውን ቁራሽ ዳቦ የምሰጠው ሰው ነው” ሲል መለሰ። ከዚያም ዳቦውን የቀረበው ሳህን ውስጥ አጥቅሶ ለይሁዳ ከሰጠው በኋላ እንዲህ አለ፦ “የሰው ልጅ ስለ እሱ በተጻፈው መሠረት ይሄዳል፤ የሰውን ልጅ አሳልፎ ለሚሰጠው ለዚያ ሰው ግን ወዮለት! ያ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር።” (ዮሐንስ 13:26፤ ማቴዎስ 26:24) በዚህ ጊዜ ይሁዳ ሰይጣን ገባበት። አስተሳሰቡ የተበላሸው ይህ ሰው የዲያብሎስን ዓላማ ለመፈጸም ፈቃደኛ በመሆኑ ‘የጥፋት ልጅ’ ሆነ።—ዮሐንስ 6:64, 70፤ 12:4፤ 17:12
ኢየሱስ ይሁዳን “እያደረግከው ያለኸውን ነገር ቶሎ አድርገው” አለው። ሌሎቹ ሐዋርያት፣ የገንዘብ ሣጥኑን የሚይዘው ይሁዳ “ለበዓሉ የሚያስፈልጉትን ነገሮች እንዲገዛ ወይም ለድሆች የሆነ ነገር እንዲሰጥ ኢየሱስ ያዘዘው” መሰላቸው። (ዮሐንስ 13:27-30) ይሁዳ ግን ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ሄደ።
ፋሲካ በተከበረበት በዚሁ ምሽት ላይ ኢየሱስ ሌላ አዲስ በዓል አቋቋመ። አንድ ቂጣ ወስዶ የምስጋና ጸሎት ካቀረበ በኋላ ቆራርሶ ሐዋርያቱ እንዲበሉት ሰጣቸው። ከዚያም “ይህ ስለ እናንተ የሚሰጠውን ሥጋዬን ያመለክታል። ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” አላቸው። (ሉቃስ 22:19) ሐዋርያቱም ቂጣውን እየተቀባበሉ በሉ።
ቀጥሎም ኢየሱስ የወይን ጠጅ የያዘውን ጽዋ አንስቶ የምስጋና ጸሎት ካቀረበ በኋላ ሰጣቸው። ሁሉም ከእሱ ጠጡ። ኢየሱስ የወይን ጠጁን አስመልክቶ እንዲህ አለ፦ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው ደሜ አማካኝነት የሚመሠረተውን አዲሱን ቃል ኪዳን ያመለክታል።”—ሉቃስ 22:20
በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ በየዓመቱ ኒሳን 14 ላይ የሞቱን መታሰቢያ እንዲያከብሩ መመሪያ ሰጠ። ይህ በዓል፣ እምነት ያላቸው የሰው ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ኩነኔ ነፃ እንዲወጡ ኢየሱስና አባቱ ያደረጉትን ዝግጅት ለማስታወስ ይረዳል። እርግጥ ነው፣ ፋሲካ ለአይሁዳውያን ነፃ መውጣትን ያመለክት ነበር፤ የመታሰቢያው በዓል ግን እምነት ያላቸው የሰው ልጆች በሙሉ ከዚያ የላቀ እውነተኛ ነፃነት እንደሚያገኙ ተስፋ ይሰጣል።
ኢየሱስ፣ ደሙ “ስለ ብዙዎች ለኃጢአት ይቅርታ” እንደሚፈስ ተናገረ። እንዲህ ያለ ይቅርታ ከሚያገኙት በርካታ ሰዎች መካከል ታማኝ ሐዋርያቱና ሌሎች ታማኝ ደቀ መዛሙርት ይገኙበታል። በአባቱ መንግሥት ከእሱ ጋር የሚሆኑት እነዚህ ሰዎች ናቸው።—ማቴዎስ 26:28, 29
-
-
ታላቅ መሆንን በተመለከተ ክርክር ተነሳኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 118
ታላቅ መሆንን በተመለከተ ክርክር ተነሳ
ማቴዎስ 26:31-35 ማርቆስ 14:27-31 ሉቃስ 22:24-38 ዮሐንስ 13:31-38
ኢየሱስ ሥልጣንን አስመልክቶ ምክር ሰጠ
ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደሚክደው አስቀድሞ ተነገረ
የኢየሱስ ተከታዮች መለያ ፍቅር ነው
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ላይ እግራቸውን በማጠብ፣ ትሑት ሆኖ ማገልገልን በተመለከተ ግሩም ትምህርት ሰጥቷቸዋል። እንዲህ ማድረጉ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ድክመት ስላለባቸው ነው። እነዚህ ሰዎች ለአምላክ ያደሩ ቢሆኑም ‘ከመካከላችን ማን ታላቅ ነው?’ የሚለው ጉዳይ አሁንም ያሳስባቸዋል። (ማርቆስ 9:33, 34፤ 10:35-37) ይህ ድክመታቸው በዚህ ምሽት እንደገና ታየ።
“‘ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?’ በሚል በመካከላቸው የጦፈ ክርክር ተነሳ።” (ሉቃስ 22:24) ኢየሱስ በማይረባ ነገር እንደገና እየተጨቃጨቁ መሆኑን ሲያይ ምንኛ አዝኖ ይሆን! ታዲያ ምን አደረገ?
ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱ እንዲህ ያለ ዝንባሌና ባሕርይ በማሳየታቸው ከመቆጣት ይልቅ በትዕግሥት የሚከተለውን አሳማኝ ሐሳብ አቀረበላቸው፦ “የአሕዛብ ነገሥታት በእነሱ ላይ ሥልጣናቸውን ያሳያሉ፤ እንዲሁም በሕዝባቸው ላይ ሥልጣን ያላቸው ሰዎች በጎ አድራጊዎች ተብለው ይጠራሉ። እናንተ ግን እንዲህ አትሁኑ። . . . ለመሆኑ በማዕድ ከተቀመጠና ቆሞ ከሚያገለግል ማን ይበልጣል?” ከዚያም “እኔ ግን በመካከላችሁ ያለሁት እንደ አገልጋይ ሆኜ ነው” በማለት እሱ በተደጋጋሚ የተወላቸውን ምሳሌ አስታወሳቸው።—ሉቃስ 22:25-27
ሐዋርያቱ ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ኢየሱስ በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ከጎኑ ሳይለዩ ቆይተዋል። በመሆኑም “አባቴ ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን እንዳደረገ ሁሉ እኔም ከእናንተ ጋር ለመንግሥት ቃል ኪዳን አደርጋለሁ” አለ። (ሉቃስ 22:29) እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች ናቸው። ከእነሱ ጋር የገባው ቃል ኪዳን በመንግሥቱ ከእሱ ጋር እንዲሆኑና አብረውት እንዲነግሡ መንገድ እንደሚከፍት አረጋገጠላቸው።
ሐዋርያቱ እንዲህ ዓይነት ግሩም ተስፋ የተዘረጋላቸው ቢሆንም አሁንም ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ናቸው። ኢየሱስ “ሰይጣን ሁላችሁንም እንደ ስንዴ ያበጥራችሁ ዘንድ ጥያቄ አቅርቧል” አላቸው፤ ስንዴ ሲበጠር ይበተናል። (ሉቃስ 22:31) ኢየሱስ “‘እረኛውን እመታለሁ፤ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ’ ተብሎ ስለተጻፈ በዚህች ሌሊት ሁላችሁም በእኔ ላይ በሚደርሰው ነገር የተነሳ ትሰናከላላችሁ” በማለትም አስጠነቀቃቸው።—ማቴዎስ 26:31፤ ዘካርያስ 13:7
ይሁንና ጴጥሮስ “ሌሎቹ ሁሉ በአንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልሰናከልም!” ሲል በልበ ሙሉነት ተናገረ። (ማቴዎስ 26:33) ኢየሱስም በዚህች ሌሊት ዶሮ ሁለት ጊዜ ሳይጮኽ እንደሚክደው ለጴጥሮስ ነገረው። ሆኖም ኢየሱስ አክሎ “እኔ . . . እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ ምልጃ አቀረብኩ፤ አንተም በተመለስክ ጊዜ ወንድሞችህን አበርታ” አለው። (ሉቃስ 22:32) ጴጥሮስ ግን “አብሬህ መሞት ቢያስፈልገኝ እንኳ በምንም ዓይነት አልክድህም” በማለት አስረግጦ ተናገረ። (ማቴዎስ 26:35) ሌሎቹ ሐዋርያትም እንደዚሁ አሉ።
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ጥቂት ጊዜ ከእናንተ ጋር እቆያለሁ። እናንተም ትፈልጉኛላችሁ፤ ለአይሁዳውያን ‘ወደምሄድበት ልትመጡ አትችሉም’ እንዳልኳቸው ሁሉ አሁን ደግሞ ለእናንተ ይህንኑ እላችኋለሁ” አላቸው። ከዚያም “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደ ወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” አለ።—ዮሐንስ 13:33-35
ኢየሱስ ከእነሱ ጋር የሚቆየው ጥቂት ጊዜ እንደሆነ ሲናገር ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፣ ወዴት ልትሄድ ነው?” ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም “እኔ ወደምሄድበት አሁን ልትከተለኝ አትችልም፤ በኋላ ግን ትከተለኛለህ” ሲል መለሰ። ጴጥሮስ ግራ ስለተጋባ “ጌታ ሆይ፣ አሁን ልከተልህ የማልችለው ለምንድን ነው? ሕይወቴን ስለ አንተ አሳልፌ ለመስጠት ፈቃደኛ ነኝ” አለው።—ዮሐንስ 13:36, 37
ቀጥሎ ደግሞ ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱን የገንዘብ ኮሮጆም ሆነ የምግብ ከረጢት ሳይዙ በገሊላ እየዞሩ እንዲሰብኩ ልኳቸው የነበረበትን ጊዜ ጠቀሰ። (ማቴዎስ 10:5, 9, 10) ከዚያም “የጎደለባችሁ ነገር ነበር?” በማለት ጠየቃቸው። እነሱም “ምንም አልጎደለብንም” አሉ። ይሁንና ወደፊትስ ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል? ኢየሱስ እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጣቸው፦ “የገንዘብ ኮሮጆ ያለው ኮሮጆውን ይያዝ፤ የምግብ ከረጢት ያለውም እንዲሁ፤ ሰይፍ የሌለው ደግሞ መደረቢያውን ሸጦ ሰይፍ ይግዛ። ይህን የምላችሁ ‘ከዓመፀኞች ጋር ተቆጠረ’ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ላይ መፈጸም ስላለበት ነው። ስለ እኔ የተነገረው ነገር ፍጻሜውን እያገኘ ነውና።”—ሉቃስ 22:35-37
ኢየሱስ ይህን ሲል ከክፉ አድራጊዎች ወይም ከዓመፀኞች ጋር በእንጨት ላይ የሚሰቀልበትን ጊዜ መጥቀሱ ነው። ከዚያ በኋላ ተከታዮቹ ከባድ ስደት ይደርስባቸዋል። ሐዋርያቱ ለሚመጣው ነገር ዝግጁ እንደሆኑ ስለተሰማቸው “ጌታ ሆይ፣ ይኸው ሁለት ሰይፎች አሉ” አሉት። እሱም “በቂ ነው” አላቸው። (ሉቃስ 22:38) ሁለት ሰይፍ መያዛቸው ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ ሌላ በጣም አስፈላጊ የሆነ ትምህርት እንዲሰጣቸው አጋጣሚ ይፈጥራል።
-
-
ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወትኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 119
ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
ኢየሱስ ቦታ ለማዘጋጀት ይሄዳል
ረዳት እንደሚያገኙ ለተከታዮቹ ቃል ገባላቸው
አብ ከኢየሱስ ይበልጣል
ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ካቋቋመ በኋላ አሁንም ከሐዋርያቱ ጋር በሰገነት ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ ነው። እንዲህ ሲል አበረታታቸው፦ “ልባችሁ አይረበሽ። በአምላክ እመኑ፤ በእኔም ደግሞ እመኑ።”—ዮሐንስ 13:36፤ 14:1
ኢየሱስ፣ ታማኝ ሐዋርያቱ እሱ በመሄዱ መሸበር የሌለባቸው ለምን እንደሆነ ሲገልጽ እንዲህ አላቸው፦ “በአባቴ ቤት ብዙ መኖሪያ ቦታ አለ። . . . ሄጄ ቦታ ባዘጋጀሁላችሁ ጊዜ እኔ ባለሁበት እናንተም እንድትሆኑ እንደገና መጥቼ እኔ ወዳለሁበት እወስዳችኋለሁ።” ሐዋርያቱ ግን ወደ ሰማይ ስለ መሄድ እያወራ እንደሆነ አልገባቸውም። በመሆኑም ቶማስ “ጌታ ሆይ፣ ወዴት እንደምትሄድ አናውቅም። ታዲያ መንገዱን እንዴት ማወቅ እንችላለን?” በማለት ጠየቀው።—ዮሐንስ 14:2-5
ኢየሱስም “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ” አለው። አንድ ሰው በሰማይ ወደሚገኘው የኢየሱስ አባት ቤት መግባት የሚችለው ክርስቶስንና ትምህርቶቹን የሚቀበል እንዲሁም የእሱን አርዓያ የሚከተል ከሆነ ብቻ ነው። ኢየሱስ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” አለ።—ዮሐንስ 14:6
በጥሞና እያዳመጠ ያለው ፊልጶስ “ጌታ ሆይ፣ አብን አሳየንና ይበቃናል” በማለት ጠየቀው። ፊልጶስ ይህን ያለው በጥንት ዘመን ሙሴ፣ ኤልያስና ኢሳይያስ የተመለከቱት ዓይነት ራእይ በማሳየት አምላክን እንዲገልጥላቸው ፈልጎ ይመስላል። ይሁንና ሐዋርያት እንዲህ ዓይነቶቹን ራእዮች ከመመልከት የበለጠ አጋጣሚ አግኝተዋል። ኢየሱስ ይህን ሲያጎላ እንዲህ ብሎ መለሰ፦ “ፊልጶስ፣ ከእናንተ ጋር ይህን ያህል ረጅም ጊዜ ኖሬም እንኳ አላወቅከኝም? እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል።” ኢየሱስ የአባቱን ባሕርይ ፍጹም በሆነ መንገድ ያንጸባረቀ በመሆኑ ከእሱ ጋር መኖርና እሱን መመልከት አብን እንደ መመልከት ይቆጠራል። እርግጥ ነው፣ አብ ከወልድ ይበልጣል፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “የምነግራችሁን ነገር የምናገረው ከራሴ አመንጭቼ አይደለም” ብሏል። (ዮሐንስ 14:8-10) ኢየሱስ ለሚያስተምረው ትምህርት ሊከበር የሚገባው አባቱ መሆኑን እየገለጸ እንደሆነ ሐዋርያቱ ማስተዋል ይችላሉ።
የኢየሱስ ሐዋርያት፣ ጌታ አስደናቂ ሥራዎችን ሲያከናውን ተመልክተዋል፤ እንዲሁም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሲያውጅ ሰምተዋል። አሁን ደግሞ “በእኔ የሚያምን ሁሉ እኔ የምሠራቸውን ሥራዎች ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ እሱ ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል” አላቸው። (ዮሐንስ 14:12) ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ እሱ ካከናወናቸው የላቁ ተአምራት እንደሚፈጽሙ መናገሩ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አገልግሎታቸውን ከእሱ አንጻር ለረጅም ጊዜና በጣም ሰፊ በሆነ ክልል ውስጥ እንደሚያከናውኑ እንዲሁም ለብዙ ሰዎች እንደሚሰብኩ መግለጹ ነው።
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ከተለየ በኋላ አይተዋቸውም፤ “ማንኛውንም ነገር በስሜ ከለመናችሁ እኔ አደርገዋለሁ” በማለት ቃል ገባላቸው። አክሎም “እኔም አብን እጠይቃለሁ፤ እሱም ለዘላለም ከእናንተ ጋር የሚሆን ሌላ ረዳት ይሰጣችኋል፤ እሱም የእውነት መንፈስ ነው” አለ። (ዮሐንስ 14:14, 16, 17) ኢየሱስ፣ ሌላ ረዳት የተባለውን መንፈስ ቅዱስን እንደሚቀበሉ ዋስትና ሰጣቸው። ይህን ረዳት የሚያገኙት በጴንጤቆስጤ ዕለት ነው።
ኢየሱስ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ ዓለም ከቶ አያየኝም፤ እናንተ ግን ታዩኛላችሁ፤ ምክንያቱም እኔ እኖራለሁ፤ እናንተም ትኖራላችሁ” በማለት ተናገረ። (ዮሐንስ 14:19) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ሰብዓዊ አካል ለብሶ ለእነሱ የሚገለጥላቸው ከመሆኑም በላይ ከጊዜ በኋላ ከሞት በማስነሳት መንፈሳዊ ፍጡራን ሆነው በሰማይ ከእሱ ጋር እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል።
ኢየሱስ በመቀጠል የሚከተለውን መሠረታዊ ሐቅ ተናገረ፦ “እኔን የሚወደኝ ትእዛዛቴን የሚቀበልና የሚጠብቅ ነው። እኔን የሚወደኝን ሁሉ ደግሞ አባቴ ይወደዋል፤ እኔም እወደዋለሁ፤ ራሴንም እገልጥለታለሁ።” ታዴዎስ እየተባለም የሚጠራው ሐዋርያው ይሁዳ በዚህ ጊዜ “ጌታ ሆይ፣ ለዓለም ሳይሆን ለእኛ ራስህን ለመግለጥ ያሰብከው ለምንድን ነው?” በማለት ጠየቀው። ኢየሱስም “ማንም ሰው እኔን የሚወደኝ ከሆነ ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል፣ . . . እኔን የማይወደኝ ሁሉ ቃሌን አይጠብቅም” በማለት መለሰለት። (ዮሐንስ 14:21-24) ከተከታዮቹ በተቃራኒ ዓለም፣ ኢየሱስ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት መሆኑን አይቀበልም።
ኢየሱስ ሊሄድ ነው፤ ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ እሱ ያስተማራቸውን ነገር ሁሉ ማስታወስ የሚችሉት እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “አብ በስሜ የሚልከው ረዳት ይኸውም መንፈስ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ያስተምራችኋል እንዲሁም የነገርኳችሁን ነገር ሁሉ እንድታስታውሱ ያደርጋችኋል።” ሐዋርያቱ፣ መንፈስ ቅዱስ ምን ያህል ኃይል እንዳለው ተመልክተዋል፤ በመሆኑም ይህ ማረጋገጫ ያጽናናቸዋል። ኢየሱስ አክሎም “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ። . . . ልባችሁ አይረበሽ፤ በፍርሃትም አይዋጥ” አላቸው። (ዮሐንስ 14:26, 27) ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሱስ አባት መመሪያና ጥበቃ ስለሚያገኙ የሚረበሹበት ምክንያት የለም።
አምላክ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው የሚያሳይ ማስረጃ በቅርቡ ይመለከታሉ። ኢየሱስ “የዚህ ዓለም ገዢ እየመጣ” እንደሆነ ከተናገረ በኋላ “እሱም በእኔ ላይ ምንም ኃይል የለውም” አለ። (ዮሐንስ 14:30) ዲያብሎስ፣ ይሁዳ ውስጥ መግባትና እሱን መቆጣጠር ችሏል። ኢየሱስ ግን የኃጢአት ዝንባሌ ስለሌለው ሰይጣን በዚህ ተጠቅሞ በአምላክ ላይ ሊያሳምፀው አይችልም። ዲያብሎስ፣ ኢየሱስ ሞቶ እንዲቀር ማድረግም አይችልም። ለምን? ኢየሱስ “አብ ባዘዘኝ መሠረት እየሠራሁ ነው” አለ። በመሆኑም አባቱ ከሞት እንደሚያስነሳው እርግጠኛ ነው።—ዮሐንስ 14:31
-
-
ፍሬ የሚያፈራ ቅርንጫፍና የኢየሱስ ወዳጅ መሆንኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 120
ፍሬ የሚያፈራ ቅርንጫፍና የኢየሱስ ወዳጅ መሆን
እውነተኛው የወይን ተክልና ቅርንጫፎቹ
በኢየሱስ ፍቅር መኖር የሚቻልበት መንገድ
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ልብ ለልብ ውይይት በማድረግ አበረታቷቸዋል። አሁን እኩለ ሌሊት ሳያልፍ አይቀርም። ኢየሱስ ለሥራ የሚያነሳሳ ምሳሌ ተናገረ።
ምሳሌውን ሲጀምር “እኔ እውነተኛው የወይን ተክል ነኝ፤ አትክልተኛው ደግሞ አባቴ ነው” አለ። (ዮሐንስ 15:1) ምሳሌው ከበርካታ ዘመናት በፊት ስለ እስራኤል ብሔር ከተነገረው ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል ነው፤ የእስራኤል ብሔር፣ የይሖዋ የወይን ተክል ተብሎ ተጠርቷል። (ኤርምያስ 2:21፤ ሆሴዕ 10:1, 2) ይሁን እንጂ ይሖዋ ይህን ብሔር ሊተወው ነው። (ማቴዎስ 23:37, 38) በመሆኑም ኢየሱስ የተናገረው ነገር አዲስ ሐሳብ ነው። በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው የወይን ተክል ኢየሱስ ነው፤ ይሖዋ በ29 ዓ.ም. ኢየሱስን በመንፈስ ቅዱስ ከቀባው ጊዜ አንስቶ ሲንከባከበው ቆይቷል። ሆኖም ኢየሱስ የወይኑ ተክል የሚያመለክተው እሱን ብቻ አለመሆኑን ሲገልጽ እንዲህ አለ፦
“በእኔ ላይ ያለውን፣ ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ [አባቴ] ቆርጦ ይጥለዋል፤ ፍሬ የሚያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ደግሞ ይበልጥ እንዲያፈራ ያጠራዋል። . . . ቅርንጫፉ ከወይኑ ተክል ጋር ተጣብቆ ካልኖረ በራሱ ፍሬ ማፍራት አይችልም፤ እናንተም ከእኔ ጋር ያላችሁን አንድነት ጠብቃችሁ ካልኖራችሁ ፍሬ ልታፈሩ አትችሉም። እኔ የወይኑ ተክል ነኝ፤ እናንተ ደግሞ ቅርንጫፎቹ ናችሁ።”—ዮሐንስ 15:2-5
ኢየሱስ ከሄደ በኋላ ረዳት የሚሆነውን መንፈስ ቅዱስ እንደሚልክላቸው ለታማኝ ደቀ መዛሙርቱ ቃል ገብቷል። ከ51 ቀናት በኋላ ሐዋርያቱና ሌሎች ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስ በወረደባቸው ጊዜ የወይኑ ተክል ቅርንጫፎች ሆነዋል። “ቅርንጫፎቹ” በሙሉ ከኢየሱስ ጋር ያላቸውን አንድነት ጠብቀው መኖር አለባቸው። ይህን የሚያደርጉበት ዓላማ ምንድን ነው?
ኢየሱስ “ማንኛውም ሰው ከእኔ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ከኖረና እኔም ከእሱ ጋር አንድ ሆኜ ከኖርኩ ብዙ ፍሬ ያፈራል፤ እናንተ ከእኔ ተለይታችሁ ምንም ነገር ልታደርጉ አትችሉምና” በማለት አብራራ። እነዚህ “ቅርንጫፎች” ማለትም የእሱ ታማኝ ተከታዮች የእሱን ባሕርያት በመምሰል፣ ለሌሎች ስለ አምላክ መንግሥት በቅንዓት በማወጅና ተጨማሪ ሰዎች ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በመርዳት ብዙ ፍሬ ያፈራሉ። አንድ ሰው ከኢየሱስ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ባይኖርና ፍሬ ባያፈራስ? ኢየሱስ ‘አንድ ሰው ከእኔ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ካልኖረ ይጣላል’ አለ። በሌላ በኩል ደግሞ “ከእኔ ጋር ያላችሁን አንድነት ከጠበቃችሁና ቃሌ በልባችሁ ከኖረ የምትፈልጉትን ማንኛውንም ነገር ብትጠይቁ ይፈጸምላችኋል” በማለት ተናገረ።—ዮሐንስ 15:5-7
አሁን ደግሞ ኢየሱስ ቀደም ሲል ሁለት ጊዜ የጠቀሰውን ርዕሰ ጉዳይ ይኸውም ትእዛዛቱን መጠበቅን አስመልክቶ ተናገረ። (ዮሐንስ 14:15, 21) ደቀ መዛሙርቱ ይህን ማድረጋቸውን ማሳየት የሚችሉበትን ግሩም መንገድ ሲገልጽ “እኔ የአብን ትእዛዛት ጠብቄ በፍቅሩ እንደምኖር እናንተም ትእዛዛቴን ብትጠብቁ በፍቅሬ ትኖራላችሁ” አላቸው። ይሁንና ይሖዋ አምላክንና ልጁን መውደድ ብቻውን በቂ አይደለም። ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “ትእዛዜ ይህ ነው፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም። የማዛችሁን ነገር የምትፈጽሙ ከሆነ ወዳጆቼ ናችሁ።”—ዮሐንስ 15:10-14
ኢየሱስ በእሱ ለሚያምኑ ሁሉ ሕይወቱን አሳልፎ በመስጠት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ይህን ፍቅሩን ያሳያል። የእሱ ምሳሌ፣ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቀውን ይህ ዓይነቱን ፍቅር ተከታዮቹም አንዳቸው ለሌላው እንዲያሳዩ ሊያነሳሳቸው ይገባል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” አለ፤ በእርግጥም ኢየሱስ ቀደም ሲል እንደተናገረው ይህ ፍቅር ተለይተው እንዲታወቁ ያደርጋል።—ዮሐንስ 13:35
ሐዋርያቱ፣ ኢየሱስ “ወዳጆች” ብሎ እንደጠራቸው ልብ ሊሉ ይገባል። ይህን ያለበትን ምክንያት ሲገልጽ “ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ” አለ። የኢየሱስ የቅርብ ወዳጆች መሆንና አባቱ የነገረውን ማወቅ እንዴት ያለ ውድ መብት ነው! ተከታዮቹ ይህን ዝምድና እንደያዙ ለመቀጠል ምንጊዜም ‘ፍሬ ማፍራት’ ይኖርባቸዋል። ይህን የሚያደርጉ ከሆነ ‘አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል’ በማለት ኢየሱስ ተናገረ።—ዮሐንስ 15:15, 16
በእነዚህ “ቅርንጫፎች” ማለትም በደቀ መዛሙርቱ መካከል ያለው ፍቅር ወደፊት የሚመጣውን ነገር በጽናት ለመወጣት ይረዳቸዋል። ኢየሱስ፣ ዓለም እንደሚጠላቸው ያስጠነቀቃቸው ቢሆንም እንደሚከተለው በማለት አጽናናቸው፦ “ዓለም ቢጠላችሁ፣ እናንተን ከመጥላቱ በፊት እኔን እንደጠላኝ ታውቃላችሁ። የዓለም ክፍል ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን በወደደ ነበር። አሁን ግን . . . የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ ከዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላችኋል።”—ዮሐንስ 15:18, 19
ኢየሱስ ዓለም እነሱን የሚጠላበትን ምክንያት ይበልጥ ሲያብራራ “የላከኝን ስለማያውቁት በስሜ ምክንያት እነዚህን ነገሮች ሁሉ ያደርጉባችኋል” አለ። ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት እሱን የሚጠሉት ሰዎች እንዲፈረድባቸው እንደሚያደርጉ ሲገልጽ እንዲህ በማለት ተናገረ፦ “ሌላ ማንም ያላደረገውን ነገር በመካከላቸው ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን እኔን አይተዋል እንዲሁም እኔንም ሆነ አባቴን ጠልተዋል።” ለነገሩ ጥላቻቸው ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል።—ዮሐንስ 15:21, 24, 25፤ መዝሙር 35:19፤ 69:4
ቀጥሎም ኢየሱስ ረዳት የሆነውን መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክላቸው በድጋሚ ቃል ገባ። ተከታዮቹ በሙሉ ይህን ኃይል ማግኘት ይችላሉ፤ እንዲሁም ይህ ኃይል ፍሬ እንዲያፈሩ ይኸውም ‘ምሥክር እንዲሆኑ’ ይረዳቸዋል።—ዮሐንስ 15:27
-
-
“አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 121
“አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”
ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር የሚቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው
የሐዋርያቱ ሐዘን ወደ ደስታ ይለወጣል
ኢየሱስና ሐዋርያቱ ፋሲካን ከበሉበት በሰገነት ላይ የሚገኝ ክፍል ወጥተው ለመሄድ ተዘጋጅተዋል። ኢየሱስ ብዙ ምክር ከሰጣቸው በኋላ “ይህን ሁሉ የነገርኳችሁ እንዳትሰናከሉ ብዬ ነው” በማለት አክሎ ተናገረ። እንዲህ ዓይነት ማስጠንቀቂያ መስጠት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ አላቸው፦ “ሰዎች ከምኩራብ ያባርሯችኋል። እንዲያውም እናንተን የሚገድል ሁሉ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንዳቀረበ አድርጎ የሚያስብበት ሰዓት ይመጣል።”—ዮሐንስ 16:1, 2
ሐዋርያቱ ይህን ሐሳብ ሲሰሙ ተረብሸው መሆን አለበት። ዓለም እንደሚጠላቸው ቀደም ሲል የነገራቸው ቢሆንም ሊገደሉ እንደሚችሉ በቀጥታ ገልጾ አያውቅም። ለምን? “ከእናንተ ጋር ስለነበርኩ እነዚህን ነገሮች በመጀመሪያ አልነገርኳችሁም” አላቸው። (ዮሐንስ 16:4) አሁን ግን ከእነሱ ሊለይ ስለሆነ ይህን መረጃ በመስጠት እያስታጠቃቸው ነው። ይህን ማድረጉ በኋላ ላይ እንዳይሰናከሉ ሊረዳቸው ይችላል።
ኢየሱስ ቀጥሎ “አሁን ግን ወደ ላከኝ ልሄድ ነው፤ ሆኖም ከመካከላችሁ ‘ወዴት ነው የምትሄደው?’ ብሎ የጠየቀኝ የለም” አላቸው። እርግጥ ነው፣ ወዴት እንደሚሄድ በዚሁ ምሽት ጥያቄ አቅርበውለት ነበር። (ዮሐንስ 13:36፤ 14:5፤ 16:5) በዚህ ወቅት ግን ስለ ስደት የተናገረው ሐሳብ ስላስደነገጣቸው በሐዘን ተውጠዋል። በመሆኑም ወደፊት ስለሚያገኘው ክብር ወይም ይህ ለእውነተኛ አገልጋዮች ምን ትርጉም እንደሚኖረው አልጠየቁትም። ኢየሱስ “እነዚህን ነገሮች ስለነገርኳችሁ ልባችሁ በሐዘን ተሞልቷል” አለ።—ዮሐንስ 16:6
ከዚያም እንዲህ አላቸው፦ “እኔ የምሄደው ለእናንተው ጥቅም ነው። ምክንያቱም እኔ ካልሄድኩ ረዳቱ በምንም ዓይነት ወደ እናንተ አይመጣም፤ ከሄድኩ ግን እሱን ወደ እናንተ እልከዋለሁ።” (ዮሐንስ 16:7) ደቀ መዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን መቀበል የሚችሉት ኢየሱስ ከሞተና ወደ ሰማይ ከሄደ ብቻ ነው፤ ከዚያ በኋላ በየትኛውም የምድር ክፍል ለሚገኙ ተከታዮቹ ረዳት እንዲሆን የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ይልክላቸዋል።
መንፈስ ቅዱስ “ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ለዓለም አሳማኝ ማስረጃ ያቀርባል።” (ዮሐንስ 16:8) በእርግጥም ዓለም በአምላክ ልጅ አለማመኑ ይጋለጣል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ማረጉ፣ ጻድቅ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ የሚያቀርብ ከመሆኑም ሌላ “የዚህ ዓለም ገዢ” የሆነው ሰይጣን ሊፈረድበት የሚገባው ለምን እንደሆነ ያሳያል።—ዮሐንስ 16:11
ኢየሱስ በመቀጠል “ገና ብዙ የምነግራችሁ ነገር አለኝ፤ አሁን ግን ልትሸከሙት አትችሉም” አለ። መንፈስ ቅዱስን ሲያፈስባቸው ይህ መንፈስ “ወደ እውነት ሁሉ” ይመራቸዋል፤ እነሱም በዚህ እውነት መሠረት መኖር ይችላሉ።—ዮሐንስ 16:12, 13
ኢየሱስ ቀጥሎ “ከጥቂት ጊዜ በኋላ አታዩኝም፤ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ታዩኛላችሁ” ማለቱ ሐዋርያቱን ግራ አጋባቸው። ምን ማለቱ እንደሆነ እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ። ኢየሱስም ስለዚህ ጉዳይ ሊጠይቁት እንደፈለጉ ስለተረዳ እንዲህ ሲል አብራራላቸው፦ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ እናንተ ታለቅሳላችሁ እንዲሁም ዋይ ዋይ ትላላችሁ፤ ዓለም ግን ይደሰታል፤ እናንተ ታዝናላችሁ፤ ሆኖም ሐዘናችሁ ወደ ደስታ ይለወጣል።” (ዮሐንስ 16:16, 20) በማግስቱ ከሰዓት በኋላ ኢየሱስ ሲገደል የሃይማኖት መሪዎቹ ደስ ይላቸዋል፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ያዝናሉ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ ሐዘናቸው ወደ ደስታ ይለወጣል! የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ሲያፈስባቸው ደግሞ ይበልጥ ይደሰታሉ።
ኢየሱስ የሐዋርያቱን ሁኔታ በምጥ ላይ ካለች ሴት ጋር በማነጻጸር እንዲህ አለ፦ “አንዲት ሴት የመውለጃዋ ሰዓት ደርሶ ስታምጥ ትጨነቃለች፤ ሕፃኑን ከወለደች በኋላ ግን አንድ ሰው ወደ ዓለም በመምጣቱ ከደስታዋ የተነሳ ሥቃይዋን ሁሉ ትረሳለች።” ከዚያም እንደሚከተለው በማለት ሐዋርያቱን አበረታታቸው፦ “እናንተም አሁን አዝናችኋል፤ ሆኖም እንደገና ስለማያችሁ ልባችሁ በደስታ ይሞላል፤ ደስታችሁን ደግሞ ማንም አይነጥቃችሁም።”—ዮሐንስ 16:21, 22
እስከዚህ ጊዜ ድረስ ሐዋርያቱ በኢየሱስ ስም ልመና አቅርበው አያውቁም። አሁን ግን “በዚያ ቀን አብን በስሜ ትለምናላችሁ” አላቸው። ይህን ሲል አብ መልስ ሊሰጣቸው ፈቃደኛ እንዳልሆነ መግለጹ ነው? አይደለም። እንዲያውም ኢየሱስ “እናንተ እኔን ስለወደዳችሁኝና የአምላክ ተወካይ ሆኜ እንደመጣሁ ስላመናችሁ አብ ራሱ ይወዳችኋል” አላቸው።—ዮሐንስ 16:26, 27
ኢየሱስ ለሐዋርያቱ የሰጣቸው ማበረታቻ ድፍረት እንዲያገኙ ሳይረዳቸው አልቀረም፤ በመሆኑም “ከአምላክ ዘንድ እንደመጣህ እናምናለን” አሉት። ይህ እምነታቸው በቅርቡ ይፈተናል። ኢየሱስ ብዙም ሳይቆይ ምን እንደሚያጋጥማቸው ሲገልጽ “እነሆ፣ ሁላችሁም ወደየቤታችሁ የምትበታተኑበትና እኔን ብቻዬን ትታችሁ የምትሄዱበት ሰዓት ቀርቧል” አለ። ይሁንና የሚከተለውን ማረጋገጫ ሰጣቸው፦ “እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በእኔ አማካኝነት ሰላም እንዲኖራችሁ ነው። በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሐንስ 16:30-33) ኢየሱስ ሐዋርያቱን ይተዋቸዋል ማለት አይደለም። እሱ ዓለምን እንዳሸነፈው ሁሉ እነሱም ዓለምን ማሸነፍ እንደሚችሉ እርግጠኛ ነው፤ ሐዋርያቱ፣ ዓለምን የሚያሸንፉት ሰይጣንና የእሱ ዓለም ንጹሕ አቋማቸውን እንዲያጎድፉ ለማድረግ ቢሞክሩም እነሱ የአምላክን ፈቃድ በታማኝነት በመፈጸም ነው።
-
-
ኢየሱስ ያቀረበው የመደምደሚያ ጸሎትኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 122
ኢየሱስ ያቀረበው የመደምደሚያ ጸሎት
አምላክንና ልጁን ማወቅ የሚያስገኘው ጥቅም
ይሖዋ፣ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያላቸው አንድነት
ኢየሱስ ለሐዋርያቱ ባለው ጥልቅ ፍቅር ተነሳስቶ በቅርቡ ከእነሱ ለሚለይበት ጊዜ ሲያዘጋጃቸው ቆይቷል። አሁን ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ለአባቱ እንዲህ ሲል ጸለየ፦ “ልጅህ ያከብርህ ዘንድ ልጅህን አክብረው፤ ይህም በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደሰጠኸው ሁሉ እሱም አንተ ለሰጠኸው ሰው ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲሰጥ ነው።”—ዮሐንስ 17:1, 2
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ፣ ለአምላክ ክብር መስጠት ከምንም በላይ አስፈላጊ እንደሆነ ተገንዝቧል። ኢየሱስ የጠቀሰው ተስፋ ይኸውም የዘላለም ሕይወት ምንኛ የሚያጽናና ነው! ኢየሱስ “በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ሥልጣን” ስለተሰጠው፣ የሰው ዘር በሙሉ ከቤዛው እንዲጠቀም ማድረግ ይችላል። ይሁንና ይህን በረከት የሚያገኙት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ አለባቸው” ብሏል፤ ኢየሱስ ከቤዛው እንዲጠቀሙ የሚያደርገው እንዲህ ዓይነት እውቀት ያላቸውን ሰዎች ብቻ ነው።—ዮሐንስ 17:3
አንድ ሰው፣ አብንና ወልድን በቅርበት ማወቅ በሌላ አባባል ከእነሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ይኖርበታል። ለነገሮች ያለው አመለካከት እነሱ ካላቸው አመለካከት ጋር መስማማት አለበት። በተጨማሪም ተወዳዳሪ የማይገኝላቸውን የይሖዋና የኢየሱስ ባሕርያት ከሌሎች ጋር ባለው ግንኙነት ለማንጸባረቅ መጣር አለበት። ከዚህም ሌላ የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ከማግኘታቸው ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር የአምላክ መከበር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልገዋል። ኢየሱስ ይህን ርዕሰ ጉዳይ እንደገና አነሳ፦
“እንድሠራው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር ላይ አከበርኩህ። ስለዚህ አባት ሆይ፣ ዓለም ከመመሥረቱ በፊት በጎንህ ሆኜ ክብር እንደነበረኝ ሁሉ አሁንም በጎንህ አድርገህ አክብረኝ።” (ዮሐንስ 17:4, 5) ኢየሱስ ይህን ሲል ቀድሞ በሰማይ የነበረውን ክብር በትንሣኤ አማካኝነት ለማግኘት እየጠየቀ ነው።
ይሁንና ኢየሱስ በአገልግሎቱ አማካኝነት ያከናወነውን ነገር አልረሳውም። “ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገልጬላቸዋለሁ። እነሱ የአንተ ነበሩ፤ አንተም ለእኔ ሰጠኸኝ፤ ደግሞም ቃልህን ጠብቀዋል” ሲል ጸለየ። (ዮሐንስ 17:6) ኢየሱስ በአገልግሎቱ ላይ ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም ከመጥራት ያለፈ ነገር አከናውኗል። ሐዋርያቱ የአምላክ ስም የሚወክለውን ነገር ይኸውም የይሖዋን ባሕርያትና ሰዎችን የሚይዝበትን መንገድ እንዲያውቁ ረድቷቸዋል።
ሐዋርያቱ ይሖዋን እንዲሁም ልጁ የሚጫወተውን ሚና ብሎም ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች አውቀዋል። ኢየሱስ እንዲህ ሲል በትሕትና ተናገረ፦ “የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁ፤ እነሱም ተቀብለውታል፤ እንዲሁም የአንተ ተወካይ ሆኜ መምጣቴን በእርግጥ አውቀዋል፤ አንተ እንደላክኸኝም አምነዋል።”—ዮሐንስ 17:8
ከዚያም ኢየሱስ በተከታዮቹና በተቀረው የሰው ዘር መካከል ያለውን ልዩነት ሲገልጽ እንዲህ አለ፦ “ስለ እነሱ እለምንሃለሁ፤ የምለምንህ ስለ ዓለም ሳይሆን አንተ ስለሰጠኸኝ ሰዎች ነው፤ ምክንያቱም እነሱ የአንተ ናቸው፤ . . . ቅዱስ አባት ሆይ፣ እኛ አንድ እንደሆንን ሁሉ እነሱም አንድ እንዲሆኑ፣ ስለሰጠኸኝ ስለ ራስህ ስም ስትል ጠብቃቸው። እኔ . . . ጠብቄአቸዋለሁ፤ . . . ከጥፋት ልጅ በቀር አንዳቸውም አልጠፉም።” የጥፋት ልጅ የተባለው ኢየሱስን አሳልፎ ሊሰጥ የሄደው የአስቆሮቱ ይሁዳ ነው።—ዮሐንስ 17:9-12
ኢየሱስ “ዓለም ጠላቸው” በማለት ጸሎቱን ቀጠለ። አክሎም “የምለምንህ ከዓለም እንድታወጣቸው ሳይሆን ከክፉው እንድትጠብቃቸው ነው። እኔ የዓለም ክፍል እንዳልሆንኩ ሁሉ እነሱም የዓለም ክፍል አይደሉም” አለ። (ዮሐንስ 17:14-16) ሐዋርያቱና ሌሎች ተከታዮቹ በዓለም ውስጥ ይኸውም ሰይጣን በሚመራው ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ውስጥ ናቸው፤ ሆኖም የኢየሱስ ተከታዮች ከዚህ ዓለምም ሆነ በዓለም ላይ ካለው ክፋት ምንጊዜም መራቅ ይኖርባቸዋል። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው?
በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን እንዲሁም ኢየሱስ ያስተማራቸውን እውነቶች ተግባራዊ በማድረግ ቅዱስ መሆን ወይም አምላክን ለማገልገል ራሳቸውን መለየት ይጠበቅባቸዋል። ኢየሱስ “በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው” በማለት ጸለየ። (ዮሐንስ 17:17) ከጊዜ በኋላ አንዳንድ ሐዋርያት በመንፈስ መሪነት መጻሕፍት ይጽፋሉ፤ እነዚህ መጻሕፍትም ቅዱስ ለመሆን በሚረዳው “እውነት” ውስጥ ይካተታሉ።
ውሎ አድሮ ‘እውነትን’ የሚቀበሉ ሌሎችም ይኖራሉ። በመሆኑም ኢየሱስ “የምለምንህ ስለ እነዚህ [አብረውት ስላሉት] ብቻ ሳይሆን በእነሱ ቃል አማካኝነት በእኔ ለሚያምኑ ጭምር ነው” በማለት ጸለየ። ኢየሱስ እነዚህን ሁሉ አስመልክቶ የጠየቀው ነገር ምንድን ነው? “ይህን ልመና የማቀርበውም ሁሉም አንድ እንዲሆኑ ነው፤ . . . አባት ሆይ፣ አንተ ከእኔ ጋር አንድነት እንዳለህና እኔም ከአንተ ጋር አንድነት እንዳለኝ ሁሉ እነሱም ከእኛ ጋር አንድነት እንዲኖራቸው ነው” ብሏል። (ዮሐንስ 17:20, 21) ኢየሱስና አባቱ ቃል በቃል አንድ አካል አይደሉም። አንድ የተባሉት በሁሉም ነገር ስለሚስማሙ ነው። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹም ከእነሱ ጋር እንዲህ ዓይነት አንድነት እንዲኖራቸው ጸለየ።
ከዚህ ጥቂት ቀደም ብሎ ኢየሱስ ለጴጥሮስና ለሌሎቹ ሐዋርያት፣ ለእነሱ በሰማይ ቦታ ለማዘጋጀት እንደሚሄድ ነግሯቸው ነበር። (ዮሐንስ 14:2, 3) አሁን ይህን ሐሳብ እንደገና በጸሎት ጠቀሰው፦ “አባት ሆይ፣ እነዚህ የሰጠኸኝ፣ እኔ ባለሁበት እነሱም ከእኔ ጋር እንዲሆኑ እፈልጋለሁ፤ ይህም ዓለም ከመመሥረቱ በፊት ስለወደድከኝ የሰጠኸኝን ክብር እንዲያዩ ነው።” (ዮሐንስ 17:24) ኢየሱስ ይህን ሲል ከረጅም ጊዜ በፊት ይኸውም አዳምና ሔዋን ልጅ ከመውለዳቸው በፊት አምላክ፣ በኋላ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለውን አንድያ ልጁን እንደወደደው መግለጹ ነው።
ኢየሱስ ጸሎቱን ሲደመድም የአምላክን ስም እንዲሁም አምላክ ለሐዋርያቱም ሆነ ወደፊት ‘እውነትን’ ለሚቀበሉ ሰዎች ያለውን ፍቅር በድጋሚ ጎላ አድርጎ ገለጸ፦ “እኔን የወደድክበት ፍቅር እነሱም እንዲኖራቸው እንዲሁም እኔ ከእነሱ ጋር አንድነት እንዲኖረኝ ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ፤ ደግሞም አሳውቃለሁ።”—ዮሐንስ 17:26
-
-
እጅግ አዝኖ እያለ ያቀረበው ጸሎትኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 123
እጅግ አዝኖ እያለ ያቀረበው ጸሎት
ማቴዎስ 26:30, 36-46 ማርቆስ 14:26, 32-42 ሉቃስ 22:39-46 ዮሐንስ 18:1
ኢየሱስ በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ
ላቡ እንደሚንጠባጠብ ደም ሆነ
ኢየሱስ ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ያቀረበውን ጸሎት ደመደመ። ከዚያም “የውዳሴ መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ሄዱ።” (ማርቆስ 14:26) በስተ ምሥራቅ ወደሚገኝ ጌትሴማኒ የተባለ የአትክልት ስፍራ አቀኑ፤ ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ወደዚህ ቦታ ይሄዳል።
በወይራ ዛፎች መካከል ወደሚገኘው ወደዚህ ውብ የአትክልት ስፍራ ሲደርሱ ኢየሱስ ከሐዋርያቱ መካከል ስምንቱ እዚያ እንዲቆዩ አደረገ። “ወደዚያ ሄጄ በምጸልይበት ጊዜ እናንተ እዚህ ተቀመጡ” ስላለ የተዋቸው በአትክልት ስፍራው መግቢያ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም ሦስት ሐዋርያቱን ይኸውም ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ አትክልት ስፍራው ገባ። እዚያ እያሉ በጣም በመረበሹ ሦስቱን ሐዋርያት “እስከ ሞት ድረስ እጅግ አዝኛለሁ። እዚህ ሁኑና ከእኔ ጋር ነቅታችሁ ጠብቁ” አላቸው።—ማቴዎስ 26:36-38
ከዚያም ኢየሱስ ከእነሱ ትንሽ ራቅ በማለት “መሬት ላይ ተደፍቶ . . . ይጸልይ ጀመር።” በጣም በተጨነቀበት በዚህ ወቅት ወደ አምላክ የሚጸልየው ስለ ምን ጉዳይ ነው? “አባት ሆይ፣ አንተ ሁሉን ነገር ማድረግ ትችላለህ፤ ይህን ጽዋ ከእኔ አርቅ። ሆኖም እኔ የምፈልገው ሳይሆን አንተ የምትፈልገው ይሁን” አለ። (ማርቆስ 14:35, 36) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነው? ቤዛ እንዲሆን የተሰጠውን ሚና መወጣት እንደማይችል መግለጹ ይሆን? በፍጹም!
ሮማውያን የሚገድሏቸውን ሰዎች ምን ያህል በጭካኔ እንደሚያሠቃዩአቸው ኢየሱስ ሰማይ እያለ ተመልክቷል። አሁን ሰው በመሆኑ የሚደርስበት አካላዊ ሥቃይ ይሰማዋል፤ ይህ ደግሞ ደስ እያለው የሚጠብቀው ነገር አይደለም። ከሁሉ በላይ በከፍተኛ ጭንቀት የተዋጠው ግን እንደተናቀ ወንጀለኛ ተቆጥሮ መገደሉ በአባቱ ስም ላይ ነቀፋ እንደሚያመጣ ስለተሰማው ነው። አምላክን ሰድበሃል በሚል ተከሶ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በእንጨት ላይ ይሰቀላል።
ኢየሱስ ረዘም ላለ ጊዜ ሲጸልይ ከቆየ በኋላ ሲመለስ ሦስቱ ሐዋርያት ተኝተው አገኛቸው። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስን እንዲህ አለው፦ “ከእኔ ጋር አንድ ሰዓት እንኳ ነቅታችሁ መጠበቅ አልቻላችሁም? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ነቅታችሁ ጠብቁ፤ ሳታሰልሱም ጸልዩ።” ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱም ውጥረት ውስጥ እንዳሉ፣ ሌሊቱ ደግሞ እንደገፋ በመገንዘብ “እርግጥ፣ መንፈስ ዝግጁ ነው፤ ሥጋ ግን ደካማ ነው” አለ።—ማቴዎስ 26:40, 41
ከዚያም ኢየሱስ ለሁለተኛ ጊዜ ትቷቸው በመሄድ “ይህን ጽዋ” እንዲያስወግድለት አምላክን ጠየቀ። ተመልሶ ሲመጣ ግን ሦስቱ ሐዋርያት ወደ ፈተና እንዳይገቡ መጸለይ ሲገባቸው አሁንም ተኝተው አገኛቸው። ኢየሱስ ሲያናግራቸው “የሚሉት ነገር ጠፋቸው።” (ማርቆስ 14:40) ኢየሱስ ለሦስተኛ ጊዜ በመሄድ ተንበርክኮ ጸለየ።
ኢየሱስ እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ የሚሞት መሆኑ በአባቱ ስም ላይ የሚያመጣው ነቀፋ በጣም አሳስቦታል። ይሖዋም የልጁን ጸሎት በመስማት መልአክ ልኮ አበረታታው። ያም ቢሆን ኢየሱስ ወደ አባቱ ምልጃ ማቅረቡን አላቆመም፤ እንዲያውም “ከበፊቱ ይበልጥ አጥብቆ መጸለዩን ቀጠለ።” ኢየሱስ በከፍተኛ ጭንቀት ተውጧል። በኢየሱስ ጫንቃ ላይ ታላቅ ኃላፊነት ወድቋል! የእሱም ሆነ እምነት ያላቸው የሰው ልጆች የዘላለም ሕይወት ተስፋ የተመካው በእሱ ላይ ነው። ከጭንቀቱ የተነሳ ላቡ “መሬት ላይ እንደሚንጠባጠብ ደም” ሆነ።—ሉቃስ 22:44
ኢየሱስ ወደ ሐዋርያቱ ለሦስተኛ ጊዜ ሲመለስ እንደገና ተኝተው አገኛቸው። በመሆኑም እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የእንቅልፍና የእረፍት ሰዓት ነው? እነሆ፣ የሰው ልጅ ለኃጢአተኞች አልፎ የሚሰጥበት ሰዓት ደርሷል። ተነሱ፣ እንሂድ። እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል።”—ማቴዎስ 26:45, 46
-
-
ክርስቶስ አልፎ ተሰጠ እንዲሁም ተያዘኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 124
ክርስቶስ አልፎ ተሰጠ እንዲሁም ተያዘ
ማቴዎስ 26:47-56 ማርቆስ 14:43-52 ሉቃስ 22:47-53 ዮሐንስ 18:2-12
ይሁዳ በአትክልቱ ስፍራ ኢየሱስን አሳልፎ ሰጠው
ጴጥሮስ የአንድን ሰው ጆሮ ቆረጠ
ኢየሱስ ተያዘ
እኩለ ሌሊት ካለፈ ቆይቷል። ካህናቱ፣ ኢየሱስን አሳልፎ ከሰጣቸው ለይሁዳ 30 የብር ሳንቲሞች ለመክፈል ተስማምተዋል። ስለዚህ ይሁዳ የካህናት አለቆችንና ፈሪሳውያንን ያቀፈ ትልቅ ጭፍራ አስከትሎ ኢየሱስን መፈለግ ጀመረ። አንድ የሮም ወታደሮች ቡድንና የጦሩ አዛዥም አብረዋቸው ናቸው።
ይሁዳ ከፋሲካ ራት ላይ ተነስቶ እንዲሄድ ኢየሱስ ከነገረው በኋላ በቀጥታ ወደ ካህናት አለቆቹ እንደሄደ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። (ዮሐንስ 13:27) እነሱም የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችንና አንድ የወታደሮች ቡድን ሰበሰቡ። ይሁዳ መጀመሪያ የወሰዳቸው ኢየሱስና ሐዋርያቱ የፋሲካን በዓል ወዳከበሩበት ቤት ሊሆን ይችላል። ከይሁዳ ጋር ያለው ጭፍራ የቄድሮንን ሸለቆ ተሻግሮ ወደ አትክልት ስፍራው ሄደ። ኢየሱስን ለማግኘት ቆርጠው የተነሱት እነዚህ ሰዎች ከመሣሪያ በተጨማሪ መብራትና ችቦ ይዘዋል።
ይሁዳ፣ ኢየሱስን የት እንደሚያገኘው እርግጠኛ በመሆን ሰዎቹን እየመራ ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጣ። ኢየሱስና ሐዋርያቱ ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመላለሱ ብዙ ጊዜ ወደ ጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ጎራ ይሉ ነበር። አሁን ጨለማ በመሆኑ የወይራ ዛፎቹ ኢየሱስን ሊሸፍኑት ይችላሉ። ወታደሮቹ ደግሞ ኢየሱስን አይተውት አያውቁ ይሆናል፤ ታዲያ እንዴት ሊለዩት ይችላሉ? ይሁዳ እነሱን ለመርዳት ምልክት ይሰጣቸዋል። “እኔ የምስመው ሰው እሱ ነው፤ ያዙትና እንዳያመልጥ ተጠንቅቃችሁ ውሰዱት” አላቸው።—ማርቆስ 14:44
ይሁዳ ጭፍሮቹን እየመራ ወደ አትክልት ስፍራው ገባና ኢየሱስን ከሐዋርያቱ ጋር ሲመለከተው በቀጥታ ወደ እሱ ሄደ። ከዚያም “ረቢ! ሰላም ለአንተ ይሁን” ብሎ ሳመው። ኢየሱስ ግን “ወዳጄ፣ እዚህ የተገኘህበት ዓላማ ምንድን ነው?” አለው። (ማቴዎስ 26:49, 50) ከዚያም “ይሁዳ፣ የሰውን ልጅ በመሳም አሳልፈህ ትሰጣለህ?” በማለት ለራሱ ጥያቄ መልስ ሰጠ። (ሉቃስ 22:48) ኢየሱስ ከዚህ በኋላ ለይሁዳ ትኩረት አልሰጠውም።
ኢየሱስ የችቦና የመብራቱ ብርሃን ወዳለበት ቦታ ወጣ ብሎ ሰዎቹን “ማንን ነው የምትፈልጉት?” አላቸው። እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ” ሲሉ መለሱለት። ኢየሱስ በድፍረት “እኔ ነኝ” አለ። (ዮሐንስ 18:4, 5) ሰዎቹ ምን ሊያደርግ እንደሆነ ስላላወቁ ወደ ኋላ አፈግፍገው መሬት ላይ ወደቁ።
ኢየሱስ በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ጨለማውን ተገን አድርጎ ከመሸሽ ይልቅ ማንን እንደሚፈልጉ በድጋሚ ጠየቃቸው። እነሱም “የናዝሬቱን ኢየሱስ” ብለው እንደገና ሲመልሱ ኢየሱስ ረጋ ብሎ “እኔ ነኝ አልኳችሁ እኮ። የምትፈልጉት እኔን ከሆነ እነዚህን ተዉአቸው ይሂዱ” አለ። በዚህ አስጨናቂ ጊዜም እንኳ ኢየሱስ፣ ከሐዋርያቱ መካከል አንዳቸውም እንደማይጠፉበት ቀደም ሲል የተናገረውን ሐሳብ አልዘነጋም። (ዮሐንስ 6:39፤ 17:12) ኢየሱስ ታማኝ ሐዋርያቱን ጠብቋቸዋል፤ “ከጥፋት ልጅ” ይኸውም ከይሁዳ በቀር አንዳቸውም አልጠፉበትም። (ዮሐንስ 18:7-9) በመሆኑም አሁን ሰዎቹ፣ ታማኝ ተከታዮቹን እንዲተዉአቸው ጠየቀ።
ወታደሮቹ ተነስተው ኢየሱስን ለመያዝ ሲሞክሩ ሐዋርያቱ ምን እየተከናወነ እንዳለ ገባቸው። በመሆኑም “ጌታ ሆይ፣ በሰይፍ እንምታቸው?” በማለት ጠየቁት። (ሉቃስ 22:49) ኢየሱስ መልስ ከመስጠቱ በፊት ጴጥሮስ ሐዋርያቱ ይዘዋቸው ከነበሩት ሁለት ሰይፎች መካከል አንደኛውን መዘዘ። ከዚያም የሊቀ ካህናቱ ባሪያ የሆነውን ማልኮስን መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቆረጠው።
ኢየሱስ ግን የማልኮስን ጆሮ በመዳሰስ ፈወሰው። ከዚያም ጴጥሮስን “ሰይፍህን ወደ ሰገባው መልስ፤ ሰይፍ የሚመዙ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉ” ብሎ በማዘዝ ጠቃሚ ትምህርት ሰጠ። ኢየሱስ ሰዎቹ እንዲይዙት ፈቃደኛ መሆኑን አሳይቷል፤ ምክንያቱን ሲገልጽ “እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉት ቅዱሳን መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” በማለት ተናገረ። (ማቴዎስ 26:52, 54) አክሎም “አብ የሰጠኝን ጽዋ መጠጣት አይኖርብኝም?” አለ። (ዮሐንስ 18:11) ኢየሱስ፣ አምላክ ለእሱ ያለውን ፈቃድ ለመፈጸም ሲል ለመሞት እንኳ ፈቃደኛ ነው።
ኢየሱስ ሰዎቹን እንዲህ አላቸው፦ “ወንበዴ የምትይዙ ይመስል ሰይፍና ቆመጥ ይዛችሁ የመጣችሁት እኔን ለመያዝ ነው? በየዕለቱ በቤተ መቅደስ ተቀምጬ አስተምር ነበር፤ ሆኖም ያን ጊዜ አልያዛችሁኝም። ይህ ሁሉ የሆነው ግን በነቢያት መጻሕፍት የተጻፈው እንዲፈጸም ነው።”—ማቴዎስ 26:55, 56
በዚህ ጊዜ ወታደሮቹና የጦር አዛዡ እንዲሁም የቤተ መቅደሱ ጠባቂዎች ኢየሱስን ይዘው አሰሩት። ሐዋርያቱ ይህን ሲመለከቱ ሸሹ። ሆኖም “አንድ ወጣት” (ደቀ መዝሙሩ ማርቆስ ሳይሆን አይቀርም) በሰዎቹ መካከል ቀርቶ ኢየሱስን መከተል ጀመረ። (ማርቆስ 14:51) ይሁን እንጂ ሰዎቹ ማንነቱን ሲያውቁ ሊይዙት ሞከሩ፤ በዚህ ጊዜ የለበሰውን በፍታ ጥሎ ሸሸ።
-
-
ኢየሱስ ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ተወሰደኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 125
ኢየሱስ ወደ ሐና ከዚያም ወደ ቀያፋ ተወሰደ
ማቴዎስ 26:57-68 ማርቆስ 14:53-65 ሉቃስ 22:54, 63-65 ዮሐንስ 18:13, 14, 19-24
ኢየሱስ ወደ ቀድሞው ሊቀ ካህናት ወደ ሐና ተወሰደ
የሳንሄድሪን ሸንጎ የመራው ሕጋዊ ያልሆነ የፍርድ ሂደት
ኢየሱስ እንደ ተራ ወንጀለኛ ከታሰረ በኋላ ወደ ሐና ተወሰደ፤ ሐና፣ ኢየሱስ ልጅ እያለ በቤተ መቅደሱ ውስጥ መምህራኑን ባስደመመበት ወቅት ሊቀ ካህናት ነበር። (ሉቃስ 2:42, 47) ከሐና ወንዶች ልጆች አንዳንዶቹ ከጊዜ በኋላ ሊቀ ካህናት ሆነው አገልግለዋል፤ አሁን ደግሞ ይህን ቦታ የያዘው የሐና አማች የሆነው ቀያፋ ነው።
ሐና ኢየሱስን በጥያቄ እያፋጠጠው ሳለ ቀያፋ የሳንሄድሪንን ሸንጎ ለማሰባሰብ ጊዜ አገኘ። ይህ ሸንጎ ሊቀ ካህናቱንና ቀደም ሲል ይህን ቦታ ይዘው የነበሩ ሰዎችን ጨምሮ 71 አባላት አሉት።
ሐና “ኢየሱስን ስለ ደቀ መዛሙርቱና ስለ ትምህርቱ ጠየቀው።” ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እኔ ለዓለም በግልጽ ተናግሬአለሁ። አይሁዳውያን ሁሉ በሚሰበሰቡበት በምኩራብና በቤተ መቅደሱ ሁልጊዜ አስተምር ነበር፤ በስውር የተናገርኩት ምንም ነገር የለም። እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? እኔ የነገርኳቸውን ነገር የሰሙትን ሰዎች ጠይቃቸው።”—ዮሐንስ 18:19-21
በዚህ ጊዜ አጠገቡ ከቆሙት የቤተ መቅደስ ጠባቂዎች አንዱ ኢየሱስን በጥፊ መታውና “ለካህናት አለቃው የምትመልሰው እንዲህ ነው?” ሲል አረመው። ኢየሱስ ግን ምንም ጥፋት እንዳልሠራ ስለሚያውቅ “የተሳሳተ ነገር ተናግሬ ከሆነ ስህተቴ ምን እንደሆነ ንገረኝ፤ የተናገርኩት ነገር ትክክል ከሆነ ግን ለምን ትመታኛለህ?” ሲል መለሰለት። (ዮሐንስ 18:22, 23) ከዚያም ሐና ኢየሱስን ወደ አማቹ ወደ ቀያፋ ላከው።
በዚህ ወቅት መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ይኸውም ሊቀ ካህናቱና የሕዝቡ ሽማግሌዎች እንዲሁም ጸሐፍት ተሰብስበዋል። የተሰበሰቡት በቀያፋ ቤት ነው። በፋሲካ ሌሊት እንዲህ ዓይነት ችሎት ማካሄድ ሕጉን የሚጥስ ቢሆንም ይህ የክፋት ዓላማቸውን ከማከናወን አላገዳቸውም።
እነዚህ ሰዎች ከአድልዎ ነፃ የሆነ ፍርድ እንደማይሰጡ ምንም ጥያቄ የለውም። ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ባስነሳበት ጊዜ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ኢየሱስን ለመግደል ወስነዋል። (ዮሐንስ 11:47-53) ከጥቂት ቀናት በፊት ደግሞ የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን ለመያዝና ለመግደል ሴራ ጠንስሰዋል። (ማቴዎስ 26:3, 4) በእርግጥም ኢየሱስ ሞት የተፈረደበት ገና ችሎት ፊት ሳይቀርብ ነው!
የካህናት አለቆቹና ሌሎቹ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ሕጋዊ ያልሆነ ስብሰባ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ ኢየሱስን ለመወንጀል የሚያበቃ ክስ ለማግኘት ሲሉ የሐሰት መረጃ የሚያቀርቡ ምሥክሮችን ለማግኘት እየሞከሩ ነው። ብዙ ሰዎች ያገኙ ቢሆንም ምሥክርነታቸው ሊስማማ አልቻለም። በመጨረሻ ሁለት ሰዎች ቀረቡና “‘ይህን በእጅ የተሠራ ቤተ መቅደስ አፍርሼ በሦስት ቀን ውስጥ በእጅ ያልተሠራ ሌላ እገነባለሁ’ ሲል ሰምተነዋል” አሉ። (ማርቆስ 14:58) ይሁንና የእነዚህ ሰዎች ቃል እንኳ ሙሉ በሙሉ ሊስማማ አልቻለም።
ከዚያም ቀያፋ ኢየሱስን “ምንም መልስ አትሰጥም? እነዚህ ሰዎች በአንተ ላይ ስለሰጡት ምሥክርነት ምን ትላለህ?” ሲል ጠየቀው። (ማርቆስ 14:60) ኢየሱስ ግን እርስ በርሱ የማይስማማ ሐሳብ የሰጡት ምሥክሮች ላቀረቡት የሐሰት ክስ ምንም መልስ አልሰጠም። ስለዚህ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ሌላ ዘዴ ተጠቀመ።
ቀያፋ፣ ማንኛውም ሰው የአምላክ ልጅ እንደሆነ ቢናገር አይሁዳውያን በጣም እንደሚቆጡ ያውቃል። ቀደም ሲል ኢየሱስ፣ አምላክ አባቱ እንደሆነ በተናገረ ጊዜ አይሁዶች ‘ራሱን ከአምላክ ጋር እኩል እንዳደረገ’ በመግለጽ ሊገድሉት ፈልገው ነበር። (ዮሐንስ 5:17, 18፤ 10:31-39) ቀያፋ ይህን ስሜታቸውን ስለሚያውቅ “አንተ የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆን አለመሆንህን እንድትነግረን በሕያው አምላክ አስምልሃለሁ!” በማለት ተንኮል ያዘለ ጥያቄ አቀረበለት። (ማቴዎስ 26:63) ኢየሱስ የአምላክ ልጅ እንደሆነ ተናግሮ ያውቃል። (ዮሐንስ 3:18፤ 5:25፤ 11:4) አሁን ይህን ባይናገር የአምላክ ልጅ እንዲሁም ክርስቶስ መሆኑን እንደ መካድ ሊቆጠር ይችላል። ስለዚህ ኢየሱስ “አዎ ነኝ፤ እናንተም የሰው ልጅ በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” አለ።—ማርቆስ 14:62
በዚህ ጊዜ ቀያፋ፣ ኢየሱስ የተናገረው ነገር በጣም የሚያስቆጣ እንደሆነ ለማስመሰል ልብሱን ቀደደና እንዲህ አለ፦ “አምላክን ተሳድቧል! ከዚህ በላይ ምን ምሥክሮች ያስፈልጉናል? ስድቡን እንደሆነ እናንተም ሰምታችኋል። እንግዲህ ምን ትላላችሁ?” የሸንጎው አባላትም “ሞት ይገባዋል” በማለት ፍትሕ የጎደለው ብያኔ ሰጡ።—ማቴዎስ 26:65, 66
ከዚያም በኢየሱስ ላይ ያሾፉበትና በቡጢ ይመቱት ጀመር። ሌሎች ደግሞ በጥፊ መቱት፤ ምራቃቸውንም ተፉበት። ፊቱን ሸፍነው እየመቱት “እስቲ ትንቢት ተናገር! የመታህ ማን ነው?” እያሉ አፌዙበት። (ሉቃስ 22:64) በሌሊት በተካሄደው ሕገ ወጥ ችሎት ላይ የአምላክ ልጅ ግፍ እየደረሰበት ነው!
-
-
ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደውኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
-
-
ምዕራፍ 126
ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደው
ማቴዎስ 26:69-75 ማርቆስ 14:66-72 ሉቃስ 22:54-62 ዮሐንስ 18:15-18, 25-27
ጴጥሮስ ኢየሱስን ካደው
ኢየሱስ በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ ሲያዝ ሐዋርያቱ ስለፈሩ ጥለውት ሸሹ። ሁለቱ ግን መሸሻቸውን አቁመው ተመለሱ። እነዚህ ሐዋርያት “ጴጥሮስና አንድ ሌላ ደቀ መዝሙር” እንደሆኑ ዘገባው ይገልጻል፤ ይህ ደቀ መዝሙር ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሆነ ከሁኔታው መረዳት ይቻላል። (ዮሐንስ 18:15፤ 19:35፤ 21:24) ምናልባትም ኢየሱስ ወደ ሐና እየተወሰደ ሳለ ሳይደርሱበት አልቀሩም። ሐና፣ ኢየሱስን ወደ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ ሲልከው ጴጥሮስና ዮሐንስ በርቀት ተከተሉት። በአንድ በኩል ለራሳቸው ሕይወት በመፍራት በሌላ በኩል ደግሞ ጌታቸው ስለሚደርስበት ነገር በመጨነቅ ልባቸው ለሁለት የተከፈለ ይመስላል።
ዮሐንስ በሊቀ ካህናቱ ዘንድ ስለሚታወቅ ወደ ቀያፋ ግቢ መግባት ቻለ። ጴጥሮስ ግን ውጭ በር ላይ ቆመ፤ ከዚያም ዮሐንስ ተመልሶ በር ጠባቂዋን አነጋገራትና ጴጥሮስን አስገባው።
ሌሊቱ ቀዝቃዛ በመሆኑ በግቢው ውስጥ ያሉት ሰዎች ከሰል አቀጣጥለዋል። ጴጥሮስ ከሰዎቹ ጋር ተቀምጦ እሳት እየሞቀ የኢየሱስን ፍርድ ‘መጨረሻ ለማየት’ እየተጠባበቀ ነው። (ማቴዎስ 26:58) በዚህ ጊዜ፣ ጴጥሮስን ያስገባችው በር ጠባቂ በእሳቱ ብርሃን በደንብ ተመለከተችው። ከዚያም “አንተም ከዚህ ሰው ደቀ መዛሙርት አንዱ ነህ አይደል?” በማለት አፋጠጠችው። (ዮሐንስ 18:17) ጴጥሮስን ያወቀችውና ከኢየሱስ ጋር እንደነበረ የተናገረችው ይህቺ ሴት ብቻ አይደለችም።—ማቴዎስ 26:69, 71-73፤ ማርቆስ 14:70
ይህ ጴጥሮስን በጣም አስደነገጠው። ማንነቱ እንዳይታወቅ ለማድረግ ሞክሯል፤ እንዲያውም ወደ ግቢው መግቢያ አካባቢ ሄዷል። ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር መሆኑን ካደ፤ አልፎ ተርፎም “ሰውየውን አላውቀውም፤ ምን እንደምታወሪም አላውቅም” አለ። (ማርቆስ 14:67, 68) በተጨማሪም “ይምልና ራሱን ይረግም” ማለትም የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን በመሃላ ለማረጋገጥ ዝግጁ እንደሆነ፣ ካልሆነ ደግሞ የሚመጣበትን እርግማን እንደሚቀበል ይገልጽ ጀመር።—ማቴዎስ 26:74
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢየሱስን ጉዳይ ችሎቱ እየተመለከተው ነው፤ ችሎቱ የሚካሄደው በቀያፋ ግቢ ውስጥ ከፍ ብሎ በሚገኝ ቤት ውስጥ ሳይሆን አይቀርም። ጴጥሮስና ሌሎች ሰዎች ከታች ሆነው ሲጠብቁ፣ ምሥክርነት ለመስጠት የሚገቡትንና የሚወጡትን የተለያዩ ሰዎች ይመለከቱ ይሆናል።
ጴጥሮስ የገሊላ ሰው መሆኑ ከአነጋገሩ ያስታውቃል፤ ስለዚህ ኢየሱስን እንደማያውቀው መናገሩ እውነት አለመሆኑ ግልጽ ነው። ከዚህም ሌላ በአካባቢው ከቆሙት መካከል አንዱ ጴጥሮስ ጆሮውን የቆረጠው የማልኮስ ዘመድ ነው። በመሆኑም ሰውየው “በአትክልቱ ስፍራ ከእሱ ጋር አይቼህ አልነበረም?” አለው። ጴጥሮስ ኢየሱስን ለሦስተኛ ጊዜ ሲክድ አስቀድሞ እንደተነገረው ዶሮ ጮኸ።—ዮሐንስ 13:38፤ 18:26, 27
በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ግቢውን መመልከት ወደሚያስችል በረንዳ ወጣ ያለ ይመስላል። ጌታ ዞር ብሎ ጴጥሮስን ትክ ብሎ አየው፤ በዚህ ወቅት ጴጥሮስ በጣም ተሰምቶት መሆን አለበት። ሰገነት ላይ በሚገኘው ክፍል ውስጥ እያሉ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ኢየሱስ የተናገረው ነገር ትዝ አለው። ጴጥሮስ የፈጸመው ድርጊት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሲገነዘብ ምን ተሰምቶት እንደሚሆን አስበው! በመሆኑም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።—ሉቃስ 22:61, 62
ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? በመንፈሳዊ ጠንካራና ለጌታው ታማኝ እንደሆነ በጣም እርግጠኛ የነበረው ጴጥሮስ ጌታውን ሊክድ የቻለው እንዴት ነው? እውነት እየተዛባ ነው፤ ኢየሱስም እንደ ከባድ ወንጀለኛ ተቆጥሯል። ጴጥሮስ ንጹሕ የሆነን ሰው ደግፎ መቆም ባይከብደውም “የዘላለም ሕይወት ቃል” ላለው ሰው ጀርባውን ሰጠ።—ዮሐንስ 6:68
ጴጥሮስ ላይ የደረሰው የሚያሳዝን ገጠመኝ፣ ጠንካራ እምነት ያለውና ለአምላክ ያደረ ሰው እንኳ ሊያጋጥመው ለሚችለው መከራ ወይም ፈተና ራሱን በሚገባ ካላዘጋጀ ሚዛኑን ሊስት እንደሚችል ያሳያል። ጴጥሮስ ያጋጠመው ነገር ለሁሉም የአምላክ አገልጋዮች ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሆናል!
-