የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2024 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከጥር 6-12
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 127-134
ወላጆች—ውድ ውርሻችሁን መንከባከባችሁን ቀጥሉ
በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ ያለህን ቦታ ከፍ አድርገህ ተመልከት
9 ይሖዋ ለሰዎች የመውለድ ችሎታ ሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ልጆቻቸው እሱን እንዲወዱትና እንዲያገለግሉት የማስተማር ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ወላጅ ከሆንክ ለዚህ ልዩ ስጦታ አድናቆት አለህ? ይሖዋ ለመላእክት ብዙ አስደናቂ ችሎታዎችን ቢሰጣቸውም ልጆች የመውለድ መብት አልሰጣቸውም። ስለዚህ ወላጆች፣ ልጆች የማሳደግ መብታቸውን ከፍ አድርገው ሊመለከቱት ይገባል። ወላጆች ቅዱስ አደራ፣ ማለትም ልጆቻቸውን “በይሖዋ ተግሣጽና ምክር” የማሳደግ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል። (ኤፌ. 6:4፤ ዘዳ. 6:5-7፤ መዝ. 127:3) የይሖዋ ድርጅት ወላጆችን ለመርዳት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ብዙ መሣሪያዎችን አዘጋጅቷል፤ ከእነዚህም መካከል ጽሑፎች፣ ቪዲዮዎች፣ ሙዚቃዎችና ኢንተርኔት ላይ የወጡ ሌሎች ነገሮች ይገኙበታል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የሰማዩ አባታችንም ሆነ ልጁ ኢየሱስ ልጆችን ይወዷቸዋል። (ሉቃስ 18:15-17) ወላጆች በይሖዋ የሚተማመኑ እንዲሁም ውድ ልጆቻቸውን ተንከባክበው ለማሳደግ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉ ከሆነ ይሖዋ ይደሰታል። እንዲሁም እንዲህ የሚያደርጉ ወላጆች ልጆቻቸው ለዘላለም የይሖዋ ቤተሰብ አባላት የመሆን አጋጣሚ እንዲከፈትላቸው ያደርጋሉ!
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ አሠልጥኗቸው
20 አስተዋይ ሁኑ። መዝሙር 127 ልጆችን ከፍላጻዎች ጋር ያመሳስላቸዋል። (መዝሙር 127:4ን አንብብ።) ፍላጻዎች የሚሠሩበት ነገርም ሆነ መጠናቸው እንደሚለያይ ሁሉ ሁለት ልጆችም ፍጹም አንድ ዓይነት ሊሆኑ አይችሉም። ስለዚህ ወላጆች እያንዳንዱ ልጅ ምን ዓይነት ሥልጠና እንደሚያስፈልገው መለየት አለባቸው። የይሖዋ አገልጋዮች የሆኑ ሁለት ልጆች ያሏቸው በእስራኤል የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ጠቃሚ ሆኖ ያገኙትን ነገር ሲናገሩ “እያንዳንዱን ልጅ በተናጠል መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናለን” ብለዋል። እርግጥ ነው፣ በዚህ መንገድ ልጆችን ማስጠናት አስፈላጊና የሚቻል ነገር መሆን አለመሆኑን መወሰን የእያንዳንዱ የቤተሰብ ራስ ኃላፊነት ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
በአምላክ ቤት ውስጥ የሚገኝ የለመለመ የወይራ ዛፍ
ጠቃሚ የሆነው የወይራ ዛፍ መለኮታዊ በረከቶችን ለመግለጽ ተስማሚ ነው። ፈሪሃ አምላክ ያለው ሰው የሚባረከው እንዴት ነው? መዝሙራዊው “ሚስትህ በቤትህ እልፍኝ ውስጥ እንደሚያፈራ ወይን ናት” ካለ በኋላ “ልጆችህ በማዕድህ ዙሪያ እንደ ወይራ ቡቃያ ናቸው” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 128:3) እዚህ ላይ የ“ወይራ ቡቃያ” የተባሉት ምንድን ናቸው? መዝሙራዊው ከልጆች ጋር ያመሳሰላቸውስ ለምንድን ነው?
የወይራ ዛፍ ያለማቋረጥ ከግንዱ ሥር አዳዲስ ችግኞች የሚበቅሉ መሆናቸው ከሌሎች ዛፎች የተለየ ያደርገዋል። ዋነኛው ግንድ ረጅም ዘመን በማስቆጠሩ የተነሳ እንደ ቀድሞው ፍሬ መስጠቱን በሚያቆምበት ጊዜ አራሾቹ የተወሰኑት ቡቃያዎች ወይም ችግኞች አድገው የዛፉ ዋና አካል እንዲሆኑ ሳይነኳቸው ይተዋቸዋል። ከጊዜ በኋላ ዋነኛው ዛፍ በማዕድ ዙሪያ እንዳሉ ልጆች አዲስና ጠንካራ በሆኑ ሦስት ወይም አራት ግንዶች ይከበባል። የእነዚህ ቡቃያዎች ሥር ከዋነኛው ግንድ ጋር አንድ ሲሆን እነርሱም ጥሩ የወይራ ፍሬ ያፈራሉ።
ይህ የወይራ ዛፍ ጉልህ ባሕርይ ወንዶች ልጆችና ሴቶች ልጆች በወላጆቻቸው ጠንካራ መንፈሳዊ ሥር በመጠቀም በእምነት እንዴት ጠንካራ ሆነው ሊያድጉ እንደሚችሉ ጥሩ አድርጎ ያሳያል። ልጆች እያደጉ ሲሄዱ ፍሬ በማፍራቱና ወላጆቻቸውን በመርዳቱ ሥራ ተካፋይ ይሆናሉ። ወላጆች ልጆቻቸው ከጎናቸው ሆነው ይሖዋን ሲያገለግሉ ሲመለከቱ ደስ ይላቸዋል።—ምሳሌ 15:20
ከጥር 13-19
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 135-137
“ጌታችን ከሌሎች አማልክት ሁሉ የላቀ ነው”
ክርስቶስ—የአምላክ ኃይል
15 ክርስቶስ ኃይል ያገኘው ከይሖዋ ነው፤ በመሆኑም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የተፈጥሮ ኃይሎችን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር እንደሚችል እርግጠኞች ለመሆን የሚያበቃ ምክንያት አለን። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎች እንመልከት። ከጥፋት ውኃ በፊት ይሖዋ “ከሰባት ቀን በኋላ በምድር ላይ 40 ቀንና 40 ሌሊት ዝናብ አዘንባለሁ” ብሎ ነበር። (ዘፍ. 7:4) በተመሳሳይም ዘፀአት 14:21 “ይሖዋም ሌሊቱን ሙሉ ኃይለኛ የምሥራቅ ነፋስ በማምጣት ባሕሩ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ” ይላል። በዮናስ 1:4 ላይ ደግሞ “ይሖዋ በባሕሩ ላይ ኃይለኛ ነፋስ አመጣ፤ ከባድ ማዕበል ስለተነሳ መርከቧ ልትሰበር ተቃረበች” የሚል ሐሳብ እናገኛለን። ይሖዋ የተፈጥሮ ኃይሎችን እንደሚቆጣጠር ማወቁ የሚያጽናና ነው። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የፕላኔታችን የወደፊት ዕጣ አስጊ አይደለም።
የይሖዋ ታማኝ ፍቅር ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?
16 ይሖዋ መጠጊያችን ከሆነ የደህንነት ስሜት ይሰማናል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ስሜታችን ከመደቆሱ የተነሳ ቀና ማለት ሊከብደን ይችላል። እንዲህ በሚሰማን ጊዜ ይሖዋ የሚረዳን እንዴት ነው? (መዝሙር 136:23ን አንብብ።) ክንዶቹን ከሥራችን አድርጎ ደግፎ ያነሳናል፤ እንዲሁም በእግራችን እንድንቆም ይረዳናል። (መዝ. 28:9፤ 94:18) የምናገኘው ጥቅም፦ ይሖዋ ምንጊዜም እንደሚደግፈን እናውቃለን፤ ይህም በሁለት መንገዶች እንደሚባርከን እንድናስታውስ ያደርገናል። አንደኛ፣ የምንኖረው የትም ይሁን የት አስተማማኝ መጠጊያ አለን። ሁለተኛ፣ አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን በጥልቅ ያስብልናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 1248
ያህ
ያህ የሚለው አጭር መጠሪያ ብዙውን ጊዜ እንደ ውዳሴና መዝሙር እንዲሁም ጸሎትና ልመና ካሉት ጥልቅ ስሜቶች ጋር ተያይዞ ይጠቀሳል፤ በአብዛኛው የሚገኘው በድልና በመዳን ወቅት ስላለው ደስታ በሚገልጹ ወይም ለአምላክ ታላቅ እጅና ኃይል እውቅና በሚሰጡ ጥቅሶች ላይ ነው። ቃሉ በዚህ መልኩ ልዩ በሆነ መንገድ እንደተሠራበት የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች አሉ። “ያህን አወድሱ!” (ሃሌሉያህ) የሚለው ሐረግ በመዝሙራት ውስጥ አምላክን ለማወደስ የተሠራበት ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገኘው በመዝሙር 104:35 ላይ ነው። ይህ ሐረግ በሌሎች መዝሙሮች ውስጥ መነሻ ላይ ብቻ (መዝ 111, 112)፣ አልፎ አልፎ በመዝሙሩ መሃል (135:3)፣ አንዳንድ ጊዜ መጨረሻ ላይ ብቻ (መዝ 104, 105, 115-117)፣ አብዛኛውን ጊዜ ግን መነሻም ሆነ መጨረሻ ላይ ይገኛል (መዝ 106, 113, 135, 146-150)። በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ሰማያዊ ፍጥረታት ይሖዋን በሚያወድሱበት ወቅት ይህን ሐረግ በተደጋጋሚ ተጠቅመዋል።—ራእይ 19:1-6
“ያህ” የሚለው ቃል የሚገኝባቸው ሌሎች ቦታዎችም ከውዳሴ መዝሙርና ለይሖዋ ከሚቀርብ ልመና ጋር የተያያዙ ናቸው። ለምሳሌ ሙሴ ባቀረበው የመዳን መዝሙር ውስጥ ይገኛል። (ዘፀ 15:2) ኢሳይያስ በመጽሐፉ ውስጥ “ያህ ይሖዋ” ብሎ ሁለቱንም ስሞች በመቀላቀል ለጉዳዩ አጽንዖት ሰጥቷል። (ኢሳ 12:2፤ 26:4) ሕዝቅያስ ለሞት በተቃረበበት ወቅት በተአምራዊ መንገድ ከተፈወሰ በኋላ በግጥም መልክ ባቀረበው ውዳሴ ላይ ያህ የሚለውን ቃል በመድገም የስሜቱን ጥልቀት ገልጿል። (ኢሳ 38:9, 11) ያህን ማወደስ የማይችሉትን ሙታንና በሕይወት ዘመናቸው እሱን ለማወደስ ቁርጥ ውሳኔ ያደረጉ ሰዎችን በሚያነጻጽረው ሐሳብ ውስጥም ተጠቅሷል። (መዝ 115:17, 18፤ 118:17-19) ይሖዋ ለሰጠው መዳን፣ ጥበቃና እርማት አድናቆት የሚገልጹ ሌሎች መዝሙሮችም አሉ።—መዝ 94:12፤ 118:5, 14
ከጥር 20-26
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 138-139
ፍርሃት እንቅፋት እንዲሆንብህ አትፍቀድ
በጉባኤ መካከል ይሖዋን አወድሱ
10 እጃችሁን አውጥታችሁ ሐሳብ ለመስጠት ባሰባችሁ ቁጥር ጭንቅ ይላችኋል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማችሁ እናንተ ብቻ አይደላችሁም። እውነቱን ለመናገር አብዛኞቻችን ሐሳብ ስንሰጥ በተወሰነ መጠን እንፈራለን። ሐሳብ ከመስጠት ወደኋላ እንድትሉ የሚያደርጋችሁን ይህን ፍርሃት ማሸነፍ እንድትችሉ በቅድሚያ የምትፈሩበት ምክንያት ምን እንደሆነ ማወቅ ያስፈልጋችኋል። ምናልባት የምትናገሩት ነገር እንዳይጠፋባችሁ ወይም የተሳሳተ ነገር እንዳትናገሩ ስለምትሰጉ ይሆን? አሊያም እናንተ የምትሰጡት ሐሳብ የሌሎቹን ያህል ጥሩ እንዳልሆነ ስለሚሰማችሁ ይሆን? እርግጥ እንዲህ ያለው ስሜት ስለ እናንተ አዎንታዊ ነገር የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ትሑት እንደሆናችሁና ሌሎችን ከራሳችሁ አስበልጣችሁ እንደምትመለከቱ ያሳያል። እንዲህ ያለው ባሕርይ ይሖዋን ያስደስተዋል። (መዝ. 138:6፤ ፊልጵ. 2:3) ሆኖም ይሖዋ በስብሰባዎች ላይ እሱን እንድታወድሱት እንዲሁም ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን እንድታበረታቱ ይፈልጋል። (1 ተሰ. 5:11) ደግሞም ስለሚወዳችሁ የሚያስፈልጋችሁን ድፍረት ይሰጣችኋል።
በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እርስ በርስ ተበረታቱ
7 ከዚህ በፊት በወጡ የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ የተሰጡትን ምክሮች መከለሳችሁ ሊረዳችሁ ይችላል። ማድረግ የምትችሉት አንዱ ነገር በደንብ መዘጋጀት ነው። (ምሳሌ 21:5) ትምህርቱን ከራሳችሁ ጋር ይበልጥ ባዋሃዳችሁት መጠን ሐሳብ መስጠት ይበልጥ ይቀላችኋል። በተጨማሪም አጭር መልስ ለመመለስ ሞክሩ። (ምሳሌ 15:23፤ 17:27) መልሳችሁ አጭር ከሆነ ያን ያህል አያስፈራችሁም። ደግሞም ብዙ ነጥቦች ከታጨቁበት ረጅም ሐሳብ ይልቅ አንድ ወይም ሁለት ዓረፍተ ነገር ብቻ የያዘ አጭር ሐሳብ ለመረዳት ይበልጥ ቀላል ነው። በራሳችሁ አባባል አጭር መልስ መመለሳችሁ በደንብ እንደተዘጋጃችሁና ትምህርቱን በሚገባ እንደተረዳችሁት ያሳያል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
‘እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ’
15 ይሁንና አንዳንዶች ስሜታችንን እጅግ የሚያቆስል ከፍተኛ በደል ፈጽመውብን ጥፋታቸውን ባያምኑ፣ ንስሐ ባይገቡና ይቅርታ ባይጠይቁንስ? (ምሳሌ 28:13) ይሖዋ ንስሐ የማይገቡ ልበ ደንዳና ኃጢአተኞችን ይቅር እንደማይል ቅዱሳን ጽሑፎች በግልጽ ያሳያሉ። (ዕብራውያን 6:4-6፤ 10:26, 27) እኛስ? ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ክርስቲያኖች ንስሐ ሳይገቡ ሆነ ብለው የክፋት ድርጊት የሚፈጽሙትን ሰዎች ይቅር እንዲሉ አይጠበቅባቸውም። እንዲህ ያሉት ሰዎች የአምላክ ጠላቶች ሆነዋል።” (ጥራዝ 1 ገጽ 862) እጅግ የከፋ ግፍ፣ አጸያፊ ወይም ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት የተፈጸመበት ክርስቲያን ንስሐ የማይገባን ኃጢአተኛ ይቅር የማለት ወይም በደሉን የመተው ግዴታ የለበትም።—መዝሙር 139:21, 22
ከጥር 27–የካቲት 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 140-143
እርዳታ ለማግኘት ካቀረባችሁት ልመና ጋር የሚስማማ እርምጃ ውሰዱ
‘የጥበበኞችን ቃል አዳምጥ’
13 የሚሰጣችሁን ምክር የአምላክ ፍቅር መገለጫ አድርጋችሁ ተመልከቱት። ይሖዋ የሚመኝልን የሚጠቅመንን ነገር ነው። (ምሳሌ 4:20-22) በቃሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ወይም በአንድ የጎለመሰ የእምነት ባልንጀራችን ተጠቅሞ ሲመክረን ፍቅሩን እየገለጸልን ነው። ዕብራውያን 12:9, 10 “ለጥቅማችን ሲል ይገሥጸናል” ይላል።
14 በምክሩ ላይ እንጂ በአሰጣጡ ላይ አታተኩሩ። አንዳንድ ጊዜ ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ችግር እንዳለው ይሰማን ይሆናል። እርግጥ፣ ምክር የሚሰጥ ማንኛውም ሰው በተቻለ መጠን የሚመከረው ሰው ምክሩን መቀበል ቀላል እንዲሆንለት ሊያደርግ ይገባል። (ገላ. 6:1) ተመካሪዎቹ እኛ ከሆንን ግን ምክሩ የተሰጠበት መንገድ ባያስደስተንም እንኳ በመልእክቱ ላይ ማተኮራችን ጠቃሚ ነው። ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ምክሩ የተሰጠበትን መንገድ ባልወደውም እንኳ ከተናገረው ነገር የማገኘው ትምህርት ይኖር ይሆን? ምክር ሰጪው ያሉትን ድክመቶች በማለፍ ከምክሩ ጥቅም ማግኘት እችል ይሆን?’ ምንም ዓይነት ምክር ቢሰጠን ከምክሩ ጥቅም ለማግኘት ጥረት ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ ነው።—ምሳሌ 15:31
በዚህ የመጨረሻ ቀን “የልብ ንጽሕናን” ጠብቆ መኖር
አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ተቃዋሚዎች፣ የኢኮኖሚ ችግርና ከባድ ሕመም በሚያሳድሩት ጫና የተነሳ ተስፋ ቆርጠዋል። እንዲህ ያሉ ነገሮች በልባቸው ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ያሳደሩበት ጊዜም አለ። ንጉሥ ዳዊትም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞት ስለነበር “መንፈሴ በውስጤ ዝላለች፤ ልቤም በውስጤ ደንግጦአል” በማለት ተናግሯል። (መዝ. 143:4) ዳዊት እንዲህ ያለውን ችግር እንዲቋቋም የረዳው ምንድን ነው? ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ስላደረገላቸው ነገሮችና እሱንም ቢሆን እንዴት እንዳዳነው መለስ ብሎ ማሰቡ ነበር። ይሖዋ ለታላቅ ስሙ ሲል ባደረጋቸው ነገሮች ላይ አሰላስሏል። ዳዊት ስለ አምላክ ሥራዎችም ዘወትር ያሰላስል ነበር። (መዝ. 143:5) በተመሳሳይም እኛ ስለ ፈጣሪያችንና ስላደረጋቸው ነገሮች በሙሉ እንዲሁም ወደፊት ስለሚያደርገው ነገር ማሰላሰላችን መከራ በሚያጋጥመን ጊዜም እንኳ የልባችንን ንጽሕና እንድንጠብቅ ይረዳናል።
“በጌታ ብቻ” ማግባት—በዘመናችንም ይቻላል?
አንቺም “ፈጥነህ መልስልኝ፤ መንፈሴ ደከመች፤ . . . ፊትህን ከእኔ አትሰውር” በማለት ወደ ይሖዋ እንደጸለየው እንደ መዝሙራዊው ዳዊት የሚሰማሽ ጊዜ ሊኖር ይችላል። (መዝ. 143:5-7, 10) እንዲህ ባሉት ጊዜያት የሰማዩ አባትሽ ለአንቺ ያለው ፈቃድ ምን እንደሆነ እንዲያሳይሽ ጊዜ ስጪው። የእሱን ቃል ለማንበብና ባነበብሽው ነገር ላይ ለማሰላሰል ጊዜ በመመደብ ይህን ማድረግ ትችያለሽ። ይህን ስታደርጊ ትእዛዛቱን ይበልጥ መረዳትና ይሖዋ ባለፉት ዘመናት ለሕዝቡ ሲል የወሰዳቸውን እርምጃዎች ማስተዋል ትችያለሽ። አምላክን ስትሰሚ እሱን መታዘዝ የጥበብ አካሄድ መሆኑን ይበልጥ እርግጠኛ ትሆኛለሽ።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 1151
መርዝ
ምሳሌያዊ ትርጉም። ክፉዎች የሰዎችን መልካም ስም ለማበላሸት የሚናገሩት ውሸትና ስድብ ገዳይ ከሆነው የእባብ መርዝ ጋር ተመሳስሏል። (መዝ 58:3, 4) መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ስም አጥፊዎች ሲናገር “ከከንፈራቸው ኋላ የእፉኝት መርዝ አለ” ይላል፤ የእባብ መርዝ የሚመነጭበት ዕጢም የሚገኘው ከከንፈሩና ከላይኛው መንጋጋው ኋላ ነው። (መዝ 140:3፤ ሮም 3:13) የሰዎች ምላስም ስም ለማጥፋት፣ ለሐሜት፣ ለሐሰት ትምህርት ወይም ለሌላ ጎጂ ንግግር ስትውል “ገዳይ መርዝ የሞላባት” ትሆናለች።—ያዕ 3:8
ከየካቲት 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 144-146
“አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ ደስተኛ ነው!”
የአንባቢያን ጥያቄዎች
1. የመዝሙሩ አውድ። ቁጥር 12 የሚጀምረው “ያን ጊዜ” ብሎ ነው፤ ይህም ከቁጥር 12 እስከ 14 ላይ የተጠቀሱትን በረከቶች የሚያገኙት፣ በቁጥር 11 ላይ ከክፉዎች ‘እንዲታደጋቸውና እንዲያድናቸው’ አምላክን የለመኑት ጻድቃን መሆናቸውን ያመለክታል። ቁጥር 15ም ይህን ሐሳብ ይደግፋል፤ በዚያ ጥቅስ ላይ “ደስተኛ” እንደሆነ ተደርጎ ሁለት ጊዜ የተገለጸው “አምላኩ ይሖዋ የሆነለት ሕዝብ” ነው።
2. ይህ አተረጓጎም አምላክ ታማኝ ሕዝቦቹን እንደሚባርካቸው የሚገልጽ ተስፋ ከያዙ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር ይስማማል። መዝሙር 144 አምላክ እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው ከታደጋቸው በኋላ ደስተኛና ባለጸጋ እንዲሆኑ በማድረግ እንደሚባርካቸው መዝሙራዊው ዳዊት ያለውን አስተማማኝ ተስፋ የሚገልጽ ነው። (ዘሌ. 26:9, 10፤ ዘዳ. 7:13፤ መዝ. 128:1-6) ለምሳሌ ያህል፣ ዘዳግም 28:4 “የሆድህ ፍሬ፣ የመሬትህ ፍሬ፣ የቤት እንስሳህ ግልገል፣ ጥጃህና የበግህ ግልገል የተባረከ ይሆናል” በማለት ይናገራል። በእርግጥም በዳዊት ልጅ በሰለሞን የግዛት ዘመን ብሔሩ ከዚያ በፊት ታይቶ የማያውቅ ሰላምና ብልጽግና አግኝቶ ነበር። ከዚህም ሌላ፣ የሰለሞን ግዛት አንዳንድ ገጽታዎች በመሲሑ አገዛዝ ወቅት የሚኖሩ ሁኔታዎችን ያመለክታሉ።—1 ነገ. 4:20, 21፤ መዝ. 72:1-20
ክርስቲያናዊ ተስፋችሁን አጠናክሩ
16 የዘላለም ሕይወት ተስፋችን ከአምላክ ያገኘነው ውድ ስጦታ ነው። ወደፊት ግሩም ሕይወት ይጠብቀናል፤ እንደምናገኘውም እርግጠኞች ነን። ተስፋችን እንደ መልሕቅ በመሆን ፈተናዎችን እንድንወጣ፣ ስደትን እንድንቋቋም አልፎ ተርፎም ሞትን እንድንጋፈጥ ይረዳናል። እንደ ራስ ቁር በመሆን አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል፤ ይህም መጥፎ የሆነውን ለመጸየፍና ጥሩ የሆነውን አጥብቀን ለመያዝ ይረዳናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ተስፋችን ወደ አምላክ እንድንቀርብ የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ እሱ ምን ያህል እንደሚወደን ያሳየናል። ተስፋችን ጠንካራ ከሆነ በእጅጉ እንጠቀማለን።
17 ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ “በተስፋው ደስ ይበላችሁ” የሚል ማበረታቻ ሰጥቷል። (ሮም 12:12) ጳውሎስ ታማኝነቱን ከጠበቀ በሰማይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝ እርግጠኛ ስለነበር ሊደሰት ችሏል። እኛም ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚጠብቅ እርግጠኞች ስለሆንን በተስፋችን ልንደሰት እንችላለን። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአምላኩ በይሖዋ ተስፋ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው፤ እሱ . . . ለዘላለም ታማኝ ነው።”—መዝ. 146:5, 6
እውነተኛ ደስታ የሚያስገኘው ምን ዓይነት ፍቅር ነው?
19 የሰው ልጆች በሰይጣን ዓለም ውስጥ ለ6,000 ዓመታት ያህል ሲሠቃዩ ኖረዋል። ዛሬ የምንኖረው በዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ሲሆን ምድር ራሳቸውን፣ ገንዘብንና ሥጋዊ ደስታን ከሚገባው በላይ በሚወዱ ሰዎች ተሞልታለች። እነዚህ ሰዎች የሚያስቡት፣ ማግኘት ስለሚችሉት ነገር ብቻ ከመሆኑም ሌላ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቁን ቦታ የሚሰጡት ለራሳቸው ፍላጎት ነው። እንዲህ ዓይነቶቹ ሰዎች መቼም ቢሆን እውነተኛ ደስታ ሊኖራቸው አይችልም። ከዚህ በተቃራኒ ግን መዝሙራዊው እንደገለጸው “የያዕቆብ አምላክ ረዳቱ የሆነ፣ በአምላኩ በይሖዋ ተስፋ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው።”—መዝ. 146:5
20 የአምላክ ሕዝቦች ለእሱ ያላቸው ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፤ ስለ አምላክ የተማሩና ለእሱ ፍቅር ያዳበሩ ሌሎች ብዙዎችም በየዓመቱ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ይተባበራሉ። ይህም የአምላክ መንግሥት እየገዛ እንዳለና በቅርቡ ለምድር ነዋሪዎች አስደናቂ በረከቶችን እንደሚያመጣ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። እውነተኛና ዘላቂ የሆነ ደስታ የሚያስገኝልን የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችን ብሎም ሉዓላዊውን አምላክ እያስደሰትን እንደሆነ ማወቃችን ነው። ይሖዋን የሚወዱ ሰዎች ለዘላለም ደስተኞች ሆነው ይኖራሉ! በሚቀጥለው ርዕስ ላይ፣ ራስ ወዳድ የሆኑ ሰዎች የሚያንጸባርቋቸውን አንዳንድ መጥፎ ባሕርያት እንመለከታለን፤ በተጨማሪም እነዚህ ባሕርያት የይሖዋ አገልጋዮች ከሚያሳዩአቸው መልካም ባሕርያት እንዴት እንደሚለዩ እንመረምራለን።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 111 አን. 9
እንስሳት
መጽሐፍ ቅዱስ እንስሳት በፍትሕና በምሕረት ሊያዙ እንደሚገባ አበክሮ ይገልጻል። ይሖዋ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በፍቅር እንደሚያሟላላቸውና ለደህንነታቸው እንደሚያስብ ገልጿል። (ምሳሌ 12:10፤ መዝ 145:15, 16) የሙሴ ሕግ የቤት እንስሳት በእንክብካቤ ሊያዙ እንደሚገባ ይደነግጋል። እስራኤላውያን የሚባዝን የቤት እንስሳ ሲያዩ ለባለቤቱ መመለስ እንዲሁም ጭነት ከብዶት ሲያዩ ጭነቱን ከእሱ ላይ ማውረድ ነበረባቸው። (ዘፀ 23:4, 5) በጭካኔ ሊያሠሯቸው አይገባም ነበር። (ዘዳ 22:10፤ 25:4) እነሱም እንደ ሰዎች ከሰንበት እረፍት ተጠቃሚ ነበሩ። (ዘፀ 20:10፤ 23:12፤ ዘዳ 5:14) አደገኛ እንስሳት ቁጥጥር ሊደረግባቸው ወይም ሊገደሉ ይገባ ነበር። (ዘፍ 9:5፤ ዘፀ 21:28, 29) የተለያዩ እንስሳትን ማዳቀል ተከልክሎ ነበር።—ዘሌ 19:19
ከየካቲት 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት መዝሙር 147-150
ያህን ለማወደስ የሚያነሳሱን በርካታ ምክንያቶች አሉ
“ያህን አወድሱ!”—ለምን?
5 ይሖዋ እስራኤላውያንን ያጽናናቸው በብሔር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግለሰብ ደረጃም ጭምር ነው። ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። መዝሙራዊው ስለ አምላክ ሲናገር “የተሰበረ ልብ ያላቸውን ይጠግናል፤ ቁስላቸውን ይፈውሳል” ብሏል። (መዝ. 147:3) በእርግጥም ይሖዋ፣ አካላዊ ችግር ላጋጠማቸውም ሆነ ስሜታቸው ለተደቆሰ ሰዎች ያስባል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ፣ እኛን ለማጽናናትና የተደቆሰውን ስሜታችንን ለመፈወስ ዝግጁ ነው። (መዝ. 34:18፤ ኢሳ. 57:15) የሚያጋጥመንን ማንኛውንም መከራ ለመቋቋም የሚያስችል ጥበብና ጥንካሬም ይሰጠናል።—ያዕ. 1:5
6 መዝሙራዊው ቀጥሎ ደግሞ ትኩረቱን በሰማይ ባሉት ነገሮች ላይ ያደረገ ሲሆን ይሖዋ “የከዋክብትን ብዛት ይቆጥራል፤ ሁሉንም በየስማቸው ይጠራቸዋል” በማለት ጽፏል። (መዝ. 147:4) መዝሙራዊው በሰማይ ስላሉት ፍጥረታት ስለጠቀሰ የትኩረት አቅጣጫውን እንደቀየረ ይሰማን ይሆናል፤ ይሁንና መዝሙራዊው ስለ ሰማያዊ አካላት የተናገረው ለምንድን ነው? እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ መዝሙራዊው ከዋክብትን ማየት ቢችልም ብዛታቸው ምን ያህል እንደሆነ በትክክል ማወቅ የሚችልበት መንገድ አልነበረም። ከበርካታ ዘመናት በኋላ በአሁኑ ወቅት የምንኖር ሰዎች ግን ከመዝሙራዊው ይበልጥ ብዙ ከዋክብትን ማየት ችለናል። አንዳንዶች ፍኖተ ሐሊብ በተባለው በእኛ ጋላክሲ ውስጥ ብቻ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ከዋክብት እንዳሉ ይገምታሉ። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ደግሞ በትሪሊዮኖች የሚቆጠሩ ጋላክሲዎች ሊኖሩ ይችላሉ! በእርግጥም የሰው ልጆች ከዋክብትን ቆጥረው መጨረስ አይችሉም! ፈጣሪ ግን ለእያንዳንዳቸው ስም ወይም መለያ ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም በይሖዋ ዘንድ እያንዳንዱ ኮከብ ከሌላው የተለየ ነው። (1 ቆሮ. 15:41) በምድር ላይ ስላሉት ሰብዓዊ ፍጥረታቱስ ምን ማለት ይችላል? እያንዳንዱ ኮከብ በማንኛውም ጊዜ የሚገኝበትን ትክክለኛ ቦታ የሚያውቀው አምላክ አንተንም በግለሰብ ደረጃ በሚገባ ያውቅሃል፤ በሌላ አባባል የት እንዳለህ፣ ምን እንደሚሰማህ እንዲሁም ምን እንደሚያስፈልግህ ሁልጊዜ ጠንቅቆ ያውቃል!
“ያህን አወድሱ!”—ለምን?
7 ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ስለ አንተ የሚያስብ ከመሆኑም ባሻገር በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ችግሮች ይረዳልሃል፤ እንዲሁም ችግሮችህን እንድትወጣ ለመርዳት የሚያስችል ኃይል አለው። (መዝሙር 147:5ን አንብብ።) በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳለህና የተጫነብህ ሸክም ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። አምላክ ‘አፈር መሆንህን ስለሚያስታውስ’ ያለብህን የአቅም ገደብ ይገነዘባል። (መዝ. 103:14) ፍጹማን ባለመሆናችን በተደጋጋሚ ጊዜ አንድ ዓይነት ስህተት እንፈጽም ይሆናል። ሁላችንም፣ ሳናስብ በተናገርነው ነገር የተነሳ ተቆጭተን እናውቃለን፤ አሊያም ደግሞ አልፎ አልፎ ብቅ እያለ በሚያስቸግረን የሥጋ ምኞት በመሸነፋችን ወይም በሌሎች የመቅናት ዝንባሌ ስላለን አዝነን እናውቃለን። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ድክመቶች ባይኖሩበትም እኛ ያሉብንን ድክመቶች በሚገባ ይረዳልናል፤ በዚህ ረገድ ያለው ማስተዋልም ቢሆን ወሰን የለውም፤ እንዲሁም አይመረመርም!—ኢሳ. 40:28
“ያህን አወድሱ!”—ለምን?
18 መዝሙራዊው፣ የጥንቶቹ የይሖዋ ሕዝቦች በአምላክ ዘንድ ልዩ ቦታ እንደነበራቸው ያውቅ ነበር። አምላክ “ቃሉን” እንዲሁም “ሥርዓቱንና ፍርዶቹን” የሰጠው ለእነሱ ብቻ ነው። (መዝሙር 147:19, 20ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜም በምድር ላይ ካሉ ሰዎች መካከል፣ በአምላክ ስም የምንጠራው እኛ ብቻ ነን፤ ይህም ታላቅ መብት ነው። ይሖዋን ስለምናውቅ፣ ቃሉ በሕይወታችን ውስጥ ስለሚመራን እንዲሁም ከእሱ ጋር ልዩ ዝምድና መመሥረት ስለቻልን አመስጋኞች ነን። እንደ መዝሙር 147 ጸሐፊ ሁሉ አንተም “ያህን አወድሱ!” እንድትል እንዲሁም ሌሎችም ይህን እንዲያደርጉ እንድታበረታታ የሚያነሳሱ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉህ አይሰማህም?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ፍጥረት የአምላክን ክብር ያውጃል!
22 መዝሙር 148:10 “የዱር አራዊትና የቤት እንስሳት ሁሉ፣ በምድር የሚሳቡ ፍጥረታትና የሚበሩ ወፎችም” ይላል። ብዙ እንስሳትና ሰማይ ላይ የሚበርሩ ፍጥረታት አስገራሚ ችሎታ አላቸው። በላይሳን የሚገኘው አልባጥሮስ የሚባለው ትልቅ የባሕር ወፍ ብዙ ርቀት መብረር ይችላል (በአንድ ወቅት በ90 ቀናት ውስጥ ብቻ 40,000 ኪሎ ሜትር በርሯል።) ብላክፖል ዋርብለር የምትባለው ወፍ ከሰሜን ወደ ደቡብ አሜሪካ በምታደርገው ጉዞ ምንም ሳታርፍ ከ80 ሰዓታት በላይ ትበርራለች። ግመል ውሃ የማጠራቀም ችሎታ ስላለው ሳይጠማው ለበርካታ ቀናት ሊቆይ ይችላል። ውሃውን የሚያጠራቅመው በተለምዶ እንደሚታሰበው በሻኛው ውስጥ ሳይሆን በምግብ መፍጫ የሰውነቱ ክፍሎች ውስጥ ነው። መሐንዲሶች ለማሽኖችና ለአዳዲስ መሣሪያዎች ንድፍ ለማውጣት እንስሳትን በጥንቃቄ የሚያጠኑ መሆናቸው ምንም አይገርምም። ጸሐፊዋ ጌይል ክሊር “በደንብ የሚሠራ . . . እንዲሁም በአካባቢ ላይ ብክለት የማያስከትል መሣሪያ መፈልሰፍ ከፈለጋችሁ ተፈጥሮን በማየት ናሙና የሚሆን ጥሩ ነገር ማግኘት ትችላላችሁ” ብለዋል።
ከየካቲት 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 1
ወጣቶች—የምታዳምጡት ማንን ነው?
ማንኛውም ነገር ሽልማቱን እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ
16 በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት ከሆንክ ወላጆችህ ስሜትህን እንደማይረዱልህ ወይም በጣም ጥብቅ እንደሆኑብህ ይሰማህ ይሆናል። እንዲያውም በወላጆችህ በጣም ከመበሳጨትህ የተነሳ፣ ይሖዋን ማገልገልህን ብትተው የተሻለ እንደሚሆን ታስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ በእነሱ ተማርረህ ይሖዋን ማገልገልህን ብታቆም ይዋል ይደር እንጂ፣ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውን ወላጆችህንና የጉባኤህን አባላት ያህል ከልቡ ስለ አንተ የሚያስብ ሰው እንደሌለ መገንዘብህ አይቀርም።
17 እስቲ አስበው፦ ወላጆችህ ምንም ዓይነት እርማት የማይሰጡህ ቢሆን በእርግጥ እንደሚወዱህ ይሰማህ ነበር? (ዕብ. 12:8) ምናልባትም ያስከፋህ ወላጆችህ አንተን የሚገሥጹበት መንገድ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ምክሩ በተሰጠበት መንገድ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ምክንያታቸውን ለማስተዋል ሞክር። ነገሩን በሰከነ መንፈስ ለማሰብና ወላጆችህ ሲገሥጹህ ከመጠን በላይ ላለመበሳጨት ጥረት አድርግ። የአምላክ ቃል “አዋቂ ሰው ንግግሩ ቁጥብ ነው፤ ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰውም የተረጋጋ ነው” ይላል። (ምሳሌ 17:27) እርማት ሲሰጥህ ተግሣጹ በተሰጠበት መንገድ ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ በተረጋጋ መንፈስ ምክሩን ተቀብለህ በተግባር አውለው፤ ይህም በሳል ሰው ለመሆን ጥረት እንደምታደርግ የሚያሳይ ነው። (ምሳሌ 1:8) ይሖዋን ከልብ የሚወዱ ወላጆች ያሉህ መሆኑ ትልቅ በረከት እንደሆነ ፈጽሞ አትዘንጋ። የወላጆችህ ፍላጎት የሕይወትን ሽልማት እንድታገኝ አንተን መርዳት ነው።
ክርስቲያናዊ መለያችን እንዳይጠፋ እንጠንቀቅ
11 ሰውን ሳይሆን አምላክን ለማስደሰት ጣር። በተወሰነ ደረጃ የአንድ ቡድን አባል በመሆን ማንነታችንን ለማሳየት መፈለጋችን ያለ ነገር ነው። ሁሉም ሰው ቢሆን ጓደኞች ያስፈልጉታል፤ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘታችን ደግሞ ጥሩ ስሜት ያሳድርብናል። በጉርምስና ወቅትም ሆነ ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት የእኩዮች ተጽዕኖ በጣም የሚያይል ሲሆን ይህ ተጽዕኖ ወጣቶች ሌሎችን የመምሰል ወይም የማስደሰት ከፍተኛ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ያደርጋል። ሆኖም ጓደኞቻችንና እኩዮቻችን ሁልጊዜ ለደኅንነታችን ያስባሉ ማለት አይቻልም። አንዳንድ ጊዜ እነርሱ የሚፈልጉት ክፉ ነገር ለመሥራት የሚተባበራቸው ሰው ማግኘት ብቻ ነው። (ምሳሌ 1:11-19) አንድ ክርስቲያን በእኩዮች ተጽዕኖ ሲሸነፍ ብዙውን ጊዜ ማንነቱን ለመደበቅ ይሞክራል። (መዝሙር 26:4) ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚህ ዓለም ሰዎች ጠባይ እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ” በማለት አስጠንቅቋል። (ሮሜ 12:2 ዘ ጀሩሳሌም ባይብል) ይሖዋ ዓለምን እንድንመስል የሚደረግብንን ማንኛውንም ግፊት እንድንቋቋም የሚያስፈልገንን ውስጣዊ ጥንካሬ ይሰጠናል።—ዕብራውያን 13:6
12 ከውጭ የሚደረግብን ተጽዕኖ ክርስቲያናዊ መለያችንን ሊያበላሽብን እንደሚችል ከተሰማን የላቀ ቦታ ያለው የሕዝቡ አመለካከት ወይም የብዙኃኑ ዝንባሌ ሳይሆን ለአምላክ ያለን ታማኝነት እንደሆነ ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። በዘፀአት 23:2 ላይ የሚገኘው “ክፉ በማድረግ ብዙዎችን አትከተል” የሚለው ምክር አስተማማኝ መሠረታዊ ሥርዓት ሆኖ ሊያገለግለን ይችላል። ካሌብ አብዛኞቹ እስራኤላውያን ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም ያለውን ችሎታ በተጠራጠሩ ጊዜ የብዙኃኑን አመለካከት ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። አምላክ የሰጠው ተስፋ እምነት የሚጣልበት መሆኑን እርግጠኛ የነበረ ሲሆን ይህ አቋሙም ከፍተኛ በረከት አስገኝቶለታል። (ዘኍልቍ 13:30፤ ኢያሱ 14:6-11) አንተስ ከአምላክ ጋር የመሠረትከው ዝምድና እንዳይበላሽ ለመከላከል ስትል የብዙኃኑን አመለካከት ለመቋቋም እንዲህ ያለ አቋም ትወስዳለህ?
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
እውነተኛ ጥበብ እየጮኸች ነው
6 እውነተኛ ጥበብ ‘መንገድ ላይ ስትጮኽ’ ብዙዎች ጥሪዋን ለመስማት አሻፈረኝ ይላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ጥበብን የሚቃወሙ ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ፤ እነሱም “አላዋቂዎች፣” “ፌዘኞች” እና “ሞኞች” ናቸው። (ምሳሌ 1:22-25ን አንብብ።) እነዚህ ሰዎች አምላካዊ ጥበብን የሚቃወሙት ለምን እንደሆነ እንዲሁም እነሱን ከመምሰል መቆጠብ የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዝርዝር እንመልከት።
11 በሦስተኛ ደረጃ፣ ጥበብን የሚቃወሙት “ሞኞች” ናቸው። እነዚህ ሰዎች፣ ሞኝ የተባሉት በአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች ለመመራት ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነው። በራሳቸው ዓይን ትክክል መስሎ የታያቸውን ነገር ያደርጋሉ። (ምሳሌ 12:15) እንዲህ ያሉት ሰዎች የጥበብ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን ይቃወማሉ። (መዝ. 53:1) አገልግሎት ላይ የምናገኛቸው እንዲህ ያሉ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች በማክበራችን ብዙውን ጊዜ የሰላ ትችት ይሰነዝሩብናል። ሆኖም የተሻለ ምክር ሊሰጡ አይችሉም። መጽሐፍ ቅዱስ “ለሞኝ ሰው እውነተኛ ጥበብ ሊገኝ የማይችል ነገር ነው፤ በከተማው በር ላይ አንዳች የሚናገረው ነገር የለውም” ይላል። (ምሳሌ 24:7) ሞኞች አንዳች የጥበብ ቃል አይወጣቸውም። በእርግጥም ይሖዋ ‘ከሞኝ ሰው እንድንርቅ’ ያስጠነቀቀን መሆኑ ተገቢ ነው።—ምሳሌ 14:7
ከየካቲት 24–መጋቢት 2
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 2
በትጋት የግል ጥናት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
‘በእውነት ውስጥ ተመላለሱ’
16 እርግጥ ማንበብና ማጥናት የምንወደው ሁላችንም አይደለንም። ሆኖም ይሖዋ ስለ እውነት ጥልቅ ግንዛቤ ለማግኘት ‘ተግተን እንድንፈልግ’ እንዲሁም ‘አጥብቀን እንድንሻ’ ጋብዞናል። (ምሳሌ 2:4-6ን አንብብ።) እንዲህ ያለውን ጥረት ስናደርግ ሁሌም እንጠቀማለን። ኮሪ መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚያነብበት መንገድ ሲናገር በእያንዳንዷ ጥቅስ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉንም የግርጌ ማስታወሻዎች አነብባለሁ፤ ሁሉንም የኅዳግ ማጣቀሻዎች እመለከታለሁ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ምርምር አደርጋለሁ። . . . ይህን ዘዴ በመጠቀሜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤ ብዙ ጥቅም አግኝቻለሁ!” እኛም የምንጠቀመው ዘዴ ይህም ሆነ ሌላ፣ እውነትን ለማጥናት ጊዜና ጥረት የምናውል ከሆነ ለእውነት ያለንን አድናቆት እናሳያለን።—መዝ. 1:1-3
እውነተኛ ጥበብ እየጮኸች ነው
3 ጥበብ፣ እውቀትን ተጠቅሞ ጥሩ ውሳኔ የማድረግ ችሎታን ሊያመለክት ይችላል። ይሁንና እውነተኛ ጥበብ ከዚህ ያለፈ ነገርን ይጨምራል። መጽሐፍ ቅዱስ “የጥበብ መጀመሪያ ይሖዋን መፍራት ነው፤ እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ ማወቅም ማስተዋል ነው” ይላል። (ምሳሌ 9:10) እንግዲያው ከባድ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ውሳኔያችን በይሖዋ አስተሳሰብ ማለትም ‘እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ ባለን እውቀት’ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በመመርመር እንዲህ ያለ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ እውነተኛ ጥበብ እንዳለን እናሳያለን።—ምሳሌ 2:5-7
4 እውነተኛ ጥበብ ሊሰጠን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ሮም 16:27) የጥበብ ምንጭ ይሖዋ ነው የምንለው ለምንድን ነው? አንደኛ፣ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ስለ ፍጥረታቱ ገደብ የለሽ እውቀት አለው። (መዝ. 104:24) ሁለተኛ፣ ይሖዋ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው። (ሮም 11:33) ሦስተኛ፣ ጥበብ የሚንጸባረቅበትን የይሖዋን ምክር የሚከተሉ ሰዎች ሁልጊዜ ጥቅም ያገኛሉ። (ምሳሌ 2:10-12) እውነተኛ ጥበብ ማግኘት ከፈለግን እነዚህን መሠረታዊ እውነታዎች መቀበል እንዲሁም ውሳኔ ከማድረጋችን ወይም አንድን እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት እነዚህን እውነታዎች ከግምት ማስገባት አለብን።
እናንት ወጣቶች፣ እምነታችሁን አጠናክሩ
2 አንተም ይሖዋን የምታገለግል አሊያም ስለ እሱ እየተማርክ ያለህ ወጣት ልትሆን ትችላለህ፤ ታዲያ የብዙኃኑን አመለካከት እንድትቀበል፣ ለምሳሌ በፈጣሪ ሳይሆን በዝግመተ ለውጥ እንድታምን ጫና እየተደረገብህ እንዳለ ይሰማሃል? ከሆነ እምነትህን ለማጠናከርና ምንጊዜም ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ አምላክ የሰጠህን የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ነው፤ የማመዛዘን ችሎታህ “ምንጊዜም ይጠብቅሃል።” ይህ ችሎታ እምነትህን ሊያጠፉ የሚችሉ ዓለማዊ ፍልስፍናዎች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብህ ይከላከልልሃል።—ምሳሌ 2:10-12ን አንብብ።
3 እውነተኛ እምነት ለመገንባት ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማዳበር ያስፈልጋል። (1 ጢሞ. 2:4) እንግዲያው የአምላክን ቃል ወይም ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችንን በምታጠናበት ጊዜ ሐሳቡን ገረፍ ገረፍ አድርገህ አትለፈው። ያነበብከውን ነገር ‘ማስተዋል’ እንድትችል የማመዛዘን ችሎታህን ተጠቀም። (ማቴ. 13:23) እንዲህ ማድረግህ አምላክ ፈጣሪ ስለመሆኑ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ስለመሆኑ ያለህን እምነት ለማጠናከር የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን፤ ደግሞም እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች በተመለከተ ብዙ “ተጨባጭ ማስረጃ” ማግኘት ይቻላል።—ዕብ. 11:1
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 1211 አን. 4
ንጹሕ አቋም
በንጹሕ አቋም መመላለስ የሚቻለው በግለሰቡ ጥንካሬ ሳይሆን በይሖዋና እሱ ባለው የማዳን ኃይል ላይ ጠንካራ እምነት በመገንባት ብቻ ነው። (መዝ 25:21) አምላክ ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው ለሚመላለሱ ሰዎች “ጋሻ” እና “መሸሸጊያ” በመሆን መንገዳቸውን እንደሚጠብቅላቸው ቃል ገብቷል። (ምሳሌ 2:6-8፤ 10:29፤ መዝ 41:12) ምንጊዜም የይሖዋን ሞገስ ለማግኘት ጥረት ስለሚያደርጉ ሕይወታቸው የተረጋጋ ይሆናል፤ ይህም ወደ ግባቸው ቀጥ ብለው ለመጓዝ ያስችላቸዋል። (መዝ 26:1-3፤ ምሳሌ 11:5፤ 28:18) ኢዮብ እንደገለጸው ነቀፋ የሌለባቸው ሰዎች በክፉዎች አገዛዝ የተነሳ መከራ ሊደርስባቸውና ከክፉዎች ጋር አብረው ሊሞቱ ቢችሉም እንኳ ይሖዋ ነቀፋ የሌለባቸውን ሰዎች የሕይወት ጎዳና እንደሚያውቅ፣ ርስታቸው ለዘላለም እንደሚኖር፣ የወደፊት ሕይወታቸው ሰላማዊ እንደሚሆንና መልካም ነገር እንደማይነፈጉ ቃል ገብቷል። (ኢዮብ 9:20-22፤ መዝ 37:18, 19, 37፤ 84:11፤ ምሳሌ 28:10) በኢዮብ ሁኔታ እንደታየው አንድ ሰው እውነተኛ ዋጋ የሚኖረውና አክብሮት የሚገባው በሀብቱ የተነሳ ሳይሆን ንጹሕ አቋሙን በመጠበቁ ነው። (ምሳሌ 19:1፤ 28:6) እንዲህ ያለ ወላጅ ያላቸው ልጆች ደስተኞች ናቸው (ምሳሌ 20:7)፤ ምክንያቱም የሚያኮራ ታሪክ ያለው መልካም ምሳሌ የሚሆን አባት አላቸው፤ ከመልካም ስሙና ካተረፈው አክብሮትም ይጠቀማሉ።