የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች
© 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
ከግንቦት 5-11
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 12
በትጋት መሥራት ብድራት ያስገኛል
ከአልማዝ ይበልጥ ውድ የሆነ ግሩም ባሕርይ
አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች መሠረታዊ ነገሮችን ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ካሉበት ሁኔታ በቀላሉ ለመገላገል ሲሉ ሐቀኝነት የጎደለው ነገር ከማድረግ ይልቅ ታታሪዎች በመሆን ጠንክረው ይሠራሉ። በዚህም መንገድ፣ ከማንኛውም ቁሳዊ ነገር ይልቅ ለሐቀኝነትና ለሌሎች ተወዳዳሪ የሌላቸው የአምላክ ባሕርያት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ በተግባር ያሳያሉ።—ምሳሌ 12:24፤ ኤፌ. 4:28
ከሥራ ደስታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
በተለይ በመጨረሻው ጥያቄ ላይ ማሰብ ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም ከሥራችን የበለጠ እርካታ የምናገኘው ሥራው ሌሎችን እንዴት እንደሚጠቅማቸው ስንመለከት ነው። ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) ደንበኞቻችንና አሠሪዎቻችን ከእኛ አገልግሎት በቀጥታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የታወቀ ነው፤ ሆኖም ሥራችን ጥቅም የሚያስገኘው ለእነዚህ ሰዎች ብቻ አይደለም። የቤተሰባችን አባላትና ሌሎች እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችም እኛ ከምንሠራው ሥራ ጥቅም ያገኛሉ።
የቤተሰባችን አባላት። አንድ አባወራ የቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ለማቅረብ ጠንክሮ የሚሠራ ከሆነ ቢያንስ በሁለት መንገዶች ይጠቅማቸዋል። አንደኛ፣ ለኑሮ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ማለትም ምግብ፣ ልብስና መጠለያ እንዲያገኙ ያደርጋል። ይህን በማድረግም ‘የራሱ ለሆኑት የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያቀርብ’ አምላክ የሰጠውን ኃላፊነት ይፈጽማል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ሁለተኛ፣ አንድ ታታሪ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ጠንክሮ መሥራት ያለውን ጥቅም ለልጆቹ በተግባር ያስተምራል። ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ሼን እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ ጠንክሮ በመሥራት ረገድ ምሳሌ የሚሆን ሰው ነው። አብዛኛውን ሕይወቱን ያሳለፈው በአናጺነት ሙያ ሲሆን ጠንካራና ሐቀኛ ሠራተኛ ነው። አንድ ሰው የእጅ ሙያ ኖሮት ሰዎችን የሚጠቅሙ ነገሮችን መሥራቱ ምን ያህል እርካታ እንደሚያስገኝለት ከእሱ ተምሬያለሁ።”
እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ‘ለተቸገረ ሰው ሊሰጡ የሚችሉት ነገር እንዲኖራቸው በእጃቸው መልካም ተግባር እያከናወኑ በትጋት እንዲሠሩ’ መክሯል። (ኤፌሶን 4:28) በእርግጥም ለራሳችንና ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ጠንክረን የምንሠራ ከሆነ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሌሎች ሰዎችም ለመርዳት የሚያስችል አቅም ይኖረናል። (ምሳሌ 3:27) በመሆኑም ጠንካራ ሠራተኛ መሆን መስጠት የሚያስገኘውን ደስታ እንድናጣጥም ያስችለናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
መንፈሰ ጠንካራ ነኝ?
● የችግርህን ክብደት መመዘን ተማር። ከባድና ቀላል ችግሮችን ለይ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝ ሰው ቁጣውን ወዲያውኑ ይገልጻል፤ ብልህ ሰው ግን ስድብን ችላ ብሎ ያልፋል” ይላል። (ምሳሌ 12:16) ትንሽ ችግር ስላጋጠመህ ብቻ በሐዘን ልትዋጥ አይገባም።
“ትምህርት ቤት ያሉ ልጆች ስለ ትናንሽ ችግሮች አካብደው ይናገራሉ። የማኅበራዊ ሚዲያ ጓደኞቻቸው ጉዳዩን ሲያራግቡላቸው ደግሞ ጭራሽ ይብስባቸዋል፤ ይህም የችግሩን ክብደት መመዘን እንዲከብዳቸው ያደርጋል።”—ጆአን
ከግንቦት 12-18
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 13
“የክፉዎች መብራት” አያታላችሁ
“የጠቢብ ትምህርት” የሕይወት ምንጭ ናት
መብራት የሕይወት ጎዳናችንን ለማብራት የምንታመንበትን መመሪያ ያመለክታል። ‘የአምላክ ቃል ለጻድቅ ሰው ለእግሩ መብራት፣ ለመንገዱም ብርሃን ነው።’ (መዝሙር 119:105) መጽሐፍ ቅዱስ የፈጣሪን የማይነጥፍ እውቀትና ጥበብ ይዟል። ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ ያለን ግንዛቤ ይበልጥ በጨመረ መጠን በሕይወታችን የምንመራበት መንፈሳዊ ብርሃን እየደመቀ ይሄዳል። ይህ ደግሞ በጣም የሚያስደስት ነው! ‘በውሸት እውቀት’ በተባለው ዓለማዊ ጥበብ መታለል አይኖርብንም።—1 ጢሞቴዎስ 6:20፤ 1 ቆሮንቶስ 1:20፤ ቆላስይስ 2:8
ክፉ ሰው ግን መብራቱ ምንም ያህል ቢደምቅ ወይም የቱንም ያህል ሀብታም መስሎ ቢታይ የኋላ ኋላ መብራቱ ይጠፋል። በጨለማ ውስጥ ሲዳክር እግሮቹ መሰናከላቸው አይቀርም። ከዚህም በላይ የወደፊት ‘ተስፋ አይኖረውም።’—ምሳሌ 24:20
የነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን አገልግሉ
3 ሰይጣን፣ በርካታ መንፈሳዊ ፍጡራንን ማሳሳቱ እንዳለ ሆኖ ሁለት ፍጹማን ሰዎችን በአምላክ ሉዓላዊነት ላይ እንዲያምፁ ማድረግ ከቻለ እኛን ማታለል የማይችልበት ምንም ምክንያት የለም። ሰይጣን የሚጠቀምበት ዘዴ አሁንም ቢሆን አልተለወጠም። የአምላክ መሥፈርቶች ከባድ አልፎ ተርፎም ደስታና እርካታ የሚያሳጡን እንደሆኑ አድርገን እንድናስብ በማድረግ ሊያታልለን ይሞክራል። (1 ዮሐ. 5:3) እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ የምናሳልፍ ከሆነ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ሊጋባብን ይችላል። የሥነ ምግባር ብልግና የፈጸመች አንዲት የ24 ዓመት ወጣት “በተለይ ከእኩዮቼ የተለየ አቋም እንዳለኝ ሆኖ መታየቱ ያስፈራኝ ስለነበር መጥፎ ጓደኝነት ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል” በማለት ተናግራለች። ምናልባት አንተም ተመሳሳይ ተጽዕኖ አጋጥሞህ ሊሆን ይችላል።
“አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል”
በትክክለኛ እውቀት ላይ ተመሥርቶ ሕይወቱን የሚመራ አስተዋይና ጻድቅ ሰው ይባረካል። ሰሎሞን “ጻድቅ እስኪጠግብ ድረስ ይበላል፤ የክፉዎች ሆድ ግን እንደ ተራበ ይኖራል” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (ምሳሌ 13:25) በቤተሰብ ሕይወታችን፣ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት፣ በአገልግሎት ወይም ተግሣጽ ሲሰጠን በሌላ አባባል በማንኛውም የሕይወት ዘርፍ ይሖዋ የሚበጀንን ያውቃል። እንዲሁም በቃሉ ውስጥ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ካደረግን በጣም አርኪ ሕይወት እንደምናገኝ የተረጋገጠ ነው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ልጆችን መረን በሚለቅ ኅብረተሰብ ውስጥ ልጅ ማሳደግ
ወላጆችም፣ ልጆቻቸው እንደነዚህ ቀጥ ያሉ ፍላጾች እንዲሆኑላቸው ማለትም ትክክል የሆነውን እንዲያደርጉና አቅጣጫቸውን ሳይስቱ እንዲጓዙ ይፈልጋሉ። በመሆኑም ጥበበኛ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው ከባድ ስህተት ሲሠሩ ችላ ብለው አያልፉም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታውን እንዲያስተካክሉ ልጆቻቸውን በፍቅር ይረዷቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኝነት በሕፃን ልብ ታስሮአል” ስለሚል ማንኛውም ልጅ ማስተካከያ ሊያደርግባቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ይኖራሉ። (ምሳሌ 22:15) በመሆኑም የአምላክ ቃል፣ ወላጆች ለልጆቻቸው ተግሣጽ እንዲሰጧቸው ይመክራል። (ኤፌሶን 6:4) እርግጥ ነው፣ ተግሣጽ የልጅን አስተሳሰብም ሆነ ባሕርይ በመቅረጽና በማስተካከል ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በመሆኑም፣ ምሳሌ 13:24 “በአርጩሜ ከመቅጣት የሚሳሳለት ልጁን ይጠላል፤ የሚወደው ግን በጥንቃቄ ይቀጣዋል” ማለቱ ምንም አያስደንቅም። እዚህ ላይ የገባው አርጩሜ የሚለው ቃል ማንኛውንም ዓይነት እርማት ያመለክታል። አንድ ወላጅ፣ ልጁ ያሉበትን መጥፎ ልማዶች እንዲያስወግድ በፍቅር ተነሳስቶ ተግሣጽ ይሰጠዋል። ምክንያቱም እነዚህ ልማዶች ሥር ከሰደዱ የልጁን የወደፊት ሕይወት ሊያበላሹት ይችላሉ። በእርግጥም፣ ልጁን የማይገሥጽ ወላጅ ለልጁ ፍቅር የለውም።
አፍቃሪ የሆነ ወላጅ አንድን ትእዛዝ የሰጠበትን ምክንያት ለልጁ ያስረዳዋል። በመሆኑም ተግሣጽ መስጠት ሲባል ማዘዝና መቅጣት ማለት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ፣ ይበልጥ አስፈላጊው ነገር ልጁ የተሰጠውን ትእዛዝ በሚገባ እንዲያስተውል መርዳት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ሕግን የሚጠብቅ አስተዋይ ልጅ ነው” ይላል።—ምሳሌ 28:7
ከግንቦት 19-25
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 14
አደጋ ሲከሰት አካሄዳችሁን አንድ በአንድ አጢኑ
ከአምላክ ላገኘኸው የሕይወት ስጦታ አድናቆት ይኑርህ
10 አንዳንዴ ለሕይወት አስጊ የሆኑ አደጋዎች እንዳይከሰቱ መከላከል አንችልም። ለምሳሌ እንደ ተፈጥሮ አደጋ፣ ወረርሽኝና ሕዝባዊ ዓመፅ ያሉ ነገሮች ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ናቸው። ሆኖም እንዲህ ያሉ አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት የሰዓት እላፊዎችን፣ አካባቢውን ለቀን እንድንወጣ የሚሰጡ መመሪያዎችንና የድንገተኛ ጊዜ ገደቦችን በመታዘዝ የሚደርስብንን አደጋ መቀነስ እንችላለን። (ሮም 13:1, 5-7) ለአንዳንዶቹ አደጋዎች አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ ይቻላል። እንዲህ ካሉት አደጋዎች ጋር በተያያዘ የአካባቢው ባለሥልጣናት አስቀድመን እንድንዘጋጅ በማሰብ የሚሰጡንን ማንኛውንም መመሪያ መከተላችን ተገቢ ነው። ለምሳሌ ውኃ፣ ቶሎ የማይበላሽ ምግብና የመጀመሪያ ደረጃ እርዳታ መስጫ ሣጥን ማዘጋጀታችን ተገቢ ሊሆን ይችላል።
11 በምንኖርበት አካባቢ ወረርሽኝ ቢከሰት ምን ማድረግ ይኖርብናል? እጃችንን እንደ መታጠብ፣ አካላዊ ርቀታችንን እንደ መጠበቅ፣ ማስክ እንደ ማድረግና የበሽታው ምልክት ከታየብን ተገልለን እንደ መቆየት ያሉ መመሪያዎችን ልንታዘዝ ይገባል። እነዚህን መመሪያዎች ለመታዘዝ ፈጣን መሆናችን አምላክ ለሰጠን የሕይወት ስጦታ ምን ያህል አድናቆት እንዳለን ያሳያል።
12 ድንገተኛ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ወቅት ከወዳጆቻችን፣ ከጎረቤቶቻችንና ከመገናኛ ብዙኃን የተዛቡ መረጃዎችን ልንሰማ እንችላለን። በዚህ ጊዜ “ቃልን ሁሉ” ከማመን ይልቅ መንግሥትና የሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡትን የተሻለ ተአማኒነት ያለው መረጃ ማዳመጣችን ተገቢ ነው። (ምሳሌ 14:15ን አንብብ።) የበላይ አካሉና ቅርንጫፍ ቢሮዎች የጉባኤ ስብሰባዎችንና የስብከቱን ሥራ በተመለከተ መመሪያ ከመስጠታቸው በፊት ስለ ጉዳዩ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት የቻሉትን ሁሉ ጥረት ያደርጋሉ። (ዕብ. 13:17) እንዲህ ያሉ መመሪያዎችን መታዘዛችን ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን ከአደጋ ይጠብቃል። በተጨማሪም ጉባኤው በማኅበረሰቡ ዘንድ ጥሩ ስም እንዲያተርፍ ያስችላል።—1 ጴጥ. 2:12
እንደ ሳዶቅ ደፋር ሁን
11 በአደገኛ ወቅት ወንድሞቻችንን እንድንረዳ ከተጠየቅን እንደ ሳዶቅ ዓይነት ድፍረት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? (1) መመሪያ ተከተል። እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን አንድነታችንን መጠበቃችን በጣም አስፈላጊ ነው። ከቅርንጫፍ ቢሮው ያገኘኸውን መመሪያ ተከተል። (ዕብ. 13:17) ሽማግሌዎች ለአደጋ ከመዘጋጀት እንዲሁም አደጋ ሲከሰት መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች ጋር በተያያዘ ያሉትን መመሪያዎች አዘውትረው መከለስ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮ. 14:33, 40) (2) ደፋር ሆኖም ጠንቃቃ ሁን። (ምሳሌ 22:3) የማመዛዘን ችሎታህን ተጠቀም። ሳያስፈልግ ራስህን አደጋ ላይ አትጣል። (3) በይሖዋ ታመን። ይሖዋ የአንተም ሆነ የወንድሞችህ ደህንነት በጥልቅ እንደሚያሳስበው አስታውስ። ደህንነትህን አደጋ ላይ ሳትጥል ወንድሞችህን እንድትደግፍ ሊረዳህ ይችላል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
‘አስተዋይ ርምጃውን ያስተውላል’
‘መሠሪ’ ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያው ቃል ሁለት ትርጉም አለው። አዎንታዊ በሆነ መልኩ ሲሠራበት አስተዋይ ወይም ብልህ ማለት ነው። (ምሳሌ 1:4፤ 2:11፤ 3:21) ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ቃሉ ክፋትን ወይም መሠሪነትን ሊያመለክት ይችላል።—መዝሙር 37:7፤ ምሳሌ 12:2፤ 24:8
‘መሠሪ’ ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያ ቃል ተንኮል የሚያውጠነጥንን ሰው የሚገልጽ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ለምን እንደሚጠላ ለመረዳት አስቸጋሪ አይሆንም። ሆኖም አስተዋይ የሆነ ሰውም ጭምር ይህንን ባሕርይ በማያሳዩ ሰዎች ሲጠላ እንመለከት የለም? ለምሳሌ፣ የማሰብ ችሎታቸውን በመጠቀም ‘ከዓለም ላለመሆን’ የሚመርጡ ሰዎች በዓለም ይጠላሉ። (ዮሐንስ 15:19) የማገናዘብ ችሎታቸውን የሚጠቀሙና እኩዮች የሚያሳድሩትን ጤናማ ያልሆነ ተጽዕኖ በመቋቋም ከመጥፎ ባሕርይ የሚርቁ ክርስቲያን ወጣቶች ይፌዝባቸዋል። እውነተኛ አምላኪዎች በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር ባለው ዓለም መጠላታቸው የሚጠበቅ ነው።—1 ዮሐንስ 5:19
ከግንቦት 26–ሰኔ 1
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 15
ሌሎች ደስተኛ ልብ እንዲኖራቸው እርዱ
ንጹሕ አቋማችንን ጠብቀን እንመላለስ!
16 ኢዮብ እንግዳ ተቀባይ ነበር። (ኢዮብ 31:31, 32) እኛም ሀብታሞች ባንሆንም እንኳ “የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል” ማዳበር እንችላለን። (ሮም 12:13) “ፍቅር ባለበት ጐመን መብላት፣ ጥላቻ ባለበት የሰባ ፍሪዳ ከመብላት ይሻላል” የሚለውን ጥቅስ በማስታወስ ያለችንን ትንሽ ነገር ከሌሎች ጋር መካፈል እንችላለን። (ምሳሌ 15:17) ንጹሕ አቋሙን ከሚጠብቅ የእምነት ባልንጀራችን ጋር ፍቅር በሰፈነበት ሁኔታ ያለችውን እንኳ ተካፍለን መመገባችን ደስታ እንደሚያስገኝልን ብሎም በመንፈሳዊ እንደሚጠቅመን ምንም ጥርጥር የለውም።
“ከበፊቱ ይበልጥ” እርስ በርስ እንበረታታ
16 በባሕርያችን ከሰዎች ጋር መግባባት ስለሚከብደን ብቻ ሌሎችን ማበረታታት እንደማንችል የሚሰማን ከሆነ ተሳስተናል። ለሌሎች የብርታት ምንጭ መሆን ያን ያህል ከባድ ነገር አይደለም፤ አንድን ሰው ሰላም ስንለው ሞቅ ያለ ፈገግታ ማሳየታችን ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። ግለሰቡ መልሶ ፈገግ ካላለ ይህ አንድ ችግር እንዳለ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል፤ በዚህ ጊዜ ግለሰቡ ሲናገር ማዳመጣችን ብቻ ያጽናናው ይሆናል።—ያዕ. 1:19
17 ኦንሪ የተባለ አንድ ወጣት ወንድም በሌሎች ዘንድ የተከበረ የጉባኤ ሽማግሌ የነበረውን አባቱን ጨምሮ የቅርብ ዘመዶቹ እውነትን ሲተዉ በጣም ተረብሾ ነበር። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ኦንሪን ሻይ ቤት ወስዶ ከጋበዘው በኋላ የልቡን አውጥቶ እንዲናገር አጋጣሚ ሰጠው። ይህም ኦንሪን በጣም ያበረታታው ከመሆኑም ሌላ ቤተሰቦቹ ወደ እውነት እንዲመለሱ መርዳት የሚችለው በታማኝነት ከጸና ብቻ እንደሆነ እንዲገነዘብ ረድቶታል። በተጨማሪም መዝሙር 46ን፣ ሶፎንያስ 3:17ንና ማርቆስ 10:29, 30ን ማንበቡ በእጅጉ አጽናንቶታል።
18 የማርተና የኦንሪ ተሞክሮ፣ ማጽናኛ ለሚያስፈልጋቸው ወንድሞችና እህቶች የብርታት ምንጭ መሆን እንደምንችል ያሳያል። ንጉሥ ሰለሞን እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በትክክለኛው ጊዜ የተነገረ ቃል . . . ምንኛ መልካም ነው! ብሩህ ዓይን [ወይም “በፈገግታ የተሞላ ፊት”] ልብን ደስ ያሰኛል፤ መልካም ዜናም አጥንትን ያበረታል።” (ምሳሌ 15:23, 30) በተጨማሪም በመጠበቂያ ግንብ ወይም በድረ ገጻችን ላይ የሚወጡትን ሐሳቦች ማንበባችን ተስፋ በምንቆርጥበት ጊዜ ሊያበረታታን ይችላል። ጳውሎስ የመንግሥቱን መዝሙሮች በአንድነት መዘመር የብርታት ምንጭ ሊሆን እንደሚችል ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በመዝሙራት፣ ለአምላክ በሚቀርብ ውዳሴና በአመስጋኝነት መንፈስ በሚዘመሩ መንፈሳዊ ዝማሬዎች ትምህርትና ማበረታቻ መስጠታችሁን ቀጥሉ፤ በልባችሁም ለይሖዋ ዘምሩ።”—ቆላ. 3:16፤ ሥራ 16:25
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
ክርስቲያኖች የሕክምና እርዳታ ይቀበላሉ?
2. ሌሎች ሐኪሞችን ማማከር ያስፈልገኝ ይሆን? በተለይ ሕመሙ ከባድ ከሆነ “ብዙ አማካሪዎች” መኖራቸው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።—ምሳሌ 15:22
ከሰኔ 2-8
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 16
ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዱ ሦስት ጥያቄዎች
በወጣትነት ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምርጫ ማድረግ
11 ከሁሉ የላቀ ደስታ ልናገኝ የምንችለው ይሖዋን በማገልገል ነው። (ምሳሌ 16:20) የኤርምያስ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ ይህን እውነታ ዘንግቶ የነበረ ይመስላል። በአንድ ወቅት በይሖዋ አገልግሎት ያገኝ የነበረውን ደስታ አጥቶ ነበር። በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ ብሎታል፦ “ለራስህ ታላቅ ነገር ትሻለህን? በሰው ልጆች ሁሉ ላይ ጥፋት አመጣለሁና አትፈልገው፤ . . . በሄድህበት ሁሉ ሕይወትህ እንዲተርፍልህ አደርጋለሁ።” (ኤር. 45:3, 5) ባሮክን ደስተኛ እንዲሆን ሊያደርገው የሚችለው ነገር ምንድን ነው ትላለህ? ታላቅ ነገር መሻት ወይስ የአምላክ አገልጋይ ሆኖ ከኢየሩሳሌም ጥፋት መትረፍ?—ያዕ. 1:12
12 ሌሎችን ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታ ከቀመሱት ወንድሞች መካከል አንዱ ራሚሮ ነው። ራሚሮ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “የተወለድኩት በአንዲስ ተራሮች በምትገኝ አንዲት መንደር ሲሆን ቤተሰቦቼ ድሆች ነበሩ። ታላቅ ወንድሜ ዩኒቨርሲቲ እየከፈለ ሊያስተምረኝ እንደሚፈልግ ነገረኝ፤ ይህ ደግሞ ትልቅ አጋጣሚ ነበር። ይሁንና ወንድሜ ይህን ሐሳብ ያቀረበልኝ የይሖዋ ምሥክር ሆኜ እንደተጠመቅኩ አካባቢ ነበር፤ በዚሁ ጊዜ አንድ አቅኚ ከእሱ ጋር በአንዲት ትንሽ ከተማ ውስጥ እንዳገለግል ሐሳብ አቀረበልኝ። ወደዚያ ሄጄ ፀጉር ማስተካከል የተማርኩ ሲሆን መተዳደሪያ ለማግኘት ፀጉር ቤት ከፈትኩ። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የምናቀርብላቸውን ግብዣ በደስታ ይቀበሉ ነበር። ከጊዜ በኋላ፣ በተወለድኩበት አካባቢ በሚነገር ቋንቋ በተቋቋመ አዲስ ጉባኤ ውስጥ ማገልገል ጀመርኩ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከተሰማራሁ አሥር ዓመት ሆኖኛል። ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ምሥራቹን እንዲሰሙ በመርዳት ያገኘሁትን ዓይነት ደስታ ሊሰጠኝ የሚችል ሌላ ሥራ የለም።”
ተለውጣችኋል?
ሁላችንም ቢሆን አስተዳደጋችንና አካባቢያችን ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረውብናል። አሁን ያለን አለባበስ፣ የምግብ ምርጫና ባሕርይ ሊመጣ የቻለው በተወሰነ መጠን በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች እንዲሁም በሕይወታችን ያጋጠሙን ነገሮች ተጽዕኖ ስላደረጉብን ነው።
2 እርግጥ ነው፣ ከምግብና ከአለባበስ ይበልጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጣቸው የሚገቡ ሌሎች ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ ከልጅነታችን ጀምሮ ምን ነገር ትክክል እንደሆነ ወይም ተቀባይነት እንዳለው አሊያም ምን ነገር ስህተት እንደሆነ ወይም ተቀባይነት እንደሌለው ስንማር ኖረናል። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ግን የግል ጉዳይ በመሆናቸው ሰዎች የሚወስዱት ምርጫ ከግለሰብ ወደ ግለሰብ ይለያያል። በተጨማሪም ሕሊናችን በምናደርጋቸው ምርጫዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። አብዛኛውን ጊዜ “ሕግ የሌላቸው አሕዛብ በተፈጥሮ በሕጉ ውስጥ ያሉትን ነገሮች [እንደሚያደርጉ]” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሮም 2:14) ታዲያ እንዲህ ሲባል በአምላክ ቃል ውስጥ ስለ አንድ ነገር በግልጽ የተቀመጠ ሕግ ከሌለ ያደግንበትን ወይም በአካባቢያችን የተለመደውን መንገድ ለመከተል ነፃነት አለን ማለት ነው?
3 ክርስቲያኖች እንዲህ የማያደርጉባቸው ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች አሉ። የመጀመሪያው ምን እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ለሰው ቀና መስሎ የሚታይ መንገድ አለ፤ በመጨረሻ ግን ወደ ሞት ይመራል።” (ምሳሌ 16:25) ፍጽምና የሚጎድለን በመሆናችን በእርግጥ የሚጠቅመንን ማወቅና አካሄዳችንን ፍጹም በተቃና መንገድ መምራት አንችልም። (ምሳሌ 28:26፤ ኤር. 10:23) ሁለተኛው ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው ዓለም ከሚከተላቸው ልማዶችና መሥፈርቶች በስተ ጀርባ ያለው “የዚህ ሥርዓት አምላክ” የሆነው ሰይጣን ስለሆነ ነው። (2 ቆሮ. 4:4፤ 1 ዮሐ. 5:19) በመሆኑም የይሖዋን በረከትና ሞገስ ማግኘት ከፈለግን በሮም 12:2 (ጥቅሱን አንብብ።) ላይ የሚገኘውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 629
ተግሣጽ
መቀበል ወይም ችላ ማለት የሚያመጣው ውጤት። ክፉዎች እና ሞኞች ወይም በሥነ ምግባር ያዘቀጡ ሰዎች የይሖዋን ተግሣጽ ሙሉ በሙሉ ችላ በማለት ለተግሣጹ ያላቸውን ጥላቻ ያሳያሉ። (መዝ 50:16, 17፤ ምሳሌ 1:7) እንዲህ ያለው ሞኝነት የሚያስከትለው መጥፎ ውጤት ተጨማሪ ተግሣጽን ይባስ ብሎም ከባድ ቅጣትን ያካትታል። የምሳሌ መጽሐፍ እንደሚለው “ሞኞች . . . በገዛ ሞኝነታቸው ይቀጣሉ።” (ምሳሌ 16:22) በራሳቸው ላይ ድህነት፣ ውርደትና በሽታ ሊያመጡ አልፎ ተርፎም ያለዕድሜያቸው ሊቀጩ ይችላሉ። የእስራኤላውያን ታሪክ ሞኝነት የሚያስከትለው ኪሳራ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያሳያል። በነቢያት አማካኝነት የተሰጣቸውን ወቀሳና እርማት ችላ በማለት ተግሣጽን እንደማይቀበሉ አሳይተዋል። ይሖዋ ጥበቃውንና በረከቱን በመንሳት የሰጣቸውን ተግሣጽም አልተቀበሉም። በመጨረሻም አስቀድሞ በተነገራቸው ማስጠንቀቂያ መሠረት ከባድ ተግሣጽ ተሰጣቸው፤ ድል ተነሱ እንዲሁም በግዞት ተወሰዱ።—ኤር 2:30፤ 5:3፤ 7:28፤ 17:23፤ 32:33፤ ሆሴዕ 7:12-16፤ 10:10፤ ሶፎ 3:2
ከሰኔ 9-15
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 17
በትዳራችሁ ውስጥ ሰላም አስፍኑ
ቂምን መተው የሚቻልበት መንገድ
ራስሽን በሐቀኝነት መርምሪ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንዳንድ ሰዎች “ቍጡ” እና “ግልፍተኛ” መሆን እንደሚቀናቸው ይገልጻል። (ምሳሌ 29:22) አንቺስ እንዲህ ዓይነት ችግር አለብሽ? እንደሚከተለው በማለት ራስሽን ጠይቂ፦ ‘ቁጣው የማይበርድለት ሰው ነኝ? በቀላሉ የምቀየም ነኝ? በጥቃቅን ነገሮች የመጨቃጨቅ ዝንባሌ አለኝ?’ መጽሐፍ ቅዱስ “ነገርን የሚደጋግም . . . የልብ ወዳጆችን ይለያያል” ይላል። (ምሳሌ 17:9፤ መክብብ 7:9) ይህ ሁኔታ በትዳር ውስጥም ሊያጋጥም ይችላል። በመሆኑም ቂም የመያዝ ዝንባሌ ካለሽ ‘የትዳር ጓደኛዬን ይበልጥ መታገሥ እችል ነበር?’ ብለሽ ራስሽን ጠይቂ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ 1 ጴጥሮስ 4:8
ችግሮችን መፍታት
1. በችግሩ ላይ ለመወያየት ጊዜ መድብ። “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ . . . ለዝምታ ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:1, 7) ከላይ በመግቢያችን ላይ እንደተመለከትነው አንዳንድ ችግሮች ቁጣና ጭቅጭቅ ሊያስነሱ ይችላሉ። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲከሰት ውይይቱ ወደ ጭቅጭቅ ከማምራቱ በፊት ራስህን በመግዛት ለጊዜው ንግግርህን ማቆም በሌላ አባባል ‘ዝም ማለት’ አለብህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤ ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ” በማለት የሚሰጠውን ምክር በመታዘዝ ትዳርህን ከከፋ ችግር መታደግ ትችላለህ።—ምሳሌ 17:14
ይሁን እንጂ “ለመናገርም ጊዜ አለው።” ችግሮች በወቅቱ መፍትሔ ካላገኙ እንደ አረም ሊፈሉ ይችላሉ። ስለሆነም አንድ ችግር ሲነሳ ጊዜ ይፍታው ብሎ ችላ ማለት አይገባም። ውይይቱን ለማቆም ከወሰንክ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጉዳዩን ደግማችሁ በማንሳት የምትወያዩበት ጊዜ በመመደብ ለትዳር ጓደኛህ አክብሮት እንዳለህ አሳይ። በጉዳዩ ላይ ለመወያየት ቀጠሮ መያዛችሁ መጽሐፍ ቅዱስ “በቊጣችሁ ላይ ፀሓይ አይግባ” በማለት የሚሰጠውን ምክር ሁለታችሁም ተግባራዊ እንድታደርጉ ያስችላችኋል። (ኤፌሶን 4:26) ከዚህም በተጨማሪ ቃልህን መጠበቅ ይኖርብሃል።
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
የምሳሌ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
17:24፦ አስፈላጊ ባልሆኑ ነገሮች ላይ ከሚያተኩሩና ዓይኖቻቸው ከወዲያ ወዲህ ከሚንከራተቱ “ተላሎች” በተለየ መልኩ በጥበብ መመላለስ እንችል ዘንድ ማስተዋልን ለማግኘት መጣር ይኖርብናል።
ከሰኔ 16-22
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 18
ከጤና እክል ጋር የሚታገሉ ሰዎችን በንግግራችሁ አበረታቱ
እውነተኛ ጥበብ እየጮኸች ነው
17 ከመናገርህ በፊት አስብ። ካልተጠነቀቅን በንግግራችን ከፍተኛ ጉዳት ልናደርስ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው” ይላል። (ምሳሌ 12:18) ሌሎች ስላለባቸው ድክመት ሐሜት ከማውራት የምንቆጠብ ከሆነ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናበረክታለን። (ምሳሌ 20:19) ንግግራችን ጉዳት የሚያደርስ ሳይሆን ፈውስ የሚያመጣ እንዲሆን ከፈለግን ልባችንን ከአምላክ ቃል በሚገኘው እውነት መሙላት አለብን። (ሉቃስ 6:45) መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው ነገር ላይ ካሰላሰልን ንግግራችን የሌሎችን መንፈስ የሚያድስ “የጥበብ ምንጭ” ይሆናል።—ምሳሌ 18:4
mrt ርዕስ 19 ሣጥን
ድንገተኛ የጤና እክል ሲያጋጥም
ጥሩ አድማጭ ሁን። ጓደኛህን መርዳት ከምትችልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ፣ ማውራት ሲፈልግ ማዳመጥ ነው። ለሚናገረው ነገር ሁሉ መልስ መስጠት እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። ብዙውን ጊዜ፣ ማዳመጥህ ብቻውን በቂ ነው። ትክክል ያልሆነ ነገር ቢናገርም እንኳ ሳትተቸው በትዕግሥት አዳምጠው። ምን እንደሚሰማው ሙሉ በሙሉ ይገባኛል ብለህ አታስብ፤ በተለይ የጓደኛህ ሕመም ከውጭ የሚታይ ዓይነት ካልሆነ ምን እንደሚሰማው ማወቅ አስቸጋሪ ነው።—ምሳሌ 11:2
ስትናገር አዎንታዊ ሁን። ምን ማለት እንዳለብህ ግራ ሊገባህ ይችላል፤ ሆኖም ዝም ከማለት ይልቅ ያለበት ሁኔታ ከባድ መሆኑን እንደምትረዳ የሚያሳዩ ጥቂት ቃላት መናገርህ ሊያጽናናው ይችላል። ምን ማለት እንዳለብህ ካላወቅክ ከልብ የመነጨ አጭር ሐሳብ ለመናገር ሞክር፤ ለምሳሌ “ምን ማለት እንዳለብኝ አላውቅም፤ ግን ስለ አንተ ከልብ አስባለሁ” ማለት ትችል ይሆናል። “ከዚህም የከፋ ሊሆን ይችል ነበር” ወይም “. . . ቢይዝህ ኖሮስ” እንደሚሉት ያሉ ሐሳቦችን ላለመሰንዘር ተጠንቀቅ።
ጓደኛህ ስላለበት ሕመም ምርምር በማድረግ እንደምታስብለት ማሳየት ትችላለህ። ያለበትን ሁኔታ ለመረዳት የምታደርገውን ጥረት ማድነቁ አይቀርም፤ እንዲሁም ይህን ማድረግህ ይበልጥ ጠቃሚ የሆነ ሐሳብ ለመስጠት ይረዳሃል። (ምሳሌ 18:13) ሆኖም ሳትጠየቅ ምክር ከመስጠት ተቆጠብ።
ጠቃሚ እርዳታ አበርክት። ‘ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚያስፈልገው አውቃለሁ’ ብለህ ከማሰብ ይልቅ በምን መልኩ ልትረዳው እንደምትችል ጠይቀው። ሆኖም ጓደኛህ ሊያስቸግርህ ስለማይፈልግ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ላይነግርህ እንደሚችል አስታውስ። ምን ዓይነት እርዳታ እንደሚያስፈልገው ካልነገረህ “እንድገዛልህ የምትፈልገው ነገር አለ?” “ቤት ላጽዳልህ?” ወይም “እንዲህ ላድርግልህ?” ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ።—ገላትያ 6:2
ተስፋ አትቁረጥ። ጓደኛህ ከሕመሙ ጋር ስለሚታገል አንዳንድ ጊዜ ቀጠሮ ላያከብር ወይም አንተን ማነጋገር ላይፈልግ ይችላል። ታጋሽ ሁን፤ እንዲሁም ስሜቱን ተረዳለት። የሚያስፈልገውን ድጋፍ መስጠትህን ቀጥል።—ምሳሌ 18:24
ከአእምሮ ጤንነት መቃወስ ጋር የሚታገሉ ሰዎችን መርዳት
“የተጨነቁትን አጽናኗቸው።”—1 ተሰሎንቄ 5:14
ጓደኛህ በጭንቀት ሊዋጥ ወይም የከንቱነት ስሜት ሊሰማው ይችላል። ምን ብለህ መናገር እንዳለብህ ግራ ቢገባህም እንኳ እንደምታስብለት መግለጽህ ብቻ ሊያጽናናውና ሊያበረታታው ይችላል።
“እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው።”—ምሳሌ 17:17
ተግባራዊ እርዳታ ስጠው። በመሰለህ መንገድ እርዳታ ከመስጠት ይልቅ ምን እንድታደርግለት እንደሚፈልግ ጠይቀው። ጓደኛህ ምን እንደሚያስፈልገው መናገር ከከበደው አብራችሁ በሆነ እንቅስቃሴ መካፈል እንደምትችሉ ንገረው፤ ለምሳሌ ‘በእግራችን ዞር ዞር እንበል’ ልትለው ትችላለህ። አሊያም ደግሞ ገበያ በመውጣት፣ ቤት በማጽዳት ወይም በሌላ ሥራ ልታግዘው እንደምትችል ንገረው።—ገላትያ 6:2
‘በትዕግሥት ያዟቸው።’—1 ተሰሎንቄ 5:14
ጓደኛህ አንዳንድ ጊዜ ማውራት ላይፈልግ ይችላል። ስለዚህ ማውራት በሚፈልግበት ጊዜ ልታዳምጠው ፈቃደኛ እንደሆንክ ንገረው። ጓደኛህ በሕመሙ የተነሳ የሚጎዳህ ነገር ሊናገር ወይም ሊያደርግ ይችል ይሆናል። ቀጠሮ ሊሰርዝብህ ወይም በቀላሉ ሊበሳጭ ይችላል። የሚያስፈልገውን ድጋፍ በምትሰጥበት ወቅት ታጋሽ ለመሆንና ስሜቱን ለመረዳት ጥረት አድርግ።—ምሳሌ 18:24
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
‘ጥበብ ጥላ ከለላ ነው’
የእስራኤሉ ንጉሥ “ዕጣ በጕያ ውስጥ ይጣላል፤ ውሳኔው በሙሉ ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው” በማለት ተናገረ። (ምሳሌ 16:33) በጥንት እስራኤል ይሖዋ ፈቃዱ ምን እንደሆነ ለማሳወቅ በዕጣ የተጠቀመባቸው ጊዜያት ነበሩ። በዚያን ጊዜ ዕጣዎች የሚዘጋጁት ከጠጠር፣ ከቁርጥራጭ እንጨት ወይም ከድንጋይ ነበር። በመጀመሪያ አንድን ጉዳይ በሚመለከት የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ በጸሎት ይጠየቃል። ከዚያም ዕጣዎቹ በአንድ በታጠፈ ልብስ ውስጥ ይጨመሩና አንድ ሰው ዕጣውን እንዲያወጣ ይደረጋል። የሚወጣው ዕጣ የአምላክ ፈቃድ እንደሆነ ተደርጎ ስለሚታይ በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኛል።
ከሰኔ 23-29
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 19
ለወንድሞቻችሁ እውነተኛ ወዳጅ ሁኑ
እርስ በርስ ያለንን ፍቅር ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?
16 በወንድሞቻችሁና በእህቶቻችሁ መጥፎ ጎን ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ አተኩሩ። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ከተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር ተሰብስባችሁ እየተጫወታችሁ ነው እንበል። በጣም ጥሩ ጊዜ አሳልፋችሁ ልትለያዩ ስትሉ አንድ ላይ ፎቶ ትነሳላችሁ። ፎቶውን ስታነሱ ለማንኛውም ብላችሁ ሁለት ተጨማሪ ፎቶዎችን አነሳችሁ። በድምሩ ሦስት ፎቶዎች አንስታችኋል ማለት ነው። አንደኛው ፎቶ ላይ አንድ ወንድም እንደተኮሳተረ አስተዋላችሁ። ይህን ፎቶ ምን ታደርጉታላችሁ? ፎቶውን ታጠፉታላችሁ፤ ምክንያቱም በሌሎቹ ሁለት ፎቶዎች ላይ ይህን ወንድም ጨምሮ ሁሉም ሰው ፈገግ ብሏል።
17 የምናስቀምጣቸውን ፎቶግራፎች በአእምሯችን ከምንይዛቸው ትዝታዎች ጋር ልናመሳስላቸው እንችላለን። ብዙውን ጊዜ፣ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ጊዜ ስናሳልፍ ጥሩ ትዝታ ይኖረናል። ሆኖም በአንድ ወቅት አንድ ወንድማችን ወይም እህታችን ደግነት የጎደለው ነገር ቢያደርጉ ወይም ቢናገሩስ? ይህን ትዝታ ምን ልናደርገው ይገባል? አንደኛውን ፎቶ እንደሰረዝነው ሁሉ ይህን ትዝታ ከአእምሯችን ብናጠፋው የተሻለ አይሆንም? (ምሳሌ 19:11፤ ኤፌ. 4:32) ወንድማችን የሠራውን አነስተኛ ስህተት ከአእምሯችን ልናጠፋው እንችላለን፤ ምክንያቱም ከዚያ ግለሰብ ጋር ብዙ አስደሳች ትዝታዎች አሉን። አእምሯችን ውስጥ መያዝ የምንፈልገው እንዲህ ያሉትን ትዝታዎች ነው።
ፍቅርህ እያደገ ይሂድ
10 እኛም ክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለመርዳት አጋጣሚ እንፈልጋለን። (ዕብ. 13:16) ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው አና ያደረገችውን እንመልከት። በአካባቢያቸው ውድመት ያደረሰ ኃይለኛ ዝናብ ተከስቶ ነበር። በኋላ ላይ እሷና ባለቤቷ አንድ ቤተሰብ ለመጠየቅ ሄዱ፤ የዚህ ቤተሰብ ቤት ጣሪያው እንደተነደለና በዚህም ምክንያት ልብሶቻቸው ሁሉ እንደቆሸሹባቸው አስተዋሉ። አና እንዲህ ብላለች፦ “ልብሳቸውን ወሰድንና አጥበን፣ ተኩሰንና አጣጥፈን መለስንላቸው። ይህ ለእኛ ምንም ማለት አልነበረም። ሆኖም ከዚህ ቤተሰብ ጋር እስከ ዛሬ ድረስ የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረት ችለናል።” አናና ባለቤቷ ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅር፣ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያደርጉላቸው አነሳስቷቸዋል።—1 ዮሐ. 3:17, 18
11 ፍቅርና ደግነት ስናሳይ ይሖዋን በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ለመምሰል የምናደርገውን ጥረት ሌሎች ማስተዋላቸው አይቀርም። እኛ ከምናስበው በላይ ደግነታችንን ያደንቁ ይሆናል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካን እገዛ ያደረጉላትን ሰዎች ሁሌም በመልካም ታስታውሳቸዋለች። እንዲህ ብላለች፦ “አገልግሎት ይዘውኝ ይወጡ ለነበሩት እህቶች በጣም አመስጋኝ ነኝ። ከቤቴ መጥተው ይወስዱኛል፣ ሻይ ቡና ወይም ምሳ ይጋብዙኛል፣ ከዚያም ቤቴ ድረስ ይሸኙኛል። አሁን ሳስበው ለእኔ ብዙ እንደደከሙ ይሰማኛል። ይህንንም ያደረጉት በደስታ ነው።” እርግጥ ነው፣ ላደረግነው ነገር የሚያመሰግነን ሁሉም ሰው አይደለም። ካን ያገዟትን ሰዎች በተመለከተ እንዲህ ብላለች፦ “ላሳዩኝ ደግነት ውለታቸውን ብመልስ ደስ ይለኝ ነበር። ሆኖም የማናቸውንም የመኖሪያ አድራሻ አላውቅም፤ ይሖዋ ግን ያውቃል። ስለዚህ ብድራታቸውን እንዲመልስላቸው እጸልያለሁ።” ካን የተናገረችው ነገር እውነት ነው። ይሖዋ ለሌሎች የምናሳየውን ትንሿን ደግነት እንኳ ያስተውላል። ውድ ዋጋ እንዳለው መሥዋዕት አድርጎ ይመለከተዋል፤ ለእሱ እንዳበደርነው አድርጎም ይቆጥረዋል።—ምሳሌ 19:17ን አንብብ።
አንዳችሁ ለሌላው ታማኝ ፍቅር ማሳየታችሁን ቀጥሉ
6 በአንድ መሥሪያ ቤት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የሠራ ሰው ታማኝ ሠራተኛ ተብሎ ሲጠራ እንሰማለን። ሆኖም ግለሰቡ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ቢያገለግልም የመሥሪያ ቤቱን ባለቤቶች አግኝቷቸው አያውቅ ይሆናል። በድርጅቱ ፖሊሲዎችም የማይስማማበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ለድርጅቱ የተለየ ፍቅር የለውም፤ ግን ገቢ ስለሚያስገኝለት በሥራው ደስተኛ ነው። ጡረታ እስኪወጣ ወይም ሌላ የተሻለ ሥራ እስኪያገኝ ድረስ በዚያ ድርጅት ውስጥ ማገልገሉን ይቀጥላል።
7 በአንቀጽ 6 ላይ በተጠቀሰው ዓይነት ታማኝነት እና በታማኝ ፍቅር መካከል ያለው ልዩነት የግለሰቡ የልብ ዝንባሌ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት የአምላክ አገልጋዮች ታማኝ ፍቅር ለማሳየት ያነሳሳቸው ምንድን ነው? እነዚህ ሰዎች ታማኝ ፍቅር ያሳዩት ይህን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ተሰምቷቸው ሳይሆን ልባቸው ስለገፋፋቸው ነው። የዳዊትን ምሳሌ እንመልከት። የዮናታን አባት ዳዊትን ለመግደል ይፈልግ የነበረ ቢሆንም ዳዊት ከልቡ ተነሳስቶ ለወዳጁ ለዮናታን ታማኝ ፍቅር አሳይቶታል። ዮናታን ከሞተ ከዓመታት በኋላ እንኳ ዳዊት ለዮናታን ልጅ ለሜፊቦስቴ ታማኝ ፍቅር ማሳየቱን ቀጥሎ ነበር።—1 ሳሙ. 20:9, 14, 15፤ 2 ሳሙ. 4:4፤ 8:15፤ 9:1, 6, 7
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-1 515
ምክር፣ መካሪ
ፍጹም ጥበብ ያለው ይሖዋ ብቻ ነው። መካሪ የማያስፈልገው እሱ ብቻ ነው። (ኢሳ 40:13፤ ሮም 11:34) ልጁ የአባቱን ምክር ስለተቀበለና ስለተከተለ እንዲሁም የአምላክ መንፈስ ስላለው “ድንቅ መካሪ” በመሆን መመሪያ መስጠት ይችላል። (ኢሳ 9:6፤ 11:2፤ ዮሐ 5:19, 30) ይህም አንድ ምክር ጠቃሚ እንዲሆን ከተፈለገ ይሖዋን ከግምት ማስገባት እንዳለበት ጎላ አድርጎ ያሳያል። ልዑሉን አምላክ የሚጻረር ማንኛውም ምክር እርባና ቢስ ነው። ምክር ተብሎ ሊጠራም አይችልም።—ምሳሌ 19:21፤ 21:30
ከሰኔ 30–ሐምሌ 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት ምሳሌ 20
በተሳካ ሁኔታ ለመጠናናት የሚረዱ ቁልፎች
በተሳካ ሁኔታ መጠናናት የሚቻለው እንዴት ነው?
3 መጠናናት አስደሳች ሊሆን ቢችልም በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው እርምጃ ነው፤ ምክንያቱም ወደ ትዳር ሊመራ ይችላል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት በሠርጋቸው ቀን፣ በሕይወት እስካሉ ድረስ እርስ በርስ ለመዋደድና ለመከባበር በይሖዋ ፊት ቃል ኪዳን ይገባሉ። ማንኛውንም ቃል ኪዳን ከመግባታችን በፊት ስለ ጉዳዩ በጥንቃቄ ልናስብበት ይገባል። (ምሳሌ 20:25ን አንብብ።) ከጋብቻ ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አንድ ወንድና አንዲት ሴት መጠናናታቸው በደንብ ለመተዋወቅና ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ ይረዳቸዋል። አንዳንዶቹ ለመጋባት ይወስኑ ይሆናል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ለመለያየት ይወስናሉ። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ለመለያየት ቢወስኑ መጠናናቱ አልተሳካም ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጠናናቱ ዓላማውን አከናውኗል፤ ጥሩ ውሳኔ ላይ እንዲደርሱ ረድቷቸዋል።
4 ከመጠናናት ጋር በተያያዘ ትክክለኛውን አመለካከት መያዝ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ያላገቡ ሰዎች ትክክለኛው አመለካከት ካላቸው ለማግባት ከማያስቡት ሰው ጋር መጠናናት አይጀምሩም። ይሁንና ትክክለኛው አመለካከት ሊኖራቸው የሚገባው ያላገቡ ክርስቲያኖች ብቻ አይደሉም። ሁላችንም ከመጠናናት ጋር በተያያዘ ትክክለኛው አመለካከት ሊኖረን ይገባል። ለምሳሌ አንዳንዶች፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት እየተጠናኑ ከሆነ የግድ መጋባት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። ይህ አመለካከት ባላገቡ ክርስቲያኖች ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል? በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ሜሊሳ የተባለች ያላገባች እህት እንዲህ ብላለች፦ “እየተጠናኑ ያሉ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ጫና ይደርስባቸዋል። በዚህም የተነሳ እየተጠናኑ ያሉ አንዳንድ ጥንዶች እንደማይጣጣሙ ቢገባቸውም ግንኙነታቸውን ከማቋረጥ ወደኋላ ይላሉ። ሌሎች ያላገቡ ክርስቲያኖች ደግሞ ከናካቴው ከመጠናናት ወደኋላ ይላሉ። ምክንያቱም ጫናው በጣም ከባድ ነው።”
የትዳር ጓደኛ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
8 ለትዳር የምታስባትን እህት ከርቀት መመልከት የምትችለው እንዴት ነው? በጉባኤ ስብሰባዎች ወይም በማኅበራዊ ግብዣዎች ላይ ስለ መንፈሳዊነቷ፣ ስለ ባሕርይዋ እና ስለ ምግባሯ የሚጠቁሙ ነገሮችን ትመለከት ይሆናል። ጓደኞቿ እነማን ናቸው? ስለ ምን ጉዳይ ማውራት ትወዳለች? (ሉቃስ 6:45) ግባችሁ ተመሳሳይ ነው? የጉባኤ ሽማግሌዎቿን ወይም እሷን በደንብ የሚያውቁ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ማነጋገር ትችል ይሆናል። (ምሳሌ 20:18) ስላተረፈችው ስምና ስለ ባሕርያቷ መጠየቅ ትችላለህ። (ሩት 2:11) ሆኖም እህትን በምትመለከትበት ጊዜ ምቾቷን የሚነሳ ነገር አታድርግ። ለስሜቷ አክብሮት ይኑርህ፤ እንዲሁም እሷ ባለችበት ሁሉ ለመገኘት ወይም ስለ እሷ ሁሉንም ነገር ለማወቅ ጥረት አታድርግ።
በተሳካ ሁኔታ መጠናናት የሚቻለው እንዴት ነው?
7 የግለሰቡን ውስጣዊ ማንነት ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? እንዲህ ማድረግ ከሚቻልባቸው ግሩም መንገዶች አንዱ በግልጽና በሐቀኝነት መነጋገር፣ ጥያቄዎችን መጠየቅ እንዲሁም በጥሞና ማዳመጥ ነው። (ምሳሌ 20:5፤ ያዕ. 1:19) ለዚህም ሲባል ለማውራት በሚያመቹ እንቅስቃሴዎች መካፈላችሁ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አብራችሁ መብላት፣ ሰዋራ ባልሆኑ ቦታዎች ላይ በእግር መንሸራሸር ወይም አብራችሁ ማገልገል ትችላላችሁ። ከጓደኞቻችሁና ከቤተሰቦቻችሁ ጋር አብራችሁ ጊዜ ማሳለፋችሁም እርስ በርስ ለመተዋወቅ ሊረዳችሁ ይችላል። ከዚህም ሌላ፣ ግለሰቡ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲሁም ከተለያዩ ሰዎች ጋር ሲሆን ምን ዓይነት ምግባር እንደሚያሳይ ለማወቅ በሚያስችሏችሁ እንቅስቃሴዎች ተካፈሉ። በኔዘርላንድስ የሚኖረው አሽዊን ምን እንዳደረገ እንመልከት። ከአሊሻ ጋር ይጠናኑ በነበረበት ወቅት ምን ያደርጉ እንደነበር ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ይበልጥ ለመተዋወቅ በሚረዱን እንቅስቃሴዎች ለመካፈል እንሞክር ነበር። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ማድረግ ከፍተኛ ጥረት አይጠይቅም። አብረን ምግብ እናበስላለን ወይም ሌሎች ሥራዎችን እንሠራለን። እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች ስንካፈል አንዳችን የሌላውን ጠንካራና ደካማ ጎን ማየት ችለናል።”
8 ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች አብራችሁ በማጥናትም ይበልጥ መተዋወቅ ትችላላችሁ። ከተጋባችሁ፣ አምላክ የትዳራችሁ ዋነኛ ክፍል እንዲሆን ለቤተሰብ አምልኮ ጊዜ መመደብ ይጠበቅባችኋል። (መክ. 4:12) ታዲያ ከአሁኑ ማለትም እየተጠናናችሁ ባላችሁበት ወቅት አብራችሁ ለማጥናት ለምን ጊዜ አትመድቡም? እርግጥ ነው፣ እየተጠናኑ ያሉ ጥንዶች ገና ቤተሰብ አልሆኑም፤ ወንድምም ቢሆን ገና የእህት ራስ አልሆነም። ያም ቢሆን አዘውትራችሁ አብራችሁ ማጥናታችሁ አንዳችሁ ስለ ሌላው መንፈሳዊነት ለማወቅ ይረዳችኋል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ማክስ እና ላይሳ እንዲህ ማድረጋቸው ሌላ ጥቅምም እንዳለው ተገንዝበዋል። ማክስ እንዲህ ብሏል፦ “መጠናናት እንደጀመርን አካባቢ ስለ ፍቅር ግንኙነት፣ ስለ ትዳርና ስለ ቤተሰብ ሕይወት የሚገልጹ ጽሑፎችን እናጠና ነበር። እነዚህ ጽሑፎች በራሳችን ቢሆን ኖሮ ላናነሳቸው በምንችላቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ እንድንወያይ መንገድ ከፍተውልናል።”
መንፈሳዊ ዕንቁዎች
it-2 196 አን. 7
መብራት
ምሳሌ 20:27 “የሰው እስትንፋስ የይሖዋ መብራት ነው፤ ውስጣዊ ማንነቱን በሚገባ ይመረምራል” ይላል። የአንድ ሰው “እስትንፋስ” ማለትም ከአፉ የሚወጣው ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ውስጣዊ ማንነቱን ይገልጣል ወይም መብራት ያበራበታል።—ከሥራ 9:1 ጋር አወዳድር።