የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ቃየን ተናዶ ወንድሙን ገደለው
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • አቤል ለይሖዋ መባውን ሲያቀርብ ቃየን ተናደደ

      ትምህርት 4

      ቃየን ተናዶ ወንድሙን ገደለው

      አዳምና ሔዋን ከኤደን የአትክልት ስፍራ ከወጡ በኋላ ብዙ ልጆችን ወለዱ። የመጀመሪያ ልጃቸው ቃየን ገበሬ ሆነ፤ ሁለተኛ ልጃቸው አቤል ደግሞ እረኛ ሆነ።

      አንድ ቀን፣ ቃየንና አቤል ለይሖዋ መባ አቀረቡ። መባ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? መባ ለአምላክ የሚሰጥ ስጦታ ነው። ይሖዋ አቤል ባቀረበው መባ የተደሰተ ቢሆንም ቃየን ባቀረበው መባ ግን አልተደሰተም። ይህም ቃየንን በጣም አናደደው። ይሖዋ ቃየንን ንዴቱ መጥፎ ነገር እንዲፈጽም ሊያደርገው እንደሚችል አስጠነቀቀው። ቃየን ግን ይሖዋ ያለውን አልሰማም።

      ቃየን አቤልን “ና ወደ ሜዳ እንሂድ” አለው። ሜዳ ላይ ብቻቸውን ሳሉ ቃየን ወንድሙን መታውና ገደለው። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ምን አደረገ? ይሖዋ ቃየንን ከቤተሰቡ ተለይቶ ወደ ሩቅ ቦታ እንዲሄድ በማድረግ ቀጣው። ቃየን ተመልሶ እንዳይመጣ ተከልክሎ ነበር።

      ቃየንና አቤል ሜዳው ላይ ሲገናኙ

      ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን? አንዳንድ ነገሮች እኛ እንደፈለግነው ሳይሆኑ ሲቀሩ ልንናደድ እንችላለን። ሰዎች መናደዳችንን ተመልክተው ምክር ሊሰጡን ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ እንደተናደድን እኛ ራሳችን ሊታወቀን ይችላል። በዚህ ጊዜ መጥፎ ነገር ከማድረጋችን በፊት ቶሎ ንዴታችንን ለማብረድ ጥረት ማድረግ አለብን።

      አቤል ይሖዋን ይወድና ትክክል የሆነውን ነገር ያደርግ ስለነበር ይሖዋ ሁልጊዜም ያስታውሰዋል። አምላክ ምድርን ገነት ሲያደርግ አቤልን ከሞት ያስነሳዋል።

      “በመጀመሪያ ከወንድምህ ጋር ታረቅ፤ ከዚያም ተመልሰህ መባህን አቅርብ።”—ማቴዎስ 5:24

      ጥያቄ፦ አዳምና ሔዋን መጀመሪያ ላይ የወለዷቸው ሁለት ልጆች እነማን ነበሩ? ቃየን ወንድሙን የገደለው ለምንድን ነው?

      ዘፍጥረት 4:1-12፤ ዕብራውያን 11:4፤ 1 ዮሐንስ 3:11, 12

  • የኖኅ መርከብ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ኖኅና ቤተሰቡ መርከቡን ሲሠሩ

      ትምህርት 5

      የኖኅ መርከብ

      ከጊዜ በኋላ በምድር ላይ የሚኖሩት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጣ። አብዛኞቹ ሰዎች ክፉዎች ነበሩ። በሰማይ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ መላእክትም እንኳ ክፉዎች ሆኑ። በሰማይ ያለውን መኖሪያቸውን ትተው ወደ ምድር ወረዱ። ለምን እንዲህ እንዳደረጉ ታውቃለህ? እንደ ሰው ሆነው ሴቶችን ማግባት ስለፈለጉ ነው።

      መላእክቱና ሴቶቹ ተጋብተው ልጆች ወለዱ። እነዚህ ልጆች ሲያድጉ በጣም ጠንካራና ጉልበተኛ ሆኑ። ሰዎችንም መጉዳት ጀመሩ። ይሖዋ ይህ ሁኔታ እንዲቀጥል አልፈለገም። ስለሆነም ክፉ ሰዎችን በውኃ ለማጥፋት ወሰነ።

      ኖኅና ቤተሰቡ መርከቡን ሲሠሩና ምግብ ሲያዘጋጁ

      ሆኖም ከእነዚህ ሰዎች የተለየ አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው ኖኅ ይባላል፤ እሱም ይሖዋን በጣም ይወድ ነበር። ኖኅ ሚስትና ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ የልጆቹ ስም ሴም፣ ካምና ያፌት ሲሆን ሁሉም ሚስት ነበራቸው። ይሖዋ ኖኅን፣ እሱና ቤተሰቡ ከጥፋት ውኃው መትረፍ እንዲችሉ ትልቅ መርከብ እንዲሠራ ነገረው። ኖኅ የሠራው መርከብ በውኃ ላይ መንሳፈፍ የሚችል ትልቅ ሣጥን ይመስል ነበር። ይሖዋ ኖኅን እንስሳትም መትረፍ እንዲችሉ ወደ መርከቡ እንዲያስገባቸው ነገረው።

      ኖኅ ወዲያውኑ መርከቡን መሥራት ጀመረ። ኖኅና ቤተሰቡ መርከቡን ሠርተው ለመጨረስ 50 ዓመት አካባቢ ፈጅቶባቸዋል። መርከቡን ልክ ይሖዋ እንዳዘዛቸው አድርገው ሠሩ። ኖኅ መርከቡን እየሠራ በነበረበት ጊዜ ሰዎች ከጥፋት ውኃው እንዲድኑ ያስጠነቅቅ ነበር። ግን ማንም አልሰማውም።

      በመጨረሻም ወደ መርከቡ የሚገቡበት ጊዜ ደረሰ። እስቲ ቀጥሎ ምን እንደሆነ እንመልከት።

      “በኖኅ ዘመን እንደነበረው ሁሉ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል።”—ማቴዎስ 24:37

      ጥያቄ፦ ይሖዋ የጥፋት ውኃ ለማምጣት የወሰነው ለምንድን ነው? ይሖዋ ለኖኅ ምን መመሪያ ሰጠው?

      ዘፍጥረት 6:1-22፤ ማቴዎስ 24:37-41፤ 2 ጴጥሮስ 2:5፤ ይሁዳ 6

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ