-
አብርሃምና ሣራ አምላክን ታዘዋልከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 8
አብርሃምና ሣራ አምላክን ታዘዋል
በባቤል አቅራቢያ የምትገኝ ዑር የምትባል አንዲት ከተማ ነበረች፤ በከተማዋ የሚኖሩ ሰዎች ይሖዋን ሳይሆን ሌሎች አማልክትን ያመልኩ ነበር። ሆኖም በዚህች ከተማ የሚኖር ይሖዋን ብቻ የሚያመልክ አንድ ሰው ነበር። ይህ ሰው አብርሃም ይባላል።
ይሖዋ አብርሃምን ‘ቤትህንና ዘመዶችህን ትተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ’ አለው። ከዚያም አምላክ እንዲህ ብሎ ቃል ገባለት፦ ‘ብዙ ሕዝብ ትሆናለህ፤ እንዲሁም በአንተ አማካኝነት ለምድር ሕዝቦች ሁሉ ጥሩ ነገር አደርግላቸዋለሁ።’
አብርሃም፣ ይሖዋ ወዴት እንደሚልከው ባያውቅም በይሖዋ ታምኗል። ስለዚህ አብርሃም፣ ሚስቱ ሣራ፣ አባቱ ታራ እንዲሁም የወንድሙ ልጅ ሎጥ ዕቃቸውን ይዘው በታዛዥነት ረጅሙን ጉዞ ጀመሩ።
አብርሃምና ቤተሰቡ ይሖዋ ሊያሳያቸው ወደፈለገው ቦታ ሲደርሱ አብርሃም 75 ዓመቱ ነበር። ያ ቦታ የከነአን ምድር ይባል ነበር። እዚያ ከደረሱ በኋላ አምላክ አብርሃምን አነጋገረው፤ ‘ይህን የምታየውን ቦታ ሁሉ ለልጆችህ እሰጣቸዋለሁ’ ብሎ ቃል ገባለት። አብርሃምና ሣራ ግን አርጅተው የነበረ ሲሆን ምንም ልጅ አልነበራቸውም። ታዲያ ይሖዋ የገባውን ቃል የሚፈጽመው እንዴት ነው?
“አብርሃም . . . ወደፊት ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ በመሄድ በእምነት ታዘዘ፤ ወዴት እንደሚሄድ ባያውቅም ይኖርበት የነበረውን ስፍራ ለቆ ወጣ።”—ዕብራውያን 11:8
-
-
በመጨረሻ ልጅ ወለዱ!ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 9
በመጨረሻ ልጅ ወለዱ!
አብርሃምና ሣራ ተጋብተው ለረጅም ጊዜ ኖረዋል። በዑር የነበራቸውን ምቹ ቤት ትተው በድንኳን እየኖሩ ነበር። ሆኖም ሣራ በይሖዋ ትታመን ስለነበር አላጉረመረመችም።
ሣራ ልጅ ማግኘት በጣም ትፈልግ ስለነበር አብርሃምን ‘አገልጋዬ አጋር ልጅ ብትወልድ ልጁ እንደ ራሴ ልጅ ይሆናል’ አለችው። ከጊዜ በኋላ አጋር ወንድ ልጅ ወለደች። የልጁ ስም እስማኤል ይባላል።
ከብዙ ዓመታት በኋላ ማለትም አብርሃም 99 ዓመት፣ ሣራ ደግሞ 89 ዓመት ሲሆናቸው ሦስት እንግዶች ወደ እነአብርሃም ቤት መጡ። አብርሃም እንግዶቹን ዛፍ ሥር እንዲያርፉና ምግብ እንዲበሉ ጠየቃቸው። እነዚህ እንግዶች እነማን እንደሆኑ ታውቃለህ? መላእክት ነበሩ! እነሱም አብርሃምን ‘በሚቀጥለው ዓመት በዚህ ጊዜ ሚስትህ ወንድ ልጅ ትወልዳለች’ አሉት። ሣራ ድንኳኑ ውስጥ ሆና የሚሉትን ትሰማ ነበር። ይህን ስትሰማ ‘አሁን እንዲህ ካረጀሁ በኋላ ልጅ መውለድ እችላለሁ?’ ብላ በማሰብ ሳቀች።
በቀጣዩ ዓመት ልክ የይሖዋ መልአክ እንደተናገረው ሣራ ወንድ ልጅ ወለደች። አብርሃም ልጁን ይስሐቅ ብሎ ስም አወጣለት፤ ይስሐቅ ማለት “ሳቅ” ማለት ነው።
ይስሐቅ አምስት ዓመት አካባቢ ሲሆነው ሣራ፣ እስማኤል በይስሐቅ ላይ ሲያሾፍበት አየች። ልጇን ለመጠበቅ ስትል አጋርንና እስማኤልን እንዲያባርራቸው አብርሃምን ጠየቀችው። አብርሃም መጀመሪያ ላይ እንደዚህ ማድረግ አልፈለገም ነበር። ሆኖም ይሖዋ ለይስሐቅ ጥበቃ ማድረግ ስለፈለገ አብርሃምን እንዲህ አለው፦ ‘ሣራ የምትልህን ስማ። እስማኤልን እኔ እንከባከበዋለሁ። የገባሁልህ ቃል የሚፈጸመው ግን በይስሐቅ በኩል ነው።’
“ሣራም የተስፋን ቃል የሰጠው እሱ ታማኝ እንደሆነ አድርጋ ስላሰበች . . . ዘር ለመፀነስ በእምነት ኃይል አገኘች።”—ዕብራውያን 11:11
-