የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የሎጥን ሚስት አስታውሱ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ሎጥና ሴት ልጆቹ ከሰዶም ሲያመልጡ የሎጥ ሚስት የጨው ዓምድ ሆና ቀረች

      ትምህርት 10

      የሎጥን ሚስት አስታውሱ

      ሎጥ፣ ከአጎቱ ከአብርሃም ጋር በከነአን ምድር ይኖር ነበር። አብርሃምና ሎጥ የነበሯቸው እንስሳት በጣም እየበዙ ስለሄዱ መሬቱ ለእነዚያ ሁሉ እንስሳት ሊበቃቸው አልቻለም። ስለዚህ አብርሃም ሎጥን እንዲህ አለው፦ ‘ከዚህ በኋላ አንድ ቦታ ላይ አብረን መኖር አንችልም። እባክህ አንተ መሄድ የምትፈልግበትን ቦታ ምረጥ፤ ከዚያም እኔ ወደ ሌላ ቦታ እሄዳለሁ።’ አብርሃም እንዲህ ብሎ መናገሩ ራስ ወዳድ ሰው እንዳልነበረ ያሳያል።

      ሎጥ ሰዶም በምትባል ከተማ አቅራቢያ የሚያምር አካባቢ አየ። በአካባቢው ብዙ ውኃ እንዲሁም የለመለመ ሣር ነበር። ስለዚህ ሎጥ ያንን ቦታ መርጦ ከቤተሰቡ ጋር በዚያ መኖር ጀመረ።

      በሰዶምና በአቅራቢያዋ በምትገኘው በገሞራ ከተማ የሚኖሩት ሰዎች በጣም መጥፎ ነበሩ። እንዲያውም ሰዎቹ በጣም መጥፎ ከመሆናቸው የተነሳ ይሖዋ እነዚያን ከተሞች ለማጥፋት ወስኖ ነበር። ነገር ግን ይሖዋ ሎጥንና ቤተሰቡን ሊያድናቸው ስለፈለገ እንዲያስጠነቅቋቸው ሁለት መላእክት ላከ። መላእክቱም ‘ቶሎ በሉ! ከዚህች ከተማ ውጡ። ይሖዋ ከተማዋን ሊያጠፋት ነው’ አሏቸው።

      ሎጥ ግን ወዲያውኑ ከከተማዋ ከመውጣት ይልቅ እዚያው ቆየ። ስለዚህ መላእክቱ ሎጥን፣ ሚስቱንና ሁለቱን ልጆቹን እጃቸውን ይዘው በፍጥነት ከከተማዋ አስወጧቸው። እንዲህም አሏቸው፦ ‘ሩጡ! ሕይወታችሁን ለማትረፍ አምልጡ፤ ወደ ኋላ አትመልከቱ። ወደ ኋላ ከተመለከታችሁ ትሞታላችሁ!’

      በሰዶምና ገሞራ ላይ እሳትና ድኝ ዘነበ

      ሎጥና ቤተሰቡ ዞአር ወደተባለች ከተማ ሲደርሱ ይሖዋ በሰዶምና በገሞራ ላይ እሳትና ድኝ አዘነበባቸው። ሁለቱም ከተሞች ሙሉ በሙሉ ጠፉ። የሎጥ ሚስት ይሖዋን ሳትታዘዝ ወደ ኋላ በመመልከቷ የጨው ዓምድ ሆነች! ሎጥና ሴቶች ልጆቹ ግን ይሖዋን በመታዘዛቸው በሕይወት ተረፉ። የሎጥ ሚስት ይሖዋን ባለመታዘዟ ሎጥና ልጆቹ በጣም አዝነው መሆን አለበት። ይህ ታሪክ የይሖዋን መመሪያ መታዘዝ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያስተምረናል።

      “የሎጥን ሚስት አስታውሱ።”—ሉቃስ 17:32

      ጥያቄ፦ ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ያጠፋቸው ለምንድን ነው? የሎጥ ሚስት የጨው ዓምድ የሆነችው ለምንድን ነው?

      ዘፍጥረት 13:1-13፤ 19:1-26፤ ሉቃስ 17:28, 29, 32፤ 2 ጴጥሮስ 2:6-9

  • የአብርሃም እምነት ተፈተነ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • አብርሃምና ይስሐቅ ወደ ሞሪያ ሲጓዙ

      ትምህርት 11

      የአብርሃም እምነት ተፈተነ

      አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅ ይሖዋን እንዲወድና እሱ በገባው ቃል ላይ እምነት እንዲኖረው አስተምሮታል። ሆኖም ይስሐቅ 25 ዓመት አካባቢ ሲሆነው ይሖዋ አብርሃምን አንድ በጣም ከባድ ነገር እንዲያደርግ ጠየቀው። ይሖዋ ለአብርሃም ያቀረበው ጥያቄ ምን ነበር?

      አምላክ አብርሃምን ‘እባክህ አንድ ልጅህን ወስደህ በሞሪያ ምድር በሚገኝ ተራራ ላይ መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው’ አለው። አብርሃም፣ ይሖዋ እንዲህ እንዲያደርግ የጠየቀው ለምን እንደሆነ አላወቀም ነበር። ቢሆንም ይሖዋን ታዟል።

      በማግስቱ ጠዋት አብርሃም ይስሐቅንና ሁለት አገልጋዮቹን ይዞ ወደ ሞሪያ ሄደ። ለሦስት ቀን ከተጓዙ በኋላ ከርቀት ተራራው ታያቸው። አብርሃም፣ እሱና ይስሐቅ መሥዋዕት አቅርበው እስኪመለሱ ድረስ አገልጋዮቹ እዚያው እንዲቆዩ ነገራቸው። አብርሃም ለእሳት ማንደጃ የሚሆነውን እንጨት ይስሐቅ እንዲሸከም አደረገ፤ እሱ ደግሞ ቢላውን ያዘ። ይስሐቅ አባቱን ‘መሥዋዕት የምናደርገው በግ የት አለ?’ ብሎ ጠየቀው። አብርሃምም ‘ልጄ፣ በጉን ይሖዋ ያዘጋጃል’ ብሎ መለሰለት።

      በመጨረሻም ተራራው ጋ ሲደርሱ መሠዊያ ሠሩ። ከዚያም አብርሃም የይስሐቅን እጆችና እግሮች አስሮ መሠዊያው ላይ አስተኛው።

      ይስሐቅ ታስሮ መሠዊያው ላይ ተኝቷል፤ አብርሃም ደግሞ በእጁ ቢላ ይዟል

      አብርሃም ቢላውን አነሳ። በዚህ ጊዜ የይሖዋ መልአክ ከሰማይ እንዲህ አለው፦ ‘አብርሃም፣ ልጁን እንዳትነካው! ልጅህን እንኳ መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ስለሆንክ በአምላክ ላይ እምነት እንዳለህ አሁን አወቅኩ።’ ከዚያም አብርሃም አንድ አውራ በግ ቀንዶቹ በዛፍ ቅርንጫፎች ተይዘው አየ። ወዲያውኑ ይስሐቅን ፈታውና በጉን መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ።.

      ከዚያ ቀን አንስቶ ይሖዋ አብርሃምን ‘ወዳጄ’ በማለት ይጠራው ጀመር። ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? አብርሃም፣ ይሖዋ አንድ ነገር እንዲያደርግ ያዘዘው ለምን እንደሆነ ቢገባውም ባይገባውም ምንጊዜም ይታዘዝ ነበር።

      አብርሃም ይስሐቅን ሲፈታው

      ከዚያም ይሖዋ ለአብርሃም ‘እባርክሃለሁ፤ ዘርህን ወይም ልጆችህን አበዛልሃለሁ’ በማለት በድጋሚ ቃል ገባለት። በተጨማሪም ይሖዋ ጥሩ ሰዎችን በሙሉ በአብርሃም ቤተሰብ በኩል እንደሚባርክ ቃል ገባ።

      “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐንስ 3:16

      ጥያቄ፦ አብርሃም በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው? ይሖዋ ለአብርሃም ምን ቃል ገባለት?

      ዘፍጥረት 22:1-18፤ ዕብራውያን 11:17-19፤ ያዕቆብ 2:21-23

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ