የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ያዕቆብ ውርስ አገኘ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ያዕቆብ ለኤሳው ወጥ በመስጠት ብኩርናውን ወሰደ

      ትምህርት 12

      ያዕቆብ ውርስ አገኘ

      ይስሐቅና ርብቃ ከመንታ ልጆቻቸው ከያዕቆብና ከኤሳው ጋር

      ይስሐቅ ርብቃን ሲያገባ 40 ዓመቱ ነበር። ርብቃን በጣም ይወዳት ነበር። ከጊዜ በኋላ ሁለት መንታ ወንዶች ልጆች ወለዱ።

      ታላቁ ልጅ ስሙ ኤሳው ነበር፤ ታናሽየው ደግሞ ያዕቆብ ይባላል። ኤሳው ከቤት ውጭ መዋል የሚወድ ጎበዝ የእንስሳት አዳኝ ነበር። ያዕቆብ ግን ቤት ውስጥ መዋል ያስደስተው ነበር።

      በዚያ ዘመን አንድ አባት ሲሞት አብዛኛው መሬትና ገንዘብ የሚሰጠው ለታላቁ ልጅ ነበር። ይህ ውርስ ይባላል። በይስሐቅ ቤተሰብ ውስጥ ደግሞ ይህ ውርስ ይሖዋ ለአብርሃም የሰጣቸውን ተስፋዎችም ይጨምር ነበር። ኤሳው፣ ይሖዋ ለአብርሃም ስለሰጠው ተስፋ ብዙም ግድ አልነበረውም፤ ያዕቆብ ግን እነዚህን ተስፋዎች ከፍ አድርጎ ይመለከት ነበር።

      ያዕቆብና ኤሳው

      አንድ ቀን ኤሳው እንስሳትን ሲያድን ውሎ በጣም ደክሞት ወደ ቤት ተመለሰ። ያዕቆብ እየሠራው የነበረው ጣፋጭ ምግብ ሸተተውና ‘በጣም ርቦኛል! እስቲ ከቀዩ ወጥ ስጠኝ!’ አለው። ከዚያም ያዕቆብ ‘ምግቡን እሰጥሃለሁ፤ መጀመሪያ ግን ውርስህን እንደምትሰጠኝ ቃል ግባልኝ’ አለው። ኤሳውም መልሶ ‘አሁን እኔ የውርስ ነገር አያሳስበኝም! ከፈለግክ ውሰደው። ብቻ የሚበላ ነገር ስጠኝ’ አለው። ኤሳው እንዲህ ማድረጉ ትክክል ይመስልሃል? ትክክል አልነበረም። ኤሳው ለምግብ ሲል በጣም ውድ የሆነ ነገር አሳልፎ ሰጠ።

      ይስሐቅ እያረጀ ሲሄድ የበኩር ልጁን ለመባረክ አሰበ። ርብቃ ግን በረከቱን ታናሽየው ልጅ ያዕቆብ እንዲያገኝ አደረገች። ኤሳው ይህን ሲያውቅ በጣም ተናደደና ወንድሙን ለመግደል አሰበ። ይስሐቅና ርብቃ፣ ያዕቆብን ወንድሙ እንዳይገድለው ስለፈሩ ‘የኤሳው ቁጣ እስኪበርድ ድረስ ወደ አጎትህ ወደ ላባ ሄደህ እዚያ ቆይ’ አሉት። ያዕቆብ የወላጆቹን ምክር ሰምቶ ሕይወቱን ለማዳን ሸሸ።

      “አንድ ሰው ዓለሙን ሁሉ የራሱ ቢያደርግና ሕይወቱን ቢያጣ ምን ይጠቅመዋል? ሰው ለሕይወቱ ምትክ የሚሆን ምን ነገር ሊሰጥ ይችላል?”—ማርቆስ 8:36, 37

      ጥያቄ፦ ኤሳው ምን ዓይነት ሰው ነበር? ያዕቆብስ ምን ዓይነት ሰው ነበር? የበኩር ልጅ የነበረው ኤሳው ቢሆንም ያዕቆብ በረከቱን ሊያገኝ የቻለው እንዴት ነው?

      ዘፍጥረት 25:20-34፤ 27:1–28:5፤ ዕብራውያን 12:16, 17

  • ያዕቆብና ኤሳው ታረቁ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ያዕቆብ ዝቅ ብሎ እየሰገደ ሲሆን ኤሳው ደግሞ ወደ ያዕቆብ እየሮጠ ነው

      ትምህርት 13

      ያዕቆብና ኤሳው ታረቁ

      ይሖዋ አብርሃምንና ይስሐቅን እንደጠበቃቸው ሁሉ ያዕቆብንም እንደሚጠብቀው ቃል ገባለት። ያዕቆብ ካራን በሚባል ቦታ መኖር ጀመረ፤ በዚያም አግብቶ ትልቅ ቤተሰብ መሠረተ፤ እንዲሁም በጣም ሀብታም ሆነ።

      ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ያዕቆብን ‘ወደ አገርህ ተመልሰህ ሂድ’ አለው። ስለዚህ ያዕቆብ ቤተሰቡን ይዞ ወደተወለደበት አገር መጓዝ ጀመረ። መንገድ ላይ ሳሉ የያዕቆብ አገልጋዮች ወደ እሱ መጥተው ‘ወንድምህ ኤሳው እየመጣ ነው፤ 400 ሰዎችም አብረውት አሉ!’ አሉት። ያዕቆብ፣ ኤሳው በእሱና በቤተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ፈራ። በመሆኑም ‘እባክህ ከወንድሜ እጅ አድነኝ’ በማለት ወደ ይሖዋ ጸለየ። በቀጣዩ ቀን ያዕቆብ ለኤሳው ብዙ በጎችን፣ ፍየሎችን፣ ላሞችን፣ ግመሎችንና አህዮችን ስጦታ አድርጎ ላከለት።

      በዚያ ሌሊት ያዕቆብ ብቻውን እያለ አንድ መልአክ አየ! መልአኩ ከያዕቆብ ጋር መታገል ጀመረ። እስኪነጋ ድረስ ሲታገሉ ቆዩ። ያዕቆብ ጉዳት ቢደርስበትም መታገሉን አላቆመም። በዚህ ጊዜ መልአኩ ‘ልቀቀኝና ልሂድ’ አለው። ያዕቆብ ግን ‘ካልባረክኸኝ አልለቅህም’ አለው።

      በመጨረሻም መልአኩ ያዕቆብን ባረከው። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ይሖዋ እንደሚረዳውና ኤሳው እሱን እንዲጎዳው እንደማይፈቅድ ተገነዘበ።

      ያን ቀን ጠዋት ያዕቆብ ከርቀት ሲመለከት ኤሳውንና ከእሱ ጋር የነበሩትን 400 ሰዎች አያቸው። ያዕቆብ ከቤተሰቦቹ ቀድሞ በመሄድ በወንድሙ ፊት ሰባት ጊዜ ሰገደ። ኤሳውም ወደ ያዕቆብ እየሮጠ መጥቶ አቀፈው። ሁለቱ ወንድማማቾች ተላቀሱ፤ በዚህ መንገድ ኤሳውና ያዕቆብ ታረቁ። ይሖዋ፣ ያዕቆብ ያደረገውን ሲመለከት ምን የተሰማው ይመስልሃል?

      ከዚህ በኋላ ኤሳው ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ያዕቆብ ደግሞ መንገዱን ቀጠለ። ያዕቆብ 12 ወንዶች ልጆች ነበሩት። ስማቸው ሮቤል፣ ስምዖን፣ ሌዊ፣ ይሁዳ፣ ዳን፣ ንፍታሌም፣ ጋድ፣ አሴር፣ ይሳኮር፣ ዛብሎን፣ ዮሴፍ እና ቢንያም ይባላል። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ዮሴፍን በመጠቀም ሕዝቡን አድኗል። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ? እስቲ እንመልከት።

      “ጠላቶቻችሁን ውደዱ እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ ጸልዩ፤ ይህን ብታደርጉ በሰማያት ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ።”—ማቴዎስ 5:44, 45

      ጥያቄ፦ ያዕቆብ በረከት ያገኘው እንዴት ነው? ከወንድሙ ጋር የታረቀው እንዴት ነው?

      ዘፍጥረት 28:13-15፤ 31:3, 17, 18፤ 32:1-29፤ 33:1-18፤ 35:23-26

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ