የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • አምላክን የታዘዘ ባሪያ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ዮሴፍ ከጶጢፋር ሚስት ሲሸሽ

      ትምህርት 14

      አምላክን የታዘዘ ባሪያ

      ዮሴፍ፣ ያዕቆብ መጨረሻ ላይ ከወለዳቸው ልጆች መካከል አንዱ ነበር። ታላላቅ ወንድሞቹ አባታቸው ዮሴፍን ከእነሱ አስበልጦ እንደሚወደው አዩ። ይህን ሲያውቁ ምን የተሰማቸው ይመስልሃል? በዮሴፍ ላይ ቅናት ስላደረባቸው ጠሉት። ዮሴፍ ሕልም አይቶ ለወንድሞቹ ነገራቸው። በሕልሙ ያየው ነገር ወንድሞቹ አንድ ቀን ለእሱ እንደሚሰግዱ የሚያመለክት ነበር። ይህ ደግሞ የባሰ እንዲጠሉት አደረጋቸው!

      ዮሴፍን ወንድሞቹ ጉድጓድ ውስጥ ሲጥሉት

      አንድ ቀን የዮሴፍ ወንድሞች በሴኬም ከተማ አቅራቢያ በጎች እየጠበቁ ነበር። ያዕቆብ ‘ወንድሞችህ ደህና መሆናቸውን አይተህ ና’ ብሎ ዮሴፍን ላከው። ወንድሞቹ ዮሴፍ ሲመጣ ከሩቅ አዩትና እርስ በርሳቸው ‘ያ ሕልም አላሚ መጣ። ኑ እንግደለው!’ ተባባሉ። ከዚያም ያዙትና ወደ አንድ ጥልቅ ጉድጓድ ወረወሩት። ከወንድሞቹ አንዱ የሆነው ይሁዳ ግን ‘አትግደሉት! ባሪያ አድርገን ብንሸጠው ይሻላል’ አለ። ስለዚህ ዮሴፍን ወደ ግብፅ ለሚሄዱ ምድያማውያን ነጋዴዎች በ20 የብር ሰቅል ሸጡት።

      ከዚያም የዮሴፍ ወንድሞች የዮሴፍን ልብስ የፍየል ደም ውስጥ ነከሩትና ወደ አባታቸው በመላክ ‘ይህ የልጅህ ልብስ አይደለም?’ አሉት። ስለዚህ ያዕቆብ ዮሴፍን አውሬ የበላው መሰለው። በዚህ የተነሳ በጣም አዘነ። ማንም ሊያጽናናው አልቻለም።

      ዮሴፍ እስር ቤት ውስጥ

      ዮሴፍ በግብፅ ለሚኖር ጶጢፋር የተባለ ባለሥልጣን ባሪያ ሆኖ ተሸጠ። ሆኖም ይሖዋ ዮሴፍን ይረዳው ነበር። ጶጢፋር፣ ዮሴፍ ጎበዝ ሠራተኛና እምነት የሚጣልበት ሰው እንደሆነ አየ። ስለዚህ ዮሴፍ የጶጢፋርን ንብረት ሁሉ እንዲቆጣጠር ተሾመ።

      የጶጢፋር ሚስት ዮሴፍ ቆንጆና ጥሩ ቁመና ያለው እንደሆነ አየች። በየቀኑ ዮሴፍን አብሯት እንዲተኛ ትጠይቀው ነበር። ዮሴፍ ምን ያደርግ ይሆን? እንዲህ አላት፦ ‘አይሆንም! ይህ ተገቢ አይደለም። ጌታዬ እኔን ያምነኛል፤ አንቺ ደግሞ ሚስቱ ነሽ። ከአንቺ ጋር ከተኛሁ በአምላክ ፊት ኃጢአት እሠራለሁ!’

      አንድ ቀን የጶጢፋር ሚስት ዮሴፍን አብሯት እንዲተኛ ለማስገደድ ሞከረች። ልብሱን ጭምድድ አድርጋ ያዘችው፤ እሱ ግን ሸሽቶ አመለጠ። ጶጢፋር ወደ ቤት ሲመለስ ዮሴፍ ከእሱ ጋር እንድትተኛ ሊያስገድዳት እንደሞከረ ነገረችው። ሆኖም ይህ ውሸት ነበር። ጶጢፋር በጣም ተናደደ፤ ስለዚህ ዮሴፍን እስር ቤት አስገባው። ሆኖም ይሖዋ ዮሴፍን አልረሳውም።

      “ስለዚህ በተገቢው ጊዜ ከፍ እንዲያደርጋችሁ ከኃይለኛው የአምላክ እጅ በታች ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ።”—1 ጴጥሮስ 5:6

      ጥያቄ፦ የዮሴፍ ወንድሞች ምን አደረጉበት? ዮሴፍ እስር ቤት የገባው ለምንድን ነው?

      ዘፍጥረት 37:1-36፤ 39:1-23፤ የሐዋርያት ሥራ 7:9

  • ይሖዋ ዮሴፍን አልረሳውም
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ዮሴፍ ለፈርዖን የሕልሞቹን ትርጉም ሲነግረው

      ትምህርት 15

      ይሖዋ ዮሴፍን አልረሳውም

      ዮሴፍ እስር ቤት ውስጥ በነበረበት ወቅት የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ሕልም አለመ፤ የሕልሙን ትርጉም ማንም ሊነግረው አልቻለም። ከፈርዖን አገልጋዮች አንዱ፣ ዮሴፍ ሕልሙን ሊፈታለት እንደሚችል ለፈርዖን ነገረው። ፈርዖንም ወዲያውኑ ዮሴፍን አስጠራው።

      ፈርዖን ዮሴፍን ‘ሕልሜን ልትፈታልኝ ትችላለህ?’ ብሎ ጠየቀው። ዮሴፍም እንዲህ አለው፦ ‘ለሰባት ዓመት ያህል በግብፅ ብዙ ምግብ ይኖራል፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ለሰባት ዓመት ረሃብ ይሆናል። በእነዚህ ዓመታት ሕዝቡ እንዳይራብ ጥበበኛ የሆነ ሰው ምረጥና ምግብ እንዲያከማች አድርግ።’ ፈርዖንም ‘አንተን መርጬሃለሁ! በግብፅ ውስጥ ከእኔ ቀጥሎ ከፍተኛው ባለሥልጣን አንተ ትሆናለህ!’ አለው። ዮሴፍ የፈርዖን ሕልም ምን ትርጉም እንዳለው ያወቀው እንዴት ነው? ይሖዋ ስለረዳው ነው።

      ዮሴፍ ሰዎቹ ምግብ እንዲያከማቹ ትእዛዝ ሲሰጥ

      በቀጣዮቹ ሰባት ዓመታት ዮሴፍ ምግብ አከማቸ። ከዚያም ልክ ዮሴፍ እንደተናገረው በመላው ምድር ረሃብ ሆነ። በሁሉም ቦታ ያሉ ሰዎች ከዮሴፍ ምግብ ለመግዛት ወደ ግብፅ ይመጡ ነበር። የዮሴፍ አባት የሆነው ያዕቆብ በግብፅ ምግብ እንዳለ ስለሰማ አሥሩን ልጆቹን ወደ ግብፅ ሄደው ምግብ እንዲገዙ ላካቸው።

      የያዕቆብ ልጆች ወደ ዮሴፍ ሄዱ፤ ዮሴፍም ወዲያውኑ አወቃቸው። እነሱ ግን ዮሴፍ መሆኑን አላወቁም ነበር። ዮሴፍ በልጅነቱ በሕልሙ አይቶ እንደነበረው ወንድሞቹ ሰገዱለት። ዮሴፍ ወንድሞቹ ባሕርያቸው ተሻሽሎ መሆን አለመሆኑን ማወቅ ፈልጎ ነበር። ስለዚህ እንዲህ አላቸው፦ ‘ሰላዮች ናችሁ። እዚህ የመጣችሁት አገራችንን እንዴት ማጥቃት እንደምትችሉ ለመሰለል ነው።’ እነሱም እንዲህ አሉት፦ ‘እኛ ሰላዮች አይደለንም! በከነአን የምንኖር 12 ወንድማማቾች ነበርን። አንዱ ወንድማችን ሞቷል፤ ትንሹ ወንድማችን ደግሞ ከአባታችን ጋር ነው።’ በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ‘ታናሽ ወንድማችሁን ይዛችሁ ኑ፤ ያኔ አምናችኋለሁ’ አላቸው። ስለዚህ ወደ አባታቸው ተመልሰው ሄዱ።

      ቤተሰቡ ምግብ ሲያልቅበት ያዕቆብ ልጆቹን እንደገና ወደ ግብፅ ላካቸው። በዚህ ጊዜ ታናሽ ወንድማቸውን ቢንያምን ይዘውት ሄዱ። ዮሴፍ ወንድሞቹን ለመፈተን ሲል የብር ጽዋውን የቢንያም የእህል ከረጢት ውስጥ ደበቀው፤ ከዚያም ወንድሞቹ ጽዋውን እንደሰረቁ አድርጎ ተናገረ። የዮሴፍ አገልጋዮች ጽዋውን የቢንያም ከረጢት ውስጥ ሲያገኙት ወንድሞቹ በጣም ደነገጡ። ከዚያም በቢንያም ፋንታ እነሱን እንዲቀጣቸው ዮሴፍን ለመኑት።

      በዚህ ጊዜ ዮሴፍ ወንድሞቹ እንደተለወጡ አወቀ። ዮሴፍ ስሜቱን መቆጣጠር ስላልቻለ ማልቀስ ጀመረ። ‘እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ። አባቴ አሁንም በሕይወት አለ?’ አላቸው። ወንድሞቹ ዮሴፍ መሆኑን ሲያውቁ በጣም ደነገጡ። እሱም እንዲህ አላቸው፦ ‘በእኔ ላይ ባደረጋችሁት ነገር አትዘኑ። አምላክ ወደዚህ የላከኝ የእናንተን ሕይወት ለማትረፍ ብሎ ነው። አሁን ቶሎ ሂዱና አባቴን ይዛችሁት ኑ።’

      የዮሴፍ ወንድሞች ለአባታቸው ዮሴፍን እንዳገኙት ለመንገርና ይዘውት ወደ ግብፅ ለመምጣት ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ከብዙ ዓመታት በኋላ ዮሴፍና አባቱ እንደገና ተገናኙ።

      ዮሴፍና አባቱ ያዕቆብ ሰላም ሲባባሉ

      “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።”—ማቴዎስ 6:15

      ጥያቄ፦ ይሖዋ ዮሴፍን የረዳው እንዴት ነው? ዮሴፍ ወንድሞቹን ይቅር እንዳላቸው ያሳየው እንዴት ነው?

      ዘፍጥረት 40:1–45:28፤ 46:1-7, 26-34፤ መዝሙር 105:17-19፤ የሐዋርያት ሥራ 7:9-15

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ