የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በእሳት የተያያዘው ቁጥቋጦ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ሙሴ በእሳት በተያያዘው ቁጥቋጦ አጠገብ ሆኖ

      ትምህርት 18

      በእሳት የተያያዘው ቁጥቋጦ

      ሙሴ በምድያም ምድር 40 ዓመት ኖረ። በዚያም ሚስት አግብቶ ልጆች ወለደ። አንድ ቀን በሲና ተራራ አጠገብ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ የሚገርም ነገር አየ። አንድ ቁጥቋጦ በእሳት ተያይዞ የነበረ ቢሆንም ቁጥቋጦው አልተቃጠለም! ሙሴ ቁጥቋጦው ለምን እንዳልተቃጠለ ለማየት ሲጠጋ ከቁጥቋጦው ውስጥ እንዲህ የሚል ድምፅ ሰማ፦ ‘ሙሴ! ወደዚህ አትጠጋ። የቆምክበት መሬት ቅዱስ ስለሆነ ጫማህን አውልቅ።’ ሙሴን በአንድ መልአክ አማካኝነት ያነጋገረው ይሖዋ ነበር።

      በዚህ ጊዜ ሙሴ ስለፈራ ፊቱን ሸፈነ። ከቁጥቋጦው ውስጥ የተሰማው ድምፅ እንዲህ አለው፦ ‘እስራኤላውያን እየደረሰባቸው ያለውን ሥቃይ አይቻለሁ። ከግብፃውያን ነፃ አውጥቼ ወደ መልካም ምድር አመጣቸዋለሁ። ሕዝቤን እየመራህ ከግብፅ የምታወጣው አንተ ነህ።’ ሙሴ ይህን ሲሰማ በጣም ተገርሞ መሆን አለበት።

      ሙሴ ‘ሰዎቹ ማን ነው የላከህ ብለው ሲጠይቁኝ ምን ልበላቸው?’ አለ። አምላክም ‘የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክና የያዕቆብ አምላክ የሆነው ይሖዋ ነው በላቸው’ ሲል መለሰለት። ከዚያም ሙሴ ‘ሕዝቡ ባይሰማኝስ?’ ብሎ ጠየቀ። ይሖዋ ሙሴን እንደሚረዳው የሚያሳይ ማረጋገጫ ሰጠው። ሙሴን ዱላውን ወደ መሬት እንዲጥል ነገረው። በዚህ ጊዜ ዱላው እባብ ሆነ! ሙሴ የእባቡን ጅራት ሲይዘው እባቡ ተመልሶ ዱላ ሆነ። ይሖዋም ‘ይህን ተአምር ስታሳይ እኔ እንደላኩህ ያምናሉ’ አለው።

      ሙሴም ‘እኔ በደንብ መናገር አልችልም’ አለ። ይሖዋም ‘ምን ማለት እንዳለብህ እነግርሃለሁ፤ እንዲሁም ወንድምህ አሮን እንዲረዳህ እልከዋለሁ’ በማለት ቃል ገባለት። ሙሴ፣ ይሖዋ ከእሱ ጋር እንደሚሆን በመተማመን ሚስቱንና ልጆቹን ይዞ ወደ ግብፅ ተመለሰ።

      “እንዴት ወይም ምን ብለን እንመልሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ፤ የምትናገሩት ነገር በዚያኑ ሰዓት ይሰጣችኋልና።”—ማቴዎስ 10:19

      ጥያቄ፦ ሙሴ በጎቹን እየጠበቀ ሳለ ምን አየ? ይሖዋ ሙሴን ምን እንዲያደርግ ነገረው?

      ዘፀአት 3:1–4:20፤ የሐዋርያት ሥራ 7:30-36

  • የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቅሰፍቶች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ሙሴና አሮን በፈርዖን ፊት ቆመው

      ትምህርት 19

      የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቅሰፍቶች

      ግብፃውያን እስራኤላውያንን ባሪያ አድርገዋቸው ስለነበር የጉልበት ሥራ ያሠሯቸው ነበር። ይሖዋ ሙሴንና አሮንን ወደ ፈርዖን በመላክ ‘“ወደ ምድረ በዳ ሄደው እንዲያመልኩኝ ሕዝቤን ልቀቅ” ብላችሁ ንገሩት’ አላቸው። ፈርዖን ‘ይሖዋ የፈለገውን ቢል ግድ አይሰጠኝም፤ እስራኤላውያንን አለቅም’ በማለት በትዕቢት መለሰ። ከዚያም ፈርዖን የእስራኤላውያንን ሥራ የባሰ አከበደባቸው። ይሖዋ ግን ፈርዖንን አንድ ትልቅ ትምህርት ሊያስተምረው ነው። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ ታውቃለህ? በግብፅ ላይ አሥር መቅሰፍቶች በማምጣት ነው። ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ፈርዖን የእኔን ትእዛዝ አልሰማም። ጠዋት ላይ ወደ አባይ ወንዝ ይሄዳል። ስለዚህ ወደ እሱ ሂድና “ሕዝቤን አለቅም ስላልክ አባይ ውስጥ ያለው ውኃ በሙሉ ወደ ደም ይቀየራል” በለው።’ ሙሴ ይሖዋን በመታዘዝ ወደ ፈርዖን ሄደ። ፈርዖን እያየ አሮን የአባይን ወንዝ በዱላው ሲመታው ወንዙ ወደ ደም ተቀየረ። በዚህ ጊዜ ወንዙ መሽተት ጀመረ፤ ዓሦቹም ሞቱ፤ በዚህ የተነሳ ሕዝቡ ከአባይ ወንዝ መጠጣት አልቻለም። ፈርዖን ግን አሁንም እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

      ከሰባት ቀን በኋላ ይሖዋ ሙሴን እንደገና ወደ ፈርዖን በመላክ እንዲህ ብሎ እንዲነግረው አዘዘው፦ ‘ሕዝቤን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ካልሆንክ የግብፅ ምድር በሙሉ በእንቁራሪት ይሞላል።’ አሮንም ዱላውን አነሳ። ከዚያም እንቁራሪቶች ከውኃ እየወጡ ወደ ሰዎች ቤት ገቡ፤ ዕቃቸው ሁሉ በእንቁራሪት ተሞላ፤ አልጋቸውም ላይ ወጡ። ሁሉም ቦታ በእንቁራሪት ተሞልቶ ነበር! በዚህ ጊዜ ፈርዖን ሙሴን ‘ይህን መቅሰፍት እንዲያቆምልን ይሖዋን ለምንልን’ አለው። ፈርዖን እስራኤላውያንን እንደሚለቅ ቃል ገባ። ስለዚህ ይሖዋ መቅሰፍቱን አስቆመ፤ ግብፃውያኑም የሞቱትን እንቁራሪቶች ሰብስበው ከመሯቸው። ምድሪቱም መሽተት ጀመረች። ፈርዖን ግን አሁንም ሕዝቡን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

      ከዚያም ይሖዋ ሙሴን ‘አሮን መሬቱን በዱላው ይምታው፤ ከዚያም አቧራው ወደ ትንኝ ይቀየራል’ አለው። ወዲያውኑ ምድሩ በሙሉ በትንኝ ተወረረ። የፈርዖን አገልጋዮች ራሳቸው ፈርዖንን ‘ይህ መቅሰፍት ከአምላክ የመጣ ነው’ አሉት። ፈርዖን ግን እስራኤላውያንን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልሆነም።

      በግብፅ ላይ ከደረሱት አሥር መቅሰፍቶች መካከል ሦስቱ፦ የአባይ ወንዝ ወደ ደም መቀየር፣ እንቁራሪቶች እና ትንኞች

      “ኃይሌንና ብርታቴን እንዲያውቁ አደርጋለሁ፤ እነሱም ስሜ ይሖዋ መሆኑን ያውቃሉ።”—ኤርምያስ 16:21

      ጥያቄ፦ የመጀመሪያዎቹ ሦስት መቅሰፍቶች የትኞቹ ናቸው? ይሖዋ እነዚህን መቅሰፍቶች ያመጣው ለምንድን ነው?

      ዘፀአት 5:1-18፤ 7:8–8:19፤ ነህምያ 9:9, 10

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ