-
ቃላቸውን አልጠበቁምከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 24
ቃላቸውን አልጠበቁም
ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ እኔ ወደ ተራራው ውጣ። ሕጎቼን በድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፌ እሰጥሃለሁ።’ ሙሴ ወደ ተራራው ወጣና በዚያ 40 ቀንና 40 ሌሊት ቆየ። ሙሴ እዚያ በቆየበት ጊዜ ውስጥ ይሖዋ አሥርቱን ትእዛዛት በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጽፎ ሰጠው።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ሙሴ ትቷቸው የሄደ መሰላቸው። ስለዚህ አሮንን ‘መሪ ያስፈልገናል። አምላክ ሥራልን!’ አሉት። አሮንም ‘ወርቃችሁን ስጡኝ’ አላቸው። ከዚያም ወርቁን አቅልጦ የጥጃ ሐውልት ሠራ። ሰዎቹም ‘ከግብፅ መርቶ ያወጣን አምላካችን ይህ ጥጃ ነው!’ አሉ። በመሆኑም የወርቁን ጥጃ ማምለክ ጀመሩ፤ እንዲሁም ትልቅ ድግስ አዘጋጁ። ይህን ማድረጋቸው ስህተት ነበር? አዎ፣ ምክንያቱም ይሖዋን ብቻ ለማምለክ ቃል ገብተው ነበር። አሁን ግን ይህን ቃላቸውን አልጠበቁም።
ይሖዋ እስራኤላውያን ያደረጉትን ነገር አየና ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ ሕዝቡ ሂድ። እኔን አልታዘዙም፤ የሐሰት አምላክ እያመለኩ ነው።’ በመሆኑም ሙሴ ሁለቱን ጽላቶች ይዞ ከተራራው ወረደ።
ሙሴ ወደ ሰፈሩ ሲጠጋ እስራኤላውያን ሲዘምሩ ሰማ። ከዚያም ሲጨፍሩና ለጥጃው ሲሰግዱ ተመለከተ። በዚህ ጊዜ ሙሴ በጣም ተናደደ። ጽላቶቹን ወደ መሬት ሲወረውራቸው ተሰባበሩ። የጥጃውንም ሐውልት ወዲያውኑ ወስዶ አቃጠለው። ከዚያም አሮንን ‘እንዲህ ያለ መጥፎ ነገር ልታደርግ የቻልከው ሕዝቡ ምን ብሎ ቢያሳምንህ ነው?’ ብሎ ጠየቀው። አሮንም እንዲህ አለ፦ ‘እባክህ አትቆጣ። እነሱ እንደሆነ ምን ዓይነት ሰዎች እንደሆኑ ታውቃለህ። አምላክ ሥራልን አሉኝ፤ ስለዚህ ወርቃቸውን እሳቱ ውስጥ ጣልኩት፤ ከዚያ ይህ ጥጃ ወጣ!’ አሮን እንዲህ ማድረግ አልነበረበትም። ሙሴ ተመልሶ ወደ ተራራው በመውጣት ሕዝቡን ይቅር እንዲል ይሖዋን ለመነው።
ይሖዋ እሱን ለመታዘዝ ፈቃደኛ የሆኑትን ሰዎች ይቅር አላቸው። እስራኤላውያን የሙሴን አመራር መከተላቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበር አስተዋልክ?
“ለአምላክ ስእለት በምትሳልበት ጊዜ ሁሉ ስእለትህን ለመፈጸም አትዘግይ፤ እሱ በሞኞች አይደሰትምና። ስእለትህን ፈጽም።”—መክብብ 5:4
-
-
ለአምልኮ የሚያገለግል የማደሪያ ድንኳንከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 25
ለአምልኮ የሚያገለግል የማደሪያ ድንኳን
ሙሴ በሲና ተራራ ላይ በነበረበት ወቅት ይሖዋ ለየት ያለ ድንኳን እንዲሠራ አዘዘው፤ ይህ ድንኳን የማደሪያ ድንኳን ተብሎ የተጠራ ሲሆን እስራኤላውያን ይሖዋን ለማምለክ ይጠቀሙበት ነበር። እስራኤላውያን ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቀሱ የማደሪያውን ድንኳን ይዘው መሄድ ይችሉ ነበር።
ይሖዋ ሙሴን ‘የማደሪያውን ድንኳን ለመሥራት እስራኤላውያን የቻሉትን ያህል መዋጮ እንዲያደርጉ ንገራቸው’ አለው። በመሆኑም እስራኤላውያን ወርቅ፣ ብር፣ መዳብ፣ የከበሩ ድንጋዮችና ጌጣጌጦች ሰጡ። በተጨማሪም ሱፍ፣ በፍታ፣ የእንስሳት ቆዳና ሌሎች ብዙ ነገሮች አመጡ። ሕዝቡ ብዙ መዋጮ ስለሰጡ ሙሴ ‘የሚበቃንን ያህል አግኝተናል! ተጨማሪ ነገር አታምጡ’ አላቸው።
የማደሪያ ድንኳኑ ሲሠራ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ብዙ ወንዶችና ሴቶች በሥራው ተካፍለዋል። ይሖዋ ለሥራው የሚያስፈልገውን ጥበብ ሰጥቷቸዋል። አንዳንዶቹ ይፈትሉ፣ ይሸምኑ ወይም ጥልፍ ይጠልፉ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ በድንጋይ፣ በወርቅ እንዲሁም በእንጨት የተለያዩ ቅርጾችን ይቀርጹ ነበር።
ሕዝቡ የማደሪያ ድንኳኑን የሠሩት ልክ ይሖዋ ባዘዛቸው መንገድ ነበር። የማደሪያ ድንኳኑን ለሁለት የሚከፍል የሚያምር መጋረጃ ሠሩ፤ አንደኛው ክፍል ቅድስት የሚባል ሲሆን ሌላኛው ክፍል ደግሞ ቅድስተ ቅዱሳን ይባል ነበር። ቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከግራር እንጨትና ከወርቅ የተሠራ የቃል ኪዳን ታቦት ነበር። ቅድስቱ ውስጥ ደግሞ ከወርቅ የተሠራ መቅረዝ፣ ጠረጴዛና ዕጣን የሚጨስበት መሠዊያ ይገኛል። ግቢው ውስጥ ከመዳብ የተሠራ ገንዳና ትልቅ መሠዊያ ነበር። የቃል ኪዳኑ ታቦት እስራኤላውያን ይሖዋን ለመታዘዝ የገቡትን ቃል ያስታውሳቸው ነበር።
ይሖዋ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ካህናት ሆነው እንዲያገለግሉ አሮንንና ልጆቹን መርጦ ነበር። እነሱም የማደሪያ ድንኳኑን መንከባከብና በዚያ ለይሖዋ መባ ማቅረብ ነበረባቸው። ቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ መግባት የሚፈቀድለት ሊቀ ካህናቱ አሮን ብቻ ነበር። እሱም በዓመት አንድ ጊዜ ወደዚያ በመግባት ለራሱ፣ ለቤተሰቡ እንዲሁም ለመላው የእስራኤል ብሔር ኃጢአት መሥዋዕት ያቀርብ ነበር።
እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከአንድ ዓመት በኋላ የማደሪያ ድንኳኑን ሠርተው ጨረሱ። አሁን በዚህ ቦታ ይሖዋን ማምለክ ይችላሉ።
ይሖዋ የማደሪያ ድንኳኑን በክብሩ ሞላው፤ እንዲሁም ከድንኳኑ በላይ ደመና እንዲታይ አደረገ። ደመናው ከማደሪያ ድንኳኑ በላይ እስካለ ድረስ እስራኤላውያን ከሰፈሩበት ቦታ አይንቀሳቀሱም ነበር። ደመናው ሲነሳ ግን ያንን ቦታ ለቀው መጓዝ እንዳለባቸው ያውቁ ነበር። የማደሪያ ድንኳኑን ይነቃቅሉና ደመናውን ተከትለው ይጓዛሉ።
“በዚህ ጊዜ ከዙፋኑ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ ‘እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል።’”—ራእይ 21:3
-