የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • አሥራ ሁለቱ ሰላዮች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • እስራኤላውያን የከነአንን ምድር ሲሰልሉ

      ትምህርት 26

      አሥራ ሁለቱ ሰላዮች

      እስራኤላውያን ከሲና ተራራ ተነስተው፣ በፋራን ምድረ በዳ በኩል በመጓዝ ቃዴስ ወደሚባል ቦታ ደረሱ። በዚያም ይሖዋ ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ለእስራኤላውያን የምሰጣቸውን የከነአንን ምድር እንዲሰልሉ ከእያንዳንዱ ነገድ አንድ አንድ ሰው መርጠህ 12 ሰዎችን ላክ።’ ሙሴም 12 ሰዎችን መረጠና እንዲህ አላቸው፦ ‘ወደ ከነአን ሄዳችሁ ምድሪቱ ጥሩ እህል የምታበቅል መሆን አለመሆኗን እዩ። ሰዎቹ ደካማ ወይም ጠንካራ መሆናቸውን እንዲሁም የሚኖሩት በድንኳን ይሁን በከተሞች አጣርታችሁ ኑ።’ ኢያሱና ካሌብን ጨምሮ 12ቱ ሰላዮች ወደ ከነአን ሄዱ።

      እስራኤላውያን ተስፋ ቆርጠው ሲያጉረመርሙ

      ከ40 ቀን በኋላ ሰላዮቹ በለስ፣ ሮማንና ወይን ይዘው ተመለሱ። ሰላዮቹ ‘ምድሪቱ ለኑሮ ተስማሚ ነች፤ ሰዎቹ ግን በጣም ጠንካሮች ናቸው፤ ከተሞቹም ረጃጅም ግንብ አላቸው’ በማለት ተናገሩ። በዚህ ጊዜ ካሌብ ‘ሰዎቹን እናሸንፋቸዋለን። አሁኑኑ እንሂድ!’ አለ። ካሌብ እንዲህ ያለው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ? እሱና ኢያሱ በይሖዋ ይተማመኑ ስለነበረ ነው። ሌሎቹ አሥር ሰላዮች ግን እንዲህ አሉ፦ ‘አይሆንም! እዚያ ያሉት ሰዎች በጣም ግዙፎች ናቸው! እኛ ከእነሱ ጋር ስንነጻጸር እንደ ፌንጣ ነን።’

      እስራኤላውያን ይህን ሲሰሙ ተስፋ ቆረጡ። ማጉረምረምና እርስ በርሳቸው እንዲህ መባባል ጀመሩ፦ ‘ወደ ከነአን ሄደን እነዚያ ሰዎች ከሚገድሉን ሌላ መሪ መርጠን ወደ ግብፅ ብንመለስ አይሻለንም?’ በዚህ ጊዜ ኢያሱና ካሌብ ‘በይሖዋ ላይ አታምፁ፤ አትፍሩ። ይሖዋ ይጠብቀናል’ አሏቸው። እስራኤላውያን ግን አልሰሟቸውም። እንዲያውም ኢያሱንና ካሌብን ለመግደል አሰቡ!

      ይሖዋ ይህን ሲያይ ምን አደረገ? ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ለእስራኤላውያን ብዙ ነገር አድርጌላቸዋለሁ፤ እነሱ ግን አሁንም አይታዘዙኝም። ስለዚህ በምድረ በዳ ለ40 ዓመት ይቆያሉ፤ ከዚያም እዚያው ይሞታሉ። እሰጣቸዋለሁ ብዬ ቃል ወደገባሁላቸው ምድር የሚገቡት ልጆቻቸው እንዲሁም ኢያሱና ካሌብ ብቻ ናቸው።’

      “እናንተ እምነት የጎደላችሁ! ለምን ትሸበራላችሁ?”—ማቴዎስ 8:26

      ጥያቄ፦ ሙሴ የላካቸው 12 ሰላዮች ከከነአን ከተመለሱ በኋላ ምን ሆነ? ኢያሱና ካሌብ በይሖዋ እንደሚተማመኑ ያሳዩት እንዴት ነው?

      ዘኁልቁ 13:1–14:38፤ ዘዳግም 1:22-33፤ መዝሙር 78:22፤ ዕብራውያን 3:17-19

  • በይሖዋ ላይ ዓመፁ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ቆሬና ተባባሪዎቹ በሙሴና በአሮን ፊት ቆመው

      ትምህርት 27

      በይሖዋ ላይ ዓመፁ

      ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ቆሬ፣ ዳታን፣ አቤሮንና ሌሎች 250 ሰዎች በሙሴና በአሮን ላይ ዓመፁ። እንዲህም አሏቸው፦ ‘አላበዛችሁትም እንዴ! አንተ መሪያችን የሆንከው ለምንድን ነው? አሮንስ ሊቀ ካህናት የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋ ከእናንተ ጋር ብቻ ነው እንዴ? ከእኛም ጋር ነው።’ ይሖዋ ግን በዚህ አልተደሰተም። እነዚህ ሰዎች ልክ በራሱ ላይ እንዳመፁ አድርጎ ነበር የቆጠረው!

      ሙሴም ቆሬንና ተባባሪዎቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘ነገ የዕጣን ማጨሻዎቻችሁ ላይ ዕጣን ጨምራችሁ ወደ ማደሪያው ድንኳን ኑ። ይሖዋ ማንን እንደሚመርጥ እናያለን።’

      በቀጣዩ ቀን ቆሬና አብረውት የነበሩት 250 ሰዎች ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ሄዱ። ዕጣን ማጨስ የሚፈቀድላቸው ካህናት ብቻ ቢሆኑም ዕጣን አጨሱ። ይሖዋ ሙሴንና አሮንን ‘ከቆሬና ከተባባሪዎቹ ራሳችሁን ለዩ’ አላቸው።

      ቆሬ ከሙሴ ጋር ለመገናኘት ወደ ማደሪያ ድንኳኑ የሄደ ቢሆንም ዳታን፣ አቤሮንና ቤተሰቦቻቸው ወደዚያ ለመሄድ ፈቃደኞች አልሆኑም። ይሖዋ እስራኤላውያንን ከቆሬ፣ ከዳታንና ከአቤሮን ድንኳን እንዲርቁ ነገራቸው። እስራኤላውያንም ወዲያውኑ እንደተባሉት አደረጉ። ዳታን፣ አቤሮንና ቤተሰቦቻቸው በድንኳኖቻቸው ደጃፍ ላይ ቆሙ። ከዚያም በድንገት መሬቱ ተሰነጠቀና ዋጣቸው! በማደሪያ ድንኳኑ መግቢያ ላይ የነበሩትን ቆሬንና 250 ተባባሪዎቹን ደግሞ እሳት ከሰማይ ወርዶ አቃጠላቸው።

      መሬቱ ተሰንጥቆ ዳታንን፣ አቤሮንንና ቤተሰቦቻቸውን ሲውጣቸው

      ይሖዋ በመቀጠል ሙሴን እንዲህ አለው፦ ‘ከእያንዳንዱ ነገድ አለቃ አንድ በትር ውሰድና የነገድ አለቃውን ስም ጻፍበት። ከሌዊ ነገድ በተወሰደው በትር ላይ ደግሞ የአሮንን ስም ጻፍ። ከዚያም በትሮቹን በማደሪያው ድንኳን ውስጥ አስቀምጣቸው፤ እኔ የምመርጠው ሰው በትር አበባ ያወጣል።’

      በቀጣዩ ቀን ሙሴ በትሮቹን በሙሉ አምጥቶ ለነገድ አለቆቹ አሳያቸው። የአሮን በትር አበባ አውጥቶና የበሰለ የአልሞንድ ፍሬ አፍርቶ ነበር። በዚህ መንገድ ይሖዋ አሮንን ሊቀ ካህናት እንዲሆን የመረጠው እሱ እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጠ።

      “በመካከላችሁ ሆነው አመራር ለሚሰጧችሁ ታዘዙ እንዲሁም ተገዙ።”—ዕብራውያን 13:17

      ጥያቄ፦ ቆሬና ተባባሪዎቹ በሙሴና በአሮን ላይ በማመፅ ምን አሏቸው? አሮንን ሊቀ ካህናት እንዲሆን የመረጠው ይሖዋ እንደሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን?

      ዘኁልቁ 16:1–17:13፤ 26:9-11፤ መዝሙር 106:16-18

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ