የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ረዓብ ሰላዮቹን ደበቀች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ረዓብ ወታደሮቹን ወደ ሌላ አቅጣጫ በመላክ ሰላዮቹን አዳነቻቸው

      ትምህርት 30

      ረዓብ ሰላዮቹን ደበቀች

      ኢያሱ የላካቸው ሰላዮች ወደ ኢያሪኮ ሄደው ረዓብ ወደምትባል ሴት ቤት ገቡ። የኢያሪኮ ንጉሥ፣ ሰላዮች መምጣታቸውን ስለሰማ ወደ ረዓብ ቤት ወታደሮችን ላከ። ረዓብ ሁለቱን ሰላዮች ጣሪያ ላይ ደበቀቻቸውና ወታደሮቹን በሌላ አቅጣጫ ላከቻቸው። ከዚያም ሰላዮቹን እንዲህ አለቻቸው፦ ‘ይሖዋ ከእናንተ ጋር እንደሆነና ምድሪቱን እንደሚሰጣችሁ ስለማውቅ እረዳችኋለሁ። እባካችሁ ቤተሰቤን እንደምታድኑልኝ ቃል ግቡልኝ።’

      ሰላዮቹ ረዓብን እንዲህ አሏት፦ ‘በቤትሽ ያለ ማንኛውም ሰው ፈጽሞ ጉዳት እንደማይደርስበት ቃል እንገባልሻለን። መስኮትሽ ላይ ቀይ ገመድ አንጠልጥይ፤ እንዲህ ካደረግሽ ቤተሰብሽ ይድናል።’

      የኢያሪኮ አጥር ሲፈርስ መስኮቱ ላይ ቀይ ገመድ የተንጠለጠለበት የረዓብ ቤት አልፈረሰም

      ረዓብ ሰላዮቹን በመስኮት በኩል በገመድ አወረደቻቸው። እነሱም ወደ ተራሮች ሄደው ለሦስት ቀን ከተደበቁ በኋላ ወደ ኢያሱ ተመልሰው ሄዱ። ከዚያም እስራኤላውያን የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር ከተማዋን ለመያዝ ተዘጋጁ። እስራኤላውያን ድል ካደረጓቸው ከተሞች የመጀመሪያዋ ኢያሪኮ ነበረች። ይሖዋ ለስድስት ቀናት ያህል በቀን አንዴ ከተማዋን እንዲዞሯት ነገራቸው። በሰባተኛው ቀን ግን ከተማዋን ሰባት ጊዜ ዞሯት። ከዚያም ካህናቱ ቀንደ መለከታቸውን ነፉ፤ ወታደሮቹ ደግሞ ባለ በሌለ ኃይላቸው ጮኹ። በዚህ ጊዜ የከተማዋ አጥር ፈራረሰ! ከአጥሩ ጋር ተያይዞ የተሠራው የረዓብ ቤት ግን አልፈረሰም። ረዓብ በይሖዋ ስለታመነች እሷም ሆነች ቤተሰቧ መትረፍ ችለዋል።

      “ረዓብም መልእክተኞቹን በጥሩ ሁኔታ ተቀብላ ካስተናገደቻቸውና በሌላ መንገድ ከላከቻቸው በኋላ በሥራ አልጸደቀችም?”—ያዕቆብ 2:25

      ጥያቄ፦ ረዓብ ሰላዮቹን የረዳቻቸው ለምንድን ነው? እስራኤላውያን በኢያሪኮ ላይ ጥቃት የሰነዘሩት እንዴት ነው? ረዓብና ቤተሰቧ ምን ሆኑ?

      ኢያሱ 2:1-24፤ 6:1-27፤ ዕብራውያን 11:30, 31፤ ያዕቆብ 2:24-26

  • ኢያሱና ገባኦናውያን
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ገባኦናውያን ያረጀ ልብስ ለብሰው ወደ ኢያሱና ወደ ሠራዊቱ መጡ

      ትምህርት 31

      ኢያሱና ገባኦናውያን

      በከነአን ምድር የሚገኙ ሌሎች ሕዝቦች በኢያሪኮ ላይ የደረሰውን ጥፋት ሰሙ። በመሆኑም የእነዚህ ሕዝቦች ነገሥታት ተባብረው ከእስራኤላውያን ጋር ለመዋጋት ወሰኑ። ገባኦናውያን ግን ሌላ ነገር ለማድረግ አሰቡ። ያረጀ ልብስ ለብሰው ወደ ኢያሱ ሄዱና እንዲህ አሉት፦ ‘የመጣነው ከሩቅ አገር ነው። ስለ ይሖዋም ሆነ በግብፅና በሞዓብ ምድር ለእናንተ ስላደረገው ነገር ሰምተናል። እባካችሁ ጥቃት እንደማትሰነዝሩብን ቃል ግቡልን፤ እኛም አገልጋዮቻችሁ እንሆናለን።’

      ኢያሱ የተናገሩትን ነገር ስላመነ በእነሱ ላይ ጥቃት ላለመሰንዘር ተስማማ። ከሦስት ቀን በኋላ ግን ገባኦናውያን የሩቅ አገር ሰዎች ሳይሆኑ በዚያው በከነአን ምድር የሚኖሩ ሰዎች እንደሆኑ አወቀ። ኢያሱ ገባኦናውያንን ‘ለምንድን ነው ያታለላችሁን?’ በማለት ጠየቃቸው። እነሱም እንዲህ ብለው መለሱ፦ ‘ስለፈራን ነው! አምላካችሁ ይሖዋ ለእናንተ እንደሚዋጋላችሁ እናውቃለን። እባካችሁ አትግደሉን።’ ኢያሱም ቃሉን በመጠበቅ ሳይገድላቸው ቀረ።

      ብዙም ሳይቆይ፣ በከነአን ምድር የሚኖሩ አምስት ነገሥታት ወታደሮቻቸውን አሰልፈው ከገባኦናውያን ጋር ለመዋጋት ተነሱ። ኢያሱና ሠራዊቱ ሌሊቱን ሙሉ ተጉዘው ገባኦናውያንን ለማዳን መጡ። በቀጣዩ ቀን ጠዋት ጦርነቱ ተጀመረ። ከነአናውያን በሁሉም አቅጣጫ መሸሽ ጀመሩ። በሸሹበት ቦታ ሁሉ ይሖዋ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው። ከዚያም ኢያሱ ‘በገባኦን ላይ ፀሐይ ትቁም’ ብሎ ይሖዋን ለመነ። ፀሐይ ከዚያ በፊት ቆማ አታውቅም፤ ታዲያ ኢያሱ ፀሐይ እንድትቆም ይሖዋን የጠየቀው ለምንድን ነው? በይሖዋ ስለታመነ ነው። ፀሐይዋ እስራኤላውያን እነዚያን የከነአን ነገሥታትና ሠራዊታቸውን በሙሉ ድል አድርገው እስኪጨርሱ ድረስ አንድ ሙሉ ቀን ሳትጠልቅ ቆየች።

      ኢያሱ ወደ ሰማይ ቀና ብሎ ፀሐይ እንድትቆም ይሖዋን ሲጠይቅ

      “ቃላችሁ ‘አዎ’ ከሆነ አዎ ይሁን፤ ‘አይደለም’ ከሆነ አይደለም ይሁን፤ ከዚህ ውጭ የሆነ ግን ከክፉው ነው።”—ማቴዎስ 5:37

      ጥያቄ፦ ገባኦናውያን ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ምን አደረጉ? ይሖዋ እስራኤላውያንን የረዳቸው እንዴት ነው?

      ኢያሱ 9:1–10:15

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ