-
አዲሱ መሪና ሁለቱ ደፋር ሴቶችከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 32
አዲሱ መሪና ሁለቱ ደፋር ሴቶች
ኢያሱ ለብዙ ዓመታት የይሖዋን ሕዝቦች ሲመራ ከቆየ በኋላ በ110 ዓመቱ ሞተ። እሱ በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ እስራኤላውያን ይሖዋን ያመልኩ ነበር። ኢያሱ ከሞተ በኋላ ግን ልክ እንደ ከነአናውያን ጣዖት ማምለክ ጀመሩ። እስራኤላውያን ባለመታዘዛቸው ይሖዋ ያቢን የተባለ የከነአን ንጉሥ እንዲያሠቃያቸው ፈቀደ። በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጮኹ። ስለዚህ ይሖዋ፣ ባርቅ የተባለ አዲስ መሪ ሾመላቸው። ባርቅ ሕዝቡ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ የመርዳት ኃላፊነት ነበረበት።
ነቢይቷ ዲቦራ ባርቅን አስጠራችው። ከዚያም ይሖዋ የላከለትን የሚከተለውን መልእክት ነገረችው፦ ‘10,000 ወንዶች ይዘህ ወደ ቂሾን ወንዝ ሂድና ከያቢን ሠራዊት ጋር ተዋጋ። የያቢን ሠራዊት አለቃ የሆነውን ሲሳራን ታሸንፈዋለህ።’ ባርቅም ዲቦራን ‘እኔ የምሄደው አንቺ አብረሽኝ የምትሄጂ ከሆነ ብቻ ነው’ አላት። እሷም እንዲህ አለችው፦ ‘አብሬህ እሄዳለሁ። ግን ሲሳራን የምትገድለው አንተ እንደማትሆን እወቅ። ይሖዋ፣ ሲሳራን የምትገድለው አንዲት ሴት እንደሆነች ተናግሯል።’
ዲቦራ ከባርቅና ከሠራዊቱ ጋር እስከ ታቦር ተራራ ድረስ አብራ ሄደች፤ በዚያም ለውጊያ ተዘጋጁ። ሲሳራ ይህን እንደሰማ የጦር ሠረገሎቹንና ሠራዊቱን ከታቦር ተራራ ሥር ባለው ሸለቆ ሰበሰበ። ዲቦራም ባርቅን ‘ዛሬ ይሖዋ እንድታሸንፍ ይረዳሃል’ አለችው። ባርቅና 10,000 ወታደሮቹ ኃይለኛ ከሆነው የሲሳራ ሠራዊት ጋር ለመጋጠም ከተራራው ወረዱ።
ከዚያም ይሖዋ የቂሾን ወንዝ ሞልቶ አካባቢውን እንዲያጥለቀልቅ አደረገ። የሲሳራ የጦር ሠረገሎች ጭቃ ስለያዛቸው መሄድ አልቻሉም። ሲሳራ ከሠረገላው ላይ ወርዶ መሸሽ ጀመረ። ባርቅና ወታደሮቹ የሲሳራን ሠራዊት አሸነፉ፤ ሲሳራ ግን አመለጠ! ሲሳራ ሸሽቶ ኢያዔል የምትባል ሴት ድንኳን ውስጥ ተደበቀ። እሷም የሚጠጣው ወተት ሰጠችውና ብርድ ልብስ አለበሰችው። ሲሳራ ደክሞት ስለነበር እንቅልፍ ወሰደው። ከዚያም ኢያዔል በቀስታ ወደ እሱ ተጠግታ ጭንቅላቱ ላይ የድንኳን ካስማ ሰካችበት። በዚህ ሁኔታ ሲሳራ ሞተ።
ባርቅ ሲሳራን ፍለጋ መጣ። ኢያዔልም ከድንኳኗ ወጥታ ‘ና፣ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ’ አለችው። ባርቅ ወደ ውስጥ ሲገባ ሲሳራን ሞቶ አገኘው። ባርቅና ዲቦራም፣ ይሖዋ ጠላቶቻቸውን እንዲያሸንፉ ስለረዳቸው በመዝሙር አወደሱት። ከዚያ በኋላ እስራኤላውያን ለ40 ዓመታት በሰላም ኖሩ።
“ምሥራቹን የሚያውጁ ሴቶች ታላቅ ሠራዊት ናቸው።”—መዝሙር 68:11
-
-
ሩትና ናኦሚከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 33
ሩትና ናኦሚ
በአንድ ወቅት እስራኤል ውስጥ ረሃብ ተከስቶ ስለነበር ናኦሚ የተባለች አንዲት እስራኤላዊት ከባሏና ከሁለት ወንዶች ልጆቿ ጋር ወደ ሞዓብ ምድር ሄደች። ከጊዜ በኋላ የናኦሚ ባል ሞተ። ከዚያም ወንዶች ልጆቿ፣ ሩትና ዖርፋ የተባሉ ሞዓባውያን ሴቶችን አገቡ። የሚያሳዝነው ነገር የናኦሚ ወንዶች ልጆችም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሞቱ።
ናኦሚ የረሃቡ ወቅት እንዳበቃ ስትሰማ ወደ እስራኤል ለመመለስ ወሰነች። ሩትና ዖርፋም አብረዋት ለመሄድ ተነሱ፤ ነገር ግን መንገድ ላይ ሳሉ ናኦሚ እንዲህ አለቻቸው፦ ‘ለልጆቼ ጥሩ ሚስቶች፣ ለእኔ ደግሞ ጥሩ ምራቶች ነበራችሁ። ሁለታችሁም ሌላ ባል ብታገቡ ደስ ይለኛል። ወደ ቤታችሁ ተመለሱ።’ ሴቶቹም ‘እኛ በጣም እንወድሻለን! ትተንሽ መሄድ አንፈልግም’ አሏት። ናኦሚ ግን በድጋሚ እንዲመለሱ ነገረቻቸው። በመጨረሻም ዖርፋ ተመለሰች፤ ሩት ግን ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነችም። በዚህ ጊዜ ናኦሚ ሩትን እንዲህ አለቻት፦ ‘ዖርፋ ወደ ሕዝቧና ወደ አማልክቷ ተመልሳለች። አንቺም አብረሻት ተመለሺ፤ ወደ እናትሽ ቤት ሂጂ።’ ሩት ግን ‘ትቼሽ አልሄድም። ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል’ አለቻት። ሩት እንዲህ ብላ ስትናገር ናኦሚ ምን የተሰማት ይመስልሃል?
ሩትና ናኦሚ እስራኤል የደረሱት ገብስ በሚታጨድበት ጊዜ ነበር። አንድ ቀን ሩት የተራረፈ እህል ለመሰብሰብ ቦዔዝ ወደተባለ ሰው እርሻ ሄደች፤ ቦዔዝ የረዓብ ልጅ ነበር። ቦዔዝ፣ ሩት በታማኝነት ናኦሚን ስትረዳ የቆየች ሞዓባዊት እንደሆነች ሰማ። ስለሆነም በእርሻ ቦታው ላይ የተወሰነ እህል ለሩት እንዲተዉላት ሠራተኞቹን ነገራቸው።
ማታ ላይ ናኦሚ ሩትን ‘ዛሬ ስትሠሪ የዋልሽው በማን እርሻ ውስጥ ነው?’ ብላ ጠየቀቻት። ሩትም ‘ቦዔዝ በተባለ ሰው እርሻ ውስጥ ነው’ አለቻት። ናኦሚም እንዲህ አለች፦ ‘ቦዔዝ እኮ የባሌ ዘመድ ነው። ከሌሎቹ ወጣት ሴቶች ጋር ሆነሽ በእሱ እርሻ ውስጥ መሥራትሽን ቀጥይ። በዚያ ምንም ችግር አይገጥምሽም።’
ሩት እህል የሚሰበሰብበት ጊዜ እስኪያበቃ ድረስ በቦዔዝ እርሻ ውስጥ መሥራቷን ቀጠለች። ቦዔዝ፣ ሩት ጎበዝ ሠራተኛና ጥሩ ሴት እንደሆነች አስተዋለ። በዚያ ዘመን አንድ ሰው ልጅ ሳይወልድ ከሞተ ዘመዱ የሆነ ሰው የሟቹን ሚስት እንዲያገባ ይደረግ ነበር። ስለዚህ ቦዔዝ ሩትን አገባት። ከዚያም ኢዮቤድ የተባለ ልጅ ወለዱ፤ ኢዮቤድ ከጊዜ በኋላ የንጉሥ ዳዊት አያት ሆኗል። የናኦሚ ጓደኞች በጣም ተደሰቱ። በመሆኑም ናኦሚን እንዲህ አሏት፦ ‘ይሖዋ በመጀመሪያ ጥሩ ረዳት እንድትሆንሽ ሩትን ሰጠሽ፤ አሁን ደግሞ የልጅ ልጅ አገኘሽ። ይሖዋ የተመሰገነ ይሁን።’
“ከወንድም ይበልጥ የሚቀርብ ጓደኛ አለ።”—ምሳሌ 18:24
-