የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ጌድዮን ምድያማውያንን አሸነፈ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ጌድዮንና ወታደሮቹ ቀንደ መለከታቸውን ነፉ፤ ማሰሮዎቻቸውንም ሰበሩ፤ ከዚያም ችቦዎቻቸውን በእጃቸው ይዘው ጮኹ

      ትምህርት 34

      ጌድዮን ምድያማውያንን አሸነፈ

      ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ እስራኤላውያን እንደገና ይሖዋን በመተው የሐሰት አማልክትን ማምለክ ጀመሩ። ለሰባት ዓመታት ያህል ምድያማውያን የእስራኤላውያንን እንስሳት ይሰርቁ እንዲሁም እርሻቸውን ያበላሹ ነበር። እስራኤላውያን ከምድያማውያን ለማምለጥ ሲሉ በዋሻዎች ውስጥና በተራሮች ላይ ይደበቁ ነበር። በመጨረሻም እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ጮኹ። ስለዚህ ይሖዋ፣ ጌድዮን ወደተባለ አንድ ወጣት መልአኩን ላከ። መልአኩ ጌድዮንን ‘ይሖዋ ኃያል ተዋጊ እንድትሆን መርጦሃል’ አለው። ጌድዮንም ‘እንዴት እስራኤልን ላድን እችላለሁ? እኔ እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል አቅም የለኝም’ አለ።

      ጌድዮን፣ ይሖዋ እንደመረጠው በእርግጠኝነት ማወቅ የሚችለው እንዴት ነው? መሬት ላይ የበግ ፀጉር ካስቀመጠ በኋላ ይሖዋን እንዲህ አለው፦ ‘ጠዋት ላይ የበጉ ፀጉር በጤዛ ርሶ በዙሪያው ያለው መሬት በሙሉ ደረቅ ከሆነ፣ እኔ እስራኤልን እንዳድን እንደምትፈልግ በዚህ አውቃለሁ።’ በማግስቱ ጠዋት መሬቱ በሙሉ ደረቅ ቢሆንም የበጉ ፀጉር ረጥቦ አገኘው! ከዚያም ጌድዮን በቀጣዩ ቀን የበጉ ፀጉር ደረቅ ሆኖ ዙሪያው ያለው መሬት እርጥብ እንዲሆን ጠየቀ። ጌድዮን ይህ መፈጸሙን ሲያይ በእርግጥ ይሖዋ እንደመረጠው አመነ። ስለዚህ ከምድያማውያን ጋር ለመዋጋት ወታደሮቹን ሰበሰበ።

      ይሖዋ ጌድዮንን እንዲህ አለው፦ ‘እስራኤላውያን እንዲያሸንፉ አደርጋለሁ። ግን ወታደሮቹ በጣም ብዙ ስለሆኑ ውጊያውን ያሸነፋችሁት በራሳችሁ ኃይል እንደሆነ ልታስቡ ትችላላችሁ። ስለዚህ የፈሩ ሁሉ ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ንገራቸው።’ በመሆኑም 22,000 ወታደሮች ወደ ቤታቸው ተመልሰው 10,000 ወታደሮች ብቻ ቀሩ። ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ ‘አሁንም ወታደሮቹ በጣም ብዙ ናቸው። ወታደሮቹን ወደ ወንዙ ውሰዳቸውና ውኃ እንዲጠጡ ንገራቸው። ውኃ በሚጠጡበት ጊዜ ንቁ ሆነው ጠላት መምጣቱን የሚከታተሉትን ብቻ ከአንተ ጋር አስቀር።’ በንቃት እየተከታተሉ ውኃ የጠጡት 300 ሰዎች ብቻ ነበሩ። ይሖዋም እነዚህ ጥቂት ሰዎች 135,000ዎቹን የምድያም ወታደሮች እንደሚያሸንፉ ቃል ገባ።

      በዚያ ቀን ምሽት ላይ ይሖዋ ጌድዮንን ‘አሁን ምድያማውያን ላይ ጥቃት ሰንዝር!’ አለው። ጌድዮን ለሰዎቹ ቀንደ መለከትና በውስጣቸው ችቦ ያለባቸው ትላልቅ ማሰሮዎች ሰጣቸው። ከዚያም ‘እኔን ተመልከቱና ልክ እንደማደርገው አድርጉ’ አላቸው። ጌድዮን ቀንደ መለከቱን ነፋ፤ ማሰሮውንም ሰበረ፤ ከዚያም ችቦውን በእጁ ያዘና ‘የይሖዋና የጌድዮን ሰይፍ!’ ብሎ ጮኸ። አብረውት የነበሩት 300 ሰዎችም ተመሳሳይ ነገር አደረጉ። ምድያማውያኑ ፈርተው በሁሉም አቅጣጫ ሸሹ። በዚህ ጊዜ ትርምስ ስለተፈጠረ እርስ በርስ መዋጋት ጀመሩ። እስራኤላውያን ይሖዋ ስለረዳቸው በድጋሚ ጠላቶቻቸውን አሸነፉ።

      በፍርሃት የተዋጡ የምድያም ወታደሮች

      “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነው ኃይል ከእኛ ሳይሆን ከአምላክ የመነጨ መሆኑ [እንዲታወቅ ነው]።”—2 ቆሮንቶስ 4:7

      ጥያቄ፦ ይሖዋ ጌድዮንን ተዋጊ አድርጎ እንደመረጠው ያረጋገጠለት እንዴት ነው? የጌድዮን ወታደሮች 300 ብቻ የነበሩት ለምንድን ነው?

      መሳፍንት 6:1-16፤ 6:36–7:25፤ 8:28

  • ሐና ልጅ ለማግኘት ጸለየች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ሐና ሕፃኑን ሳሙኤልን ወደ ቤተ መቅደሱ ወስዳ ለኤሊ ስትሰጠው

      ትምህርት 35

      ሐና ልጅ ለማግኘት ጸለየች

      ሕልቃና የሚባል አንድ እስራኤላዊ ሐና እና ፍናና የተባሉ ሁለት ሚስቶች ነበሩት፤ ሆኖም ሕልቃና አስበልጦ የሚወደው ሐናን ነበር። ፍናና ብዙ ልጆች ነበሯት፤ ሐና ግን ምንም ልጅ አልነበራትም፤ ስለዚህ ፍናና ሁልጊዜ በሐና ላይ ታሾፍባት ነበር። ሕልቃና በሴሎ በሚገኘው የማደሪያ ድንኳን ይሖዋን ለማምለክ በየዓመቱ ቤተሰቡን ይዞ ይሄድ ነበር። በአንድ ወቅት ወደ ሴሎ ሄደው ሳለ ሕልቃና የሚወዳት ሚስቱ ሐና በጣም እንዳዘነች አስተዋለ። ስለዚህ ‘ሐና፣ እባክሽ አታልቅሺ። እኔ አለሁልሽ። እኔ እኮ በጣም ነው የምወድሽ’ አላት።

      በኋላም ሐና ብቻዋን ሆና ለመጸለይ ሄደች። ይሖዋን እንዲረዳት እያለቀሰች ለመነችው። እንዲህ በማለት ቃል ገባች፦ ‘ይሖዋ ሆይ፣ ወንድ ልጅ ብትሰጠኝ ለአንተ እሰጠዋለሁ፤ እሱም ዕድሜውን ሙሉ ያገለግልሃል።’

      ሊቀ ካህናቱ ኤሊ ሐና እያለቀሰች ስትጸልይ ሲያያት

      ሊቀ ካህናቱ ኤሊ፣ ሐና እያለቀሰች ስትጸልይ ሲያይ የሰከረች መሰለው። ሐናም እንዲህ አለችው፦ ‘ሰክሬ አይደለም ጌታዬ። ከባድ ችግር ስላለብኝ ይሖዋ እንዲረዳኝ እየለመንኩት ነው።’ ኤሊም እንደተሳሳተ ሲገባው ‘አምላክ የምትፈልጊውን ነገር ይስጥሽ’ አላት። ሐናም ተጽናንታ ሄደች። ከዚያም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ስሙንም ሳሙኤል አለችው። ሐና ልጅ በማግኘቷ ምን ያህል ተደስታ ሊሆን እንደሚችል አስበው።

      ሐና ለይሖዋ የገባችውን ቃል አልረሳችም። ልክ ሳሙኤል ጡት መጥባት እንዳቆመ ወደ ማደሪያ ድንኳኑ አመጣችው። ከዚያም ኤሊን እንዲህ አለችው፦ ‘ስጸልይ የነበረው ይህን ልጅ ለማግኘት ነበር። በሕይወቱ ሙሉ ይሖዋን እንዲያገለግል ለእሱ እሰጠዋለሁ።’ ሕልቃናና ሐና በየዓመቱ ሳሙኤልን ለመጠየቅ ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ሲሄዱ አዲስ ልብስ ያመጡለት ነበር። ይሖዋ ከዚያ በኋላ ለሐና ሌሎች ሦስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆች ሰጣት።

      “ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል፤ ሳታቋርጡ ፈልጉ፣ ታገኛላችሁ።”—ማቴዎስ 7:7

      ጥያቄ፦ ሐና ያዘነችው ለምንድን ነው? ይሖዋ ሐናን የባረካት እንዴት ነው?

      1 ሳሙኤል 1:1–2:11, 18-21

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ