የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ዮፍታሔ የገባው ቃል
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ዮፍታሔ ልጁ ልትቀበለው መውጣቷን አይቶ ልብሱን ሲቀድ

      ትምህርት 36

      ዮፍታሔ የገባው ቃል

      እስራኤላውያን በድጋሚ ይሖዋን ትተው የሐሰት አማልክትን ማምለክ ጀመሩ። አሞናውያን ጥቃት ሰንዝረውባቸው ከእነሱ ጋር በተዋጉበት ወቅት እነዚህ የሐሰት አማልክት ምንም አልረዷቸውም። እስራኤላውያን ለብዙ ዓመታት ሥቃይ ደረሰባቸው። በመጨረሻም ይሖዋን ‘ኃጢአት ሠርተናል። እባክህ ከጠላቶቻችን አድነን’ ብለው ለመኑት። እስራኤላውያን ጣዖቶቻቸውን አስወግደው ይሖዋን ማምለክ ጀመሩ። ይሖዋም ሲሠቃዩ ማየት አልፈለገም።

      በመሆኑም ዮፍታሔ የተባለ አንድ ተዋጊ ሕዝቡን እየመራ ከአሞናውያን ጋር እንዲዋጋ ተመረጠ። ዮፍታሔ ለይሖዋ እንዲህ በማለት ቃል ገባ፦ ‘ይህን ጦርነት እንድናሸንፍ ከረዳኸን፣ ወደ ቤት ስመለስ ሊቀበለኝ የሚወጣውን የመጀመሪያ ሰው ለአንተ እሰጥሃለሁ።’ ይሖዋም የዮፍታሔን ጸሎት ሰምቶ በጦርነቱ እንዲያሸንፍ ረዳው።

      ዮፍታሔ ወደ ቤቱ ሲመለስ በመጀመሪያ ልትቀበለው የወጣችው ልጁ ነበረች፤ ዮፍታሔ ከእሷ ሌላ ልጅ አልነበረውም። እየጨፈረችና ከበሮ እየመታች ልትቀበለው ወጣች። ዮፍታሔ ምን ያደርግ ይሆን? ለይሖዋ የገባውን ቃል አስታወሰና እንዲህ አለ፦ ‘ወይኔ፣ ልጄ! ልቤን ሰበርሽው። ለይሖዋ ቃል ገብቻለሁ። የገባሁትን ቃል ለመጠበቅ ደግሞ በሴሎ ባለው የማደሪያ ድንኳን እንድታገለግዪ አንቺን መላክ አለብኝ።’ በዚህ ጊዜ ልጁ እንዲህ አለችው፦ ‘አባዬ፣ ለይሖዋ ቃል ከገባህ ቃልህን መጠበቅ አለብህ። ብቻ ወደ ተራሮች ሄጄ ከሴት ጓደኞቼ ጋር ለሁለት ወር ያህል አብሬ ጊዜ እንዳሳልፍ ፍቀድልኝ። ከዚያ እሄዳለሁ።’ ከዚያ በኋላ የዮፍታሔ ልጅ ዕድሜዋን በሙሉ በማደሪያ ድንኳኑ በታማኝነት አገልግላለች። ጓደኞቿም በየዓመቱ ወደ ሴሎ እየሄዱ ይጠይቋት ነበር።

      የዮፍታሔ ልጅ ጓደኞች እሷን ለመጠየቅ ወደ ማደሪያ ድንኳኑ ሄደው

      “ከእኔ ይልቅ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ሁሉ ለእኔ ሊሆን አይገባም።”—ማቴዎስ 10:37

      ጥያቄ፦ ዮፍታሔ ለይሖዋ የገባው ቃል ምን ነበር? የዮፍታሔ ልጅ አባቷ የገባውን ቃል ስትሰማ ምን አደረገች?

      መሳፍንት 10:6–11:11፤ 11:29-40፤ 1 ሳሙኤል 12:10, 11

  • ይሖዋ ሳሙኤልን አነጋገረው
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ሳሙኤል የማደሪያውን ድንኳን በሮች ሲከፍት

      ትምህርት 37

      ይሖዋ ሳሙኤልን አነጋገረው

      ሊቀ ካህናቱ ኤሊ በማደሪያ ድንኳኑ ውስጥ ካህናት ሆነው የሚያገለግሉ ሆፍኒ እና ፊንሃስ የሚባሉ ሁለት ልጆች ነበሩት። ሆፍኒ እና ፊንሃስ የይሖዋን ሕግ አይታዘዙም ነበር፤ እንዲሁም በሕዝቡ ላይ በደል ይፈጽሙ ነበር። እስራኤላውያን ለይሖዋ መሥዋዕት ይዘው ሲመጡ ሆፍኒ እና ፊንሃስ ምርጥ የሆነውን ሥጋ ለራሳቸው ይወስዱ ነበር። ኤሊ ልጆቹ የሚያደርጉትን ነገር ቢሰማም ምንም እርምጃ አልወሰደም። ታዲያ ይሖዋ ዝም ብሎ ይመለከታቸው ይሆን?

      ሳሙኤል ዕድሜው ከሆፍኒ እና ከፊንሃስ በጣም የሚያንስ ቢሆንም የእነሱን ምሳሌ አልተከተለም። ይሖዋ በሳሙኤል ተደስቶ ነበር። አንድ ቀን ሳሙኤል ተኝቶ ሳለ አንድ ድምፅ ሲጠራው ሰማ። ሳሙኤልም ተነስቶ ወደ ኤሊ እየሮጠ ሄደና ‘አቤት፣ ጠራኸኝ?’ አለው። ኤሊ ግን ‘አይ አልጠራሁህም። ተመልሰህ ተኛ’ አለው። ሳሙኤልም ተመልሶ ተኛ። ከዚያም በድጋሚ ያንን ድምፅ ሰማና ወደ ኤሊ ሄደ፤ ሆኖም በዚህ ጊዜም ኤሊ አልጠራውም ነበር። ሳሙኤል ለሦስተኛ ጊዜ ያንን ድምፅ ሲሰማ፣ ኤሊ ሳሙኤልን እየጠራው ያለው ይሖዋ እንደሆነ ተገነዘበ። ስለዚህ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ ‘ድጋሚ ያንን ድምፅ ከሰማህ “ይሖዋ ሆይ፣ እኔ አገልጋይህ እየሰማሁ ስለሆነ ተናገር” በለው።’

      ሳሙኤል ተመልሶ ተኛ። ከዚያም ‘ሳሙኤል! ሳሙኤል!’ የሚል ድምፅ ሰማ። ሳሙኤልም ‘እኔ አገልጋይህ እየሰማሁ ስለሆነ ተናገር’ አለ። ይሖዋም እንዲህ አለው፦ ‘ኤሊንና ቤተሰቡን ልቀጣ እንደሆነ ለኤሊ ንገረው። ኤሊ ልጆቹ በማደሪያ ድንኳኔ ውስጥ መጥፎ ነገር እንደሚያደርጉ እያወቀ ምንም እርምጃ አልወሰደም።’ በቀጣዩ ቀን ጠዋት ሳሙኤል እንደተለመደው የማደሪያውን ድንኳን በሮች ከፈተ። ይሖዋ የነገረውን ነገር ለሊቀ ካህናቱ ለመናገር ፈርቶ ነበር። ኤሊ ግን ጠራውና እንዲህ አለው፦ ‘ልጄ፣ ይሖዋ የነገረህ መልእክት ምንድን ነው? ሁሉንም ነገር ንገረኝ።’ ስለሆነም ሳሙኤል ለኤሊ ሁሉንም ነገር ነገረው።

      ሳሙኤል ይሖዋ የነገረውን መልእክት ለኤሊ ሲነግረው

      ሳሙኤል እያደገ ሄደ፤ ይሖዋ ምንጊዜም ከሳሙኤል ጋር ሆኖ ይረዳው ነበር። በሁሉም ቦታ የሚገኙ እስራኤላውያን፣ ይሖዋ ሳሙኤልን ነቢይና ፈራጅ አድርጎ እንደመረጠው አወቁ።

      “በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ።”—መክብብ 12:1

      ጥያቄ፦ ሳሙኤል ከሆፍኒ እና ከፊንሃስ የተለየ የሆነው እንዴት ነው? ይሖዋ ለሳሙኤል ምን መልእክት ነገረው?

      1 ሳሙኤል 2:12-17, 22-26፤ 3:1-21፤ 7:6

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ