-
ዳዊት እና ጎልያድከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 40
ዳዊት እና ጎልያድ
ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ እሴይ ቤት ሂድ። ከእሴይ ልጆች መካከል አንዱ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ ይሆናል።’ ስለዚህ ሳሙኤል ወደ እሴይ ቤት ሄደ። ከዚያም የመጀመሪያ ልጁን ሲያይ ‘ይሖዋ የመረጠው ይህን ወጣት መሆን አለበት’ ብሎ አሰበ። ይሖዋ ግን ሳሙኤልን ‘የመረጥኩት እሱን አይደለም። እኔ የማየው የሰውን መልክ ብቻ ሳይሆን እውነተኛ ባሕርይውን ጭምር ነው’ አለው።
እሴይ ሌሎቹን ስድስት ልጆቹን ጠርቶ ሳሙኤል ፊት አቀረባቸው። ሳሙኤል ግን ‘ይሖዋ እነዚህንም አልመረጣቸውም። ሌላ ልጅ የለህም?’ አለው። እሴይም ‘የመጨረሻው ልጄ ዳዊት አለ። ውጭ በጎቹን እየጠበቀ ነው’ አለ። ዳዊት ወደ ቤት ሲገባ ይሖዋ ሳሙኤልን ‘የመረጥኩት እሱን ነው!’ አለው። ሳሙኤልም በዳዊት ራስ ላይ ዘይት በማፍሰስ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ቀባው።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ከፍልስጤማውያን ጋር ለመዋጋት ተሰለፉ፤ ፍልስጤማውያን ጎልያድ የሚባል ግዙፍ ተዋጊ ነበራቸው። ጎልያድ በየቀኑ በእስራኤላውያን ላይ ያሾፍ ነበር። ‘ከእኔ ጋር የሚዋጋ ሰው ካለ ይምጣ። እሱ ካሸነፈኝ እኛ የእናንተ ባሪያዎች እንሆናለን። እኔ ካሸነፍኩት ደግሞ እናንተ የእኛ ባሪያዎች ትሆናላችሁ’ እያለ ይጮኽ ነበር።
የዳዊት ወንድሞች ወታደሮች ስለነበሩ ዳዊት ለእነሱ ምግብ ለማድረስ ወደ እስራኤል ጦር ሰፈር መጣ። ከዚያም ጎልያድ የሚናገረውን ሲሰማ ‘እኔ እዋጋዋለሁ!’ አለ። ንጉሥ ሳኦል ግን ‘አንተ እኮ ገና ልጅ ነህ’ አለው። ዳዊትም ‘ይሖዋ ይረዳኛል’ በማለት መለሰ።
ሳኦል የጦር ልብሱን ለዳዊት ሊሰጠው ፈልጎ ነበር፤ ዳዊት ግን ‘ይህን ለብሼ መዋጋት አልችልም’ አለ። ከዚያም ዳዊት ወንጭፉን ይዞ ወደ ወንዝ ሄደ። አምስት ድቡልቡል ድንጋዮች መረጠና ኮሮጆው ውስጥ ጨመራቸው። ከዚያም ወደ ጎልያድ እየሮጠ ሄደ። ጎልያድም ‘እስቲ ወደዚህ ና። ሥጋህን ለሰማይ አሞሮችና ለምድር አራዊት እሰጣለሁ’ በማለት ጮኸበት። ዳዊት ግን አልፈራም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ሰይፍና ጦር ይዘህ ትመጣብኛለህ፤ እኔ ግን በይሖዋ ስም እመጣብሃለሁ። የምትዋጋው ከእኛ ጋር ሳይሆን ከአምላክ ጋር ነው። እዚህ ያሉት ሰዎች ሁሉ ይሖዋ ከሰይፍ ወይም ከጦር የበለጠ ኃይል እንዳለው ያያሉ። ሁላችሁንም በእጃችን አሳልፎ ይሰጣችኋል።’
ዳዊትም አንድ ድንጋይ ወንጭፉ ላይ አድርጎ ባለ በሌለ ኃይሉ አሽከረከረው። ይሖዋ ዳዊትን ስለረዳው ድንጋዩ ሄዶ የጎልያድ ግንባር ውስጥ ተቀረቀረ። ከዚያም ግዙፉ ጎልያድ መሬት ላይ ተደፋ፤ በዚህ ሁኔታ ዳዊት ጎልያድን ገደለው። ፍልስጤማውያንም ሸሹ። አንተስ እንደ ዳዊት በይሖዋ ትተማመናለህ?
“ይህ በሰዎች ዘንድ አይቻልም፤ በአምላክ ዘንድ ግን እንዲህ አይደለም፤ በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል።”—ማርቆስ 10:27
-
-
ዳዊት እና ሳኦልከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 41
ዳዊት እና ሳኦል
ዳዊት ጎልያድን ከገደለ በኋላ ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን የሠራዊቱ መሪ አደረገው። ዳዊት ብዙ ጦርነቶችን አሸነፈ፤ እስራኤላውያንም በጣም ወደዱት። ዳዊት ከጦርነት በሚመለስበት ወቅት፣ ሴቶች ‘ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤ ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ’ ብለው እየዘፈኑና እየጨፈሩ ይቀበሉት ነበር። ስለዚህ ሳኦል በዳዊት ይቀና ጀመር፤ በዚህም የተነሳ ሊገድለው ፈለገ።
ዳዊት በገና ሲጫወት ጎበዝ ነበር። አንድ ቀን ዳዊት ለሳኦል በገና እየተጫወተለት ሳለ ንጉሡ በዳዊት ላይ ጦሩን ወረወረበት። ሆኖም ዳዊት ጎንበስ ሲል ጦሩ ግድግዳው ላይ ተሰካ። ከዚያ በኋላም ሳኦል በተደጋጋሚ ዳዊትን ለመግደል ሞክሯል። በመጨረሻም ዳዊት ሸሽቶ በረሃ ውስጥ ተደበቀ።
ሳኦል 3,000 ወታደሮችን ይዞ ዳዊትን ፍለጋ ሄደ። ከዚያም አንድ ዋሻ ውስጥ ገባ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች የተደበቁት እዚሁ ዋሻ ውስጥ ነበር። ከዳዊት ጋር የነበሩት ሰዎችም ‘ሳኦልን ለመግደል ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ አታገኝም’ በማለት ዳዊትን አደፋፈሩት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ቀስ ብሎ ወደ ንጉሥ ሳኦል ተጠጋና የልብሱን ጫፍ ቆረጠ። ሳኦል፣ ዳዊት ምን እንዳደረገ አላወቀም ነበር። በኋላ ግን ዳዊት፣ ይሖዋ ለቀባው ንጉሥ አክብሮት ባለማሳየቱ በጣም አዘነ። አብረውት የነበሩት ሰዎችም በሳኦል ላይ ጉዳት እንዲያደርሱበት አልፈቀደላቸውም። ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ ሳኦልን በመጥራት ሊገድለው ይችል እንደነበረ ነገረው። ታዲያ ሳኦል ከዚህ በኋላ ዳዊትን ማሳደዱን ይተው ይሆን?
በፍጹም፤ ሳኦል ዳዊትን ማሳደዱን አልተወም። አንድ ቀን ዳዊትና የእህቱ ልጅ አቢሳ ተደብቀው ወደ ሳኦል ድንኳን ገቡ። የሳኦል ጠባቂ የነበረው አበኔርም ተኝቶ ነበር። በዚህ ጊዜ አቢሳ ‘ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነው! ሳኦልን ልግደለው’ አለ። ዳዊት ግን እንዲህ ብሎ መለሰ፦ ‘ይሖዋ ራሱ በሳኦል ላይ እርምጃ ይወስድበታል። አሁን ጦሩንና የውኃ መያዣውን ይዘን እንሂድ።’
ከዚያም ዳዊት፣ ሳኦል በሰፈረበት አካባቢ የሚገኝ ተራራ ላይ ወጣ። ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ ‘አበኔር፣ ንጉሡን የማትጠብቀው ለምንድን ነው? የሳኦል የውኃ መያዣና ጦር የት አለ?’ ሳኦልም እየተናገረ ያለው ዳዊት መሆኑን ሲያውቅ ‘ልትገድለኝ ትችል ነበር፤ ግን አልገደልከኝም። ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ አንተ እንደምትሆን አውቃለሁ’ አለ። ከዚያም ሳኦል ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ። ሳኦል ዳዊትን ይጠላው የነበረ ቢሆንም ከቤተሰቡ አባላት መካከል ዳዊትን የሚወድ ሰው ነበር።
“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ።”—ሮም 12:18, 19
-