-
ዮናታን ደፋርና ታማኝ ነበርከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 42
ዮናታን ደፋርና ታማኝ ነበር
የንጉሥ ሳኦል የመጀመሪያ ልጅ የሆነው ዮናታን ደፋር ተዋጊ ነበር። ዳዊት ራሱ ዮናታን ከንስር ይበልጥ ፈጣንና ከአንበሳ ይበልጥ ጠንካራ እንደሆነ ተናግሯል። አንድ ቀን ዮናታን የተወሰኑ ፍልስጤማውያን ወታደሮችን አንድ ተራራ ላይ አየ። ከዚያም አገልጋዩን ‘የምንዋጋው ይሖዋ ምልክት ከሰጠን ብቻ ነው። ፍልስጤማውያኑ ኑና ግጠሙን ካሉን ሄደን እንዋጋለን’ አለው። ፍልስጤማውያኑም ‘ወደ እኛ ኑና እንጋጠም!’ ብለው ጮኹ። ስለዚህ ዮናታንና አገልጋዩ ወደ ተራራው ወጥተው ከፍልስጤማውያኑ ጋር በመዋጋት አሸነፏቸው።
ዮናታን የሳኦል የመጀመሪያ ልጅ በመሆኑ ቀጣዩ ንጉሥ የሚሆነው እሱ ነበር። ሆኖም ዮናታን ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን ይሖዋ የመረጠው ዳዊትን እንደሆነ ያውቅ ነበር፤ ቢሆንም በዳዊት አልቀናም። እንዲያውም ዮናታንና ዳዊት የቅርብ ጓደኛሞች ሆኑ። አንዳቸው ሌላውን ለመጠበቅና እርስ በርስ ለመረዳዳት ቃል ገቡ። ዮናታን ዳዊትን በጣም እንደሚወደው ለማሳየት ልብሱን፣ ሰይፉን፣ ቀስቱንና ቀበቶውን ሰጠው።
ዳዊት ከሳኦል እየሸሸ በነበረበት ወቅት ዮናታን ወደ ዳዊት ሄዶ ‘በርታ፤ ደፋር ሁን። ይሖዋ ንጉሥ እንድትሆን መርጦሃል። አባቴም ቢሆን ይህን ያውቃል’ አለው። አንተም እንደ ዮናታን ያለ ጥሩ ጓደኛ ቢኖርህ ደስ አይልህም?
ዮናታን ጓደኛውን ለመርዳት ሲል በተደጋጋሚ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሏል። ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን መግደል እንደሚፈልግ ያውቅ ነበር፤ ስለዚህ አባቱን እንዲህ አለው፦ ‘ዳዊትን ብትገድል ኃጢአት ይሆንብሃል፤ ዳዊት ምንም መጥፎ ነገር አልሠራም።’ በዚህ ጊዜ ሳኦል በዮናታን በጣም ተበሳጨ።
ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ ሳኦልና ዮናታን ጦርነት ላይ ሞቱ። ዮናታን ከሞተ በኋላ ዳዊት የዮናታንን ልጅ ሜፊቦስቴን ፈልጎ ለማግኘት ጥረት አደረገ። ዳዊት ሜፊቦስቴን ካገኘው በኋላ እንዲህ አለው፦ ‘አባትህ በጣም ጥሩ ጓደኛዬ ስለነበር ከአሁን በኋላ እኔ እንከባከብሃለሁ። ቤተ መንግሥቴ ውስጥ ትኖራለህ፤ እንዲሁም ከእኔ ጋር ትበላለህ።’ ዳዊት ጓደኛውን ዮናታንን ፈጽሞ አልረሳውም።
“እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።”—ዮሐንስ 15:12, 13
-
-
ንጉሥ ዳዊት የሠራው ኃጢአትከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 43
ንጉሥ ዳዊት የሠራው ኃጢአት
ሳኦል ከሞተ በኋላ ዳዊት ንጉሥ ሆነ። በወቅቱ ዳዊት 30 ዓመቱ ነበር። ለተወሰኑ ዓመታት ንጉሥ ሆኖ ከገዛ በኋላ አንድ ከባድ ስህተት ሠራ። አንድ ቀን ምሽት ላይ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ አንዲት ቆንጆ ሴት አየ። ዳዊት ስለ ሴትየዋ ማንነት ሲጠይቅ ስሟ ቤርሳቤህ እንደሆነና ኦርዮ የሚባል አንድ ወታደር ሚስት እንደሆነች ነገሩት። ዳዊት ቤርሳቤህን ወደ ቤተ መንግሥቱ አስመጣት። ከዚያም አብሯት ተኛ፤ እሷም አረገዘች። ዳዊት ያደረገውን ነገር ለመደበቅ ሞከረ። ለጦር አዛዡ መልእክት ልኮ ኦርዮን ውጊያው ላይ ፊት ለፊት እንዲያሰልፈውና ሌሎቹ ወታደሮች ጥለውት እንዲሸሹ እንዲያደርግ ነገረው። ኦርዮ በጦርነቱ ከተገደለ በኋላ ዳዊት ቤርሳቤህን አገባት።
ሆኖም ይሖዋ የተፈጸመውን መጥፎ ድርጊት በሙሉ ተመልክቶ ነበር። ታዲያ ምን ያደርግ ይሆን? ይሖዋ ነቢዩ ናታንን ወደ ዳዊት ላከው። ናታን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘አንድ ሀብታም ሰውና አንድ ድሃ ሰው ነበሩ፤ ሀብታሙ ሰው ብዙ በጎች ነበሩት፤ ድሃው ግን የነበረችው አንዲት ትንሽ የበግ ጠቦት ብቻ ነበረች። እሷንም በጣም ይወዳት ነበር። ሀብታሙ ሰው ድሃው የነበረችውን አንዲት ጠቦት ወሰደበት።’ በዚህ ጊዜ ዳዊት በጣም ተናዶ ‘ያ ሀብታም ሰው መሞት ይገባዋል!’ አለ። ከዚያም ናታን ዳዊትን ‘ያ ሀብታም ሰው አንተ ነህ!’ አለው። ዳዊት በጣም አዘነ፤ ከዚያም ጥፋቱን በማመን ‘በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርቻለሁ’ አለ። ይህ ኃጢአት በዳዊትና በቤተሰቡ ላይ ብዙ ችግር አምጥቷል። ይሖዋ ዳዊትን የቀጣው ቢሆንም ዳዊት ሐቀኛና ትሑት በመሆኑ በሕይወት እንዲኖር ፈቅዶለታል።
ዳዊት ለይሖዋ ቤተ መቅደስ መገንባት ፈልጎ ነበር፤ ይሖዋ ግን ቤተ መቅደሱን እንዲገነባ የመረጠው ልጁን ሰለሞንን ነበር። ዳዊት ቤተ መቅደሱን ለመገንባት የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለሰለሞን ማዘጋጀት ጀመረ፤ እንዲህም አለ፦ ‘የይሖዋ ቤተ መቅደስ በጣም ውብ መሆን አለበት። ሰለሞን ገና ልጅ ነው፤ ስለዚህ የሚያስፈልገውን ነገር በማዘጋጀት እረዳዋለሁ።’ ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚሆን በጣም ብዙ ገንዘብ ሰጠ። እንዲሁም ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሠራተኞችን አዘጋጀለት። ወርቅና ብር አሰባሰበ፤ ከጢሮስና ከሲዶናም የአርዘ ሊባኖስ እንጨት አስመጣ። ዳዊት መሞቻው ሲቃረብ ለሰለሞን ቤተ መቅደሱ እንዴት እንደሚሠራ የሚያሳይ ንድፍ ሰጠው። እንዲህም አለው፦ ‘ይሖዋ እነዚህን ነገሮች በጽሑፍ እንዳሰፍርልህ ነግሮኛል። ይሖዋ ይረዳሃል። አትፍራ። ደፋር ሁን፤ ሥራውን በትጋት አከናውን።’
“የሠራውን በደል የሚሸፋፍን አይሳካለትም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ሁሉ ግን ምሕረት ያገኛል።”—ምሳሌ 28:13
-