የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የይሖዋ ቤተ መቅደስ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • እሳት ከሰማይ ወርዶ በመሠዊያው ላይ ያለውን መሥዋዕት ሲበላ

      ትምህርት 44

      የይሖዋ ቤተ መቅደስ

      ንጉሥ ሰለሞን ሲጸልይ

      ሰለሞን የእስራኤል ንጉሥ ከሆነ በኋላ ይሖዋ ‘ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?’ በማለት ጠየቀው። ሰለሞንም እንዲህ አለ፦ ‘እኔ ገና ልጅ ነኝ፤ ምን ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም። እባክህ ሕዝብህን መምራት እንድችል ጥበብ ስጠኝ።’ ከዚያም ይሖዋ እንዲህ አለው፦ ‘ጥበብ እንድሰጥህ ስለጠየቅክ በምድር ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ የበለጠ ጥበበኛ አደርግሃለሁ። ብዙ ሀብትም እሰጥሃለሁ። እኔን ከታዘዝክ ረጅም ዕድሜ ትኖራለህ።’

      ሰለሞን ቤተ መቅደሱን መገንባት ጀመረ። ምርጥ የሆነውን ወርቅ፣ ብር፣ እንጨትና ድንጋይ ተጠቅሞ ቤተ መቅደሱን ገነባ። በሺዎች የሚቆጠሩ ጥሩ ችሎታ ያላቸው ወንዶችና ሴቶች ቤተ መቅደሱን በመገንባቱ ሥራ ተካፍለዋል። ከሰባት ዓመት በኋላ ቤተ መቅደሱ ተሠርቶ አለቀ፤ ከዚያም ቤተ መቅደሱን ለይሖዋ ለመወሰን ዝግጅት ተደረገ። በዚያም መሠዊያ ይገኝ የነበረ ሲሆን ቤተ መቅደሱ ለይሖዋ በተወሰነበት ጊዜ መሠዊያው ላይ መሥዋዕት ቀርቦ ነበር። ሰለሞን በመሠዊያው ፊት ተንበርክኮ እንዲህ በማለት ጸለየ፦ ‘ይሖዋ ሆይ፣ የዚህ ቤተ መቅደስ መጠንም ሆነ ውበት ለአንተ በጣም ያንስሃል፤ ግን እባክህ አምልኳችንን ተቀበል፤ ጸሎታችንንም ስማ።’ ታዲያ ይሖዋ ሰለሞን የገነባውን ቤተ መቅደስም ሆነ ያቀረበውን ጸሎት ተቀብሎታል? ሰለሞን ጸሎቱን እንደጨረሰ እሳት ከሰማይ ወርዶ በመሠዊያው ላይ የቀረበውን መሥዋዕት አቃጠለ። ይሖዋ በዚህ መንገድ ቤተ መቅደሱን እንደተቀበለው አሳየ። እስራኤላውያንም ይህን ሲያዩ በጣም ተደሰቱ።

      እሳት ከሰማይ ወርዶ በመሠዊያው ላይ ያለውን መሥዋዕት ሲበላ

      በመላው እስራኤልም ሆነ ራቅ ብለው በሚገኙ ቦታዎች የነበሩ ሰዎች በንጉሥ ሰለሞን ጥበብ ይደነቁ ነበር። ሰዎች ችግር ሲገጥማቸው መፍትሔ ለማግኘት ወደ ሰለሞን ይመጡ ነበር። የሳባ ንግሥትም ከባድ ጥያቄዎች በመጠየቅ ልትፈትነው መጥታ ነበር። ለጥያቄዎቿ የሰጠውን መልስ ስትሰማ ግን እንዲህ አለች፦ ‘ሰዎች ስለ አንተ የነገሩኝን ነገር አላመንኩም ነበር፤ አሁን ግን እነሱ ከተናገሩትም በላይ ጥበበኛ እንደሆንክ አይቻለሁ። አምላክህ ይሖዋ ባርኮሃል።’ ሰለሞን ይገዛ በነበረበት ዘመን እስራኤላውያን አስደሳች ሕይወት ይኖሩ ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ ሁኔታዎች ተለወጡ።

      “ከሰለሞን የሚበልጥ እዚህ አለ።”—ማቴዎስ 12:42

      ጥያቄ፦ ይሖዋ ለሰለሞን ለየት ያለ ጥበብ የሰጠው ለምንድን ነው? ይሖዋ ቤተ መቅደሱን እንደተቀበለው ያሳየው እንዴት ነው?

      1 ነገሥት 2:12፤ 3:4-28፤ 4:29–5:18፤ 6:37, 38፤ 7:15–8:66፤ 10:1-13፤ 2 ዜና መዋዕል 7:1፤ 9:22

  • የእስራኤል መንግሥት ተከፈለ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • አኪያህ በኢዮርብዓም ፊት ልብሱን 12 ቦታ ሲቀደው

      ትምህርት 45

      የእስራኤል መንግሥት ተከፈለ

      ሰለሞን ይሖዋን ያመልክ በነበረበት ጊዜ ሁሉ በእስራኤል ውስጥ ሰላም ነበር። ሆኖም ሰለሞን ከተለያዩ አገሮች የመጡ ብዙ ሚስቶችን አገባ፤ እነዚህ ሴቶች ደግሞ ጣዖት ያመልኩ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሰለሞንም ጣዖት ማምለክ ጀመረ። ይሖዋ በዚህ በጣም ተናደደ። ስለዚህ ሰለሞንን እንዲህ አለው፦ ‘የእስራኤል መንግሥት ለሁለት ይከፈላል። ትልቁን ክፍል ከአንተ ቤተሰብ ላይ ወስጄ ከአገልጋዮችህ ለአንዱ እሰጠዋለሁ፤ የአንተ ቤተሰብ የሚገዛው ትንሹን ብቻ ይሆናል።’

      ይሖዋ ይህን ውሳኔውን በሌላ መንገድም ገለጸ። ከሰለሞን አገልጋዮች አንዱ የሆነው ኢዮርብዓም በመንገድ ላይ ሲሄድ ነቢዩ አኪያህን አገኘው። አኪያህም የራሱን ልብስ 12 ቦታ ቀደደና ኢዮርብዓምን እንዲህ አለው፦ ‘ይሖዋ የእስራኤልን መንግሥት ከሰለሞን ቤተሰብ ወስዶ ለሁለት ይከፍለዋል። አንተ በአሥር ነገዶች ላይ ንጉሥ ስለምትሆን አሥሩን ቁራጭ ውሰድ።’ ንጉሥ ሰለሞን ይህን ሲሰማ ኢዮርብዓምን ለመግደል ፈለገ! ስለዚህ ኢዮርብዓም ወደ ግብፅ ሸሸ። ከጊዜ በኋላ ሰለሞን ሞተና ልጁ ሮብዓም ነገሠ። በዚህ ጊዜ ኢዮርብዓም ወደ እስራኤል ቢመለስ ምንም ችግር እንደማያጋጥመው ተሰማው።

      እስራኤላውያን ኢዮርብዓም ላቆመው የወርቅ ጥጃ መሥዋዕት ሲያቀርቡ

      የእስራኤል ሽማግሌዎች ሮብዓምን ‘ለሕዝቡ መልካም ነገር የምታደርግ ከሆነ ለአንተ ታማኝ ይሆናሉ’ አሉት። ወጣት ጓደኞቹ ግን ‘ሕዝቡን በጭካኔ መግዛት አለብህ! እንዲያውም የበለጠ እንዲሠሩ አድርጋቸው!’ አሉት። ሮብዓም የወጣቶቹን ምክር ተቀበለ። ሕዝቡን በጭካኔ ይገዛ ጀመር፤ ስለዚህ አሥሩ የእስራኤል ነገዶች በሮብዓም ላይ ዓመፁ። ከዚያም ኢዮርብዓምን በአሥሩ ነገዶች ላይ ንጉሥ አደረጉት፤ ይህ የአሥሩ ነገድ መንግሥት የእስራኤል መንግሥት ተብሎ ይጠራ ጀመር። የቀሩት ሁለት ነገዶች መንግሥት ደግሞ የይሁዳ መንግሥት ተብሎ ይጠራ ጀመር፤ ሁለቱ ነገዶች ለሮብዓም ታማኝ ሆኑ። በዚህ መንገድ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ተከፈሉ።

      ኢዮርብዓም ሕዝቡ ለአምልኮ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ አልፈለገም፤ ምክንያቱም ኢየሩሳሌም የምትገኘው በሮብዓም ግዛት ውስጥ ነበር። ኢዮርብዓም ‘ሕዝቡ ወደዚያ ከሄደ በእኔ ላይ ዓምፆ ሮብዓምን ሊደግፍ ይችላል’ ብሎ አሰበ። ስለዚህ ሁለት የወርቅ ጥጃዎች ሠርቶ እስራኤላውያንን እንዲህ አላቸው፦ ‘ኢየሩሳሌም በጣም ይርቃችኋል። እዚሁ ማምለክ ትችላላችሁ።’ በመሆኑም ሕዝቡ እንደገና ይሖዋን ትቶ የወርቅ ጥጃዎቹን ማምለክ ጀመረ።

      “ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ። ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ኅብረት አለው? . . . ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ድርሻ አለው?”—2 ቆሮንቶስ 6:14, 15

      ጥያቄ፦ የእስራኤል መንግሥት የተከፈለው ለምን ነበር? ንጉሥ ሮብዓምና ንጉሥ ኢዮርብዓም ምን መጥፎ ነገሮችን ሠርተዋል?

      1 ነገሥት 11:1-13, 26-43፤ 12:1-33

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ