የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን አሳየ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • እሳት ከሰማይ ወርዶ የኤልያስን መሥዋዕት ሲበላ

      ትምህርት 46

      ይሖዋ እውነተኛ አምላክ መሆኑን አሳየ

      በአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ላይ የነገሡት ብዙዎቹ ነገሥታት ክፉዎች ነበሩ፤ ንጉሥ አክዓብ ደግሞ በጣም ክፉ ከነበሩት ነገሥታት አንዱ ነው። አክዓብ የባአል አምላኪ የሆነች አንዲት ክፉ ሴት አገባ። ስሟ ኤልዛቤል ይባላል። አክዓብና ኤልዛቤል በአገሪቱ ውስጥ የባአል አምልኮ እንዲስፋፋ አድርገዋል፤ እንዲሁም የይሖዋን ነቢያት ገድለዋል። ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? በነቢዩ ኤልያስ አማካኝነት ለአክዓብ መልእክት ላከ።

      ኤልያስ ንጉሥ አክዓብን ‘አንተ በፈጸምከው ክፋት የተነሳ በእስራኤል ምድር ዝናብ አይዘንብም’ አለው። በምድሪቱ ላይ እህል መብቀል ካቆመ ከሦስት ዓመት በላይ አልፏል፤ ስለዚህ ሕዝቡ ተራበ። በኋላም ይሖዋ በድጋሚ ኤልያስን ወደ አክዓብ ላከው። በዚህ ጊዜ ንጉሡ ኤልያስን ‘አንተ ችግር ፈጣሪ ነህ! ይህ ሁሉ ችግር የመጣው በአንተ ምክንያት ነው’ አለው። ኤልያስም እንዲህ አለ፦ ‘ይህ ድርቅ የመጣው በእኔ ምክንያት አይደለም። ድርቁ የመጣው አንተ ባአልን በማምለክህ ነው። አሁን እውነተኛው አምላክ ማን እንደሆነ ይታያል። ሕዝቡንና የባአልን ነቢያት በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ሰብስብ።’

      ሕዝቡ በተራራው ላይ ተሰበሰበ። ኤልያስም እንዲህ አለ፦ ‘አንዱን ምረጡ። እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ከሆነ እሱን ተከተሉ። እውነተኛው አምላክ ባአል ከሆነ ደግሞ እሱን ተከተሉ። አሁን 450ዎቹ የባአል ነቢያት መሥዋዕት ያዘጋጁና ወደ አምላካቸው ይጸልዩ፤ እኔም መሥዋዕት አዘጋጅቼ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ። እሳት በመላክ መልስ የሚሰጠው አምላክ እሱ እውነተኛው አምላክ ነው።’ ሕዝቡም በሐሳቡ ተስማማ።

      የባአል ነቢያት መሥዋዕት አዘጋጁ። ከዚያም ቀኑን ሙሉ ‘ባአል ሆይ፣ መልስልን!’ እያሉ ሲጮኹ ዋሉ። ባአል ምንም መልስ ሳይሰጥ ሲቀር ኤልያስ በባአል ማሾፍ ጀመረ። እንዲህ አለ፦ ‘ድምፃችሁን ከፍ አድርጋችሁ ጩኹ እንጂ። ተኝቶ ሊሆን ስለሚችል የሚቀሰቅሰው ያስፈልገው ይሆናል።’ የባአል ነቢያት እስከ ምሽት ድረስ መጣራታቸውን ቀጠሉ። ግን ምንም መልስ አልነበረም።

      ኤልያስ መሥዋዕቱን በመሠዊያው ላይ አስቀመጠና ውኃ አፈሰሰበት። ከዚያም ‘ይሖዋ ሆይ፣ እባክህ እውነተኛው አምላክ አንተ መሆንህን ለሕዝቡ አሳውቃቸው’ በማለት ጸለየ። ይሖዋም ወዲያውኑ ከሰማይ እሳት በመላክ መሥዋዕቱን አቃጠለው። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ‘እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ነው!’ በማለት ጮኸ። ከዚያም ኤልያስ ‘የባአል ነቢያት እንዳያመልጡ ያዟቸው!’ አለ። በዚያ ቀን 450ዎቹ የባአል ነቢያት ተገደሉ።

      ከባሕሩ በላይ ትንሽ ደመና ሲታይ ኤልያስ አክዓብን ‘ከባድ ዝናብ እየመጣ ነው። ሠረገላህን አዘጋጅና ወደ ቤት ሂድ’ አለው። ሰማዩ በደመና ጠቆረ፤ ነፋስም ነፈሰ፤ ከባድ ዝናብም መጣል ጀመረ። በመጨረሻ የድርቁ ወቅት አበቃ። አክዓብ ሠረገላውን በፍጥነት እየነዳ ሄደ። ኤልያስ ግን እየሮጠ በይሖዋ እርዳታ ከሠረገላው ቀድሞ ሄደ! ታዲያ የኤልያስ ችግር ሙሉ በሙሉ ተወገደ ማለት ነው? እስቲ እንመልከት።

      “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ።”—መዝሙር 83:18

      ጥያቄ፦ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ምን ተከናወነ? ይሖዋ የኤልያስን ጸሎት የመለሰው እንዴት ነው?

      1 ነገሥት 16:29-33፤ 17:1፤ 18:1, 2, 17-46፤ ያዕቆብ 5:16-18

  • ይሖዋ ኤልያስን አበረታታው
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ኤልያስ በኮሬብ ተራራ ላይ ከዋሻው ውጭ ሆኖ የአምላክን መልአክ ሲሰማ

      ትምህርት 47

      ይሖዋ ኤልያስን አበረታታው

      ኤልዛቤል በባአል ነቢያት ላይ የደረሰውን ነገር ስትሰማ በጣም ተናደደች። ከዚያም ‘ነገ አንተም እንደነዚያ የባአል ነቢያት ትገደላለህ’ ብሎ ለኤልያስ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከችበት። ኤልያስ በጣም ስለፈራ ወደ በረሃ ሸሸ። ከዚያም ‘ይሖዋ፣ አሁንስ በቅቶኛል። ብሞት ይሻለኛል’ በማለት ወደ ይሖዋ ጸለየ። ኤልያስ በጣም ስለደከመው አንድ ዛፍ ሥር ተኛ።

      ከዚያም አንድ መልአክ ቀሰቀሰውና ‘ተነስና ብላ’ አለው። ኤልያስም በጋሉ ድንጋዮች ላይ የተቀመጠ ዳቦና ውኃ የያዘ ዕቃ አየ። ከበላና ከጠጣ በኋላ ተመልሶ ተኛ። መልአኩ በድጋሚ ቀሰቀሰውና ‘ብላ። ረጅም መንገድ ስለምትሄድ ኃይል ይሰጥሃል’ አለው። ስለዚህ ኤልያስ እንደገና በላ። ከዚያም 40 ቀንና 40 ሌሊት ተጉዞ ወደ ኮሬብ ተራራ ደረሰ። በዚያም ኤልያስ አንድ ዋሻ ውስጥ ገብቶ ተኛ። ከዚያም ይሖዋ አነጋገረው። ‘ኤልያስ፣ እዚህ ምን ታደርጋለህ?’ አለው። ኤልያስም እንዲህ በማለት መለሰ፦ ‘እስራኤላውያን ለአንተ የገቡትን ቃል ትተዋል። መሠዊያዎችህን አፍርሰዋል፤ ነቢያትህንም ገድለዋል። አሁን ደግሞ እኔንም ሊገድሉኝ ይፈልጋሉ።’

      ይሖዋም ‘ውጣና ተራራው ላይ ቁም’ አለው። በመጀመሪያ ኃይለኛ ነፋስ ነፈሰ። ከዚያም የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ፤ በኋላም እሳት ተነሳ። በመጨረሻ ኤልያስ ዝግ ያለና ለስለስ ያለ ድምፅ ሰማ። በዚህ ጊዜ ኤልያስ ፊቱን በልብሱ ሸፍኖ ከዋሻው ውጭ ቆመ። ከዚያም ይሖዋ ኤልያስ የሸሸው ለምን እንደሆነ ጠየቀው። ኤልያስም ‘የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ’ አለው። ይሖዋ ግን እንዲህ አለው፦ ‘ብቻህን አይደለህም። በእስራኤል ውስጥ እኔን የሚያመልኩ 7,000 ሰዎች አሉ። ሂድና ኤልሳዕን በአንተ ፋንታ ነቢይ እንዲሆን ሹመው።’ ኤልያስ ወዲያውኑ ሄዶ ይሖዋ ያዘዘውን አደረገ። ይሖዋ እንድታደርግ የሚፈልግብህን ነገር ስታደርግ ይሖዋ አንተንም እንደሚረዳህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። እስቲ ቀጥሎ ደግሞ በድርቁ ወቅት የተፈጸመ አንድ ሁኔታ እንመልከት።

      “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ።”—ፊልጵስዩስ 4:6

      ጥያቄ፦ ኤልያስ የሸሸው ለምንድን ነው? ይሖዋ ኤልያስን ምን አለው?

      1 ነገሥት 19:1-18፤ ሮም 11:2-4

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ