-
የአንዲት ድሃ ሴት ልጅ ከሞት ተነሳከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 48
የአንዲት ድሃ ሴት ልጅ ከሞት ተነሳ
በድርቁ ወቅት ይሖዋ ኤልያስን እንዲህ አለው፦ ‘ወደ ሰራፕታ ሂድ። በዚያ የምትኖር አንዲት ባሏ የሞተባት ሴት ምግብ ትሰጥሃለች።’ ኤልያስ ወደ ከተማዋ መግቢያ እንደደረሰ ይሖዋ በነገረው መሠረት አንዲት ድሃ ሴት እንጨት ስትለቅም አየ። ከዚያም የሚጠጣው ውኃ እንድትሰጠው ጠየቃት። ውኃ ለማምጣት ስትሄድ ድጋሚ ጠራትና ‘እባክሽ ቁራሽ ዳቦም ይዘሽልኝ ነይ’ አላት። ሴትየዋ ግን ‘የምሰጥህ ዳቦ የለኝም። እንዳልጋግርልህ እንኳ ያለኝ ዱቄትና ዘይት ለእኔና ለልጄ ትንሽ ዳቦ ለመጋገር ብቻ የሚበቃ ነው’ አለችው። ኤልያስም ‘ለእኔ ዳቦ ከጋገርሽልኝ ዳግመኛ ዝናብ እስኪዘንብ ድረስ ዱቄቱና ዘይቱ እንደማያልቅ ይሖዋ ተናግሯል’ አላት።
ስለዚህ ሴትየዋ ወደ ቤት ገብታ ለይሖዋ ነቢይ ዳቦ ጋገረችለት። ልክ ይሖዋ ቃል እንደገባው በድርቁ ወቅት ሴትየዋና ልጇ የሚበሉት ምግብ አላጡም። ዱቄቱም ሆነ ዘይቱ አላለቀም።
ከዚያም አንድ በጣም የሚያሳዝን ነገር ተፈጠረ። የሴትየዋ ልጅ በጣም ታመመና ሞተ። እሷም ኤልያስን እንዲረዳት ለመነችው። ኤልያስም ትንሹን ልጅ ከእሷ ተቀብሎ በሰገነቱ ላይ ወዳለ ክፍል ወሰደው። ከዚያም አልጋ ላይ አስተኛውና ‘ይሖዋ፣ እባክህ ይህን ልጅ አስነሳው’ በማለት ጸለየ። ይሖዋ ልጁን ከሞት ቢያስነሳው በጣም አስደናቂ ተአምር ይሆናል። ምክንያቱም እስከምናውቀው ድረስ ከዚያ በፊት ማንም ሰው ከሞት ተነስቶ አያውቅም። በተጨማሪም ይህች ሴትና ልጇ እስራኤላውያን አልነበሩም።
ሆኖም የልጁ ሕይወት ተመለሰለትና መተንፈስ ጀመረ! ኤልያስም ሴትየዋን ‘ይኸው! ልጅሽ ተነስቷል’ አላት። እሷም በጣም ተደስታ ኤልያስን እንዲህ አለችው፦ ‘አንተ በእርግጥም የአምላክ ሰው ነህ። ምክንያቱም የምትናገረው ይሖዋ እንድትናገር ያዘዘህን ነገር ብቻ ነው፤ የተናገርከውም ነገር ሁልጊዜ ይፈጸማል።’
“ቁራዎችን ተመልከቱ፦ አይዘሩም፣ አያጭዱም እንዲሁም የእህል ማከማቻ ወይም ጎተራ የላቸውም፤ ሆኖም አምላክ ይመግባቸዋል። ታዲያ እናንተ ከወፎች እጅግ የላቀ ዋጋ የላችሁም?”—ሉቃስ 12:24
-
-
ክፉዋ ንግሥት ተቀጣችከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 49
ክፉዋ ንግሥት ተቀጣች
በኢይዝራኤል ከሚገኘው የንጉሥ አክዓብ ቤተ መንግሥት አጠገብ ናቡቴ የተባለ ሰው የወይን እርሻ ይገኝ ነበር። አክዓብ ይህን የወይን እርሻ የራሱ ማድረግ ስለፈለገ እርሻውን እንዲሸጥለት ናቡቴን ጠየቀው። ሆኖም የይሖዋ ሕግ በውርስ የተላለፈ መሬት እንዳይሸጥ ይከለክል ስለነበር ናቡቴ እርሻውን ለመሸጥ ፈቃደኛ አልሆነም። ናቡቴ ትክክለኛውን ነገር በማድረጉ አክዓብ ናቡቴን አመሰገነው? በፍጹም። አክዓብ በጣም ተናደደ። ከመበሳጨቱም የተነሳ አኩርፎ ተኛ፤ ምግብ ለመብላትም ፈቃደኛ አልሆነም።
የአክዓብ ሚስት የሆነችው ክፉዋ ንግሥት ኤልዛቤል አክዓብን እንዲህ አለችው፦ ‘አንተ እኮ የእስራኤል ንጉሥ ነህ። የፈለግከውን ነገር ማግኘት ትችላለህ። ያንን መሬት እኔ እሰጥሃለሁ።’ ከዚያም ለከተማዋ ሽማግሌዎች ደብዳቤ በመጻፍ ናቡቴን ‘አምላክን ሰድቧል’ ብለው እንዲከሱትና በድንጋይ ወግረው እንዲገድሉት ነገረቻቸው። ሽማግሌዎቹም ኤልዛቤል እንደነገረቻቸው አደረጉ፤ ከዚያም ኤልዛቤል አክዓብን ‘ናቡቴ ሞቷል። አሁን የወይን እርሻውን መውሰድ ትችላለህ’ አለችው።
ኤልዛቤል ያስገደለችው ናቡቴን ብቻ አልነበረም። ይሖዋን የሚወዱ ሌሎች ብዙ ሰዎችንም አስገድላለች። ጣዖት ታመልክ እንዲሁም ብዙ መጥፎ ነገሮች ታደርግ ነበር። ይሖዋ ኤልዛቤል ያደረገችውን መጥፎ ነገር በሙሉ አይቷል። ታዲያ ምን ያደርጋት ይሆን?
አክዓብ ከሞተ በኋላ ልጁ ኢዮራም ነገሠ። ይሖዋም ኤልዛቤልንና ቤተሰቧን እንዲቀጣ ኢዩ የተባለ ሰው ላከ።
ኢዩ ሠረገላውን እየነዳ ኤልዛቤል ወደምትኖርበት ወደ ኢይዝራኤል ሄደ። ኢዮራምም ሠረገላው ላይ ተቀምጦ ኢዩን ለማግኘት ወጣ፤ ከዚያም ኢዩን ‘የመጣኸው በሰላም ነው?’ ብሎ ጠየቀው። ኢዩም ‘እናትህ ኤልዛቤል ክፉ ነገር ማድረጓን እስካልተወች ድረስ ምንም ሰላም የለም’ አለው። ኢዮራም ይህን ሲሰማ ሠረገላውን አዙሮ ለማምለጥ ሞከረ። ሆኖም ኢዩ በቀስት ስለወጋው ኢዮራም ሞተ።
ከዚያም ኢዩ ወደ ኤልዛቤል ቤተ መንግሥት ሄደ። ኤልዛቤልም ኢዩ እየመጣ መሆኑን ስትሰማ ተኳኩላና ፀጉሯን አሰማምራ ፎቅ ላይ ባለው መስኮት በኩል ትመለከት ጀመር። ኢዩ ሲደርስ ኤልዛቤል በንቀት አናገረችው። ኢዩም ከእሷ ጎን ቆመው የነበሩትን አገልጋዮቿን ‘ወደ ታች ወርውሯት!’ አላቸው። እነሱም ኤልዛቤልን በመስኮት ወረወሯት፤ እሷም መሬት ላይ ወድቃ ሞተች።
ከዚያ በኋላ ኢዩ የአክዓብን 70 ወንዶች ልጆች አስገደለ፤ እንዲሁም የባአልን አምልኮ ከምድሪቱ ላይ አስወገደ። ይሖዋ ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅና መጥፎ ነገር የሚሠሩ ሰዎችን በተገቢው ጊዜ እንደሚቀጣቸው አስተዋልክ?
“በመጀመሪያ በስግብግብነት የተገኘ ውርስ፣ የኋላ ኋላ በረከት አይሆንም።”—ምሳሌ 20:21
-