የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የይሖዋ የእሳት ፈረሶችና የጦር ሠረገሎች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ኤልሳዕና አገልጋዩ በሶርያ ሠራዊት ተከብበው

      ትምህርት 52

      የይሖዋ የእሳት ፈረሶችና የጦር ሠረገሎች

      የሶርያ ንጉሥ ቤንሃዳድ በእስራኤል ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ይሰነዝር ነበር። ሆኖም ጥቃት በሚሰነዝርበት ጊዜ ሁሉ ነቢዩ ኤልሳዕ የእስራኤልን ንጉሥ አስቀድሞ ያስጠነቅቀው ስለነበር ከጥቃቱ ያመልጥ ነበር። ስለዚህ ቤንሃዳድ ኤልሳዕን ለመያዝ ወሰነ። ኤልሳዕ ዶታን የሚባል ከተማ ውስጥ እንዳለ ስለሰማ እሱን ለመያዝ የሶርያን ሠራዊት ወደዚያ ላከ።

      ሶርያውያን ሌሊት ላይ ዶታን ደረሱ። በቀጣዩ ቀን ጠዋት የኤልሳዕ አገልጋይ ወደ ውጭ ሲወጣ ከተማዋ በብዙ ሠራዊት እንደተከበበች አየ። እሱም በጣም ስለፈራ ‘ኤልሳዕ፣ ምን ብናደርግ ይሻላል?’ በማለት ጮኸ። ኤልሳዕም ‘ከእነሱ ጋር ካሉት ከእኛ ጋር ያሉት ይበልጣሉ’ አለው። ወዲያውኑም ይሖዋ የኤልሳዕ አገልጋይ በከተማዋ ዙሪያ ያሉት ተራሮች በሙሉ በእሳት ፈረሶችና የጦር ሠረገሎች እንደተሞሉ እንዲያይ አደረገው።

      ኤልሳዕና አገልጋዩ በዙሪያቸው ያለውን የመላእክት ሠራዊት ሲያዩ

      የሶርያ ወታደሮች ኤልሳዕን ለመያዝ ሲሞክሩ ኤልሳዕ ‘እባክህ ይሖዋ እነዚህን ሰዎች አሳውራቸው’ በማለት ጸለየ። በዚህ ጊዜ ዓይናቸው ማየት ቢችልም እንኳ የት እንዳሉ ግራ ገባቸው። ኤልሳዕ ወታደሮቹን እንዲህ አላቸው፦ ‘የመጣችሁት ወደተሳሳተ ቦታ ነው። ተከተሉኝና ወደምትፈልጉት ሰው እወስዳችኋለሁ።’ እነሱም ኤልሳዕን ተከትለው የእስራኤል ንጉሥ እስከሚኖርባት እስከ ሰማርያ ድረስ ሄዱ።

      ሶርያውያኑ የት እንዳሉ የገባቸው ሰማርያ ውስጥ ከገቡ በኋላ ነበር። የእስራኤል ንጉሥም ‘ልግደላቸው?’ በማለት ኤልሳዕን ጠየቀው። ኤልሳዕ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ሊጎዱት ሞክረው የነበሩትን ሰዎች ይበቀል ይሆን? በፍጹም። ኤልሳዕ እንዲህ አለ፦ ‘አትግደላቸው። የሚበሉት ምግብ ስጣቸውና አሰናብታቸው።’ ስለዚህ ንጉሡ ትልቅ ድግስ አዘጋጅቶላቸው ከበሉና ከጠጡ በኋላ ወደ ቤታቸው ሄዱ።

      የሶርያ ወታደሮች ሰማርያ ውስጥ ምግብ ሲበሉ

      “በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።”—1 ዮሐንስ 5:14

      ጥያቄ፦ ይሖዋ ኤልሳዕንና አገልጋዩን የጠበቃቸው እንዴት ነው? ይሖዋ አንተንም ሊጠብቅህ እንደሚችል ይሰማሃል?

      2 ነገሥት 6:8-24

  • ዮዳሄ ያሳየው ድፍረት
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ ትንሹን ንጉሥ ኢዮዓስን በሕዝቡ ፊት ሲያቀርበው

      ትምህርት 53

      ዮዳሄ ያሳየው ድፍረት

      ኤልዛቤል ጎቶልያ የምትባል ልጅ ነበረቻት፤ ጎቶልያ ልክ እንደ እናቷ ክፉ ነበረች። ጎቶልያ የይሁዳን ንጉሥ አግብታ ነበር። ባሏ ሲሞት ወንድ ልጇ በአባቱ ምትክ መግዛት ጀመረ። ልጇ ሲሞት ግን ጎቶልያ ራሷ ይሁዳን መግዛት ጀመረች። ከዚያም ሌላ ሰው ሥልጣኑን እንዳይወስድባት ስትል የራሷን የልጅ ልጆች ጨምሮ የንጉሣውያኑን ቤተሰብ በሙሉ ለማስገደል ሞከረች። በዚህም የተነሳ ሰው ሁሉ ይፈራት ነበር።

      ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄና ሚስቱ የሆሼባ፣ ጎቶልያ የምታደርገው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ተገንዝበው ነበር። ስለዚህ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ከጎቶልያ የልጅ ልጆች አንዱ የሆነውን ኢዮዓስ የተባለውን ሕፃን ደብቀው ወሰዱት። ከዚያም በቤተ መቅደሱ ውስጥ አሳደጉት።

      ኢዮዓስ ሰባት ዓመት ሲሆነው ዮዳሄ መቶ አለቆቹንና ሌዋውያኑን በሙሉ በመሰብሰብ ‘የቤተ መቅደሱን በሮች ጠብቁ፤ ማንንም እንዳታስገቡ’ አላቸው። ከዚያም ዮዳሄ ኢዮዓስን የይሁዳ ንጉሥ አድርጎ ሾመው፤ በራሱም ላይ ዘውድ አደረገለት። የይሁዳ ሰዎችም ‘ንጉሡ ለዘላለም ይኑር!’ ብለው ጮኹ።

      ንግሥት ጎቶልያ ስትጮኽ

      ንግሥት ጎቶልያ የሕዝቡን ጩኸት ስትሰማ በፍጥነት ወደ ቤተ መቅደሱ መጣች። አዲሱን ንጉሥ ስታይ ‘ይህ ተንኮል ነው! ተንኮል ነው!’ ብላ ጮኸች። ከዚያም መቶ አለቆቹ ይህችን ክፉ ንግሥት ይዘው አወጧትና ገደሏት። በሕዝቡ ላይ ያሳደረችው መጥፎ ተጽዕኖስ ይወገድ ይሆን?

      ዮዳሄ ሕዝቡ ‘ይሖዋን ብቻ እናመልካለን’ ብለው ለይሖዋ ቃል እንዲገቡ አደረገ። እንዲሁም የባአልን ቤተ መቅደስ እንዲያፈርሱና ጣዖታቱን እንዲሰባብሩ አደረገ። በተጨማሪም ሕዝቡ በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ በድጋሚ ይሖዋን ማምለክ እንዲችሉ በዚያ የሚያገለግሉ ካህናትንና ሌዋውያንን ሾመ። የረከሰ ሰው ወደ ቤተ መቅደሱ እንዳይገባ የሚከላከሉ በር ጠባቂዎችንም መደበ። ከዚያም ዮዳሄና መቶ አለቆቹ ኢዮዓስን ወደ ቤተ መንግሥቱ ወስደው ዙፋን ላይ አስቀመጡት። የይሁዳ ሰዎች በጣም ተደሰቱ። በመጨረሻ ክፉዋ ንግሥት ጎቶልያ በመገደሏና የባአል አምልኮ በመወገዱ ይሖዋን በነፃነት ማገልገል ቻሉ። በእርግጥም ዮዳሄ በድፍረት የወሰደው እርምጃ ብዙ ሰዎችን ጠቅሟል።

      “ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ከዚህ ይልቅ ነፍስንም ሆነ ሥጋን በገሃነም ሊያጠፋ የሚችለውን ፍሩ።”—ማቴዎስ 10:28

      ጥያቄ፦ ዮዳሄ ድፍረት ያሳየው እንዴት ነው? ይሖዋ አንተንም ደፋር እንድትሆን ሊረዳህ የሚችል ይመስልሃል?

      2 ነገሥት 11:1–12:12፤ 2 ዜና መዋዕል 21:1-6፤ 22:10–24:16

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ