-
ይሖዋ ዮናስን በትዕግሥት አስተማረውከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 54
ይሖዋ ዮናስን በትዕግሥት አስተማረው
የአሦር ከተማ በሆነችው በነነዌ የሚኖሩት ሰዎች በጣም ክፉዎች ነበሩ። ይሖዋ ነቢዩ ዮናስን ‘ወደ ነነዌ ሰዎች ሄደህ ክፉ ሥራችሁን ተዉ ብለህ ንገራቸው’ ብሎ አዘዘው። ዮናስ ግን ወደ ነነዌ መሄድ ሲገባው አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ተርሴስ የሚሄድ መርከብ ላይ ተሳፈረ።
መርከቡ በባሕሩ ላይ እየሄደ ሳለ ከባድ ማዕበል ስለተነሳ መርከበኞቹ በጣም ፈሩ። በመሆኑም ‘ይህ የደረሰብን ለምንድን ነው?’ ብለው ወደ አምላኮቻቸው ጸለዩ። በመጨረሻም ዮናስ እንዲህ አላቸው፦ ‘ይህ የደረሰባችሁ በእኔ ምክንያት ነው። እኔ ይሖዋ ያዘዘኝን ነገር ትቼ ወደ ሌላ ቦታ እየሄድኩ ነው። እኔን ወደ ባሕሩ ከጣላችሁኝ ማዕበሉ ይቆማል።’ መርከበኞቹ ዮናስን ሊጥሉት አልፈለጉም፤ ዮናስ ግን እንዲጥሉት በተደጋጋሚ ነገራቸው። ከዚያም ዮናስን ወደ ባሕሩ ሲወረውሩት ማዕበሉ ቆመ።
ዮናስ የሚሞት መስሎት ነበር። ባሕሩ ውስጥ እየሰመጠ ሲሄድ ወደ ይሖዋ ጸለየ። ይሖዋም አንድ ትልቅ ዓሣ ላከለት። ዓሣው ዮናስን ዋጠው፤ ዮናስ ግን አልሞተም። ዮናስ በዓሣው ውስጥ ሆኖ ‘ከዚህ በኋላ ሁልጊዜ አንተን እታዘዛለሁ’ በማለት ወደ ይሖዋ ጸለየ። ይሖዋም ዮናስን ለሦስት ቀናት ዓሣው ውስጥ አቆየው፤ ከዚያም ዓሣው ዮናስን ደረቅ ምድር ላይ እንዲተፋው አደረገ።
ዮናስ ከባሕሩ ከወጣ በኋላ ይሖዋ ወደ ነነዌ እንዲሄድ በድጋሚ አዘዘው። በዚህ ጊዜ ግን ዮናስ የተባለውን አደረገ። ወደ ነነዌ ሄዶ እነዚያን ክፉ ሰዎች ‘ነነዌ በ40 ቀን ውስጥ ትጠፋለች’ አላቸው። ከዚያም አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ፤ የነነዌ ሰዎች የዮናስን መልእክት ሰምተው ክፉ ነገር መሥራት አቆሙ። የነነዌ ንጉሥ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ ‘ወደ አምላክ ጸልዩ፤ ንስሐም ግቡ። ምናልባት ምሕረት ያደርግልን ይሆናል።’ ይሖዋ የነነዌ ሰዎች ንስሐ መግባታቸውን ሲያይ ነነዌን ሳያጠፋት ቀረ።
ዮናስ ከተማዋ ስላልጠፋች በጣም ተበሳጨ። እስቲ አስበው፦ ይሖዋ ለዮናስ ትዕግሥትና ምሕረት አሳይቶታል፤ ዮናስ ግን የነነዌ ሰዎች ምሕረት እንዲደረግላቸው አልፈለገም። በመሆኑም ከከተማዋ ወጣና በአንዲት የቅል ተክል ጥላ ሥር አኩርፎ ተቀመጠ። ከዚያም የቅል ተክሏ ደረቀች፤ በዚህ ጊዜ ዮናስ በጣም ተናደደ። ስለዚህ ይሖዋ እንዲህ አለው፦ ‘አንተ ይህች ተክል ስለደረቀች አዘንክ። እኔስ በነነዌ ለሚኖሩ ሰዎች ማዘን የለብኝም? ንስሐ ስለገቡ አላጠፋኋቸውም።’ ይሖዋ ዮናስን ሊያስተምረው የፈለገው ነገር ምን ነበር? በነነዌ የሚኖሩ ሰዎች ሕይወት ከየትኛውም ተክል የበለጠ ዋጋ እንዳለው ሊያስተምረው ፈልጎ ነበር።
“ይሖዋ . . . እናንተን የታገሠው፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ ስለማይፈልግ ነው።”—2 ጴጥሮስ 3:9
-
-
የይሖዋ መልአክ ሕዝቅያስን አዳነውከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 55
የይሖዋ መልአክ ሕዝቅያስን አዳነው
የአሦር መንግሥት ከአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ጋር ተዋግቶ በማሸነፍ እስራኤላውያንን መግዛት ጀመረ። አሁን ደግሞ የአሦር ንጉሥ የሆነው ሰናክሬም የሁለቱን ነገድ የይሁዳ መንግሥት በማሸነፍ አይሁዳውያንንም መግዛት ፈለገ። በመሆኑም የይሁዳን ከተሞች አንድ በአንድ መውሰድ ጀመረ። ሆኖም በዋነኝነት መያዝ የፈለገው ኢየሩሳሌምን ነው። ሰናክሬም ይሖዋ ኢየሩሳሌምን እንደሚጠብቃት አላወቀም ነበር።
የይሁዳ ንጉሥ የሆነው ሕዝቅያስ፣ ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን እንዳይወጋ ለማድረግ ሲል ብዙ ገንዘብ ሰጠው። ሰናክሬም ግን ገንዘቡን የወሰደ ቢሆንም እንኳ ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ ኃይለኛ የሆኑትን ወታደሮቹን ላከ። አሦራውያኑ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጠጉ ሲመጡ የከተማዋ ነዋሪዎች በጣም ፈሩ። በዚህ ጊዜ ሕዝቅያስ እንዲህ አላቸው፦ ‘አትፍሩ። አሦራውያን ኃይለኛ ተዋጊዎች ቢሆኑም እንኳ ይሖዋ እኛን ከእነሱ የበለጠ ኃይለኛ ሊያደርገን ይችላል።’
ሰናክሬም መልእክተኛውን ራብሻቁን ወደ ኢየሩሳሌም በመላክ በሕዝቡ ላይ እንዲያሾፍባቸው አደረገ። ራብሻቁ ከከተማዋ ውጭ ቆሞ እንዲህ በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ፦ ‘ይሖዋ ሊረዳችሁ አይችልም። ሕዝቅያስ አያታላችሁ። እናንተን ከእኛ ሊያድናችሁ የሚችል አምላክ የለም።’
ሕዝቅያስ ምን ማድረግ እንዳለበት ይሖዋን ጠየቀ። ይሖዋም እንዲህ ብሎ መለሰለት፦ ‘ራብሻቁ የተናገረው ነገር ሊያስፈራህ አይገባም። ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን መያዝ አይችልም።’ ከዚያም ሰናክሬም ለሕዝቅያስ ደብዳቤ ላከለት። ደብዳቤው እንዲህ የሚል ነበር፦ ‘እጅ ብትሰጥ ይሻልሃል። ይሖዋ ሊያድንህ አይችልም።’ ሕዝቅያስ እንዲህ በማለት ጸለየ፦ ‘ይሖዋ ሆይ፣ ሰዎች ሁሉ አንተ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆንህን እንዲያውቁ ስትል እባክህ አድነን።’ ይሖዋም እንዲህ አለው፦ ‘የአሦር ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም አይገባም። ኢየሩሳሌምን እኔ ራሴ አድናታለሁ።’
ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን እንደሚይዛት እርግጠኛ ሆኖ ነበር። ሆኖም ሌሊት ላይ ይሖዋ የአሦር ወታደሮች ወደሰፈሩበት ከከተማዋ ውጭ ወደሚገኝ ቦታ መልአኩን ላከ። መልአኩ 185,000 ወታደሮችን ገደለ! ንጉሥ ሰናክሬም ኃይለኛ የሆኑት ወታደሮቹ ተገደሉበት። ስለዚህ በደረሰበት ሽንፈት አፍሮ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ሕዝቅያስንና ኢየሩሳሌምን አዳነ። አንተ በዚያ ወቅት ኢየሩሳሌም ውስጥ ብትኖር ኖሮ በይሖዋ ትታመን ነበር?
“የይሖዋ መልአክ በሚፈሩት ዙሪያ ይሰፍራል፤ ደግሞም ይታደጋቸዋል።”—መዝሙር 34:7
-