የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ኢየሩሳሌም ጠፋች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ኢየሩሳሌምና ቤተ መቅደሱ ሲቃጠሉ

      ትምህርት 58

      ኢየሩሳሌም ጠፋች

      የይሁዳ ሰዎች በተደጋጋሚ ይሖዋን ትተው የሐሰት አማልክትን ያመልኩ ነበር። ለብዙ ዓመታት ይሖዋ እነሱን ለመርዳት ሞክሮ ነበር። አይሁዳውያንን እንዲያስጠነቅቋቸው በርካታ ነቢያትን ልኮ የነበረ ቢሆንም እነሱ ግን ነቢያቱ የነገሯቸውን አልሰሙም። እንዲያውም በነቢያቱ ላይ ያሾፉባቸው ነበር። ታዲያ ይሖዋ የይሁዳ ሰዎች ጣዖት ማምለካቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ምን እርምጃ ወስዶ ይሆን?

      የባቢሎን ንጉሥ የሆነው ናቡከደነጾር ብዙ አገሮችን ድል አድርጎ ነበር። ኢየሩሳሌምን ለመጀመሪያ ጊዜ ድል ባደረገበት ወቅት ንጉሥ ዮአኪንን፣ መኳንንቱን፣ ተዋጊዎቹንና የእጅ ጥበብ ባለሙያዎቹን በሙሉ ይዞ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው። በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚገኙትንም ውድ ዕቃዎች በሙሉ ወሰደ። ከዚያም ናቡከደነጾር ሴዴቅያስን የይሁዳ ንጉሥ አደረገው።

      ሴዴቅያስ መጀመሪያ ላይ ናቡከደነጾርን ይታዘዝ ነበር። ሆኖም በአካባቢው የሚኖሩ ሕዝቦችና ሐሰተኛ ነቢያቱ ሴዴቅያስን በባቢሎን ላይ እንዲያምፅ መከሩት። ኤርምያስ ግን ‘በባቢሎን ላይ ካመፅክ በይሁዳ ውስጥ ግድያ፣ ረሃብና በሽታ ይኖራል’ በማለት አስጠነቀቀው።

      ሴዴቅያስ ለስምንት ዓመት ያህል ንጉሥ ሆኖ ከገዛ በኋላ በባቢሎን ላይ ዓመፀ። የግብፅ ንጉሥ እንዲረዳው ጠየቀ። ከዚያም ናቡከደነጾር ኢየሩሳሌምን እንዲወጉ ወታደሮቹን ላከ፤ ወታደሮቹም ኢየሩሳሌምን ከበቧት። ኤርምያስም ሴዴቅያስን እንዲህ አለው፦ ‘ይሖዋ “ለባቢሎን እጅህን ከሰጠህ አንተም ሆንክ ከተማዋ ትተርፋላችሁ” ብሏል። እጅ ካልሰጠህ ግን ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ያቃጥሏታል፤ አንተንም ይወስዱሃል።’ ሴዴቅያስ ግን እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።

      ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ የባቢሎን ወታደሮች የኢየሩሳሌምን አጥር አፍርሰው በመግባት ከተማዋን በእሳት አቃጠሏት። ቤተ መቅደሱን አቃጠሉ፤ ብዙ ሰዎችን ገደሉ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እስረኛ አድርገው ወሰዱ።

      ሴዴቅያስ ከኢየሩሳሌም አመለጠ፤ ሆኖም ባቢሎናውያን አሳደዱት። ኢያሪኮ አካባቢ ሲደርስ ያዙትና ወደ ናቡከደነጾር አመጡት። የባቢሎን ንጉሥ፣ ሴዴቅያስ ዓይኑ እያየ ልጆቹ እንዲገደሉ አደረገ። ከዚያም ናቡከደነጾር የሴዴቅያስን ዓይኖች አሳወረና እስር ቤት አስገባው፤ ሴዴቅያስም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ እስር ቤት ውስጥ ሞተ። ይሖዋ ግን ለይሁዳ ሰዎች ‘ከ70 ዓመት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም እንድትመለሱ አደርጋለሁ’ በማለት ቃል ገባላቸው።

      ታዲያ ወደ ባቢሎን የተወሰዱት ወጣቶች ምን ይገጥማቸው ይሆን? ይሖዋን በታማኝነት ማምለካቸውን ይቀጥሉ ይሆን?

      “ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ አምላክ ሆይ፣ ፍርድህ ሁሉ እውነትና ጽድቅ ነው።”—ራእይ 16:7

      ጥያቄ፦ ናቡከደነጾር ማን ነበር? ኢየሩሳሌምን ምን አደረጋት? ሴዴቅያስ ማን ነበር?

      2 ነገሥት 24:1, 2, 8-20፤ 25:1-24፤ 2 ዜና መዋዕል 36:6-21፤ ኤርምያስ 27:12-14፤ 29:10, 11፤ 38:14-23፤ 39:1-9፤ ሕዝቅኤል 21:27

  • ይሖዋን የታዘዙ አራት ልጆች
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ዳንኤል፣ ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ የንጉሡን ምግብ ለመብላት ፈቃደኞች አልሆኑም

      ትምህርት 59

      ይሖዋን የታዘዙ አራት ልጆች

      ናቡከደነጾር ከንጉሡና ከመሳፍንቱ ዘር የሆኑትን አይሁዳውያን ወደ ባቢሎን ከወሰዳቸው በኋላ አሽፈኔዝ የተባለውን የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን በእነሱ ላይ ኃላፊ አድርጎ ሾመው። ናቡከደነጾር አሽፈኔዝን ወደ ባቢሎን ከመጡት ወጣቶች መካከል ይበልጥ ጤናማና ጎበዝ የሆኑትን እንዲመርጥ አዘዘው። እነዚህ ወጣቶች በባቢሎን ውስጥ ባለሥልጣን እንዲሆኑ ለሦስት ዓመት ያህል ሥልጠና ይሰጣቸዋል። ወጣቶቹ የባቢሎንን ቋንቋ ማንበብ፣ መጻፍና መናገር እንዲችሉ መማር ነበረባቸው። እንዲሁም ንጉሡና መኳንንቱ የሚበሉትን ዓይነት ምግብ መብላት ይጠበቅባቸው ነበር። ከእነዚህ ልጆች መካከል አራቱ ዳንኤል፣ ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ነበሩ። አሽፈኔዝ ለእነዚህ ልጆች ብልጣሶር፣ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎ በማለት ባቢሎናውያን የሚጠሩበት ዓይነት ስም አወጣላቸው። ታዲያ እነዚህ ልጆች የባቢሎናውያንን ትምህርት መማራቸው ይሖዋን ማምለካቸውን እንዲያቆሙ ያደርጋቸው ይሆን?

      እነዚህ አራት ልጆች ይሖዋን ለመታዘዝ ወስነው ነበር። የይሖዋ ሕግ የአንዳንድ እንስሳትን ሥጋ እንዳይበሉ ይከለክል ስለነበር የንጉሡን ምግብ መብላት እንደሌለባቸው ተገንዝበው ነበር። ስለዚህ አሽፈኔዝን ‘እባክህ የንጉሡን ምግብ እንድንበላ አታድርገን’ አሉት። አሽፈኔዝ ግን ‘ይህን ምግብ ሳትበሉ ቀርታችሁ ንጉሡ ከስታችሁ ቢያይ እኔን ይገድለኛል!’ አላቸው።

      ዳንኤል አንድ ሐሳብ መጣለት። አሽፈኔዝን እንዲህ አለው፦ ‘እባክህ ለአሥር ቀን ያህል አትክልትና ውኃ ብቻ ስጠን። ከዚያም የንጉሡን ምግብ ከሚበሉት ልጆች ይልቅ እኛ ከስተን እንደሆነና እንዳልሆነ ታያለህ።’ አሽፈኔዝም በዚህ ሐሳብ ተስማማ።

      አሥሩ ቀን ካለፈ በኋላ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ከሌሎቹ ልጆች የበለጠ ጤናማ ሆነው ተገኙ። ይሖዋም እሱን ስለታዘዙት ደስ አለው። እንዲያውም ለዳንኤል ራእዮችንና ሕልሞችን የመረዳት ችሎታ ሰጠው።

      ሥልጠናቸውን ከጨረሱ በኋላ አሽፈኔዝ ልጆቹን ናቡከደነጾር ፊት አቀረባቸው። ንጉሡም ካነጋገራቸው በኋላ ዳንኤል፣ ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ከሌሎቹ ልጆች የበለጠ ጎበዝና አስተዋይ ሆነው አገኛቸው። ስለዚህ በቤተ መንግሥቱ እንዲያገለግሉ ሾማቸው። ንጉሡ ከበድ ያለ ጉዳይ ሲያጋጥመው ምክር ይጠይቃቸው ነበር። ይሖዋ እነዚህን ልጆች ንጉሡን ከሚያገለግሉት ጥበበኛ ሰዎችና ከአስማተኞቹ ሁሉ ይበልጥ ጥበበኛ አደረጋቸው።

      ዳንኤል፣ ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ከአገራቸው ርቀው የሚኖሩ ቢሆንም የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸውን አልረሱም። አንተስ ወላጆችህ አብረውህ በማይሆኑበት ጊዜም ጭምር ይሖዋን ሁልጊዜ ትታዘዛለህ?

      “ወጣት በመሆንህ ማንም ሰው ሊንቅህ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ታማኞች ለሆኑት በንግግር፣ በምግባር፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርዓያ ሁን።”—1 ጢሞቴዎስ 4:12

      ጥያቄ፦ ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ ይሖዋን የታዘዙት ለምንድን ነው? ይሖዋስ እነሱን የረዳቸው እንዴት ነው?

      ዳንኤል 1:1-21

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ