የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • በትልቅ ዛፍ የተመሰለ መንግሥት
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • ንጉሥ ናቡከደነጾር በሕልሙ ያየው ዛፍ ሲቆረጥ

      ትምህርት 62

      በትልቅ ዛፍ የተመሰለ መንግሥት

      አንድ ቀን ናቡከደነጾር ተኝቶ ሳለ የሚያስፈራ ሕልም አየ። በመሆኑም የባቢሎንን ጥበበኛ ሰዎች አስጠርቶ የሕልሙን ትርጉም ጠየቃቸው። ሆኖም አንዳቸውም ትርጉሙን ሊነግሩት አልቻሉም። በመጨረሻም ዳንኤልን አስጠራውና የሕልሙን ትርጉም ጠየቀው።

      ናቡከደነጾር ዳንኤልን እንዲህ አለው፦ ‘በሕልሜ አንድ ዛፍ አየሁ። ዛፉ በጣም አድጎ ሰማይ ደረሰ። ከየትም ቦታ ሆኖ ይህን ዛፍ ማየት ይቻል ነበር። የሚያማምሩ ቅጠሎችና ብዙ ፍሬዎች ነበሩት። እንስሳት በጥላው ሥር ያርፉ፣ ወፎችም በቅርንጫፎቹ ላይ ጎጇቸውን ይሠሩ ነበር። ከዚያም አንድ መልአክ ከሰማይ ወረደ። እንዲህም አለ፦ “ዛፉን ቁረጡ፤ ቅርንጫፎቹንም ጨፍጭፉ። ጉቶው ግን በብረትና በመዳብ ታስሮ ከነሥሩ መሬት ውስጥ ይቆይ። ልቡ ከሰው ልብ ይለወጥ፤ የአውሬም ልብ ይሰጠው፤ እንደዚያም ሆኖ ለሰባት ዘመናት ይቆይ። ሁሉም ሰዎች አምላክ በሁሉም ላይ ገዢ እንደሆነና መንግሥቱን ለፈለገው ሰው እንደሚሰጥ ይገነዘባሉ።”’

      ይሖዋ ለዳንኤል የዚህን ሕልም ትርጉም ገለጠለት። ዳንኤል የሕልሙን ትርጉም ሲረዳ ደነገጠ። ከዚያም ንጉሡን እንዲህ አለው፦ ‘ንጉሥ ሆይ፣ ሕልሙ ስለ ጠላቶችህ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር፤ ሆኖም ሕልሙ አንተን የሚመለከት ነው። የተቆረጠው ትልቅ ዛፍ አንተ ነህ። መንግሥትህ ከአንተ ይወሰዳል፤ እንዲሁም እንደ ዱር እንስሳ በሜዳ ላይ ሣር ትበላለህ። ሆኖም መልአኩ ጉቶው ከነሥሩ መሬት ውስጥ እንደሚቆይ ስለተናገረ በድጋሚ ንጉሥ ትሆናለህ።’

      ከአንድ ዓመት በኋላ አንድ ቀን ንጉሡ በቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ እየተመላለሰ ባቢሎንን በአድናቆት ይመለከት ነበር። ከዚያም እንዲህ አለ፦ ‘የገነባኋትን አስደናቂ ከተማ ተመልከቱ። እንደ እኔ ያለ ታላቅ ንጉሥ የለም!’ ልክ እየተናገረ ሳለ ከሰማይ የመጣ አንድ ድምፅ ‘ናቡከደነጾር! አሁን መንግሥትህ ከአንተ ተወስዷል’ አለው።

      ወዲያውኑ ናቡከደነጾር አእምሮውን ስቶ እንደ ዱር እንስሳ ሆነ። ስለሆነም ከቤተ መንግሥቱ ወጥቶ ከዱር እንስሳት ጋር መኖር ጀመረ። የናቡከደነጾር ፀጉር እንደ ንስር ላባ ረዘመ፤ ጥፍሮቹም አድገው እንደ ወፍ ጥፍሮች ሆኑ።

      ሰባት ዓመታት ካለፉ በኋላ ናቡከደነጾር እንደገና ጤናማ ሆነ፤ ይሖዋም የባቢሎን ንጉሥ አደረገው። ከዚያም ናቡከደነጾር እንዲህ አለ፦ ‘የሰማያት ንጉሥ የሆነውን ይሖዋን አወድሳለሁ። አሁን ይሖዋ በሁሉም ላይ ገዢ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ኩራተኞችን ያዋርዳል፤ ንጉሣዊ ሥልጣንንም ለፈለገው ሰው መስጠት ይችላል።’

      “ኩራት ጥፋትን፣ የትዕቢት መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።”—ምሳሌ 16:18

      ጥያቄ፦ የናቡከደነጾር ሕልም ትርጉም ምንድን ነው? ናቡከደነጾር ምን ትምህርት አገኘ?

      ዳንኤል 4:1-37

  • በግድግዳው ላይ የታየው ጽሑፍ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
    • አንድ እጅ በግድግዳው ላይ ሲጽፍ

      ትምህርት 63

      በግድግዳው ላይ የታየው ጽሑፍ

      ከጊዜ በኋላ ቤልሻዛር የባቢሎን ንጉሥ ሆነ። አንድ ቀን ቤልሻዛር በአገሩ ላሉ አንድ ሺህ ታላላቅ ሰዎች የራት ግብዣ አዘጋጀ። ቤልሻዛር፣ ናቡከደነጾር ከይሖዋ ቤተ መቅደስ የወሰዳቸውን የወርቅ ዕቃዎች እንዲያመጡ አገልጋዮቹን አዘዘ። ቤልሻዛርና እንግዶቹ በወርቅ ዕቃዎቹ እየጠጡ የራሳቸውን አማልክት አወደሱ። ከዚያም በድንገት የሰው እጅ ታየና በምግብ አዳራሹ ግድግዳ ላይ ለመረዳት አስቸጋሪ የሆኑ ቃላት መጻፍ ጀመረ።

      በዚህ ጊዜ ቤልሻዛር በጣም ፈራ። በመሆኑም አስማተኞቹን አስጠራና ‘የእነዚህን ቃላት ትርጉም የሚነግረኝ ሰው ካለ በባቢሎን ውስጥ ሦስተኛ ገዢ እንዲሆን አደርገዋለሁ’ አላቸው። አስማተኞቹ ትርጉሙን ለመረዳት ቢሞክሩም አልቻሉም። ከዚያም ንግሥቲቱ መጣችና እንዲህ አለችው፦ ‘ለናቡከደነጾር እንቆቅልሾችንና ከባድ ነገሮችን ይፈታለት የነበረ ዳንኤል የሚባል ሰው አለ። እሱ የእነዚህን ቃላት ትርጉም ሊነግርህ ይችላል።’

      በመሆኑም ዳንኤልን ንጉሡ ፊት አቀረቡት። ቤልሻዛርም እንዲህ አለው፦ ‘እነዚህን ቃላት አንብበህ ትርጉማቸውን ከነገርከኝ የወርቅ ሐብል እሰጥሃለሁ፤ እንዲሁም በባቢሎን ላይ ሦስተኛ ገዢ ትሆናለህ።’ ዳንኤልም እንዲህ አለ፦ ‘ስጦታህን አልፈልግም፤ ሆኖም የእነዚህን ቃላት ትርጉም እነግርሃለሁ። አባትህ ናቡከደነጾር ትዕቢተኛ በሆነ ጊዜ ይሖዋ አዋርዶት ነበር። አንተም በእሱ ላይ የደረሰውን ነገር በሙሉ ታውቃለህ፤ ሆኖም በቤተ መቅደሱ ዕቃዎች የወይን ጠጅ በመጠጣት ይሖዋን እንደምትንቅ አሳይተሃል። ስለዚህ አምላክ ሚኒ፣ ሚኒ፣ ቲቄል እና ፋርሲን የሚሉትን እነዚህን ቃላት አጻፈ። የእነዚህ ቃላት ትርጉም “ሜዶናውያንና ፋርሳውያን ባቢሎንን ያሸንፏታል፤ አንተም ከዚህ በኋላ ንጉሥ አትሆንም” የሚል ነው።’

      የንጉሥ ቂሮስ ወታደሮች ወንዙን ተሻግረው ወደ ባቢሎን በሮች ሲሄዱ

      በዚያ ዘመን ባቢሎንን ማሸነፍ የሚቻል አይመስልም ነበር። ምክንያቱም ከተማዋ በጠንካራ ግንብ የታጠረች ነበረች፤ እንዲሁም በዙሪያዋ የኤፍራጥስ ወንዝ ይገኝ ነበር። ሆኖም በዚያ ሌሊት ሜዶናውያንና ፋርሳውያን በከተማዋ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ። የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ ጥልቅ የሆነውን የኤፍራጥስን ወንዝ አቅጣጫ በማስቀየር ወታደሮቹ ያለምንም ችግር ወደ ከተማዋ በሮች እንዲሄዱ አደረገ። ወደዚያ ሲደርሱ በሮቹ ክፍት ነበሩ! ወታደሮቹ ወደ ከተማዋ ገብተው ድል አደረጓት፤ ንጉሡንም ገደሉት። ከዚያም ቂሮስ የባቢሎን ገዢ ሆነ።

      ቂሮስም እንዲህ በማለት አዋጅ አስነገረ፦ ‘ይሖዋ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደሱን መልሼ እንድገነባ አዞኛል። ከአምላክ ሕዝብ መካከል በግንባታው መካፈል የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ ይችላል።’ በመሆኑም ይሖዋ ቃል በገባው መሠረት ኢየሩሳሌም ከጠፋች ከ70 ዓመት በኋላ አብዛኞቹ አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ። ቂሮስ፣ ናቡከደነጾር ከቤተ መቅደሱ ወስዷቸው የነበሩትን የወርቅና የብር ዕቃዎች ወደ ኢየሩሳሌም መለሰ። ይሖዋ ቂሮስን በመጠቀም ሕዝቡን የረዳው እንዴት እንደሆነ አስተዋልክ?

      “ወደቀች! ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! የአጋንንት መኖሪያ . . . ሆነች!”—ራእይ 18:2

      ጥያቄ፦ በግድግዳው ላይ የታየው ጽሑፍ ትርጉም ምንድን ነው? ይሖዋ ቂሮስን ምን እንዲያደርግ አዘዘው?

      ዕዝራ 1:1-11፤ ዳንኤል 5:1-30፤ ኢሳይያስ 44:27–45:2፤ ኤርምያስ 25:11, 12

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ