-
ዳንኤል አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጣለከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 64
ዳንኤል አንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጣለ
በባቢሎን ላይ የነገሠው ሌላው ንጉሥ ደግሞ ሜዶናዊው ዳርዮስ ነበር። ዳርዮስ፣ ዳንኤል ከሌሎቹ ባለሥልጣናት ሁሉ የተለየ እንደሆነ አስተዋለ። ስለዚህ ዳንኤልን በባለሥልጣናቱ ላይ ሾመው። እነዚህ ሰዎች በዳንኤል ስለቀኑ ሊገድሉት ፈለጉ። ዳንኤል በየቀኑ ሦስት ጊዜ ወደ ይሖዋ እንደሚጸልይ ያውቁ ነበር፤ ስለዚህ ዳርዮስን እንዲህ አሉት፦ ‘ንጉሥ ሆይ፣ ሁሉም ሰው ወደ አንተ ብቻ እንዲጸልይ የሚያዝዝ ሕግ ይውጣ። ይህን ሕግ የማያከብር ማንኛውም ሰው ወደ አንበሶች ጉድጓድ ይጣል።’ ዳርዮስ በሐሳባቸው ተስማማ፤ ስለዚህ በሕጉ ላይ ፈረመ።
ዳንኤል ስለ አዲሱ ሕግ እንደሰማ ወደ ቤቱ ሄደ። የቤቱም መስኮት ተከፍቶ ነበር፤ ዳንኤልም መስኮቱ አጠገብ ተንበርክኮ ወደ ይሖዋ ጸለየ። በዳንኤል የቀኑት ሰዎች በሩን በርግደው ሲገቡ ዳንኤልን ሲጸልይ አገኙት። ስለዚህ ወደ ዳርዮስ ሄደው እንዲህ አሉት፦ ‘ዳንኤል አንተን አይታዘዝም። በቀን ሦስት ጊዜ ወደ አምላኩ ይጸልያል።’ ዳርዮስ ዳንኤልን ይወደው ስለነበር እንዲሞት አልፈለገም። ቀኑን ሙሉ ዳንኤልን ማዳን የሚችልበትን መንገድ ሲያስብ ዋለ። ሆኖም ንጉሡ የፈረመበትን ሕግ ራሱም እንኳ ሊቀይረው አይችልም ነበር። ስለዚህ ዳንኤልን አስፈሪ አንበሶች ወዳሉበት ጉድጓድ እንዲጥሉት ትእዛዝ አስተላለፈ።
በዚያ ሌሊት ዳርዮስ የዳንኤል ነገር በጣም ስላስጨነቀው እንቅልፍ ሊወስደው አልቻለም። በጠዋት ወደ ጉድጓዱ ሄዶ ዳንኤልን ‘አምላክህ ከአንበሶቹ አድኖሃል?’ አለው።
በዚህ ጊዜ ዳርዮስ አንድ ድምፅ ሰማ። የሰማው የዳንኤልን ድምፅ ነበር! ዳንኤል ዳርዮስን እንዲህ አለው፦ ‘የይሖዋ መልአክ የአንበሶቹን አፍ ዘጋ። ስለዚህ አንበሶቹ ምንም አልጎዱኝም።’ ዳርዮስ ይህን ሲሰማ በጣም ተደሰተ! ዳንኤልን ከጉድጓዱ እንዲያወጡት አዘዘ። ዳንኤል ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰበትም ነበር። ከዚያም ንጉሡ ‘ዳንኤልን የከሰሱትን ሰዎች አምጥታችሁ ጉድጓዱ ውስጥ ጣሏቸው’ በማለት አዘዘ። እነዚያ ሰዎች ወደ ጉድጓዱ ሲጣሉ አንበሶቹ በሏቸው።
ዳርዮስ እንዲህ በማለት ለሕዝቡ ትእዛዝ አስተላለፈ፦ ‘ሁሉም ሰው የዳንኤልን አምላክ መፍራት አለበት። ምክንያቱም ዳንኤልን ከአንበሶቹ አድኖታል።’
አንተስ እንደ ዳንኤል በየቀኑ ወደ ይሖዋ ትጸልያለህ?
“ይሖዋ፣ ለአምላክ ያደሩ ሰዎችን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን . . . ያውቃል።”—2 ጴጥሮስ 2:9
-
-
አስቴር ሕዝቧን ከጥፋት አዳነችከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
-
-
ትምህርት 65
አስቴር ሕዝቧን ከጥፋት አዳነች
አስቴር የፋርስ ከተማ በሆነችው በሹሻን የምትኖር አይሁዳዊት ነበረች። ከብዙ ዓመታት በፊት ናቡከደነጾር የአስቴርን ቤተሰቦች ከኢየሩሳሌም ወደ ሹሻን አምጥቷቸው ነበር። አስቴርን ያሳደጋት የአጎቷ ልጅ የሆነው መርዶክዮስ ሲሆን እሱም የፋርሱ ንጉሥ የአሐሽዌሮስ አገልጋይ ነበር።
ንጉሥ አሐሽዌሮስ አዲስ ንግሥት ለመምረጥ ፈለገ። ስለዚህ አገልጋዮቹ በአገሪቱ ያሉትን ቆንጆ ሴቶች አመጡለት፤ ካመጡለት ሴቶች መካከል አስቴርም ትገኝበት ነበር። ንጉሡ ከመጡት ሴቶች በሙሉ ንግሥት እንድትሆን የመረጠው አስቴርን ነው። መርዶክዮስ አስቴርን አይሁዳዊ መሆኗን ለማንም እንዳትናገር አዟት ነበር።
ሃማ የተባለ አንድ ኩራተኛ ሰው ከሌሎቹ መኳንንት ሁሉ የበላይ ሆኖ ተሾመ። ሃማ ሰው ሁሉ እንዲሰግድለት ይፈልግ ነበር። መርዶክዮስ ለሃማ ለመስገድ ፈቃደኛ አልሆነም፤ ሃማ በዚህ በጣም ስለተበሳጨ መርዶክዮስን ሊገድለው ፈለገ። ሃማ፣ መርዶክዮስ አይሁዳዊ መሆኑን ሲሰማ በአገሪቱ የሚገኙትን አይሁዳውያን በሙሉ ለማስገደል አሰበ። ከዚያም ንጉሡን ‘አይሁዳውያን በጣም አደገኛ ሰዎች ናቸው፤ እነሱን ማጥፋት አለብህ’ አለው። አሐሽዌሮስም ሃማን ‘የፈለግከውን ማድረግ ትችላለህ’ አለው፤ ሕግ ለማውጣት የሚያስችል ሥልጣንም ሰጠው። ሃማ፣ አዳር በተባለው ወር በ13ኛው ቀን ሕዝቡ አይሁዳውያንን በሙሉ እንዲገድሉ የሚያዝዝ ሕግ አወጣ። ይሖዋ ይህ ሁሉ ሲፈጸም ይመለከት ነበር።
አስቴር ይህ ሕግ መውጣቱን አላወቀችም ነበር። ስለዚህ መርዶክዮስ የወጣውን ሕግ ቅጂ ለአስቴር ላከላትና ‘ሄደሽ ንጉሡን አነጋግሪው’ አላት። አስቴር ግን እንዲህ ብላ መለሰችለት፦ ‘ሳይጠራ ወደ ንጉሡ የሚሄድ ሰው በሙሉ ይገደላል። ንጉሡ ደግሞ እኔን ለ30 ቀን ያህል አልጠራኝም! ቢሆንም እሄዳለሁ። ንጉሡ በትረ መንግሥቱን ከዘረጋልኝ በሕይወት እተርፋለሁ። ካልዘረጋልኝ ግን እሞታለሁ።’
አስቴር ወደ ንጉሡ ግቢ ሄደች። ንጉሡ አስቴርን ሲያያት በትረ መንግሥቱን ዘረጋላት። እሷም ወደ እሱ ቀረበች፤ ንጉሡም ‘አስቴር፣ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?’ አላት። እሷም ‘አንተና ሃማ ዛሬ ባዘጋጀሁት ግብዣ ላይ እንድትገኙልኝ እፈልጋለሁ’ አለችው። በግብዣው ላይ፣ አስቴር በቀጣዩ ቀን በምታዘጋጀው ሌላ ግብዣ ላይ እንዲገኙ አሐሽዌሮስንና ሃማን ጋበዘቻቸው። በሁለተኛው ግብዣ ላይ ንጉሡ በድጋሚ ‘አስቴር፣ ምን እንዳደርግልሽ ትፈልጊያለሽ?’ ብሎ ጠየቃት። አስቴርም ‘አንድ ሰው እኔንና ሕዝቤን ሊገድለን ነው። እባክህ አድነን’ አለችው። ንጉሡም ‘ለመሆኑ ይህ ሰው ማን ነው?’ በማለት ጠየቃት። እሷም ‘ይህ ክፉ ሰው ሃማ ነው’ አለችው። አሐሽዌሮስ በጣም በመናደዱ ወዲያውኑ ሃማን አስገደለው።
ይሁንና ሃማ ያወጣውን ሕግ ንጉሡ ራሱም እንኳ ሊሽረው አይችልም ነበር። ስለዚህ ንጉሡ መርዶክዮስን በመኳንንቱ ላይ ሾመውና አዲስ ሕግ እንዲያወጣ ሥልጣን ሰጠው። መርዶክዮስ አይሁዳውያን በጠላቶቻቸው ላይ ጥቃት በመሰንዘር ራሳቸውን እንዲከላከሉ የሚፈቅድ ሕግ አወጣ። በመሆኑም አዳር በተባለው ወር በ13ኛው ቀን አይሁዳውያን ጠላቶቻቸውን አሸነፉ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ በየዓመቱ ይህን ቀን ማክበር ጀመሩ።
“በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ በዚያ ጊዜ ለእነሱም ሆነ ለአሕዛብ መመሥከር ትችላላችሁ።”—ማቴዎስ 10:18
-