የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ክፍል 1)
    መጠበቂያ ግንብ—2014 | ጥቅምት 1
    • ዳዊት እና ኢዮብ ስለ አምላክ መንግሥት ሲወያዩ
      ዳዊት እና ኢዮብ ስለ አምላክ መንግሥት ሲወያዩ

      መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት

      የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው?​—ክፍል 1

      የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ዳዊት የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር ኢዮብ የሚባልን ሰው ቤቱ ሄዶ እያወያየው እንዳለ አድርገን እናስብ።

      ማስተዋልን ‘አጥብቀህ ፈልግ’

      ዳዊት፦ ኢዮብ፣ እንዲህ እየተገናኘን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናደርገው ውይይት በጣም ያስደስተኛል።a ባለፈው ጊዜ ስንወያይ ስለ አምላክ መንግሥት አንድ ጥያቄ አንስተህ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ‘የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው በ1914 ነው’ የሚሉት ለምን እንደሆነ ጠይቀኸኝ ነበር።

      ኢዮብ፦ አዎን፣ አንድ የእናንተን ጽሑፍ ሳነብ የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው በ1914 እንደሆነ የሚናገር ሐሳብ አገኘሁ። የምታምኑበት ነገር በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተመሠረተ ስለምትናገሩ ለዚህ የምታቀርቡትን ማስረጃ ለማየት ጓጉቻለሁ።

      ዳዊት፦ ልክ ነህ፤ የምናምነው ነገር በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ነው።

      ኢዮብ፦ ይኸውልህ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብቤያለሁ። ይሁን እንጂ 1914 የሚለውን ዓመት የሚጠቅስ ሐሳብ አላገኘሁም። ስለዚህ ኢንተርኔት ላይ ገብቼ አንድ መጽሐፍ ቅዱስ አወጣሁና “1914” የሚለውን ቁጥር እንዲፈልግልኝ አደረግኩ። እንዲህም አድርጌ ይህን ዓመት ማግኘት አልቻልኩም።

      ዳዊት፦ ኢዮብ፣ ሁለት የሚያስመሰግኑ ነገሮችን አድርገሃል። አንደኛ፣ ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ አንብበሃል። ይህም የአምላክን ቃል እንደምትወድ ያሳያል።

      ኢዮብ፦ አዎን፣ እወደዋለሁ። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ያለ መጽሐፍ የለም።

      ዳዊት፦ እኔም በዚህ እስማማለሁ። ሁለተኛ ደግሞ የጥያቄውን መልስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለማግኘት ያደረግከውን ጥረት አድንቄያለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ ማስተዋልን ‘አጥብቀን እንድንፈልግ’ ያበረታታል፤ አንተም ያደረግከው ይህንኑ ነው።b እንዲህ ዓይነት ጥረት ማድረግህ የሚያስመሰግን ነው።

      ኢዮብ፦ አመሰግናለሁ። ምርምር ማድረጌን ማቆም አልፈልግም። እንዲያውም ስለ 1914 ተጨማሪ ምርምር አድርጌ በዚህ በምናጠናው መጽሐፍ ላይ አንዳንድ መረጃዎችን አግኝቻለሁ። መጽሐፉ አንድ ንጉሥ ስላየው ሕልም ይጠቅሳል፤ ካልተሳሳትኩ፣ ሕልሙ የሚናገረው ተቆርጦ ስለነበረና ተመልሶ ስላቆጠቆጠ አንድ ትልቅ ዛፍ መሰለኝ።

      ዳዊት፦ አዎ፣ ልክ ነህ። በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ የሚገኝ ትንቢት ነው። ሕልሙን የተመለከተው የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ነው።

      ኢዮብ፦ አዎ፣ እሱ ነው። ትንቢቱን ደጋግሜ አንብቤዋለሁ። እውነቱን ለመናገር ግን ከአምላክ መንግሥት ወይም ከ1914 ጋር ምን እንደሚያገናኘው አልገባኝም።

      ዳዊት፦ ይህ የሚያስገርም አይደለም፤ ነቢዩ ዳንኤልም እንኳ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ የጻፋቸውን ነገሮች ሙሉ በሙሉ አልተረዳም ነበር!

      ኢዮብ፦ እውነትህን ነው?

      ዳዊት፦ አዎ። እንዲያውም ዳንኤል 12:8 ምን እንደሚል ተመልከት፤ “እኔም ሰማሁ፤ ነገር ግን አላስተዋልሁትም።”

      ኢዮብ፦ አሃ፣ ያልገባኝ እኔ ብቻ አይደለሁም ማለት ነው። ያልገባኝ እኔ ብቻ እንዳልሆንኩ ማወቄ አስደስቶኛል።

      ዳዊት፦ ምን መሰለህ ኢዮብ፣ ዳንኤል የትንቢቱን ትርጉም መረዳት ያልቻለው ሰዎች በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ትንቢቶች ትርጉም ሙሉ በሙሉ ማስተዋል እንዲችሉ አምላክ የፈቀደበት ጊዜ ገና ስላልደረሰ ነበር። አሁን በእኛ ዘመን ግን የትንቢቶቹን ትርጉም መረዳት እንችላለን።

      ኢዮብ፦ እንዲህ እንድትል ያደረገህ ምንድን ነው?

      ዳዊት፦ እስቲ የሚቀጥለውን ቁጥር ላሳይህ። ዳንኤል 12:9 “ቃሉ እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ የተዘጋና የታተመ ስለ ሆነ ሂድ” ይላል። ስለዚህ ትንቢቶቹን መረዳት የሚቻለው ከዳንኤል ዘመን በኋላ ብዙ ጊዜ ቆይቶ ይኸውም ‘በፍጻሜው ዘመን’ ነው ማለት ነው። አሁን የምንኖረው በዚህ የፍጻሜ ዘመን ውስጥ እንደሆነ የሚጠቁሙ ብዙ ማስረጃዎች እንዳሉ በቅርቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውይይታችን ላይ እንመለከታለን።c

      ኢዮብ፦ ታዲያ በዳንኤል መጽሐፍ ላይ ያለውን ይህን ትንቢት ልታብራራልኝ ትችላለህ?

      ዳዊት፦ እሺ፣ ደስ ይለኛል።

      የናቡከደነፆር ሕልም

      ዳዊት፦ በመጀመሪያ ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልሙ ያየው ምን እንደሆነ አጠር አድርጌ ልግለጽልህ። ከዚያ ስለ ትርጉሙ እንነጋገራለን።

      ኢዮብ፦ እሺ።

      ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ አንድ ትልቅ ዛፍ ሲያልም
      ንጉሥ ናቡከደነፆር ስለ አንድ ትልቅ ዛፍ ሲያልም

      ዳዊት፦ ናቡከደነፆር በሕልሙ፣ ቁመቱ እስከ ሰማይ የሚደርስ አንድ ግዙፍ ዛፍ አየ። ከዚያም አንድ የአምላክ መልእክተኛ ዛፉ እንዲቆረጥ ትእዛዝ ሲያስተላልፍ ሰማ። ጉቶው ግን በመሬት ውስጥ እንዲተው አዘዘ። “ሰባት ዓመት” ካለፈ በኋላ ዛፉ እንደገና ማደግ ይጀምራል።d ይህ ትንቢት የመጀመሪያ ፍጻሜውን የሚያገኘው በራሱ በናቡከደነፆር ላይ ነበር። ናቡከደነፆር ጫፉ እስከ ሰማይ እንደሚደርሰው ዛፍ ሁሉ ታዋቂ ንጉሥ የነበረ ቢሆንም ‘ለሰባት ዓመት’ ተቆርጦ ነበር። በዚህ ጊዜ ምን እንደተከናወነ ታስታውሳለህ?

      ኢዮብ፦ አይ፣ አላስታውስም።

      ዳዊት፦ ችግር የለውም፣ እኔ እነግርሃለሁ። ናቡከደነፆር ለሰባት ዓመታት አእምሮውን ስቶ እንደቆየ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። በመሆኑም በእነዚህ ዓመታት ንጉሥ ሆኖ ማስተዳደር አልቻለም። ይሁን እንጂ በሰባቱ ዓመታት ፍጻሜ ላይ ናቡከደነፆር አእምሮው የተመለሰለት ሲሆን እንደገና ንጉሥ ሆኖ መግዛት ጀመረ።e

      ኢዮብ፦ እሺ፣ እስካሁን ያልከው ገብቶኛል። ግን ይህ ሁሉ ከአምላክ መንግሥትና ከ1914 ጋር ምን ግንኙነት አለው?

      ዳዊት፦ በአጭሩ ለመናገር ያህል፣ ይህ ትንቢት ሁለት ፍጻሜዎች አሉት። የመጀመሪያ ፍጻሜውን ያገኘው የንጉሥ ናቡከደነፆር ንግሥና ሲቋረጥ ነው። ሁለተኛው ፍጻሜ ደግሞ ከአምላክ አገዛዝ መቋረጥ ጋር የተያያዘ ነው። ስለዚህ ከአምላክ መንግሥት ጋር የሚያያዘው ይኼኛው የትንቢቱ ፍጻሜ ነው።

      ኢዮብ፦ ትንቢቱ ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዘ ሁለተኛ ፍጻሜ እንዳለው እንዴት አወቅህ?

      ዳዊት፦ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ትንቢቱ ራሱ ይህን የሚጠቁም ሐሳብ ይዟል። ዳንኤል 4:17 (የ1954 ትርጉም) ትንቢቱ የተሰጠው “ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፣ ለወደደውም እንዲሰጠው . . . ሕያዋን ያውቁ ዘንድ” እንደሆነ ይናገራል። “በሰዎች መንግሥት ላይ” የሚለውን አገላለጽ ልብ ብለኸዋል?

      ኢዮብ፦ አዎ፣ ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንደሚሠለጥን ይናገራል።

      ዳዊት፦ ልክ ነህ። “ልዑሉ” የተባለው ማን ይመስልሃል?

      ኢዮብ፦ አምላክ ይመስለኛል።

      ዳዊት፦ ልክ ነው። ስለዚህ ትንቢቱ የሚናገረው ስለ ናቡከደነፆር ብቻ እንዳልሆነ ከዚህ ማየት ይቻላል። ትንቢቱ ስለ “ሰዎች መንግሥት” ማለትም አምላክ የሰው ልጆችን በሙሉ ለማስተዳደር ስላቋቋመው መንግሥትም የሚናገር ነው። ይህ ትንቢት የሚገኝበትን ዐውድ ብንመረምር ይህ ሐሳብ ይበልጥ ግልጽ ይሆንልናል።

      ኢዮብ፦ እንዴት?

      የዳንኤል መጽሐፍ ዋነኛ ጭብጥ

      ዳዊት፦ የዳንኤል መጽሐፍ በተደጋጋሚ የሚጠቅሰው አንድ ጉዳይ አለ። የአምላክ ልጅ በሆነው በኢየሱስ የሚመራ የአምላክ መንግሥት እንደሚቋቋም ይናገራል። እስቲ፣ አንድ ሁለት ምዕራፎች ወደ ኋላ መለስ ብለን እንመልከት። እባክህ ዳንኤል 2:44⁠ን ታነበዋለህ?

      ኢዮብ፦ እሺ። “በነዚያ ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”

      ዳዊት፦ አመሰግንሃለሁ። ይህ ጥቅስ ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገር ሐሳብ የያዘ ይመስልሃል?

      ኢዮብ፦ እኔ እንጃ። እርግጠኛ አይደለሁም።

      ዳዊት፦ ይኸውልህ፣ ይህ መንግሥት “ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” መባሉን ልብ በል። እንዲህ ማለት የሚቻለው ስለ አምላክ መንግሥት ብቻ ነው፤ እንዲህ ሊባልለት የሚችል ሰብዓዊ መንግሥት አለ?

      ኢዮብ፦ አይ፣ አይመስለኝም።

      ዳዊት፦ በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዘ ሌላ ትንቢትም አለ። እሱም በ⁠ዳንኤል 7:13, 14 (የ1954 ትርጉም) ላይ የሚገኘው ትንቢት ነው። ትንቢቱ ወደፊት ስለሚመጣ አንድ ገዢ ሲናገር እንዲህ ይላል፦ “ግዛትና ክብር መንግሥትም ተሰጠው፤ ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።” በዚህ ትንቢት ላይ አሁን ከምንነጋገረው ጉዳይ ጋር የተያያዘ ነገር እንደተጠቀሰ ልብ አልክ?

      ኢዮብ፦ አዎ፣ ስለ አንድ መንግሥት ይጠቅሳል።

      ዳዊት፦ ትክክል ነህ። ደግሞም የሚጠቅሰው ስለ አንድ ተራ መንግሥት አይደለም። “ወገኖችና አሕዛብ በልዩ ልዩ ቋንቋም የሚናገሩ ሁሉ” ለዚህ መንግሥት እንደሚገዙለት ልብ በል። በሌላ አነጋገር፣ ይህ መንግሥት መላውን ዓለም የሚገዛ ነው።

      ኢዮብ፦ ይህን አላስተዋልኩትም ነበር፤ ግን ልክ ነህ። ጥቅሱ የሚለው እንደዚህ ነው።

      ዳዊት፦ በተጨማሪም ትንቢቱ “ግዛቱም የማያልፍ የዘላለም ግዛት ነው፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው” እንደሚል ልብ በል። ይህ ትንቢት ዳንኤል 2:44 ላይ ካነበብነው ትንቢት ጋር በጣም የሚመሳሰል ነው አይደል?

      ኢዮብ፦ አዎ፣ ይመሳሰላል።

      ዳዊት፦ እስቲ እስካሁን የተወያየነውን በአጭሩ እንከልስ። በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ ያለው ትንቢት የተነገረው ‘ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንደሚገዛ’ ሰዎች እንዲያውቁ ነው። ይህ በራሱ ትንቢቱ በናቡከደነፆር ላይ ካገኘው የበለጠ ፍጻሜ እንዳለው የሚጠቁም ነው። ደግሞም በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ በአምላክ ልጅ የሚመራ መንግሥት እንደሚቋቋም የሚገልጹ ሌሎች ትንቢቶችን እናገኛለን። ታዲያ በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ ያለው ትንቢት ከአምላክ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንዳለው ማሰቡ ምክንያታዊ አይመስልህም?

      ኢዮብ፦ ይመስለኛል። ይሁን እንጂ አሁንም ከ1914 ጋር ያለው ግንኙነት አልገባኝም።

      “ሰባት ዓመትም ይለፍበት”

      ዳዊት፦ አሁን ደግሞ ወደ ንጉሥ ናቡከደነፆር እንመለስ። በትንቢቱ የመጀመሪያ ፍጻሜ ላይ ንጉሥ ናቡከደነፆር በዛፉ ተመስሏል። ዛፉ ተቆርጦ የቆየባቸው ሰባት ዓመታት ናቡከደነፆር አእምሮውን በመሳቱ የተነሳ አገዛዙ የተቋረጠበትን ጊዜ ያመለክታል። እነዚያ ሰባት ዓመታት ሲያበቁ አእምሮው ተመልሶለት ወደ ንግሥናው ተመለሰ። በትንቢቱ ሁለተኛ ፍጻሜ መሠረት ደግሞ የአምላክ አገዛዝ ለተወሰነ ጊዜ ይቋረጣል፤ ይሁን እንጂ የሚቋረጠው አምላክ አንድ ዓይነት እንከን ስለሚገጥመው አይደለም።

      ኢዮብ፦ ምን ለማለት እንደፈለግክ አልገባኝም።

      ዳዊት፦ በጥንት ዘመን በኢየሩሳሌም ሆነው የሚገዙ እስራኤላውያን ነገሥታት “በእግዚአብሔር ዙፋን” ላይ እንደተቀመጡ ተገልጿል።f እሱን ወክለው የአምላክን ሕዝብ ያስተዳድሩ ነበር። ስለዚህ የእነዚያ ነገሥታት አገዛዝ የአምላክን አገዛዝ የሚወክል ነበር ማለት ነው። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ከእነዚህ ነገሥታት አብዛኞቹ በአምላክ ላይ ዓመፁ፤ አብዛኞቹ ተገዢዎቻቸውም የእነሱን መጥፎ ምሳሌ ተከተሉ። እስራኤላውያን ባለመታዘዛቸው የተነሳ አምላክ በ607 ዓ.ዓ. ባቢሎናውያን ድል እንዲያደርጓቸው ፈቀደ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ በኢየሩሳሌም ይሖዋን የሚወክሉ ነገሥታት አልነበሩም። በመሆኑም የአምላክ አገዛዝ የተቋረጠው ከዚህ አንጻር ነው። እስካሁን የነገርኩህ ግልጽ ሆኖልሃል?

      ኢዮብ፦ አዎ።

      ዳዊት፦ ስለዚህ ‘ሰባቱ ዓመታት’ ማለትም የአምላክ አገዛዝ ተቋርጦ የሚቆይባቸው ዘመናት የጀመሩት በ607 ዓ.ዓ. ነው። ሰባቱ ዓመታት ሲያበቁ አምላክ እሱን የሚወክል አዲስ ንጉሥ ያነግሳል፤ ይህ የሚሆነው ግን በሰማይ ነው። በዳንኤል ትንቢት ውስጥ ያነበብናቸው ሌሎቹ ትንቢቶችም የሚፈጸሙት በዚሁ ጊዜ ነው። ስለዚህ ዋናው ጥያቄ ‘ሰባቱ ዓመታት የሚያበቁት መቼ ነው?’ የሚለው ነው። ይህን ጥያቄ መመለስ ከቻልን የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀምረው መቼ እንደሆነ እናውቃለን።

      ኢዮብ፦ አሃ። ስለዚህ ሰባቱ ዓመታት የሚያበቁት በ1914 ነው እያልከኝ ነው?

      ዳዊት፦ ትክክል!

      ኢዮብ፦ ግን ይህን እንዴት እናውቃለን?

      ዳዊት፦ ይኸውልህ፣ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት እነዚህ ሰባት ዓመታት ገና እንዳላበቁ የሚጠቁም ሐሳብ ተናግሯል።g ስለዚህ ሰባቱ ዓመታት በጣም ረጅም ጊዜን የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው። ሰባቱ ዓመታት የጀመሩት ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት ሲሆን ወደ ሰማይ ተመልሶ ከሄደ በኋላም እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ አላበቁም ነበር። በተጨማሪም በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ትንቢቶች ትርጉም “እስከ ፍጻሜው ዘመን ድረስ” ግልጽ እንደማይሆን አስታውስ።h የሚገርመው፣ በ1880ዎቹ ማብቂያ ላይ ቅን የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ የሚገኘውን ጨምሮ ሌሎች ትንቢቶችንም በጥንቃቄ መመርመር ጀመሩ። ከዚያም ሰባቱ ዓመታት በ1914 እንደሚያበቁ አስተዋሉ። በተጨማሪም ከ1914 ወዲህ በዓለም ላይ የታዩት ታላላቅ ክስተቶች በእርግጥም የአምላክ መንግሥት በዚህ ዓመት በሰማይ መግዛት እንደጀመረ አረጋግጠዋል። የፍጻሜው ዘመን ወይም የመጨረሻዎቹ ቀኖች የጀመሩት በዚህ ዓመት ነበር። ይህ ሐሳብ አዲስ ሊሆንብህ ስለሚችል ለመረዳት ጊዜ እንደሚያስፈልግህ ይሰማኛል።

      ኢዮብ፦ አዎ። ሐሳቡን በደንብ ለመረዳት ደጋግሜ ማንበብ አለብኝ።

      ዳዊት፦ ትችላለህ። እኔም ብሆን እነዚህን ትንቢቶችና ፍጻሜያቸውን ለመረዳት ጊዜ ወስዶብኛል። ይሁን እንጂ ዛሬ ያደረግነው ውይይት፣ ቢያንስ ቢያንስ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ አምላክ መንግሥት የሚያምኑት ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንድታስተውል ረድቶሃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

      ኢዮብ፦ በትክክል። የምታምኑባቸው ነገሮች በሙሉ የተመሠረቱት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መሆኑ ሁልጊዜም ያስደንቀኛል።

      ዳዊት፦ አንተም ለምታምነው ነገር ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ማድረግ እንደምትፈልግ አስተውያለሁ። እንደነገርኩህ ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ መረዳት ከባድ ነው። ምናልባት አሁንም አንዳንድ ጥያቄዎች ይኖሩህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰባቱ ዓመታት ከአምላክ መንግሥት ጋር ግንኙነት እንዳላቸውና በ607 ዓ.ዓ. እንደጀመሩ ተወያይተናል። ይሁን እንጂ እነዚህ ሰባት ዓመታት ልክ 1914 ላይ እንዳበቁ እንዴት እናውቃለን?i

      ኢዮብ፦ አዎን፣ እኔም ስለ እሱ እያሰብኩ ነበር።

      ዳዊት፦ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ የሰባቱ ዓመታት ትክክለኛ ርዝማኔ ምን ያህል እንደሆነ እንድናውቅ ይረዳናል። በሚቀጥለው ጊዜ ስመጣ ስለዚህ ጉዳይ ብንነጋገር ምን ይመስልሃል?j

      ኢዮብ፦ እሺ፣ ጥሩ ነው።

      ለመረዳት ያስቸገረህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ ናቸው።

      a የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለማስተማር ባደረጉት ዝግጅት አማካኝነት ከሰዎች ጋር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ርዕስ በርዕስ ይወያያሉ።

      b ምሳሌ 2:3-5

      c በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት።

      d ዳንኤል 4:13-17

      e ዳንኤል 4:20-36

      f 1 ዜና መዋዕል 29:23

      g ኢየሱስ የመጨረሻዎቹን ቀኖች አስመልክቶ በተናገረው ትንቢት ላይ “የተወሰኑት የአሕዛብ ዘመናት እስኪፈጸሙ ድረስም ኢየሩሳሌም [የአምላክን አገዛዝ የምትወክለው ከተማ] በአሕዛብ ትረገጣለች” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 21:24) ስለዚህ በኢየሱስ ዘመንም ቢሆን የአምላክ አገዛዝ ተቋርጦ ነበር፤ እንዲሁም ይህ ሁኔታ እስከ መጨረሻዎቹ ቀኖች የሚቀጥል ነበር።

      h ዳንኤል 12:9

      i ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ተጨማሪ ክፍል ላይ 1914​—በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ዓመት የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

      j በዚህ ዓምድ ሥር ከዚህ ቀጥሎ የሚወጣው ርዕስ የሰባቱን ዓመታት ርዝማኔ ለማስላት የሚረዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ያብራራል።

  • የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው? (ክፍል 2)
    መጠበቂያ ግንብ—2014 | ኅዳር 1
    • ኢዮብ ዳዊትን ወደ ቤት እንዲገባ ሲጋብዘው
      ኢዮብ ዳዊትን ወደ ቤት እንዲገባ ሲጋብዘው

      መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት

      የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው?​—ክፍል 2

      የይሖዋ ምሥክሮች ከሰዎች ጋር ምን ዓይነት ውይይት እንደሚያደርጉ የሚያሳይ ምሳሌ ከዚህ በታች ቀርቧል። ዳዊት የሚባል አንድ የይሖዋ ምሥክር ኢዮብ የሚባልን ሰው ቤቱ ሄዶ እያወያየው እንዳለ አድርገን እናስብ።

      የናቡከደነፆርን ሕልም በአጭሩ መከለስ

      ዳዊት፦ ታዲያስ ኢዮብ፣ እንደምን አለህ? በየሳምንቱ እንዲህ እየተገናኘን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናደርገው ውይይት በጣም ያስደስተኛል።a ለመሆኑ እንዴት ነህ?

      ኢዮብ፦ እኔ ደህና ነኝ፤ አንተስ?

      ዳዊት፦ እኔም በጣም ደህና ነኝ። ባለፈው ጊዜ ባደረግነው ውይይት ላይ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው በ1914 ነው ብለው የሚያምኑት ለምን እንደሆነ ተነጋግረን ነበር።b ይህን እንድናምን ያደረገንን አንዱን ማስረጃም ተመልክተናል፤ ይህ ማስረጃ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በ⁠ዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ በተገለጸ አንድ ትንቢት ላይ ነው። በዳንኤል ምዕራፍ 4 ላይ ያለውን ሐሳብ ታስታውሰዋለህ?

      ኢዮብ፦ አዎ፣ ሐሳቡ የሚናገረው ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕልሙ ስላየው አንድ ትልቅ ዛፍ ነው።

      ዳዊት፦ ልክ ነህ። ናቡከደነፆር በሕልሙ፣ ቁመቱ እስከ ሰማይ የሚደርስ አንድ ግዙፍ ዛፍ አየ። ከዚያም አንድ የአምላክ መልእክተኛ ዛፉ እንዲቆረጥ፣ ጉቶውና ሥሩ ግን በመሬት ውስጥ እንዲቆይ ትእዛዝ ሲያስተላልፍ ሰማ። “ሰባት ዓመት” ካለፈ በኋላ ዛፉ እንደገና ማደግ ይጀምራል።c በተጨማሪም ትንቢቱ ሁለት ፍጻሜዎች አሉት የምንለው ለምን እንደሆነ ተወያይተናል። የመጀመሪያው የትንቢቱ ፍጻሜ ምን እንደሆነ ታስታውሳለህ?

      ኢዮብ፦ አዎ፣ ትንቢቱ በመጀመሪያ የተፈጸመው በራሱ በናቡከደነፆር ላይ ነው አይደል? ለሰባት ዓመታት አእምሮውን ስቶ ነበር።

      ዳዊት፦ በትክክል። ናቡከደነፆር ለተወሰነ ጊዜ አእምሮውን ስለሳተ አገዛዙ ተቋርጦ ነበር። ይሁን እንጂ ትንቢቱ ዋነኛ ፍጻሜውን ሲያገኝ የአምላክ አገዛዝም ‘ለሰባት ዓመታት’ ይቋረጣል። ባለፈው እንዳየነው በትንቢቱ ላይ የተገለጹት “ሰባት ዓመታት” የጀመሩት ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. በጠፋች ጊዜ ነበር። ከዚያን ጊዜ ወዲህ በምድር ላይ ይሖዋን ወክለው የእሱን ሕዝብ የሚገዙ ነገሥታት አልተነሱም። ይሁን እንጂ ‘ሰባቱ ዓመታት’ ሲያበቁ አምላክ የእሱን ሕዝብ የሚገዛ አዲስ ንጉሥ ያነግሣል፤ ይህ የሚሆነው ግን በሰማይ ነው። በሌላ አነጋገር፣ የአምላክ መንግሥት በሰማይ መግዛት የሚጀምረው ‘ሰባቱ ዓመታት’ ሲያበቁ ነው። ‘ሰባቱ ዓመታት’ የጀመሩት መቼ እንደሆነ ቀደም ብለን ተወያይተናል። ስለዚህ ‘የሰባቱን ዓመታት’ ርዝማኔ ማወቅ ከቻልን የአምላክ መንግሥት መግዛት የሚጀምረው መቼ እንደሆነ ማወቅ እንችላለን ማለት ነው። እስካሁን ያልኩት ግልጽ ሆኖልሃል?

      ኢዮብ፦ አዎን፣ ባለፈው የተወያየንበትን መከለስህ ነጥቦቹን እንዳስታውስ ረድቶኛል።

      ዳዊት፦ በጣም ጥሩ። እንግዲያውስ ሰባቱ ዓመታት ምን ያህል ርዝማኔ እንዳላቸው እንመልከት። ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ለማስታወስ እንዲረዳኝ እኔ ራሴ አንተ ጋር ከመምጣቴ በፊት ስለ ጉዳዩ አንብቤ ነበር። እስቲ የቻልኩትን ያህል በደንብ ለማብራራት ልሞክር።

      ኢዮብ፦ እሺ።

      ሰባቱ ዓመታት አበቁ፤ እንዲሁም የመጨረሻዎቹ ቀኖች ጀመሩ

      ዳዊት፦ ትንቢቱ በናቡከደነፆር ላይ የመጀመሪያውን ፍጻሜ ሲያገኝ በትንቢቱ ላይ የተገለጹት “ሰባት ዓመታት” ርዝማኔ ቃል በቃል ሰባት ዓመት የነበረ ይመስላል። ይሁን እንጂ ትንቢቱ ከአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን ሲያገኝ ‘ሰባቱ ዓመታት’ ቃል በቃል ሰባት ዓመታትን ሳይሆን ከዚያ የበለጠ ጊዜን የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው።

      ኢዮብ፦ እንዲህ ያልከው ለምንድን ነው?

      ዳዊት፦ በመጀመሪያ፣ ሰባቱ ዓመታት የጀመሩት ኢየሩሳሌም በ607 ዓ.ዓ. በጠፋች ጊዜ እንደሆነ አስታውስ። ከዚህ ዓመት ጀምረን ቃል በቃል ሰባት ዓመታት ብንቆጥር 600 ዓ.ዓ. ላይ እንደርሳለን። ይሁን እንጂ ከአምላክ አገዛዝ ጋር በተያያዘ በዚህ ዓመት ምንም የተፈጸመ ነገር የለም። ከዚህም ሌላ ባለፈው ጊዜ እንደተመለከትነው ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት እነዚህ “ሰባት ዓመታት” እንዳላበቁ ተናግሯል።

      ኢዮብ፦ አሃ፣ ልክ ነው። አሁን አስታወስኩት።

      ዳዊት፦ ከዚህ አንጻር እነዚህ “ሰባት ዓመታት” ቃል በቃል ሰባት ዓመታት ሳይሆኑ ከዚህ የበለጠ ርዝማኔ ያለውን ጊዜ የሚያመለክቱ መሆን አለባቸው።

      ዳዊት እና ኢዮብ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ሲያደርጉ
      ዳዊት እና ኢዮብ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ሲያደርጉ

      ኢዮብ፦ ምን ያህል ጊዜ?

      ዳዊት፦ ከዳንኤል መጽሐፍ ጋር ተያያዥነት ያለው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው የራእይ መጽሐፍ ሰባቱ ዓመታት ምን ያህል ርዝማኔ እንዳላቸው በትክክል እንድናውቅ ይረዳናል። መጽሐፉ ሦስት ተኩል ዘመናት ወይም ዓመታት የ1,260 ቀናት ርዝማኔ እንዳላቸው ይናገራል።d ሰባት ዓመታት ደግሞ የሦስት ተኩል ዘመናት ወይም ዓመታት እጥፍ ናቸው፤ ስለዚህ ሰባቱ ዓመታት የ2,520 ቀናት ርዝማኔ ይኖራቸዋል ማለት ነው። እስካሁን ያልኩት ግልጽ ነው?

      ኢዮብ፦ አዎን፣ ገብቶኛል። ይሁን እንጂ ይህ፣ የአምላክ መንግሥት በ1914 መግዛት መጀመሩን የሚያሳየው እንዴት እንደሆነ አልገባኝም።

      ዳዊት፦ እሺ፣ ይህ ጊዜ ከአምላክ መንግሥት ጋር ምን ግንኙነት እንዳለው እንመልከት። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አንድ ቀን የአንድ ዓመት ርዝማኔ እንዳለው ተደርጎ የተገለጸበት ጊዜ አለ።e ስለዚህ አንድ ቀን እንደ አንድ ዓመት የሚለውን ደንብ ከተጠቀምን ሰባቱ ዓመታት 2,520 ዓመታት ይሆናሉ ማለት ነው። ከ607 ዓ.ዓ. ጀምረን 2,520 ዓመታት ብንቆጥር 1914 ላይ እንደርሳለን።f ስለዚህ 1914 ሰባቱ ዓመታት የሚያበቁበትና ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት የሚጀምርበት ዓመት ይሆናል ማለት ነው። ደግሞም መጽሐፍ ቅዱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት እንደሚፈጸሙ የተናገራቸው ክስተቶች ከ1914 ወዲህ ግልጽ በሆነ ሁኔታ መፈጸም ጀምረዋል።

      ኢዮብ፦ ምን ዓይነት ክስተቶች?

      ዳዊት፦ ኢየሱስ እሱ መግዛት በሚጀምርበት ጊዜ በምድር ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች አስመልክቶ በ⁠ማቴዎስ 24:7 ላይ ምን እንዳለ እስቲ እንመልከት። “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ ይነሳል፤ በተለያየ ስፍራ የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ ይከሰታል” ብሏል። ኢየሱስ በዚህ ወቅት የምግብ እጥረትና የምድር ነውጥ እንደሚኖር መናገሩን ልብ በል። ደግሞም ባለፈው መቶ ዓመት ውስጥ እነዚህ ችግሮች በዓለማችን ላይ በብዛት ታይተዋል አይደል?

      ኢዮብ፦ አዎ፣ ልክ ነህ።

      ዳዊት፦ በተጨማሪም ኢየሱስ፣ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ጦርነት እንደሚኖር እዚህ ጥቅስ ላይ ተናግሯል። የራእይ መጽሐፍም በፍጻሜው ዘመን በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን መላውን ዓለም የሚነኩ ጦርነቶች እንደሚኖሩ የሚገልጽ ትንቢት ይዟል።g የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት የፈነዳው መቼ እንደሆነ ታስታውሳለህ?

      ኢዮብ፦ በ1914 ነው፤ አሃ፣ ኢየሱስ መግዛት ጀምሯል ያልከውም በዚህ ዓመት ነው ለካ! እንደዚህ አስቤው አላውቅም ነበር።

      ዳዊት፦ እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረስነው እነዚህን ሁሉ ማስረጃዎች ይኸውም ስለ ሰባቱ ዓመታት የሚገልጸውን ትንቢትና ስለ ፍጻሜው ዘመን የሚናገሩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በማስተያየት ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መግዛት የጀመረውም ሆነ የመጨረሻዎቹ ቀኖች የጀመሩት በ1914 እንደሆነ ያምናሉ።h

      ኢዮብ፦ ይህንን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ትንሽ ጊዜ የሚያስፈልገኝ ይመስለኛል።

      ዳዊት፦ ይገባኛል። ከዚህ በፊት እንደነገርኩህ እኔም ይህንን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ጊዜ ወስዶብኛል። ይሁን እንጂ እስካሁን ያደረግነው ውይይት 1914 የሚለው ዓመት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በቀጥታ ባይጠቀስም እንኳ የይሖዋ ምሥክሮች ስለ 1914 የሚያምኑት ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንድትረዳ አስችሎሃል የሚል ተስፋ አለኝ።

      ኢዮብ፦ አዎን፣ ይሄ ነገራችሁ ሁልጊዜም ያስደንቀኛል፤ ለምትናገሩት ነገር ሁሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማስረጃ ታቀርባላችሁ። የምትናገሩት የራሳችሁን አመለካከት አይደለም። ይሁንና ጉዳዩ እንዲህ የተወሳሰበው ለምንድን ነው ብዬ እያሰብኩ ነበር። ኢየሱስ በሰማይ መግዛት የሚጀምረው በ1914 እንደሆነ አምላክ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር ማድረግ አይችልም ነበር?

      ዳዊት፦ ይህ በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው። እንዲያውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ያልተቀመጡ ብዙ ነገሮች አሉ። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ጥረት ይጠይቅባቸዋል፤ በመሆኑም ‘አምላክ መጽሐፍ ቅዱስን በዚህ መንገድ ያስጻፈው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ይነሳል። ስለዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ ስመጣ ብንነጋገርበት ምን ይመስልሃል?

      ኢዮብ፦ ደስ ይለኛል።

      ለመረዳት ያስቸገረህ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አለ? የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች ወይም ስለ ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸው ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስትገናኝ ጥያቄህን ከማቅረብ ወደኋላ አትበል። የይሖዋ ምሥክሮች ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከአንተ ጋር ለመወያየት ፈቃደኛ ናቸው።

      ከናቡከደነፆር ሕልም ጋር የተያያዙ ዓመታትንና ክስተቶችን የሚያሳይ ሠንጠረዥ
      ከናቡከደነፆር ሕልም ጋር የተያያዙ ዓመታትንና ክስተቶችን የሚያሳይ ሠንጠረዥ

      a የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ለማስተማር ባደረጉት ዝግጅት አማካኝነት ከሰዎች ጋር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ርዕስ በርዕስ ይወያያሉ።

      b በዚህ መጽሔት የጥቅምት 1, 2014 እትም ላይ የወጣውን “መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት—የአምላክ መንግሥት መግዛት የጀመረው መቼ ነው?—ክፍል 1” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

      c ዳንኤል 4:23-25⁠ን ተመልከት።

      d ራእይ 12:6, 14⁠ን (የ1980 ትርጉም) ተመልከት።

      e ዘኍልቍ 14:34⁠ን እና ሕዝቅኤል 4:6⁠ን ተመልከት።

      f “ናቡከደነፆር ስለ አንድ ዛፍ ያየው ሕልም” የተሰኘውን ሠንጠረዥ ተመልከት።

      g ራእይ 6:4

      h በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ተመልከት።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ