የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w22 ነሐሴ ገጽ 2-7
  • ወጣቶች—ከተጠመቃችሁ በኋላ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወጣቶች—ከተጠመቃችሁ በኋላ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ጎልማሳ ክርስቲያን መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
  • ግብ ማውጣት መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚረዳህ እንዴት ነው?
  • ፍቅርህ እያደገ ይሂድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • በመንፈሳዊ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • እድገት ማድረግህን ቀጥል
    ለዘላለም በደስታ ኑር!—አሳታፊ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ
  • መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2016
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2022
w22 ነሐሴ ገጽ 2-7

የጥናት ርዕስ 32

ወጣቶች—ከተጠመቃችሁ በኋላ እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ

“በሁሉም ነገር . . . በፍቅር እንደግ።”—ኤፌ. 4:15

መዝሙር 56 እውነትን የራስህ አድርግ

ማስተዋወቂያa

1. በርካታ ወጣቶች የትኞቹን መልካም ነገሮች አከናውነዋል?

በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ክርስቲያኖች ይጠመቃሉ። አንተስ ይህን እርምጃ ወስደሃል? ከሆነ፣ መንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ በአንተ ተደስተዋል፤ ይሖዋም ተደስቷል። (ምሳሌ 27:11) እስካሁን የትኞቹን ነገሮች እንዳከናወንክ እስቲ ቆም ብለህ አስብ። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት አጥንተሃል፤ ምናልባትም ያጠናኸው ለበርካታ ዓመታት ሊሆን ይችላል። ማጥናትህ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ እንድታምን አድርጎሃል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ባለቤት የሆነውን አምላክ ማወቅና መውደድ ችለሃል። ለይሖዋ ያለህ ፍቅር በጣም ስላደገ ራስህን ለእሱ ወስነህ ተጠምቀሃል። ይህ ምንኛ የሚያስደስት ነው!

2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

2 ከመጠመቅህ በፊት እምነትህ በተለያዩ መንገዶች እንደተፈተነ ምንም ጥያቄ የለውም። ዕድሜህ እየጨመረ ሲሄድ ደግሞ አዳዲስ ፈተናዎች ያጋጥሙሃል። ሰይጣን ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ለማዳከምና እሱን ማገልገልህን እንድታቆም ለማድረግ ይሞክራል። (ኤፌ. 4:14) ይህ እንዲሆን ፈጽሞ ልትፈቅድ አይገባም። ይሖዋን በታማኝነት ማገልገልህን ለመቀጠልና ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል ለመጠበቅ ምን ሊረዳህ ይችላል? እድገት ማድረግህን መቀጠል ማለትም ወደ ክርስቲያናዊ ‘ጉልምስና ለመድረስ መጣጣር’ አለብህ። (ዕብ. 6:1) ይሁንና ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ጎልማሳ ክርስቲያን መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

3. ሁሉም ክርስቲያኖች ከተጠመቁ በኋላ ምን ማድረግ አለባቸው?

3 እያንዳንዳችን ከተጠመቅን በኋላ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቹ የሰጣቸውን ምክር መከተል ይኖርብናል። ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን “ሙሉ ሰው” እንዲሆኑ አበረታቷቸዋል። (ኤፌ. 4:13) በሌላ አባባል ‘እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ’ ብሏቸዋል። ጳውሎስ መንፈሳዊ እድገትን ልጆች ከሚያደርጉት እድገት ጋር አመሳስሎታል። ወላጆች ሕፃን ልጃቸውን በጣም እንደሚወዱትና እንደሚኮሩበት ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ልጁ ሁልጊዜ ሕፃን ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ውሎ አድሮ “የልጅነትን ጠባይ” መተው አለበት። (1 ቆሮ. 13:11) ከክርስቲያኖች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ከተጠመቅን በኋላ እድገት ማድረጋችንን መቀጠል አለብን። ይህን ለማድረግ የሚረዱንን አንዳንድ ነጥቦች እስቲ እንመልከት።

4. መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚረዳህ የትኛው ባሕርይ ነው? አብራራ። (ፊልጵስዩስ 1:9)

4 ለይሖዋ ያለህን ፍቅር አሳድግ። አሁንም ይሖዋን በጣም እንደምትወደው ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ለእሱ ያለህን ፍቅር ማሳደግ ትችላለህ። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 1:9 ላይ አንዱን መንገድ ጠቁሟል። (ጥቅሱን አንብብ።) ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ፍቅራቸው “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድ” ጸልዮአል። ስለዚህ ፍቅራችን እየጨመረ እንዲሄድ ማድረግ እንችላለን ማለት ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው “ትክክለኛ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ” በማግኘት ነው። ይሖዋን ይበልጥ ባወቅነው መጠን ይበልጥ እንወደዋለን፤ እንዲሁም ለባሕርያቱና የተለያዩ ነገሮችን ለሚያከናውንበት መንገድ አድናቆት እናዳብራለን። እሱን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት ይጨምራል፤ እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር ማድረግ አንፈልግም። የእሱ ፈቃድ ምን እንደሆነ እንዲሁም ፈቃዱን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ጥረት እናደርጋለን።

5-6. ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳደግ የምንችለው እንዴት ነው? አብራራ።

5 ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል፤ በመሆኑም ስለ ኢየሱስ ይበልጥ በማወቅ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳደግ እንችላለን። (ዕብ. 1:3) ኢየሱስን ማወቅ የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው ዘዴ አራቱን ወንጌሎች ማጥናት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማድ እስካሁን ካላዳበርክ ለምን አሁን አትጀምርም? ስለ ኢየሱስ የሚናገሩትን ዘገባዎች ስታነብ በባሕርያቱ ላይ ትኩረት አድርግ። ኢየሱስ በቀላሉ የሚቀረብ ሰው ነበር፤ ትናንሽ ልጆችን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ አቅፏቸዋል። (ማር. 10:13-16) ደቀ መዛሙርቱ ነፃነት እንዲሰማቸው ያደርግ ነበር፤ እሱ ባለበት የፈለጉትን ነገር መናገር አይከብዳቸውም። (ማቴ. 16:22) በዚህ ረገድ ኢየሱስ የአባቱን ምሳሌ ተከትሏል። ይሖዋም በቀላሉ የሚቀረብ አምላክ ነው። ወደ እሱ መጸለይ እንችላለን። በምንጸልይበት ጊዜም ልባችንን በፊቱ ማፍሰስ እንችላለን። እንደማይኮንነን እርግጠኞች ነን። በጣም ይወደናል፤ ያስብልናል።—1 ጴጥ. 5:7

6 ኢየሱስ ለሰዎች ይራራ ነበር። ሐዋርያው ማቴዎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ሕዝቡንም ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።” (ማቴ. 9:36) ይሖዋስ ምን ይሰማዋል? ኢየሱስ “በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም” ብሏል። (ማቴ. 18:14) ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ኢየሱስን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ ለይሖዋ ያለን ፍቅር ያድጋል።

7. ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር መቀራረብህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

7 በጉባኤህ ውስጥ ካሉ የጎለመሱ ወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረብህም ይሖዋን ይበልጥ ለመውደድና መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ይረዳሃል። ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ልብ ብለህ ተመልከት። ይሖዋን ለማገልገል በመወሰናቸው ቅንጣት ታክል አይቆጩም። በይሖዋ አገልግሎት ሲካፈሉ ያገኟቸውን አንዳንድ ተሞክሮዎች እንዲነግሩህ ለምን አትጠይቃቸውም? አስፈላጊ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ምክር ጠይቃቸው። ደግሞም “ብዙ አማካሪዎች ባሉበት” ስኬት እንደሚገኝ አትርሳ።—ምሳሌ 11:14

ፎቶግራፎች፦ 1. አንዲት ወጣት እህት “ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው?” እና “የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች” የተባሉትን ብሮሹሮች ተጠቅማ ምርምር ስታደርግ። 2. እህት ትምህርት ቤት ውስጥ በአስተማሪዋ እና በክፍሏ ልጆች ፊት ማብራሪያ ስትሰጥ።

በትምህርት ቤት ስለ ዝግመተ ለውጥ ልትማር ትችላለህ፤ ለዚህ ሁኔታ መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 8-9⁠ን ተመልከት)

8. የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በተመለከተ ጥርጣሬ ካደረብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

8 ጥርጣሬህን አሸንፍ። በአንቀጽ 2 ላይ እንደተጠቀሰው ሰይጣን መንፈሳዊ እድገት እንዳታደርግ ሊያግድህ ይሞክራል። ለዚህ የሚጠቀምበት አንዱ ዘዴ አንዳንዶቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በተመለከተ ጥርጣሬ እንዲፈጠርብህ ማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክን የሚያቃልል ትምህርት ስለሆነው ስለ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ መማርህ አይቀርም። ልጅ እያለህ ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ እምብዛም አስበህበት አታውቅ ይሆናል። አሁን ግን ዕድሜህ ከፍ ስላለ ትምህርት ቤት ውስጥ ስለ ዝግመተ ለውጥ ትማር ይሆናል። አስተማሪዎችህ ዝግመተ ለውጥን ለመደገፍ የሚጠቅሷቸው ማስረጃዎች አሳማኝና ምክንያታዊ መስለው ሊታዩህ ይችላሉ። ሆኖም አስተማሪዎችህ ፈጣሪ መኖሩን ስለሚያሳየው ማስረጃ በቁም ነገር አስበውበት እንኳ አያውቁ ይሆናል። ምሳሌ 18:17 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት አስታውስ፤ ጥቅሱ “ክሱን አስቀድሞ ያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤ ይህም ሌላው ወገን መጥቶ እስኪመረምረው ድረስ ነው” ይላል። በትምህርት ቤት የምትማራቸውን ነገሮች በጭፍን ከማመን ይልቅ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች በጥንቃቄ መርምር። በጽሑፎቻችን ተጠቅመህ ምርምር አድርግ። ቀደም ሲል በዝግመተ ለውጥ ያምኑ የነበሩ ወንድሞችንና እህቶችን አነጋግር። የሚወደን ፈጣሪ እንዳለ ያሳመናቸው ምን እንደሆነ ጠይቃቸው። እንዲህ ያሉ ገንቢ ውይይቶችን ማድረግህ እውነታውን እንድታስተውል ይረዳሃል።

9. ከሜሊሳ ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

9 ሜሊሳb የተባለች እህት ስለ ፍጥረት ምርምር በማድረጓ በጣም ተጠቅማለች። እንዲህ ብላለች፦ “ትምህርት ቤት ውስጥ ስለ ዝግመተ ለውጥ የተማርንበት መንገድ በጣም አሳማኝ ይመስል ነበር። መጀመሪያ ላይ፣ ያደረብኝን ጥርጣሬ በተመለከተ ምርምር ማድረግ አስፈርቶኝ ነበር። ዝግመተ ለውጥን እውነት ሆኖ ባገኘውስ የሚል ስጋት አድሮብኝ ነበር። ሆኖም ይሖዋ በጭፍን እንድናገለግለው እንደማይፈልግ አስተዋልኩ። ስለዚህ ጥርጣሬ የፈጠሩብኝን ነገሮች በተመለከተ ምርምር አደረግኩ። ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (በአማርኛ አይገኝም) የሚለውን መጽሐፍ እንዲሁም ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እና የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የሚሉትን ብሮሹሮች አነበብኩ። እንዲህ በማድረጌ በጣም ተጠቅሜያለሁ። እንዲያውም አስቀድሜ ምርምር አድርጌ ቢሆን ኖሮ የተሻለ ነበር።”

10-11. የሥነ ምግባር ንጽሕናህን ለመጠበቅ ምን ሊረዳህ ይችላል? (1 ተሰሎንቄ 4:3, 4)

10 ከመጥፎ ምግባር ራቅ። በጉርምስና ዕድሜ ወቅት የፆታ ስሜት ሊያይል ይችላል፤ እንዲሁም የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽም ሌሎች ከፍተኛ ጫና ሊያሳድሩብህ ይችላሉ። ሰይጣን ለምኞቶችህ እጅ እንድትሰጥ ይፈልጋል። ታዲያ የሥነ ምግባር ንጽሕናህን ለመጠበቅ ምን ሊረዳህ ይችላል? (1 ተሰሎንቄ 4:3, 4⁠ን አንብብ።) በምትጸልይበት ወቅት የሚሰማህን ስሜት በሙሉ ግልጥልጥ አድርገህ ለይሖዋ ንገረው፤ እንዲሁም ብርታት እንዲሰጥህ ጠይቀው። (ማቴ. 6:13) ይሖዋ የሚፈልገው ሊረዳህ እንጂ ሊፈርድብህ እንዳልሆነ አስታውስ። (መዝ. 103:13, 14) መጽሐፍ ቅዱስም ሊረዳህ ይችላል። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሜሊሳ መጥፎ ሐሳቦችን ማሸነፍ አታግሏት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ማንበቤ ተስፋ እንዳልቆርጥ ረድቶኛል። የይሖዋ ንብረት እንደሆንኩ እንዲሁም እሱን ማገልገል እንደምፈልግ አስታውሶኛል።”—መዝ. 119:9

11 ችግሮችህን ብቻህን ለመፍታት አትሞክር። ስላጋጠመህ ፈተና ለወላጆችህ ንገራቸው። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ስላሉ የግል ጉዳዮች መናገር ቀላል አይደለም። ሆኖም እንዲህ ማድረግህ በጣም አስፈላጊ ነው። ሜሊሳ እንዲህ ብላለች፦ “ድፍረት ለማግኘት ከጸለይኩ በኋላ ስለ ችግሩ ለአባቴ ነገርኩት። ከዚያ በኋላ እፎይታ ተሰማኝ። ይሖዋ እንደኮራብኝ እርግጠኛ ነበርኩ።”

12. ጥሩ ውሳኔ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

12 በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመራ። እያደግክ ስትሄድ የራስህን ውሳኔ ለማድረግ ተጨማሪ ነፃነት ታገኛለህ። ሆኖም የሕይወት ተሞክሮህ አሁንም ውስን ነው። ታዲያ ከይሖዋ ጋር ያለህን ወዳጅነት የሚያበላሽ ስህተት ላለመሥራት ምን ይረዳሃል? (ምሳሌ 22:3) ካሪ የተባለች እህት ጥሩ ውሳኔ እንድታደርግ የረዳት ምን እንደሆነ ተናግራለች። የጎለመሱ ክርስቲያኖች ከእያንዳንዱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ቀጥተኛ ሕግ እንደማያስፈልጋቸው ተገነዘበች። “ሕጎችን ብቻ ሳይሆን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችንም መረዳት ነበረብኝ” ብላለች። አንተም መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ይህ ዘገባ ስለ ይሖዋ አስተሳሰብ ምን ያስተምረኛል? በሕይወቴ ውስጥ ልጠቀምባቸው የምችላቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል? እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ (መዝ. 19:7፤ ኢሳ. 48:17, 18) መጽሐፍ ቅዱስን ስታነብና በውስጡ ባሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ስታሰላስል ይሖዋን የሚያስደስቱ ውሳኔዎችን ማድረግ ቀላል ይሆንልሃል። እድገት ማድረግህን ስትቀጥል የይሖዋን አስተሳሰብ ስለምትረዳ ከእያንዳንዱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ቀጥተኛ ሕግ እንደማያስፈልግህ ታስተውላለህ።

ሁለት ወጣት እህቶች አብረው “መጠበቂያ ግንብ” ሲዘጋጁ።

አንዲት ወጣት ምን ዓይነት ጓደኞች መርጣለች? (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

13. ጥሩ ጓደኞች ምን ዓይነት ተጽዕኖ ሊያሳድሩብህ ይችላሉ? (ምሳሌ 13:20)

13 ይሖዋን የሚወዱ ጓደኞች ምረጥ። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የጓደኛ ምርጫህ በመንፈሳዊ እድገትህ ላይ ትልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ምሳሌ 13:20⁠ን አንብብ።) ለምሳሌ ሣራ የተባለች እህት ደስታዋን አጥታ ነበር። ከዚያ ግን አመለካከቷን ለመቀየር የሚረዳ ነገር አጋጠማት። ሣራ እንዲህ ብላለች፦ “ልክ በሚያስፈልገኝ ጊዜ ጥሩ ጓደኞች አገኘሁ። ከአንዲት ወጣት እህት ጋር በየሳምንቱ አብረን መጠበቂያ ግንብ እንዘጋጅ ነበር። ሌላ ጓደኛዬ ደግሞ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት እንድጀምር ረዳችኝ። ጓደኞቼ ባሳደሩብኝ በጎ ተጽዕኖ የተነሳ የግል ጥናትንና ጸሎትን በቁም ነገር መመልከት ጀመርኩ። ከይሖዋ ጋር ያለኝ ወዳጅነት መጠናከር ጀመረ፤ ደስታዬም ተመለሰልኝ።”

14. ጁሊየን ጥሩ ጓደኞች ማፍራት የቻለው እንዴት ነው?

14 በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ጓደኞችን ማፍራት የምትችለው እንዴት ነው? በአሁኑ ወቅት የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ጁሊየን እንዲህ ብሏል፦ “በወጣትነቴ ከተለያዩ ወንድሞች ጋር አብሬ በማገልገል ጥሩ ጓደኞች ማፍራት ችያለሁ። እነዚህ ጓደኞቼ በቅንዓት ያገለግሉ ነበር። አገልግሎት ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ እንድገነዘብ ረዱኝ። በመሆኑም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ግብ አወጣሁ። በተጨማሪም የዕድሜ እኩዮቼን ብቻ ጓደኛ ማድረጌ ተጨማሪ ጥሩ ጓደኞች የማግኘት አጋጣሚ አሳጥቶኝ እንደነበር ተገነዘብኩ። በኋላም በቤቴል ጥሩ ጓደኞች አገኘሁ። የእነሱ ምሳሌ በመዝናኛ ምርጫዬ ረገድ ማሻሻያ እንዳደርግ ረድቶኛል። ይህም ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ አስችሎኛል።”

15. ጳውሎስ ጓደኝነትን በተመለከተ ለጢሞቴዎስ ምን ማሳሰቢያ ሰጥቶታል? (2 ጢሞቴዎስ 2:20-22)

15 በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው መጥፎ ተጽዕኖ እያሳደረብህ እንዳለ ብትገነዘብስ? ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች መንፈሳዊ አመለካከት እንደሌላቸው ተገንዝቦ ነበር፤ በመሆኑም እንዲህ ካሉ ሰዎች እንዲርቅ ጢሞቴዎስን አሳስቦታል። (2 ጢሞቴዎስ 2:20-22⁠ን አንብብ።) ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት በጣም ውድ ነው። ከፍተኛ ጥረት አድርገን ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ማንም ሰው እንዲያበላሽብን ልንፈቅድ አይገባም።—መዝ. 26:4

ግብ ማውጣት መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚረዳህ እንዴት ነው?

16. ምን ዓይነት ግቦች ማውጣት ይኖርብሃል?

16 ጠቃሚ ግቦች አውጣ። እምነትህን ለማጠናከርና ይበልጥ ጎልማሳ ለመሆን የሚረዱህን ግቦች አውጣ። (ኤፌ. 3:16) ለምሳሌ የግል ጥናት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ልማድህን ለማሻሻል ትወስን ይሆናል። (መዝ. 1:2, 3) ወይም ደግሞ አዘውትረህ መጸለይና የጸሎትህን ይዘት ማሻሻል እንደሚያስፈልግህ ታስተውል ይሆናል። ምናልባትም ከመዝናኛ ምርጫ ወይም ከጊዜ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ይበልጥ ራስህን መግዛት ያስፈልግህ ይሆናል። (ኤፌ. 5:15, 16) ይሖዋ እድገት ማድረግህን ለመቀጠል የምታደርገውን ጥረት ሲያይ በጣም ይደሰታል።

“መጠበቂያ ግንብ” ሲዘጋጁ ከነበሩት እህቶች አንዷ አንዲትን አረጋዊት እህት አስቤዛ ለመግዛት ስትረዳ።

ይህች ወጣት እህት የትኞቹን ግቦች አውጥታለች? (አንቀጽ17⁠ን ተመልከት)

17. ሌሎችን መርዳት ምን ጥቅም ያስገኛል?

17 ሌሎች ሰዎችን ስትረዳ ይበልጥ ጎልማሳ ትሆናለህ። ኢየሱስ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” ብሏል። (ሥራ 20:35) ጊዜህንና የወጣትነት ጉልበትህን ተጠቅመህ ሌሎችን የምትረዳ ከሆነ አንተም በእጅጉ ትጠቀማለህ። ለምሳሌ በጉባኤህ ውስጥ ያሉ አረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን ለመርዳት ግብ ማውጣት ትችላለህ። ምናልባትም ልትላላክላቸው ወይም በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አጠቃቀም ረገድ ልታግዛቸው ትችል ይሆናል። ወንድም ከሆንክ፣ ወንድሞችህንና እህቶችህን ይበልጥ ማገልገል እንድትችል የጉባኤ አገልጋይ የመሆን ግብ አውጣ። (ፊልጵ. 2:4) የመንግሥቱን ምሥራች በማካፈል ከክርስቲያን ጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎችም ፍቅር ማሳየት ትችላለህ። (ማቴ. 9:36, 37) ሁኔታህ የሚፈቅድልህ እስከሆነ ድረስ በአንድ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ለመካፈል ግብ አውጣ።

18. በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈልህ መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚረዳህ እንዴት ነው?

18 የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ አጋጣሚዎችን ይከፍትልሃል። በአቅኚነት ማገልገልህ በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት እንድትካፈል በር ሊከፍትልህ ይችላል። በቤቴል ማገልገል ወይም በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ መካፈል ትችል ይሆናል። ኬትሊን የተባለች ወጣት አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ከተጠመቅኩ በኋላ መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ የረዳኝ ዋነኛው ነገር ተሞክሮ ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር አብሬ ማገልገሌ ነው። የእነሱ ምሳሌነት የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀቴን እንዳሳድግ እንዲሁም የማስተማር ችሎታዬን እንዳሻሽል አነሳስቶኛል።”

19. መንፈሳዊ እድገት ማድረግህን መቀጠልህ የትኞቹን በረከቶች ያስገኝልሃል?

19 መንፈሳዊ እድገት ማድረግህን መቀጠልህ ብዙ በረከቶችን ያስገኝልሃል። ከንቱ ግቦችን በማሳደድ ዕድሜህን አታባክንም። (1 ዮሐ. 2:17) መጥፎ ውሳኔዎችን ማድረግ ከሚያስከትለው የስሜት ሥቃይ ትድናለህ። በተቃራኒው እውነተኛ ስኬትና ደስታ ታገኛለህ። (ምሳሌ 16:3) መልካም ምሳሌነትህ ወጣቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ የእምነት ባልንጀሮችህን ያበረታታል። (1 ጢሞ. 4:12) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋን ማስደሰትና ከእሱ ጋር የቅርብ ወዳጅነት መመሥረት የሚያስገኘውን ሰላምና እርካታ ታጣጥማለህ።—ምሳሌ 23:15, 16

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ከተጠመቅን በኋላ እድገት ማድረጋችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

  • አንድ ወጣት መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ የትኞቹን እርምጃዎች መውሰድ ይችላል?

  • ጠቃሚ ግቦችን ማውጣታችን መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ የሚረዳን እንዴት ነው?

መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ

a ወጣቶች ሲጠመቁ ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች በጣም ይደሰታሉ። እርግጥ ነው፣ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ከተጠመቁ በኋላ መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን መቀጠል አለባቸው። ይህ ርዕስ፣ በቅርቡ የተጠመቁ ወጣት ክርስቲያኖች ወደ መንፈሳዊ ጉልምስና ለመድረስ እድገት ማድረግ የሚችሉባቸውን የተለያዩ መንገዶች ያብራራል፤ ይህም ለመላው ጉባኤ ጥቅም ያስገኛል።

b አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ