ኃይል የሚያገኙት ከየት ነው?
በዚህ ፎቶ ላይ ያለውን ቢራቢሮ በደንብ ብትመለከተው ከአራቱ ክንፎቹ አንዱ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጪ እንደሆነ ትረዳለህ። ሆኖም ቢራቢሮው መመገቡንና መብረሩን አላቋረጠም። ይህ እንግዳ የሆነ ነገር አይደለም። ቢራቢሮዎች ክንፋቸው 70 በመቶ ተጎድቶ ዕለታዊ ተግባራቸውን ሲያከናውኑ ተስተውለዋል።
በተመሳሳይም ብዙ ሰዎች የቆራጥነት መንፈስ አሳይተዋል። ከባድ አካላዊ ወይም ስሜታዊ ችግሮች ቢያጋጥሟቸውም እንኳ ተስፋ አልቆረጡም።—ከ2 ቆሮንቶስ 4:16 ጋር አወዳድር።
ሐዋርያው ጳውሎስ በሚስዮናዊ ጉዞዎቹ ወቅት ያጋጠሙትን ከባድ ችግሮች በጽናት ተወጥቷቸዋል። ተገርፏል፣ ተደብድቧል፣ በድንጋይ ተወግሯል እንዲሁም ታስሯል። ከዚህም በላይ በአንድ ዓይነት ሕመም ምክንያት ተሠቃይቷል፤ ምናልባት የማያቋርጥ ‘የሥጋ መውጊያ’ የሆነበት የዓይን ችግር ሳይሆን አይቀርም።—2 ቆሮንቶስ 12:7-9፤ ገላትያ 4:15
የመንፈስ ጭንቀት በየጊዜው ያስከትልበት ከነበረው ከባድ ሥቃይ ጋር ለብዙ ዓመታት ሲታገል የነበረ ዴቪድ የተባለ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ያስቻለው ይሖዋ የሰጠው ኃይል እንደሆነ ያምናል። እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “በተደጋጋሚ ጊዜያት በብዙ ትግል ያደረግሁት መሻሻል እልም ብሎ የጠፋ ያህል ሆኖ ይሰማኝ ነበር። እንዲህ ዓይነቱ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ሲያጋጥመኝ ሙሉ በሙሉ በይሖዋ እታመን ነበር፤ ይሖዋም በእርግጥ ረድቶኛል። ያለማቋረጥ ለብዙ ሰዓታት የምጸልይባቸው ጊዜያት ነበሩ። ይሰማኝ የነበረው የብቸኝነትም ሆነ ምንም ዋጋ የለኝም የሚለው ስሜት ከይሖዋ ጋር ስነጋገር ይወገድ ነበር። የነበረብኝን ከፍተኛ ድካም ለመቋቋም ለረጅም ጊዜ እታገል የነበረ ቢሆንም በይሖዋ እርዳታ ከዚህ ድካም ከመላቀቄም አልፎ ሌሎችን መርዳት የምችልበት ኃይል አግኝቻለሁ።”
ይሖዋ አምላክ ጳውሎስን አበርትቶታል። በዚህም ምክንያት ጳውሎስ “ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝና” ሊል ችሏል። (2 ቆሮንቶስ 12:10) አዎን፣ ጳውሎስ የነበረበት ድካም አምላክ በሚሰጠው ኃይል እንዲታመን አድርጎታል። ሐዋርያው “ኃይልን በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ብርታት አገኛለሁ” ብሏል። (ፊልጵስዩስ 4:13 አዓት) በእርግጥም ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ኃይል ይሰጣቸዋል።