-
ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?—ክፍል 1፦ አምላክ መኖሩን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?የወጣቶች ጥያቄ
-
-
የወጣቶች ጥያቄ
ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?—ክፍል 1፦ አምላክ መኖሩን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?
ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?
አምላክ ሁሉንም ነገሮች እንደፈጠረ ታምናለህ? ከሆነ ብቻህን አይደለህም፤ ብዙ ወጣቶች እንዲሁም አዋቂዎች ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ሕይወትም ሆነ ጽንፈ ዓለም የተገኘው የፈጣሪ እጅ ሳይኖርበት በዝግመተ ለውጥ እንደሆነ የሚያምኑም አሉ።
ይህን ታውቅ ነበር? ብዙውን ጊዜ እንደሚታየው ሁለቱም ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች በምን እንደሚያምኑ ከመናገር ባለፈ እንደዚያ ያመኑት ለምን እንደሆነ በእርግጠኝነት አያውቁም።
አንዳንድ ሰዎች ሕይወት በፍጥረት እንደተገኘ የሚያምኑት በቤተ ክርስቲያን እንደዚያ ተብለው ስለተማሩ ብቻ ነው።
ብዙ ሰዎች በዝግመተ ለውጥ የሚያምኑት በትምህርት ቤት እንደዚያ ተብለው ስለተማሩ ብቻ ነው።
እነዚህ ተከታታይ ርዕሶች፣ ሁሉ ነገር የመጣው በፍጥረት እንደሆነ ያለህን እምነት ማጠናከርና የምታምንበትን ነገር ለሌሎች ማስረዳት እንድትችል ይጠቅሙሃል። በመጀመሪያ ግን የሚከተለውን መሠረታዊ ጥያቄ ራስህን ጠይቅ፦
አምላክ መኖሩን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?
ይህን ጥያቄ መመለስህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ፣ አእምሮህን ይኸውም ‘የማሰብ ችሎታህን’ እንድትጠቀም ያበረታታል። (ሮም 12:1) በመሆኑም አምላክ መኖሩን የምታምነው በሚከተሉት ነገሮች ላይ የተነሳ መሆን የለበትም፦
ስሜት (እንዲሁ ከሰው የሚበልጥ አንድ አካል እንዳለ ይሰማኛል)
የሌሎች ተጽዕኖ (የምኖረው ሃይማኖተኛ በሆነ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው)
ጫና (ወላጆቼ በአምላክ ማመን እንዳለብኝ ነግረውኛል፤ እንዲህ ባላደርግ ግን . . .)
ከዚህ ይልቅ አምላክ መኖሩን አንተ ራስህ ልታረጋግጥና ስለምታምንበት ነገር በቂ ምክንያት ሊኖርህ ይገባል።
አምላክ መኖሩን እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው? “አምላክ መኖሩን እንዳምን ያደረገኝ ምንድን ነው?” የሚለው የመልመጃ ሣጥን ስለምታምንበት ነገር እርግጠኛ እንድትሆን ይረዳሃል። በተጨማሪም ሌሎች ወጣቶች ለዚህ ጥያቄ የሰጡትን መልስ ማንበብህ ሊጠቅምህ ይችላል።
“ክፍል ውስጥ አስተማሪው ሰውነታችን ስለሚሠራበት መንገድ ሲያስረዳን አምላክ መኖሩን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆንኩ። በጣም ትንሽ የሚመስሉትን ጨምሮ በሰውነታችን ውስጥ እያንዳንዱን ሥራ የሚያከናውኑ የአካላችን ክፍሎች አሉ፤ ብዙውን ጊዜ እነዚህ ሥራዎች የሚከናወኑት እኛ ሳናስተውለው ነው። የሰው አካል በእርግጥም አስደናቂ ነው!”—ቴሬዛ
“ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ፣ ግዙፍ መርከብ ወይም መኪና ስመለከት ‘ይህን የሠራው ማን ነው?’ ብዬ ራሴን እጠይቃለሁ። ለምሳሌ መኪናን የሠሩት ማሰብ የሚችሉ የሰው ልጆች ናቸው፤ መኪናው መንቀሳቀስ እንዲችል በውስጡ ያሉት ትናንሽ ነገሮች በሙሉ በትክክል መሥራት መቻል አለባቸው። አንድ መኪና ንድፍ አውጪ ካስፈለገው እኛ የሰው ልጆች የተሠራንበት መንገድም ያው ነው።”—ሪቻርድ
“ብሩህ አእምሮ ያላቸው ሰዎች እንኳ ለብዙ መቶ ዓመታት ምርምር በማድረግ ስለ ጽንፈ ዓለም ማወቅ የቻሉት ነገር በጣም አነስተኛ ነው፤ ከዚህ አንጻር፣ ጽንፈ ዓለም የመጣው የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ሳይፈጥረው ነው ብሎ ማሰብ ጨርሶ ምክንያታዊ አይደለም!”—ካረን
“ስለ ሳይንስ ይበልጥ በተማርኩ ቁጥር ዝግመተ ለውጥ ሊታመን የሚችል አለመሆኑን ይበልጥ እየተረዳሁ መጣሁ። ለምሳሌ ያህል፣ በተፈጥሮ ላይ የሚታዩት ንድፎች በሒሳብ ስሌት ቢቀመጡ ዝንፍ የማይሉ መሆናቸውን አስባለሁ፤ እንዲሁም የሰው ልጆች ከሌሎች ፍጥረታት በተለየ መልኩ ማን እንደሆኑ፣ ከየት እንደመጡና ስለ ወደፊቱ ጊዜ የማወቅ ጉጉት ያላቸው መሆኑ ያስገርመኛል። ዝግመተ ለውጥ እነዚህን ነገሮች ለማብራራት የሰው ልጆችን ከእንስሳት ጋር አያይዞ ይገልጽ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የሰው ልጆች ልዩ የሆኑበትን ምክንያት ማብራራት አልቻለም። እንደ እኔ እንደ እኔ፣ ይበልጥ ‘እምነት’ የሚጠይቀው በዝግመተ ለውጥ ማመን እንጂ በፈጣሪ ማመን አይደለም።”—አንቶኒ
የማምንበትን ነገር ማስረዳት የምችልበት መንገድ
አብረውህ የሚማሩ ልጆች ‘እንዴት በማታየው ነገር ታምናለህ?’ ብለው ቢያሾፉብህስ? ዝግመተ ለውጥ በሳይንስ “የተረጋገጠ” ሐቅ እንደሆነ ቢነግሩህስ?
በመጀመሪያ ደረጃ፣ ስለምታምንበት ነገር እርግጠኛ ሁን። መሸማቀቅ ወይም መፍራት የለብህም። (ሮም 1:16) ደግሞም የሚከተሉትን ነጥቦች አትዘንጋ፦
እንዲህ ብለህ የምታምነው አንተ ብቻ አይደለህም፤ ብዙ ሰዎች አምላክ መኖሩን ያምናሉ። ከእነዚህም መካከል በሙያቸው የላቁ የተማሩ ሰዎች ይገኙበታል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ መኖሩን የሚያምኑ የሳይንስ ሊቃውንት አሉ።
ሰዎች አምላክ መኖሩን እንደማያምኑ የሚናገሩት ስለ እሱ መረዳት ያልቻሉት ነገር ስላለ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ስለሚያምኑበት ነገር ማስረጃ ከማቅረብ ይልቅ እንደሚከተለው ያሉ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፦ “አምላክ ካለ፣ መከራ ሲደርስ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?” በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ጉዳዩን የሚመለከቱት ከሳይንሳዊ ማስረጃ አንጻር አይደለም።
የሰው ልጆች “መንፈሳዊ” ፍላጎት አላቸው። (ማቴዎስ 5:3) ሰዎች በአምላክ የማመን ፍላጎት አላቸው። በመሆኑም አንድ ሰው አምላክ እንደሌለ ቢነግርህ ስለደረሰበት መደምደሚያ ማብራሪያ መስጠት ያለበት እሱ እንጂ አንተ አይደለህም።—ሮም 1:18-20
አምላክ መኖሩን ማመን ምክንያታዊ ነው። ሕይወት ያለው ነገር በራሱ ሊመጣ እንደማይችል ከሚገልጸው የተረጋገጠ ሐቅ ጋር ይስማማል። ሕይወት ያለው ነገር፣ ሕይወት ከሌለው ነገር እንደመጣ የሚገልጸው ሐሳብ በማስረጃ ሊረጋገጥ አልቻለም።
ታዲያ አንድ ሰው በአምላክ መኖር በማመንህ ላይ ጥያቄ ቢያነሳ ምን ብለህ ልትመልስለት ትችላለህ? አንዳንድ አማራጮችን እስቲ እንመልከት።
አንድ ሰው እንዲህ ቢልህ፦ “አምላክ እንዳለ የሚያምኑት ያልተማሩ ሰዎች ብቻ ናቸው።”
እንዲህ ብለህ ልትመልስለት ትችላለህ፦ “ይህ አመለካከት እውነታውን ያገናዘበ እንደሆነ አይሰማኝም። እንዲያውም በተለያዩ እውቅ ዩኒቨርሲቲዎች በሚሠሩ ከ1,600 በሚበልጡ የሳይንስ ፕሮፌሰሮች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በአምላክ መኖር እንደማያምኑ ወይም መኖሩን እንደሚጠራጠሩ አልገለጹም።a እነዚህ ፕሮፌሰሮች አምላክ መኖሩን በማመናቸው ብቻ ያልተማሩ ናቸው ትላለህ?”
አንድ ሰው እንዲህ ቢልህ፦ “አምላክ ካለ፣ መከራ ሲደርስ ዝም ብሎ የሚመለከተው ለምንድን ነው?”
እንዲህ ብለህ ልትመልስለት ትችላለህ፦ “ምናልባት እንዲህ ያልከው አምላክ የሚያደርገውን ነገር ስላልተረዳህ ይኸውም እስካሁን ለምን እርምጃ እንዳልወሰደ ግልጽ ስላልሆነልህ ይሆናል። ትክክል ነኝ? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] ዛሬ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው መከራ ይህን ያህል የበዛው ለምን እንደሆነ አጥጋቢ መልስ አግኝቻለሁ። ይሁን እንጂ መልሱን ለመረዳት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን መመርመር አስፈላጊ ነው። ታዲያ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ?”
ቀጣዩ ርዕስ፣ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ እኛ ስለተገኘንበት መንገድ አጥጋቢ መልስ አይሰጥም የምንለው ለምን እንደሆነ ያብራራል።
a ምንጭ፦ Social Science Research Council, “Religion and Spirituality Among University Scientists,” by Elaine Howard Ecklund , February 5, 2007.
-
-
ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?-ክፍል 2፦ ዝግመተ ለውጥ ትክክል መሆኑን ልትጠራጠር የሚገባው ለምንድን ነው?የወጣቶች ጥያቄ
-
-
የወጣቶች ጥያቄ
ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?-ክፍል 2፦ ዝግመተ ለውጥ ትክክል መሆኑን ልትጠራጠር የሚገባው ለምንድን ነው?
አሌክስ ግራ ተጋብቷል። አምላክ እንዳለና ሕይወት የተገኘው በፍጥረት እንደሆነ ያምናል። ዛሬ ግን የባዮሎጂ መምህሩ፣ ዝግመተ ለውጥ አሳማኝ ሳይንሳዊ ማስረጃ ያለው ሐቅ እንደሆነ አስረግጦ ተናገረ። አሌክስ ሞኝ ተደርጎ መታየት አልፈለገም። በመሆኑም እንዲህ ብሎ አሰበ፦ ‘የሳይንስ ሊቃውንት ዝግመተ ለውጥ እውነት እንደሆነ ካረጋገጡ እኔ ማን ሆኜ ነው የማልቀበለው?’
አንተስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞህ ያውቃል? ምናልባት “እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” የሚለውን ሐሳብ ከልጅነትህ ጀምሮ ታምንበት ይሆናል። (ዘፍጥረት 1:1) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በፍጥረት ማመን የተሳሳተ እንደሆነ፣ ዝግመተ ለውጥ ደግሞ የተረጋገጠ ሐቅ እንደሆነ አንዳንዶች ሊያሳምኑህ ሞክረው ሊሆን ይችላል። ታዲያ ልታምናቸው ይገባል? ዝግመተ ለውጥ ትክክል መሆኑን ልትጠራጠር የሚገባው ለምንድን ነው?
ዝግመተ ለውጥ ትክክል መሆኑን እንድትጠራጠር የሚያደርጉ ሁለት ምክንያቶች
የሳይንስ ሊቃውንት ዝግመተ ለውጥን በተመለከተ እርስ በርሳቸው አይስማሙም። የሳይንስ ሊቃውንት ስለ ዝግመተ ለውጥ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ምርምር ቢያደርጉም ሁሉንም ሊያስማማ የሚችል ማብራሪያ ላይ መድረስ አልቻሉም።
እስቲ አስበው፦ በጉዳዩ እውቀት አላቸው የሚባሉት የሳይንስ ሊቃውንት እንኳ ዝግመተ ለውጥን በተመለከተ አንድ ዓይነት ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ አንተ በዚህ ጽንሰ ሐሳብ ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ብታነሳ ምን ይደንቃል?—መዝሙር 10:4
የምታምነው ነገር በሕይወትህ ላይ ለውጥ ያመጣል። ዛካሪ የተባለ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “ሕይወት የተገኘው በአጋጣሚ ከሆነ የእኛ ሕይወትም ሆነ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉት ነገሮች በሙሉ ምንም ዓላማ የላቸውም ማለት ነው።” ይህ ወጣት የተናገረው ሐሳብ እውነት ነው። ደግሞስ ሕይወት የተገኘው በዝግመተ ለውጥ ከሆነ የመኖራችን ዓላማ ምንድን ነው? (1 ቆሮንቶስ 15:32) በሌላ በኩል ግን ሁሉም ነገር የተገኘው በፍጥረት ከሆነ ስለምንኖርበት ዓላማ እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስመልክቶ ለሚነሱብን ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ማግኘት እንችላለን።—ኤርምያስ 29:11
እስቲ አስበው፦ ስለ ዝግመተ ለውጥ እና ስለ ፍጥረት እውነቱን ማወቅህ በሕይወትህ ላይ ለውጥ የሚያመጣው እንዴት ነው?—ዕብራውያን 11:1
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጥያቄዎች
የአንዳንዶች አመለካከት፦ ‘በጽንፈ ዓለም ውስጥ ያሉ ነገሮች በሙሉ የተገኙት ቢግ ባንግ ተብሎ በሚጠራ አንድ ድንገተኛ ፍንዳታ የተነሳ ነው።’
ይህ ፍንዳታ እንዲካሄድ ያደረገው ማን ነው? ወይም ምንድን ነው?
ይበልጥ ምክንያታዊ የሆነው የትኛው ነው? ሁሉም ነገር የተገኘው ከምንም እንደሆነ ማመን ነው ወይስ ሁሉንም ነገር ያስገኘ አንድ ነገር ወይም አካል እንዳለ አምኖ መቀበል?
የአንዳንዶች አመለካከት፦ ‘የሰው ልጆች፣ ከእንስሳት በዝግመተ ለውጥ ተሻሽለው የመጡ ናቸው።’
የሰው ልጆች የመጡት ከእንስሳት ለምሳሌ ያህል እንደ ዝንጀሮ ካሉ እንስሳት በዝግመተ ለውጥ ተሻሽለው ከሆነ በሰዎች እና በዝንጀሮዎች የማሰብ ችሎታ መካከል ይህን ያህል ልዩነት ሊኖር የቻለው እንዴት ነው?a
ውስብስብ እንዳልሆኑ ተደርገው የሚቆጠሩ ሕይወት ያላቸው ነገሮች እንኳ እጅግ ሲበዛ ውስብስብ የሆኑት ለምንድን ነው?b
የአንዳንዶች አመለካከት፦ ‘ዝግመተ ለውጥ እውነት መሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል።’
እንዲህ ብሎ የተናገረው ሰው ራሱ ማስረጃውን መርምሯል?
በትምህርታቸው የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎች በሙሉ በዝግመተ ለውጥ እንደሚያምኑ ስለተነገራቸው ብቻ ይህን ትምህርት አምነው የሚቀበሉት ስንቶቹ ናቸው?
a በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች፣ ዝንጀሮ መሰል የሆኑ እንስሳት እንደ እኛ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ የሌላቸው የአንጎላቸው መጠን ከእኛ ስለሚያንስ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና ይህ የመከራከሪያ ነጥብ ትክክል አይደለም፤ እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ ለማወቅ የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባለውን ብሮሹር ገጽ 28 ተመልከት።
-
-
ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?—ክፍል 3፦ ፈጣሪ እንዳለ የማምነው ለምንድን ነው?የወጣቶች ጥያቄ
-
-
የወጣቶች ጥያቄ
ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?—ክፍል 3፦ ፈጣሪ እንዳለ የማምነው ለምንድን ነው?
“ፈጣሪ እንዳለ የምታምን ከሆነ ሰዎች ሞኝ አድርገው ሊመለከቱህ ይችላሉ፤ ይህ ዓይነት እምነት ሊኖርህ የቻለው ወላጆችህ የነገሩህን ወይም ሃይማኖትህ ያስተማረህን በጭፍን ስለምትቀበል እንደሆነ ይሰማቸዋል።”—ጃኔት
አንተስ እንደ ጃኔት ተሰምቶህ ያውቃል? ምናልባትም ‘ፈጣሪ እንዳለ ማመኔ ትክክል ነው?’ በማለት አስበህ ይሆናል። በዚያ ላይ ደግሞ ማንም ሰው ቢሆን ሞኝ ተደርጎ እንዲቆጠር አይፈልግም። ታዲያ ፈጣሪ መኖሩን እርግጠኛ እንድትሆን ምን ሊረዳህ ይችላል?
በምታምንበት ነገር ላይ ሊሰነዘር የሚችል ተቃውሞ
1. ፈጣሪ እንዳለ የምታምን ከሆነ ሰዎች ሳይንስን እንደማትቀበል ይሰማቸዋል።
“አስተማሪያችን፣ ‘ፈጣሪ እንዳለ የሚያምኑት፣ ዓለማችን እንዴት እንደመጣ ለመመርመር የሚሰንፉ ሰዎች ናቸው’ በማለት ተናገረች።”—ማሪያ
ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች ከግምት ውስጥ ያላስገቧቸው አንዳንድ እውነታዎች አሉ። እንደ አይዛክ ኒውተን እና ጋሊሊዮ ያሉ ታዋቂ የሳይንስ ባለሙያዎች ፈጣሪ መኖሩን ያምኑ ነበር። ይሁንና ፈጣሪ እንዳለ ማመናቸው ለሳይንስ ፍቅር እንዳይኖራቸው አላገዳቸውም። በዛሬው ጊዜም ፈጣሪ መኖሩን ማመን ከሳይንስ ጋር እንደማይጋጭ የሚያምኑ የሳይንስ ባለሙያዎች አሉ።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ፈጣሪ መኖሩን የሚያምኑ አንዳንድ የሕክምና እና የሳይንስ ባለሙያዎች የተናገሩትን ለማንበብ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍትን ክፈት፤ ከዚያም በፍለጋ ሣጥኑ ላይ “ስለምታምንበት ነገር ምን ትላለች” ወይም “ስለሚያምንበት ነገር ምን ይላል” ወይም “ስለሚያምኑበት ነገር ምን ይላሉ” የሚሉትን ሐረጎች (ትዕምርተ ጥቅሶቹን ጨምረህ) ጻፍ። እነዚህ ሰዎች በፈጣሪ እንዲያምኑ የረዳቸው ምን እንደሆነ የተናገሩትን ሐሳብ ልብ በል።
ዋናው ነጥብ፦ ፈጣሪ እንዳለ ስላመንክ ብቻ ፀረ ሳይንስ ነህ ማለት አይደለም። እንዲያውም ስለ ተፈጥሮ ይበልጥ ስትማር ሁሉንም ነገር የፈጠረው አምላክ እንደሆነ ያለህ እምነት ይጠናከራል።—ሮም 1:20
2. መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት በሚናገረው ሐሳብ የምታምን ከሆነ ሰዎች አክራሪ ሃይማኖተኛ እንደሆንክ ይሰማቸዋል።
“ብዙ ሰዎች፣ ፈጣሪ አለ ብሎ ማመን ቀልድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። እነዚህ ሰዎች ‘በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ተረት ነው’ ብለው ያስባሉ።”—ጃዝሚን
ልታውቀው የሚገባ ነገር፦ ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚናገረውን ሐሳብ የሚረዱበት መንገድ የተሳሳተ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በፍጥረት እናምናለን የሚሉ አንዳንድ ሰዎች (ክሪኤሽኒስቶች) ምድር ከተፈጠረች ብዙ ጊዜ እንዳልሆናት እንዲሁም ሕይወት ያላቸው ነገሮች የተፈጠሩት እያንዳንዳቸው የ24 ሰዓት ርዝመት ባላቸው ስድስት ቀናት ውስጥ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ ሁለቱንም ሐሳቦች አይደግፍም።
ዘፍጥረት 1:1 “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ይናገራል። ይህ ሐሳብ፣ ምድር የተፈጠረችው በቢሊዮኖች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት እንደሆነ ከሚገልጸው ሳይንሳዊ ሐሳብ ጋር አይጋጭም።
በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው “ቀን” የሚለው ቃል ረዘም ያለ ጊዜን ሊያመለክት ይችላል። እንዲያውም በዘፍጥረት 2:4 (የ1954 ትርጉም) ላይ “ቀን” የሚለው ቃል ስድስቱን የፍጥረት ቀናት በሙሉ ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ዋናው ነጥብ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት የሚናገረው ሐሳብ በሳይንስ ከተረጋገጡ እውነታዎች ጋር ይስማማል።
ስለምታምንበት ነገር አስብ
ፈጣሪ እንዳለ የምናምነው በጭፍን አይደለም። እንዲያውም እንዲህ ዓይነት እምነት ማመዛዘንን ይጠይቃል። እስቲ የሚከተለውን ሐሳብ ልብ በል፦
በየቀኑ የምትመለከታቸው ነገሮች በሙሉ አንድ ንድፍ ካለ ያንን ንድፍ ያወጣ አካል እንደሚኖር ይጠቁማሉ። አንድን የፎቶ ካሜራ፣ አውሮፕላን ወይም ቤት ስትመለከት እነዚህን ነገሮች የሠራ ሰው እንዳለ ማሰብህ አይቀርም። ታዲያ ዓይናችንን፣ በሰማይ ላይ የምትበረውን ወፍ ወይም ምድርን የሠራ አካል የለም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው?
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ መሐንዲሶች በፍጥረታት ላይ የሚታዩትን ንድፎች በመመልከት በፈጠራ ሥራዎቻቸው ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎችን ያደርጋሉ፤ ደግሞም ለፈጠራ ሥራዎቻቸው ተገቢው እውቅና እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ። ታዲያ ሰዎች ላከናወኑት የፈጠራ ሥራ እውቅና እየሰጠን ከሁሉ የተሻሉ ንድፎች ባለቤት ለሆነው አካል እውቅና አንሰጥም ብንል ተገቢ ይሆናል?
የአውሮፕላንን ንድፍ ያወጣ አንድ ሰው እንደሚኖር የታወቀ ነው፤ ታዲያ ወፎች፣ ንድፍ አውጪ እንደሌላቸው ማሰብ ምክንያታዊ ነው?
ማስረጃዎቹን ለመመርመር የሚረዱህ መሣሪያዎች
ተፈጥሮን በሚገባ በመመልከት ፈጣሪ እንዳለ ያለህን እምነት ማጠናከር ትችላለህ።
እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍትን ክፈት፤ ከዚያም በፍለጋ ሣጥኑ ላይ “ንድፍ አውጪ አለው” የሚለውን ሐረግ (ትዕምርተ ጥቅሶቹን ጨምረህ) ጻፍ። በፍለጋ ውጤቱ ላይ ከሚመጡልህ “ንድፍ አውጪ አለው?” በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡ የንቁ! ርዕሶች መካከል አንተን የሚስቡህን ምረጥ። እነዚህን ርዕሶች ስታነብብ በርዕሱ ላይ የተብራራውን የተፈጥሮ ንድፍ አስደናቂ የሚያደርገው ምን እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። በርዕሶቹ ላይ የተብራሩት ሐሳቦች ንድፍ አውጪ እንዳለ ያሳመኑህ እንዴት ነው?
ይበልጥ ለማወቅ ሞክር፦ ፈጣሪ እንዳለ እርግጠኛ እንድትሆን የሚያደርጉ ማስረጃዎችን ጠለቅ ብለህ መመርመር የምትፈልግ ከሆነ የሚከተሉትን ብሮሹሮች አንብብ።
ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው?
ምድር በሕዋ ላይ የምትገኝበት ቦታ ሕይወት ያላቸው ነገሮችን ለማኖር ተስማሚ እንድትሆን አድርጓታል፤ እንዲሁም ለሕይወት የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሙሉ በሚገባ ይዛለች።—ከገጽ 4-10 ተመልከት።
በተፈጥሮ ላይ የምናያቸው ነገሮች ንድፍ አላቸው።—ከገጽ 11-17 ተመልከት።
በዘፍጥረት መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ስለ ፍጥረት የሚገልጸው ዘገባ ከሳይንስ ጋር ይስማማል።—ከገጽ 24-28 ተመልከት።
የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች
ሕይወት ያለው ነገር በአጋጣሚ ሕይወት ከሌላቸው ነገሮች ሊገኝ አይችልም።—ከገጽ 4-7 ተመልከት።
ሕይወት ያላቸው ነገሮች በጣም ውስብስብ ናቸው፤ በመሆኑም በአጋጣሚ በተከናወነ አንድ ሂደት አማካኝነት ተሻሽለው የመጡ ሊሆኑ አይችሉም።—ከገጽ 8-12 ተመልከት።
ዲ ኤን ኤ ያለው መረጃ የመያዝ ችሎታ ከየትኛውም ዘመናዊ የቴክኖሎጂ መሣሪያ ይበልጣል።—ከገጽ 13-21 ተመልከት።
ሕይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ከአንድ አካል እየተሻሻሉ አልመጡም። ከቅሪተ አካላት የተገኙ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት ዋና ዋና የእንስሳት ምድቦች የተገኙት በአንድ ጊዜ ነው፤ ቅሪተ አካላቱ እነዚህ የእንስሳት ምድቦች አንዳቸው ከሌላው እየተሻሻሉ እንደመጡ አይጠቁሙም።—ከገጽ 22-29 ተመልከት።
“አምላክ መኖሩን ያሳመነኝ ትልቁ ነገር በተፈጥሮ ላይ ያስተዋልኩት ነገር ነው፤ በምድር ላይ ያሉት እንስሳትም ሆኑ በጽንፈ ዓለም ውስጥ የሚታየው ሥርዓት ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኛ እንድሆን አድርጎኛል።”—ቶማስ
-
-
ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?—ክፍል 4፦ ፈጣሪ እንዳለ ለሰዎች ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?የወጣቶች ጥያቄ
-
-
የወጣቶች ጥያቄ
ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?—ክፍል 4፦ ፈጣሪ እንዳለ ለሰዎች ማስረዳት የምችለው እንዴት ነው?
ፈጣሪ መኖሩን ታምናለህ፤ ሆኖም በትምህርት ቤት ውስጥ በሌሎች ፊት ይህን መናገር ያስፈራህ ይሆናል። ምናልባትም የትምህርት ቤት መጽሐፎችህ የዝግመተ ለውጥ ሐሳብን የሚደግፉ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በመሆኑም አስተማሪዎችህና አብረውህ የሚማሩት ልጆች በእምነትህ የተነሳ እንዳያሾፉብህ ፈርተህ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ስለ ፈጣሪ መኖር ያለህን እምነት በድፍረት ማስረዳት የምትችለው እንዴት ነው?
ማስረዳት ትችላለህ!
እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል፦ ‘ሳይንስ ነክ ስለሆኑ ጉዳዮች ለመወያየትም ሆነ ስለ ዝግመተ ለውጥ ለመከራከር ብቃቱ ያለኝ አይመስለኝም።’ ዳንዬል የተባለች ወጣት እንዲህ ተሰምቷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ከአስተማሪዬ እና አብረውኝ ከሚማሩት ልጆች ጋር መከራከር አልፈልግም ነበር።” ዳያናም በዚህ ሐሳብ ትስማማለች፤ “ሳይንሳዊ ቃላትን እየተጠቀሙ ሲከራከሩኝ ግራ ይገባኝ ነበር” ብላለች።
ይሁን እንጂ ዓላማህ በክርክር ማሸነፍ አይደለም። በዚያ ላይ ደግሞ ሁሉንም ነገሮች የፈጠረ ፈጣሪ እንዳለ የምታምነው ለምን እንደሆነ ለማስረዳት የሳይንስ ሊቅ መሆን አያስፈልግህም።
ይህን ለማድረግ ሞክር፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዕብራውያን 3:4 ላይ የሚገኘውን አሳማኝ ነጥብ ተጠቅመህ ለማስረዳት ሞክር፤ ጥቅሱ “እያንዳንዱ ቤት የራሱ ሠሪ አለው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው” በማለት ይናገራል።
ካሮል የተባለች አንዲት ወጣት በዕብራውያን 3:4 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተጠቅማ ሰዎችን ስታስረዳ እንዲህ ትላለች፦ “ጥቅጥቅ ባለ ጫካ ውስጥ እየሄዳችሁ እንዳለ አድርጋችሁ አስቡ። በአካባቢው ሰው ድርሽ ብሎ የሚያውቅ አይመስልም። ነገር ግን ድንገት ወደ መሬት ስትመለከቱ አንድ ስቴኪኒ ወድቆ አያችሁ። በዚህ ጊዜ ምን ታስባላችሁ? አብዛኞቹ ሰዎች ‘የሆነ ሰው ወደዚህ አካባቢ መጥቶ ነበር’ ብለው ማሰባቸው አይቀርም። እንደ ስቴኪኒ ያለ ትንሽ እና ውስብስብ ያልሆነ ነገር እንኳ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንዳለ የሚጠቁም ከሆነ ጽንፈ ዓለምና በውስጡ ያሉ ነገሮች ከሁሉ የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል እንዳለ ማስረጃ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይሆንም?”
አንድ ሰው እንዲህ ቢልህስ? “ሁሉም ነገሮች የተገኙት በፍጥረት ከሆነ ታዲያ አምላክን ማን ፈጠረው?”
እንዲህ ብለህ መመለስ ትችላለህ፦ “ፈጣሪን በተመለከተ ልንረዳቸው የማንችላቸው ነገሮች መኖራቸው ብቻ ፈጣሪ የለም ብለን ለመደምደም መሠረት አይሆነንም። ለምሳሌ፣ የያዝከውን የሞባይል ስልክ የሠራው ማን እንደሆነ አታውቅ ይሆናል፤ የሆነ ሰው እንደሠራው ግን ታምናለህ አይደል? [ሐሳቡን እንዲገልጽ ዕድል ስጠው።] የሚገርምህ ነገር፣ ፈጣሪን በተመለከተ ማወቅ የምንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እንዲያውም ስለ እሱ ማወቅ የምትፈልግ ከሆነ እኔ የማውቀውን ልነግርህ እችላለሁ።”
በደንብ ተዘጋጅ
መጽሐፍ ቅዱስ ‘እናንተ ስላላችሁ ተስፋ፣ ምክንያት እንድታቀርቡ ለሚጠይቃችሁ ሰው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር ዝግጁዎች ሁኑ፤ ይህን ስታደርጉ ግን በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት ይሁን’ በማለት ይመክራል። (1 ጴጥሮስ 3:15) በመሆኑም ለሁለት ነገሮች ይኸውም ምን እና እንዴት እንደምትናገር ትኩረት ሰጥተህ ተዘጋጅ።
ምን መናገር ትችላለህ? አምላክን የምትወደው ከሆነ ስለ እሱ ለመናገር መነሳሳትህ አይቀርም። ነገር ግን አምላክን ምን ያህል እንደምትወደው ስለተናገርክ ብቻ ሰዎች ሁሉንም ነገር የፈጠረው አምላክ እንደሆነ ያምናሉ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ፈጣሪ እንዳለ ማመን ምክንያታዊ እንደሆነ ለማስረዳት የፍጥረት ሥራዎችን እንደ ምሳሌ ተጠቀም።
እንዴት መናገር አለብህ? በራስ መተማመን ይኑርህ፤ ሆኖም አነጋገርህ ሌሎችን እንደምትንቅ ወይም ራስህን እንደምታመጻድቅ የሚያሳይ ሊሆን አይገባም። ሰዎች የምታምንበትን ነገር ስትናገር ሊያዳምጡህ ፈቃደኛ የሚሆኑት እነሱ የሚያምኑበትን ነገር እንደምታከብር እንዲሁም የፈለጉትን የማመን መብት እንዳላቸው አምነህ እንደምትቀበል ሲመለከቱ ነው።
“የሌሎችን አመለካከት አለማንቋሽሽ ወይም ‘ሁሉን አውቃለሁ’ ባይ አለመሆን በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማኛል። አንድ ሰው ራሱን እንደሚያመጻድቅ በሚያሳይ መንገድ የሚናገር ከሆነ ጥሩ ውጤት አያገኝም።”—ኢሌይን
እምነትህን ማስረዳት እንድትችል የሚያግዙ መሣሪያዎች
ስለምታምንበት ነገር ለሰዎች እንዴት እንደምታስረዳ መዘጋጀት ለአየሩ ሁኔታ ተስማሚ የሆነ ትጥቅ ከማዘጋጀት ጋር ሊመሳሰል ይችላል
አሊሲያ የተባለች ወጣት “በደንብ ካልተዘጋጀን፣ ለኃፍረት እንዳንዳረግ በመፍራት ዝም ማለታችን አይቀርም” ብላለች። አሊሲያ እንደተናገረችው አንድ ሰው ስኬታማ መሆን ከፈለገ ዝግጅት ማድረጉ ወሳኝ ነው። ጄና ደግሞ እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ቀላልና በደንብ የታሰበበት ምሳሌ ማዘጋጀት፣ ከሰዎች ጋር ስለ ፈጣሪ መኖር ስነጋገር ይበልጥ ቀላል እንደሚያደርግልኝ አስተውያለሁ።”
ታዲያ እንዲህ ዓይነት ምሳሌዎችን ከየት ማግኘት ትችላለህ? ብዙ ወጣቶች የሚከተሉትን ጽሑፎች ጠቃሚ ሆነው አግኝተዋቸዋል፦
ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው?
የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች
አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር ይገልጣሉ (ቪዲዮ በእንግሊዝኛ)
“ንድፍ አውጪ አለው?” በሚል ዓምድ ሥር በንቁ! መጽሔት ላይ የሚወጡት ተከታታይ ርዕሶች። (የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ገብተህ በፍለጋ ሣጥኑ ላይ “ንድፍ አውጪ አለው” የሚለውን ሐረግ [ከነትእምርተ ጥቅሱ] በመጻፍ ርዕሶቹን ፈልግ)
የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍትን ተጠቅመህ ተጨማሪ ምርምር አድርግ።
“ፍጥረት ወይስ ዝግመተ ለውጥ?” በሚል ርዕስ ሥር ከዚህ በፊት የወጡ ርዕሶችን መመልከትህም ሊጠቅምህ ይችላል።
ይህን ለማድረግ ሞክር፦ አንተን ይበልጥ ያሳመኑህን ምሳሌዎች ምረጥ። እንዲህ ማድረግህ ምሳሌዎቹን በቀላሉ ለማስታወስና ይበልጥ አሳማኝ በሆነ መንገድ ለማስረዳት ያስችልሃል። ስለምታምንበት ነገር ሌሎችን ማስረዳት የምትችልበትን መንገድ ተለማመድ።
-