የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g04 12/8 ገጽ 15-16
  • ልጆችን ተንከባክቦ የማሳደግ አስፈላጊነት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ልጆችን ተንከባክቦ የማሳደግ አስፈላጊነት
  • ንቁ!—2004
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአንጎል ነርቮች መገናኛዎች ወይም ሲናፕስስ
  • አንድ ሕፃን የሚኖረው ችሎታ ባገኘው እንክብካቤ ላይ ይመካል?
  • የወላጅነት የሥራ ድርሻ
    ንቁ!—2004
  • ሕፃናት የሚያስፈልጋቸውና የሚፈልጉት
    ንቁ!—2004
  • ልጆችን ከሕፃንነታቸው ጀምሮ ማሠልጠን ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
    ንቁ!—2004
ንቁ!—2004
g04 12/8 ገጽ 15-16

ልጆችን ተንከባክቦ የማሳደግ አስፈላጊነት

አንድ ሰው በሕፃንነቱ የተማራቸው ወይም ሳይማር ያለፋቸው ነገሮች ወደፊት በሚኖሩት ችሎታዎች ላይ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ። ታዲያ ልጆች የተሟላ እድገት ያላቸውና የተሳካላቸው ሰዎች እንዲሆኑ ከወላጆቻቸው ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ነገር ምንድን ነው? አንዳንዶች በቅርብ አሥርተ ዓመታት የተደረጉ ምርምሮችን መሠረት በማድረግ የደረሱበትን ድምዳሜ ተመልከት።

የአንጎል ነርቮች መገናኛዎች ወይም ሲናፕስስ

የሳይንስ ሊቃውንት የአንጎልን አሠራር በምስል ለመቅረጽ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች እየተሻሻሉና እየተራቀቁ በመምጣታቸው የአንጎልን የእድገት ሂደት በይበልጥ ለማጥናት ችለዋል። እነዚህ ጥናቶች መረጃዎችን ማመዛዘን፣ ስሜቶችን ተገቢ በሆኑ መንገዶች መግለጽና አንደበተ ርቱዕ መሆን የሚያስችሉትን የአንጎል አሠራሮች ለማዳበር የአንድ ሕፃን የጨቅላነት ዕድሜ ወሳኝነት እንዳለው አረጋግጠዋል። ኔሽን መጽሔት “የአንጎል መዋቅር፣ በዘር ውርስ በሚገኙ መረጃዎችና በአካባቢያዊ ተጽዕኖዎች መካከል በየጊዜው በሚኖረው መስተጋብር በሚቀረጽበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት የአንጎል ነርቭ አውታሮች በጣም ከፍተኛ በሆነ ፍጥነት ይዘረጋሉ” ይላል።

ከእነዚህ ሲናፕስስ ተብለው ከሚጠሩት የነርቭ መገናኛዎች አብዛኞቹ የሚፈጠሩት አንድ ሕፃን በተወለደ ጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደሆነ ሳይንቲስቶች ያምናሉ። የሕፃናት አስተዳደግ ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ቤሪ ብሬዘልተን እንደሚሉት “ከማስተዋል፣ ራስን ከማወቅና ሌሎችን ከማመን ችሎታ እንዲሁም ከመማር ፍላጎት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው የሕፃን ልጅ የነርቭ አውታር የሚቀረጸው” በዚህ ጊዜ ነው።

የአንድ ሕፃን አንጎል በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ዓመታት ውስጥ በመጠን፣ በነርቭ አውታሮች መዋቅርና በሚያከናውነው ተግባር በሚያስደንቅ ፍጥነት ያድጋል። ሕፃኑ ለአእምሮ እድገት በሚያመችና ብዙ ትምህርት በሚያገኝበት አካባቢ ከኖረ የሲናፕስስ ግንኙነቶች በጣም ይበራከቱና በአንጎል ውስጥ እጅግ ብዙ የነርቭ አውታር መሥመሮች ይፈጠራሉ። ማሰብ፣ መማርና ማገናዘብ የሚያስችሉት እነዚህ የነርቭ አውታሮች ናቸው።

የአንድ ሕፃን አንጎል የሚያገኘው ማነቃቂያ በበዛ መጠን መሥራት የሚጀምሩት የነርቭ ሴሎች ብዛትና በሴሎቹ መካከል የሚፈጠረው መተሳሰር የዚያኑ ያህል ይጨምራል። ይህ ማነቃቂያ እንደ ቁጥርና ቋንቋ በመሰሉት ትምህርቶች ብቻ የሚመጣ አለመሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። ሳይንቲስቶች ስሜታዊ ማነቃቂያም እንደሚያስፈልግ ተገንዝበዋል። ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ያልታቀፉ፣ ያልተሻሹና ሰዎች ያላጫወቷቸው ልጆች የሚኖሯቸው የሲናፕስስ ግንኙነቶች አነስተኛ ናቸው።

አንድ ሕፃን የሚኖረው ችሎታ ባገኘው እንክብካቤ ላይ ይመካል?

ሕፃናት እያደጉ ሲሄዱ በአንጎል ውስጥ አረም የማረም ዓይነት ሂደት ይካሄዳል። ሰውነት አስፈላጊ ያልሆኑ የሲናፕስስ መሥመሮችን ያስወግዳል። ይህ ደግሞ አንድ ልጅ በሚኖረው ሊዳብር የሚችል ችሎታ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። የአንጎል ተመራማሪ የሆኑት ማክስ ሲናደር እንደሚሉት “አንድ ሕፃን ትክክለኛውን ዓይነት ማነቃቂያ በትክክለኛው ዕድሜ ላይ ካላገኘ የነርቭ አውታሮቹ በትክክል ሊያድጉ አይችሉም።” በዚህም ምክንያት ዶክተር ፍሬዘር መስተርድ እንደሚሉት የልጁ የመማር፣ የመናገርና ቁጥሮችን የማስላት ችሎታ ዝቅተኛ ሊሆን እንዲሁም ትልቅ ሰው በሚሆንበት ጊዜ ከጤናና ከባሕርይ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊያጋጥሙት ይችላሉ።

ስለዚህ አንድ ሰው ሕፃን በነበረበት ጊዜ ያጋጠሙት ሁኔታዎች ትልቅ ሰው ሲሆን በሚኖረው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። ሰውየው መንፈሰ ጠንካራ ወይም ደካማ፣ ለሰው አዛኝ ወይም ጨካኝ፣ አርቆ አሳቢ ወይም ጠባብ አእምሮ ያለው መሆኑ ሕፃን ሳለ ባጋጠሙት ነገሮች ላይ ሊመካ ይችላል። ስለዚህ ወላጆች የሚኖራቸው ሚና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። አንድ የሕፃናት ሐኪም “ከእነዚህ የልጅነት ገጠመኞች መካከል በጣም ወሳኝ የሆነው አሳቢና አስተዋይ የሆነ አሳዳጊ ወላጅ ማግኘት ነው” ብለዋል።

ይህ በጣም ቀላል ሊመስል ይችላል። ልጆቻችሁን በእንክብካቤ ብታሳድጓቸው ወደፊት የተሳካ ሕይወት ይኖራቸዋል። ይሁን እንጂ ለልጆች ተገቢውን እንክብካቤ መስጠት ቀላል ነገር እንዳልሆነ ወላጆች ያውቃሉ። በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ በደመ ነፍስ የሚለመድ ነገር እንዳልሆነ ግልጽ ነው።

አንድ ጥናት እንዳመለከተው ጥያቄ ከቀረበላቸው ወላጆች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት ልጃቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ የመማር ችሎታውን፣ በራስ የመተማመን መንፈሱንና የመማር ፍላጎቱን ሊያዳብርለት ወይም ሊያዳክምበት እንደሚችል አያውቁም። ይህ ደግሞ የልጃችሁን የተፈጥሮ ችሎታ ማዳበር የሚቻልበት ጥሩ መንገድ ምንድን ነው? አመቺ የሆነ ሁኔታ ሊፈጠርለት የሚችለው እንዴት ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ያስነሳል። እነዚህን ጉዳዮች ቀጥሎ እንመለከታለን።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አእምሯቸውን የሚያነቃቁላቸው ነገሮች ሳያገኙ ብቻቸውን ያደጉ ሕፃናት ጥሩ እድገት ሊኖራቸው አይችልም

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ