በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይገኛሉ—አንተስ?
◼ “የት?” ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። “መዳናችን ቀርቧል!” በተባለው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ! በመቶዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች የሚካሄዱት እነዚህ የሦስት ቀን የአውራጃ ስብሰባዎች በግንቦት ወር ማገባደጃ ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ይጀመራሉ። ከዚያም በመጪዎቹ ወራት በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ከተሞች ውስጥ መካሄዳቸውን ይቀጥላሉ። በቅርቡ በተደረጉ 2,981 የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ ወደ 11 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተገኝተው ነበር!
በአብዛኞቹ ቦታዎች የሦስቱም ቀናት ስብሰባ የሚጀመረው ከጠዋቱ 3:30 ላይ በሚሰማ ሙዚቃ ይሆናል። በዓርቡ ዕለት ስብሰባ ላይ “ይሖዋ የሰጠውን የመዳን ተስፋ በትኩረት ተከታተሉ” እንዲሁም “ችግረኛውና ምስኪኑ ወደ እርሱ በጮኸ ጊዜ ይሖዋ የሚረዳው እንዴት ነው?” እንደሚሉት ያሉ ንግግሮች ይቀርባሉ። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ “ይሖዋ ‘ዘላለማዊ ድነት’ እንድናገኝ ያደረገልን ዝግጅቶች” የሚል ርዕስ ባለው የስብሰባውን ጭብጥ የሚያብራራ ንግግር ይደመደማል።
ዓርብ ከሰዓት በኋላ ከሚቀርቡት ንግግሮች መካከል “ይሖዋ አረጋውያንን ይንከባከባል፣” “ይሖዋ ከከባድ ውጥረት ያድነናል” እንዲሁም “መላእክት ‘አገልግሎት’ በመስጠት ረገድ የሚያበረክቱት ድርሻ” የሚሉት ይገኙበታል። በተጨማሪም “ይሖዋ—ሕዝቦቹን ‘የሚታደግ’ አምላክ” በሚል ጭብጥ አራት ተከታታይ ንግግሮች ከቀረቡ በኋላ የዕለቱ ስብሰባ “በአንቺ ላይ የተደገነ መሣሪያም ይሁን የሚከስሽ አንደበት አይሳካለትም” በሚል ንግግር ይደመደማል።
ቅዳሜ ጠዋት “ያለማሰለስ መስበካችሁን ቀጥሉ” በሚል ጭብጥ ሦስት ተከታታይ ንግግሮች ይቀርባሉ። በተጨማሪም “ከወፍ አዳኙ ወጥመድ መዳን” እና “‘የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር’ መመርመር” የሚሉ ንግግሮች ይቀርባሉ። የጠዋቱ ክፍለ ጊዜ በጥምቀት ንግግሩ ይደመደማል፤ ከዚያም ለጥምቀት ብቃቱን ያሟሉ ዕጩዎች ይጠመቃሉ።
ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ ከሚቀርቡት ንግግሮች መካከል “የጤና አጠባበቅን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ያለው ዓይነት አመለካከት ይኑራችሁ፣” “ሕይወታችሁን የሚቆጣጠረው የትኛው መንፈስ ነው?” እንዲሁም “ትዳራችሁ ‘በሦስት የተገመደ ገመድ’ እንዲሆን ጥረት አድርጉ” እና “እናንት ወጣቶች፣ ታላቁን ‘ፈጣሪያችሁን አስቡ’” የሚሉት ይገኙበታል። “አኗኗራችሁ የይሖዋን ቀን እንዳልዘነጋችሁ የሚያሳይ ነው?” የሚለው የመደምደሚያ ንግግር ለዘመናችን የሚሆን ጠቃሚ ምክር ይዟል።
በእሁዱ ጠዋት ክፍለ ጊዜ ላይ “መንግሥተ ሰማይ . . .” በሚል ጭብጥ አራት ተከታታይ ንግግሮች ይቀርባሉ። እነዚህ ንግግሮች ኢየሱስ ስለተናገራቸው አንዳንድ ምሳሌዎች አጠር ያለ ማብራሪያ ይሰጣሉ።
ከዚያም በአውራጃ ስብሰባው ላይ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠውን ድራማ የሚያስተዋውቅ ንግግር ይቀርባል። ድራማው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በአንደኛ ነገሥት ምዕራፍ 13 ላይ የተመሠረተና ጥንታዊ አለባበስ የሚንጸባረቅበት ነው። በአውራጃ ስብሰባው የመጨረሻ ዕለት ማለትም እሁድ ከሰዓት በኋላ “በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የምናገኘው መዳን ቀርቧል!” የሚል የሕዝብ ንግግር ይቀርባል።
እርስዎም በስብሰባው ላይ ለመገኘት አሁኑኑ እቅድ ያውጡ። በሚኖሩበት አካባቢ ስብሰባው የሚካሄድበትን ቦታ ለማወቅ ከፈለጉ በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሽ በመሄድ አሊያም ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች በመጻፍ መጠየቅ ይችላሉ። የመጋቢት 1, 2006 መጠበቂያ ግንብ ይህ የአውራጃ ስብሰባ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግባቸውን ቦታዎች ይዞ ወጥቷል።