የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • 1ኛው ቁልፍ፦ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ማስቀደም
    ንቁ!—2009 | ጥቅምት
    • 1ኛው ቁልፍ፦ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን ነገር ማስቀደም

      ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ እወቁ።’—ፊልጵስዩስ 1:10

      ምን ማለት ነው? የተሳካ የቤተሰብ ሕይወት ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ እያንዳንዱ የትዳር ጓደኛ ከራሱ፣ ከንብረቱ፣ ከሥራው፣ ከጓደኞቹና ሌላው ቀርቶ ከዘመዶቹም እንኳ በፊት የትዳር ጓደኛውን ፍላጎት ያስቀድማል። የተሳካ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት፣ አንዳቸው ከሌላው ጋር እንዲሁም ከልጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ያሳልፋሉ። ሁለቱም ለቤተሰቡ ጥቅም ሲሉ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ናቸው።—ፊልጵስዩስ 2:4

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለቤተሰብ ትልቅ ቦታ ይሰጣል። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን የማያቀርብ ሰው “እምነት የለሽ ከሆነ ሰው የከፋ ነው” ሲል ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8) ሆኖም አንድ ሰው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ነገሮች በጊዜ ሂደት ሊለወጡ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በቤተሰብ ሕይወት ዙሪያ ምክር የሚሰጡ አንድ ሰው፣ እሳቸው ባዘጋጁት አንድ ስብሰባ ላይ የተገኙ ብዙ ሰዎች ከቤተሰባቸው ይልቅ ለሥራቸው የበለጠ ትኩረት እንደሚሰጡ ተገንዝበዋል። እኚህ ሰው እንደተናገሩት ሰዎቹ ወደዚህ ስብሰባ የመጡት በቤተሰብ ውስጥ የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት የሚያስችላቸውን “አቋራጭ መንገድ” ለመማር አስበው ይመስላል። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? አንድ ሰው ለቤተሰቡ ቅድሚያ እንደሚሰጥ በተግባር ማሳየት የመናገሩን ያህል ቀላል አይሆንለትም።

      ይህን ለማድረግ ሞክር፦ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ቅድሚያ የምትሰጣቸው ነገሮች ምን እንደሆኑ ገምግም።

      ◼ የትዳር ጓደኛዬ ወይም ልጄ ከእኔ ጋር ማውራት ሲፈልጉ በተቻለ መጠን ባፋጣኝ ትኩረት እሰጣቸዋለሁ?

      ◼ ስለምሠራቸው ነገሮች ለሌሎች ሳወራ ብዙውን ጊዜ የምናገረው ከቤተሰቤ ጋር ስለማደርጋቸው ነገሮች ነው?

      ◼ በሥራ ቦታም ሆነ በሌላ ሥፍራ ተጨማሪ ኃላፊነት ሲሰጠኝ ከቤተሰቤ ጋር የማሳልፈውን ጊዜ የሚሻማብኝ ከሆነ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኔን እገልጻለሁ?

      ከላይ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች ‘አዎ’ ብለህ ከመለስክ ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባህን ነገር እንዳስቀደምክ ሊሰማህ ይችላል። ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛህና ልጆችህ በዚህ ረገድ ምን ይሰማቸዋል? እኛ ስለተሰማን ብቻ ቅድሚያ ልንሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን አስቀድመናል ማለት አይቻልም። ይኸው መሠረታዊ ሥርዓት በሚቀጥሉት ገጾች ላይ በምናነሳቸው ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ነጥቦች ረገድም ይሠራል።

      ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ለቤተሰብህ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ማሳየት የምትችልባቸውን አንድ ወይም ሁለት መንገዶች አስብ። (ለምሳሌ ያህል፦ ከትዳር ጓደኛህና ከልጆችህ ጋር ብዙ ጊዜ እንዳታሳልፍ እንቅፋት የሚሆኑብህን ነገሮች እንዴት መቀነስ እንደምትችል አስብ።)

      ይህን ቁርጥ ውሳኔህን ለቤተሰብህ አባላት ለምን አትነግራቸውም? አንዱ የቤተሰብ አባል ለመለወጥ ፈቃደኛ ከሆነ ሌሎቹም እንደዚያው ለማድረግ መነሳሳታቸው አይቀርም።

      [በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ከምንም በላይ ለትዳር ጓደኛውና ለልጆቹ ቅድሚያ የሚሰጥ ወላጅ የቤተሰብ ሕይወቱ የተሳካ ይሆንለታል

  • 2ኛው ቁልፍ፦ ቃል ኪዳንን ማክበር
    ንቁ!—2009 | ጥቅምት
    • 2ኛው ቁልፍ፦ ቃል ኪዳንን ማክበር

      “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው።”—ማቴዎስ 19:6

      ምን ማለት ነው? የተሳካ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት ትዳራቸውን የሚመለከቱት ዘላቂ ጥምረት እንደሆነ አድርገው ነው። አንድ ችግር ሲነሳ ችግሩን ለመፍታት ጥረት ያደርጋሉ እንጂ ይህን ሰበብ አድርገው ቤተሰባቸውን ጥለው አይሄዱም። የትዳር ጓደኛሞች የገቡትን ቃል ኪዳን የሚያከብሩ ከሆነ የመረጋጋት ስሜት ይኖራቸዋል። የትዳር አጋራቸው የጋብቻ ጥምረቱን አክብሮ መኖሩን እንደሚቀጥል ይተማመናሉ።

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ቃል ኪዳንን ማክበር በብዙ መንገዶች ሲታይ ለትዳር እንደ ጀርባ አጥንት ነው። ሆኖም ባልና ሚስት በተደጋጋሚ የሚጋጩ ከሆነ ቃል ኪዳናቸውን ማክበራቸው በአብዛኛው ማነቆ እንደሆነባቸው ሊሰማቸው ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ በተጋቡበት ጊዜ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ አብረው ለመኖር የገቡት ቃል ተራ ስምምነት እንደሆነ በማሰብ መውጫ ቀዳዳ ይፈልጉ ይሆናል። እነዚህ ሰዎች ትዳራቸውን ቃል በቃል ትተው አይሄዱ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ መወያየት የሚጠይቁ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በማኩረፍ ወይም በሌላ መንገድ ትዳሩን “ትተው ሊሄዱ” ይችላሉ።

      ይህን ለማድረግ ሞክር፦ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ምን ያህል ቃል ኪዳንህን እንደምታከብር ገምግም።

      ◼ በምንጋጭበት ጊዜ እሱን/እሷን ማግባቴ ይቆጨኛል?

      ◼ ብዙ ጊዜ የትዳር ጓደኛዬ ካልሆነ ሰው ጋር ጥሩ ጊዜ ስለማሳለፍ አውጠነጥናለሁ?

      ◼ አንዳንድ ጊዜ ለትዳር ጓደኛዬ “ትቼሽ/ትቼህ እሄዳለሁ” ወይም “የሚወደኝ ሌላ ሰው እፈልጋለሁ” እያልኩ እናገራለሁ?

      ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ቃል ኪዳንህን ከፍ አድርገህ መመልከትህን እንድትቀጥል ልታደርጋቸው ስለምትችላቸው አንድ ወይም ሁለት ነገሮች አስብ። (ለምሳሌ ያህል፣ ለትዳር ጓደኛህ አልፎ አልፎ ማስታወሻ መጻፍ፣ የትዳር ጓደኛህን ፎቶዎች በቢሮህ ውስጥ ፊት ለፊት ማስቀመጥ፣ ወይም በየቀኑ ለትዳር ጓደኛህ ሰላም ለማለት ያህል ስልክ መደወል ትችላለህ።)

      ልታደርጋቸው የምትችላቸው በርከት ያሉ አማራጮችን ካዘጋጀህ በኋላ የትዳር ጓደኛህን ይበልጥ የሚያስደስታት የትኛውን ብታደርግ እንደሆነ ለምን አትጠይቃትም?

      [በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      መንገድ ዳር የተሠራ መከታ ተሽከርካሪ ከመንገድ እንዳይወጣ እንደሚከላከል ሁሉ ቃል ኪዳናችሁን ማክበራችሁም ትዳራችሁን ይጠብቅላችኋል

      [ምንጭ]

      © Corbis/age fotostock

  • 3ኛው ቁልፍ፦ ተባብሮ መሥራት
    ንቁ!—2009 | ጥቅምት
    • 3ኛው ቁልፍ፦ ተባብሮ መሥራት

      “ከአንድ፣ ሁለት መሆን ይሻላል፤ አንዱ ቢወድቅ፣ ባልንጀራው ደግፎ ያነሣዋል።”—መክብብ 4:9, 10

      ምን ማለት ነው? የተሳካ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን አምላክ የሰጠውን የራስነት ሥርዓት ያከብራሉ። (ኤፌሶን 5:22-24) ያም ሆኖ ባልም ሆነ ሚስት ትዳራቸው የተሳካ የሚሆነው በግላቸው በሚያደርጉት ጥረት ሳይሆን ተባብረው በመሥራታቸው መሆኑን ያውቃሉ። ባልና ሚስት ተባብረው የሚሠሩ ከሆነ እንዳላገባ ሰው አያስቡም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “አንድ ሥጋ” ናቸው፤ ይህ መግለጫ የጋብቻው ጥምረት ዘላቂ መሆኑን ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው የጠበቀ ቅርርብ እንዳለም ያመለክታል።—ዘፍጥረት 2:24

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንተና የትዳር ጓደኛህ ተባብራችሁ የማትሠሩ ከሆነ ጥቃቅን የሆኑ ነገሮችም እንኳ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ችግር ይሆኑና ችግሩን መፍታት ትታችሁ አንዳችሁ በሌላው ጉድለት ላይ እንድታነጣጥሩ ያደርጓችኋል። በአንጻሩ ደግሞ ተባብራችሁ የምትሠሩ ከሆነ፣ ከተቃራኒ አቅጣጫ እንደሚመጡ ሁለት የአውሮፕላን አብራሪዎች ሳይሆን የጋራ የበረራ እቅድ እንዳላቸው የአውሮፕላን አብራሪና ረዳቱ ትሆናላችሁ። በማትስማሙበት ጊዜም አንዳችሁ ሌላውን ጥፋተኛ በማድረግና በመወቃቀስ ጊዜና ጉልበት ከማባከን ይልቅ ተግባራዊ የሆኑ መፍትሔዎችን ትፈልጋላችሁ።

      ይህን ለማድረግ ሞክር፦ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ተባብሮ ስለመሥራት ያለህን ስሜት ገምግም።

      ◼ የማገኘውን ገንዘብ ሠርቼ ያመጣሁት እኔ ስለሆንኩ ብቻ “የእኔ ብቻ” እንደሆነ አድርጌ እመለከተዋለሁ?

      ◼ የትዳር ጓደኛዬ ከዘመዶቿ ጋር የምትቀራረብ ቢሆንም እኔ ከእነሱ ለመራቅ እሞክራለሁ?

      ◼ በደንብ ዘና ለማለት ስፈልግ ከትዳር ጓደኛዬ መራቅ እንዳለብኝ ይሰማኛል?

      ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ከትዳር ጓደኛህ ጋር ተባብረህ እንደምትሠራ ይበልጥ ማሳየት የምትችልባቸውን አንድ ወይም ሁለት መንገዶች አስብ።

      አንድን ጉዳይ በሚመለከት የትዳር ጓደኛህ ምን ሐሳብ እንዳላት ለምን አትጠይቃትም?

      [በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ተባብሮ መሥራት ሲባል የጋራ የበረራ እቅድ እንዳላቸው የአውሮፕላን አብራሪና ረዳቱ መሆን ማለት ነው

  • 4ኛው ቁልፍ፦ መከባበር
    ንቁ!—2009 | ጥቅምት
    • 4ኛው ቁልፍ፦ መከባበር

      “ጩኸትና ስድብ ሁሉ . . . ከእናንተ መካከል ይወገድ።”—ኤፌሶን 4:31

      ምን ማለት ነው? ችግር ያለባቸውም ሆኑ የተሳካላቸው ቤተሰቦች አለመግባባት ያጋጥማቸዋል። ይሁን እንጂ የተሳካ የቤተሰብ ሕይወት ያላቸው ቤተሰቦች ስለተነሳው አለመግባባት ሲወያዩ የሽሙጥ ንግግር፣ ስድብና ሌላ ዓይነት የዘለፋ አነጋገሮችን አይጠቀሙም። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለራሱ እንዲደረግለት የሚፈልገውን ነገር ለሌላው ያደርጋል።—ማቴዎስ 7:12

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ቃላት አውዳሚ ውጤት የሚያስከትሉ የጦር መሣሪያዎች ሊሆኑ ይችላሉ። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ከጠበኛና ከቁጡ ሴት ጋር ከመቀመጥ በምድረ በዳ መቀመጥ ይሻላል” ይላል። (ምሳሌ 21:19 የ1954 ትርጉም) እርግጥ ነው፣ ይህ ምሳሌ ጠበኛ ለሆነ ባልም ይሠራል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን ማሳደግን በሚመለከት “ቅስማቸው እንዳይሰበር ልጆቻችሁን አታበሳጯቸው” ይላል። (ቆላስይስ 3:21) ሁልጊዜ ነቀፋ የሚሰነዘርባቸው ልጆች ወላጆቻቸውን በጭራሽ ማስደሰት እንደማይችሉ ሊሰማቸው ይችላል። እንዲያውም ወላጆቻቸውን ለማስደሰት ጥረት ማድረጋቸውን ከናካቴው ሊያቆሙ ይችላሉ።

      ይህን ለማድረግ ሞክር፦ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት በቤተሰብህ ውስጥ መከባበር ይታይ እንደሆነ ገምግም።

      ◼ በቤተሰቤ ውስጥ አለመግባባት ሲነሳ አብዛኛውን ጊዜ አንደኛው የቤተሰብ አባል ተናዶ ቤቱን ጥሎ ይወጣል?

      ◼ የትዳር ጓደኛዬን ወይም ልጆቼን ሳነጋግር “ደደብ” ወይም “የማትረባ” እንደሚሉት ያሉ የስድብ ቃላትን መጠቀም ይቀናኛል?

      ◼ ያደግኩት በሚሰዳደቡ ሰዎች መካከል ነው?

      ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። በአነጋገርህ አክብሮት ማሳየት የምትችልባቸውን አንድ ወይም ሁለት መንገዶች አስብና እንድትሠራባቸው ግብ አውጣ። (በንግግርህ ውስጥ “አንተ” ወይም “አንቺ” በማለት ፈንታ “እኔ” እያልክ ለመናገር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ለምሳሌ ያህል፣ “አንቺ ሁልጊዜ . . .” ከማለት ይልቅ “እንዲህ ስትዪኝ ይከፋኛል” በል።)

      ስላወጣኸው ግብ ለትዳር ጓደኛህ ለምን አትነግራትም? ከዚያም ከሦስት ወራት በኋላ ምን ያህል ለውጥ እንዳደረግህ ለማወቅ ጠይቃት።

      ከልጆችህ ጋር ስትነጋገር የስድብ ቃላትን እንዳትጠቀም የሚረዱህን አንዳንድ መንገዶች አስብ።

      ልጆችህን አመናጭቀሃቸው ወይም በሽሙጥ ተናግረሃቸው ከነበረ ለምን ይቅርታ አትጠይቃቸውም?

      [በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      የውቅያኖስ ሞገድ ዐለትን እንደሚሸረሽር ሁሉ ጎጂ ቃላት የመሰንዘር ልማድም የቤተሰብን ትስስር ሊያዳክም ይችላል

  • 5ኛው ቁልፍ፦ ምክንያታዊነት
    ንቁ!—2009 | ጥቅምት
    • 5ኛው ቁልፍ፦ ምክንያታዊነት

      “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።” —ፊልጵስዩስ 4:5

      ምን ማለት ነው? የተሳካ ትዳር ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ ባልና ሚስት ስህተት ሲሠሩ አንዳቸው ለሌላው ይቅርታ ያደርጋሉ። (ሮም 3:23) በተጨማሪም በልጆቻቸው ላይ ከልክ በላይ ጥብቅ አይሆኑም፤ ወይም መረን አይለቋቸውም። እንዲሁም በቤት ውስጥ መጠነኛ ሕጎች ያወጣሉ። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም “በመጠኑ” እርማት ይሰጣሉ።—ኤርምያስ 30:11

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ከላይ የሆነው ጥበብ . . . ምክንያታዊ [ነው]” ይላል። (ያዕቆብ 3:17) አምላክም ቢሆን ፍጹም ካልሆኑ ሰዎች ፍጽምና አይጠብቅም። ታዲያ ባልና ሚስት አንዳቸው ከሌላው ፍጽምና መጠበቃቸው ምክንያታዊ ነው? በእርግጥም ጥቃቅን ስህተቶችን መለቃቀም ቅሬታን ከመፍጠር በቀር የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ‘ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንደምንሰናከል’ አምነን መቀበላችን የተሻለ ነው።—ያዕቆብ 3:2

      የተሳካ ትዳር ያላቸው ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያታዊነት ያንጸባርቃሉ። የሚሰጡት ተግሣጽም ከልክ ያለፈ አይደለም፤ ወይም ደግሞ ‘በቀላሉ የማይደሰቱ’ ዓይነት ሰዎች አይደሉም። (1 ጴጥሮስ 2:18) ኃላፊነት እንደሚሰማቸው ላስመሠከሩ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ልጆቻቸው ነፃነት ይሰጣሉ እንጂ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን ለመቆጣጠር አይሞክሩም። ወላጆች በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጃቸውን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር መሞከራቸው ከድካም በቀር የሚፈይድላቸው ነገር እንደማይኖር አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ገልጿል።

      ይህን ለማድረግ ሞክር፦ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ በመስጠት ምን ያህል ምክንያታዊ እንደሆንክ ገምግም።

      ◼ የትዳር ጓደኛህን ለመጨረሻ ጊዜ ያመሰገንካት መቼ ነው?

      ◼ የትዳር ጓደኛህን ለመጨረሻ ጊዜ የተቸሃትስ መቼ ነበር?

      ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ለመጀመሪያው ጥያቄ መልስ መስጠት ካዳገተህና ለሁለተኛው ጥያቄ ግን ያላንዳች ችግር መልስ ከሰጠህ ከትዳር ጓደኛህ በምትጠብቀው ነገር ይበልጥ ምክንያታዊ ለመሆን ግብ አውጣ።

      ሁለታችሁም በዚህ ረገድ ምን ማድረግ እንደምትችሉ ከትዳር ጓደኛህ ጋር ለምን አትወያይም?

      በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆቻችሁ ኃላፊነት የሚሰማቸው ወጣቶች መሆናቸውን ካሳዩ በምን ረገድ ነፃነት ልትሰጧቸው እንደምትችሉ አስቡ።

      ቤት እንዲገቡ የሚጠበቅባቸውን ሰዓት በተመለከተ ወይም በሌሎች ጉዳዮች ላይ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ልጆቻችሁ ጋር ግልጽ ውይይት ለምን አታደርጉም?

      [በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ጠንቃቃ የሆነ አሽከርካሪ እንደሚያደርገው ምክንያታዊ የሆነ የቤተሰብ አባልም ለሌሎች ፍላጎት ቅድሚያ ይሰጣል

  • 6ኛው ቁልፍ፦ ይቅር ባይነት
    ንቁ!—2009 | ጥቅምት
    • 6ኛው ቁልፍ፦ ይቅር ባይነት

      “እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።”—ቆላስይስ 3:13

      ምን ማለት ነው? የተሳካ ትዳር ያላቸው ባልና ሚስት ካለፈው ስህተታቸው የሚማሩ ቢሆንም ያለፈውን ሁሉ እያስታወሱ “ማርፈድ እንደሆነ ልማድሽ ነው” ወይም “መቼም ቢሆን አትሰማም” እንደሚሉት ያሉ የተጋነኑ አነጋገሮችን አይጠቀሙም። ባልም ሆነ ሚስት ‘በደልን ንቆ መተው መከበሪያ ነው’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ያስታውሳሉ።—ምሳሌ 19:11

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አምላክ ‘ይቅር ለማለት ዝግጁ’ ነው፤ ሰዎች ግን አብዛኛውን ጊዜ እንደ አምላክ ይቅር ባዮች አይደሉም። (መዝሙር 86:5 NW) እልባት ሳይበጅላቸው የቀሩ ተደራራቢ በደሎች ተጠራቅመው ይቅር ማለት አስቸጋሪ የሚመስልበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ። ይህም ሁለቱም ስሜታቸውን አውጥተው መናገር እንዲከብዳቸውና አንዳቸው ለሌላው ስሜት ደንታ ቢስ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። እንዲሁም ሁለቱም ፍቅር በሌለበት ትዳር ውስጥ የግዳቸውን እየኖሩ እንዳሉ እንዲሰማቸው ያደርጋል።

      ይህን ለማድረግ ሞክር፦ የሠርጋችሁ ሰሞን ወይም ለጋብቻ በምትጠናኑበት ወቅት የተነሳችኋቸውን ፎቶግራፎች ተመልከት። ችግሮች ተነስተው አመለካከትህ ከመለወጡ በፊት የነበረህን ፍቅር ለማደስ ጥረት አድርግ። ከትዳር ጓደኛህ ጋር ስትተዋወቁ በዚያን ጊዜ የማረከህ ባሕርይ ምን እንደነበር አስብ።

      ◼ አሁንስ ከትዳር ጓደኛህ በጣም የምታደንቀው ባሕርይ ምንድን ነው?

      ◼ ይበልጥ ይቅር ባይ መሆንህ በልጆቻችሁ ላይ ስለሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ አስብ።

      ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ከትዳር ጓደኛህ ጋር አለመግባባት ሲፈጠር ቀደም ሲል የተሰማህን ቅሬታ አሁን ላለማንሳት ማድረግ ስለምትችላቸው አንድ ወይም ሁለት ነገሮች አስብ።

      ለትዳር ጓደኛህ የትኛውን ባሕርይዋን እንደምታደንቅላት ጠቅሰህ ለምን አታመሰግናትም?—ምሳሌ 31:28, 29

      ከልጆቻችሁ ጋር ባለህ ግንኙነት ይቅር ባይ መሆንህን የምታሳይባቸውን አንዳንድ መንገዶች አስብ።

      ይቅር ባይ መሆን እያንዳንዱን የቤተሰብ አባል እንዴት እንደሚጠቅመው ከልጆቻችሁ ጋር ለምን አትወያዩበትም?

      [በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ይቅር ስትሉ ዕዳውን ሰረዛችሁ ማለት ነው፤ የሰረዛችሁትን ዕዳ እንደገና መጠየቅ አትችሉም

  • 7ኛው ቁልፍ፦ ጽኑ መሠረት
    ንቁ!—2009 | ጥቅምት
    • 7ኛው ቁልፍ፦ ጽኑ መሠረት

      ምን ማለት ነው? አንድ ቤት ለብዙ አሥርተ ዓመታት ጸንቶ የሚቆመው እንዲሁ እንዳልሆነ ሁሉ ጠንካራ ቤተሰቦችም ጸንተው የሚቀጥሉት እንዲያው በአጋጣሚ አይደለም። አንድ ጠንካራ ሕንፃ ጽኑ መሠረት እንደሚያስፈልገው ሁሉ ጠንካራ ቤተሰብም ጽኑ መሠረት ያስፈልገዋል። የተሳካ የቤተሰብ ሕይወት፣ ጠቀሜታው በተረጋገጠ መመሪያ ላይ የተመሠረተ ነው።

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ስለ ቤተሰብ ሕይወት ምክር የሚሰጡ መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በብዛት ይገኛሉ። አንዳንድ የትዳር አማካሪዎች ችግር የገጠማቸውን ባልና ሚስት አብረው እንዲኖሩ ሲያበረታቱ ሌሎች ደግሞ እንዲፋቱ ይመክሯቸዋል። ባለሙያዎቹ ራሳቸውም እንኳ ይህን በተመለከተ ያላቸውን አስተሳሰብ ከጊዜ በኋላ ይለውጣሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችል ልዩ ሥልጠና ያገኘች አንዲት ዝነኛ አማካሪ ሥራዋን በጀመረችበት ወቅት ምን አመለካከት እንደነበራት በ1994 እንዲህ ስትል ጽፋለች፦ “ልጆች ደስታ በሌለበት ትዳር ውስጥ ከሚያድጉ ይልቅ ደስተኛ ከሆኑ ነጠላ ወላጆች ጋር ቢያድጉ ይሻላቸዋል። ከመጥፎ ትዳር ጋር ከመታገል መፋታት ይሻላል ብዬ አስብ ነበር።” ከሃያ ዓመት የሥራ ልምድ በኋላ ግን አመለካከቷ ተለወጠ። “ፍቺ የብዙ ልጆችን ሕይወት ያበላሻል” ብላለች።

      የሰዎች አመለካከት በየጊዜው ይለዋወጣል፤ ይሁንና በጣም ጥሩ የሚባለው ምክር ሁልጊዜ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት መሠረታዊ መመሪያዎች ጋር በሆነ መልኩ ይመሳሰላል። እነዚህን ተከታታይ ርዕሶች ስታነብ ከገጽ 3 እስከ 8 አናት ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እንደሰፈረ አስተውለህ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቶቹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ብዙዎች የተሳካ የቤተሰብ ሕይወት እንዲኖራቸው ረድተዋቸዋል። የተሳካላቸው ቤተሰቦችም ቢሆኑ እንደ ሌሎች ቤተሰቦች ችግር ያጋጥማቸዋል። ልዩነቱ ለትዳርና ለቤተሰብ ሕይወት ጽኑ መሠረት የሚሆኑ መመሪያዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘታቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለውን መመሪያ የሚሰጥ መሆኑ የሚጠበቅ ነገር ነው፤ ምክንያቱም የቤተሰብ መሥራች የመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17

      ይህን ለማድረግ ሞክር፦ ከገጽ 3 እስከ 8 አናት ላይ ደመቅ ብለው የተጻፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በወረቀት ላይ ጻፍ። አንተን የረዳህ ሌላ ጥቅስ ካስታወስክ እሱንም በዝርዝሩ ውስጥ ጨምረው። ከዚያም ወረቀቱን በቅርብ ልታገኘው በምትችልበት ቦታ አስቀምጠውና ዘወትር ተመልከተው።

      ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። በራስህ ቤተሰብ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክሮች ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።

      [በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

      ጽኑ መሠረት ያለው ቤት አደገኛ የአየር ጠባይ መቋቋም እንደሚችል ሁሉ ቤተሰብህም በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጽኑ ሆኖ ከተገነባ ከባድ ችግሮችን መቋቋም ይችላል

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ