የአምላክ ስም እንዲታወቅ እየተደረገ ነው!
● በካናዳ አገር በኩቤክ ሲቲ አጠገብ በሚገኘው በኦርሊየንዝ ደሴት ተዘዋውረህ የሚያምረውን አካባቢ ብትቃኝ የዚህች ደሴት የጥንት ሰፋሪዎች ሃይማኖተኞች እንደነበሩ በግልጽ ማየት ትችላለህ። የጥንቱን ዘመን የሚያስታውሱ ታሪካዊ የሆኑ በመንገድ ዳር የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ዛሬም በደሴቲቱ ዙሪያ በሚገኙ ጎዳናዎች ላይ ማየት ይቻላል፤ እያንዳንዱ መንደር የራሱ ቤተ ክርስቲያን አለው።
በሴንት-ፒር ከተማ በኩቤክ ከሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ እጅግ ጥንታዊ የሆነ ቤተ ክርስቲያን የሚገኝ ሲሆን የተሠራውም በ1717 ነው። ይህ ሕንፃ በአሁኑ ጊዜ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ማሳያ ሲሆን በውስጡ ልዩ የሆነ ነገር ይዟል። ከመሠዊያው በላይ ይሖዋ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱሱን አምላክ ስም የሚወክሉት ቴትራግራማተን በመባል የሚታወቁት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት ይገኛሉ።
በዛሬው ጊዜ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የአምላክን ስም ማየት ቀርቶ መስማት እንኳ አይቻልም። እንዲያውም በቫቲካን በ2008 የወጣ አንድ ሰነድ የአምላክን ስም በካቶሊክ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓቶች፣ መዝሙሮችና ጸሎቶች ላይ “መጠቀምም ሆነ መጥራት አይገባም” የሚለውን የሊቀ ጳጳሱን ትእዛዝ ይዞ ወጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ አምላክ ስሙ “በምድር ዙሪያ ሁሉ እንዲታወቅ” እንደሚፈልግ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።—ዘፀአት 9:16
የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላክን ለማስደሰት ስሙ በሕንፃ ላይ ተቀርጾ እንዲታይ ከማድረግ የበለጠ ነገር እንደሚያስፈልግ ያምናሉ። በየዓመቱ በምድር ዙሪያ ሰዎችን ስለ አምላክ ስምና ዓላማ ለማስተማር ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ሰዓት ያሳልፋሉ። እንዲያውም ይሖዋ የተባለውን የአምላክ ስም በተገቢው ቦታ ላይ እንዲገባ አድርገዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሳትሙት የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም የተባለው መጽሐፍ ቅዱስ ወደ 7,000 ጊዜ ገደማ የሚገኘውን ይሖዋ የሚለውን ስም በቦታው በማስቀመጥ መጀመሪያ ለተጻፈበት ቋንቋ ታማኝ ሆኗል። እስካሁን ድረስ የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በከፊል አሊያም በሙሉ በ83 ቋንቋዎች ከ165,000,000 በላይ ቅጂዎች ታትሟል። እንደ እውነቱ ከሆነ ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም በመጠቀም ረገድ የሚነሳው ጥያቄ ‘ስሙን የምንጠቀምበት ምን ምክንያት አለን?’ የሚለው ሳይሆን ‘ስሙን የማንጠቀምበት ምን ምክንያት አለን?’ የሚለው ነው።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ስም ወደ 7,000 ጊዜ ገደማ የሚገኝበት የአዲስ ዓለም የቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም በከፊል አሊያም በሙሉ በ83 ቋንቋዎች ታትሟል