የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g 9/11 ገጽ 14
  • የሩሲያ ባሕላዊ የእንጨት ላይ ሥዕል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የሩሲያ ባሕላዊ የእንጨት ላይ ሥዕል
  • ንቁ!—2011
ንቁ!—2011
g 9/11 ገጽ 14

የሩሲያ ባሕላዊ የእንጨት ላይ ሥዕል

● ሩሲያን የሚጎበኙ በርካታ ሰዎች እንደ ማትሮሽካ አሻንጉሊቶች ያሉ የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን መግዛት ያስደስታቸዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት እነዚህን ዕቃዎች ከእንጨት የሚሠሩት፣ በየመንደሩ የሚገኙ ጥሩ ችሎታ ያላቸው የእጅ ባለሞያዎች ነበሩ። በባሕላዊ መንገድ በእንጨት ላይ የሚሠራው ሥዕል ሆህሎማ በመባል ይታወቃል።

ላለፉት መቶ ዓመታት ሩሲያውያን በጥንቃቄ በተቀረጹና ሥዕል በተሳለባቸው የእንጨት ሳሕኖች ሲመገቡ የኖሩ ሲሆን በእንጨት በተሠሩ ማንኪያዎች፣ ኩባያዎች እንዲሁም ሌሎች ዕቃዎች ሲጠቀሙ ቆይተዋል። በእነዚህ ዕቃዎች ላይ የሚሳሉት ሥዕሎች በአብዛኛው እንስሳት ወይም እጽዋት ሊሆኑ ይችላሉ። በተለያዩ መንደሮች ውስጥ ነዋሪዎቹ በአጠቃላይ፣ ልዩ ልዩ የእንጨት ዕቃዎችን በመሥራት የሚጠመዱባቸው ጊዜያት ነበሩ።

በመንደር ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የግብርና ሥራ በማይበዛበትና ለረጅም ጊዜ በሚዘልቀው ቀዝቃዛ የክረምት ወቅት እነዚህን ዕቃዎች በማምረቱ ሥራ ላይ ይሠማሩ ነበር። ከሁለት መቶ ወይም ከዚያ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በአንዳንድ ከተሞች ወይም መንደሮች እነዚህን የዕደ ጥበብ ውጤቶች መሥራት በጣም አትራፊ ነበር። ለምሳሌ ያህል የሴሜኖቭ ነዋሪዎች በሙሉ የግብርና ሥራቸውን ትተው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ከእንጨት የተሠሩ ጎድጓዳና ዝርግ ሳሕኖችን፣ ኩባያዎችንና ማንኪያዎችን አምርተዋል።

በኒዥኒ ኖቭጎሮድ አቅራቢያ የሚኖሩ ነዋሪዎች ሥዕል የተሳለባቸው ዕቃዎች የማይለቅ የወርቅ ቅብ እንዲኖራቸው ማድረግ የሚቻልበትን ዘዴ ፈለሰፉ። በዚያን ወቅት ሙቀት መቋቋም የሚችሉ ቀለሞችና ቫርኒሾች ማምረት የተቻለ ሲሆን ተሠርተው ያለቁት ዕቃዎች በምድጃ ውስጥ ይተኮሱ ነበር። የብር ቀለም ያለው ዕቃ በከፍተኛ ሙቀት ውስጥ ማለፉ ወርቃማ መልክ እንዲይዝ ያስችለዋል። በኒዥኒ ኖቭጎሮድ አካባቢ ያሉ ሆህሎማ የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ዛሬም ይህንኑ ዘዴ ይጠቀማሉ።

የሆህሎማ ሥዕሎች በሩሲያ ደኖችና አረንጓዴ መስኮች ላይ የሚገኙትን አበቦችና እጽዋት አልፎ ተርፎም ወፎችንና ዓሦችን ያካትታሉ። ብዙውን ጊዜ የተጠቀለሉ የሣር ቀንበጦችና ቅጠሎች እንደ እንጆሪ ካሉ የተለያዩ ፍራፍሬዎች ጋር ይሳላሉ። አብዛኛውን ጊዜ ሥዕሎቹ የሚሳሉት በቀይ፣ በጥቁር፣ በወርቃማና በአረንጓዴ ቀለም ነው። በአሁኑ ጊዜ በብዙ የዓለም ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ ሰዎች፣ ዓይን የሚማርክና የሩሲያ ገጠራማ አካባቢዎችን የሚያሳይ ሥዕል በተሳለባቸው የሆህሎማ የዕደ ጥበብ ሥራዎች የምግብ ቤት ጠረጴዛቸውን ያስውባሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ