የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ወጪህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2013 | ሰኔ
    • የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ፦ የመግዛት አባዜ ተጠናውቶናል?

      የመግዛት አባዜ የተጠናወተን ለምንድን ነው?

      በ2012 ይፋ በሆነ አንድ ዓለም አቀፍ ጥናት ላይ፣ ጥያቄ ከቀረበላቸው ሰዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት የማያስፈልጋቸውን ዕቃ እንደሚገዙ ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ፣ ሰዎች የመግዛት አባዜ እንደተጠናወታቸው ይሰማቸዋል። በእርግጥም ጉዳዩ አሳሳቢ ነው። ብዙ ሸማቾች ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ በሚሄድ የዕዳ ማጥ ውስጥ ተዘፍቀዋል። ብዙ ነገሮችን መግዛት እርካታ ከማስገኘት ይልቅ የባሰ ጭንቀትና ብስጭት እንደሚያስከትል ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ታዲያ የመግዛት አባዜ የተጠናወተን ለምንድን ነው?

      ሸማቾች ለአፍታ እንኳ ጋብ የማይል የማስታወቂያ ውርጅብኝ ይዥጎደጎድባቸዋል። የንግድ አስተዋዋቂዎች ዓላማ ምንድን ነው? ለማግኘት የምንመኛቸው ነገሮች፣ የግድ እንደሚያስፈልጉን ሆኖ እንዲሰማን ማድረግ ነው። የንግድ አስተዋዋቂዎች ሸማቾች በአብዛኛው በስሜት እንደሚነዱ ያውቃሉ። በመሆኑም የማስታወቂያዎቹ አቀራረብና ሸቀጦች የሚቀርቡበት መንገድ ሸማቾች ዕቃዎቹን ለመግዛት እንዲጓጉ የሚያደርግ ነው።

      ሰዎች የማያስፈልጋቸውን ነገር የሚገዙት ለምንድን ነው? (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “በአብዛኛው ሸማቾች አንድ አዲስ ነገር ለመግዛት በሚነሱበት ጊዜ ሸቀጡን ሲፈልጉ፣ ሲያገኙና የራሳቸው ሲያደርጉ በዓይነ ሕሊናቸው ይታያቸዋል።” ሸማቾች ገበያ ሲወጡ በውስጣቸው ያለው የአድሬናሊን መጠን በጣም እንደሚጨምር አንዳንድ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የሽያጭ ባለሙያ የሆኑት ጂም ፑለር እንዲህ ብለዋል፦ “ሻጩ፣ ሸማቹ እንዲህ ያለ ስሜት እንዳለው ካስተዋለ የደንበኛውን ቀልብ ለመሳብ ጥረት ያደርጋል፤ ከዚያም የሸማቹ መጓጓትና ብዙም የማያቅማማ መሆኑ የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ዕቃውን ገዝቶ እንዲሄድ ያግባባዋል።”

      ታዲያ የብልሃተኛ አሻሻጮች ሰለባ ከመሆን ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? ስሜታዊ ሳትሆን ሰከን ባለ መንፈስ የንግድ አስተዋዋቂዎች የሚሰጡትን ተስፋ ከእውነታው ጋር አወዳድር።

      የሚሰጡህ ተስፋ፦ “ሕይወትህ ይሻሻላል”

      የተሻለ ሕይወት መኖር የማይፈልግ ሰው የለም። የንግድ አስተዋዋቂዎች ትክክለኛውን ዕቃ ከገዛን ምኞታችን በሙሉ ማለትም ጥሩ ጤንነት፣ ከስጋትና ከጭንቀት ነፃ የሆነ ኑሮና ከሰዎች ጋር የተሻለ ግንኙነት እንደሚኖረን የሚገልጹ መልእክቶች ያዥጎደጉዱብናል።

      እውነታው፦

      ቁሳዊ ንብረታችን እየጨመረ መምጣቱ ሕይወታችንን ከማሻሻል ይልቅ ደስታችን እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል። ተጨማሪ ቁሳዊ ነገር በገዛን ቁጥር ለእነዚህ ነገሮች አስፈላጊውን እንክብካቤ ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜና ገንዘብ ያስፈልገናል። እንዲሁም ከዕዳ ጋር ተያይዞ የሚመጣው ጭንቀት እየጨመረ ሊሄድ ብሎም ከቤተሰባችንና ከወዳጆቻችን ጋር የምናሳልፈው ጊዜ እየቀነሰ ሊመጣ ይችላል።

      ቁሳዊ ንብረታችን እየጨመረ መምጣቱ ሕይወታችንን ከማሻሻል ይልቅ ደስታችን እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል

      ጠቃሚ መመሪያ፦ ‘አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ አይደለም።’—ሉቃስ 12:15

      የሚሰጡህ ተስፋ፦ “በሌሎች ዘንድ ያለህ ግምትና ክብር ይጨምራል”

      አብዛኞቹ ሰዎች ዕቃ የሚገዙት የሌሎችን ትኩረት ለመሳብ እንደሆነ አምነው መቀበል ይከብዳቸዋል። ይሁን እንጂ ጂም ፑለር እንዲህ ብለዋል፦ “ሰዎች ዕቃ ለመግዛት ከሚነሳሱባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ከወዳጆቻቸው፣ ከጎረቤቶቻቸው፣ ከሥራ ባልደረቦቻቸውና ከዘመዶቻቸው ጋር ለመፎካከር ነው። አብዛኛዎቹ ማስታወቂያዎች የናጠጡ ሀብታሞች አንድን ምርት እየተጠቀሙበት ሲደሰቱ የሚያሳዩት ለዚህ ነው። እንዲህ ያሉ ማስታወቂያዎች ለሸማቾች የሚያስተላልፉት መልእክት “ይህ ሰው አንተ ልትሆን ትችላለህ!” የሚል ነው።

      እውነታው፦

      ማንነታችንን የምንለካው ራሳችንን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ከሆነ ዕድሜ ልካችንን እርካታ እንዳጣን እንኖራለን። ስንመኘው የነበረን አንድ ነገር በእጃችን ስናስገባው ሌላ ነገር መመኘት እንጀምራለን።

      ጠቃሚ መመሪያ፦ “ገንዘብን የሚወድ፣ ገንዘብ አይበቃውም።”—መክብብ 5:10

      የሚሰጡህ ተስፋ፦ “ማንነትህን ማሳየት አለብህ”

      አብረቅራቂ ዕቃዎች (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ “ማንነታችንን (ወይም መሆን የምንፈልገውን) ለሌሎች ከምናሳውቅባቸው የተለመዱ መንገዶች አንዱ ንብረት ማሳየት ነው።” የንግድ አስተዋዋቂዎች ይህን ስለሚያውቁ የንግድ አርማዎችን፣ በተለይ ውድ የሆኑ ዕቃዎችን የኑሮ ደረጃቸው ከፍ ካሉ ሰዎች ሕይወት ወይም ትልቅ ቦታ ከሚሰጠው አንድ ነገር ጋር ለማዛመድ ይጥራሉ።

      አንተ ራስህን የምታየው እንዴት ነው? ሌሎችስ እንዴት እንዲያዩህ ትፈልጋለህ? ዘናጭ እንደሆንክ ወይም ጥሩ ቁመና እንዳለህ? መሆን የምትፈልገው ምንም ይሁን ምን የንግድ አስተዋዋቂዎች አንድ ጥሩ ስም ያለው ዕቃ ከገዛህ የምትፈልገው ዓይነት ሰው መሆን እንደምትችል ተስፋ ይሰጡሃል።

      እውነታው፦

      የምንገዛው ዕቃ ምንም ይሁን ምን እውነተኛ ማንነታችንን ሊለውጠው አይችልም፤ ወይም እንደ ሐቀኝነትና ታማኝነት ያሉ ድንቅ ባሕርያት ባለቤት ሊያደርገን አይችልም።

      ጠቃሚ መመሪያ፦ “ውበታችሁ . . . የወርቅ ጌጣ ጌጦች በማድረግ ወይም በልብስ አይሁን፤ ከዚህ ይልቅ . . . የተሰወረ የልብ ሰው ይሁን።”—1 ጴጥሮስ 3:3, 4

      ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

      [ሥዕል]

      የንግድ አስተዋዋቂዎች የሚሰጡት ተስፋ በአብዛኛው ከእውነታው የራቀ ነው። ይሁን እንጂ ሚዛናዊና ደስተኛ ሕይወት ለመምራት የሚያስችል አስተማማኝ መመሪያ አለ። በዚህ ርዕስ የተጠቀሱት ጠቃሚ መመሪያዎች በሙሉ የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰዱ ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ሰው ቁሳዊ ነገሮች ቢኖሩት ስህተት እንደሆነ አይገልጽም። ይሁንና “ከገንዘብ ፍቅር ነፃ” የሆነ ሕይወት መምራት የበለጠ ደስታ እንደሚያስገኝ ያስተምራል።—ዕብራውያን 13:5

      ዘመናዊ የማስተዋወቂያ ዘዴዎች

      ዘመናዊ የንግድ አስተዋዋቂዎች በቴሌቪዥን፣ በኅትመት ውጤቶችና በኢንተርኔት ከማስተዋወቅ በተጨማሪ ከቀን ወደ ቀን ቁጥራቸው እየጨመረ በሄደ የተራቀቁ ዘዴዎች ይጠቀማሉ።

      የንግድ አርማዎችን በዘዴ ማሳየት፦ ምርቶችና የንግድ አርማዎች በቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ በፊልሞችና በቪዲዮ ጨዋታዎች ላይ እግረ መንገድ እንዲታዩ ይደረጋል።

      ሰዎችን በስውር ማሰማራት፦ በክፍያ የሚሠሩ ወኪሎች እንደሚከፈላቸው ሳያስታውቁ አንድን ዕቃ ተጠቅሞ በማሳየት ወይም ስለ ዕቃው በማውራት ምርቱን ያስተዋውቃሉ።

      ሰው በሰው ማስተዋወቅ፦ ሸማቾች ስለ ሸቀጦቹ ለወዳጆቻቸውና በማኅበራዊ ድረ ገጾች ለሚያገኟቸው ሰዎች አስተያየት እንዲሰጡ ይደረጋሉ። እንዲህ ባለው የማስተዋወቅ ሥራ እንዲካፈሉ ለማበረታታት ሲባልም የሚያስተዋውቁትን ዕቃ ወይም ሌሎች ሽልማቶችን ያገኛሉ።

  • ወጪህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2013 | ሰኔ
    • ወጪህን መቆጣጠር የምትችለው እንዴት ነው?

      ማስታወቂያዎች ከሚያሳድሩብን ተጽዕኖ በተጨማሪ ስሜታችንና ልማዳችን አላግባብ ገንዘብ እንድናወጣ ሊያደርጉን ይችላሉ። ወጪህን ለመቆጣጠር የሚረዱህ ስድስት የመፍትሔ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

      1. ያማረህን ሁሉ ከመግዛት ተቆጠብ። ገበያ መውጣት ወይም በቅናሽ ዋጋ የሚገኙ ዕቃዎችን መግዛት ያስደስትሃል? ከሆነ ያየኸውን ሁሉ ለመግዛት ልትፈተን ትችላለህ። አንድ ነገር ከመግዛትህ በፊት ቆም ብለህ ማሰብህ ይህንን ስሜት ለመቋቋም ይረዳሃል፤ ለመግዛት የምታወጣውን ገንዘብ እንዲሁም የዕቃው ባለንብረት መሆን ብሎም ለዕቃው ጥገናና እንክብካቤ ማድረግ ምን እንደሚጠይቅብህ አርቀህ አስብ። ከዚህ በፊት ያማረህን በመግዛትህ የተቆጨህባቸውን ጊዜያት አስብ። የመጨረሻ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት የማሰቢያ ጊዜ ይኑርህ።

      2. ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ስትል ብቻ አትግዛ። ገበያ መውጣት የተሰማህን መጥፎ ስሜት ለጊዜው ሊያስታግሥልህ ይችላል። መጥፎ ስሜቱ ተመልሶ ሲመጣ ግን ዕቃ በመግዛት ከመጥፎ ስሜትህ ለመገላገል ያለህ ፍላጎት ይጨምራል። ዕቃዎችን በመግዛት ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ሊያበረታቱህ የሚችሉ ወዳጆችን ፈልግ፤ ወይም በእግር እንደመጓዝ ያሉ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን አድርግ።

      3. ለመዝናናት ብለህ አትሸምት። በሚስብ ሁኔታ የተዘጋጁ የገበያ አዳራሾች መሸመትን አዝናኝ እንዲሆን አድርገዋል። ወደ ገበያ አዳራሾች የምትሄደው ወይም ኢንተርኔት የምትቃኘው ለመዝናናት ያህል ብቻ ይሆናል። ይሁንና አብዛኞቹ የምታያቸው ነገሮች የመግዛት ፍላጎትህን ለመቀስቀስ ተብለው የተዘጋጁ መሆናቸውን ማወቅ ይኖርብሃል። ያሰብከውን ነገር ብቻ ለመግዛት ጥረት አድርግ፤ በዚህ ውሳኔህ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ።

      4. አብረህ የምትውላቸውን ሰዎች ምረጥ። የጓደኞችህ አኗኗር ወይም የሚያወሩት ነገር በፍላጎትህ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል። ከጓደኞችህ እኩል ለመሆን ስትል ከአቅምህ በላይ ገንዘብ የምታወጣ ከሆነ ለገንዘብና ለቁሳዊ ነገሮች ብዙ ግምት የማይሰጡ ጓደኞችን መምረጥ ይሻልሃል።

      5. በዱቤ ስትገዛ ጥንቃቄ አድርግ። ክሬዲት ካርድ ወይም ዱቤ ዕቃ መግዛትን ቀላል ቢያደርግልህም በኋላ ላይ የሚመጣውን ጣጣ እንዳታገናዝብ እንቅፋት ሊሆንብህ ይችላል። የወሩን ዕዳህን በዚያው ወር ውስጥ ከፍለህ ለመጨረስ ሞክር። የክሬዲት ካርድህ ኩባንያ ምን ያህል ወለድና የአገልግሎት ክፍያ እንደሚጠይቅ እወቅ፤ ከዚያም አነስተኛ ክፍያ የሚጠይቁ ድርጅቶችን አፈላልግ። ከፍተኛ ክፍያ የሚጠይቁና ለአንተ ምንም ፋይዳ የሌላቸውን ጥቅማ ጥቅሞች የሚሰጡ ውድ ካርዶችን ከመጠቀም ተጠንቀቅ። ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ ዕቃዎችን በዱቤ ከመግዛት ይልቅ ገንዘቡን አጠራቅመህ እጅ በእጅ ከፍለህ ግዛ።

      6. የገንዘብ አቅምህን እወቅ። የገንዘብ አቅምህ ምን ያህል እንደሆነ በእርግጠኝነት ካላወቅክ ከአቅምህ በላይ ልታወጣ ትችላለህ። ገቢና ወጪህን በየጊዜው መዝግበህ በመያዝ የገንዘብ አቅምህን እወቅ። ገቢህንና ባለፉት ወራት የነበሩህን ወጪዎች መሠረት በማድረግ ወርኃዊ ባጀት አውጣ። ወጪዎችህን ተከታትለህ በመመዝገብ ከባጀትህ ጋር አስተያይ። ከገንዘብ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ለመረዳት የቸገረህ ጉዳይ ካለ የምታምነው ወዳጅህ እንዲረዳህ ጠይቀው።

      ልጆቻችሁ የመግዛት አባዜ እንዳይጠናወታቸው ተጠንቀቁ

      የንግድ አስተዋዋቂዎች በተለይ ልጆችን ዒላማ ያደርጋሉ፤ ይህም የሚያስደንቅ አይደለም። በዛሬው ጊዜ ወጣቶች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ገንዘብ ያወጣሉ። በዩናይትድ ስቴትስ በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያጠፋሉ።

      ይሁን እንጂ ጁልየት ሾር የተባሉ ተመራማሪ እንደተናገሩት የመግዛት አባዜ የተጠናወታቸው ልጆች በመንፈስ ጭንቀት የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ሲሆን ከወላጆቻቸውም ጋር ጥሩ ግንኙነት የላቸውም። ታዲያ ልጆቻችሁን ከዚህ አባዜ መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው? እስቲ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመጠበቅ የተጠቀሙባቸውን ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መንገዶች ቀጥለን እንመልከት።

      አስተምሩ፦ “ማስታወቂያዎች የትም ቦታ የሚገኙ ስለሆኑ ልጆችን ከማስታወቂያዎች ሙሉ በሙሉ መጠበቅ አይቻልም። በመሆኑም የንግድ አስተዋዋቂዎች የራሳቸው የሆነ ዓላማ እንዳላቸውና ዓላማቸውም ለቀጠራቸው ድርጅት ገንዘብ ማስገኘት እንደሆነ ለሴት ልጆቻችን እንነግራቸዋለን። ለእኛ ጥቅም እንደማያስቡ እናስረዳቸዋለን።”—ጄምስ እና ጄሲካ

      በአቋማችሁ ጽኑ፦ “ልጆች የሚፈልጉትን ነገር ለማስገዛት ሊነዘንዟችሁ ይችላሉ። ይሁን እንጂ እጅ መስጠት አይኖርባችሁም። ውሎ አድሮ የፈለጉትን ሁሉ ማግኘት እንደማይችሉ ይማራሉ። ወላጅ እንደመሆናችን መጠን ሴት ልጃችንን ስናሳድግ ሚዛናችንን እንዴት መጠበቅ እንደምንችልና ምን ገደብ ማውጣት እንዳለብን እንነጋገር ነበር።”—ስኮት እና ኬሊ

      ተጋላጭነታቸውን ቀንሱ፦ “ቤተሰባችን ቴሌቪዥን በብዛት አይመለከትም። ቴሌቪዥን ማየት የቤተሰባችን ልማድ አይደለም። ቴሌቪዥን ከመመልከት ይልቅ ሌሎች ነገሮችን በማድረግ ጊዜውን እናሳልፋለን። አብረን ምግብ አብስለን እንበላለን፤ በተጨማሪም ልጆቻችን ጎበዝ አንባቢዎች ናቸው።”—ጆን እና ጄኔፈር

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ