የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ቅልጥፍና
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • ጥናት 4

      ቅልጥፍና

      ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

      ስታነብም ሆነ ስትናገር የምትጠቀምባቸው ቃላትና የምትናገረው ሐሳብ ያላንዳች መደነቃቀፍና መዘበራረቅ እንዲንቆረቆሩ አድርግ። ቅልጥፍና ያለው ተናጋሪ ንግግሩ አይቆራረጥም ወይም ቅርፍፍ ያለ አይሆንም። እንዲሁም በቃላት አይደነቃቀፍም ወይም ሐሳብ ለማመንጨት አይንገታገትም።

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      አንድ ተናጋሪ ቅልጥፍና ከሌለው የአድማጮቹ አእምሮ ሊባዝን ይችላል። የተሳሳተ መልእክትም ሊያስተላልፍ ይችላል። ንግግሩም አድማጮችን የማሳመን ኃይል አይኖረውም።

      ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ አንዳንድ ቃላት ላይ ትደነቃቀፋለህ? ወይም ደግሞ ንግግር ስትሰጥ ብዙውን ጊዜ ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት ትቸገራለህ? ከሆነ በቅልጥፍና ረገድ ችግር አለብህ ማለት ሊሆን ይችላል። ቅልጥፍና ያለው ተናጋሪ ሲናገርም ሆነ ሲያነብብ ያለ ችግርና ያለምንም መደነቃቀፍ ቃላቱን ማውጣትና ሐሳቡን መግለጽ ይችላል። ይህ ማለት ግን ያለፋታ ያወራል፣ በጣም ይፈጥናል ወይም እንዳመጣለት ይናገራል ማለት አይደለም። ንግግሩ ማራኪና ለዛ ያለው ይሆናል። ይህ የንግግር ባሕርይ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶታል።

      ቅልጥፍና እንዳይኖርህ እንቅፋት የሚሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ምናልባት ከዚህ ቀጥሎ ከተዘረዘሩት መካከል ለየት ያለ ትኩረት ልትሰጠው የሚገባህ ነጥብ ይኖር ይሆን? (1) ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ አንዳንድ እንግዳ ቃላት ካጋጠሙህ እየቆጠርህ ማንበብ ትጀምር ይሆናል። (2) አሁንም አሁንም ቆም የምትል ከሆነ ሐሳቡ የተቆራረጠ ይሆናል። (3) የዝግጅት ማነስ ለችግሩ አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይችላል። (4) ንግግር ስትሰጥ ቅልጥፍና እንዳይኖርህ የሚያደርገው የተለመደ ችግር ነጥቦችህ በቅደም ተከተል ተደራጅተው አለመቀመጣቸው ነው። (5) አንድ ሰው የሚያውቃቸው ቃላት ውስን ከሆኑም ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት ሲሞክር ሊደነቃቀፍ ይችላል። (6) አጽንኦት የሚሰጣቸው ቃላት ከበዙም ቅልጥፍና አይኖረውም። (7) የሰዋስው ሕግን በሚገባ አለማወቅም ቅልጥፍና እንዳይኖር እንቅፋት ሊሆን ይችላል።

      ቅልጥፍና ከሌለህ አድማጮችህ ቃል በቃል የመንግሥት አዳራሹን ለቅቀው ባይወጡም በሐሳብ ሊባዝኑ ይችላሉ። ከዚህም የተነሣ የምትናገረው አብዛኛው ነገር ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ ሊቀር ይችላል።

      በሌላ በኩል ደግሞ አድማጮችን ለተግባር የሚቀሰቅስና ቅልጥፍና ያለው እንዲሆን ያሰብከው ንግግር አድማጮችን የሚኮንን አልፎ ተርፎም የሚያሸማቅቅ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይኖርብሃል። በአንተና በአድማጮችህ መካከል ካለው የአስተዳደግ ልዩነት የተነሳ አድማጮችህ ለሰዎች ስሜት እንደማትጠነቀቅ ወይም ንግግርህ ቅንነት እንደሚጎድለው ከተሰማቸው የተነሣህበት ዓላማ መና ሊቀር ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ልምድ ያለው ተናጋሪ ቢሆንም እንኳ አላግባብ የሰዎችን ትኩረት ወደ ራሱ ላለመሳብ ሲል የቆሮንቶስ ሰዎችን የቀረባቸው “በድካምና በፍርሃት በብዙ መንቀጥቀጥ” መሆኑ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ነው።​—⁠1 ቆሮ. 2:​3

      ሊወገዱ የሚገባቸው ልማዶች። ብዙ ሰዎች በሚናገሩበት ጊዜ “እ-እ-እ” የማለት ልማድ አላቸው። ሌሎች ደግሞ አንድ ሐሳብ ከመጀመራቸው በፊት “አሁን” የሚለውን ቃል ወይም በተናገሩ ቁጥር “እንግዲያው” ወይም “ስለዚህ” የሚሉትንና እነዚህን የመሳሰሉ ማያያዣዎች ይደጋግማሉ። ምናልባት እንደነዚህ ያሉትን መግለጫዎች ምን ያህል ደጋግመህ እንደምትጠቀም አይታወቅህ ይሆናል። አንድ ሰው ስትናገር እንዲያዳምጥህና እነዚህን ቃላት በጠራህ ቁጥር እንዲደግምልህ ልታደርግ ትችላለህ። ቃላቱን ምን ያህል እንደምትደጋግማቸው ስታስተውል ትገረም ይሆናል።

      አንዳንድ ሰዎች ሲያነብቡም ሆነ ሲናገሩ በተደጋጋሚ ወደኋላ እየተመለሱ ያሉትን ነገር የመድገም ልማድ አላቸው። ይህም አንድ ዓረፍተ ነገር ጀምረው መሃል ከደረሱ በኋላ አቋርጠው ወደኋላ በመመለስ ቢያንስ የተወሰነውን ክፍል እንደገና ይደግማሉ ማለት ነው።

      ሌሎች ደግሞ የሚናገሩበት ፍጥነት በቂ ሆኖ ሳለ አንድ ሐሳብ ይጀምሩና ዓረፍተ ነገሩን ሳይቋጩ ወደ ሌላ ሐሳብ ይሸጋገራሉ። ቃላቱ ያለ አንዳች እንቅፋት የሚንቆረቆሩ ቢሆንም ድንገተኛ የሐሳብ ለውጥ መደረጉ ለንግግሩ ቅልጥፍና እንቅፋት ይሆናል።

      ማሻሻል የሚቻልበት መንገድ። እየተናገርህ ሳለ ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት የምትቸገር ከሆነ የምታውቃቸውን ቃላት ብዛት ለመጨመር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች እንዲሁም ሌሎች ጽሑፎች ስታነብብ ለአንተ አዲስ የሆኑ ቃላትን ልብ ለማለት ሞክር። የእነዚህ ቃላት ትርጉም ምን እንደሆነ ለማወቅ መዝገበ ቃላት ተመልከት። ከዚያም አንዳንዶቹን ከአሁን ቀደም ከምታውቃቸው ቃላት ጋር ተጠቀምባቸው። በቋንቋህ መዝገበ ቃላት የማይገኝ ከሆነ ቋንቋውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው እንዲረዳህም ልትጠይቅ ትችላለህ።

      ድምፅን ከፍ አድርጎ የማንበብ ልማድ ማዳበር በዚህ ረገድ ለማሻሻል ይረዳል። አስቸጋሪ ሆነው ያገኘሃቸውን ቃላት ድምፅህን ከፍ አድርገህ ደጋግመህ ተለማመዳቸው።

      ንባብህ ቅልጥፍና ያለው እንዲሆን ቃላቱ በዓረፍተ ነገሩ ውስጥ ያላቸውን አገባብ መረዳት ይኖርብሃል። የጸሐፊውን መልእክት በትክክል ለማስተላለፍ በርከት ያሉ ቃላትን አንድ ላይ ማንበብ ያስፈልጋል። አንድ ላይ መሆን ያለባቸውን ቃላት ልብ በል። ምልክት ማድረግ እንደሚሻል ከተሰማህ እንደዚያ ማድረግ ትችላለህ። ግብህ ቃላቱን በትክክል ማንበብ ብቻ ሳይሆን ሐሳቡን ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተላለፍም ነው። ከአንቀጹ ጋር በደንብ እስክትተዋወቅ ድረስ ዓረፍተ ነገሮቹን አንድ በአንድ አጥናቸው። የሐሳቡን ቅደም ተከተል በደንብ ተረዳ። ከዚያም ድምፅህን ከፍ አድርገህ ተለማመድ። ሳትደነቃቀፍና አለቦታው ሳትቆም ማንበብ እስክትችል ድረስ አንቀጹን ደግመህ ደጋግመህ አንብበው። ከዚያ ወደሚቀጥለው አንቀጽ ተሻገር።

      ከዚያ ደግሞ ፍጥነትህን ጨምር። ቃላቱ በዓረፍተ ነገሩ ውስጥ ያላቸውን አገባብ ከተረዳህ በአንድ ጊዜ በርከት ያሉ ቃላትን መመልከት ከመቻልህም ሌላ ቀጥሎ ያለውን ሐሳብ አስቀድመህ መገመት ትችላለህ። ይህም ለንባብህ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

      አንድን ጽሑፍ ያለ ቅድሚያ ዝግጅት ማንበብን ልማድ ማድረግ ጠቃሚ ሥልጠና ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል አስቀድመህ ሳትዘጋጅ የዕለቱን ጥቅስና አብሮ የተሰጠውን ሐሳብ ድምፅህን ከፍ አድርገህ የማንበብ ልማድ አዳብር። አንድን ቃል በተናጠል ከማየት ይልቅ የተወሰነ መልእክት የሚያስተላልፉ በርከት ያሉ ቃላትን ለማየት ሞክር።

      ከሰዎች ጋር ስትወያይ ንግግርህ ቅልጥፍና እንዲኖረው፣ ከመናገርህ በፊት ምን እንደምትል ማሰብ ይኖርብሃል። ዕለት ተዕለት ከሰዎች ጋር ስትነጋገር ይህን ልማድ አዳብር። መናገር ከመጀመርህ በፊት ምን መልእክት ማስተላለፍ እንደምትፈልግና በምን ቅደም ተከተል እንደምትናገረው አስብ። አትጣደፍ። መሃል ላይ ሳትቆም ወይም የሐሳብ ለውጥ ሳታደርግ በአንድ ጊዜ አንድ የተሟላ መልእክት ለማስተላለፍ ሞክር። ዓረፍተ ነገሮችህ አጭርና ቀላል መሆናቸው የተሻለ ሊሆን ይችላል።

      ምን ማለት እንደፈለግህ ጠንቅቀህ የምታውቅ ከሆነ ቃላቱ በቀላሉ ይመጡልሃል። አብዛኛውን ጊዜ የምትጠቀምባቸውን ቃላት አስቀድሞ መምረጥ አያስፈልግም። እንዲያውም ሐሳቡ ብቻ ግልጽ እንዲሆንልህ ካደረግህ በኋላ የምትጠቀምባቸውን ቃላት እየተናገርህ ሳለህ ማሰቡ ጥሩ ልምምድ ሊሆንልህ ይችላል። ይህን ካደረግህና አእምሮህ በቃላቱ ላይ ሳይሆን በሐሳቡ ላይ ካተኮረ ቃላቱ ብዙም ሳትጨነቅ ሊመጡልህ ይችላሉ። ይህም በውስጥህ ያለውን ስሜት በሚገባ ለመግለጽ ያስችልሃል። ይሁን እንጂ ስለምትናገረው ሐሳብ ሳይሆን ስለ ቃላቱ ማሰብ ከጀመርህ ንግግርህ ሊደነቃቀፍ ይችላል። ብዙ ልምምድ ባደረግህ መጠን ጥሩ ተናጋሪና አንባቢ ለመሆን የሚረዳውን የቅልጥፍና ባሕርይ ልታዳብር ትችላለህ።

      ሙሴ ይሖዋን በመወከል ወደ እስራኤል ሕዝብና ወደ ግብጹ ፈርዖን እንዲሄድ ሲላክ ብቁ እንዳልሆነ ተሰምቶት ነበር። ለምን? አንደበተ ርቱዕ ሰው ስላልነበረ ነው። ምናልባትም የመኮላተፍ ችግር ኖሮበት ሊሆን ይችላል። (ዘጸ. 4:​10፤ 6:​12) ሙሴ የራሱን ምክንያቶች ቢያቀርብም አምላክ አልተቀበለውም። ይሖዋ አሮንን እንደ ቃል አቀባይ አድርጎ ከመላክም በተጨማሪ ሙሴ ራሱ መናገር እንዲችል ረድቶታል። ሙሴ ለግለሰቦች ወይም ጥቂት ቁጥር ላላቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ጭምር በተደጋጋሚ ጥሩ አድርጎ ለመናገር በቅቷል። (ዘዳ. 1:​1-3፤ 5:​1፤ 29:​2፤ 31:​1, 2, 30፤ 33:​1) በይሖዋ በመታመን አቅምህ የሚፈቅድልህን ሁሉ ካደረግህ አንተም አንደበትህን አምላክን ለማክበር ልትጠቀምበት ትችላለህ።

      የመንተባተብን ችግር መቋቋም

      አንድ ሰው እንዲንተባተብ የሚያደርጉት ብዙ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆናል። ለአንዳንዶች ጥሩ ውጤት የሚያመጡት ሕክምናዎች ለሌሎች ምንም ላይፈይዱ ይችላሉ። ይሁን እንጂ መሻሻል በማድረግ የሚገኘውን ደስታ ለማጣጣም ሳይታክቱ መሞከር በጣም አስፈላጊ ነው።

      በስብሰባ ላይ ሐሳብ ስለመስጠት ስታስብ ፍርሃት አልፎ ተርፎም ጭንቀት ያድርብሃል? ይሖዋ እንዲረዳህ ጸልይ። (ፊልጵ. 4:​6, 7) ማተኮር ያለብህ ይሖዋን በማወደስና ሌሎችን በመርዳት ላይ ነው። ችግሩ ሙሉ በሙሉ ይወገዳል ብለህ አትጠብቅ። ከዚህ ይልቅ ችግሩን ለመቋቋም በሚረዱህ ነገሮች ላይ አተኩር። የይሖዋን በረከትና የወንድሞችህን ማበረታቻ ስታገኝ ይበልጥ የተሻለ ነገር ለማድረግ እንደምትነሳሳ ጥርጥር የለውም።

      ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት የመናገር ልምድ እንድታገኝ ይረዳሃል። በሚያስቡልህና እንድትሻሻል በሚፈልጉ የተወሰኑ ሰዎች ፊት በደንብ መናገር እንደቻልክ ስታይ ትበረታታለህ። ይህ ደግሞ በሌላም ጊዜ ንግግር ለመስጠት የሚያስችል ድፍረት እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል።

      ንግግር የምትሰጥ ከሆነ በደንብ ተዘጋጅ። በምታቀርበው ትምህርት ተመሰጥ። ስትናገር ተገቢውን ስሜት ለማንጸባረቅ ሞክር። እየተናገርህ ሳለ መንተባተብ ከጀመርህ በተቻለ መጠን ድምፅህንም ሆነ ንግግርህን ዝግ አድርግ። የመንገጭላህ ጡንቻዎች ዘና እንዲሉ አድርግ። አጫጭር ዓረፍተ ነገሮችን ተጠቀም። በንግግር መሀል እ-እ-እ ማለትን የመሳሰሉ ልማዶችን ቀንስ።

      የመንተባተብ ችግራቸውን የተቋቋሙ አንዳንድ ሰዎች የሚያስቸግሯቸውን ቃላት አንዴ ካወቋቸው በኋላ እነዚህን ቃላት መጠቀም ትተው በምትኩ ተመሳሳይ ትርጉም ያላቸውን ሌሎች ቃላት ይጠቀማሉ። ሌሎች ደግሞ ይበልጥ የሚያስቸግሯቸውን የንግግር ድምፆች ለይተው በማውጣት ደግመው ደጋግመው መለማመዱን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል።

      ከሰው ጋር ስትነጋገር የምትንተባተብ ከሆነ ተስፋ ቆርጠህ ውይይቱን አታቁም። አንተ እንደገና መቀጠል እስክትችል ድረስ እርሱ እንዲናገር ማድረግ ትፈልግ ይሆናል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ሐሳብህን በአጭሩ ጻፍለት ወይም አንድ ጽሑፍ አሳየው።

      እዚህ ግብ ላይ መድረስ የምትችለው እንዴት ነው?

      • መጽሔቶችንና መጻሕፍትን በምታነብበት ጊዜ አዳዲስ ቃላት ስታገኝ ምልክት አድርግ፣ ትክክለኛ ትርጉማቸውን ፈልግ እንዲሁም ሌላ ጊዜ ተጠቀምባቸው።

      • በየዕለቱ ቢያንስ ከአምስት እስከ አሥር ደቂቃ ለሚያህል ጊዜ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማንበብን ተለማመድ።

      • በንባብ የሚቀርቡ ክፍሎችን በሚገባ ተዘጋጅ። የተወሰነ መልእክት የሚያስተላልፉ በርከት ያሉ ቃላትን አንድ ላይ ተመልከት። የሐሳቡን ቅደም ተከተል በደንብ ተረዳ።

      • ከሰዎች ጋር በምታደርገው የዕለት ተዕለት ውይይት፣ ከመናገርህ በፊት ምን እንደምትል ማሰብንና ንግግርህን ሳታቋርጥ አንድ ሙሉ ዓረፍተ ነገር መናገርን ተማር።

      መልመጃ:- መሳፍንት 7:​1-25ን በማየት የእያንዳንዱን አንቀጽ ይዘት ተራ በተራ በጥንቃቄ መርምር። ምን እንደሚል በደንብ ተረዳ። እንግዳ የሚሆኑብህ ቃላት ካሉ መዝገበ ቃላት ተመልከት። እያንዳንዱን የተጸውኦ ስም ድምፅህን ከፍ አድርገህ እያነበብህ ተለማመድ። ከዚያ ጠቅላላ አንቀጹን ድምፅህን ከፍ አድርገህ አንብብ። በተቻለ መጠን በትክክል ለማንበብ ጥረት አድርግ። አንዱን አንቀጽ በደንብ እንደተለማመድህ ሲሰማህ ወደሚቀጥለው አንቀጽ ተሻገር። በዚህ መልኩ ጠቅላላውን ምዕራፍ አንብብ። ከዚያ ትንሽ ፍጥነትህን በመጨመር እንደገና ሁሉንም አንብበው። አስፈላጊ በሚሆንበት ቦታ ላይ ከበፊቱም የበለጠ ፈጠን እያልክ ለተጨማሪ ጊዜ ደግመህ አንብበው። ይሁን እንጂ እስክትደነቃቀፍ ድረስ መፍጠን የለብህም።

  • በተገቢው ቦታ ቆም ማለት
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • ጥናት 5

      በተገቢው ቦታ ቆም ማለት

      ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

      በንግግርህ መሃል በተገቢ ቦታዎች ላይ ቆም በል። አንዳንዴ ለአጭር ጊዜ ቆም ትል ወይም ድምፅህን ለጊዜው ብቻ በጣም ዝቅ ታደርግ ይሆናል። በተገቢው ቦታ ላይ ቆም ብለሃል ሊባል የሚችለው በዓላማ ካደረግኸው ብቻ ነው።

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      በተገቢው ቦታ ላይ ቆም ማለት አድማጮች ንግግሩን በቀላሉ እንዲረዱት በማድረግ ረገድ ትልቅ ድርሻ አለው። ከዚህም በተጨማሪ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች እንዲጎሉ ያደርጋል።

      በንግግር መካከል በትክክለኛው ቦታ ላይ ቆም ማለት በጣም አስፈላጊ ነው። ንግግር ስታቀርብም ይሁን በተናጠል ከሰዎች ጋር ስትወያይ በተገቢው ቦታ ቆም እያልክ መናገርህ ጠቃሚ ነው። በዚህ መልኩ ቆም የማትል ከሆነ የምትናገረው ነገር አንድ ግልጽ የሆነ መልእክት የሚያስተላልፍ መሆኑ ይቀርና እንዲሁ ቃላትን የምታነበንብ ሊመስል ይችላል። በአንጻሩ ግን ይህንን ማድረግህ ንግግርህ ግልጽ እንዲሆን ይረዳል። ከዚህም በላይ ዋና ዋና ነጥቦችህ በአድማጮች አእምሮ ውስጥ እንዲቀረጹ ሊያደርግ ይችላል።

      መቼ ቆም ማለት እንዳለብህ እንዴት ማወቅ ትችላለህ? ደግሞስ ርዝማኔው ምን ያህል መሆን አለበት?

      ሐሳቡን በትክክል ለማስተላለፍ ቆም ማለት። ሥርዓተ ነጥብ የጽሑፍ ቋንቋ አቢይ ክፍል ነው። የአንድን ሐሳብ ወይም ጥያቄ መጨረሻ ሊጠቁም ይችላል። በአንዳንድ ቋንቋዎች ደግሞ ከሌላ ምንጭ የተጠቀሱ ሐሳቦችን ለመለየት ያገለግላል። አንዳንድ ሥርዓተ ነጥቦች አንዱ የዓረፍተ ነገር ክፍል ከሌላው ጋር ያለውን ዝምድና ያመለክታሉ። ሰውዬው ለራሱ እያነበበ ከሆነ ሥርዓተ ነጥቦቹን ያያቸዋል። ይሁን እንጂ ለሌሎች በሚያነብበት ጊዜ በጽሑፉ ላይ ያሉትን ሥርዓተ ነጥቦች ትርጉም በድምፁ ቃና ማንጸባረቅ ይኖርበታል። (ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት “ጥርት ያለ ንባብ” የሚለውን ጥናት ቁጥር 1 ተመልከት።) ሥርዓተ ነጥቡ ቆም ማለትን የሚጠይቅ ሆኖ እያለ ቆም ሳትል ከቀረህ ሌሎች ሰዎች ያነበብኸውን ነገር መረዳት ሊቸግራቸው አልፎ ተርፎም የጽሑፉ መልእክት ሊዛባ ይችላል።

      ከሥርዓተ ነጥብ በተጨማሪ በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ሐሳቦቹ የገቡበት መንገድም የት ቦታ ቆም ማለት ተገቢ እንደሚሆን በመጠቆም ረገድ የራሱ ድርሻ አለው። በአንድ ወቅት አንድ ታዋቂ ሙዚቀኛ እንዲህ ብሏል:- “እኔ ኖታውን ከሌሎች ፒያኖ ተጫዋቾች የተለየ አድርጌ ተጫውቼው አይደለም። ምሥጢሩ ያለው በኖታዎቹ መካከል እንዴትና መቼ ቆም ማለት እንዳለብህ ማወቁ ላይ ነው።” በንግግርም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በተገቢው ቦታ ቆም ማለት ጥሩ አድርገህ ለተዘጋጀኸው ትምህርት ውበትና ለዛ ይጨምርለታል።

      ለሌሎች ለማንበብ ስትዘጋጅ በጽሑፉ ላይ ምልክት ማድረጉን ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል። ትንሽ ቆም የምትልበት ቦታ ላይ አንድ የቁም ሰረዝ አድርግ። ረዘም ላለ ጊዜ ቆም የምትልበት ቦታ ላይ ደግሞ ሁለት የተጠጋጉ የቁም ሰረዞችን ተጠቀም። በትክክል ለማንበብ የምትቸገርበት ቦታ ካለና በተደጋጋሚ ጊዜ ያለ ቦታው ቆም የምትል ከሆነ ያስቸገረህ ሐረግ ውስጥ ያሉትን አብረው የሚነበቡ ቃላት ለማያያዝ በእርሳስ ምልክት አድርግባቸው። ከዚያም ሐረጉን ሙሉ በሙሉ አንብበው። ብዙ ልምድ ያላቸው ተናጋሪዎችም የሚጠቀሙበት ዘዴ ይኸው ነው።

      በዕለት ተዕለት ውይይቶች ወቅት ምን ማለት እንደምትፈልግ ስለምታውቅ ብዙውን ጊዜ ቆም በማለት ረገድ ችግር አይኖርብህም። ይሁን እንጂ ሐሳቡ የት ቦታ ላይ ቆም ማለት እንደሚጠይቅ ግምት ውስጥ ሳታስገባ እንዲሁ በልማድ በየቦታው ቆም የምትል ከሆነ የንግግርህ ኃይል ይዳከማል እንዲሁም መልእክቱ ይሸፈናል። “ቅልጥፍና” በሚለው ጥናት 4 ውስጥ በዚህ ረገድ ማሻሻያ ለማድረግ የሚረዱ ሐሳቦች ተሰጥተዋል።

      የሐሳብ ለውጥ ለማድረግ ቆም ማለት። ከአንዱ ዋና ነጥብ ወደ ሌላው በምትሸጋገርበት ጊዜ ቆም ማለትህ አድማጮችህ መለስ ብለው የሚያስቡበት፣ ራሳቸውን ከነጥቡ ጋር የሚያስተያዩበት፣ ውይይቱ ወደ የት አቅጣጫ እያመራ እንዳለ የሚያብላሉበት እንዲሁም ቀጣዩን ነጥብ በግልጽ መጨበጥ የሚችሉበት ፋታ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። መኪና በምታሽከረክርበት ጊዜ አንድ መንገድ ይዘህ ስትጓዝ ቆይተህ ወደ ሌላ መንገድ ስትታጠፍ ፍጥነትህን መቀነስ እንደሚያስፈልግህ ሁሉ ከአንዱ ሐሳብ ወደ ሌላው ስትሻገርም ቆም ማለት አስፈላጊ ነው።

      አንዳንድ ተናጋሪዎች ያለ ፋታ ከአንዱ ሐሳብ ወደ ሌላው የሚሸጋገሩበት አንዱ ምክንያት በንግግራቸው ብዙ ነጥቦችን ለማካተት ስለሚሞክሩ ነው። አንዳንዶቹ ደግሞ የዕለት ተዕለት ውይይታቸውም ከዚህ የተለየ ስላልሆነ ነው። ምናልባት በቅርብ የሚያገኟቸው ሰዎችም አነጋገር ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። ይህ ግን ውጤታማ አስተማሪ ለመሆን አይበጅም። አድማጮች ሊሰሙት ደግሞም ሊያስታውሱ ይገባል የምትለውን ነጥብ ስትናገር መልእክቱ ግልጽ እንዲሆንላቸው ጊዜ መስጠት ያስፈልግሃል። ንግግሩ ግልጽ እንዲሆን ቆም ማለት የግድ አስፈላጊ መሆኑን አትዘንጋ።

      ንግግርህን የምታቀርበው አስተዋጽኦ ይዘህ ከሆነ በዋና ዋና ነጥቦች መካከል የት ቦታ ላይ ቆም ማለት እንደምትችል በግልጽ በሚያሳይ መንገድ የተዋቀረ መሆን አለበት። በንባብ የሚቀርብ ጽሑፍ ከሆነ ከአንዱ ዋና ነጥብ ወደሌላው በሚሸጋገርበት ቦታ ላይ ምልክት አድርግ።

      የሐሳብ ለውጥ ለማድረግ ሲባል ቆም የምትልበት የጊዜ መጠን ሥርዓተ ነጥብ ላይ ቆም ከምትልበት ጊዜ ይበልጥ ረዘም ይላል። ይሁን እንጂ ንግግርህ እስኪንዛዛ ድረስ መሆን የለበትም። ረዘም ላለ ጊዜ ቆም የምትል ከሆነ ጥሩ ዝግጅት እንዳላደረግህና ቀጥሎ ምን ማለት እንዳለብህ የምታስብ ሊያስመስልብህ ይችላል።

      ለማጥበቅ ሲባል ቆም ማለት። ብዙውን ጊዜ ማጥበቅ የፈለግኸውን ሐሳብ ወይም ጥያቄ ረገጥ አድርገህ ከተናገርህ ወይም ካነበብህ በኋላ ቆም ማለት የአድማጮችን አእምሮ ያነቃል። እንዲህ ማድረግ አድማጮች በተነገረው ነገር ላይ እንዲያሰላስሉ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል ወይም ከዚያ ቀጥሎ የሚነገረውን ነገር በጉጉት እንዲጠብቁ ያነሳሳቸዋል። ሁለቱ ተመሳሳይ ነገሮች አይደሉም። ስለዚህ የትኛውን ዘዴ ብትጠቀም የተሻለ እንደሚሆን ወስን። ይሁንና ለማጉላት ብሎ ቆም የማለት ዘዴ ሊሠራበት የሚገባው አስፈላጊ ለሆኑ ነጥቦች ብቻ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብሃል። አለበለዚያ እነዚህ ነጥቦች ይደበቃሉ።

      ኢየሱስ ናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ ድምፁን ከፍ አድርጎ ቅዱሳን ጽሑፎችን ባነበበበት ወቅት ቆም የማለትን ዘዴ ጥሩ አድርጎ ተጠቅሞበታል። በመጀመሪያ ከነቢዩ ኢሳይያስ ጥቅልል ስለ እርሱ የተጻፈውን አነበበ። ይሁን እንጂ የጥቅሱን ተግባራዊ ገጽታ ከማብራራቱ በፊት ጥቅልሉን እንደነበረ መልሶ ለአገልጋዩ ሰጠና ተቀመጠ። ከዚያም በምኩራብ ያሉት ሰዎች ሁሉ ዓይን በእርሱ ላይ ባረፈ ጊዜ “ዛሬ ይህ መጽሐፍ በጆሮአችሁ ተፈጸመ” አላቸው።​—⁠ሉቃስ 4:​16-21

      በሁኔታዎች አስገዳጅነት ቆም ማለት። አልፎ አልፎ ንግግርህን የሚረብሹ ነገሮች ቆም እንድትል ያደርጉህ ይሆናል። በአካባቢው የሚያልፍ ተሽከርካሪ ድምፅ ወይም የሚያለቅስ ሕፃን አገልግሎት ላይ ካገኘኸው ሰው ጋር የምታደርገውን ውይይት ለትንሽ ጊዜ እንድታቋርጥ ያስገድድህ ይሆናል። በስብሰባ ቦታ የሚረብሽ ድምፅ ቢፈጠር ለመደማመጥ የሚያስቸግር እስካልሆነ ድረስ ድምፅህን ከፍ አድርገህ መቀጠል ትችል ይሆናል። ይሁን እንጂ የሚረብሸው ድምፅ ከፍተኛና ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ከሆነ ቆም ማለት ይኖርብሃል። በመሠረቱ መናገርህን ብትቀጥልም አድማጮች ሊያዳምጡህ አይችሉም። እንግዲያው አድማጮችህ ከምትነግራቸው መልካም ነገር ሙሉ ጥቅም እንዲያገኙ ስትል ቆም እያሉ የመናገርን ዘዴ ጥሩ አድርገህ ተጠቀምበት።

      የሌሎችን ሐሳብ ለመስማት ቆም ማለት። የምታቀርበው ንግግር መደበኛ በሆነ መንገድ ተሳትፎ ማድረግን የሚጠይቅ ባይሆንም አድማጮች ለራሳቸው መልስ እንዲሰጡ ማድረግ አስፈላጊ ነው። አድማጮችህ እንዲያስቡ የሚያደርግ ጥያቄ ካነሳህ በኋላ በደንብ ቆም ብለህ ጊዜ ካልሰጠሃቸው ጥያቄዎችህ እምብዛም ዋጋ አይኖራቸውም።

      እርግጥ ከመድረክ ንግግር ስትሰጥ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎች ስትመሠክርም ቆም ማለት ያስፈልግሃል። አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ ፋታ አይሰጡም። አንተም ተመሳሳይ ችግር ካለብህ ይህንን የንግግር ባሕርይ ለማዳበር ልባዊ ጥረት አድርግ። ይህ የንግግር ባሕርይ ከሌሎች ጋር ያለህን የሐሳብ ግንኙነት የሚያሻሽልልህ ከመሆኑም ሌላ በመስክ አገልግሎት ያለህን ውጤታማነት ለማሳደግ ይረዳሃል። በንግግር መሃል ቆም ማለት የዓረፍተ ነገሩን መልእክት በትክክል ለማስተላለፍ፣ ነጥቡን ለማጉላት፣ የአድማጮችን ትኩረት ለማግኘትና ነቃ ብለው እንዲያዳምጡ ለማድረግ ይረዳል መባሉ ተገቢ ነው።

      ዕለት ተዕለት ከሰዎች ጋር በምናደርገው ውይይት ሐሳባችንን እንገልጻለን፤ የእነርሱንም ሐሳብ እናዳምጣለን። እነርሱ ሲናገሩ የምታዳምጥና የሚሉትን ነገር በትኩረት የምትከታተል ከሆነ እነርሱም አንተን ለማዳመጥ ይገፋፋሉ። ይህም ሐሳባቸውን እንዲገልጹ ፋታ መስጠትን ይጠይቅብሃል።

      ብዙውን ጊዜ አገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው እኛ ብቻ ከመናገር ይልቅ እነርሱም ሐሳብ እንዲሰጡ ስናደርግ ነው። ብዙ ምሥክሮች ከሰላምታ ልውውጡ በኋላ ርዕሰ ጉዳያቸውን አስተዋውቀው አንድ ጥያቄ ማንሳቱን ውጤታማ ሆኖ አግኝተውታል። የሚያነጋግሩት ሰው ሐሳቡን እንዲገልጽ ፋታ ለመስጠት ቆም ካሉ በኋላ ምን ማለት እንደፈለገ መረዳታቸውን ይገልጻሉ። በውይይቱ ወቅት በየመሃሉ ሐሳቡን የሚገልጽበት አጋጣሚ ይሰጡታል። ግለሰቡ እየተወያዩበት ስላለው ርዕሰ ጉዳይ ምን ዓይነት አመለካከት እንዳለው ከገባቸው በተሻለ መንገድ መርዳት እንደሚችሉ ያውቃሉ።​—⁠ምሳሌ 20:​5

      እርግጥ ሁሉም ሰው ለምታነሳው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ይሰጣል ማለት አይደለም። ይሁንና ሰዎች አዎንታዊ መልስ ላይሰጡ ይችላሉ የሚለው ሐሳብ በኢየሱስ ላይ ተጽእኖ አልነበረውም። ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹ እንኳ ሳይቀሩ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። (ማር. 3:​1-5) ግለሰቡ እንዲናገር አጋጣሚ መስጠት በጉዳዩ ላይ እንዲያስብበት ስለሚያደርገው በልቡ ያለውን አውጥቶ ሊነግረን ይችላል። እንዲያውም የአገልግሎታችን አንዱ ዓላማ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትንና ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ውሳኔ ሊያደርጉባቸው የሚገቡትን ክብደት ያላቸው ጉዳዮች በማንሳት የታሰበበት ምላሽ እንዲሰጡ ማነሳሳት ነው።​—⁠ዕብ. 4:​12

      በእርግጥም በአገልግሎት ከሰዎች ጋር ስንወያይ በተገቢው ቦታ ላይ ቆም እያልን መናገር ራሱን የቻለ ጥበብ ነው። ይህን የንግግር ባሕርይ በሚገባ ከሠራንበት የምናስተላልፈው ሐሳብ ግልጽ ከመሆኑም በተጨማሪ በአድማጫችን አእምሮ ውስጥ ይቀረጻል።

      ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

      • ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ ለሥርዓተ ነጥቦች ለየት ያለ ትኩረት ስጥ።

      • ጥሩ ችሎታ ያላቸውን ተናጋሪዎች በጥሞና በማዳመጥ የት ቦታ ላይና ለምን ያህል ጊዜ ቆም እንደሚሉ አስተውል።

      • አድማጮችህ እንዲያስታውሱት የምትፈልገውን ነገር ከተናገርህ በኋላ ነጥቡ በአእምሮአቸው እንዲቀረጽ ትንሽ ቆም በል።

      • ከሰዎች ጋር ስትወያይ ሐሳባቸውን እንዲገልጹ በመጋበዝ የሚሰጡትን መልስ አዳምጥ። አስጨርሳቸው። በመሃል አቋርጠህ አትግባ።

      መልመጃ:- ማርቆስ 9:​1-13ን ድምፅህን ከፍ አድርገህ አንብብ። እያንዳንዱ ሥርዓተ ነጥብ ላይ ስትደርስ ለሥርዓተ ነጥቡ እንደሚስማማ ቆም እያልክ አንብብ። ንባብህ መንዛዛት የለበትም። ጥሩ አድርገህ ከተለማመድህ በኋላ አንድ ሰው ንባብህን እያዳመጠ ቆም በማለት ረገድ ማሻሻል የምትችልባቸውን ቦታዎች እንዲጠቁምህ አድርግ።

  • ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • ጥናት 6

      ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅ

      ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

      አድማጮች እየተብራራ ያለውን ሐሳብ እንዲረዱ በሚያስችል መንገድ ቃላትንና ሐረጎችን ማጉላት።

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      አንድ ተናጋሪ ቁልፍ ቃላትን ወይም ሐረጎችን በተገቢው ሁኔታ የሚያጠብቅ ከሆነ አድማጮቹ በትኩረት እንዲከታተሉት ማድረግ ከመቻሉም ሌላ ሊያሳምናቸውና ለሥራ ሊያነሳሳቸው ይችላል።

      ንግግር በምትሰጥበትም ሆነ ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ እያንዳንዱን ቃል በትክክል መጥራትህ ብቻ ሳይሆን ቁልፍ የሆኑትን ቃላትና መልእክት አዘል አገላለጾች፣ ሐሳቡን በግልጽ ለማስተላለፍ በሚያስችል መንገድ ጠበቅ አድርገህ ማንበብህም በጣም አስፈላጊ ነው።

      ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅ ሲባል ጥቂት ወይም ብዙ ቃላትን ማጉላት ማለት ብቻ አይደለም። መጥበቅ ያለባቸው ትክክለኛዎቹ ቃላት ናቸው። የተሳሳቱ ቃላትን የምታጠብቅ ከሆነ አድማጮች የምትናገረው ነገር ትርጉም ግልጽ ላይሆንላቸው ይችላል። ይህ ደግሞ አእምሯቸው እንዲባዝን ምክንያት ይሆናል። ትምህርቱ ጥሩ ቢሆንም እንኳ ተናጋሪው ቁልፍ ቃላትን ወይም ሐረጎችን በሚገባ የማያጠብቅ ከሆነ አቀራረቡ አድማጮቹን ለሥራ የመቀስቀስ ኃይል አይኖረውም።

      የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ግነቱን መጨመር የሚቻል ሲሆን ብዙ ጊዜ የሚከተሉት ዘዴዎች በአንድነት ሲሠራባቸው እናገኛለን:- የድምፅን መጠን ከፍ ማድረግ፣ ግለትን መጨመር፣ ዝግና ረጋ ብሎ መናገር፣ ከአንድ ሐሳብ በፊት ወይም በኋላ (ወይም በሁለቱም ቦታ) ቆም ማለትና አካላዊ መግለጫ ናቸው። በአንዳንድ ቋንቋዎች ድምፅን ከፍ ወይም ዝቅ በማድረግ ማጉላት ይቻላል። ይበልጥ ተስማሚ የሚሆነው የትኛው ዘዴ እንደሆነ ለመወሰን ትምህርቱንና ሌሎች ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ አስገባ።

      የት ላይ ማጉላት እንዳለብህ ለመወሰን የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል። (1) በየትኛውም ዓረፍተ ነገር ውስጥ ቢሆን መጥበቅ ያለባቸውን ቃላት ለመወሰን የሚረዳህ ዓረፍተ ነገሩ ብቻ ሳይሆን በዙሪያው ያለው ሐሳብ ጭምር ነው። (2) አንድ ዋና ነጥብ የሚጀምርበት ወይም የሐሳብ ለውጥ የሚደረግበት ቦታ ጎላ ብሎ እንዲታይ ለማድረግ ቁልፍ ቃላትንና ሐረጎችን የማጥበቅን ዘዴ ልትጠቀም ትችላለህ። ይህንኑ ዘዴ በመጠቀም አድማጮች የአንድ ነጥብ ማጠቃለያ ላይ እንደደረስክ እንዲገነዘቡ ማድረግም ይቻል ይሆናል። (3) አንድ ተናጋሪ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚሰማው ለማንጸባረቅም ተስማሚ የሆኑትን ቃላት ወይም ሐረጎች ሊያጠብቅ ይችላል። (4) ይህ ዘዴ የአንድን ንግግር ዋና ዋና ነጥቦች ለማጉላትም ሊሠራበት ይችላል።

      አንድ ሰው ንግግር ሲሰጥም ሆነ ለሌሎች ሲያነብ በእነዚህ መንገዶች ለማጥበቅ እንዲችል በመጀመሪያ ራሱ ትምህርቱን በግልጽ ሊረዳው እንዲሁም አድማጮቹ እንዲገባቸው የመርዳት ልባዊ ፍላጎት ሊኖረው ይገባል። በዕዝራ ዘመን የተሰጠውን ትምህርት በተመለከተ ነህምያ 8:​8 እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔርንም ሕግ መጽሐፍ አነበቡ፤ ዕዝራም እግዚአብሔርን ማወቅ ያስተምርና ያስታውቅ ነበር፣ ሕዝቡም የሚነበበውን ያስተውሉ ነበር።” በወቅቱ የአምላክን ሕግ ያነብቡና ያብራሩ የነበሩት ሰዎች አድማጮቻቸው የሚነበበውን ነገር ትርጉም እንዲያስተውሉና አስታውሰውም ተግባራዊ እንዲያደርጉት መርዳት እንዳለባቸው ተገንዝበው እንደነበር ግልጽ ነው።

      ችግሩ ምን ሊሆን ይችላል? አብዛኛዎቹ ሰዎች በዕለት ተዕለት ንግግራቸው ሐሳባቸውን ቁልጭ አድርገው መግለጽ አይቸግራቸውም። ይሁን እንጂ ሌላ ሰው የጻፈውን ጽሑፍ በሚያነብቡበት ጊዜ የትኛው ቃል ወይም ሐሳብ መጥበቅ እንዳለበት ለመወሰን ይቸገራሉ። ለዚህ ዋነኛ መፍትሔው መልእክቱን በግልጽ መረዳት ነው። ይህም ጽሑፉን በደንብ ማጥናትን ይጠይቃል። በመሆኑም በጉባኤ ስብሰባ ላይ አንድ ጽሑፍ እንድታነብብ ከተመደብህ ጥሩ አድርገህ መዘጋጀት ይኖርብሃል።

      አንዳንድ ሰዎች ቁልፍ ቃላትን ወይም ሐረጎችን ብቻ ከማጥበቅ ይልቅ ትርጉም ኖረውም አልኖረው እንዲሁ አለፍ አለፍ እያሉ አንዳንድ ቃላትን ያጠብቃሉ። ሌሎች ደግሞ መስተዋድዶችንና መስተጻምሮችን ሳይቀር ከልክ በላይ ያጠብቃሉ። የምናጎላው ነገር ሐሳቡን ግልጽ ለማድረግ የሚረዳ ካልሆነ የአድማጮችን ትኩረት ከመስረቅ በቀር ፋይዳ አይኖረውም።

      አንዳንድ ተናጋሪዎች ቁልፍ ቃላትን ለማጥበቅ በማሰብ ጮክ ብለው ስለሚናገሩ አድማጮች ንግግሩ ወቀሳ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ይህ ደግሞ የሚያመጣው ጥሩ ውጤት አይኖርም። ተናጋሪው የሚያጠብቅበት መንገድ የተጋነነ ከሆነ አድማጮቹን የናቃቸው ሊያስመስልበት ይችላል። ከዚህ ይልቅ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በመናገር ትምህርቱ ቅዱስ ጽሑፋዊና ምክንያታዊ መሆኑን እንዲያስተውሉ መርዳቱ ምንኛ የተሻለ ይሆናል!

      ማሻሻል የሚቻልበት መንገድ። ብዙውን ጊዜ ቁልፍ ቃላትን ወይም ሐረጎችን በማጥበቅ ረገድ ችግር ያለበት ሰው ችግሩ እንዳለበት እንኳ አይታወቀውም። ምናልባት ሌላ ሰው ይህን ድክመቱን እንዲጠቁመው ያስፈልግ ይሆናል። በዚህ ረገድ ማሻሻል የሚያስፈልግህ ከሆነ የትምህርት ቤቱ የበላይ ተመልካች ይረዳሃል። ጥሩ ተናጋሪ የሆነ ሌላ ወንድምም ቢሆን ምክር እንዲሰጥህ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። ስታነብብ እና ስትናገር በጥሞና አዳምጦ ልታሻሽል የምትችልባቸውን አቅጣጫዎች እንዲጠቁምህ ጠይቀው።

      በመጀመሪያ ምክር ሰጪህ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እያነበብህ እንድትለማመድ ሐሳብ ሊያቀርብልህ ይችል ይሆናል። መልእክቱን ግልጽ ለማድረግ የሚረዱትን ቃላትና ሐረጎች መርጠህ ማጉላት እንድትችል እያንዳንዱን ዓረፍተ ነገር ማጤን እንደሚያስፈልግህ ሊመክርህ ይችላል። በሰያፍ ለተጻፉት አንዳንድ ቃላት ለየት ያለ ትኩረት እንድትሰጥ ያሳስብህ ይሆናል። በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ያሉ ቃላት እርስ በርስ እንደሚደጋገፉ አትዘንጋ። ብዙ ጊዜ ማጉላት ያለብህ በርከት ያሉ ቃላትን እንጂ አንድን ቃል አይደለም። በአንዳንድ ቋንቋዎች ተማሪዎቹ ቁልፍ ቃላትን ወይም ሐረጎችን በተገቢው ሁኔታ ለማጥበቅ የሚረዱ አናባቢ ምልክቶችን ልብ ብለው እንዲያነቡ ምክር ሊሰጣቸው ይችላል።

      በመቀጠል ደግሞ ማጉላት ያለብህን ነገር መወሰን እንድትችል በዓረፍተ ነገሩ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ሰፋ አድርገህ እንድትመለከት ይመክርህ ይሆናል። የአንቀጹ ዋና ነጥብ ምንድን ነው? ይህስ በእያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ጎላ አድርገህ መግለጽ ያለብህን ሐሳብ በተመለከተ ወሳኝነት ያለው እንዴት ነው? ዋናውን ርዕስና ነጥቡ የተጠቀሰበትን ንዑስ ርዕስ ተመልከት። ይህስ የምታጎላውን ሐሳብ ለመምረጥ የሚረዳህ እንዴት ነው? እነዚህ ሁሉ ግምት ውስጥ መግባት ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው። ይሁንና የምታጎላቸው ቃላት በጣም ብዙ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ይኖርብሃል።

      ምክር ሰጪህ አስተዋጽኦ ይዘህ ንግግር ስትሰጥም ይሁን በቀጥታ ከአንድ ጽሑፍ በምታነብበት ጊዜ ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ለማጥበቅ ነጥቡ እየተብራራ ያለበትን አቅጣጫ ልብ እንድትል ያሳስብህ ይሆናል። እያንዳንዱ ነጥብ የሚያበቃበትን ወይም ትምህርቱ ከአንዱ ሐሳብ ወደሌላ አስፈላጊ ነጥብ የሚሸጋገርበትን ቦታ ልብ ማለት ያስፈልግሃል። አቀራረብህ እነዚህን ነጥቦች በደንብ ለመለየት የሚያስችል ከሆነ አድማጮችህ ከትምህርቱ እንዲጠቀሙ እንደረዳሃቸው ይሰማቸዋል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ከዚህ ቀጥሎ፣ በመጨረሻ እና እንግዲያው እንደሚሉት ያሉትን ቃላት ለየት ባለ ቃና በመጥራት ይህንን ማድረግ ትችል ይሆናል።

      እንዲሁም ምክር ሰጪህ በተለየ ስሜት መግለጽ የምትፈልጋቸው ነጥቦች ላይ እንድታተኩር ሐሳብ ይሰጥህ ይሆናል። ይህንንም ለማድረግ በጣም፣ በፍጹም፣ በምንም ዓይነት፣ የማይታሰብ ነው፣ በጣም አስፈላጊ፣ እና ምንጊዜም የሚሉትን ቃላት ጎላ አድርገህ ልትገልጻቸው ትችል ይሆናል። እንዲህ ማድረግህ አድማጮች ለመልእክቱ በሚኖራቸው ስሜት ረገድ የራሱ ድርሻ አለው። ይህ ጉዳይ “ወዳጃዊ ስሜት የሚያንጸባርቅ” በሚለው በ11ኛው ጥናት ላይ ተጨማሪ ሐሳብ ይሰጥበታል።

      ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ በማጥበቅ ረገድ መሻሻል ከፈለግህ አድማጮችህ እንዲያስታውሷቸው የምትፈልጋቸው ዋና ዋና ነጥቦች በቅድሚያ ለአንተ ግልጽ ሊሆኑልህ ይገባል። ይህ ነጥብ “ዋና ዋና ነጥቦችን አጽንዖት ሰጥቶ ማንበብ” በሚለው ጥናት 7 ውስጥ ለሌሎች ከማንበብ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ማብራሪያ ይሰጥበታል። “ዋና ዋና ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ማድረግ” በሚለው ጥናት 37 ውስጥ ደግሞ ከንግግር ጋር በተያያዘ ይብራራል።

      በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን እየጣርክ ከሆነ ጥቅሶችን ስለምታነብበት መንገድ አጥብቀህ ልታስብ ይገባል። ‘ይህን ጥቅስ የማነብበት ምክንያት ምንድን ነው?’ እያልክ ራስህን የመጠየቅ ልማድ ይኑርህ። አንድ አስተማሪ ቃላቱን አስተካክሎ መናገሩ ብቻውን በቂ ላይሆን ይችላል። ሐሳቡን በስሜት ማንበቡም ቢሆን በቂ ነው ማለት አይደለም። አንድ ሰው ላነሳው ጥያቄ መልስ እየሰጠህ ወይም ስለ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እያስተማርህ ከሆነ እየተብራራ ያለውን ነጥብ የሚደግፉትን የጥቅሱን ቃላት ወይም ሐሳቦች ጎላ አድርጎ መግለጹ ተገቢ ይሆናል። አለበለዚያ ግን ጥቅሱን የምታነብብለት ሰው መልእክቱን ሳይጨብጠው ሊቀር ይችላል።

      ብዙም ልምድ የሌለው አንድ ተናጋሪ ለማጉላት በማሰብ አንዳንድ ቃላትን ወይም ሐረጎችን ከልክ በላይ ያጠብቅ ይሆናል። ሁኔታውን የሙዚቃ ኖታዎችን አቀናጅቶ ለመጫወት እየሞከረ ካለ ጀማሪ ሙዚቀኛ ጋር ማመሳሰል ይቻላል። ሰውዬው ልምድ እያገኘ ሲሄድ “ኖታዎቹን” ጥሩ አድርጎ በመጫወት ውብ የሆነ “ሙዚቃ” ማውጣት ይችላል።

      አንዴ መሠረታዊ የሆኑትን ነገሮች ከተማርክ በኋላ ተሞክሮ ያላቸውን ተናጋሪዎች በመመልከት ተጨማሪ ልምድ መቅሰም ትችላለህ። በዚህ መንገድ በተለያየ መጠን ቃላትንና ሐረጎችን ማጉላት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ማስተዋልህ አይቀርም። እንዲሁም የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ነጥቡን ማጉላት መልእክቱን ግልጽ ለማድረግ ምን ያህል ጉልህ ድርሻ እንዳለው እየተገነዘብህ ትሄዳለህ። ቁልፍ ቃላትን በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅን መማር የንባብህንም ሆነ የንግግርህን ውጤታማነት ያሻሽልልሃል።

      በተገቢው ሁኔታ ማጥበቅን መማር ያለብህ ለምታቀርበው ክፍል ስትል ብቻ መሆን የለበትም። ውጤታማ ተናጋሪ ሆነህ እንድትገኝ ይህ የንግግር ባሕርይ ተዋህዶህ ለሌሎች ጆሮ በሚጥም መንገድ ተፈላጊውን ነጥብ ማጥበቅ እስክትችል ድረስ መለማመድህን ቀጥል።

      እንዴት ልታዳብረው ትችላለህ?

      • በዓረፍተ ነገር ውስጥ የሚገኙትን ቁልፍ ቃላት ነጥለህ ማውጣትን ተማር። ቁልፍ የሆኑትን ቃላት ለመለየት በዙሪያው ያለውን ሐሳብ ልብ በል።

      • (1) የሐሳብ ለውጥ የተደረገበትን ቦታ ለመጠቆም እንዲሁም (2) ስለ ጉዳዩ ያለህን ስሜት ለማንጸባረቅ የማጉላትን ዘዴ ለመጠቀም ሞክር።

      • ጥቅስ በምታነብበት ጊዜ ከተጠቀሰበት ምክንያት ጋር በቀጥታ የሚዛመዱትን ቃላት የማጉላት ልማድ ይኑርህ።

      መልመጃ፦ (1) በአገልግሎት አዘውትረህ የምትጠቀምባቸውን ሁለት ጥቅሶች ምረጥ። እያንዳንዱን ጥቅስ ስትጠቀም ማስረዳት የፈለግኸው ነገር ምን እንደሆነ አስብ። ከዚያም ድምፅህን እያሰማህ ነጥቦቹን የሚደግፍልህን ቃል (ወይም ቃላት) ጎላ አድርገህ አንብብ። (2) ዕብራውያን 1:​1-14ን አጥና። በምዕራፉ ውስጥ እየተብራራ ያለውን ነጥብ ግልጽ ለማድረግ (ቁጥር 1 ላይ) “ነቢያት”፣ (ቁጥር 2 ላይ) “ልጁ” እንዲሁም (ቁጥር 4 እና 5 ላይ) “መላእክት” የሚሉት ቃላት ለየት ያለ ግነት የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ዋናውን ነጥብ በሚያጎላ መንገድ በማጥበቅ መላውን ምዕራፍ እያነበብህ ተለማመድ።

  • ዋና ዋና ነጥቦችን አጽንዖት ሰጥቶ ማንበብ
    በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም
    • ጥናት 7

      ዋና ዋና ነጥቦችን አጽንዖት ሰጥቶ ማንበብ

      ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

      ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ በእያንዳንዱ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ባለው ነጥብ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ በጠቅላላው ትምህርት ውስጥ ያሉትን ዋና ዋና ነጥቦች ለየት ያለ አጽንዖት ሰጥተህ ማንበብ ይኖርብሃል።

      አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

      ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች አጽንዖት እየሰጠህ ካነበብህ አድማጮችህ መልእክቱን በቀላሉ ማስታወስ ይችላሉ።

      አንድ ጥሩ አንባቢ በአንድ ዓረፍተ ነገር ላይም ሆነ ዓረፍተ ነገሩ በሚገኝበት አንቀጽ ላይ ብቻ አያተኩርም። ከዚህ ይልቅ በጠቅላላው ትምህርት ውስጥ ላሉት ዋና ዋና ነጥቦች ትኩረት ይሰጣል። ይህም አጽንዖት በሚሰጥባቸው ነጥቦች ምርጫ ረገድ የራሱ ድርሻ አለው።

      አንባቢው ይህን ሳያደርግ ከቀረ በንባቡ ወቅት ጎልቶ ወይም ከሌሎች ልቆ የሚታይ ነጥብ አይኖርም። ክፍሉ ሲያልቅ ለየት ብሎ የሚታወስ ነጥብ ማግኘት ሊያስቸግር ይችላል።

      አንድ አንባቢ ለዚህ የንግግር ባሕርይ ትኩረት የሚሰጥ ከሆነ ብዙውን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ሕያው አድርጎ ማንበብ ይችላል። ይህም የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመራም ይሁን የጉባኤ ስብሰባ በሚደረግበት ጊዜ የሚነበቡት አንቀጾች ይበልጥ ትርጉም አዘል እንዲሆኑ ይረዳል። በተለይ በአውራጃ ስብሰባ ላይ እንደምናየው በንባብ የሚቀርብ ንግግር በሚሆንበት ጊዜ ዋና ዋና ነጥቦችን አጽንዖት ሰጥቶ ማንበብ በጣም አስፈላጊ ነው።

      ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተወሰነ ክፍል እንድታነብብ ትመደብ ይሆናል። አጽንዖት ሊሰጠው የሚገባው ነጥብ የትኛው ነው? የምታነብበው ክፍል በአንድ ዋና ነጥብ ወይም ጉልህ ክንውን ላይ ያተኮረ ከሆነ ይህ ነጥብ ጎላ ብሎ እንዲታይ ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ይሆናል።

      የምታነብበው ነገር ግጥምም ይሁን ስድ ንባብ፣ ምሳሌም ይሁን ትረካ ጥሩ አድርገህ ካነበብኸው አድማጮችህ ይጠቀማሉ። (2 ጢሞ. 3:​16, 17) ይህንን ለማድረግ ትምህርቱንና አድማጮችህን ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል።

      በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት ወይም በጉባኤ ስብሰባ ላይ ስታነብብ አጽንዖት ልትሰጣቸው የሚገቡት ዋና ዋና ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? የጥያቄዎቹን መልሶች እንደ ዋና ዋና ነጥቦች አድርገህ ልትመለከታቸው ትችላለህ። ከዚህ በተጨማሪ ከንዑስ ርዕሱ ጋር የሚዛመዱት ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ አድርግ።

      በጉባኤ የሚቀርቡትን ንግግሮች በንባብ በሚቀርብ ጽሑፍ መልክ ማዘጋጀቱ የሚበረታታ አይደለም። ይሁን እንጂ አንዳንድ የአውራጃ ስብሰባ ንግግሮች በሁሉም ቦታዎች በተመሳሳይ መልክ እንዲሰጡ ሲባል በንባብ እንዲቀርቡ ሆነው ይዘጋጃሉ። ተናጋሪው በዚህ ዓይነቱ ንግግር ውስጥ የሚገኙትን ዋና ዋና ነጥቦች አጽንዖት ሰጥቶ ለማንበብ አስቀድሞ ትምህርቱን በጥንቃቄ ሊያብላላው ይገባል። ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? እነዚህን ለይቶ ማውጣት መቻል አለበት። ዋና ዋና ነጥቦች የሚባሉት ተናጋሪውን የማረኩት ነጥቦች ሳይሆኑ ትምህርቱ ያተኮረባቸው ቁልፍ ሐሳቦች ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ዋናው ነጥብ በአጭር ዓረፍተ ነገር ይቀመጥና ዝርዝር ሐሳቡ ከዚያ ቀጥሎ በትረካ ወይም በማብራሪያ መልክ ይቀርባል። አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ሐሳቡ በዝርዝር ከቀረበ በኋላ መልእክቱን ጠቅለል አድርጎ በሚያስጨብጥ ዓረፍተ ነገር ይደመደማል። ተናጋሪው እነዚህን ቁልፍ ነጥቦች ለይቶ ካወጣ በኋላ በጽሑፉ ላይ ምልክት ሊያደርግባቸው ይገባል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ነጥቦች ከአራት ወይም ከአምስት አይበልጡም። ከዚህ በኋላ ለአድማጮቹ በሚያነብበት ጊዜ እነዚህ ነጥቦች ግልጽ ሆነው እንዲታዩ ማድረግ የሚችልበትን መንገድ መለማመድ ይኖርበታል። በንግግሩ ውስጥ ጎላ ብለው የሚታዩት ነጥቦች እነዚህ ይሆናሉ ማለት ነው። ተናጋሪው ትምህርቱን ያቀረበው በተገቢው መንገድ አጽንዖት እየሰጠ ከሆነ ዋና ዋና ነጥቦቹ በአድማጮች አእምሮ ውስጥ መቀረጻቸው አይቀርም። ደግሞም የተናጋሪው ግብ ይህ መሆን አለበት።

      አንድ ተናጋሪ አድማጮቹ ዋና ዋና ነጥቦቹን እንዲለዩ ለመርዳት አጽንዖት መስጠት የሚችልባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል ግለቱን ሊጨምር፣ ፍጥነቱን ሊቀይር፣ በስሜት ሊናገር ወይም ተስማሚ አካላዊ መግለጫ ሊጠቀም ይችላል።

      ሊታወሱ የሚገባቸው ነገሮች

      • ትምህርቱ ያተኮረባቸውን ዋና ዋና ነጥቦች ለመለየት ጽሑፉን በሚገባ አጥናው። ከዚያም ያገኘሃቸውን ነጥቦች ምልክት አድርግባቸው።

      • ለሌሎች በምታነብበት ጊዜ ዋና ዋናዎቹ ነጥቦች ጎላ ብለው እንዲታዩ ለማድረግ እንደ አስፈላጊነቱ ግለትህን ጨምር፣ ፍጥነትህን ቀንስ ወይም በስሜት ተናገር።

      መልመጃ:- በሳምንቱ ከሚጠናው የመጠበቂያ ግንብ ርዕስ ላይ አምስት አንቀጾች ምረጥ። ለአንቀጾቹ በወጡት ጥያቄዎች መልስ ላይ አስምር። ከዚያም አድማጮችህ መልሱን በቀላሉ ማግኘት በሚያስችላቸው መንገድ አንቀጾቹን እያነበብህ ተለማመድ።

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ