የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 15—ዕዝራ
ጸሐፊው:- ዕዝራ
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም
ተጽፎ ያለቀው:- 460 ከክ.ል.በፊት ገደማ
የሚሸፍነው ጊዜ:- 537 እስከ 467 ከክ.ል.በፊት ገደማ
ኢየሩሳሌም በባቢሎን ግዛት ሥር ባድማ ሆና የምትቆይባቸው በትንቢት የተነገሩት 70 ዓመታት የሚያበቁበት ጊዜ ተቃርቧል። እርግጥ ባቢሎን ምርኮኞቿን በፍጹም ነፃ እንደማትለቅቅ ይነገርላታል፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት ባቢሎን ከነበራት ጥንካሬ የበለጠ ኃይል ያላቸው መሆኑ ይረጋገጣል። የይሖዋ ሕዝቦች ነፃ የሚወጡበት ጊዜ እጅግ ተቃርቦ ነበር። የፈራረሰው የይሖዋ ቤተ መቅደስ እንደገና ይገነባል፤ እንዲሁም በይሖዋ መሠዊያ ላይ በድጋሚ የስርየት መሥዋዕቶች ይቀርባሉ። ኢየሩሳሌም እውነተኛ የይሖዋ አምላኪዎች በሚያሰሙት የደስታና የውዳሴ ድምፅ እንደገና ትሞላለች። ኤርምያስ ከተማዋ ባድማ ሆና የምትቆይበትን የጊዜ ርዝመት የተነበየ ሲሆን ኢሳይያስ ደግሞ ምርኮኞቹ ነፃነታቸውን የሚጎናጸፉት እንዴት እንደሆነ ተንብዮአል። ኢሳይያስ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ሦስተኛ የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነችውን ትዕቢተኛዋን ባቢሎንን የሚገለብጣት የፋርሱ ቂሮስ እንደሆነ የገለጸ ሲሆን ይህንን መሪ የይሖዋ “እረኛ” በማለት ጠርቶታል።—ኢሳ. 44:28፤ 45:1, 2፤ ኤር. 25:12
2 የባቢሎን ንጉሥ ቤልሻዛርና መኳንንቱ ለአጋንንታዊ አማልክቶቻቸው ክብር እየጠጡ በነበሩበት በጥቅምት 5, 539 ከክርስቶስ ልደት በፊት (እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር) ምሽት ላይ ባቢሎን ወደቀች። ንጉሡና መኳንንቱ ከይሖዋ ቤተ መቅደስ በዘረፏቸው ቅዱስ ዕቃዎች መጠጥ በመጠጣት አረማዊ ፈንጠዝያቸው ይባስ በክፋት የተሞላ እንዲሆን አድርገዋል! ቂሮስ ትንቢቱን ለመፈጸም በዚያን ዕለት ምሽት በባቢሎን ቅጥር አቅራቢያ መገኘቱ ምንኛ ተስማሚ ነው!
3 ይህ ጊዜ ማለትም 539 ከክርስቶስ ልደት በፊት ከዓለም ታሪክም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር የሚስማማ ወሳኝ ዓመት ነው። ቂሮስ የባቢሎን ገዥ በሆነበት በመጀመሪያው ዓመት አይሁዳውያን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው የይሖዋን ቤት መልሰው እንዲገነቡ በመፍቀድ “በመንግሥቱ ሁሉ ዐዋጅ [አስነገረ።]” ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ይህ ትእዛዝ የወጣው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ538 መገባደጃ ላይ ወይም በ537 መጀመሪያ ላይ ሳይሆን አይቀርም።a ከዚያም ታማኝ ቀሪዎች ጊዜው ከማለፉ በፊት ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው መሠዊያውን የገነቡ ሲሆን በ537 ከክርስቶስ ልደት በፊት “በሰባተኛው ወር” (በቲሽሪ፣ ማለትም ከመስከረም እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ) የመጀመሪያዎቹን መሥዋዕቶች አቀረቡ። ይህም ናቡከደነፆር ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ባድማ ባደረጋቸው በ70 ዓመት በተመሳሳይ ወር ማለት ነው።—ዕዝራ 1:1-3፤ 3:1-6
4 ተመልሶ መቋቋም! ይህ የዕዝራ መጽሐፍ መቼት ነው። ጸሐፊው ከምዕራፍ 7 ቁጥር 27 እስከ ምዕራፍ 9 ድረስ ያለውን ታሪክ ሲዘግብ “እኔ” እያለ መናገሩ ይህን መጽሐፍ የጻፈው ዕዝራ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። ዕዝራ የሙሴ “ሕግ ፈጣን ጸሐፊ” የነበረ ከመሆኑም በላይ “የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ” የነበረ የእምነት ሰው በመሆኑ የዜና መዋዕልን መጻሕፍት እንደመዘገበ ሁሉ ይህንንም ታሪክ ለመመዝገብ ጥሩ ብቃት ነበረው። (ዕዝራ 7:6, 10 የ1954 ትርጉም) የዕዝራ መጽሐፍ የዜና መዋዕል መጻሕፍት ቀጣይ ክፍል እንደመሆኑ መጠን በተመሳሳይ ጊዜ ማለትም በ460 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ተጽፏል ተብሎ ይታመናል። መጽሐፉ የአይሁድ ብሔር በየቦታው ተበታትኖ ይገኝ ከነበረበትና ሕዝቡም “ሞት የተፈረደባቸው” እንደሆኑ ተደርገው ከተገለጹበት ጊዜ አንስቶ፣ የሁለተኛው ቤተ መቅደስ ግንባታ እንዲሁም ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሰ በኋላ ካህናቱን የማጥራቱ ሥራ እስከተጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ያሉትን የ70 ዓመታት ታሪክ ይሸፍናል።—ዕዝራ 1:1፤ 7:7፤ 10:17፤ መዝ. 102:20
5 ዕዝራ የሚለው የዕብራይስጥ ስም ትርጉሙ “እርዳታ” ማለት ነው። የዕዝራና የነህምያ መጻሕፍት መጀመሪያ ላይ አንድ ጥቅልል ነበሩ። (ነህ. 3:32፣ የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ከጊዜ በኋላ አይሁዳውያን ጥቅልሉን ለሁለት ከፈሉትና አንደኛና ሁለተኛ ዕዝራ ብለው ሰየሟቸው። በዕብራይስጥ ቋንቋ የተዘጋጁ ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱሶች ሁለቱን መጻሕፍት እንደ ሌሎች ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱሶች ዕዝራ እና ነህምያ ብለው ይጠሯቸዋል። ዕዝራ በአረማይክም ሆነ በዕብራይስጥ ቋንቋዎች የተካነ ስለነበር የመጽሐፉ የተወሰነ ክፍል (4:8 እስከ 6:18 እና 7:12-26) የተጻፈው በአረማይክ ሲሆን የተቀረው ደግሞ በዕብራይስጥ ነበር።
6 በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ምሑራን የዕዝራን መጽሐፍ ትክክለኛነት ይቀበላሉ። የዕዝራ መጽሐፍ ትክክለኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል መሆኑን በማስመልከት ደብልዩ ኤፍ ኦልብራይት ዚ ባይብል አፍተር ትዌንቲ ይርስ ኦቭ አርኪኦሎጂ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “በኤርምያስና በሕዝቅኤል እንዲሁም በዕዝራና በነህምያ መጻሕፍት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳይደረግ ተጠብቀው እንደቆዩ በማያሻማ መንገድ የሚያረጋግጡ የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎች አሉ። እነዚህ ማስረጃዎች በዘመኑ የነበረውን ታሪክና ታሪኩ የተፈጸመበትን ቅደም ተከተል ትክክለኛነት ያረጋግጣሉ።”
7 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች ከዕዝራ መጽሐፍ በቀጥታ ጠቅሰው የተናገሩት ሐሳብ ወይም የወሰዱት ጥቅስ ባይኖርም የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መሆኑ ግን ምንም አያጠያይቅም። መጽሐፉ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች እስከተሰበሰቡበት ጊዜ ድረስ ይሖዋ ከአይሁዳውያን ጋር ስለነበረው ግንኙነት ይተርካል። የአይሁዳውያን ወግ እንደሚገልጸው ይህንን የማሰባሰብ ሥራ በአብዛኛው ያከናወነው ዕዝራ ነው። ከዚህም በላይ የዕዝራ መጽሐፍ ተመልሶ ስለ መቋቋም የተነገሩት ትንቢቶች በሙሉ በትክክል መፈጸማቸውን የሚያረጋግጥ መሆኑ የተቀሩት መለኮታዊ ዘገባዎች ክፍል እንደሆነና ከእነርሱም ጋር ሙሉ በሙሉ እንደሚስማማ ማስረጃ ይሆናል። በተጨማሪም መጽሐፉ ንጹሑን አምልኮ ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ እንዲሁም የይሖዋ አምላክን ታላቅ ስም ያስቀድሳል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
14 በመጀመሪያ ደረጃ፣ የዕዝራ መጽሐፍ ይሖዋ የተናገራቸው ትንቢቶች ምንም ዝንፍ ሳይሉ በትክክል ፍጻሜ ማግኘታቸውን በማሳየት ረገድ ጠቀሜታ አለው። ኤርምያስ፣ ኢየሩሳሌም እንደምትጠፋ በትክክል እንደተነበየ ሁሉ ከ70 ዓመት በኋላ ተመልሳ እንደምትቋቋምም ተንብዮአል። (ኤር. 29:10) ይሖዋ ልክ ጊዜው ሲደርስ ታማኝ የሆኑት ቀሪ ሕዝቦቹን እውነተኛውን አምልኮ እንዲያካሂዱ ወደ ተስፋይቱ ምድር በመመለስ ፍቅራዊ ደግነቱን አሳይቷል።
15 ዳግም የተገነባው ቤተ መቅደስ የይሖዋ አምልኮ በሕዝቡ መካከል እንደገና ከፍ እንዲል አድርጓል። እንዲሁም ይሖዋ እውነተኛውን አምልኮ ለማራመድ ሲሉ ወደ እርሱ የሚመለሱትን ሰዎች አስደናቂ በሆነ መንገድ በምሕረቱ እንደባረካቸው ማስረጃ ይሆናል። የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ያህል ክብር የተላበሰ ባይሆንም እንኳ ከመለኮታዊ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ ዓላማውን ለማከናወን አገልግሏል። ይሄኛው ቤተ መቅደስ ሲገነባ ዕጹብ ድንቅ የግንባታ ዕቃዎች አልነበሩም። ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ የቃል ኪዳኑ ታቦት ይጎድል ስለነበር ውድ በሆኑ መንፈሳዊ ዕቃዎች ረገድም ከሰሎሞን ቤተ መቅደስ ያንሳል።b የዘሩባቤል ቤተ መቅደስ ሲመረቅ የነበረው ሥነ ሥርዓት በሰሎሞን ዘመን ለቤተ መቅደሱ ምረቃ ከተካሄደው ሥነ ሥርዓት ጋርም የሚወዳደር አይደለም። መሥዋዕት እንዲሆኑ የቀረቡት ከብቶችና በጎች ብዛት በሰሎሞን ቤተ መቅደስ ከቀረቡት መሥዋዕቶች አንድ በመቶ እንኳን አይሆኑም። በቀደመው ቤተ መቅደስ ላይ እንደታየው እንደ ደመና ያለ ክብር ቤተ መቅደሱን አልሞላውም፤ እንዲሁም የሚቃጠለውን መሥዋዕት የሚበላ እሳት ከይሖዋ ዘንድ አልወረደም። ይሁን እንጂ ሁለቱም ቤተ መቅደሶች የእውነተኛውን አምላክ የይሖዋን አምልኮ ከፍ ከፍ የማድረግ ታላቅ ዓላማ ፈጽመዋል።
16 ዘሩባቤል የገነባው ቤተ መቅደስ፣ ሙሴ የሠራው የማደሪያው ድንኳን እንዲሁም ሰሎሞን እና ሄሮድስ የገነቧቸው ቤተ መቅደሶች የተለያዩ ገጽታዎች ያሏቸው የአንድ ነገር አምሳያ ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ‘በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለችውን፣ እውነተኛ ድንኳን’ ያመለክታሉ። (ዕብ. 8:2) ይህ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በክርስቶስ የማስተሰርያ መሥዋዕት አማካኝነት ይሖዋን በማምለክ ወደ እርሱ ለመቅረብ የሚያስችል ዝግጅት ነው። (ዕብ. 9:2-10, 23) የይሖዋ ታላቅ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በክብር ከሁሉም የሚበልጥ ሲሆን በውበቱና በማራኪነቱም የሚወዳደረው የለም። ውበቱ ፈጽሞ የማይጠፋ ሲሆን ማንኛውም ዓይነት ሕንጻ አይተካከለውም።
17 የዕዝራ መጽሐፍ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ ትምህርት ይዟል። በመጽሐፉ ውስጥ የይሖዋ ሕዝቦች ለሥራው በፈቃዳቸው ስጦታ እንዳመጡ እናነባለን። (ዕዝራ 2:68፤ 2 ቆሮ. 9:7) ይሖዋ ለእርሱ ክብር የሚያመጡ ስብሰባዎች መቼም ቢሆን እንዳይቋረጡ እንደሚያደርግና ስብሰባዎቹን እንደሚባርክ መማራችን ማበረታቻ ይሰጠናል። (ዕዝራ 6:16, 22) ለይሖዋ አምልኮ የሙሉ ልብ ድጋፍ ለመስጠት ከቀሪዎቹ ጋር የተመለሱትን የናታኒሞችንና የሌሎች የባዕድ አገር አማኞችን ግሩም ምሳሌም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንመለከታለን። (2:43, 55) እንዲሁም ዓረማዊ ከሆኑ ጎረቤቶቻቸው ጋር ጋብቻ በመመሥረት የተሳሳተ ጎዳና የተከተሉት ሰዎች ምክር ሲሰጣቸው በትሕትና ንስሐ መግባታቸውን ተመልከት። (10:2-4) መጥፎ ወዳጅነት መለኮታዊ ሞገስ እንዲያጡ አድርጓቸዋል። (9:14, 15) ለሥራው ደስታ የሞላበት ቅንዓት ማሳየታቸው የእርሱን ሞገስና በረከት አስገኝቶላቸዋል።—6:14, 21, 22
18 በኢየሩሳሌም በይሖዋ ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ንጉሥ ባይኖርም እንኳ እስራኤላውያን ተመልሰው መቋቋማቸው ይሖዋ፣ እርሱ በወሰነው ጊዜ በዳዊት መሥመር የሚመጣውን ቃል የተገባለት ንጉሥ እንደሚያስነሳ በተስፋ እንዲጠባበቁ አድርጓቸዋል። ተመልሶ የተቋቋመው ብሔር መሲሑ የሚገለጥበት ጊዜ እስከሚደርስ ድረስ የአምላክን ቅዱስ ቃልና አምልኮውን መጠበቅ በሚያስችለው አቋም ላይ ይገኝ ነበር። እነዚህ ቀሪዎች እምነት ጎድሏቸው ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ባይሆኑ ኖሮ መሲሑ በእነማን መካከል ይገለጥ ነበር? በእርግጥም በዕዝራ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ዘገባዎች መሲሑና ንጉሡ ወደሚገለጥበት ጊዜ በሚያመራው ታሪክ ውስጥ ጉልህ ቦታ የሚሰጣቸው ክንውኖች ናቸው! መጽሐፉ በሙሉ በዛሬው ጊዜ ለምናደርገው ጥናት በጣም ጠቃሚ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 452-454, 458
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 1079