የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 16—ነህምያ
ጸሐፊው:- ነህምያ
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም
ተጽፎ ያለቀው:- ከክ.ል.በፊት ከ443 በኋላ
የሚሸፍነው ጊዜ:- ከክ.ል.በፊት ከ456 እስከ ከ443 በኋላ
“ያህ ያጽናናል” የሚል ትርጉም ባለው ስም የሚጠራው ነህምያ የፋርሱ ንጉሥ አርጤክስስ (ሎንጊማነስ) አይሁዳዊ አገልጋይ ሲሆን ሥራው ለንጉሡ ጠጅ ማቅረብ ነበር። ይህ ኃላፊነት እምነት ለሚጣልበት ሰው የሚሰጥ ከፍተኛ ቦታ ከመሆኑም በላይ ንጉሡ ደስተኛ በሆነበት ጊዜ የእርሱን ቸርነት ለማግኘት የሚያስችል አጋጣሚ ስለሚከፍት ብዙ ሰዎች የሚመኙት ሥራ ነው። ይሁን እንጂ ነህምያ ከምንም ነገር በላይ ኢየሩሳሌምን ‘የደስታቸው ቍንጮ’ አድርገው ከሚመለከቱ የታመኑ ግዞተኞች አንዱ ነበር። (መዝ. 137:5, 6) በነህምያ አእምሮ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ የያዘው ነገር ሥልጣን ወይም ቁሳዊ ሀብት ሳይሆን የይሖዋ አምልኮ ተመልሶ መቋቋም ነበር።
2 በ456 ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ “በሕይወት ተርፈው ከምርኮ” ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱት ጥቂት አይሁዳውያን የተደላደለ ኑሮ አልነበራቸውም። የነበሩበት ሁኔታ በጣም የሚያሳዝን ነበር። (ነህ. 1:3) የከተማዋ ቅጥር እንደፈራረሰ ሲሆን ሕዝቡም ዘወትር በማይተኙላቸው ጠላቶቻቸው ፊት መሳለቂያ ሆኖ ነበር። ነህምያ በሁኔታው በጣም አዝኗል። ይሁን እንጂ ይሖዋ የኢየሩሳሌምን ቅጥር በሚመለከት አንድ ነገር ለማድረግ የወሰነው ጊዜ ደርሷል። ጠላቶች ኖሩም አልኖሩ፣ በዙሪያዋ ያለውን የመከላከያ ቅጥር ጨምሮ ኢየሩሳሌም መገንባቷ የግድ ነበር። ይህ ክንውን ይሖዋ የመሲሑን መምጣት አስመልክቶ በነቢዩ ዳንኤል በኩል ከተናገረው ትንቢት ጋር በተያያዘ ጠቋሚ ዓመት ሆኖ ያገለግላል። (ዳን. 9:24-27) በዚህም ምክንያት ይሖዋ መለኮታዊውን ፈቃድ ለመፈጸም ታማኝና ቀናተኛ የነበረውን ነህምያን በመጠቀም ሁኔታዎቹን አቅጣጫ አስይዟል።
3 በስሙ የተጠራውን መጽሐፍ የጻፈው ነህምያ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። “የሐካልያ ልጅ የነህምያ ቃል” የሚሉት የመክፈቻ ቃላት እንዲሁም ጸሐፊው “እኔ” እያለ መጻፉ ይህንን በግልጽ የሚያረጋግጥ ነው። (ነህ. 1:1) መጀመሪያ ላይ የዕዝራና የነህምያ መጻሕፍት ዕዝራ በሚል ስም የሚጠሩ አንድ መጽሐፍ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ አይሁዳውያን መጽሐፉን አንደኛና ሁለተኛ ዕዝራ በማለት የከፈሉት ሲሆን ቆየት ብሎም ሁለተኛ ዕዝራ በመባል የሚታወቀው ክፍል ነህምያ ተብሎ ተጠራ። በዕዝራ መጽሐፍ መደምደሚያ ላይ እና በነህምያ መግቢያ ላይ በተገለጹት ክንውኖች መካከል የ12 ዓመት ገደማ ልዩነት አለ። የነህምያ መጽሐፍ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ456 መጨረሻ አንስቶ ከ443 በኋላ እስካለው ጊዜ ድረስ የተፈጸመውን ታሪክ ይሸፍናል።—1:1፤ 5:14፤ 13:6
4 የነህምያ መጽሐፍ ከቀሩት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ሙሉ በሙሉ ስለሚስማማ የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መሆኑ አያጠያይቅም። ስለ ሕጉ በተዘዋዋሪ መንገድ ያወሳባቸው በርካታ ቦታዎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከባዕድ አገር ሰዎች ጋር ትዳር መመሥረትን (ዘዳ. 7:3፤ ነህ. 10:30)፣ ብድርን (ዘሌ. 25:35-38፤ ዘዳ. 15:7-11፤ ነህ. 5:2-11) እንዲሁም የዳስ በዓልን (ዘዳ. 31:10-13፤ ነህ. 8:14-18) ስለመሳሰሉት ጉዳዮች የጠቀሳቸው ነጥቦች ይገኙበታል። ከዚህም በላይ መጽሐፉ ኢየሩሳሌም ተቃውሞ ባለበትና “በመከራ ጊዜ” እንደምትሠራ የሚገልጸው የዳንኤል ትንቢት ፍጻሜ ማግኘት የሚጀምርበትን ጊዜ ይጠቁማል።—ዳን. 9:25
5 ነህምያ የከተማዋን ቅጥር ለመገንባት ወደ ኢየሩሳሌም ስለተጓዘበት ዓመት ይኸውም ስለ 455 ከክርስቶስ ልደት በፊትስ ምን ማለት ይቻላል? ከግሪክ፣ ከፋርስ እና ከባቢሎን የተገኙ አስተማማኝ የታሪክ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አርጤክስስ ወደ ዙፋን የወጣው (accession year) በ475 ከክርስቶስ ልደት በፊት ሲሆን የግዛት ዘመኑ (regnal year) መቆጠር የጀምረው ደግሞ በ474 ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው።a በዚህ መሠረት 20ኛው የግዛት ዘመኑ 455 ከክርስቶስ ልደት በፊት ይሆናል ማለት ነው። ነህምያ 2:1-8 እንደሚጠቁመው የንጉሡ ጠጅ አሳላፊ የሆነው ነህምያ ኢየሩሳሌምን፣ ቅጥሯንና በሮቿን ለማደስና መልሶ ለመገንባት ከንጉሡ ፈቃድ ያገኘው በዚህ ዓመት የፀደይ ወቅት ማለትም በአይሁዳውያኑ አቆጣጠር በኒሳን ወር ነበር። የዳንኤል ትንቢት “ኢየሩሳሌምን ለማደስና ለመጠገን ዐዋጁ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ፣ ገዥው መሲሕ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ” 69 የዓመታት ሳምንታት ወይም 483 ዓመታት እንደሚያልፉ የተናገረ ሲሆን ኢየሱስ በ29 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ሲቀባ ይህ ትንቢት በአስገራሚ ሁኔታ ፍጻሜውን አግኝቷል። ይህ ዓመት ከዓለም የታሪክ ማስረጃዎችም ሆነ ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ጋር ይስማማል።b (ዳን. 9:24-27፤ ሉቃስ 3:1-3, 23) በእርግጥም የነህምያ መጽሐፍና የሉቃስ ወንጌል ይሖዋ አምላክ የእውነተኛ ትንቢት ምንጭና አስፈጻሚ መሆኑን በማሳየት ረገድ ከዳንኤል መጽሐፍ ጋር አስገራሚ በሆነ መንገድ የተሳሰሩ ናቸው! የነህምያ መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መሆኑ አጠያያቂ አይደለም።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
16 ነህምያ ያሳየው ለአምላክ የማደር ባሕርይ ትክክለኛውን አምልኮ ለሚወዱ ሁሉ ለሥራ የሚያንቀሳቅስ ኃይል ሊሆንላቸው ይገባል። ነህምያ በይሖዋ ሕዝብ መካከል የበላይ ተመልካች ሆኖ በትሕትና ለማገልገል ሲል የነበረውን ከፍተኛ ቦታ ትቷል። ከሕዝቡ አበል የመቀበል መብት የነበረው ቢሆንም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረም። ፍቅረ ነዋይ ወጥመድ እንደሆነ በመግለጽ በጥብቅ አውግዞታል። ነህምያ በመላው ብሔር ዘንድ የይሖዋን አምልኮ በቅንዓት የማካሄድና የመጠበቅ ዝንባሌ እንዲሰፍን ለማድረግ ጥሯል። (5:14, 15፤ 13:10-13) ነህምያ ፍጹም ከራስ ወዳድነት የራቀና ልባም፣ የተግባር ሰው እንዲሁም አደጋ ቢጋረጥበት እንኳ ጽድቅን ከመከተል ወደኋላ የማይል ሰው በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። (4:14, 19, 20፤ 6:3, 15) አምላካዊ ፍርሃት የነበረው ሰው ሲሆን አብረውት የሚያገለግሉትን ሰዎች እምነት ለመገንባትም ይጥር ነበር። (13:14፤ 8:9) ነህምያ የይሖዋን ሕግ፣ በተለይ ደግሞ ስለ እውነተኛው አምልኮ እንዲሁም ከአረማውያን ጋር ትዳር መመሥረትን የመሳሰሉ የባዕድ አገር ተጽዕኖዎች ስለማስወገድ የሚገልጸውን የሕጉን ክፍል በትጋት አስፈጽሟል።—13:8, 23-29
17 ነህምያ ስለ ይሖዋ ሕግ ሰፊ እውቀት እንደነበረውና ይህን እውቀቱንም ጥሩ አድርጎ እንደተጠቀመበት በመላው መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ማየት ይቻላል። ነህምያ፣ ይሖዋ በዘዳግም 30:1-4 ላይ በገባው ቃል መሠረት የሚጠይቀውን ነገር በታማኝነት እንደሚፈጽምለት ሙሉ እምነት በማሳደር የአምላክን በረከት ለምኗል። (ነህ. 1:8, 9) አይሁዳውያን ቀደም ባሉት ጊዜያት የተጻፉትን ነገሮች እንዲያውቋቸው ለማድረግ ሲል በርከት ያሉ ስብሰባዎችን አዘጋጅቷል። ነህምያና ዕዝራ የአምላክን ሕግ በሚያነቡበት ጊዜ ቃሉን ለሕዝቡ ግልጽ በማድረግና በተግባር በማዋል ረገድ ትጉዎች ነበሩ።—8:8, 13-16፤ 13:1-3
18 ነህምያ የነበረው በይሖዋ ሙሉ በሙሉ የመታመን ዝንባሌና በትሕትና ያቀረበው ልመና እኛም በተመሳሳይ በጸሎት አማካኝነት በአምላክ ላይ የመታመን ዝንባሌ እንድናዳብር ሊያበረታታን ይገባል። ባቀረበው ጸሎት ላይ አምላክን ከፍ ከፍ እንዳደረገ፣ የገዛ ሕዝቡን ኃጢአት መገንዘቡን በግልጽ እንዳሳየና የይሖዋ ስም እንዲቀደስ እንደተማጸነ ልብ በል። (1:4-11፤ 4:14፤ 6:14፤ 13:14, 29, 31) ሕዝቡ ነህምያ የሰጣቸውን ጥበብ ያዘለ መመሪያ ያለምንም ማንገራገር መቀበላቸውና ከእርሱ ጎን ተሰልፈው የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ደስታ ማግኘታቸው፣ ይህ ቀናተኛ የበላይ ተመልካች በአምላክ ሕዝብ መካከል የብርታት ምንጭ ሆኖ እንደነበር በግልጽ ያሳያል። በእርግጥም ሌሎችን ለሥራ የሚያንቀሳቅስ ግሩም ምሳሌ ነበር! ይሁን እንጂ ጥበበኛ የበላይ ተመልካች በሌለበት ጊዜ ፍቅረ ነዋይ፣ ሙስና እና ዓይን ያወጣ ክህደት ሰርጎ ለመግባት አፍታም አልፈጀም! በእርግጥም ይህ ታሪክ ዛሬ በአምላክ ሕዝብ መካከል ላሉት የበላይ ተመልካቾች በሙሉ መንጋውን በንቃትና በትጋት የመጠበቅን፣ የክርስቲያን ወንድሞቻቸውን ፍላጎት ለማሟላት ቅናት የማሳየትን እንዲሁም የሌሎችን ስሜት የመረዳትንና እነርሱን በእውነተኛው አምልኮ ጎዳና በመምራት በኩል ጥብቅ የመሆንን አስፈላጊነት ሊያስገነዝባቸው ይገባል።
19 ነህምያ በአምላክ ቃል ላይ ጠንካራ እምነት እንዳለው አሳይቷል። ቅዱሳን ጽሑፎችን በቅንዓት ከማስተማሩም በላይ ተመልሶ በተቋቋመው የአምላክ ሕዝብ መካከል በትውልድ የሚገኙ መንፈሳዊ ውርሻዎችን እንዲሁም የካህናቱንና የሌዋውያኑን አገልግሎት ለማጽናት ተጠቅሞባቸዋል። (ነህ. 1:8፤ 11:1 እስከ 12:26፤ ኢያሱ 14:1 እስከ 21:45) ይህ ለአይሁዳውያኑ ቀሪዎች ትልቅ ማበረታቻ እንደሆነላቸው አያጠራጥርም። ቀደም ሲል ዘሩን እንዲሁም በእርሱ መንግሥት አማካኝነት የሚመጣውን የላቀ ትርጉም ያለው ተሐድሶ በሚመለከት በተሰጠው ታላቅ ተስፋ ላይ ያላቸውን እምነት አጠናክሮላቸዋል። የይሖዋ አገልጋዮች ከአምላክ መንግሥት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማስቀደም በድፍረት እንዲጋደሉና በመላው ምድር ላይ እውነተኛውን አምልኮ በማስፋፋቱ ሥራ እንዲጠመዱ የሚያነሳሳቸው የአምላክ መንግሥት የያዘው የተሐድሶ ተስፋ ነው።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 613-616
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 899-901