የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 22—ማሕልየ መሓልይ
ጸሐፊው:- ሰሎሞን
የተጻፈበት ቦታ:- ኢየሩሳሌም
ተጽፎ ያለቀው:- 1020 ከክ.ል.በፊት ገደማ
“ለእስራኤል የተሰጠው ይህ ድንቅ መዝሙር በዓለም ላይ ለሚገኝ ለማንኛውም ሰው የተገባ አይደለም።” ለማሕልየ መሓልይ ያላቸውን አድናቆት ለመግለጽ ይህን የተናገሩት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ይኖሩ የነበሩት አይሁዳዊው ረቢ አኪባ ናቸው።a የመጽሐፉ መጠሪያ የተገኘው “ከመዝሙር ሁሉ የሚበልጥ የሰሎሞን መዝሙር” ከሚሉት የመጽሐፉ መክፈቻ ቃላት ነው። የዕብራይስጡ መጠሪያ ቃል በቃል ሲተረጎም “የመዝሙራት መዝሙር” ማለት ነው። ይህ ደግሞ ከሁሉ በላይ ያለውን ሰማይ እንደሚያመለክተው “ሰማየ ሰማያት” እንደሚለው ሐረግ ሁሉ መዝሙሩም የላቀ መሆኑን ያሳያል። (ዘዳ. 10:14) ማሕልየ መሓልይ የተለያዩ መዝሙራት ስብስብ ሳይሆን አንድ ወጥ መዝሙር ነው። “በዘመናት ሁሉ ከተጻፉት መዝሙሮች የሚበልጥ፣ ከፍተኛ የሆነ የጥራት ደረጃ ያለው መዝሙር” ተብሏል።b
2 በመጽሐፉ መግቢያ ላይ እንደተገለጸው የዚህ መዝሙር ጸሐፊ የኢየሩሳሌም ንጉሥ የነበረው ሰሎሞን ነው። ሰሎሞን የዕብራይስጥ ሥነ ግጥምን በተመለከተ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለውን ይህን እጅግ ውብ የሆነ መዝሙር ለመጻፍ ከፍተኛ ብቃት ነበረው። (1 ነገ. 4:32) ጥልቅ ትርጉም ያለውና ውበትን ግሩም አድርጎ የሚገልጽ በጣም አስደሳች ግጥም ነው። በተለይ አንባቢው ግጥሙ የተጻፈበትን የመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ በዓይነ ልቦናው መመልከት ከቻለ ይህን በይበልጥ ሊገነዘብ ይችላል። (ማሕ. 4:11, 13፤ 5:11፤ 7:4) ለመዝሙሩ መጻፍ ምክንያት የሆነው ሁኔታም ቢሆን ለየት ያለ ነበር። የሳባን ንግሥት እንኳ ሳይቀር ሊያስደንቅ የቻለ ከፍተኛ ጥበብ፣ ታላቅ ኃይል እንዲሁም ለማመን የሚያዳግት ቁሳዊ ብልጽግና የነበረው ታላቁ ንጉሥ ሰሎሞን በፍቅር የወደቀላትን ተራ የገጠር ልጃገረድ ግን ሊማርክ አልቻለም። ልጃገረዲቱ እረኛ ለሆነው ፍቅረኛዋ ታማኝ ስለነበረች ንጉሡ ሊያገኛት አልቻለም። በዚህም ምክንያት መጽሐፉ ያልተሳካው የሰሎሞን የፍቅር መዝሙር ተብሎ ቢጠራ ተገቢ ይሆናል። ይሖዋ አምላክ ከዚያ በኋላ በሚመጡት ዘመናት የሚኖሩ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ጥቅም እንዲያገኙበት ሲል ሰሎሞን ይህን መጽሐፍ እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል። ሰሎሞን መጽሐፉን የጻፈው በኢየሩሳሌም ሲሆን የተጻፈበት ጊዜም ቤተ መቅደሱ ተሠርቶ ካለቀ ጥቂት ዓመታት ቆየት ብሎ በ1020 ከክርስቶስ ልደት በፊት ገደማ ሳይሆን አይቀርም። ሰሎሞን ይህን መዝሙር በጻፈበት ወቅት “ሥልሳ ንግሥቶች፣ ሰማንያ ቁባቶች” የነበሩት ሲሆን በዘመነ መንግሥቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ “ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች” ነበሩት።—ማሕ. 6:8፤ 1 ነገ. 11:3
3 በጥንቶቹ ዘመናት ማሕልየ መሓልይ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለመሆኑ ምንም ዓይነት ጥያቄ ተነስቶ አያውቅም። ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ዘመን ከመጀመሩ ከበርካታ ዓመታት በፊት አንስቶ፣ ይህ መጽሐፍ በመንፈስ ከተጻፉት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተለይቶ አይታይም ነበር። በግሪክኛው የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ውስጥም ተካትቷል። ጆሴፈስ ባዘጋጀው የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ አስገብቶታል። ስለዚህ በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም መጽሐፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል መሆኑን ለማረጋገጥ የሚቀርቡትን ማስረጃዎች ለማሕልየ መሓልይ መጽሐፍም መጥቀስ ይቻላል።
4 ይሁን እንጂ አንዳንዶች በማሕልየ መሓልይ ውስጥ ስለ አምላክ የተጠቀሰ ነገር የለም በማለት መጽሐፉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ስለመሆኑ ጥያቄ አንስተዋል። “አምላክ” የሚለው ቃል በመጽሐፉ ውስጥ መጠቀሱ ብቻውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደማያደርገው ሁሉ አለመጠቀሱም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንዳይሆን አያግደውም። በምዕራፍ 8 ቁጥር 6 ላይ ፍቅር ስላለው ኃይል ሲገለጽ በበኩረ ጽሑፉ ውስጥ መለኮታዊው ስም በአጭር አጠራሩ “የያህ ነበልባል” በሚል ሐረግ ተጠቅሶ ይገኛል። ይህ መጽሐፍ ኢየሱስ “በእነርሱ የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ እየመሰላችሁ፣ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ” በማለት ከተናገረላቸውና በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ከነበራቸው መጻሕፍት አንዱ መሆኑ ፈጽሞ አያጠራጥርም። (ዮሐ. 5:39) ከዚህም በላይ በመንፈሳዊ ሁኔታ በክርስቶስና በእርሱ “ሙሽራ” መካከል ያለውን ዓይነት ከሁለት ወገን የሚመነጭ ታላቅ ፍቅር ግሩም አድርጎ የሚገልጽ መጽሐፍ መሆኑ ማሕልየ መሓልይን በመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ስብስብ ውስጥ ልዩ ቦታ ያሰጠዋል።—ራእይ 19:7, 8፤ 21:9
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
16 በዘመናችን የሚኖር አንድ የአምላክ ሰው ከዚህ የፍቅር መዝሙር ምን ትምህርት ሊያገኝ ይችላል? በመጽሐፉ ውስጥ ታማኝነት፣ ወዳጅን አለመክዳትና አምላካዊ ሥርዓቶችን መጠበቅ ጎላ ተደርገው ተገልጸዋል። መዝሙሩ አንድ እውነተኛ አፍቃሪ መልካም ምግባር ያለውና ልበ ንጹሕ መሆኑ ምን ያህል ማራኪ እንደሆነ ያስተምራል። እውነተኛ ፍቅር ሊወድቅ፣ ሊጠፋ ወይም በገንዘብ ሊደለል እንደማይችልም ይገልጻል። ወጣት ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች እንዲሁም ባሎችና ሚስቶች ፈተና በሚያጋጥማቸው ወይም ማታለያዎች በሚቀርቡላቸው ጊዜ ታማኝነትን ስለመጠበቅ ከሚገልጸው ከዚህ ምሳሌ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ።
17 ይህ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ መዝሙር ለመላው የክርስቲያን ጉባኤም በጣም ጠቃሚ ነው። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች፣ ማሕልየ መሓልይ በመንፈስ የተጻፉ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መሆኑን ተቀብለዋል። ከእነዚህ ክርስቲያኖች አንዱ “በጽናትና ቅዱሳት መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ እንዲኖረን፣ ቀደም ብሎ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል” ብሏል። (ሮሜ 15:4) በመንፈስ ተነሳስቶ ከላይ ያለውን የጻፈው ጳውሎስ “በእግዚአብሔር ቅናት እቀናላችኋለሁ፤ እናንተን እንደ ንጽሕት ድንግል ለክርስቶስ ለማቅረብ ለአንድ ባል አጭቻችኋለሁና” በማለት ለክርስቲያን ጉባኤ የጻፈው ሱላማጢሷ ልጃገረድ ለእረኛው የነበራትን ፍጹም ፍቅር አስቦ ሳይሆን አይቀርም። በተጨማሪም ጳውሎስ፣ ክርስቶስ ለጉባኤው ያለውን ፍቅር ባል ለሚስቱ ካለው ፍቅር ጋር አመሳስሎታል። (2 ቆሮ. 11:2፤ ኤፌ. 5:23-27) ኢየሱስ ክርስቶስ መልካም እረኛቸው ከመሆኑም በላይ ለቅቡዓን ተከታዮቹ በቃላት ሊገለጽ የማይችለውን በሰማያት ከእርሱ ጋር “ጋብቻ” የመመሥረት አስደሳች አጋጣሚ የዘረጋላቸው ንጉሣቸው ነው።—ራእይ 19:9 NW፤ ዮሐ. 10:11
18 እነዚህ ቅቡዓን የክርስቶስ ኢየሱስ ተከታዮች ከሱላማጢሷ ልጃገረድ ምሳሌ ብዙ ጥቅም እንደሚያገኙ የተረጋገጠ ነው። እነርሱም በዚህ ዓለም ብልጭልጭ ሀብት ሳይታለሉ ጽኑ ፍቅር በማሳየትና ሽልማታቸውን እስኪያገኙ ድረስ ሚዛናቸውን በመጠበቅ የጸና አቋም ይዘው መቀጠል ይኖርባቸዋል። ልባቸው በላይ ባሉት ነገሮች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ ‘ከሁሉ አስቀድመው የእግዚአብሔርን መንግሥት ይሻሉ።’ እረኛቸው ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅር ቃላት ሲያናግራቸው በታላቅ ደስታ ይሰሙታል። ይህ ወዳጃቸው በዓይን የማይታይ ቢሆንም ከጎናቸው ቆሞ ዓለምን እንዲያሸንፉ እንደሚያበረታታቸው ማወቃቸው በጣም ያስደስታቸዋል። ለንጉሡ እረኛቸው እንደ “ያህ ነበልባል” ኃይለኛ የሆነ የማይበርድ ፍቅር ስላላቸው ይህን ዓለም አሸንፈው ክብራማ የሆነውን የሰማይ መንግሥት በመውረስ ከእርሱ ጋር ይተባበራሉ። በዚህ መንገድ የያህ ስም ይቀደሳል!—ማቴ. 6:33፤ ዮሐ. 16:33
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዘ ጂዊሽ ሚሽና (ያዳይም 3:5)
b የክላርክ ኮሜንታሪ፣ ጥራዝ 3 ገጽ 841