የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 52—1 ተሰሎንቄ
ጸሐፊው:- ጳውሎስ
የተጻፈበት ቦታ:- ቆሮንቶስ
ተጽፎ ያለቀው:- በ50 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በመቄዶንያ የምትገኘውን የተሰሎንቄን ከተማ የጎበኘውና በዚያም የክርስቲያን ጉባኤ ያቋቋመው በ50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሁለተኛውን የስብከት ጉዞውን ሲያደርግ ነበር። ይህ በሆነ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ጳውሎስ ከስልዋኖስና (በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ከተጠቀሰው ከሲላስና) ከጢሞቴዎስ ጋር በቆሮንቶስ በነበረበት ወቅት የተሰሎንቄን ሰዎች ለማጽናናትና እምነታቸውን ለመገንባት ሲል የመጀመሪያ ደብዳቤውን ለመጻፍ ተነሳሳ። ይህ የሆነው በ50 ከክርስቶስ ልደት በኋላ መገባደጃ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ደብዳቤ ከጳውሎስ መልእክቶች መካከል የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል ለመሆን የበቃ የመጀመሪያው ጽሑፍ ከመሆኑም ሌላ ከማቴዎስ ወንጌል በቀር ከሌሎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ ቀድሞ የተጻፈ ይመስላል።
2 ደብዳቤው ትክክለኛና እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑን የሚደግፉ በርካታ ማስረጃዎች አሉ። ጳውሎስ፣ ስሙን በደብዳቤው ላይ በማስፈር ጸሐፊው እሱ መሆኑን የገለጸ ሲሆን መጽሐፉም በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ከሌላው የአምላክ ቃል ጋር ይስማማል። (1 ተሰ. 1:1፤ 2:18) መልእክቱ፣ የሙራቶሪያንን ቁርጥራጭ ጨምሮ በብዙዎቹ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ዝርዝር ውስጥ በስም ተጠቅሶ ይገኛል። የአንደኛ ተሰሎንቄን መጽሐፍ በስም የጠቀሰውን ኢራኒየስን (ሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ) ጨምሮ ብዙዎቹ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊዎች ከዚህ መጽሐፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጠቅሰው ጽፈዋል። በ200 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ እንደተጻፈ የሚታመነው የቼስተር ቢቲ ፓፒረስ ቁጥር 2 (P46) የአንደኛ ተሰሎንቄን መጽሐፍ የያዘ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በቤልጅየም ጌንት ከተማ የሚገኝና በሦስተኛው መቶ ዘመን የተጻፈ አንድ ሌላ ፓፒረስ (P30) ደግሞ የአንደኛና የሁለተኛ ተሰሎንቄ መጽሐፍትን ቁርጥራጮች ይዟል።a
3 ጳውሎስ ይህንን ደብዳቤ ከመጻፉ በፊት በተሰሎንቄ ጉባኤ የነበረውን ሁኔታ በአጭሩ መመልከታችን ሐዋርያው በዚህ ከተማ ይኖሩ ስለነበሩት ወንድሞች በጥልቅ ያሰበው ለምን እንደሆነ ለመገንዘብ ይረዳናል። ጉባኤው ገና ሲመሠረት ጀምሮ ከባድ ስደትና ተቃውሞ አጋጥሞት ነበር። ሉቃስ፣ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 17 ላይ ጳውሎስና ሲላስ ተሰሎንቄ እንደሄዱና “በዚያም የአይሁድ ምኩራብ” እንደነበረ ዘግቧል። እዚያም ጳውሎስ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ለሦስት ሰንበት ሰበከ፤ ጳውሎስ በተሰሎንቄ በሙያው ተሰማርቶ ለመሥራት ከሁሉም በላይ ደግሞ ጉባኤ ለመመሥረትና ለማደራጀት ችሎ ስለነበር ከሦስት ሰንበት የበለጠ እንደቆየ መመልከት ይቻላል።—ሥራ 17:1፤ 1 ተሰ. 2:9፤ 1:6, 7
4 በሐዋርያት ሥራ 17:4-7 ላይ የሚገኘው ዘገባ የሐዋርያው ጳውሎስ ስብከት በተሰሎንቄ ያስገኘውን ውጤት በዝርዝር ይገልጻል። አይሁዳውያን፣ ጳውሎስ በክርስቲያናዊ አገልግሎቱ ባገኘው ስኬት ስለቀኑ ሕዝቡን አሰባስበው ረብሻ በማስነሳት በከተማዋ ውስጥ ሁከት ፈጠሩ። ወደ ኢያሶን ቤት ገብተው በመረበሽ ኢያሶንንና ሌሎች ወንድሞችን ወደ ከተማው ባለ ሥልጣናት ጎትተው በመውሰድ እንዲህ እያሉ ጮኹ:- “እነዚህ ሰዎች ዓለሙን ሁሉ ሲያውኩ ቈይተው፣ አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል፤ ኢያሶንም በቤቱ ተቀብሎአቸዋል፤ እነዚህም ሁሉ፣ ‘ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ’ በማለት የቄሳርን ሕግ የሚጥሱ ናቸው።” ባለ ሥልጣናቱ፣ ኢያሶንንና ሌሎቹን ወንድሞች ዋስ እንዲጠሩ ካደረጉ በኋላ ለቀቋቸው። ጳውሎስና ሲላስ፣ በጉባኤ ውስጥ ላሉት ወንድሞችና ለራሳቸውም ደህንነት ሲባል በሌሊት ወደ ቤርያ ተላኩ። ያም ቢሆን በተሰሎንቄ ጉባኤ ማቋቋም ተችሏል።
5 የአይሁድ ከፍተኛ ተቃውሞ ጳውሎስን እስከ ቤርያ ተከትሎት የሄደ ሲሆን በዚያም የሚያከናውነውን የስብከት ሥራ ለማስቆም ጥረት ተደርጎ ነበር። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በግሪክ ወደምትገኘው አቴንስ አመራ። ያም ሆኖ ግን በመከራ ሥር ስለሚገኙት የተሰሎንቄ ወንድሞቹ ሁኔታ ለማወቅ ይመኝ ነበር። ሁለት ጊዜ ወደ ተሰሎንቄ ሊመለስ ቢሞክርም ‘ሰይጣን እንዳዘገየው’ ተናግሯል። (1 ተሰ. 2:17, 18) ጳውሎስ አዲስ የተቋቋመው ጉባኤ ሁኔታ ስላሳሰበውና እየደረሰባቸው ያለው መከራ ስላስጨነቀው፣ ወንድሞችን እንዲያጽናናቸው ብሎም በእምነት እንዲጸኑ እንዲረዳቸው ጢሞቴዎስን ወደ ተሰሎንቄ ላከው። ጢሞቴዎስ፣ የተሰሎንቄ ሰዎች ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም በታማኝነት አቋማቸውን ጠብቀው እንደጸኑ የሚገልጽ አስደሳች ዘገባ ይዞ ሲመለስ ጳውሎስ እጅግ ተደስቶ ነበር። በዚህ ጊዜ የእነሱ ጽናት በመቄዶንያና በአካይያ ለሚኖሩ አማኞች ሁሉ ምሳሌ ሆኖ ነበር። (1:6-8፤ 3:1-7) ጳውሎስ፣ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በታማኝነት በመጽናታቸው ይሖዋ አምላክን ቢያመሰግንም ወደ ጉልምስና ማደጋቸውን እንዲቀጥሉ ተጨማሪ መመሪያና ምክር እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝቦ ነበር። በመሆኑም ከጢሞቴዎስና ከስልዋኖስ ጋር በቆሮንቶስ በነበረበት ጊዜ ለተሰሎንቄ ሰዎች የመጀመሪያ ደብዳቤውን ጻፈ።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
13 ጳውሎስ በዚህ ደብዳቤ ላይ ለወንድሞቹ ፍቅርና አሳቢነት አሳይቷል። እሱም ሆነ የእምነት ባልንጀሮቹ በተሰሎንቄ ለሚገኙት ውድ ወንድሞች የአምላክን ወንጌል ብቻ ሳይሆን ሕይወታቸውን ጭምር ለማካፈል ፈቃደኛ በመሆን በፍቅር ረገድ የላቀ ምሳሌ ትተዋል። ሁሉም የበላይ ተመልካቾች ለጉባኤዎቻቸው እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ሊኖራቸው ይገባል! ይህን የመሰለው የፍቅር መግለጫ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ እርስ በርስ ፍቅር እንዲኖራቸው ያነሳሳል፤ ጳውሎስ “እኛ ለእናንተ ፍቅር እንዳለን ሁሉ እርስ በርስ ያላችሁን ፍቅርና ለሌሎችም ያላችሁን ፍቅር ጌታ ያብዛላችሁ፤ ያትረፍርፍላችሁም” ሲል ተናግሯል። በሁሉም የአምላክ ሕዝቦች ዘንድ በፈቃደኝነት የሚገለጸው እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በጣም ያንጻል። ‘ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቅዱሳኑ ሁሉ ጋር በሚመጣበት ጊዜ በአምላካችንና በአባታችን ፊት ነቀፋ የሌለብንና ቅዱሳን ሆነን እንድንገኝ ልባችንን ያጸናል።’ ይህ ዓይነቱ ፍቅር ክርስቲያኖች ምግባረ ብልሹ ከሆነውና ሥነ ምግባር ከጎደለው ዓለም በመለየት በቅድስናና በክብር እንዲመላለሱና በዚህም አምላክን እንዲያስደስቱ ይረዳቸዋል።—3:12, 13፤ 2:8፤ 4:1-8
14 ይህ ደብዳቤ፣ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በዘዴና በፍቅር ምክር መስጠት የሚቻልበትን መንገድ የሚጠቁም ግሩም ምሳሌ ይዟል። የተሰሎንቄ ወንድሞች ቀናተኛና ታማኝ ቢሆኑም ማስተካከል የሚገባቸው ነገሮች ነበሩ። ይሁን እንጂ ጳውሎስ በእያንዳንዱ ምክር ላይ መልካም ጎኖቻቸውን እያነሳ ወንድሞችን አመስግኗቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ስለ ሥነ ምግባር ርኩሰት ሲያስጠነቅቅ በመጀመሪያ አምላክን በሚያስደስት መንገድ እየተመላለሱ በመሆናቸው ካመሰገናቸው በኋላ እያንዳንዱ የገዛ ሰውነቱን በቅድስናና በክብር እንዲይዝ እንዲሁም በዚህ አካሄዳቸው “በበለጠ ሁኔታ” እንዲገፉበት አሳስቧል። ከዚያም በመካከላቸው ስላለው የወንድማማች መዋደድ ካመሰገናቸው በኋላ “ከዚህ በበለጠ” ይህን ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ መክሯቸዋል፤ እንዲሁም በራሳቸው ጉዳይ ላይ ብቻ እንዲያተኩሩና በውጭ ባሉት ዘንድ በሚያስከብር መንገድ እንዲመላለሱ አሳስቧቸዋል። ጳውሎስ፣ ወንድሞቹ ‘እርስ በርሳቸውም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሁልጊዜ መልካም የሆነውን ነገር ለማድረግ እንዲጣጣሩ’ በዘዴ ነግሯቸዋል።—4:1-7, 9-12፤ 5:15
15 ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ‘መምጣት’ ወይም መገኘት አራት ጊዜ ጠቅሷል። በተሰሎንቄ የሚገኙት አዲስ ክርስቲያኖች ይህ ትምህርት ትኩረታቸውን ሳይስበው አልቀረም። በጳውሎስና በተባባሪዎቹ ላይ የቀረበው “እነዚህም ሁሉ፣ ‘ኢየሱስ የሚባል ሌላ ንጉሥ አለ’ በማለት የቄሳርን ሕግ የሚጥሱ ናቸው” የሚለው ክስ እንደሚያመለክተው ጳውሎስ በተሰሎንቄ በነበረበት ወቅት በክርስቶስ ስለሚመራው የአምላክ መንግሥት በድፍረት ሰብኳል። (ሥራ 17:7፤ 1 ተሰ. 2:19፤ 3:13፤ 4:15፤ 5:23) የተሰሎንቄ ወንድሞች የአምላክን መንግሥት ተስፋ ያደርጉና በይሖዋ ያምኑ የነበረ ሲሆን አምላክ ‘ከሙታን ያስነሣውና ከሰማይ የሚመጣው ልጁ ኢየሱስ’ ከመጪው ቁጣ እንደሚያድናቸው ይጠባበቁ ነበር። ዛሬም በተመሳሳይ የአምላክን መንግሥት ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ ፍቅራቸው እንዲበዛ እንዲሁም ጽኑ ልብ እንዲኖራቸው ብሎም ነቀፋ የሌለባቸው ሆነው እንዲገኙ የሚያበረታታውን በአንደኛ ተሰሎንቄ ላይ የተሰጠውን መልካም ምክር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋቸዋል፤ እንዲህ ካደረጉ ‘ወደ መንግሥቱና ወደ ክብሩ ለጠራቸው ለእግዚአብሔር እንደሚገባ መኖር’ ይችላሉ።—1 ተሰ. 1:8, 10፤ 3:12, 13፤ 2:12
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በኩርት እና ባርባራ አላንድ ተዘጋጅቶ በኢ ኤፍ ሮድስ በ1987 የተተረጎመው ዘ ቴክስት ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ ገጽ 97, 99