የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 57—ፊልሞና
ጸሐፊው:- ጳውሎስ
የተጻፈበት ቦታ:- ሮም
ተጽፎ ያለቀው:- ከ60–61 ከክ.ል.በኋላ ገደማ
ፍቅራዊ ስሜት የተንጸባረቀበትና በጥበብ የተጻፈው ይህ የጳውሎስ ደብዳቤ በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖችን ትኩረት በእጅጉ የሚስብ ነው። “የአሕዛብ ሐዋርያ” የሆነው ጳውሎስ ከጻፋቸውና እስከ ዛሬ ድረስ ተጠብቀው ከቆዩት መልእክቶች ሁሉ አነስተኛው መልእክት ፊልሞና ሲሆን ከአጠቃላዩ መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን ከሁለተኛና ከሦስተኛ ዮሐንስ በስተቀር ከሌሎቹ መጻሕፍት ያነሰ ነው። በተጨማሪም ይህ መልእክት፣ ጳውሎስ ለአንድ ጉባኤ ወይም በኃላፊነት ላይ ለሚገኝ የበላይ ተመልካች ሳይሆን ለአንድ ግለሰብ የጻፈው ብቸኛው “የግል” ደብዳቤ ነው፤ የሚያወሳውም ጳውሎስ የትንሿ እስያ እምብርት በሆነችው ቈላስይስ የተባለች የፍርግያ ከተማ ውስጥ ከሚኖረው ፊልሞና የተባለ ባለጠጋ ክርስቲያን ወንድሙ ጋር ሊወያይ ስለፈለገው ልዩ ጉዳይ ብቻ ነው።—ሮሜ 11:13
2 የደብዳቤው ዓላማ በግልጽ ተቀምጧል፤ ጳውሎስ በሮም ለመጀመሪያ ጊዜ ታስሮ በነበረበት ወቅት (59-61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ) የአምላክን መንግሥት ለመስበክ ነፃነት ነበረው። ለስብከቱ ጥሩ ምላሽ ከሰጡት መካከል ከጳውሎስ ወዳጅ ከፊልሞና ቤት የኮበለለ አናሲሞስ የተባለ ባሪያ ይገኝበት ነበር። በኋላ ላይ አናሲሞስ ክርስቲያን ሆነ፤ ስለዚህ ጳውሎስ፣ አናሲሞስ ወደ ፊልሞና ለመመለስ ፈቃደኛ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ሊልከው ወሰነ። ጳውሎስ በኤፌሶንና በቈላስይስ ለሚገኙት ጉባኤዎችም ደብዳቤ የጻፈው በዚህ ወቅት ነበር። ይህ ሐዋርያ በእነዚህ በሁለቱም ደብዳቤዎች ላይ ክርስቲያን የሆኑ ባሪያዎችና ጌቶች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ረገድ ተገቢ የሆነው አካሄድ ምን እንደሆነ የሚጠቁም ጥሩ ምክር ለግሷል። (ኤፌ. 6:5-9፤ ቈላ. 3:22 እስከ 4:1) ከሁሉም በላይ ግን ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ የጻፈው አናሲሞስን እንዲቀበለው ፊልሞናን ለመለመን ሲል ነበር። ጳውሎስ ደብዳቤዎቹን ራሱ የመጻፍ ልማድ ባይኖረውም ይህን ደብዳቤ ግን የጻፈው በገዛ እጆቹ ነበር። (ፊል. 19) ደብዳቤውን ራሱ መጻፉ ላቀረበው ምልጃ ክብደት ጨምሮለታል።
3 ጳውሎስ፣ በሮም አማኞችን ያገኘው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ሰብኮ ስለሚሆን ደብዳቤው የተጻፈው ከ60-61 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሳይሆን አይቀርም። በተጨማሪም በቁጥር 22 ላይ የመፈታት ተስፋ እንዳለው መግለጹ ደብዳቤው የተጻፈው በእስር ላይ የተወሰነ ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ይሆናል ብለን እንድንደመድም ያደርገናል። ለፊልሞና እንዲሁም በኤፌሶንና በቈላስይስ ለሚገኙት ጉባኤዎች የተጻፉት እነዚህ ሦስት ደብዳቤዎች የተላኩት በቲኪቆስና በአናሲሞስ አማካኝነት ይመስላል።—ኤፌ. 6:21, 22፤ ቈላ. 4:7-9
4 የፊልሞና መልእክት የመጀመሪያ ቁጥር ላይ የጳውሎስ ስም መጠቀሱ ደብዳቤውን የጻፈው እሱ መሆኑን ያረጋግጥልናል። ኦሪጀንና ተርቱሊያንም የፊልሞናን ደብዳቤ ጳውሎስ እንደጻፈው አምነው ተቀብለዋል።a መጽሐፉ በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በተዘጋጀው የሙራቶሪ ቁርጥራጭ ውስጥ ከሌሎች የጳውሎስ መልእክቶች ጋር መጠቀሱ ትክክለኛነቱን ያረጋግጣል።
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
7 ከዚህ ደብዳቤ መመልከት እንደሚቻለው ጳውሎስ “ማኅበራዊ ወንጌል” በመስበክ በጊዜው የነበረውን ሥርዓትና እንደ ባርነት ያሉ ልማዶችን ለማስወገድ እየሞከረ አልነበረም። ክርስቲያን የሆኑ ባሮችን እንኳ በራሱ ፈቃድ ነፃ እንዲወጡ አላደረገም፤ ከዚህ ይልቅ ኮብላዩ ባሪያ አናሲሞስ፣ ከሮም እስከ ቈላስይስ ያለውን ከ1,400 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዞ ወደ ጌታው ወደ ፊልሞና እንዲመለስ ልኮታል። ስለዚህ ጳውሎስ፣ ስለ ‘እግዚአብሔር መንግሥት እንዲሰብክና ስለ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያስተምር’ ይሖዋ በሰጠው ተልእኮ ላይ በማተኮር በሌሎች ጉዳዮች ውስጥ ሳይገባ ሐዋርያ እንደመሆኑ መጠን የተሰጠውን ታላቅ ሥራ አከናውኗል።—ሥራ 28:31፤ ፊል. 8, 9
8 ለፊልሞና የተላከው ደብዳቤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ክርስቲያኖች መካከል የነበረውን ፍቅርና አንድነት የሚያሳይ በመሆኑ ደብዳቤው ግንዛቤን የሚያሰፋ ነው። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች አንዳቸው ሌላውን ‘ወንድም’ እና ‘እህት’ እያሉ ይጠሩ እንደነበር ከደብዳቤው መመልከት እንችላለን። (ፊል. 2, 20) ከዚህም በተጨማሪ በክርስቲያን ወንድሞች መካከል ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ግልጽ ያደርጋል። ጳውሎስ ለወንድሞች ያለውን ፍቅር፣ ለሰብዓዊ ግንኙነቶችና ለሌሎች ንብረት ያለውን አክብሮት፣ የተጠቀመበትን ውጤታማ ዘዴ እንዲሁም ያሳየውን በምሳሌነት የሚጠቀስ ትሕትና እንመለከታለን። ጳውሎስ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ያለው የበላይ ተመልካች እንደመሆኑ መጠን ባለው ሥልጣን በመጠቀም ፊልሞና አናሲሞስን ይቅር እንዲለው ለማስገደድ ከመሞከር ይልቅ ክርስቲያናዊ ፍቅርንና በሁለቱ መካከል ያለውን የግል ወዳጅነት መሠረት በማድረግ በትሕትና ለምኖታል። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የበላይ ተመልካቾች፣ ጳውሎስ በዘዴ ለፊልሞና ሐሳብ ካቀረበበት መንገድ ጠቃሚ ትምህርት ሊያገኙ ይችላሉ።
9 ጳውሎስ ያቀረበውን ጥያቄ ፊልሞና እንደሚቀበለው ይጠብቅ እንደነበረ ግልጽ ነው፤ ፊልሞናም እንዲህ ማድረጉ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:14 ላይ እንዲሁም ጳውሎስ በኤፌሶን 4:32 ላይ የሰጡትን ትምህርት ተግባራዊ ማድረጉን የሚያሳይ ይሆናል። በተመሳሳይም ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች አንድ ወንድም ሲያስቀይማቸው ደግና ይቅር ባይ እንዲሆኑ ሊጠበቅባቸው ይችላል። ፊልሞና፣ ባሪያው የሆነውንና ያሻውን ሊያደርግበት ሕጋዊ ፈቃድ የነበረውን ሰው ይቅር ካለ ዛሬ ክርስቲያኖች ያስቀየማቸውን ወንድም ይቅር ለማለት ዝግጁ መሆን አለባቸው፤ ፊልሞና ካደረገው ነገር ጋር ሲወዳደር እንዲህ ማድረግ ብዙም የሚያስቸግር አይደለም።
10 ለፊልሞና የተላከው ይህ ደብዳቤ የይሖዋ መንፈስ እንዳለበት በግልጽ ማየት ይቻላል። ጳውሎስ ስሜትን በቀላሉ ሊጎዳ የሚችልን ችግር ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ መፍታቱ የአምላክን መንፈስ አሠራር በግልጽ አሳይቷል። እንዲሁም ጳውሎስ ያሳየው ወዳጃዊ ስሜትና ጥልቅ ፍቅር እንዲሁም በእምነት ባልንጀሮቹ ላይ መታመኑም ይህንን ያሳያል። ለፊልሞና የተላከው ደብዳቤ እንደ ሌሎቹ ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን የሚያስተምር፣ ክርስቲያናዊ አንድነትን የሚያበረታታ እንዲሁም የአምላክን መንግሥት ተስፋ በሚያደርጉትና የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነት በአኗኗራቸው በሚንጸባረቀው ‘በቅዱሳኑ’ መካከል በሰፊው የሚታየውን ፍቅርና እምነት የሚያጎላ መሆኑ ደብዳቤው በአምላክ መንፈስ መጻፉን የሚያረጋግጥ ነው።—ቁ. 5
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ፣ በጂ ደብልዩ ብሮሚሊ በ1986 የተዘጋጀ ጥራዝ 3 ገጽ 831