የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • bt ምዕ. 4 ገጽ 28-35
  • “ያልተማሩና ተራ ሰዎች”

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • “ያልተማሩና ተራ ሰዎች”
  • ‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • “በእኛ ኃይል” አይደለም (የሐዋርያት ሥራ 3:11-26)
  • “ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም” (የሐዋርያት ሥራ 4:1-22)
  • “ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ . . . ወደ አምላክ ጸለዩ” (የሐዋርያት ሥራ 4:23-31)
  • ‘በሰው ሳይሆን በአምላክ’ ፊት ተጠያቂዎች (የሐዋርያት ሥራ 4:32 እስከ 5:11)
  • ይቅር ባይነትን ከጌታው ተምሯል
    በእምነታቸው ምሰሏቸው
  • ይቅር ባይነትን ከጌታው ተምሯል
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • ፍርሃትንና ጥርጣሬን ለማሸነፍ ታግሏል
    በእምነታቸው ምሰሏቸው
  • ፈተናዎች ቢደርሱበትም ታማኝ መሆኑን አሳይቷል
    በእምነታቸው ምሰሏቸው
ለተጨማሪ መረጃ
‘ስለ አምላክ መንግሥት በሚገባ መመሥከር’
bt ምዕ. 4 ገጽ 28-35

ምዕራፍ 4

“ያልተማሩና ተራ ሰዎች”

ሐዋርያቱ ድፍረት የተሞላበት እርምጃ ወሰዱ፤ ይሖዋም ባረካቸው

በሐዋርያት ሥራ 3:1 እስከ 5:11 ላይ የተመሠረተ

1, 2. ጴጥሮስና ዮሐንስ በቤተ መቅደሱ በር አቅራቢያ ምን ተአምር ፈጸሙ?

ፀሐይዋ ማዘቅዘቅ ጀምራለች፤ ሕዝቡ ወዲያ ወዲህ ይተራመሳል። ቀናተኛ የሆኑ አይሁዳውያንና የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ወደ ቤተ መቅደሱ ግቢ እየተመሙ ነው። ‘የጸሎት ሰዓት’ ተቃርቧል።a (ሥራ 2:46፤ 3:1) በሕዝቡ መካከል የነበሩት ጴጥሮስና ዮሐንስ “ውብ” ተብሎ ወደሚጠራው የቤተ መቅደሱ በር አመሩ። ከሕዝቡ ጫጫታና ከሰዎቹ ኮቴ በላይ ጎላ ብሎ የሚሰማ የልመና ድምፅ አለ፤ ለማኙ፣ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ሽባ የሆነ በመካከለኛ ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው ነው።—ሥራ 3:2፤ 4:22

2 ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደሚለምነው ሰው ሲቃረቡ ሰውየው እንደ ልማዱ ገንዘብ ለመናቸው። ሐዋርያቱ ቆም ብለው ሲያዩት፣ ሰውየው አንድ ነገር ሊሰጡት እንደሆነ ተስፋ በማድረግ በጉጉት ይመለከታቸው ጀመር። ጴጥሮስም “እኔ ብርና ወርቅ የለኝም፤ ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ። በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነስና ተራመድ!” አለው። ጴጥሮስ ሽባ የሆነውን ሰው እጁን ይዞ አስነሳው፤ ሰውየው በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥ ብሎ ቆመ! በአካባቢው የነበሩት ሰዎች ይህን ሲመለከቱ ምን ያህል ተደንቀው ሊሆን እንደሚችል አስብ! (ሥራ 3:6, 7) ሰውየው የተፈወሱትን እግሮቹን በግርምት ሲያይና ፈራ ተባ እያለ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲራመድ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ይህ ሰው በደስታ መዝለሉና ከፍ ባለ ድምፅ አምላክን ማመስገኑ አያስገርምም!

3. ሽባ የነበረው ሰውም ሆነ በዚያ ተሰብስበው የነበሩት ሰዎች ምን የላቀ ስጦታ የማግኘት አጋጣሚ ተከፍቶላቸው ነበር?

3 በደስታ የተዋጡት ሰዎች ጴጥሮስና ዮሐንስ ወዳሉበት የሰለሞን መተላለፊያ ወደሚባለው ስፍራ ግር ብለው እየሮጡ መጡ። ጴጥሮስም በአንድ ወቅት ኢየሱስ ቆሞ ሲያስተምርበት በነበረው በዚሁ ቦታ ሆኖ አሁን የተፈጸመው ነገር ምን ትርጉም እንዳለው ያብራራላቸው ጀመር። (ዮሐ. 10:23) በዚያ ለተሰበሰቡት ሰዎችም ሆነ ሽባ ለነበረው ሰው ከብር ወይም ከወርቅ የላቀ ዋጋ ያለው ስጦታ አቀረበላቸው። ይህ ስጦታ ከበሽታ ከመፈወስም የሚበልጥ ነገር ነው። ንስሐ እንዲገቡና ኃጢአታቸው እንዲደመሰስ አጋጣሚ የሚከፍት ነው፤ አልፎ ተርፎም ይሖዋ ‘የሕይወት ዋና ወኪል’ አድርጎ የሾመው የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች መሆን የሚችሉበት አጋጣሚ ያገኛሉ።—ሥራ 3:15

4. (ሀ) ሽባው ሰው በተአምር መፈወሱን ያዩ ባለሥልጣናት ምን ለማድረግ ሞክረዋል? (ለ) ለየትኞቹ ሁለት ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?

4 ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ቀን ነው! አንድ ሰው ካለበት አካላዊ ችግር ተፈውሶ እንደ ልቡ መራመድ ችሏል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ በማገልገል በምሳሌያዊ ሁኔታ ከእሱ ጋር መራመድ እንዲችሉ መንፈሳዊ ፈውስ የሚያገኙበት አጋጣሚ ተሰጣቸው። (ቆላ. 1:9, 10) በሌላ በኩል ግን በዚያ ቀን የተከናወኑት ነገሮች፣ ታማኞቹ የክርስቶስ ተከታዮች የባለሥልጣናቱ ዓይን ውስጥ እንዲገቡ አድርገዋል፤ እነዚህ ባለሥልጣናት፣ ኢየሱስ የመንግሥቱ ምሥራች እንዲሰበክ የሰጠው ትእዛዝ እንዳይፈጸም ለማገድ መሞከራቸው አልቀረም። (ሥራ 1:8) ታዲያ “ያልተማሩና ተራ ሰዎች” የሆኑት ጴጥሮስና ዮሐንስ ለሕዝቡ በመሠከሩበት ጊዜ ከተጠቀሙበት ዘዴና ካሳዩት ባሕርይ ምን እንማራለን?b (ሥራ 4:13) እነሱም ሆኑ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ለተቃውሞ ምላሽ የሰጡበትን መንገድ መኮረጅ የምንችለውስ እንዴት ነው?

“በእኛ ኃይል” አይደለም (የሐዋርያት ሥራ 3:11-26)

5. ጴጥሮስ ሕዝቡን ካነጋገረበት መንገድ ምን እንማራለን?

5 ጴጥሮስና ዮሐንስ በሕዝቡ ፊት ቆሙ፤ በዚያ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ከጥቂት ጊዜ በፊት ኢየሱስ እንዲሰቀል ሲጮኹ የነበሩ መሆናቸውን ያውቃሉ። (ማር. 15:8-15፤ ሥራ 3:13-15) ጴጥሮስ ሽባው ሰው የተፈወሰው በኢየሱስ ስም መሆኑን በግልጽ ሲናገር ምን ያህል ድፍረት ጠይቆበት እንደሚሆን ገምት። ጴጥሮስ እውነቱን አለዝቦ ለማቅረብ አልሞከረም። ሕዝቡ ለክርስቶስ ሞት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተጠያቂ መሆኑን ፊት ለፊት ተናግሯል። ያም ሆኖ ሕዝቡ ይህን ያደረገው “ባለማወቅ” ስለነበር ጴጥሮስ ለእነሱ ጥላቻ አላደረበትም። (ሥራ 3:17) እንዲያውም ያነጋገራቸው “ወንድሞች” እያለ ነው፤ ትኩረት ያደረገውም አዎንታዊ በሆነው የመንግሥቱ መልእክት ገጽታ ላይ ነው። ንስሐ ከገቡና በክርስቶስ ካመኑ ከይሖዋ ዘንድ “የመታደስ ዘመን” ይመጣላቸዋል። (ሥራ 3:19) እኛም በተመሳሳይ ስለመጪው የአምላክ ፍርድ በምናውጅበት ጊዜ ደፋሮች መሆንና እውነታውን በግልጽ መናገር ይኖርብናል። ይህ ሲባል ግን በኃይለ ቃል እንናገራለን ወይም ሌሎችን እንኮንናለን ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የምንሰብክላቸውን ሰዎች የወደፊት ወንድሞቻችን አድርገን እንመለከታቸዋለን፤ ደግሞም ልክ እንደ ጴጥሮስ አዎንታዊ በሆነው የመንግሥቱ መልእክት ገጽታ ላይ ይበልጥ ትኩረት እናደርጋለን።

6. ጴጥሮስና ዮሐንስ ትሕትና ያሳዩት እንዴት ነው?

6 ሐዋርያቱ ትሑቶች ነበሩ። የፈጸሙትን ተአምር በራሳቸው ኃይል እንዳከናወኑት አድርገው አልተናገሩም። ጴጥሮስ በዚያ የተሰበሰቡትን ሰዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “በእኛ ኃይል ወይም እኛ ለአምላክ ያደርን በመሆናችን የተነሳ ይህን ሰው እንዲራመድ ያስቻልነው ይመስል ለምን ትኩር ብላችሁ ታዩናላችሁ?” (ሥራ 3:12) ጴጥሮስም ሆነ ሌሎቹ ሐዋርያት በአገልግሎታቸው ያገኙት ማንኛውም መልካም ውጤት በአምላክ እንጂ በራሳቸው ኃይል የተገኘ እንዳልሆነ ያውቁ ነበር። በመሆኑም ላገኙት ስኬት መወደስ ያለባቸው ይሖዋና ኢየሱስ መሆናቸውን በመግለጽ ትሕትናቸውን አስመሥክረዋል።

7, 8. (ሀ) ለሰዎች ምን ስጦታ ልንሰጥ እንችላለን? (ለ) “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት” ዘመን እንደሚመጣ የተሰጠው ተስፋ በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

7 እኛም በስብከቱ ሥራ በምንካፈልበት ጊዜ ትሑቶች መሆን አለብን። የአምላክ መንፈስ፣ ዛሬ ላሉት ክርስቲያኖች ተአምራዊ ፈውስ የመፈጸም ኃይል እንደማይሰጣቸው የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ሰዎች በአምላክና በክርስቶስ ላይ እምነት እንዲኖራቸው እንዲሁም ጴጥሮስ ለሕዝቡ ያቀረበውን ዓይነት ስጦታ እንዲያገኙ የመርዳት መብት አለን፤ ይህ ስጦታ የኃጢአት ይቅርታና ከይሖዋ ዘንድ የሚመጣውን መታደስ ያስገኝላቸዋል። በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ግብዣችንን በመቀበል ተጠምቀው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ይሆናሉ።

8 በእርግጥም የምንኖረው ጴጥሮስ “ነገሮች ሁሉ የሚታደሱበት” ብሎ በገለጸው ዘመን ነው። “አምላክ በጥንቶቹ ቅዱሳን ነቢያቱ አፍ” በተናገረው ቃል ፍጻሜ መሠረት በ1914 መንግሥቱ በሰማይ ተቋቁሟል። (ሥራ 3:21፤ መዝ. 110:1-3፤ ዳን. 4:16, 17) ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ክርስቶስ በምድር ላይ የሚከናወነውን መንፈሳዊ የተሃድሶ ሥራ በበላይነት መከታተል ጀምሯል። በመሆኑም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች በመሆን ወደ መንፈሳዊው ገነት መግባት ችለዋል። እነዚህ ሰዎች፣ እየተበላሸ የሚሄደውን አሮጌውን ስብዕና አውልቀው በመጣል “እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውን . . . አዲሱን ስብዕና” ለብሰዋል። (ኤፌ. 4:22-24) ሽባ የሆነው ለማኝ በተፈወሰበት ጊዜ እንደሆነው ሁሉ ይህ አስደናቂ ሥራም ሊሳካ የቻለው በሰው ጥረት ሳይሆን በአምላክ መንፈስ ነው። እኛም እንደ ጴጥሮስ ሌሎችን ስናስተምር የአምላክን ቃል በድፍረትና ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም ይኖርብናል። ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ በመርዳት ረገድ ስኬታማ የምንሆነው በራሳችን ሳይሆን በአምላክ ኃይል ነው።

“ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም” (የሐዋርያት ሥራ 4:1-22)

9-11. (ሀ) የአይሁድ መሪዎች ጴጥሮስና ዮሐንስ የተናገሩትን መልእክት ሲሰሙ ምን አደረጉ? (ለ) የሐዋርያቱ ቁርጥ አቋም ምን ነበር?

9 ጴጥሮስ ባቀረበው ንግግር እንዲሁም ፈውስ በማግኘቱ በደስታ እየዘለለ በሚጮኸው ሽባ የነበረ ሰው ምክንያት በአካባቢው ሁካታ ተፈጥሯል። ስለሆነም የቤተ መቅደሱን ጸጥታ እንዲያስጠብቅ የተሾመው የቤተ መቅደሱ ሹምና የካህናት አለቆቹ ሁኔታውን ለማጣራት በጥድፊያ መጡ። እነዚህ ሰዎች ሰዱቃውያን ሳይሆኑ አይቀሩም። ሰዱቃውያን ከሮማውያን ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠርን የሚያበረታቱ ሀብታምና ፖለቲካዊ ተደማጭነት ያላቸው ሃይማኖታዊ ኑፋቄ ናቸው፤ ለፈሪሳውያን ትልቅ ቦታ የነበረውን የቃል ሕግ የማይቀበሉና በትንሣኤ የማያምኑ ነበሩ።c በመሆኑም በጴጥሮስና በዮሐንስ በጣም ተበሳጭተው መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ ቤተ መቅደሱ ውስጥ በድፍረት እያስተማሩ ነው!

10 በቁጣ የተሞሉት ተቃዋሚዎች ጴጥሮስንና ዮሐንስን እስር ቤት ከከተቷቸው በኋላ በቀጣዩ ቀን በአይሁዳውያን ከፍተኛ ሸንጎ ፊት አቀረቧቸው። ራሳቸውን ሊቅ አደርገው በሚቆጥሩት በእነዚህ ገዢዎች አመለካከት ጴጥሮስና ዮሐንስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ የማስተማር መብት የሌላቸው “ያልተማሩና ተራ ሰዎች” ነበሩ። የትኛውም ታዋቂ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤት ገብተው አልተማሩም። ይሁን እንጂ በድፍረትና በልበ ሙሉነት መናገር መቻላቸው ችሎቱን አስደንቆት ነበር። ጴጥሮስና ዮሐንስ እንዲህ ውጤታማ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ምን ነበር? አንዱ ምክንያት ‘ከኢየሱስ ጋር የነበሩ’ መሆናቸው ነው። (ሥራ 4:13) ጌታቸው እንደ ጸሐፍት ሳይሆን እንደ ባለሥልጣን ያስተምር ነበር።—ማቴ. 7:28, 29

11 ሸንጎው፣ ሐዋርያቱን መስበካቸውን እንዲያቆሙ አዘዛቸው። ሸንጎው የሚያስተላልፈው ውሳኔ በዚያ ማኅበረሰብ ውስጥ ትልቅ ቦታ ይሰጠው ነበር። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢየሱስ በዚሁ ሸንጎ ፊት ቀርቦ ሳለ አባላቱ “ሞት ይገባዋል” ብለው ፈርደውበታል። (ማቴ. 26:59-66) ያም ሆኖ ጴጥሮስና ዮሐንስ ምንም አልፈሩም። በእነዚህ ሀብታም፣ የተማሩና ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች ፊት ቆመው በድፍረት ሆኖም በአክብሮት እንዲህ አሉ፦ “አምላክን ከመስማት ይልቅ እናንተን መስማት በአምላክ ፊት ተገቢ እንደሆነና እንዳልሆነ እስቲ እናንተው ፍረዱ። እኛ ግን ስላየነውና ስለሰማነው ነገር ከመናገር ወደኋላ ማለት አንችልም።”—ሥራ 4:19, 20

ሊቀ ካህናቱና የካህናት አለቆቹ

ሊቀ ካህናቱ ሕዝቡን ወክሎ በአምላክ ፊት ይቀርባል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የሳንሄድሪንን ሸንጎ በበላይነት የሚመራውም እሱ ነበር። የአይሁድ መሪዎች ተደርገው የሚቆጠሩት በዙሪያው ያሉት ሌሎቹ ሰዎች ደግሞ የካህናት አለቆች ይባሉ ነበር። ከእነሱም መካከል እንደ ሐና ያሉ የቀድሞ ሊቀ ካህናት ይገኙበታል፤ ሊቀ ካህናት ከሚመረጡባቸው ቤተሰቦች (እነዚህ ቤተሰቦች ምናልባትም ከአራት ወይም ከአምስት አይበልጡም) የተውጣጡ ሌሎች በዕድሜ የጎለመሱ ወንዶችም ከካህናት አለቆች መካከል ይገኛሉ። ኤሚል ሹረር የተባሉት ምሁር እንደገለጹት “ይህ መብት ያላቸው ቤተሰቦች አባል መሆን ብቻ እንኳ” በካህናት መካከል “ልዩ ክብር ያሰጥ ነበር።”

ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ሊቀ ካህናት የሚያገለግሉት ዕድሜ ልካቸውን እንደሆነ ይገልጻሉ። (ዘኁ. 35:25) በሐዋርያት ሥራ ላይ የሰፈረው ታሪክ በተፈጸመበት ዘመን ግን የሮም እንደራሴዎችና በሮማውያን በጎ ፈቃድ የሚገዙ ነገሥታት ሊቀ ካህናቱን እንዳሻቸው ይሾሙና ይሽሩ ነበር። እንደዛም ሆኖ እነዚህ አረማዊ ገዢዎች ሊቀ ካህናቱን የሚሾሙት ከአሮን ዘሮች መካከል የነበረ ይመስላል።

12. ደፋርና ልበ ሙሉ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል?

12 አንተስ እንዲህ ዓይነት ድፍረት አለህ? በአካባቢህ ለሚገኙ ሀብታም፣ የተማሩ ወይም ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች ለመመሥከር አጋጣሚ ስታገኝ ምን ይሰማሃል? የቤተሰብህ አባላት፣ አብረውህ የሚማሩ ልጆች ወይም የሥራ ባልደረቦችህ በእምነትህ የተነሳ ቢያፌዙብህስ? ፍርሃት ያድርብሃል? ከሆነ እንዲህ ያለውን ስሜት ማሸነፍ ትችላለህ። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ሐዋርያቱን በልበ ሙሉነትና በአክብሮት ለእምነታቸው መከላከያ ማቅረብ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 10:11-18) ከሞት ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ ድረስ ሁልጊዜ” አብሯቸው እንደሚሆን ቃል ገብቶላቸዋል። (ማቴ. 28:20) በአሁኑ ወቅት ኢየሱስ ለእምነታችን እንዴት መከላከያ ማቅረብ እንደምንችል ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት ያስተምረናል። (ማቴ. 24:45-47፤ 1 ጴጥ. 3:15) በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ትምህርት ይሰጠናል፤ ‘ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን’ የተባለውን ስብሰባ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አማካኝነትም እንሠለጥናለን፤ jw.org ላይ “የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው” በሚለው ዓምድ ሥር ያሉትን ርዕሶች እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል። ታዲያ እነዚህን ዝግጅቶች በጥሩ ሁኔታ እየተጠቀምክባቸው ነው? እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ይበልጥ ደፋርና ልበ ሙሉ ትሆናለህ። ሐዋርያቱ እንዳደረጉት ሁሉ አንተም ስላየሃቸውና ስለሰማሃቸው አስደናቂ መንፈሳዊ እውነቶች ከመናገር ምንም ነገር እንዲያግድህ አትፈቅድም።

አንዲት እህት በሥራ ቦታዋ በሻይ እረፍቷ ላይ ለሥራ ባልደረባዋ ስትመሠክር።

የተማርካቸውን አስደናቂ መንፈሳዊ እውነቶች ለሌሎች ከመናገር ምንም ነገር እንዲያግድህ አትፍቀድ

“ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ . . . ወደ አምላክ ጸለዩ” (የሐዋርያት ሥራ 4:23-31)

13, 14. ተቃውሞ በሚያጋጥመን ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ለምንስ?

13 ጴጥሮስና ዮሐንስ ከእስር እንደተፈቱ ከሌሎቹ ወንድሞች ጋር ተገናኙ። መስበካቸውን ለመቀጠል የሚያስችል ድፍረት ለማግኘትም አብረው “ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ . . . ወደ አምላክ ጸለዩ።” (ሥራ 4:24) ጴጥሮስ፣ የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ በምንጥርበት ጊዜ በራሳችን ኃይል መታመን ሞኝነት መሆኑን በሚገባ ያውቃል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከልክ በላይ በራሱ በመተማመን ኢየሱስን “ሌሎቹ ሁሉ በአንተ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልሰናከልም!” ብሎት ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ጴጥሮስ ወዲያውኑ በሰው ፍርሃት ተሸንፎ ወዳጁንና አስተማሪውን ካደው። ያም ሆኖ ጴጥሮስ ከስህተቱ ተምሯል።—ማቴ. 26:33, 34, 69-75

14 ስለ ክርስቶስ የመመሥከር ተልእኮህን ለመወጣት ቆራጥነት ብቻውን በቂ አይደለም። ተቃዋሚዎች እምነትህን እንድትክድ ወይም መስበክህን እንድታቆም ለማድረግ በሚጥሩበት ጊዜ ጴጥሮስና ዮሐንስ የተዉትን ምሳሌ ተከተል። ይሖዋ ብርታት እንዲሰጥህ ጸልይ። የጉባኤውን እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። ስላጋጠሙህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለጉባኤ ሽማግሌዎችና ለሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች ንገራቸው። ሌሎች ስለ አንተ የሚያቀርቡት ጸሎት ለመጽናት የሚያስችል ኃይል ይሰጥሃል።—ኤፌ. 6:18፤ ያዕ. 5:16

15. መስበካቸውን ያቆሙ ሰዎች ተስፋ መቁረጥ የሌለባቸው ለምንድን ነው?

15 ሌሎች በሚያደርሱብህ ተጽዕኖ ተሸንፈህ መስበክህን አቁመህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ሁሉም ሐዋርያት ለተወሰነ ጊዜ መስበካቸውን አቁመው ነበር፤ ያም ሆኖ ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ መስበክ ጀምረዋል። (ማቴ. 26:56፤ 28:10, 16-20) እንግዲያው የፈጸምከው ስህተት ተስፋ እንዲያስቆርጥህ አትፍቀድ፤ ከዚህ ይልቅ ከስህተትህ ተምረህ ሌሎችም ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጽሙ አበረታታ።

16, 17. በኢየሩሳሌም የነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች ካቀረቡት ጸሎት ምን እንማራለን?

16 ባለሥልጣናት ስደት ሲያደርሱብን መጸለይ ያለብን ምን ብለን ነው? ደቀ መዛሙርቱ፣ ፈተና አያጋጥመን ብለው እንዳልጸለዩ ልብ በል። ኢየሱስ “እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል” ሲል የተናገረውን ሐሳብ እንደሚያስታውሱ ግልጽ ነው። (ዮሐ. 15:20) እነዚህ ታማኝ ደቀ መዛሙርት የጸለዩት ይሖዋ የተቃዋሚዎቻቸውን ዛቻ ‘እንዲመለከት’ ነው። (ሥራ 4:29) ደቀ መዛሙርቱ ትኩረት ያደረጉት በአምላክ ፈቃድ መፈጸም ላይ ነው፤ እየደረሰባቸው ያለው ስደት የትንቢት ፍጻሜ መሆኑን ተረድተዋል። ደቀ መዛሙርቱ፣ ሰብዓዊ ገዢዎች ምንም አሉ ምን ኢየሱስ እንዲጸልዩ ባስተማራቸው መሠረት የአምላክ ፈቃድ ‘በምድር ላይ መፈጸሙ’ እንደማይቀር ያውቁ ነበር።—ማቴ. 6:9, 10

17 ደቀ መዛሙርቱ፣ ፈቃዱን ለማድረግ እንዲረዳቸው አምላክን ለመኑ፤ “ባሪያዎችህም ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው” በማለት ጸለዩ። ይሖዋስ ወዲያው ምን ምላሽ ሰጣቸው? “ተሰብስበውበት የነበረው ቦታ ተናወጠ፤ ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው የአምላክን ቃል በድፍረት መናገር ጀመሩ።” (ሥራ 4:29-31) የአምላክ ፈቃድ እንዳይፈጸም ሊያግድ የሚችል ምንም ነገር የለም። (ኢሳ. 55:11) ያጋጠሙን እንቅፋቶች ምንም ያህል ከባድ ቢሆኑ ወይም ተቃዋሚዎቻችን የቱንም ያህል ኃያል ቢሆኑ፣ ወደ አምላክ ከጸለይን ቃሉን በድፍረት ለመናገር የሚያስችለንን ብርታት እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

‘በሰው ሳይሆን በአምላክ’ ፊት ተጠያቂዎች (የሐዋርያት ሥራ 4:32 እስከ 5:11)

18. በኢየሩሳሌም የነበረው ጉባኤ አባላት አንዳቸው ለሌላው ምን ያደርጉ ነበር?

18 በኢየሩሳሌም አዲስ የተቋቋመው ጉባኤ በጥቂት ጊዜ ውስጥ 5,000 አባላት ያሉት ጠንካራ ጉባኤ ሆነ።d ደቀ መዛሙርቱ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ቢሆኑም “አንድ ልብና ነፍስ” ነበራቸው። በአስተሳሰብም ሆነ በዓላማ ፍጹም አንድነት ነበራቸው። (ሥራ 4:32፤ 1 ቆሮ. 1:10) ደቀ መዛሙርቱ ይሖዋ ጥረታቸውን እንዲባርክላቸው በመጸለይ ብቻ አልተወሰኑም። በመንፈሳዊ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ በሰብዓዊ እርስ በርሳቸው ይረዳዱ ነበር። (1 ዮሐ. 3:16-18) ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያት በርናባስ እያሉ ይጠሩት የነበረው ደቀ መዝሙሩ ዮሴፍ መሬቱን በመሸጥ ገንዘቡን በሙሉ በስጦታ ሰጥቷል፤ ይህን ያደረገው ከሩቅ አገር የመጡት ሰዎች በኢየሩሳሌም ቆይተው ስለ አዲሱ እምነታቸው ተጨማሪ እውቀት እንዲቀስሙ ለመርዳት ሲል ነው።

19. ይሖዋ ሐናንያንና ሰጲራን የቀሰፋቸው ለምንድን ነው?

19 ሐናንያና ሰጲራ የሚባሉ ባልና ሚስትም መሬታቸውን በመሸጥ ገንዘብ ሰጡ። ገንዘቡን ሙሉ በሙሉ የሰጡ ለማስመሰል ሞክረው ነበር፤ ሆኖም ‘የተወሰነውን ደብቀው አስቀርተዋል።’ (ሥራ 5:2) ይሖዋ እነዚህን ባልና ሚስት ቀሰፋቸው፤ ይህን ያደረገው ግን የሰጡት ገንዘብ ትንሽ ስለነበር ሳይሆን ውስጣዊ ዝንባሌያቸው መጥፎ ስለሆነና ለማጭበርበር ስለሞከሩ ነው። ‘የዋሹት ሰውን ሳይሆን አምላክን ነው።’ (ሥራ 5:4) ኢየሱስ እንዳወገዛቸው ግብዝ ሰዎች ሁሉ ሐናንያና ሰጲራም የአምላክን ሞገስ ሳይሆን በሰዎች ዘንድ ከበሬታ ማግኘት ፈልገው ነበር።—ማቴ. 6:1-3

20. ለይሖዋ ከመስጠት ጋር በተያያዘ ምን ማስታወስ ይኖርብናል?

20 ዛሬ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮችም በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም እንደነበሩት ታማኝ ደቀ መዛሙርት የልግስና መንፈስ ያሳያሉ፤ የፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ ይደግፋሉ። ማንም ሰው ጊዜውንም ሆነ ገንዘቡን ለዚህ ሥራ እንዲያውል አይገደድም። እንዲያውም ይሖዋ ቅር እያለን ወይም ተገደን እንድናገለግለው አይፈልግም። (2 ቆሮ. 9:7) በምንሰጥበት ጊዜ ይሖዋ የሚመለከተው የገንዘቡን መጠን ሳይሆን ያን ለማድረግ ያነሳሳንን ውስጣዊ ግፊት ነው። (ማር. 12:41-44) አምላክን የምናገለግለው በራስ ወዳድነት ተነሳስተን አሊያም በሰዎች ዘንድ ለመከበር ብለን መሆን የለበትም፤ እንደ ሐናንያና ሰጲራ መሆን ፈጽሞ አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ እንደ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና በርናባስ ምንጊዜም ለአምላክና ለሰው ባለን እውነተኛ ፍቅር ተገፋፍተን ይሖዋን እናገልግለው።—ማቴ. 22:37-40

ጴጥሮስ—ከዓሣ አጥማጅነት ወደ ቀናተኛ ሐዋርያነት

ጴጥሮስ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አምስት የተለያዩ ስሞች ተሰጥተውታል። በዕብራይስጥ ሲምዖን፣ በግሪክኛ አቻው ደግሞ ስምዖን ተብሎ ይጠራ ነበር፤ እንዲሁም ጴጥሮስ በሚለውና ሴማዊ አቻው በሆነው ኬፋ በሚለው ስምም ተጠርቷል። በተጨማሪም ይህ ሐዋርያ፣ ስምዖን ጴጥሮስ የተባለ ሁለቱን ስሞች አንድ ላይ ያጣመረ ስም ነበረው።—ማቴ. 10:2፤ ዮሐ. 1:42፤ ሥራ 15:14

ሐዋርያው ጴጥሮስ ዓሣ የሞላበት ቅርጫት ይዞ።

ጴጥሮስ ባለትዳር ሲሆን አማቱና ወንድሙም የሚኖሩት ከእሱ ጋር ነበር። (ማር. 1:29-31) ዓሣ አጥማጁ ጴጥሮስ ከገሊላ ባሕር በስተ ሰሜን የምትገኘው የቤተሳይዳ ሰው ነው። (ዮሐ. 1:44) በኋላም በቅፍርናሆም አቅራቢያ መኖር ጀመረ። (ሉቃስ 4:31, 38) ኢየሱስ በገሊላ ባሕር ዳርቻ ተሰብስበው የነበሩትን ብዙ ሰዎች ያስተማራቸው በጴጥሮስ ጀልባ ላይ ተቀምጦ ነበር። ንግግሩን እንደጨረሰም ጴጥሮስን መረቡን ወደ ባሕሩ እንዲጥል ነገረው፤ ጴጥሮስ ይህን ሲያደርግ በተአምር እጅግ ብዙ ዓሣዎችን ያዘ። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ በፍርሃት ተውጦ በኢየሱስ እግር ሥር ወደቀ፤ ኢየሱስ ግን “አይዞህ አትፍራ፤ ከአሁን ጀምሮ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” አለው። (ሉቃስ 5:1-11) ጴጥሮስ ከወንድሙ ከእንድርያስ እንዲሁም ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ሆኖ ዓሣ እያጠመደ ነበር። ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲሆኑ ግብዣ ባቀረበላቸው ጊዜ አራቱም ዓሣ የማጥመድ ሥራቸውን ትተው ተከተሉት። (ማቴ. 4:18-22፤ ማር. 1:16-18) ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ ኢየሱስ የእሱ “ሐዋርያት” (“የተላኩ” ማለት ነው) እንዲሆኑ ከመረጣቸው 12 ሰዎች መካከል አንዱ ጴጥሮስ ነበር።—ማር. 3:13-16

ኢየሱስ በአንዳንድ ለየት ያሉ ወቅቶች ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ አብረውት እንዲሆኑ ያደርግ ነበር። እነዚህ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ሲለወጥ፣ የኢያኢሮስን ሴት ልጅ ከሞት ሲያስነሳ እንዲሁም በጌትሴማኒ የአትክልት ስፍራ በጣም አዝኖ በነበረበት ጊዜ አብረውት ነበሩ። (ማቴ. 17:1, 2፤ 26:36-46፤ ማር. 5:22-24, 35-42፤ ሉቃስ 22:39-46) ኢየሱስን ስለ መገኘቱ ምልክት እንዲነግራቸው የጠየቁትም እነዚሁ ሦስት ሐዋርያትና እንድርያስ ነበሩ።—ማር. 13:1-4

ጴጥሮስ ግልጽና ቀናተኛ፣ አንዳንዴም ችኩልነት የሚታይበት ሰው ነበር። ብዙውን ጊዜ ከባልንጀሮቹ ቀድሞ የመናገር ልማድ የነበረው ይመስላል። በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ ሌሎቹ 11 ሐዋርያት የተናገሯቸው ሐሳቦች አንድ ላይ ቢደመሩ እንኳ ጴጥሮስ የተናገራቸውን አያክሉም። ሌሎቹ ዝም ቢሉም ጴጥሮስ ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ወደኋላ አይልም ነበር። (ማቴ. 15:15፤ 18:21፤ 19:27-29፤ ሉቃስ 12:41፤ ዮሐ. 13:36-38) ኢየሱስ እግሩን እንዳያጥበው ተቃውሞ ያሰማው፣ እርማት በተሰጠው ጊዜ ደግሞ እጁንና ራሱንም ጭምር እንዲያጥበው ጥያቄ ያቀረበው እሱ ነበር!—ዮሐ. 13:5-10

ጴጥሮስ፣ ኢየሱስን በጣም ይወደው ስለነበር መከራ መቀበልም ሆነ መሞት እንደሌለበት ሊያሳምነው ሞክሮ ነበር። ኢየሱስ ግን ጴጥሮስ ሳያመዛዝን ለሰነዘረው ሐሳብ ጠንከር ያለ እርማት ሰጥቶታል። (ማቴ. 16:21-23) ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት፣ ጴጥሮስ ሌሎቹ ሐዋርያት ሁሉ ኢየሱስን ጥለውት ቢሸሹም እንኳ እሱ ፈጽሞ እንደዚያ እንደማያደርግ ተናግሮ ነበር። ኢየሱስ በጠላቶቹ እጅ በወደቀበት ጊዜ ጴጥሮስ በድፍረት ሰይፉን መዞ ኢየሱስን ለማስጣል ሞክሯል፤ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ድረስም በድፍረት ተከትሎት ሄዷል። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ጌታውን ሦስት ጊዜ ካደው፤ ከዚያም ያደረገውን ነገር መለስ ብሎ ሲያስብ ምርር ብሎ አለቀሰ።—ማቴ. 26:31-35, 51, 52, 69-75

ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ በገሊላ ለነበሩት ሐዋርያቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመገለጡ ትንሽ ቀደም ብሎ ጴጥሮስ ለሌሎቹ ሐዋርያት ዓሣ ሊያጠምድ መሄዱ እንደሆነ ነገራቸው፤ እነሱም አብረውት ሄዱ። በኋላም ጴጥሮስ በባሕሩ ዳርቻ የቆመው ሰው ኢየሱስ መሆኑን ሲያውቅ ባሕሩ ውስጥ ዘሎ በመግባት ወደ ዳርቻው እየዋኘ ሄደ። ሐዋርያቱ ኢየሱስ ያዘጋጀላቸውን ቁርስ እየተመገቡ ሳሉ ኢየሱስ፣ ጴጥሮስን “ከእነዚህ” ማለትም በፊታቸው ካሉት ዓሣዎች አብልጦ ይወደው እንደሆነ ጠየቀው። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጴጥሮስ፣ እንደ ዓሣ አጥማጅነት ባሉ የንግድ ሥራዎች ከመጠላለፍ ይልቅ ሙሉ ጊዜውን የእሱ ተከታይ እንዲሆን ማበረታታቱ ነበር።—ዮሐ. 21:1-22

ከ62 እስከ 64 ዓ.ም. ገደማ ጴጥሮስ በባቢሎን (በአሁኗ ኢራቅ) ምሥራቹን ሰብኳል፤ በዚያ በርካታ አይሁዳውያን ይኖሩ ነበር። (1 ጴጥ. 5:13) ጴጥሮስ በስሙ የተሰየመውን የመጀመሪያ መልእክቱን፣ ምናልባትም ሁለተኛውንም መልእክቱን ጭምር በመንፈስ መሪነት የጻፈው በባቢሎን ሳለ ነው። ጴጥሮስ “ለተገረዙት ሐዋርያ ሆኖ እንዲያገለግል” ኢየሱስ ‘ኃይል ሰጥቶታል።’ (ገላ. 2:8, 9) ጴጥሮስም የተሰጠውን ተልእኮ በርኅራኄና በቅንዓት ተወጥቷል።

ዮሐንስ—ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር

ሐዋርያው ዮሐንስ የዘብዴዎስ ልጅ ሲሆን የሐዋርያው ያዕቆብ ወንድም ነው። የእናቱ ስም ሰሎሜ ሳይሆን አይቀርም፤ ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ሰሎሜ የኢየሱስ እናት የማርያም እህት ናት። (ማቴ. 10:2፤ 27:55, 56፤ ማር. 15:40፤ ሉቃስ 5:9, 10) በመሆኑም ዮሐንስ የኢየሱስ ዘመድ ሳይሆን አይቀርም። የዮሐንስ ቤተሰቦች ሀብታሞች የነበሩ ይመስላል። ዘብዴዎስ ያካሂድ የነበረው ዓሣ የማጥመድ ሥራ ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ ሰዎችን ቀጥሮ ያሠራ ነበር። (ማር. 1:20) ሰሎሜ ከኢየሱስ ጋር አብራ ትጓዝ እንዲሁም በገሊላ በነበረበት ጊዜ ታገለግለው ነበር፤ በኋላም የኢየሱስን አስከሬን ለቀብር ለማዘጋጀት የተለያዩ ቅመሞች ይዛ መጥታለች። (ማር. 16:1፤ ዮሐ. 19:40) ዮሐንስ የራሱ ቤት ሳይኖረው አይቀርም።—ዮሐ. 19:26, 27

ሐዋርያው ዮሐንስ ጥቅልል ይዞ።

ዮሐንስ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረ ይመስላል፤ መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን አይቶ “የአምላክ በግ ይኸውላችሁ!” ባለ ጊዜ ከእንድርያስ ጋር አብሮ የነበረው ዮሐንስ ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐ. 1:35, 36, 40) የዘብዴዎስ ልጅ ዮሐንስ በዚህ መንገድ ከኢየሱስ ጋር ከተዋወቀ በኋላ ከእሱ ጋር ወደ ቃና ሳይሄድ አልቀረም፤ በዚያም የመጀመሪያው የኢየሱስ ተአምር የዓይን ምሥክር ለመሆን የበቃ ይመስላል። (ዮሐ. 2:1-11) ይህ የወንጌል ጸሐፊ፣ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም፣ በሰማርያና በገሊላ ያከናወናቸውን ነገሮች ሕያው በሆነ መንገድ በዝርዝር መግለጹ የእነዚህ ክንውኖችም የዓይን ምሥክር ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። ዮሐንስ ጠንካራ እምነት ነበረው፤ ምክንያቱም እንደ ያዕቆብ፣ ጴጥሮስና እንድርያስ ሁሉ እሱም የኢየሱስ ተከታይ እንዲሆን ግብዣ ሲቀርብለት የዓሣ ማጥመጃ መረቡን፣ ጀልባውንና መተዳደሪያውን ትቶ ወዲያውኑ ግብዣውን ተቀብሏል።—ማቴ. 4:18-22

ዮሐንስ በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ የጴጥሮስን ያህል ብዙ ጊዜ አልተጠቀሰም። ይሁን እንጂ እሱም ቁጥብ የሚባል ዓይነት ሰው አልነበረም፤ ኢየሱስ ዮሐንስንና ወንድሙን ያዕቆብን ቦአኔርጌስ ማለትም “የነጎድጓድ ልጆች” ብሎ መጥራቱ ይህን ያሳያል። (ማር. 3:17) ዮሐንስ መጀመሪያ ላይ ከሌሎች ልቆ የመገኘት ፍላጎት ነበረው፤ እንዲያውም እሱና ወንድሙ እናታቸውን ወደ ኢየሱስ በመላክ በመንግሥቱ ውስጥ ከፍ ያለ ሥልጣን እንዲሰጣቸው እስከመጠየቅ ደርሰው ነበር። ይህ ፍላጎታቸው ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ቢሆንም የአምላክ መንግሥት እውን ስለመሆኑ ጠንካራ እምነት እንደነበራቸው ያሳያል። ኢየሱስ እነዚህ ወንድማማቾች ያቀረቡት የሥልጣን ጥያቄ የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ለሁሉም ሐዋርያቱ ስለ ትሕትና አስፈላጊነት ምክር ሰጥቷል።—ማቴ. 20:20-28

የዮሐንስ የኃይለኝነት ባሕርይ የታየባቸው ሌሎች አጋጣሚዎችም አሉ፤ በአንድ ወቅት፣ የኢየሱስ ተከታይ ያልሆነን ሰው በኢየሱስ ስም አጋንንት እንዳያስወጣ ሊከለክለው ሞክሯል። በሌላ ጊዜ ደግሞ ኢየሱስ አንዳንድ ነገሮችን እንዲያዘጋጁለት ወደ አንድ የሳምራውያን መንደር መልእክተኞች በላከ ጊዜ በዚያ የነበሩት ሰዎች ጥሩ ምላሽ አልሰጡም፤ በዚያ ወቅት ዮሐንስ እሳት ከሰማይ ወርዶ እንዲያጠፋቸው ማዘዝ ፈልጎ ነበር። በእነዚህ ወቅቶች ኢየሱስ ዮሐንስን ገሥጾታል። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው ዮሐንስ ከጊዜ በኋላ ሚዛናዊነትንና ርኅራኄን ማዳበር ችሎ ነበር። (ሉቃስ 9:49-56) ዮሐንስ አንዳንድ ድክመቶች የነበሩበት ሰው ቢሆንም “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር” ነው። በመሆኑም ኢየሱስ ሊሞት በተቃረበበት ጊዜ እናቱን ማርያምን እንዲንከባከብለት አደራ ያለው ዮሐንስን ነው።—ዮሐ. 19:26, 27፤ 21:7, 20, 24

ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ሁሉ ዮሐንስ ከሌሎቹ ሐዋርያት በላይ ረጅም ዕድሜ ኖሯል። (ዮሐ. 21:20-22) ዮሐንስ ለ70 ዓመታት ያህል ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። በሕይወቱ መገባደጃ አካባቢ ይኸውም የሮም ንጉሠ ነገሥት በነበረው በደሚሸን የንግሥና ዘመን ‘ስለ አምላክ በመናገሩና ስለ ኢየሱስ በመመሥከሩ’ የተነሳ ጳጥሞስ በምትባል ደሴት ታስሮ ነበር። በዚያም ሳለ በ96 ዓ.ም. ገደማ፣ በራእይ መጽሐፍ ላይ የዘገባቸውን ራእዮች አይቷል። (ራእይ 1:1, 2, 9) ዮሐንስ ከእስር ከተፈታ በኋላ ወደ ኤፌሶን እንደሄደና በዚያም በስሙ የተሰየመውን ወንጌል ጨምሮ 1ኛ፣ 2ኛ እና 3ኛ ዮሐንስ በመባል የሚታወቁትን መልእክቶች እንደጻፈ ይነገራል፤ ከዚያም በ100 ዓ.ም. ገደማ እዚያው ኤፌሶን ውስጥ እንደሞተ ይታመናል።

a በቤተ መቅደሱ ውስጥ ጠዋትና ምሽት ላይ ከሚቀርቡት መሥዋዕቶች ጋር ጸሎቶችም ይቀርቡ ነበር። የምሽቱ መሥዋዕት የሚቀርበው “ከቀኑ በዘጠኝ ሰዓት” ገደማ ነበር።

b “ጴጥሮስ—ከዓሣ አጥማጅነት ወደ ቀናተኛ ሐዋርያነት” የሚለውን ሣጥንና “ዮሐንስ—ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

c “ሊቀ ካህናቱና የካህናት አለቆቹ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

d በ33 ዓ.ም. በኢየሩሳሌም የነበሩት ፈሪሳውያን ቁጥር 6,000 ገደማ ነበር፤ የሰዱቃውያን ቁጥር ደግሞ ከዚህም እንደሚያንስ ይገመታል። እነዚህ ሁለት ቡድኖች፣ ስለ ኢየሱስ በሚታወጀው ስብከት የተነሳ ስጋት ላይ የወደቁበት ሌላው ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ