-
የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
-
-
ትምህርት 1
የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው?
ዴንማርክ
ታይዋን
ቬኔዙዌላ
ሕንድ
የምታውቃቸው የይሖዋ ምሥክሮች አሉ? ምናልባትም ጎረቤቶችህ፣ የሥራ ባልደረቦችህ ወይም አብረውህ የሚማሩት ልጆች የይሖዋ ምሥክሮች ይሆናሉ። ወይም ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት አድርገህ ታውቅ ይሆናል። ይሁን እንጂ እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ምን ዓይነት ሰዎች ነን? ስለ እምነታችን ለሰዎች የምንናገረውስ ለምንድን ነው?
እንደ ማንኛውም ሰው ነን። የተለያየ አስተዳደግና ማኅበራዊ ሁኔታ ያለን ሰዎች ነን። አንዳንዶቻችን የይሖዋ ምሥክር ከመሆናችን በፊት የሌላ ሃይማኖት አባላት ነበርን፤ ሌሎቻችን ደግሞ በአምላክ የማናምን ሰዎች ነበርን። የይሖዋ ምሥክር ከመሆናችን በፊት ግን ሁላችንም ጊዜ ወስደን የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች በጥንቃቄ መርምረናል። (የሐዋርያት ሥራ 17:11) ከዚያም የተማርነውን ነገር ስላመንንበት ይሖዋ አምላክን ለማምለክ በግለሰብ ደረጃ ውሳኔ አደረግን።
መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናታችን ጠቅሞናል። እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ እኛም ከተለያዩ ችግሮችና ከራሳችን ድክመት ጋር መታገል ያስፈልገናል። ይሁን እንጂ በዕለታዊ ሕይወታችን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ለማድረግ ስለምንጥር በሕይወታችን ውስጥ ጉልህ ለውጥ መመልከት ችለናል። (መዝሙር 128:1, 2) ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተማርናቸውን መልካም ነገሮች ለሌሎች የምናካፍልበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።
የአምላክን መመሪያዎች አክብረን እንኖራለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት እነዚህ መመሪያዎች በአካልም ሆነ በአስተሳሰብ ጤናማ እንድንሆን የሚረዱን ከመሆኑም ሌላ ለሰዎች አክብሮት እንዲኖረን እንዲሁም እንደ ሐቀኝነትና ደግነት ያሉትን ጥሩ ባሕርያት እንድናፈራ ያስችሉናል። የአምላክ መመሪያዎች፣ ዜጎች ጤናማና ጠቃሚ የማኅበረሰቡ አባላት እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፤ አልፎ ተርፎም ቤተሰቦች አንድነትና ጥሩ ሥነ ምግባር እንዲኖራቸው እገዛ ያደርጋሉ። “አምላክ እንደማያዳላ” ስለምናምን በዘርና በፖለቲካ ያልተከፋፈለና ዓለም አቀፋዊ የሆነ መንፈሳዊ የወንድማማች ማኅበር አለን። በዚህም የተነሳ፣ እንደ ማንኛውም ሰው ብንሆንም ልዩ ሕዝብ መሆን ችለናል።—የሐዋርያት ሥራ 4:13፤ 10:34, 35
የይሖዋ ምሥክሮችን ከሌሎች ሰዎች ጋር የሚያመሳስላቸው ምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናታቸው የትኞቹን መመሪያዎች ማወቅ ችለዋል?
-
-
የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን የምንጠራው ለምንድን ነው?በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
-
-
ትምህርት 2
የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን የምንጠራው ለምንድን ነው?
ኖኅ
አብርሃምና ሣራ
ሙሴ
ኢየሱስ ክርስቶስ
ብዙ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው መጠሪያ የአንድ አዲስ ሃይማኖት ስም ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ ከ2,700 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት እውነተኛው አምላክ፣ አገልጋዮቹን “ምሥክሮቼ” ብሏቸዋል። (ኢሳይያስ 43:10-12) እስከ 1931 ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል እንታወቅ ነበር። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን መጠራት የጀመርነው ለምንድን ነው?
አምላካችንን ለይቶ ያሳውቃል። በጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በሺዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ይገኝ ነበር። በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ይህ ስም እንደ ጌታ፣ አምላክ ወይም እግዚአብሔር (እንደ አማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ) በመሳሰሉት የማዕረግ ስሞች ተተክቷል። ይሁን እንጂ እውነተኛው አምላክ ራሱን ለሙሴ ሲገልጥ “ይሖዋ” የሚለውን የግል ስሙን የነገረው ሲሆን “ይህ ለዘላለም ስሜ ነው” ብሎታል። (ዘፀአት 3:15) እውነተኛው አምላክ በዚህ መንገድ ራሱን ከሌሎች የሐሰት አማልክት ለይቷል። እኛም በአምላክ ቅዱስ ስም በመጠራታችን እንኮራለን።
ተልእኳችንን ይገልጻል። ከጻድቁ አቤል ጀምሮ የኖሩ በርካታ ሰዎች በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው መሥክረዋል። ከዚያ በኋላ በነበሩት ምዕተ ዓመታትም ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴ፣ ዳዊትና ሌሎችም ከዚህ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” ጋር ተባብረዋል። (ዕብራውያን 11:4 እስከ 12:1) አንድ ግለሰብ የፍርድ ችሎት ፊት ቀርቦ ስለ አንድ ሰው ንጽሕና እንደሚመሠክር ሁሉ እኛም ስለ አምላካችን እውነቱን ለማሳወቅ ቆርጠን ተነስተናል።
የኢየሱስን ምሳሌ እንደምንከተል ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ታማኝና እውነተኛ ምሥክር” ይለዋል። (ራእይ 3:14) ኢየሱስ ራሱም ‘የአምላክን ስም እንዳሳወቀ’ እንዲሁም ስለ አምላክ ‘እውነቱን እንደመሠከረ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:26፤ 18:37) እንግዲያው የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች የሆኑ ሁሉ በይሖዋ ስም መጠራት እና ስሙን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮችም ይህንን ለማድረግ ይጥራሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው መጠራት የጀመሩት ለምንድን ነው?
ይሖዋ በምድር ላይ ምሥክሮች የነበሩት ከመቼ ጀምሮ ነው?
ከሁሉ የሚበልጠው የይሖዋ ምሥክር ማን ነው?
-
-
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዳግመኛ የተገለጠው እንዴት ነው?በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
-
-
ትምህርት 3
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዳግመኛ የተገለጠው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ 1870ዎቹ
የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ እትም፣ 1879
መጠበቂያ ግንብ በአሁኑ ጊዜ
ክርስቶስ ከሞተ በኋላ ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል የሐሰት አስተማሪዎች እንደሚነሱና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደሚበክሉ መጽሐፍ ቅዱስ ተንብዮ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:29, 30) ከጊዜ በኋላ ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጸመ። ሐሰተኛ አስተማሪዎች የኢየሱስን ትምህርቶች ከአረማውያን ሃይማኖት ጋር ስለቀላቀሉት እውነተኛ ያልሆነ ክርስትና ተፈጠረ። (2 ጢሞቴዎስ 4:3, 4) ታዲያ በዛሬው ጊዜ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለን እውቀት ትክክለኛ መሆኑን እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?
ይሖዋ እውነቱን የሚገልጥበት ጊዜ ደረሰ። ይሖዋ ‘በፍጻሜው ዘመን እውነተኛው እውቀት እንደሚበዛ’ ተንብዮ ነበር። (ዳንኤል 12:4) እውነትን ይፈልጉ የነበሩ ጥቂት ሰዎች አብዛኞቹ የአብያተ ክርስቲያናት መሠረተ ትምህርቶች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ እንደሌላቸው በ1870 ተገነዘቡ። ስለዚህም የመጀመሪያዎቹንና ያልተበረዙትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ለመረዳት ምርምር ማድረግ ጀመሩ፤ ይሖዋም መንፈሳዊ ማስተዋል እንዲያገኙ በመርዳት ጥረታቸውን ባርኮላቸዋል።
ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናት ጀመሩ። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ያጠኑ የነበሩት በቀድሞ ዘመን የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ርዕስ በርዕስ ይወያዩ ነበር። ይህን ዘዴ ዛሬም ድረስ እንጠቀምበታለን። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ለመረዳት የሚያስቸግር የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲያጋጥማቸው ጉዳዩን ግልጽ የሚያደርጉ ሌሎች ጥቅሶችን ይመረምሩ ነበር። ከተቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማ መደምደሚያ ላይ ሲደርሱ የደረሱበትን መደምደሚያ በጽሑፍ ያሰፍሩታል። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን እንዲተረጉም ያደረጉ ሲሆን ይህም ስለ አምላክ ስምና መንግሥት፣ አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር ስላለው ዓላማ፣ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታ እንዲሁም ስለ ትንሣኤ ተስፋ እውነቱን ለማወቅ አስቻላቸው። ያደረጉት ምርምር ከተለያዩ የሐሰት እምነቶችና ልማዶች ነፃ አውጥቷቸዋል።—ዮሐንስ 8:31, 32
በ1879 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እውነቱን በስፋት የሚያሳውቁበት ጊዜ እንደደረሰ አስተዋሉ። ስለሆነም በዚያ ዓመት፣ ዛሬም የምናትመውን የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የተባለውን መጽሔት ማዘጋጀት ጀመሩ። በአሁኑ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን በ240 አገሮች ከ750 በሚበልጡ ቋንቋዎች ለሰዎች እንሰብካለን። በእርግጥም እውነተኛ እውቀት የዚህን ዘመን ያህል የበዛበት ጊዜ የለም!
ክርስቶስ ከሞተ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምን ሆነ?
በአምላክ ቃል ውስጥ ያለው እውነት በዘመናችን ሊገለጥ የቻለው እንዴት ነው?
-
-
አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ያዘጋጀነው ለምንድን ነው?በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
-
-
ትምህርት 4
አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ያዘጋጀነው ለምንድን ነው?
ኮንጎ (ኪንሻሳ)
ሩዋንዳ
መለኮታዊው ስም በመዝሙር 69:31 ላይ የሚገኝበት የሲማከስ ቅጂ ቁራጭ፣ በሦስተኛው ወይም በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የተዘጋጀ
የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ አሥርተ ዓመታት የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞችን ተጠቅመዋል፤ አትመዋል እንዲሁም አሰራጭተዋል። ይሁንና የአምላክ ፈቃድ ሁሉም ሰው “የእውነትን ትክክለኛ እውቀት” እንዲያገኝ በመሆኑ ይህን ለማድረግ የሚረዳ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ ከጊዜ በኋላ ተገነዘብን። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) በመሆኑም በ1950 በዘመናዊ ቋንቋ ያዘጋጀነውን አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለ መጽሐፍ ቅዱስ በከፊል ማውጣት ጀመርን። በአሁኑ ጊዜ ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች በተተረጎመው በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በታማኝነትና በትክክል ለማስተላለፍ ጥረት ተደርጓል።
ለመረዳት የማይከብድ መጽሐፍ ቅዱስ ያስፈልግ ነበር። ቋንቋዎች በጊዜ ሂደት እየተለወጡ ይሄዳሉ፤ በመሆኑም በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ውስጥ የሚገኙት ቃላትና አገላለጾች የቆዩና ለመረዳት የሚያስቸግሩ ከመሆናቸውም ሌላ ግልጽ አይደሉም። በተጨማሪም ይበልጥ ትክክለኛና ለበኩረ ጽሑፉ ቅርብ የሆኑ ብዙ ጥንታዊ የቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች በመገኘታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ስለተጻፈበት የዕብራይስጥ፣ የአረማይክ እና የግሪክኛ ቋንቋ የተሻለ ግንዛቤ ሊኖር ችሏል።
የአምላክን ቃል ምንም ሳይለውጥ በታማኝነት የሚያስተላልፍ ትርጉም ያስፈልግ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክ ቃል እንዳሻቸው ከመለወጥ ይልቅ የበኩረ ጽሑፉን ሐሳብ ምንም ሳይለውጡ ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል። አብዛኞቹ ትርጉሞች ግን ይሖዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም ከቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አውጥተውታል።
ለመጽሐፍ ቅዱስ ባለቤት እውቅና የሚሰጥ ትርጉም ያስፈልግ ነበር። (2 ሳሙኤል 23:2) ከታች ባለው ሥዕል ላይ እንደሚታየው በጥንቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ 7,000 ጊዜ ያህል ይገኝ የነበረው የይሖዋ ስም በአዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ ትክክለኛው ቦታው ላይ ተመልሷል። (መዝሙር 83:18) ለበርካታ ዓመታት ጥልቅ ምርምር ከተደረገ በኋላ የተዘጋጀው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ሐሳብ በትክክል የሚያስተላልፍ በመሆኑ ለማንበብ ያስደስታል። አዲስ ዓለም ትርጉም በራስህ ቋንቋ ኖረም አልኖረ የይሖዋን ቃል በየቀኑ የማንበብ ልማድ እንድታዳብር እናበረታታሃለን።—ኢያሱ 1:8፤ መዝሙር 1:2, 3
አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ያዘጋጀነው ለምንድን ነው?
የአምላክን ፈቃድ ማወቅ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በየቀኑ ምን የማድረግ ልማድ ቢኖረው ጥሩ ነው?
-