የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ሽማግሌዎች ጉባኤውን የሚያገለግሉት እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 15

      ሽማግሌዎች ጉባኤውን የሚያገለግሉት እንዴት ነው?

      አንድ ሽማግሌ ከጉባኤው አባላት ጋር ሲያወራ

      ፊንላንድ

      አንድ ሽማግሌ ጉባኤ ውስጥ ሲያስተምር

      ማስተማር

      ሽማግሌዎች የጉባኤውን አባላት ሲያበረታቱ

      እረኝነት

      አንድ ሽማግሌ በስብከቱ ሥራ ላይ

      መመሥከር

      በድርጅታችን ውስጥ ደሞዝ የሚከፈላቸው ቀሳውስት የሉንም። ከዚህ ይልቅ የክርስቲያን ጉባኤ በተቋቋመበት ጊዜ እንደተደረገው ሁሉ ዛሬም ብቃት ያላቸው የበላይ ተመልካቾች የአምላክን ‘ጉባኤ እንዲጠብቁ’ ይሾማሉ። (የሐዋርያት ሥራ 20:28) እነዚህ ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንዶች ናቸው፤ ሽማግሌዎች ጉባኤው በሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ግንባር ቀደም ሆነው የሚካፈሉ ከመሆኑም ሌላ “በግዴታ ሳይሆን በአምላክ ፊት በፈቃደኝነት . . . አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በመመኘት ሳይሆን ለማገልገል በመጓጓት” ለጉባኤው እንደ እረኞች ሆነው ያገለግላሉ። (1 ጴጥሮስ 5:1-3) ሽማግሌዎች እኛን የሚጠቅሙ ምን ሥራዎችን ያከናውናሉ?

      ይንከባከቡናል እንዲሁም ይጠብቁናል። ሽማግሌዎች ለጉባኤው አባላት ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች የሚሰጡ ከመሆኑም ሌላ በመንፈሳዊ ሁኔታ አደጋ ላይ እንዳይወድቁ ጥበቃ ያደርጋሉ። አምላክ ይህን አስፈላጊ የሆነ ሥራ በአደራ እንደሰጣቸው ስለሚገነዘቡ ለሕዝቦቹ ደህንነትና ደስታ አስተዋጽኦ ለማበርከት ይጥራሉ እንጂ በእነሱ ላይ የበላይ ለመሆን አይሞክሩም። (2 ቆሮንቶስ 1:24) አንድ እረኛ በመንጋው ውስጥ የሚገኘውን እያንዳንዱን በግ በትጋት እንደሚንከባከብ ሁሉ ሽማግሌዎችም እያንዳንዱን የጉባኤ አባል በግለሰብ ደረጃ ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ።—ምሳሌ 27:23

      የአምላክን ፈቃድ ማድረግ የምንችልበትን መንገድ ያስተምሩናል። ሽማግሌዎች በየሳምንቱ የሚደረጉትን የጉባኤ ስብሰባዎች በመምራት እምነታችንን ያጠናክሩልናል። (የሐዋርያት ሥራ 15:32) በተጨማሪም እነዚህ ለአምላክ ያደሩ ወንዶች በወንጌላዊነቱ ሥራ ግንባር ቀደም በመሆን በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች አብረውን ይካፈላሉ፤ እንዲሁም ሥልጠና ይሰጡናል።

      በግለሰብ ደረጃ ያበረታቱናል። የጉባኤያችን ሽማግሌዎች መንፈሳዊነታችንን እንድናጠናክር በግለሰብ ደረጃ ለመርዳት ሲሉ በየቤታችን እየመጡ ወይም በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ከቅዱሳን መጻሕፍት ማጽናኛና ማበረታቻ ይሰጡናል።—ያዕቆብ 5:14, 15

      አብዛኞቹ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ከሚያከናውኑት ሥራ በተጨማሪ ጊዜያቸውንና ትኩረታቸውን የሚጠይቁ ሌሎች ኃላፊነቶች አሏቸው፤ ከእነዚህም መካከል ሰብዓዊ ሥራቸውና የቤተሰብ ኃላፊነታቸው ይገኙበታል። በመሆኑም እነዚህን ትጉ ወንድሞቻችንን ልናከብራቸው ይገባል።—1 ተሰሎንቄ 5:12, 13

      • ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ምን ኃላፊነት አለባቸው?

      • ሽማግሌዎች በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስቡልን የሚያሳዩት በምን መንገዶች ነው?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      ሽማግሌ ሆነው ለማገልገል ብቁ የሚሆኑት እነማን ናቸው? ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ሊያሟሏቸው የሚገቡትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች በ1 ጢሞቴዎስ 3:1-10, 12 እና በቲቶ 1:5-9 ላይ ማግኘት ትችላለህ።

  • የጉባኤ አገልጋዮች ምን ሚና ይጫወታሉ?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 16

      የጉባኤ አገልጋዮች ምን ሚና ይጫወታሉ?

      አንድ የጉባኤ አገልጋይ ጽሑፍ ሲያከፋፍል

      ምያንማር

      አንድ የጉባኤ አገልጋይ መንፈሳዊ ትምህርት ሲሰጥ

      ክፍል ማቅረብ

      አንድ የጉባኤ አገልጋይ ስብሰባ ሲመራ

      የስምሪት ስብሰባ መምራት

      አንድ የጉባኤ አገልጋይ የመንግሥት አዳራሹን በመንከባከቡ ሥራ ላይ ሲካፈል

      የስብሰባ አዳራሹን መንከባከብ

      በጉባኤ ውስጥ በኃላፊነት የሚያገለግሉ ክርስቲያን ወንዶች በሁለት እንደሚከፈሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፤ እነሱም ‘ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች’ ናቸው። (ፊልጵስዩስ 1:1) አብዛኛውን ጊዜ በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ እነዚህን ኃላፊነቶች የሚወጡ በርካታ ወንድሞች ይኖራሉ። ታዲያ የጉባኤ አገልጋዮች እኛን የሚጠቅሙ ምን ሥራዎችን ያከናውናሉ?

      የሽማግሌዎች አካልን ያግዛሉ። በየትኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ የጉባኤ አገልጋዮች መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው፣ እምነት የሚጣልባቸውና በትጋት የሚሠሩ ወንድሞች ናቸው። ከድርጅታዊ አሠራር ጋር የተያያዙ እንዲሁም የስብሰባ አዳራሹን የሚመለከቱ ተደጋጋሚ ሆኖም አስፈላጊ ሥራዎችን ያከናውናሉ። የጉባኤ አገልጋዮች እነዚህን ሥራዎች በማከናወናቸው ሽማግሌዎች በማስተማርና በእረኝነት ሥራዎች ላይ ማተኮር ይችላሉ።

      ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት ይሰጣሉ። አንዳንድ የጉባኤ አገልጋዮች፣ ወደ ስብሰባ ለሚመጡ ሁሉ ጥሩ አቀባበል እንዲያደርጉ አስተናጋጅ ሆነው ይመደባሉ። ሌሎች ደግሞ በድምፅ ወይም በጽሑፍ ክፍል ውስጥ ያገለግላሉ፤ የሒሳብ አገልጋይ ሆነው ይሠራሉ፤ አሊያም የጉባኤው አባላት የሚሰብኩባቸውን ክልሎች ያከፋፍላሉ። በተጨማሪም የስብሰባ አዳራሹ በአግባቡ እንዲያዝ በማድረግ ረገድ እርዳታ ያበረክታሉ። ከዚህም ሌላ የጉባኤ አገልጋዮች፣ አረጋውያንን እንዲረዱ ሽማግሌዎች ሊጠይቋቸው ይችላሉ። የጉባኤ አገልጋዮች ምንም ዓይነት ኃላፊነት ቢሰጣቸው ሥራቸውን በፈቃደኝነት ስለሚያከናውኑ ሁሉም የጉባኤው አባላት ሊያከብሯቸው ይገባል።—1 ጢሞቴዎስ 3:13

      ግሩም ምሳሌ የሚሆኑ ክርስቲያን ወንዶች ናቸው። ክርስቲያን ወንዶች፣ የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሆኑ የሚሾሙት ጥሩ መንፈሳዊ ባሕርያት ስላሏቸው ነው። የጉባኤ አገልጋዮች በስብሰባዎች ላይ ክፍል በማቅረብ እምነታችንን ያጠናክሩልናል። በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት በመካፈል በቅንዓት እንድናገለግል ያነሳሱናል። ከሽማግሌዎች ጋር ተባብረው በመሥራት በጉባኤው ውስጥ ደስታና አንድነት እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። (ኤፌሶን 4:16) ውሎ አድሮ ደግሞ እነሱም ሽማግሌ ሆነው ለማገልገል የሚያስፈልገውን ብቃት ሊያሟሉ ይችላሉ።

      • የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው የሚሾሙት ምን ዓይነት ወንዶች ናቸው?

      • አገልጋዮች የጉባኤው እንቅስቃሴ የተቀላጠፈ እንዲሆን የሚረዱት እንዴት ነው?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      ስብሰባ ላይ ስትገኝ ጊዜ ወስደህ ከሽማግሌዎች ወይም ከጉባኤ አገልጋዮች መካከል ከአንዱ ጋር ለመተዋወቅ ጥረት አድርግ፤ በዚህ መንገድ ሁሉንም ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውን በደንብ ማወቅ ትችላለህ።

  • የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 17

      የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

      አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ከባለቤቱ ጋር

      ማላዊ

      አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች የስምሪት ስብሰባ ሲመራ

      የስምሪት ስብሰባ

      አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በስብከቱ ሥራ ላይ

      የመስክ አገልግሎት

      አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ስብሰባ ሲያደርግ

      የሽማግሌዎች ስብሰባ

      የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ስለ በርናባስና ስለ ሐዋርያው ጳውሎስ በተደጋጋሚ ይጠቅሳሉ። እነዚህ ወንድሞች ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች በመሆን የጥንቶቹን ጉባኤዎች ይጎበኙ ነበር። ይህን ያደርጉ የነበረው ለምንድን ነው? ስለ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ደህንነት ከልባቸው ያስቡ ስለነበር ነው። ጳውሎስ “ወንድሞች በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማወቅ” ሲል ‘ተመልሶ ሊጠይቃቸው’ እንደሚፈልግ ተናግሯል። እነሱን ሄዶ ለማበረታታት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ለመጓዝ ፈቃደኛ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 15:36) ዛሬም ያሉት ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ተመሳሳይ ስሜት አላቸው።

      ማበረታቻ ይሰጡናል። እያንዳንዱ የወረዳ የበላይ ተመልካች ወደ 20 ገደማ የሚሆኑ ጉባኤዎችን በዓመት ሁለት ጊዜ የሚጎበኝ ሲሆን በእያንዳንዱ ጉብኝት ወቅት ከጉባኤው ጋር ለአንድ ሳምንት ይቆያል። ከእነዚህ ወንድሞችና ያገቡ ከሆኑ ደግሞ ከሚስቶቻቸው ተሞክሮም ብዙ ጥቅም ልናገኝ እንችላለን። የወረዳ የበላይ ተመልካቾችም ሆኑ ሚስቶቻቸው፣ ወጣት ሽማግሌ ሳይሉ ከሁላችንም ጋር ለመተዋወቅ ጥረት ያደርጋሉ፤ በተጨማሪም አብረውን በመስክ አገልግሎት ለመሰማራትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ለማስጠናት ይፈልጋሉ። እነዚህ የበላይ ተመልካቾች ከሽማግሌዎች ጋር ሆነው እረኝነት ያደርጋሉ፤ እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የሚያበረታቱና እምነትን የሚያጠናክሩ ንግግሮች ያቀርባሉ።—የሐዋርያት ሥራ 15:35

      ለሁሉም አሳቢነት ያሳያሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾች የጉባኤዎች መንፈሳዊ ሁኔታ ከልብ ያሳስባቸዋል። ስለ ጉባኤው እንቅስቃሴ ለመወያየት ከሽማግሌዎችና ከጉባኤ አገልጋዮች ጋር ስብሰባ የሚያደርጉ ሲሆን ለእነዚህ ወንድሞች ኃላፊነቶቻቸውን ከሚወጡበት መንገድ ጋር በተያያዘ ጠቃሚ ምክር ይለግሷቸዋል። አቅኚዎች በአገልግሎታቸው ውጤታማ መሆን እንዲችሉ ይረዷቸዋል፤ እንዲሁም ከአዳዲሶች ጋር መጨዋወትና ስላደረጉት መንፈሳዊ እድገት መስማት በጣም ያስደስታቸዋል። ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡት እነዚህ ወንድሞች በሙሉ ‘ለእኛ ጥቅም አብረውን የሚሠሩ ባልደረቦቻችን’ ናቸው። (2 ቆሮንቶስ 8:23) በመሆኑም እምነታቸውንና ለአምላክ ያደሩ በመሆን ረገድ የሚተዉትን ምሳሌ መከተል አለብን።—ዕብራውያን 13:7

      • የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጉባኤዎችን የሚጎበኙበት ዓላማ ምንድን ነው?

      • ከጉብኝታቸው ጥቅም ልታገኝ የምትችለው እንዴት ነው?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤያችሁን የሚጎበኝባቸው ቀናት ሲነገሩ ማስታወሻህ ላይ መጻፍህ በስብሰባ አዳራሹ የሚሰጠው ንግግር እንዳያመልጥህ ለማድረግ ይረዳሃል። ከእሱ ወይም ከባለቤቱ ጋር በደንብ ለመተዋወቅ እንድትችል በዚያ ሳምንት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ላይ እንዲገኙ ከፈለግክ ለአስጠኚህ ንገረው።

  • አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጠማቸውን ወንድሞቻችንን የምንረዳው እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 18

      አስቸጋሪ ሁኔታ ያጋጠማቸውን ወንድሞቻችንን የምንረዳው እንዴት ነው?

      የይሖዋ ምሥክሮች ዶሚኒካን ሪፑብሊክ ውስጥ አደጋ የደረሰባቸውን ሲረዱ

      ዶሚኒካን ሪፑብሊክ

      የእርዳታ ሠራተኞች ጃፓን ውስጥ የፈረሰን የመንግሥት አዳራሽ መልሰው ሲገነቡ

      ጃፓን

      አንድ የይሖዋ ምሥክር በሄይቲ በደረሰው የተፈጥሮ አደጋ የተጎዳን ሰው ሲያጽናና

      ሄይቲ

      ድንገተኛ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በአደጋው የተጎዱ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ወዲያውኑ ዝግጅት ያደርጋሉ። እንዲህ ያለው ጥረት በመካከላቸው ያለው ፍቅር ከልብ የመነጨ መሆኑን ያሳያል። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 1 ዮሐንስ 3:17, 18) ታዲያ ወንድሞቻችንን በየትኞቹ መንገዶች መርዳት እንችላለን?

      ገንዘብ እናዋጣለን። በይሁዳ ታላቅ ረሃብ በተከሰተ ጊዜ በአንጾኪያ የነበሩ የጥንት ክርስቲያኖች ለመንፈሳዊ ወንድሞቻቸው የገንዘብ እርዳታ ልከው ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 11:27-30) በተመሳሳይም በአንድ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ወንድሞቻችን ከባድ ችግር እንዳጋጠማቸው ስናውቅ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት እንዲቻል በጉባኤያችን በኩል የገንዘብ መዋጮ እንልካለን።—2 ቆሮንቶስ 8:13-15

      በተግባር የተደገፈ እርዳታ እንሰጣለን። ድንገተኛ አደጋ በደረሰባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሽማግሌዎች እያንዳንዱ የጉባኤ አባል የት እንዳለና ደህንነቱን ያጣራሉ። የአደጋ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴ ተጎጂዎቹ ምግብ፣ ንጹሕ ውኃ፣ ልብስ፣ መጠለያና የሕክምና አገልገሎት ማግኘት የሚችሉበትን ዝግጅት ያስተባብራል። በዚህ ጊዜ ተፈላጊ የሆኑ ሙያዎች ያሏቸው በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ወጪያቸውን ችለው በእርዳታ አቅርቦት ሥራ ለመካፈል ወይም የተጎዱ ቤቶችንና የስብሰባ አዳራሾችን ለመጠገን ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀርባሉ። አንድነት ስላለንና አብረን በመሥራት ረገድ ልምድ ስላካበትን እንደዚህ ባሉት ጊዜያት የሚያስፈልጉትን የእርዳታ ቁሳቁሶችና ሠራተኞች በፍጥነት ማሰባሰብ እንችላለን። በዋነኝነት የእርዳታ እጃችንን የምንዘረጋው “በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች” ቢሆንም በሚቻለን ጊዜ ሁሉ እገሌ ከገሌ ሳንል የማንኛውም ሃይማኖት አባላት የሆኑ ሰዎችንም እንረዳለን።—ገላትያ 6:10

      መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ እንሰጣለን። አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች ከሌሎች ይበልጥ ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል። እንደነዚህ ባሉት ጊዜያት ብርታት የምናገኘው “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” ከሆነው ከይሖዋ ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) በጭንቀት ላይ ለሚገኙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋዎች በደስታ በመናገር በቅርቡ የአምላክ መንግሥት የመከራና የሥቃይ ምክንያት የሚሆኑ ነገሮችን በሙሉ እንደሚያስወግድ እናረጋግጥላቸዋለን።—ራእይ 21:4

      • የይሖዋ ምሥክሮች አደጋ በሚደርስበት ጊዜ አፋጣኝ እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ የሆኑት ለምንድን ነው?

      • ከአደጋ ለተረፉ ሰዎች ምን ዓይነት መንፈሳዊ ማጽናኛ መስጠት እንችላለን?

  • ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 19

      ታማኝና ልባም ባሪያ ማን ነው?

      ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲነጋገር
      አንዲት የይሖዋ ምሥክር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ጽሑፍ ስታጠና

      ሁላችንም ከሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ ጥቅም እናገኛለን

      ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል አባላት

      ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ አራት ደቀ መዛሙርቱ ይኸውም ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ዮሐንስና እንድርያስ ወደ እሱ ለብቻቸው መጥተው አነጋግረውት ነበር። ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን የእሱን መገኘት የሚያሳውቀውን ምልክት በሚናገርበት ወቅት እንደሚከተለው በማለት አንድ ወሳኝ ጥያቄ አነሳ፦ “በተገቢው ጊዜ ምግባቸውን እንዲሰጣቸው ጌታው በቤተሰቦቹ ላይ የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ በእርግጥ ማን ነው?” (ማቴዎስ 24:3, 45፤ ማርቆስ 13:3, 4) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ይህን ጥያቄ ሲያቀርብ ‘ጌታቸው’ እንደመሆኑ መጠን በመጨረሻው ዘመን ለተከታዮቹ ሳያሰልሱ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርቡ ሰዎችን እንደሚሾም ማረጋገጡ ነበር። ታዲያ እነዚህ ሰዎች እነማን ናቸው?

      ጥቂት ቁጥር ያላቸው በመንፈስ የተቀቡ የኢየሱስ ተከታዮችን ያቀፈ ቡድን ነው። ‘ባሪያው’ የይሖዋ ምሥክሮችን የበላይ አካል ያመለክታል። አብረውት ይሖዋን ለሚያመልኩት የእምነት ባልንጀሮቹ ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ ያቀርባል። የሚያስፈልገንን “ምግብ በተገቢው ጊዜ” የምናገኘው ከታማኙ ባሪያ ነው።—ሉቃስ 12:42

      የአምላክን ቤተሰብ ያስተዳድራል። (1 ጢሞቴዎስ 3:15) ኢየሱስ፣ የይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል የሚያከናውነውን ሥራ የማስተዳደሩን ከባድ ኃላፊነት የሰጠው ለባሪያው ነው፤ ይህም ቁሳዊ ንብረቶቹን መቆጣጠርን፣ የስብከቱን ሥራ መምራትን እንዲሁም በጉባኤዎች በኩል እኛን ማስተማርን ይጨምራል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” በአገልግሎታችን ላይ በምንጠቀምባቸው ጽሑፎች እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎቻችን ላይ በሚቀርቡት ትምህርቶች አማካኝነት የሚያስፈልገንን መንፈሳዊ ምግብ በተገቢው ጊዜ እያቀረበልን ነው።

      ባሪያው ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችና ምሥራቹን እንዲሰብክ ለተሰጠው ኃላፊነት ታማኝ ሲሆን በምድር ላይ የሚገኘውን የክርስቶስ ንብረት በጥበብ በማስተዳደርም ልባም መሆኑን አሳይቷል። (የሐዋርያት ሥራ 10:42) ይሖዋ የሕዝቦቹ ቁጥር እንዲያድግ በማድረግ እንዲሁም ባሪያው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ዝግጅት እንዲያቀርብ በመርዳት ይህ ባሪያ የሚያከናውነውን ሥራ እየባረከው ነው።—ኢሳይያስ 60:22፤ 65:13

      • ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን በመንፈሳዊ እንዲመግብ የሾመው ማንን ነው?

      • ባሪያው፣ ታማኝና ልባም የሆነው በምን መንገዶች ነው?

  • በዛሬው ጊዜ የበላይ አካሉ ሥራውን የሚያከናውነው እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 20

      በዛሬው ጊዜ የበላይ አካሉ ሥራውን የሚያከናውነው እንዴት ነው?

      በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል

      የመጀመሪያው መቶ ዘመን የበላይ አካል

      በመጀመሪያው ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ከበላይ አካሉ የተላከውን ደብዳቤ ሲያነቡ

      የበላይ አካሉ ደብዳቤ ሲነበብ

      በአንደኛው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም የሚገኙ ‘ሐዋርያትንና ሽማግሌዎችን’ ያቀፈ አንድ ትንሽ ቡድን መላውን የቅቡዓን ክርስቲያኖች ጉባኤ ወክሎ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ውሳኔዎችን የሚያስተላልፍ የበላይ አካል ሆኖ አገልግሏል። (የሐዋርያት ሥራ 15:2) የዚህ የበላይ አካል አባላት በአንድ ድምፅ ውሳኔ ማስተላለፍ የቻሉት በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ስለተወያዩና የመንፈስ ቅዱስን አመራር ስለተከተሉ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 15:25) ዛሬም ያለው የበላይ አካል የእነሱን ምሳሌ ይከተላል።

      አምላክ ፈቃዱን ለማድረግ በበላይ አካሉ ይጠቀማል። የበላይ አካል አባላት ሆነው የሚያገለግሉት ቅቡዓን ወንድሞች ለአምላክ ቃል ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ሲሆን ከመንፈሳዊ ነገሮችም ሆነ ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የረጅም ጊዜ ልምድ ያካበቱ ናቸው። እነዚህ ወንድሞች ዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር ስለሚመለከቱ ጉዳዮች ለመወያየት በየሳምንቱ ስብሰባ ያደርጋሉ። በአንደኛው መቶ ዘመን ይደረግ እንደነበረው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረጉ መመሪያዎች የሚተላለፉት በደብዳቤዎች፣ በተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና በሌሎች ወንድሞች አማካኝነት ነው። ይህም የአምላክ ሕዝቦች አስተሳሰባቸውም ሆነ ተግባራቸው አንድ ዓይነት እንዲሆን አስችሏል። (የሐዋርያት ሥራ 16:4, 5) የበላይ አካሉ የመንፈሳዊ ምግቦችን ዝግጅት እንዲሁም ወንድሞች ለኃላፊነት ቦታ የሚሾሙበትን ሁኔታ በበላይነት ይከታተላል፤ በተጨማሪም ለመንግሥቱ ስብከት ሥራ ቅድሚያ እንድንሰጥ ያበረታታናል።

      የበላይ አካሉ የአምላክን መንፈስ አመራር ይከተላል። የበላይ አካሉ መመሪያ ለማግኘት የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ ወደሆነው ወደ ይሖዋና የጉባኤው ራስ ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ዘወር ይላል። (1 ቆሮንቶስ 11:3፤ ኤፌሶን 5:23) የበላይ አካሉ አባላት ራሳቸውን የአምላክ ሕዝቦች መሪዎች እንደሆኑ አድርገው አይቆጥሩም። እነሱም ሆኑ የቀሩት ቅቡዓን ክርስቲያኖች “ምንጊዜም በጉ [ኢየሱስ] በሄደበት ሁሉ ይከተሉታል።” (ራእይ 14:4) የበላይ አካሉ አባላት ስለ እነሱ ለምናቀርበው ጸሎት አመስጋኞች ናቸው።

      • በመጀመሪያው መቶ ዘመን የበላይ አካል አባላት የነበሩት እነማን ናቸው?

      • በዛሬው ጊዜ የበላይ አካሉ የአምላክን አመራር ለማግኘት ምን ያደርጋል?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል በቅዱሳን መጻሕፍትና በመንፈስ ቅዱስ አመራር በመታገዝ በአንድ ጉዳይ ላይ ተወያይቶ እልባት መስጠት የቻለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ የሐዋርያት ሥራ 15:1-35⁠ን አንብብ።

  • ቤቴል ምንድን ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 21

      ቤቴል ምንድን ነው?

      ቤቴል ውስጥ በሥነ ጥበብ ክፍል እየሠሩ ያሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች

      የሥነ ጥበብ ክፍል፣ ዩናይትድ ስቴትስ

      በጀርመን ቤቴል የሕትመት ክፍል ውስጥ  እየሠራ ያለ የይሖዋ ምሥክር

      ጀርመን

      በኬንያ ቤቴል የልብስ ንጽሕና ክፍል ውስጥ እየሠራች ያለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር

      ኬንያ

      በኮሎምቢያ ቤቴል የመመገቢያ አዳራሽ ውስጥ እየሠሩ ያሉ አስተናጋጆች

      ኮሎምቢያ

      ቤቴል የሚለው የዕብራይስጥ ስም “የአምላክ ቤት” የሚል ትርጉም አለው። (ዘፍጥረት 28:17, 19 የግርጌ ማስታወሻ) የይሖዋ ምሥክሮች ለስብከቱ ሥራ አመራርና ድጋፍ ለመስጠት የሚጠቀሙባቸው በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሕንፃዎች በዚህ መጠሪያ መሰየማቸው የተገባ ነው። የበላይ አካሉ የሚገኘው በኒው ዮርክ ግዛት፣ ዩናይትድ ስቴትስ ባለው ዋና መሥሪያ ቤት ሲሆን በበርካታ አገሮች የሚገኙትን ቅርንጫፍ ቢሮዎች እንቅስቃሴ ይከታተላል። በእነዚህ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚያገለግሉት ክርስቲያኖች በሙሉ የቤቴል ቤተሰብ በመባል ይታወቃሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ልክ እንደ ቤተሰብ አብረው ይኖራሉ፣ አብረው ይሠራሉ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን አብረው ያጠናሉ።—መዝሙር 133:1

      የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ቤተሰብ የሚኖርበት ልዩ ቦታ። በእያንዳንዱ ቤቴል ውስጥ ሙሉ ጊዜያቸውን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግና ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ለማከናወን የሚያውሉ ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ይገኛሉ። (ማቴዎስ 6:33) የሚኖሩበት ክፍልና ምግብ ይሟላላቸዋል፤ እንዲሁም የግል ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚያግዛቸው አነስተኛ አበል ይሰጣቸዋል። ከዚህ ውጭ ግን አንዳቸውም ቢሆኑ ደሞዝ አይከፈላቸውም። በቤቴል ውስጥ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ የራሳቸው የሥራ ምድብ ያላቸው ሲሆን አንዳንዶቹ ቢሮ ውስጥ ሌሎቹ ደግሞ ወጥ ቤት ወይም መመገቢያ አዳራሽ ውስጥ እንዲሠሩ ይመደባሉ። በሕትመትና በመጻሕፍት መጠረዣ ክፍል፣ በቤት ጽዳት፣ በልብስ እጥበት፣ በጥገና ክፍል እንዲሁም በሌሎች ክፍሎች ውስጥ የሚሠሩም አሉ።

      የስብከቱን ሥራ የሚደግፉ ሰዎች የሚገኙበት ሥራ የበዛበት ቦታ። የሁሉም ቤቴሎች ዋነኛ ዓላማ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች ማዳረስ ነው። ይህ ብሮሹር ለዚህ አንድ ምሳሌ ነው። የተጻፈው በበላይ አካሉ አመራር ሲሆን በኤሌክትሮኒክ ቅጂ ተዘጋጅቶ በመላው ዓለም ወደሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትርጉም ቡድኖች ተሰራጨ፤ ከዚያም ከፍተኛ ፍጥነት ባላቸው የተለያዩ የቤቴል ማተሚያ ቤቶች ከታተመ በኋላ ከ110,000 በላይ ወደሆኑት ጉባኤዎች ተላከ። በእያንዳንዱ ሂደት ላይ የቤቴል ቤተሰቦች እጅግ አጣዳፊ ለሆነው ምሥራቹን የመስበክ ሥራ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።—ማርቆስ 13:10

      • በቤቴል የሚያገለግሉት ምን ዓይነት ሰዎች ናቸው? ምን ዝግጅትስ ይደረግላቸዋል?

      • በእያንዳንዱ ቤቴል የሚከናወነው እንቅስቃሴ የትኛውን አጣዳፊ ሥራ ይደግፋል?

  • በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ምን ዓይነት ሥራ ይከናወናል?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 22

      በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ምን ዓይነት ሥራ ይከናወናል?

      በሰለሞን ደሴቶች ቅርንጫፍ ቢሮ የሚካሄደውን ሥራ የሚያደራጁ ወንድሞች

      የሰለሞን ደሴቶች

      በካናዳ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግል አንድ የይሖዋ ምሥክር

      ካናዳ

      ጽሑፎችን የሚያጓጉዙ ከባድ መኪናዎች

      ደቡብ አፍሪካ

      የቤቴል ቤተሰብ አባላት በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ ተመድበው የሚያገለግሉ ሲሆን በአገራቸው ወይም በሌሎች አገሮች ከሚከናወነው የስብከት እንቅስቃሴ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ያከናውናሉ። ቤቴላውያን በትርጉም ቡድኖች ውስጥ፣ በመጽሔቶች ሕትመት፣ በመጻሕፍት ጥረዛና በጽሑፍ ማቆያ እንዲሁም በድምፅ/ምስል ቀረጻ ክፍል ውስጥ ይሠራሉ፤ አሊያም በቅርንጫፍ ቢሮው ሥር ካሉ አካባቢዎች ጋር የተያያዙ ሌሎች ሥራዎችን ያከናውናሉ።

      የቅርንጫፍ ኮሚቴ፣ ሥራውን በበላይነት ይከታተላል። የበላይ አካሉ የእያንዳንዱን ቅርንጫፍ ቢሮ እንቅስቃሴ የሚከታተል የቅርንጫፍ ኮሚቴ ይሾማል፤ ይህ ኮሚቴ ሦስት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ብቃት ያላቸው ሽማግሌዎችን ያቀፈ ነው። የቅርንጫፍ ኮሚቴው በሥሩ በሚገኙት አገሮች ስላለው እንቅስቃሴና ስለተፈጠሩ ችግሮች ለበላይ አካሉ በየጊዜው ያሳውቃል። የበላይ አካሉም እነዚህን ሪፖርቶች መሠረት በማድረግ ወደፊት በሚወጡ ጽሑፎች እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ምን እንደሆነ ይወስናል። የበላይ አካሉ ተወካዮች ቅርንጫፍ ቢሮዎችን እንዲጎበኙ በየጊዜው የሚላኩ ሲሆን እነዚህ የበላይ ተመልካቾች ለቅርንጫፍ ኮሚቴ አባላት ሥራቸውን ስለሚያከናውኑበት መንገድ መመሪያ ይሰጧቸዋል። (ምሳሌ 11:14) በጉብኝቱ ወቅት በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ ለሚኖሩት ወንድሞች ማበረታቻ ለመስጠት ልዩ ፕሮግራም የሚዘጋጅ ሲሆን በዚህ ዝግጅት ላይ የዋና መሥሪያ ቤት ተወካዩ ንግግር ያቀርባል።

      ቅርንጫፍ ቢሮው በሥሩ ያሉ ጉባኤዎችን ይደግፋል። በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚገኙ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች የአዳዲስ ጉባኤዎችን መቋቋም ያጸድቃሉ። በተጨማሪም እነዚህ ወንድሞች በቅርንጫፍ ቢሮው ክልል ውስጥ የሚገኙ አቅኚዎች፣ ሚስዮናውያንና የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር በተያያዘ መመሪያ ይሰጣሉ። ትላልቅ ስብሰባዎችን ያደራጃሉ፣ የአዳዲስ ስብሰባ አዳራሾችን ግንባታ ያስተባብራሉ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ጉባኤ የሚያስፈልገው ጽሑፍ መላኩን ይከታተላሉ። በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚከናወኑ ሥራዎች በሙሉ የስብከቱ ሥራ ሥርዓት ባለው መልኩ እንዲከናወን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።—1 ቆሮንቶስ 14:33, 40

      • የቅርንጫፍ ኮሚቴዎች የበላይ አካሉን የሚያግዙት እንዴት ነው?

      • በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ምን ዓይነት ሥራ ይከናወናል?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      ማንኛውም ሰው ከሰኞ እስከ ዓርብ ባሉት ቀናት አስጎብኚ ተመድቦለት ቅርንጫፍ ቢሮዎቻችንን መጎብኘት ይችላል። አንተም ቤቴልን እንድትጎበኝ እንጋብዝሃለን። ለጉብኝት በምትሄድበት ጊዜ ስብሰባ ስትሄድ የሚኖርህ ዓይነት አለባበስ ይኑርህ። ቤቴልን መጎብኘትህ መንፈሳዊ ጥቅም ያስገኝልሃል።

  • ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁትና የሚተረጎሙት እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 23

      ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁትና የሚተረጎሙት እንዴት ነው?

      ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል እየሠራ ያለ ሰው

      የጽሑፍ ዝግጅት ክፍል፣ ዩናይትድ ስቴትስ

      በደቡብ ኮሪያ የሚገኝ አንድ የትርጉም ቡድን

      ደቡብ ኮሪያ

      አርሜንያ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች የተተረጎመ መጽሐፍ የያዘ ሰው

      አርሜንያ

      ቡሩንዲ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች የተተረጎመ መጽሐፍ የያዘች ልጅ

      ቡሩንዲ

      ስሪ ላንካ ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች የተተረጎሙ መጽሔቶችን የያዘች ሴት

      ስሪ ላንካ

      ‘ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ ምሥራቹን’ በማወጁ ሥራ የተቻለንን ለማድረግ ስንል ከ750 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ጽሑፎችን እናዘጋጃለን። (ራእይ 14:6) ይህን ከባድ ሥራ የምንወጣው እንዴት ነው? በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ጸሐፊዎችና በርካታ ተርጓሚዎች እገዛ ሲሆን በሥራው ላይ የሚካፈሉት በሙሉ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።

      ዋናው ጽሑፍ በእንግሊዝኛ ይዘጋጃል። የበላይ አካሉ በዋናው መሥሪያ ቤታችን የሚገኘውን የጽሑፍ ዝግጅት ክፍል እንቅስቃሴ በበላይነት ይቆጣጠራል። ይህ ክፍል፣ በዋናው መሥሪያ ቤትና በአንዳንድ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ ሆነው የሚሠሩት ጸሐፊዎች የሚያከናውኑትን ሥራ ይከታተላል። የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ጸሐፊዎች መኖራቸው ጽሑፎቻችን በልዩ ልዩ ባሕሎች ውስጥ ያሉ ሰዎችን የሚማርኩ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ እንዲሆኑ አድርጓል፤ ይህም ጽሑፎቹ ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት እንዲያገኙ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

      ጽሑፉ ለተርጓሚዎች ይላካል። የተዘጋጀው ጽሑፍ ከታረመና እንዲወጣ ከጸደቀ በኋላ በምድር ዙሪያ ወደሚገኙ የትርጉም ቡድኖች በኤሌክትሮኒክ ፋይል ይላካል፤ እነዚህ ቡድኖች ጽሑፉን የሚተረጉሙ፣ ትርጉሙን ከእንግሊዝኛው ጋር እያመሳከሩ የሚያርሙና የማጣሪያ ንባብ የሚያከናውኑ ተርጓሚዎችን ያቀፉ ናቸው። ተርጓሚዎቹ የእንግሊዝኛውን መልእክት፣ በሚተረጉሙበት ቋንቋ ሙሉ በሙሉ ለማስተላለፍ የሚያስችላቸውን ‘ትክክለኛውን ቃል’ ለመምረጥ ጥረት ያደርጋሉ።—መክብብ 12:10

      ኮምፒውተር ሥራውን ያቀላጥፈዋል። ኮምፒውተር፣ ጸሐፊዎችና ተርጓሚዎች የሚያከናውኑትን ሥራ መተካት አይችልም። ይሁን እንጂ ተርጓሚዎች፣ መዝገበ ቃላቶችንና ለትርጉም ሥራ የሚያግዙ ሌሎች ጽሑፎችን በኮምፒውተር ማግኘታቸው ሥራቸውን ለማፋጠን ይረዳቸዋል። በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች መልቲላንጉዌጅ ኤሌክትሮኒክ ፐብሊሺንግ ሲስተም (ሜፕስ) የተባለ የኮምፒውተር ፕሮግራም ሠርተዋል፤ ይህ ፕሮግራም ትርጉሙን በመቶዎች በሚቆጠሩ ቋንቋዎች ለመጻፍ፣ ጽሑፉን ከሥዕሉ ጋር ለማቀናበርና ለሕትመት ለማዘጋጀት ያስችላል።

      በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩ ተናጋሪዎች ብቻ ባሏቸው ቋንቋዎች እንኳ ጽሑፎቻችንን ለመተርጎም ይህን ያህል ጥረት የምናደርገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የይሖዋ ፈቃድ “ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ” ስለሆነ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4

      • ጽሑፎቻችን የሚዘጋጁት እንዴት ነው?

      • ጽሑፎቻችንን በበርካታ ቋንቋዎች የምንተረጉመው ለምንድን ነው?

  • በዓለም ዙሪያ ለምናከናውነው ሥራ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የምናገኘው እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 24

      በዓለም ዙሪያ ለምናከናውነው ሥራ የሚያስፈልገውን ገንዘብ የምናገኘው እንዴት ነው?

      በፈቃደኝነት ተነሳስቶ መዋጮ የሚያደርግ ሰው
      የይሖዋ ምሥክሮች እየሰበኩ

      ኔፓል

      በቶጎ በሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ቡድን ውስጥ የሚያገለግሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች

      ቶጎ

      በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ የሚያገለግሉት ፈቃደኛ ሠራተኞች

      ብሪታንያ

      ድርጅታችን በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶችንና ሌሎች ጽሑፎችን አትሞ ያለ ምንም ክፍያ ያሰራጫል። የስብሰባ አዳራሾችንና ቅርንጫፍ ቢሮዎችን እንገነባለን እንዲሁም እንጠግናለን። በሺዎች የሚቆጠሩት ቤቴላውያንና ሚስዮናውያን የሚያስፈልጓቸው ነገሮች እንዲሟሉላቸው እናደርጋለን፤ እንዲሁም አደጋ በሚደርስበት ጊዜ እርዳታ እንሰጣለን። ‘ታዲያ ለእነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚሆን ገንዘብ የሚገኘው ከየት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

      አሥራት ወይም የአባልነት ክፍያ አንጠይቅም፤ ሙዳየ ምጽዋትም አናዞርም። የወንጌላዊነት ሥራችንን ማከናወን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ቢሆንም የገንዘብ እርዳታ አንጠይቅም። ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የወጣው የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሁለተኛ እትም፣ ‘ይሖዋ እንደሚደግፈን ስለምናምን ከሰዎች ድጋፍ ለማግኘት በፍጹም እንደማንለምን ወይም እንደማንማጠን’ ገልጾ ነበር፤ ደግሞም እንዲህ አድርገን አናውቅም!—ማቴዎስ 10:8

      ለሥራችን የገንዘብ ድጋፍ የምናገኘው በፈቃደኝነት ከሚሰጥ መዋጮ ነው። ብዙ ሰዎች ለምናከናውነው መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር ሥራ አድናቆት ስላላቸው የገንዘብ መዋጮ ያደርጋሉ። የይሖዋ ምሥክሮችም በመላው ምድር ለሚከናወነው የአምላክን ፈቃድ የመፈጸም ሥራ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ሌላ ጥሪታቸውን በደስታ ይሰጣሉ። (1 ዜና መዋዕል 29:9) በስብሰባ አዳራሾች ውስጥ እንዲሁም በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መዋጮ ለማድረግ የሚፈልጉ ሰዎች መዋጯቸውን የሚያስገቡባቸው ሣጥኖች ይገኛሉ። መዋጮ ለማድረግ jw.org/am የተባለውን ድረ ገጻችንንም መጠቀም ይቻላል። መዋጮ ሣጥኖች ውስጥ ከሚገኘው ገንዘብ አብዛኛውን የሚያዋጡት፣ ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች በቤተ መቅደሱ መዋጮ ዕቃ ውስጥ በመጨመሯ ኢየሱስ እንዳመሰገናት ድሃ መበለት ያሉ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች ናቸው። (ሉቃስ 21:1-4) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ማንኛውም ሰው “በልቡ ያሰበውን” መስጠት እንዲችል በየጊዜው ‘የተወሰነ ገንዘብ ማስቀመጥ’ ይችላል።—1 ቆሮንቶስ 16:2፤ 2 ቆሮንቶስ 9:7

      የተለያዩ ሰዎች፣ በሚያደርጉት መዋጮ አማካኝነት የመንግሥቱን ስብከት ሥራ በመደገፍ የአምላክ ፈቃድ እንዲፈጸም አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፤ ይሖዋም ‘ባሏቸው ውድ ነገሮች እሱን ማክበር’ የሚፈልጉትን የእነዚህን ሰዎች ልብ ማነሳሳቱን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን።—ምሳሌ 3:9

      • ድርጅታችንን ከሌሎች ሃይማኖቶች የሚለየው ምንድን ነው?

      • በፈቃደኝነት የሚደረጉትን መዋጮዎች የምንጠቀምባቸው እንዴት ነው?

  • የስብሰባ አዳራሾችን የምንሠራው ለምንድን ነው? የሚገነቡትስ እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 25

      የስብሰባ አዳራሾችን የምንሠራው ለምንድን ነው? የሚገነቡትስ እንዴት ነው?

      በቦሊቪያ የሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ቡድን

      ቦሊቪያ

      በናይጄሪያ የሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ እንደገና ከመገንባቱ በፊት
      በናይጄሪያ የሚገኝ አንድ የስብሰባ አዳራሽ እንደገና ከተገነባ በኋላ

      ናይጄሪያ፣ በፊትና አሁን

      በታሂቲ የስብሰባ አዳራሽ ሲገነባ

      ታሂቲ

      በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የሚሰጠው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያጠነጥነው የኢየሱስ አገልግሎት ዋነኛ ጭብጥ በነበረው በአምላክ መንግሥት ዙሪያ ነው።—ሉቃስ 8:1

      በማኅበረሰቡ ውስጥ የእውነተኛ አምልኮ ማዕከል ናቸው። የመንግሥቱን ምሥራች የመስበኩ ሥራ የሚደራጀው በእነዚህ የስብሰባ አዳራሾች ነው። (ማቴዎስ 24:14) የስብሰባ አዳራሾች መጠናቸውም ሆነ አሠራራቸው ይለያይ እንጂ ሁሉም ልከኛ የሆኑ የመሰብሰቢያ ቦታዎች ናቸው፤ በአብዛኛው በአንድ አዳራሽ ውስጥ ከአንድ የሚበልጡ ጉባኤዎች ይሰበሰባሉ። በቅርብ ዓመታት ውስጥ የጉባኤዎቻችን ቁጥር በጣም በመጨመሩ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ (በአማካይ በየቀኑ አምስት) አዳዲስ የስብሰባ አዳራሾችን ገንብተናል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?—ማቴዎስ 19:26

      አዳራሾቹ የሚገነቡት ለዚህ ዓላማ በሚደረጉ መዋጮዎች ነው። እነዚህ መዋጮዎች ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው የሚላኩ ሲሆን የስብሰባ አዳራሽ መገንባት ወይም ማደስ የሚያስፈልጋቸው ጉባኤዎች በዚህ ገንዘብ መጠቀም ይችላሉ።

      አዳራሾቹን የሚገነቡት ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ ደሞዝ የማይከፈላቸው ፈቃደኛ ሠራተኞች ናቸው። በብዙ አገሮች የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ቡድኖች አሉ። የግንባታ አገልጋዮችና ሌሎች ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚገኙባቸው ቡድኖች በአንድ አገር ውስጥ ከጉባኤ ወደ ጉባኤ አልፎ ተርፎም በጣም ሩቅ ወደሆኑ አካባቢዎች እየሄዱ ጉባኤዎች የራሳቸውን የስብሰባ አዳራሽ መገንባት እንዲችሉ እገዛ ያበረክታሉ። በሌሎች አገሮች ደግሞ ብቃት ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በተመደበላቸው አካባቢ ውስጥ የሚከናወኑትን የስብሰባ አዳራሽ ግንባታና እድሳት ሥራዎች እንዲከታተሉ ይሾማሉ። በፈቃደኝነት በሥራው የሚካፈሉ ችሎታ ያላቸው በርካታ ባለሙያዎች ቢኖሩም እንኳ በእያንዳንዱ የግንባታ ቦታ አብዛኛውን የግንባታ ሥራ የሚያከናውኑት የጉባኤው አባላት ናቸው። ይህ ሁሉ ሥራ መከናወን የቻለው በይሖዋ መንፈስ ድጋፍና የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ነፍሳቸው በሚያደርጉት እገዛ ነው።—መዝሙር 127:1፤ ቆላስይስ 3:23

      • የስብሰባ አዳራሾችን የምንገነባው ለምንድን ነው?

      • በመላው ዓለም የስብሰባ አዳራሾችን መገንባት የተቻለው እንዴት ነው?

  • የስብሰባ አዳራሻችንን በመንከባከብ ረገድ አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 26

      የስብሰባ አዳራሻችንን በመንከባከብ ረገድ አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

      ኢስቶንያ ውስጥ የስብሰባ አዳራሻቸውን የሚያጸዱ የይሖዋ ምሥክሮች

      ኢስቶንያ

      ዚምባብዌ ውስጥ የስብሰባ አዳራሻቸውን የሚያጸዱ የይሖዋ ምሥክሮች

      ዚምባብዌ

      በሞንጎሊያ በሚገኝ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አምፖል እየቀየረ ያለ የይሖዋ ምሥክር

      ሞንጎሊያ

      ፖርቶ ሪኮ ውስጥ ያለን አንድ የስብሰባ አዳራሽ ቀለም እየቀባ ያለ የይሖዋ ምሥክር

      ፖርቶ ሪኮ

      እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክሮች የስብሰባ አዳራሽ የአምላክ ቅዱስ ስም ይጠራበታል። በመሆኑም የሕንፃውን ንጽሕናና ውበት በመጠበቁ እንዲሁም አዳራሹን በማደሱ ሥራ መካፈልን እንደ ትልቅ መብት የምንመለከተው ከመሆኑም ሌላ ቅዱስ የሆነው አምልኳችን ክፍል እንደሆነ አድርገን እንቆጥረዋለን። በዚህ ሥራ ሁሉም ሰው መካፈል ይችላል።

      ከስብሰባዎች በኋላ በሚደረገው መጠነኛ ጽዳት ተካፈል። ወንድሞችና እህቶች ከእያንዳንዱ ስብሰባ በኋላ በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ቀለል ያለ ጽዳት ማከናወን ያስደስታቸዋል። በሳምንት አንድ ጊዜ ደግሞ ይበልጥ ሰፋ ያለ ጽዳት ይደረጋል። አንድ ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ጽዳቱ የሚያካትታቸው ነገሮች የተጻፉበትን ዝርዝር በመያዝ ሥራውን ያስተባብራል። ወንድሞችና እህቶች እንደ አስፈላጊነቱ ወለሉን ይጠርጋሉ፣ ይወለውላሉ፣ አቧራ ያነሳሉ፣ ወንበሮችን ያስተካክላሉ፣ መጸዳጃ ቤቶችን ያጸዳሉ፣ መስተዋቶችን ይወለውላሉ፣ ቆሻሻ ይደፋሉ፣ ግቢውን ያጸዳሉ እንዲሁም አትክልቶችን ይንከባከባሉ። ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ አዳራሹ የተሟላ ጽዳት ይደረግለታል። ልጆቻችንም በአንዳንድ ሥራዎች እንዲካፈሉ በማድረግ ለአምልኮ ቦታችን አክብሮት እንዲኖራቸው ልናሠለጥናቸው እንችላለን።—መክብብ 5:1

      ለአዳራሹ ጥገና በሚደረግበት ጊዜ እገዛ አድርግ። በየዓመቱ የስብሰባ አዳራሹ ውስጡም ሆነ ውጭው በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ በደንብ ይገመገማል። ይህን መሠረት በማድረግ በየጊዜው የጥገና ሥራ ይከናወናል፤ ይህም አዳራሹ ምንጊዜም በጥሩ ሁኔታ እንዲገኝ ስለሚያደርግ አላስፈላጊ ከሆነ ወጪ ያድናል። (2 ዜና መዋዕል 24:13፤ 34:10) የስብሰባ አዳራሻችን ንጹሕና በተገቢው ሁኔታ የተያዘ ከሆነ አምላካችንን ለማምለክ የሚመጥን ይሆናል። በዚህ ሥራ በመካፈል ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና ለአምልኮ ቦታችን ያለንን አክብሮት እናሳያለን። (መዝሙር 122:1) አዳራሻችንን ጥሩ አድርገን መያዛችን የአካባቢው ሰዎች ስለ እኛ በጎ አመለካከት እንዲኖራቸውም ያደርጋል።—2 ቆሮንቶስ 6:3

      • የአምልኮ ቦታችንን ችላ ማለት የማይገባን ለምንድን ነው?

      • የስብሰባ አዳራሹን ንጽሕና ለመጠበቅ ምን ዝግጅቶች ተደርገዋል?

  • ከስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 27

      ከስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

      በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት እየተጠቀመ ያለ ሰው

      እስራኤል

      አንድ የይሖዋ ምሥክር ምርምር እያደረገ ያለን አንድ ወጣት ሲረዳ

      ቼክ ሪፑብሊክ

      አንዲት ትንሽ ልጅ በመዝሙር መጽሐፏ ላይ ስሟን ስትጽፍ

      ቤኒን

      በዎችታወር ላይብረሪ  ተጠቅሞ ምርምር እያደረገ ያለ ሰው

      ኬይመን ደሴቶች

      የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትህን ለማሳደግ የሚረዳህ ምርምር ማድረግ ትፈልጋለህ? ስለ አንድ ጥቅስ ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሰ አንድ ግለሰብ፣ ቦታ ወይም ሌላ ነገር ይበልጥ ለማወቅ ትፈልጋለህ? አሊያም በግል ባሳሰበህ አንድ ጉዳይ ረገድ ሊረዳህ የሚችል ሐሳብ በአምላክ ቃል ውስጥ ይገኝ እንደሆነ ምርምር ለማድረግ አስበሃል? ከሆነ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ለምን ጎራ አትልም?

      ጠቃሚ የሆኑ የምርምር መሣሪያዎች ይገኙበታል። የይሖዋ ምሥክሮች በቋንቋህ ያዘጋጇቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎች በሙሉ አይኖሩህ ይሆናል። በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ግን በቅርብ የወጡት ብዙዎቹ ጽሑፎች ይገኛሉ። በተጨማሪም የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች፣ ጥሩ መዝገበ ቃላትና ሌሎች ጠቃሚ የማመሳከሪያ መጻሕፍት ሊኖሩ ይችላሉ። ከስብሰባ በፊትና በኋላ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ባሉት መሣሪያዎች መጠቀም ትችላለህ። ቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ ኮምፒውተር ካለ ደግሞ ዎችታወር ላይብረሪ የተባለው ፕሮግራም ይኖረዋል። ይህ ፕሮግራም በርካታ ጽሑፎቻችንን የያዘ ሲሆን አንድን ቃል፣ ጥቅስ ወይም ርዕሰ ጉዳይ ፈልጎ በማውጣት በቀላሉ ምርምር ለማድረግ ያስችላል።

      በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ለሚካፈሉ ተማሪዎች ጠቃሚ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ ክፍል እንድታቀርብ ከተመደብክ በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ተጠቅመህ ክፍልህን መዘጋጀት ትችላለህ። የቤተ መጻሕፍቱን ሁኔታ የመከታተል ኃላፊነት ያለበት የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ የበላይ ተመልካች ነው። በቅርብ የወጡ ጽሑፎች በሙሉ መግባታቸውንና በሚገባ ተስተካክለው መቀመጣቸውን መከታተል የእሱ ኃላፊነት ነው። የምትፈልገውን መረጃ እንዴት እንደምታገኝ የስብሰባው የበላይ ተመልካች ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪህ ሊያሳዩህ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ማንኛውንም ጽሑፍ ከስብሰባ አዳራሹ ይዞ መውጣት አይቻልም። መጻሕፍቱን በአግባቡ መያዝ እንዳለብንና ጽሑፎቹ ላይ ምንም ዓይነት ምልክት ማድረግ እንደማይገባንም የታወቀ ነው።

      ‘ስለ አምላክ እውቀት መቅሰም’ ከፈለግን “እንደተሸሸገ ሀብት” አጥብቀን ልንሻው እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ምሳሌ 2:1-5) እንዲህ ያለውን እውቀት ለማግኘት በምታደርገው ፍለጋ በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙት መሣሪያዎች ሊረዱህ ይችላሉ።

      • በስብሰባ አዳራሹ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ምን ዓይነት የምርምር መሣሪያዎች ይገኛሉ?

      • በቤተ መጻሕፍቱ በሚገባ መጠቀም እንድትችል እነማን ሊረዱህ ይችላሉ?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      የራስህን ቤተ መጻሕፍት ማደራጀት ከፈለግክ በጽሑፍ ክፍል የትኞቹ ጽሑፎች እንዳሉ መጠየቅ ትችላለህ። በቅድሚያ የትኞቹ ጽሑፎች እንደሚያስፈልጉህ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪህ ሐሳብ ሊሰጥህ ይችላል።

  • በድረ ገጻችን ላይ ምን መረጃ ማግኘት ይቻላል?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 28

      በድረ ገጻችን ላይ ምን መረጃ ማግኘት ይቻላል?

      አንዲት ሴት በላፕቶፕ ኮምፒውተሯ ላይ ምርምር ስታደርግ

      ፈረንሳይ

      ኮምፒውተር እየተጠቀሙ ያሉ አባትና ልጅ

      ፖላንድ

      በኢንተርኔት ላይ የምልክት ቋንቋ ቪዲዮ የምትመለከት ሴት

      ሩሲያ

      ኢየሱስ ክርስቶስ ለተከታዮቹ “ሰዎች መልካም ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሏቸው ነበር። (ማቴዎስ 5:16) ይህንንም ለማድረግ ስንል ኢንተርኔትን ጨምሮ ዘመኑ ባፈራቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንጠቀማለን። jw.org በተባለው የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ድረ ገጽ ላይ ስለ እምነታችንና ስለምናደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ይቻላል። ይህ ድረ ገጽ ምን ይዟል?

      ብዙ ሰዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ። ብዙ ሰዎች ለሚጠይቋቸው በጣም አስፈላጊ ጥያቄዎች በድረ ገጻችን ላይ መልስ ማግኘት ትችላለህ። ለምሳሌ ያህል፣ መከራ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣል? እና የሞቱ ሰዎች እንደገና በሕይወት መኖር ይችላሉ? የተባሉት ትራክቶች ከ600 በሚበልጡ ቋንቋዎች በዚህ ድረ ገጽ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለውን መጽሐፍ ቅዱስ ከ130 በሚበልጡ ቋንቋዎች ማግኘት ይቻላል፤ እንዲሁም ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ ጽሑፎች ብሎም በቅርብ የወጡ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶች ድረ ገጻችን ላይ ይገኛሉ። ከእነዚህ ጽሑፎች አብዛኞቹን እዚያው ድረ ገጹ ላይ ማንበብ ወይም ማዳመጥ ይቻላል፤ አሊያም እንደ ኤም ፒ3፣ ፒ ዲ ኤፍ ወይም ኢ ፐብ ባሉ የታወቁ ፎርማቶች የተዘጋጁ ጽሑፎችን ማውረድ ይቻላል። ሌላው ቀርቶ ለምሥራቹ ፍላጎት ያለው ሰው ስታገኝ ከድረ ገጹ ላይ የተወሰኑ ገጾችን በራሱ ቋንቋ በማተም ልትሰጠው ትችላለህ! በበርካታ የምልክት ቋንቋዎችም በቪዲዮ የተቀረጹ ጽሑፎች ተዘጋጅተዋል። ከዚህም ሌላ በድራማ መልክ የተቀረጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማዎችን ብሎም ዘና በምትልበት ጊዜ የምታዳምጣቸው ጣዕመ ዜማዎችንና መዝሙሮችን ማውረድ ትችላለህ።

      ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚገልጹ ትክክለኛ መረጃዎች። ስለ ዓለም አቀፉ ሥራችን፣ የይሖዋ ምሥክሮችን ስለሚመለከቱ ክንውኖች እንዲሁም አደጋ የደረሰባቸውን ለመርዳት ስለምናከናውነው እንቅስቃሴ የሚገልጹ ወቅታዊ ዜናዎችና ቪዲዮዎች ድረ ገጻችን ላይ ይወጣሉ። በቅርቡ ስለምናደርጋቸው የክልል ስብሰባዎች የሚገልጹ ማስታወቂያዎችንና የቅርንጫፍ ቢሮዎቻችንን አድራሻዎችም ማግኘት ትችላለህ።

      በእነዚህ መንገዶች አማካኝነት በጣም ርቀው በሚገኙ የዓለም ክፍሎች ሳይቀር የእውነት ብርሃን እንዲበራ እናደርጋለን። አንታርክቲካን ጨምሮ በሁሉም አህጉራት የሚኖሩ ሰዎች ይህን ብርሃን ማየት ችለዋል። በምድር ሁሉ “የይሖዋ ቃል በፍጥነት መስፋፋቱን እንዲቀጥልና” በዚህም አምላክ እንዲከበር እንጸልያለን።—2 ተሰሎንቄ 3:1

      • jw.org ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

      • በድረ ገጻችን ላይ የትኞቹን ነገሮች መመልከት ትፈልጋለህ?

      ጥንቃቄ የሚያሻው ነገር፦

      ስለ ድርጅታችን የሐሰት መረጃዎችን ለማሰራጨት ተቃዋሚዎች ያዘጋጇቸው አንዳንድ ድረ ገጾች አሉ። ዓላማቸው፣ ሰዎች ይሖዋን እንዳያገለግሉት ማድረግ ነው። ከእነዚህ ድረ ገጾች መራቅ ይኖርብናል።—መዝሙር 1:1፤ 26:4፤ ሮም 16:17

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ