የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ምን ጥቅም ታገኛለህ?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 5

      ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ምን ጥቅም ታገኛለህ?

      አርጀንቲና ውስጥ ባለ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች

      አርጀንቲና

      ሴራሊዮን ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲያደርጉ

      ሴራ ሊዮን

      ቤልጅየም ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲያደርጉ

      ቤልጅየም

      ማሌዥያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲያደርጉ

      ማሌዥያ

      ብዙ ሰዎች በሃይማኖታዊ ፕሮግራሞች ላይ መንፈሳዊ መመሪያም ሆነ ማጽናኛ ማግኘት ባለመቻላቸው እንደነዚህ ወዳሉ ቦታዎች መሄድ አቁመዋል። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የሚኖርብህ ለምንድን ነው? እዚያ ምን ጥቅም ታገኛለህ?

      አፍቃሪና አሳቢ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመሰብሰብ ትደሰታለህ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት ክርስቲያኖች በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ ይታቀፉ የነበረ ሲሆን አምላክን ለማምለክ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማጥናት እንዲሁም እርስ በርስ ለመበረታታት ይሰበሰቡ ነበር። (ዕብራውያን 10:24, 25) በስብሰባዎቻቸው ላይ አፍቃሪ ከሆኑ መንፈሳዊ ወንድሞቻቸው ጋር ስለሚገናኙ ከእውነተኛ ወዳጆቻቸው ጋር እንደሆኑ ይሰማቸው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 1:3፤ 3 ዮሐንስ 14) እኛም የእነሱን ምሳሌ ስለምንከተል በስብሰባዎቻችን እንደሰታለን።

      የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ትማራለህ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ዛሬም ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች አንድ ላይ እንሰበሰባለን። ብቃት ያላቸው አስተማሪዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለታዊ ሕይወታችን እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርግ ማስተዋል እንድንችል ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያብራሩልናል። (ዘዳግም 31:12፤ ነህምያ 8:8) ሁሉም ሰው መዘመር እንዲሁም ውይይት በሚደረግባቸው የስብሰባው ክፍሎች ላይ ሐሳብ መስጠት የሚችል ሲሆን ይህም ክርስቲያናዊ ተስፋችንን ለመግለጽ ያስችለናል።—ዕብራውያን 10:23

      በአምላክ ላይ ያለህ እምነት ይጠናከራል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ከነበሩት ጉባኤዎች ለአንዱ ሲጽፍ “ላያችሁ እጓጓለሁና፤ ይህን ስል እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው” ብሎ ነበር። (ሮም 1:11, 12) በስብሰባዎቻችን ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አዘውትረን መገናኘታችን እምነታችንን የሚያጠናክርልን ከመሆኑም ሌላ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምተን ለመኖር ባደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ለመጽናት ያስችለናል።

      አንተስ ከላይ የተጠቀሱትን ጥቅሞች ማግኘት ትፈልጋለህ? ከሆነ በስብሰባዎቻችን ላይ እንድትገኝ እንጋብዝሃለን። በስብሰባው ላይ ጥሩ አቀባበል እንደሚደረግልህ አትጠራጠር። መግቢያ በነፃ ሲሆን ሙዳየ ምጽዋትም አይዞርም።

      • በጉባኤ ስብሰባዎቻችን ላይ የእነማንን ምሳሌ እንከተላለን?

      • በስብሰባዎች ላይ በመገኘት ምን ጥቅም እናገኛለን?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      በስብሰባዎቻችን ላይ ከመገኘትህ በፊት የስብሰባ አዳራሻችን ምን እንደሚመስል ማየት ከፈለግክ አንድ የይሖዋ ምሥክር አዳራሹን እንዲያስጎበኝህ መጠየቅ ትችላለህ።

  • ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 6

      ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

      የይሖዋ ምሥክሮች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ይቀራረባሉ

      ማዳጋስካር

      አንድ የይሖዋ ምሥክር የእምነት ባልንጀራውን ሲረዳ

      ኖርዌይ

      ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀራቸውን ሄደው ሲጠይቁ

      ሊባኖስ

      የይሖዋ ምሥክሮች አብረው ጊዜ ያሳልፋሉ

      ጣሊያን

      የበጋውን ሐሩርና የክረምቱን ቁር መቋቋም አሊያም ጥቅጥቅ ያለ ደን አቋርጠን መጓዝ ቢኖርብንም እንኳ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሳናሰልስ እንገኛለን። የዕለት ተዕለት ኑሮ ከሚያስከትለው ጫና በተጨማሪ ቀኑን ሙሉ በሥራ ተወጥረን መዋላችን ኃይላችንን ቢያሟጥጥብንም በስብሰባዎቻችን ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ለመሆን ይህን ያህል ጥረት የምናደርገው ለምንድን ነው?

      ለደህንነታችን አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቻችንን በአእምሮው በመያዝ “አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ” ብሏል። (ዕብራውያን 10:24) ይህ አገላለጽ አንዳችን ስለ ሌላው “በጥልቅ ማሰብ” ይኸውም እርስ በርስ በደንብ መተዋወቅ እንደሚኖርብን ያመለክታል። በሌላ አባባል ሐዋርያው፣ ስለ ሌሎች እንድናስብ እያበረታታን ነው። በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ክርስቲያን ቤተሰቦች ጋር በደንብ ስንተዋወቅ አንዳንዶቹ እኛ ያጋጠመንን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ተቋቁመው እንዳለፉና እኛም እንዲህ እንድናደርግ ሊረዱን እንደሚችሉ እንገነዘባለን።

      ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል። አብረውን ከሚሰበሰቡት ሰዎች ጋር ያለን ቅርርብ ከተራ ትውውቅ ያለፈ ነው፤ እነዚህ ሰዎች የቅርብ ወዳጆቻችን ናቸው። በሌሎች አጋጣሚዎችም አብረናቸው በመሆን አስደሳች ጊዜ እናሳልፋለን። እንዲህ ያለው ቅርርብ ምን ጥቅም ያስገኛል? አንዳችን የሌላውን ባሕርያት ይበልጥ እንድናደንቅ የሚያነሳሳን ሲሆን ይህም በመካከላችን የጠበቀ ፍቅር እንዲኖር ያደርጋል። እንዲህ ያለ ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታችን ደግሞ ባልንጀሮቻችን የሆነ ችግር ሲያጋጥማቸው ቶሎ እንድንደርስላቸው ይገፋፋናል። (ምሳሌ 17:17) ከሁሉም የጉባኤያችን አባላት ጋር በመቀራረብ ‘እርስ በርሳችን እኩል እንደምንተሳሰብ’ እናሳያለን።—1 ቆሮንቶስ 12:25, 26

      አንተም የአምላክን ፈቃድ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ወዳጅነት እንድትመሠርት እናበረታታሃለን። እንደነዚህ ያሉ ወዳጆችን በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ታገኛለህ። ከእኛ ጋር እንዳትቀራረብ ምንም ነገር እንዲያግድህ አትፍቀድ።

      • በስብሰባዎች ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

      • በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ ከእኛ ጋር የምትተዋወቀው መቼ ነው?

  • ስብሰባዎቻችን ምን ይመስላሉ?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 7

      ስብሰባዎቻችን ምን ይመስላሉ?

      በኒው ዚላንድ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲያደርጉ

      ኒው ዚላንድ

      በጃፓን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ሲያደርጉ

      ጃፓን

      ኡጋንዳ ውስጥ አንድ ልጅ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ

      ኡጋንዳ

      በሊቱዌንያ ያሉ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት ምን እንደሚመስል ሲያሳዩ

      ሊቱዌኒያ

      የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ ይዘምሩ፣ ይጸልዩ እንዲሁም ቅዱሳን መጻሕፍትን እያነበቡ ይወያዩ ነበር፤ የስብሰባው ዋነኛ ገጽታዎች እነዚህ ሲሆኑ ከዚህ ውጭ ለየት ያለ የአምልኮ ሥርዓት አያካሂዱም ነበር። (1 ቆሮንቶስ 14:26) በእኛ ስብሰባዎች ላይ የሚከናወነው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው።

      ትምህርቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ 30 ደቂቃ የሚወስድ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ንግግር የሚቀርብ ሲሆን ንግግሩም ቅዱሳን መጻሕፍት ከሕይወታችንና ከምንኖርበት ዘመን ጋር በተያያዘ በሚሰጡት መመሪያ ላይ ያተኮረ ነው። ጥቅሶች ሲነበቡ ሁላችንም መጽሐፍ ቅዱሳችንን አውጥተን እንድንከታተል እንበረታታለን። ከንግግሩ በኋላ አንድ ሰዓት የሚወስድ “የመጠበቂያ ግንብ” ጥናት ይደረጋል፤ በመጠበቂያ ግንብ የጥናት እትም ላይ በወጣ አንድ ርዕስ ላይ በሚደረገው በዚህ ውይይት ሁሉም የጉባኤው አባላት እንዲካፈሉ ይጋበዛሉ። ይህ ውይይት የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሕይወታችን ውስጥ ሥራ ላይ እንድናውል ይረዳናል። በምድር ዙሪያ በሚገኙት ከ110,000 የሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ የሚጠናው ርዕስ ተመሳሳይ ነው።

      የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል እርዳታ እናገኛለን። በሳምንቱ መሃል ደግሞ ሦስት ክፍሎች ያሉት ስብሰባ እናደርጋለን፤ ይህ ስብሰባ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን በመባል ይጠራል፤ ትምህርቱ የተመሠረተው በየወሩ በሚወጣው የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ ላይ ነው። የዚህ ስብሰባ የመጀመሪያ ክፍል “ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት” የሚባል ሲሆን የጉባኤው አባላት አስቀድመው ያነበቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ይብራራል። ቀጥሎ የሚቀርበው “በአገልግሎት ውጤታማ ለመሆን ተጣጣር” የተባለው ክፍል ደግሞ ከሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መወያየት እንደምንችል የሚያሳዩ ሠርቶ ማሳያዎችን ያካተተ ነው። ምክር ሰጪው የንባብና የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል የሚረዱ ነጥቦችን ይነግረናል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​13) “ክርስቲያናዊ ሕይወት” የተባለው የመጨረሻው ክፍል፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችልባቸውን መንገዶች ይጠቁመናል። በዚህ ክፍል ውስጥ በጥያቄና መልስ የሚካሄድ ውይይት የሚካተት ሲሆን ይህም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያለንን ግንዛቤ ያሰፋልናል።

      በስብሰባዎቻችን ላይ በምትገኝበት ጊዜ በስብሰባው ላይ በሚቀርበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት መደነቅህ አይቀርም።—ኢሳይያስ 54:13

      • የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ምን ትምህርቶች ይቀርባሉ?

      • ከሳምንታዊ ስብሰባዎቻችን በየትኛው ላይ መገኘት ትፈልጋለህ?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      በሚቀጥለው ጊዜ በሚኖረው ስብሰባ ላይ ከሚቀርቡት ትምህርቶች አንዳንዶቹ ምን እንደሆኑ ለማወቅ ሞክር። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በዕለት ተዕለት ሕይወትህ የሚጠቅምህ ምን ትምህርት ማግኘት የምትችል ይመስልሃል?

  • ስብሰባ ስንሄድ ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት የምንሰጠው ለምንድን ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 8

      ስብሰባ ስንሄድ ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት የምንሰጠው ለምንድን ነው?

      አንድ አባት ወደ ጉባኤ ስብሰባ ከመሄዳቸው በፊት ልጁን ሲያለባብስ

      አይስላንድ

      አንዲት እናትና ልጇ ወደ ስብሰባ ለመሄድ ሲዘጋጁ

      ሜክሲኮ

      ጥሩ አለባበስ ያላቸው በጊኒ ቢሳው ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች

      ጊኒ ቢሳው

      በፊሊፒንስ ያለ አንድ ቤተሰብ ወደ ስብሰባ ሲሄድ

      ፊሊፒንስ

      የይሖዋ ምሥክሮች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ ጥሩ አለባበስ እንደሚኖራቸው አስተውለሃል? በዚህ ብሮሹር ላይ ያሉትን ሥዕሎች ስትመለከትም ይህን ልብ ብለህ ይሆናል። ለአለባበሳችን ይህን ያህል ትኩረት የምንሰጠው ለምንድን ነው?

      ለአምላካችን አክብሮት እንዳለን ለማሳየት። አምላክ ከውጫዊው ገጽታችን ባሻገር ልባችንን እንደሚመለከት የተረጋገጠ ነው። (1 ሳሙኤል 16:7) ይሁን እንጂ አምላክን ለማምለክ በምንሰበሰብበት ወቅት ለእሱም ሆነ ለእምነት ባልንጀሮቻችን አክብሮት ማሳየት እንፈልጋለን። ፍርድ ቤት ብንቀርብ ለዳኛው ሥልጣን አክብሮት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ እንደምንለብስ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ወደ ስብሰባዎች ስንሄድ የሚኖረን አለባበስ “የምድር ሁሉ ዳኛ” የሆነውን ይሖዋ አምላክንና የአምልኮ ቦታውን ምን ያህል ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ያሳያል።—ዘፍጥረት 18:25

      የምንመራባቸውን እሴቶች በአለባበሳችን ለማሳየት። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች “በልከኝነትና በማስተዋል” እንዲለብሱ ያበረታታል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) “በልከኝነት” መልበስ ሲባል አላስፈላጊ ትኩረት የሚስብ ይኸውም የይታይልኝ መንፈስ የሚንጸባረቅበት፣ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ወይም ሰውነት የሚያሳይ ልብስ አለመልበስ ማለት ነው። “በማስተዋል” መልበስ ሲባል ደግሞ የሚያምር ሆኖም ቅጥ ያጣ ወይም ዝርክርክ ያልሆነ አለባበስ ሊኖረን ይገባል ማለት ነው። እርግጥ ነው፣ በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ብንመራም በአለባበስ ረገድ የየራሳችን የተለያዩ ምርጫዎች ይኖሩናል። አለባበሳችን የሚያምርና ሥርዓታማ መሆኑ ‘አዳኛችን የሆነውን አምላክ ትምህርት’ ያለ ምንም ቃል ‘ውበት የሚያጎናጽፈው’ ከመሆኑም ሌላ ‘አምላክን ያስከብራል።’ (ቲቶ 2:10፤ 1 ጴጥሮስ 2:12) ስብሰባ ስንሄድ ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት መስጠታችን ሌሎች ለይሖዋ አምልኮ ባላቸው አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል።

      ያም ሆኖ አለባበስህ ለስብሰባ እንደማይመጥን በማሰብ ወደ ስብሰባ አዳራሽ ከመምጣት ወደኋላ አትበል። ሥርዓታማ፣ ንጹሕና የሚማርክ ልብስ መልበስ ብዙ ገንዘብ አይጠይቅም።

      • ለአምላክ በምናቀርበው አምልኮ ረገድ አለባበሳችን ምን ቦታ አለው?

      • ከአለባበሳችን ጋር በተያያዘ የምንመራባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?

  • ለስብሰባዎች ጥሩ አድርገን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 9

      ለስብሰባዎች ጥሩ አድርገን መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

      አንድ የይሖዋ ምሥክር ለጉባኤ ስብሰባ ሲዘጋጅ

      ካምቦዲያ

      አንዲት የይሖዋ ምሥክር ለጉባኤ ስብሰባ ስትዘጋጅ
      አንዲት የይሖዋ ምሥክር በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተሳትፎ ስታደርግ

      ዩክሬን

      ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናህ ከሆነ የምታጠኑትን ክፍል ቀደም ብለህ ሳትዘጋጅ አትቀርም። ከጉባኤ ስብሰባዎችም የበለጠ ጥቅም ለማግኘት ስብሰባ ከመሄድህ በፊት ተመሳሳይ ዝግጅት ብታደርግ ጥሩ ነው። ለስብሰባዎች በመዘጋጀት ረገድ ጥሩ ልማድ ካዳበርን የተሻለ ጥቅም ማግኘት እንችላለን።

      የምትዘጋጅበትን ጊዜና ቦታ ወስን። ትኩረትህ ሳይከፋፈል መዘጋጀት የምትችለው መቼ ነው? የቀኑን ሥራ ከመጀመርህ በፊት ማለዳ ላይ መዘጋጀት ይሻልሃል ወይስ ምሽት ላይ ልጆች ሁሉ ከተኙ በኋላ? ረዘም ላለ ጊዜ ማጥናት ባትችል እንኳ ለዝግጅት ምን ያህል ጊዜ ልትመድብ እንደምትችል ወስን፤ ከዚያም ያንን ጊዜ ምንም ነገር እንዳይሻማብህ ለማድረግ ሞክር። ጸጥ ያለ ቦታ ምረጥ፤ እንዲሁም ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ሞባይል ስልክህን በማጥፋት ትኩረትህን ሊከፋፍሉ የሚችሉ ነገሮችን አስወግድ። ጥናትህን ከመጀመርህ በፊት መጸለይህ በቀን ውሎህ ያሳለፍካቸውን ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ለመርሳትና በአምላክ ቃል ላይ ትኩረት ለማድረግ ይረዳሃል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

      በጽሑፍህ ላይ ምልክት በማድረግ ሐሳብ ለመስጠት ተዘጋጅ። መጀመሪያ ላይ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ ጠቅለል ያለ ግንዛቤ እንዲኖርህ ለማድረግ ሞክር። ስለ ትምህርቱ ወይም ስለ ምዕራፉ ርዕስ ቆም ብለህ አስብ፤ እያንዳንዱ ንዑስ ርዕስ ከትምህርቱ ጭብጥ ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ለማስተዋል ሞክር፤ እንዲሁም ሥዕሎቹንና ዋና ዋና ነጥቦቹን የሚያጎሉትን የክለሳ ጥያቄዎች ተመልከት። ከዚያም እያንዳንዱን አንቀጽ እያነበብክ የጥያቄውን መልስ ለማግኘት ሞክር። ምዕራፍና ቁጥራቸው ብቻ የተጠቀሱትን ጥቅሶች አውጥተህ አንብብ፤ እንዲሁም ከትምህርቱ ጋር እንዴት እንደሚያያዙ ቆም ብለህ አስብ። (የሐዋርያት ሥራ 17:11) የጥያቄውን መልስ አንቀጹ ውስጥ ስታገኘው ምልክት አድርግበት፤ ቁልፍ በሆኑ ቃላት ወይም ሐረጎች ላይ ማስመርህ በኋላ ላይ መልሱን በቀላሉ ለማስታወስ ይረዳሃል። ከዚያም ስብሰባው ላይ ሐሳብህን መግለጽ የምትፈልግ ከሆነ እጅህን አውጥተህ በራስህ አባባል አጠር ያለ መልስ መስጠት ትችላለህ።

      በየሳምንቱ በስብሰባዎቻችን ላይ ውይይት የሚደረግባቸውን የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች በመመርመር የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት በምታስቀምጥበት “ሀብት ማከማቻ” ውስጥ አዳዲስ ትምህርቶችን ትጨምራለህ።—ማቴዎስ 13:51, 52

      • ለስብሰባዎች በመዘጋጀት ረገድ ምን ዓይነት ልማድ ማዳበር ትችላለህ?

      • በስብሰባ ላይ ሐሳብ ለመስጠት መዘጋጀት የምትችለው እንዴት ነው?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      ከላይ በተገለጸው ዘዴ በመጠቀም ለመጠበቂያ ግንብ ጥናት ወይም ለጉባኤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተዘጋጅ። በሚቀጥለው ስብሰባ ላይ የምትሰጠውን ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስን ከሚያስጠናህ ሰው ጋር ተዘጋጅ።

  • የቤተሰብ አምልኮ ምንድን ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 10

      የቤተሰብ አምልኮ ምንድን ነው?

      አንድ ቤተሰብ፣ የቤተሰብ አምልኮ ሲያደርግ

      ደቡብ ኮሪያ

      አንድ ባልና ሚስት መጽሐፍ ቅዱስን አብረው ሲያጠኑ

      ብራዚል

      አንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስን ሲያጠና

      አውስትራሊያ

      አንድ ቤተሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ውይይት ሲያደርግ

      ጊኒ

      ይሖዋ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የቤተሰብ አባላት አንድ ላይ ጊዜ በማሳለፍ መንፈሳዊነታቸውን እንዲያጠናክሩና እርስ በርስ ይበልጥ እንዲቀራረቡ እንደሚፈልግ ገልጿል። (ዘዳግም 6:6, 7) የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ቤተሰቦችም በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ የሚያደርጉበት ጊዜ የሚመድቡት ለዚህ ነው፤ በእነዚህ ወቅቶች ቤተሰቦች በሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ላይ ዘና ባለ መንፈስ ይወያያሉ። ብቻህን የምትኖር ቢሆንም እንኳ እንዲህ ያለው ፕሮግራም በምትፈልገው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ ከአምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ለማጠናከር አጋጣሚ ይፈጥርልሃል።

      ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ያስችላል። “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።” (ያዕቆብ 4:8) በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ስለ ይሖዋ ባሕርያትና ስላደረጋቸው ነገሮች በጥልቀት መማራችን ስለ እሱ ይበልጥ ለማወቅ ያስችለናል። ለመጀመሪያ ጊዜ የቤተሰብ አምልኮ ስታደርጉ መጽሐፍ ቅዱስን አብራችሁ ማንበብ ትችላላችሁ፤ ለምሳሌ በክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ ላይ የሚወጣውን ሳምንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም መከተል ይቻላል። በምታነብቡበት ጊዜ ሁሉም የቤተሰብ አባል የተወሰነ ክፍል እንዲደርሰው ማድረግ ትችላላችሁ፤ ከዚያም ከንባቡ ባገኛችሁት ነገር ላይ ተወያዩ።

      የቤተሰብ አባላት እርስ በርሳቸው እንዲቀራረቡ ያደርጋል። ባሎችና ሚስቶች እንዲሁም ወላጆችና ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን በቤተሰብ ማጥናታቸው ይበልጥ እንዲቀራረቡ ያደርጋቸዋል። የአምልኮ ፕሮግራማቸው ሁሉም በጉጉት የሚጠብቁት እንዲሁም አስደሳችና ሰላማዊ ሊሆን ይገባል። ወላጆች የልጆቻቸውን ዕድሜ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ሊወያዩባቸው የሚችሉ ጠቃሚ ርዕሶችን ሊመርጡ ይችላሉ፤ ምናልባትም በመጠበቂያ ግንብ እና በንቁ! መጽሔቶች ላይ ወይም jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ የሚወጡ ዓምዶችን መጠቀም ይፈልጉ ይሆናል። ልጆቻችሁ በትምህርት ቤት ስላጋጠማቸው ችግር አንስታችሁ እንዴት ሊቋቋሙት እንደሚችሉ መወያየት ትችላላችሁ። በJW ብሮድካስት (tv.jw.org) ላይ የሚተላለፈውን ፕሮግራም ከተመለከታችሁ በኋላ ለምን አትወያዩበትም? እንዲሁም በስብሰባዎች ላይ የሚዘመሩ መዝሙሮችን መለማመድ የምትችሉ ሲሆን ከቤተሰብ አምልኮው በኋላም ቀለል ያሉ ምግቦችን በማቅረብ አብራችሁ ጊዜ ልታሳልፉ ትችላላችሁ።

      በየሳምንቱ አብራችሁ ይሖዋን በማምለክ የምታሳልፉት ይህ ልዩ ጊዜ የቤተሰባችሁ አባላት በሙሉ በአምላክ ቃል እንዲደሰቱ ያደርጋል፤ ይሖዋም ጥረታችሁን አብዝቶ ይባርክላችኋል።—መዝሙር 1:1-3

      • ለቤተሰብ አምልኮ ጊዜ የምንመድበው ለምንድን ነው?

      • ወላጆች ይህ ጊዜ ለሁሉም የቤተሰብ አባላት አስደሳች እንዲሆን ምን ማድረግ ይችላሉ?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      በጉባኤ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች የቤተሰብ አምልኮ ፕሮግራማቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ጠይቃቸው። በተጨማሪም ልጆችህን ስለ ይሖዋ ለማስተማር የሚጠቅሙህ ጽሑፎች ከፈለግክ ከስብሰባ አዳራሽ መውሰድ ትችላለህ።

  • በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 11

      በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የምንገኘው ለምንድን ነው?

      በሜክሲኮ የተደረገ የይሖዋ ምሥክሮች የክልል ስብሰባ

      ሜክሲኮ

      ጀርመን ውስጥ በተደረገ የክልል ስብሰባ ላይ አዲስ ጽሑፍ መውጣቱ ሲነገር

      ጀርመን

      ቦትስዋና ውስጥ በክልል ስብሰባ ላይ የተገኙ የይሖዋ ምሥክሮች

      ቦትስዋና

      ኒካራጉዋ ውስጥ አንዲት ወጣት ስትጠመቅ

      ኒካራጉዋ

      ጣሊያን ውስጥ በተደረገ የክልል ስብሰባ ላይ ድራማ ሲቀርብ

      ጣሊያን

      በእነዚህ ሰዎች ፊት ላይ የደስታ ስሜት የሚነበበው ለምንድን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ስለተገኙ ነው። በዓመት ውስጥ ሦስት ጊዜ እንዲሰበሰቡ ታዘው እንደነበሩት እንደ ጥንቶቹ የአምላክ ሕዝቦች ሁሉ እኛም ብዙ ሆነን የምንሰበሰብ ሲሆን ልክ እንደ እነሱ እኛም ይህን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን። (ዘዳግም 16:16) በየዓመቱ ሦስት ትላልቅ ስብሰባዎች የምናደርግ ሲሆን ሁለት ጊዜ የአንድ ቀን የወረዳ ስብሰባ እንዲሁም አንድ ጊዜ የሦስት ቀን የክልል ስብሰባ እናደርጋለን። ከእነዚህ ስብሰባዎች ምን ጥቅም እናገኛለን?

      ክርስቲያናዊ ወንድማማችነታችንን ያጠናክሩልናል። እስራኤላውያን ይሖዋን “በታላቅ ጉባኤ መካከል” ማወደስ ያስደስታቸው እንደነበረ ሁሉ እኛም በእነዚህ ልዩ ወቅቶች አንድ ላይ ሆነን እሱን ማምለክ ያስደስተናል። (መዝሙር 26:12፤ 111:1) እነዚህ ስብሰባዎች ከሌሎች ጉባኤዎች አልፎ ተርፎም ከሌሎች አገራት ከመጡ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመገናኘትና አብረን ጊዜ ለማሳለፍ አጋጣሚ ይፈጥሩልናል። እኩለ ቀን ሲሆን ከስብሰባው ቦታ ሳንወጣ ምሳችንን መመገባችን እነዚህ መንፈሳዊ ዝግጅቶች አስደሳች እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ያበረክታል። (የሐዋርያት ሥራ 2:42) ከዚህም ሌላ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦችን ያቀፈውን “የወንድማማች ማኅበር” አንድ የሚያደርገውን ፍቅር ለመቅመስ የሚያስችል አጋጣሚ እናገኛለን።—1 ጴጥሮስ 2:17

      መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ያስችሉናል። እስራኤላውያን በስብሰባዎች ላይ ቅዱሳን መጻሕፍት ይብራሩላቸው ስለነበር ‘ቃሉን መረዳት’ ችለዋል። (ነህምያ 8:8, 12) እኛም ብንሆን በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኛቸውን ማሳሰቢያዎች ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። እያንዳንዱ ፕሮግራም ከቅዱሳን መጻሕፍት በተወሰደ ጭብጥ ላይ የተመሠረተ ነው። በስብሰባው ላይ የሚቀርቡት ግሩም ንግግሮች፣ ሲምፖዚየሞችና ሠርቶ ማሳያዎች የአምላክን ፈቃድ በሕይወታችን ውስጥ እንዴት መፈጸም እንደምንችል ያስተምሩናል። ባለንበት አስቸጋሪ ጊዜ፣ ክርስቲያኖች በመሆናቸው የሚያጋጥሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በጽናት የተወጡ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ተሞክሮ ስንሰማ እንበረታታለን። በክልል ስብሰባዎች ላይ የሚኖሩት ድራማዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ታሪኮች ሕያው አድርገው በማቅረብ ከዘገባው ትምህርት እንድናገኝ ይረዱናል። ራሳቸውን ለአምላክ መወሰናቸውን ለሕዝብ ለማሳየት ለሚፈልጉ በሙሉ በሁሉም ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የጥምቀት ሥነ ሥርዓት ይዘጋጃል።

      • ትላልቅ ስብሰባዎች አስደሳች ወቅት የሆኑት ለምንድን ነው?

      • በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በመገኘት ምን ጥቅም ማግኘት ትችላለህ?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      ስለ ወንድማማች ማኅበራችን ይበልጥ ለማወቅ ከፈለግክ ወደፊት በምናደርገው ትልቅ ስብሰባ ላይ እንድትገኝ እንጋብዝሃለን። በስብሰባው ላይ ምን ዓይነት ርዕሰ ጉዳዮች እንደሚቀርቡ ማየት እንድትችል የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚህ የስብሰባ ፕሮግራም ሊያሳይህ ይችላል። ቀጣዩ ስብሰባ የሚደረግበትን ቀንና ቦታ ማስታወሻህ ላይ ጻፈው፤ ከዚያም ስብሰባው ላይ ለመገኘት ጥረት አድርግ።

  • የመንግሥቱን ምሥራች የምንሰብከው እንዴት ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 12

      የመንግሥቱን ምሥራች የምንሰብከው እንዴት ነው?

      የይሖዋ ምሥክሮች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሲሰብኩ

      ስፔን

      አንድ የይሖዋ ምሥክር መናፈሻ ውስጥ ሲሰብክ

      ቤላሩስ

      አንዲት የይሖዋ ምሥክር በስልክ ስትሰብክ

      ሆንግ ኮንግ

      በስብከት ሥራቸው ላይ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች

      ፔሩ

      ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል” በማለት ተናግሮ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) ይሁን እንጂ ይህ ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ የሚከናወነው እንዴት ነው? ኢየሱስ ምድር ሳለ የተወውን ምሳሌ በመከተል ነው።—ሉቃስ 8:1

      ሰዎችን ቤታቸው ሄደን ለማነጋገር ጥረት እናደርጋለን። ኢየሱስ ምሥራቹን ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ እንዲሰብኩ ደቀ መዛሙርቱን አሠልጥኗቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:11-13፤ የሐዋርያት ሥራ 5:42፤ 20:20) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት እነዚህ ወንጌላውያን የሚሰብኩበት ክልል ተመድቦላቸው ነበር። (ማቴዎስ 10:5, 6፤ 2 ቆሮንቶስ 10:13) ዛሬም በተመሳሳይ የስብከት ሥራችን በሚገባ የተደራጀ ሲሆን እያንዳንዱ ጉባኤም ሊሸፍነው የሚገባ የራሱ ክልል ተመድቦለታል። ይህም “ለሰዎች እንድንሰብክና በተሟላ ሁኔታ እንድንመሠክር” የሚያዝዘውን የኢየሱስን መመሪያ ለመፈጸም ያስችለናል።—የሐዋርያት ሥራ 10:42

      ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ ለመስበክ ጥረት እናደርጋለን። ኢየሱስ ብዙ ሕዝብ በሚገኝባቸው ቦታዎችም ለምሳሌ በባሕር ዳርቻዎችና በውኃ ጉድጓዶች አቅራቢያ በመስበክ አርዓያ ትቶልናል። (ማርቆስ 4:1፤ ዮሐንስ 4:5-15) እኛም ሰዎችን ማግኘት በምንችልበት ቦታ ሁሉ ይኸውም በመንገድ ላይ፣ በንግድ አካባቢዎችና በመናፈሻ ቦታዎች አሊያም ደግሞ በስልክ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እናወያያቸዋለን። በተጨማሪም አመቺ አጋጣሚ በምናገኝበት ጊዜ ለጎረቤቶቻችን፣ ለሥራ ባልደረቦቻችን፣ አብረውን ለሚማሩ ልጆችና ለዘመዶቻችን ሁሉ እንመሠክራለን። ምሥራቹን ለመስበክ የምናደርገው ይህ ሁሉ ጥረት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “የማዳኑን ምሥራች” እንዲሰሙ አስችሏል።—መዝሙር 96:2

      ስለ አምላክ መንግሥትና ወደፊት ስለሚያመጣቸው ነገሮች የሚገልጸውን ምሥራች ልትነግረው የምትፈልገው ሰው አለ? ይህን አስደሳች ተስፋ ሚስጥር አድርገህ አትያዘው። ዛሬ ነገ ሳትል ይህን ምሥራች ለሌሎች ተናገር!

      • መሰበክ ያለበት “ምሥራች” የትኛው ነው?

      • የይሖዋ ምሥክሮች፣ ኢየሱስ ምሥራቹን የሰበከበትን መንገድ የሚኮርጁት እንዴት ነው?

      ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት

      ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርከውን ነገር ለአንድ የምታውቀው ሰው እንዴት በዘዴ መናገር እንደምትችል የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚህ እንዲያሳይህ ጠይቀው።

  • አቅኚነት ምንድን ነው?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 13

      አቅኚነት ምንድን ነው?

      በአገልግሎት ላይ ያሉ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን

      ካናዳ

      በስብከቱ ሥራ ላይ ያሉ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን

      ከቤት ወደ ቤት

      አቅኚዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሲመሩ

      የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

      አንዲት አቅኚ መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና

      የግል ጥናት

      “አቅኚ” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚሠራበት ወደ አዲስ አካባቢ የሚሄዱ እንዲሁም ፈር ቀዳጅ በመሆን ለሌሎች መንገድ የሚጠርጉ ሰዎችን ለማመልከት ነው። ኢየሱስ፣ ሕይወት የሚያስገኝ አገልግሎት ለማከናወንና ወደ መዳን የሚመራውን በር ለመክፈት ወደ ምድር በመምጣቱ አቅኚ ሊባል ይችላል። (ማቴዎስ 20:28) በዛሬው ጊዜም ተከታዮቹ፣ ሰዎችን ‘ደቀ መዛሙርት በማድረጉ’ ሥራ የሚችሉትን ያህል ጊዜ በማሳለፍ የእሱን ምሳሌ እየተከተሉ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች ደግሞ የአቅኚነት አገልግሎት ብለን በምንጠራው መስክ ይካፈላሉ።

      አቅኚዎች የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ናቸው። ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች የምሥራቹ አስፋፊዎች ወይም ሰባኪዎች ናቸው። አንዳንዶች ግን ፕሮግራማቸውን አስተካክለው በየወሩ 70 ሰዓት በስብከቱ ሥራ በማሳለፍ የዘወትር አቅኚዎች ሆነው ያገለግላሉ። ብዙዎች ይህን ለማድረግ ሲሉ በሰብዓዊ ሥራቸው ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ይቀንሳሉ። ሌሎች ደግሞ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ልዩ አቅኚዎች ሆነው እንዲያገለግሉ የሚመደቡ ሲሆን እነዚህ ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ በየወሩ 130 ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ያሳልፋሉ። አቅኚዎች ይሖዋ የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች እንደሚያሟላላቸው ቅንጣት ታክል ስለማይጠራጠሩ ባላቸው በመርካት ቀለል ያለ ሕይወት ይመራሉ። (ማቴዎስ 6:31-33፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-8) ልዩ ወይም የዘወትር አቅኚ መሆን የማይችሉ ክርስቲያኖች ደግሞ በሚመቻቸው ወር ረዳት አቅኚዎች ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን በዚያ ወቅት በስብከቱ ሥራ በወር ውስጥ 30 ወይም 50 ሰዓት ያሳልፋሉ።

      አቅኚዎች በዚህ መስክ እንዲሰማሩ የሚያነሳሳቸው ለይሖዋና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር ነው። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ያሉበትን መንፈሳዊ ሁኔታ ሲመለከት አዝኖላቸው ነበር፤ እኛም በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ያሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ አሳዛኝ እንደሆነ እናስተውላለን። (ማርቆስ 6:34) በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ለወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያደርግ እውቀት እንዳለን እንገነዘባለን፤ ይህ እውቀት በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሊጠቅማቸው ይችላል። አቅኚዎች ለሰዎች ያላቸው ፍቅር ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ በስብከቱ ሥራ እንዲያሳልፉ ያነሳሳቸዋል። (ማቴዎስ 22:39፤ 1 ተሰሎንቄ 2:8) እንዲህ በማድረጋቸው እምነታቸው የሚጠናከርና ወደ አምላክ ይበልጥ የሚቀርቡ ከመሆኑም ሌላ ይህ ነው የማይባል ደስታ ያገኛሉ።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

      • አቅኚነት ምንድን ነው?

      • አንዳንዶች በአቅኚነት እንዲካፈሉ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው?

  • አቅኚዎች ምን ዓይነት የትምህርት አጋጣሚዎች ተከፍተውላቸዋል?
    በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ፈቃድ የሚያደርጉት እነማን ናቸው?
    • ትምህርት 14

      አቅኚዎች ምን ዓይነት የትምህርት አጋጣሚዎች ተከፍተውላቸዋል?

      የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራ ላይ

      ዩናይትድ ስቴትስ

      በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እየተማሩ ያሉ ተማሪዎች
      ለሚስዮናዊ አገልግሎት እየሰለጠኑ ያሉ ተማሪዎች

      ጊልያድ ትምህርት ቤት፣ ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ

      አንድ ሚስዮናዊ ባልና ሚስት ፓናማ ውስጥ ሲሰብኩ

      ፓናማ

      ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ለረጅም ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች መለያ ሆነው ቆይተዋል። ሙሉ ጊዜያቸውን የስብከቱን ሥራ ለማከናወን የሚያውሉ ክርስቲያኖች ‘አገልግሎታቸውን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም’ እንዲችሉ የሚረዷቸው ለየት ያሉ የትምህርት አጋጣሚዎች አሏቸው።—2 ጢሞቴዎስ 4:5

      የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት፦ አንድ የዘወትር አቅኚ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አንድ ዓመት ካሳለፈ በኋላ ስድስት ቀን የሚፈጅ ሥልጠና መውሰድ ይችላል፤ ትምህርት ቤቱ የሚካሄደው በአካባቢው ባለ የስብሰባ አዳራሽ ሊሆን ይችላል። የዚህ ትምህርት ቤት ዓላማ አቅኚዎች ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ፣ በሁሉም የአገልግሎታቸው ዘርፎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ እንዲሁም በታማኝነት በአገልግሎታቸው መጽናት እንዲችሉ መርዳት ነው።

      የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት፦ ሁለት ወር የሚፈጀው ይህ ትምህርት ቤት፣ የሚኖሩበትን አካባቢ ትተው ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ለመሄድ ፈቃደኛ የሆኑ ተሞክሮ ያላቸው አቅኚዎችን ለማሠልጠን የተዘጋጀ ነው። እነዚህ አቅኚዎች በምድር ላይ ከኖሩት ወንጌላውያን ሁሉ የላቀውን ወንጌላዊ ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” የሚሉ ያህል ነው። (ኢሳይያስ 6:8፤ ዮሐንስ 7:29) ከሚኖሩበት አካባቢ ርቀው መሄዳቸው አኗኗራቸውን ቀላል ማድረግ ይጠይቅባቸው ይሆናል። የሚሄዱበት አካባቢ ባሕል፣ የአየር ጠባይ እንዲሁም ምግብ ከለመዱት ፈጽሞ የተለየ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም አዲስ ቋንቋ መማር ያስፈልጋቸው ይሆናል። ትምህርት ቤቱ፣ ከ23 እስከ 65 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነጠላ ወንድሞች፣ እህቶች እንዲሁም ባለትዳሮች በተመደቡበት ቦታ የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ባሕርያት ብሎም ይሖዋና ድርጅቱ ይበልጥ እንዲጠቀሙባቸው የሚያስችሏቸውን ክህሎቶች እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።

      ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት፦ “ጊልያድ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “የምሥክሮች ክምር” የሚል ትርጉም አለው። ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመ ከ1943 ወዲህ ከጊልያድ የተመረቁ ከ8,000 በላይ ተማሪዎች ሚስዮናውያን እንዲሆኑ የተላኩ ሲሆን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ውጤታማ የሆነ ምሥክርነት መስጠት ችለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 13:47) ለምሳሌ ያህል፣ ሚስዮናውያን መጀመሪያ ወደ ፔሩ ሲላኩ በዚያች አገር አንድም ጉባኤ አልነበረም። አሁን ግን ከ1,000 የሚበልጡ ጉባኤዎች አሉ። ሚስዮናውያኖቻችን መጀመሪያ ወደ ጃፓን ሲሄዱ በአገሪቱ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች አሥር አይሞሉም ነበር። አሁን ግን ከ200,000 በላይ ሆነዋል። በጊልያድ የሚሰጠው የአምስት ወር ሥልጠና ተማሪዎቹ የአምላክን ቃል ጥልቀት ባለው መንገድ እንዲያጠኑ ያስችላቸዋል። ልዩ አቅኚዎች፣ በመስክ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን፣ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩ ወይም በወረዳ ሥራ የሚካፈሉ ክርስቲያኖች በትምህርት ቤቱ እንዲሠለጥኑ ይጋበዛሉ፤ በዚህ የሚሰጠው ጥልቀት ያለው ሥልጠና በዓለም ዙሪያ የሚከናወነውን ሥራ ለማጠናከር አስተዋጽኦ ያበረክታል።

      • የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ዓላማ ምንድን ነው?

      • በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት መሠልጠን የሚችሉት እነማን ናቸው?

አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
ውጣ
ግባ
  • አማርኛ
  • አጋራ
  • የግል ምርጫዎች
  • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
  • የአጠቃቀም ውል
  • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
  • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
  • JW.ORG
  • ግባ
አጋራ