የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • kr ምዕ. 4 ገጽ 39-48
  • ይሖዋ ስሙን ከፍ ከፍ አድርጎታል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ስሙን ከፍ ከፍ አድርጎታል
  • የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክ ስም መቀደስ
  • የአምላክን ስም ለመሸከምና ከፍ ከፍ ለማድረግ መዘጋጀት
  • ይሖዋ “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች” ወሰደ
  • የአምላክ ስም በዓለም ዙሪያ ከፍ ከፍ እየተደረገ ነው
  • የአምላክን ስም ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
    ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም
  • የይሖዋን ታላቅ ስም አክብሩ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2013
  • የአምላክ ስም ማን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (ለሕዝብ የሚሰራጭ)—2019
  • የአምላክ ስም
    ንቁ!—2017
ለተጨማሪ መረጃ
የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
kr ምዕ. 4 ገጽ 39-48

ምዕራፍ 4

ይሖዋ ስሙን ከፍ ከፍ አድርጎታል

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

የአምላክ ሕዝቦች ለመለኮታዊው ስም ትልቅ ቦታ ሰጡ

1, 2. አዲስ ዓለም ትርጉም የአምላክን ስም ከፍ ከፍ የሚያደርገው እንዴት ነው?

ማክሰኞ ታኅሣሥ 2, 1947 በብሩክሊን ኒው ዮርክ ቤቴል የሚገኙ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቅቡዓን ወንድሞች አንድ ትልቅ ሥራ ለማከናወን ተነሱ። ሥራው በጣም ከባድ ቢሆንም እነዚህ ወንድሞች ለቀጣዮቹ 12 ዓመታት በትጋት ሲሠሩ ቆዩ። በመጨረሻም መጋቢት 13, 1960 እሁድ ዕለት፣ ሲያከናውኑት የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ የመጨረሻ ክፍል አጠናቀቁ። ከሦስት ወራት በኋላም ሰኔ 18, 1960 ወንድም ናታን ኖር የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱን በማንቸስተር፣ እንግሊዝ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ አስታወቀ፤ በስብሰባው ላይ የተገኙት ሁሉ ይህን ሲሰሙ በጣም ተደሰቱ። ተናጋሪው ‘የዛሬዋ ዕለት በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች የሐሴት ቀን ናት!’ በማለት የተሰብሳቢዎቹን ስሜት አስተጋብቷል። ለእነዚህ ወንድሞች ደስታ አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች አንዱ ይህ አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የአምላክን የግል ስም በበኩረ ጽሑፉ ላይ በነበረበት ቦታ ሁሉ የሚያስገባ መሆኑ ነው፤ ይህም ከሌሎች ትርጉሞች ልዩ ያደርገዋል።

1) የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በ1950 ሲሰራጭ፤ 2) በጋና ሰዎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስን እያሳዩ

የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በ1950 በተደረገው የቲኦክራሲው እድገት በተባለ ትልቅ ስብሰባ ላይ ወጣ (በስተ ግራ፦ ያንኪ ስታዲየም፣ ኒው ዮርክ ሲቲ፤ በስተ ቀኝ፦ ጋና)

2 አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የአምላክን ስም ከትርጉማቸው ውስጥ አውጥተውታል። የይሖዋ ቅቡዕ አገልጋዮች ግን ሰይጣን፣ የአምላክን ስም የሰው ልጆች እንዲረሱት ለማድረግ የጠነሰሰውን ሴራ ለማክሸፍ ቁርጥ አቋም ወስደዋል። በዚያ ዕለት የወጣው አዲስ ዓለም ትርጉም የተባለው የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የመግቢያ ሐሳብ እንዲህ ይላል፦ “የዚህ የትርጉም ሥራ ዋነኛ ዓላማ መለኮታዊው ስም . . . በትክክለኛ ቦታው ላይ ተመልሶ እንዲቀመጥ ማድረግ ነው።” አዲስ ዓለም ትርጉም፣ ይሖዋ የተባለውን የአምላክ የግል ስም ከ7,000 ጊዜ በላይ ተጠቅሞበታል። በእርግጥም ይህ ትርጉም የሰማዩ አባታችንን የይሖዋን ስም እጅግ ከፍ ከፍ አድርጓል!

3. (ሀ) የአምላክን ስም ትርጉም በተመለከተ ወንድሞች ምን ተገነዘቡ? (ለ) ዘፀአት 3:13, 14⁠ን ልንረዳው የሚገባው እንዴት ነው? (“የአምላክ ስም ትርጉም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

3 ቀደም ባሉት ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የአምላክ ስም “ያለና የሚኖር” የሚል ትርጉም እንዳለው ያስቡ ነበር። (ዘፀ. 3:14 አ.መ.ት) በመሆኑም የጥር 1, 1926 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ይሖዋ የሚለው ስም፣ አምላክ በራሱ ሕልውና ያለው እንደሆነና . . . መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ እንደሌለው ያመለክታል።” ይሁንና አዲስ ዓለም ትርጉምን የተረጎሙት ሰዎች ሥራቸውን በጀመሩበት ወቅት የይሖዋ ስም ትርጉም፣ አምላክ በራሱ ሕልውና ያለው መሆኑን የሚያመለክት እንዳልሆነ ተገንዝበው ነበር፤ ከዚህ ይልቅ ስሙ በዋነኝነት የሚያመለክተው ይሖዋ፣ የዓላማ እና የተግባር አምላክ መሆኑን ነው። “ይሖዋ” የሚለው ስም ቃል በቃል ሲተረጎም “እንዲሆን ያደርጋል” ማለት እንደሆነ ተረዱ። በእርግጥም ይሖዋ፣ ጽንፈ ዓለምና የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ወደ ሕልውና እንዲመጡ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ፈቃዱና ዓላማው ፍጻሜውን እንዲያገኝ ማድረጉን ቀጥሏል። ይሁን እንጂ የአምላክ ስም ከፍ ከፍ መደረጉ ይህን ያህል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እኛስ በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

የአምላክ ስም መቀደስ

4, 5. (ሀ) “ስምህ ይቀደስ” ብለን ስንጸልይ ምን እንዲደረግ እየጠየቅን ነው? (ለ) አምላክ ስሙን የሚቀድሰው እንዴት እና መቼ ነው?

4 ይሖዋ፣ ስሙ ከፍ ከፍ እንዲደረግ ይፈልጋል። እንዲያውም ዋነኛ ዓላማው ስሙ እንዲቀደስ ማድረግ ነው፤ ኢየሱስ ባስተማረው የጸሎት ናሙና ላይ ያቀረበው የመጀመሪያ ልመና “ስምህ ይቀደስ” የሚል መሆኑም ይህን ያሳያል። (ማቴ. 6:9) ታዲያ እኛስ ይህን ጸሎት ስናቀርብ ምን እንዲደረግ እየጠየቅን ነው?

5 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 1 ላይ እንዳየነው “ስምህ ይቀደስ” የሚለው ልመና በኢየሱስ የጸሎት ናሙና ላይ ከተጠቀሱት ከአምላክ ዓላማ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሦስት ልመናዎች አንዱ ነው። ሌሎቹ ሁለቱ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም” የሚሉት ናቸው። (ማቴ. 6:10) ይሖዋ፣ መንግሥቱ እንዲመጣና ፈቃዱ እንዲፈጸም የሚያደርግ እርምጃ እንዲወስድ እንደምንለምነው ሁሉ ስሙ እንዲቀደስ የሚያደርግ እርምጃም እንዲወስድ እንለምነዋለን። በሌላ አባባል፣ በኤደን ከተነሳው ዓመፅ ጀምሮ በይሖዋ ስም ላይ የተከመረውን ነቀፋ ለማስወገድ አምላክ እርምጃ እንዲወስድ እየጠየቅን ነው። ይሖዋ እንዲህ ላለው ጸሎት ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው? “በብሔራት መካከል የረከሰውን፣ . . . ታላቅ ስሜን በእርግጥ እቀድሰዋለሁ” በማለት ተናግሯል። (ሕዝ. 36:23፤ 38:23) ይሖዋ በአርማጌዶን ክፋትን ጠራርጎ በሚያስወግድበት ወቅት ስሙን በፍጥረታት ሁሉ ፊት ይቀድሳል።

6. የአምላክ ስም እንዲቀደስ በማድረግ ረገድ ምን ድርሻ ማበርከት እንችላለን?

6 በታሪክ ዘመናት በሙሉ ይሖዋ፣ ስሙ እንዲቀደስ በማድረግ ረገድ አገልጋዮቹ ድርሻ እንዲኖራቸው አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። እርግጥ ነው፣ የሰው ልጆች የአምላክ ስም ይበልጥ እንዲቀደስ ማድረግ አይችሉም። ምክንያቱም የአምላክ ስም፣ ፍጹም በሆነ መልኩ ቅዱስ ነው። ታዲያ ስሙን መቀደስ የምንችለው እንዴት ነው? ኢሳይያስ “ቅዱስ አድርጋችሁ ልትመለከቱ የሚገባው የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ነው” ብሏል። ይሖዋ ራሱም ሕዝቡን በተመለከተ እንዲህ ብሏል፦ “ስሜን ይቀድሳሉ . . . የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ።” (ኢሳ. 8:13፤ 29:23) እንግዲያው የአምላክን ስም የምንቀድሰው ስሙን ከሌሎች ስሞች ሁሉ የተለየና የላቀ እንደሆነ አድርገን በመመልከት፣ ስሙ የሚወክለውን አካል በማክበር እንዲሁም ሰዎች ስሙን ቅዱስ አድርገው እንዲመለከቱት በመርዳት ነው። በተለይ ደግሞ ይሖዋ ገዢያችን እንደሆነ በመቀበልና እሱን በሙሉ ልባችን በመታዘዝ ለአምላክ ስም አክብሮታዊ ፍርሃት እንዳለን እናሳያለን።—ምሳሌ 3:1፤ ራእይ 4:11

የአምላክን ስም ለመሸከምና ከፍ ከፍ ለማድረግ መዘጋጀት

7, 8. (ሀ) በዘመናችን ያሉ የአምላክ ሕዝቦች በስሙ ከመጠራታቸው በፊት የተወሰነ ጊዜ ያለፈው ለምንድን ነው? (ለ) ከዚህ ቀጥሎ የትኞቹን ነጥቦች እንመረምራለን?

7 በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮች ከ1870ዎቹ ዓመታት ጀምሮ የአምላክን ስም በጽሑፎቻቸው ላይ ሲጠቀሙ ቆይተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የነሐሴ 1879 እትም እንዲሁም በዚያው ዓመት የታተመው ሶንግስ ኦቭ ዘ ብራይድ የተባለው መዝሙር መጽሐፍ ላይ የይሖዋ ስም ይገኝ ነበር። ያም ሆኖ ይሖዋ፣ ሕዝቡ በዚህ ቅዱስ ስም መጠራት እንዲጀምሩ ከመፍቀዱ በፊት ይህን ታላቅ መብት ለመቀበል የሚያስፈልገውን ብቃት እንዲያሟሉ የረዳቸው ይመስላል። ታዲያ ይሖዋ፣ ቀደም ባሉት ዓመታት የነበሩት እነዚያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስሙን ለመሸከም እንዲችሉ ያዘጋጃቸው እንዴት ነው?

8 በ1800ዎቹ ዓመታት መገባደጃና በ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብለን ብንመለከት ይሖዋ፣ ከስሙ ጋር የተያያዙ አስፈላጊ እውነቶች ይበልጥ ግልጽ እንዲሆኑላቸው ሕዝቦቹን የረዳቸው እንዴት እንደሆነ መገንዘብ እንችላለን። እስቲ ከእነዚህ እውነቶች መካከል ሦስቱን እንመልከት።

9, 10. (ሀ) በቀድሞዎቹ ዓመታት የሚወጡት የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በኢየሱስ ላይ ትኩረት ያደርጉ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ከ1919 ወዲህ ምን ለውጥ ተደረገ? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል? (“መጠበቂያ ግንብ የአምላክን ስም ከፍ ከፍ ያደረገው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

9 በመጀመሪያ የይሖዋ አገልጋዮች፣ የአምላክ ስም ሊሰጠው ስለሚገባው ቦታ ትክክለኛ አመለካከት አዳበሩ። ቀደም ባሉት ዓመታት የነበሩት ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የቤዛው ዝግጅት የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ትምህርት እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። መጠበቂያ ግንብ አብዛኛውን ጊዜ በኢየሱስ ላይ ትኩረት ያደርግ የነበረውም በዚህ ምክንያት ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይህ መጽሔት መታተም በጀመረበት ዓመት ላይ የኢየሱስ ስም የተጠቀሰበት ቦታ የይሖዋ ስም ከተጠቀሰበት በአሥር እጥፍ ይበልጣል። የመጋቢት 15, 1976 መጠበቂያ ግንብ ቀደም ባሉት ጊዜያት የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለኢየሱስ “ከሚገባው በላይ ትኩረት” ይሰጡ እንደነበር ገልጿል። እያደር ግን እነዚህ ክርስቲያኖች የአምላክ የግል ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንደተሰጠው እንዲያስተውሉ ይሖዋ ረዳቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህን ማወቃቸው ምን እንዲያደርጉ አነሳሳቸው? ከላይ በተጠቀሰው መጠበቂያ ግንብ ላይ እንደተገለጸው በተለይ ከ1919 ወዲህ፣ “በሰማይ ላለው የመሲሑ አባት ይኸውም ለይሖዋ የበለጠ አክብሮት መስጠት ጀመሩ።” እንዲያውም ከ1919 በኋላ ባለው አሥር ዓመት ውስጥ የአምላክ ስም በመጠበቂያ ግንብ ላይ ከ6,500 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል።

10 እነዚህ ወንድሞቻችን ለይሖዋ ስም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ለአምላክ ስም ያላቸውን ፍቅር አሳይተዋል። በጥንት ዘመን እንደኖረው እንደ ሙሴ ‘የይሖዋን ስም አውጀዋል።’ (ዘዳ. 32:3፤ መዝ. 34:3) ይሖዋም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ቃል በገባው መሠረት፣ ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር በመመልከት ሞገሱን አሳይቷቸዋል።—መዝ. 119:132፤ ዕብ. 6:10

11, 12. (ሀ) ከ1919 ወዲህ በጽሑፎቻችን ላይ ምን ለውጥ ተደረገ? (ለ) ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ በምን ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እየረዳቸው ነበር? ለምን?

11 ሁለተኛ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከአምላክ የተሰጣቸውን ተልእኮ በተመለከተ ትክክለኛ አመለካከት አዳበሩ። ሥራውን በበላይነት የሚመሩት ቅቡዓን ወንድሞች ከ1919 በኋላ በይሖዋ መንፈስ እየተመሩ የኢሳይያስን ትንቢት መመርመር ጀመሩ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም፣ ጽሑፎቻችን ትኩረት የሚያደርጉበት ርዕሰ ጉዳይ ተለወጠ። ይህ ማስተካከያ ‘በተገቢው ጊዜ የቀረበ ምግብ’ እንደሆነ የታየው እንዴት ነው?—ማቴ. 24:45

12 ይሖዋ “‘እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ’ . . . ‘አዎ፣ የመረጥኩት አገልጋዬ ናችሁ’” በማለት በኢሳይያስ በኩል የተናገረው ሐሳብ ከ1919 በፊት በመጠበቂያ ግንብ ላይ ተብራርቶ አያውቅም ነበር። (ኢሳይያስ 43:10-12⁠ን አንብብ።) ከ1919 በኋላ ግን ጽሑፎቻችን በዚህ ጥቅስ ላይ ትኩረት ማድረግ የጀመሩ ሲሆን ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይሖዋ በሰጣቸው ሥራ ይኸውም ስለ እሱ በመመሥከሩ ሥራ እንዲካፈሉ ማበረታቻ ተሰጣቸው። እንዲያውም ከ1925 እስከ 1931 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ ኢሳይያስ ምዕራፍ 43 በ57 የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ላይ ተብራርቷል፤ እያንዳንዱ እትም ኢሳይያስ የተናገረው ሐሳብ በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ገልጿል። በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው በእነዚያ ዓመታት ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ እሱ በሰጣቸው ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እየረዳቸው ነበር። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? “ብቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ በቅድሚያ [ለመፈተን]” ይመስላል። (1 ጢሞ. 3:10) እነዚያ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአምላክን ስም የመሸከም መብት ከማግኘታቸው በፊት፣ በትክክል የእሱ ምሥክሮች መሆናቸውን በሥራቸው ለይሖዋ ማሳየት ነበረባቸው።—ሉቃስ 24:47, 48

የአምላክ ስም ትርጉም

ቴትራግራማተን፣ የአምላክን ስም የሚወክሉት አራት የዕብራይስጥ ፊደላት

ይሖዋ የሚለው ስም “መሆን” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ግስ የተገኘ ነው። አንዳንድ ምሁራን ይህ ግስ ከአምላክ ስም ጋር በተያያዘ የገባበት መንገድ አስደራጊ መሆንን የሚያመለክት እንደሆነ ይገልጻሉ። በመሆኑም ብዙዎች የአምላክ ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው ያስባሉ። ይህ ፍቺ፣ ይሖዋ ፈጣሪ በመሆን ያከናወነውን ተግባር ጥሩ አድርጎ ይገልጸዋል። ይሖዋ፣ ጽንፈ ዓለምና የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት ወደ ሕልውና እንዲመጡ ያደረገ ከመሆኑም ሌላ ፈቃዱና ዓላማው ፍጻሜውን እንዲያገኝ ማድረጉን ቀጥሏል።

ታዲያ በዘፀአት 3:13, 14 ላይ ለሚገኘው ሙሴ ላነሳው ጥያቄ ይሖዋ የሰጠውን መልስ መረዳት የሚኖርብን እንዴት ነው? ሙሴ፣ ይሖዋን እንዲህ በማለት ጠይቆት ነበር፦ “ወደ እስራኤላውያን ሄጄ ‘የአባቶቻችሁ አምላክ ወደ እናንተ ልኮኛል’ ስላቸው እነሱ ደግሞ ‘ስሙ ማን ነው?’ ብለው ቢጠይቁኝ ምን ልበላቸው?” ይሖዋም ሙሴን “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” አለው።

ሙሴ፣ አምላክን የጠየቀው ስሙን እንዲነግረው እንዳልሆነ ልብ በል። ሙሴም ሆነ እስራኤላውያን የአምላክን ስም በደንብ ያውቁ ነበር። ሙሴ የፈለገው፣ ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ የሚያሳይና እምነቱን የሚያጠናክርለት እንዲሁም የስሙ ትርጉም ምን እንደሆነ የሚጠቁም ነገር እንዲነግረው ነው። በመሆኑም ይሖዋ “መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ” በማለት ሲመልስ ስለ ማንነቱ አስገራሚ የሆነ ነገር እየገለጸ ነበር፦ በእያንዳንዱ ሁኔታ ዓላማውን ለመፈጸም መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ለሙሴና ለእስራኤላውያን አዳኝና ሕግ ሰጪ ከመሆኑም ሌላ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ የሚያሟላ አምላክ ሆኖላቸዋል። በመሆኑም ይሖዋ ለሕዝቡ የገባውን ቃል ለመፈጸም ሲል መሆን የሚፈልገውን ሁሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይሖዋ የሚለው ስም ይህን ሐሳብ የሚያጠቃልል ቢሆንም የስሙ ትርጉም፣ መሆን የሚፈልገውን እንደሚሆን የሚገልጽ ብቻ አይደለም። የስሙ ትርጉም፣ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል ፍጥረታቱ እሱ የሚፈልገውን እንዲሆኑ እንደሚያደርግም ያመለክታል።b

b አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ ተጨማሪ መረጃ ሀ4⁠ን ተመልከት።

መጠበቂያ ግንብ የአምላክን ስም ከፍ ከፍ ያደረገው እንዴት ነው?

ባለፉት ዓመታት ሁሉ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት የሽፋን ገጽ ላይ ለይሖዋ ስም ይበልጥ ትኩረት ለመስጠት ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በመጽሔቱ የሽፋን ገጽ ላይ የተደረጉ አንዳንድ ለውጦችን ልብ በል።

  • የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የተባለው መጽሔት የሐምሌ  1879 እትም ሽፋን

    የጽዮን መጠበቂያ ግንብ፣ ሐምሌ 1879

    መጽሔቱ ከመግቢያው ጀምሮ በይሖዋ ስም ይጠቀም ነበር። የዚህ መጽሔት ሁለተኛ እትም “‘የጽዮን መጠበቂያ ግንብ’ ደጋፊ ይሖዋ ራሱ እንደሆነ እናምናለን” የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር።

  • መጠበቂያ ግንብ፣ ጥቅምት 15, 1931

    ይሖዋ የሚለው ስም እንዲሁም ኢሳይያስ 43:12 ላይ ያለው ጥቅስ የሽፋኑ ገጽ ላይ መውጣት ጀመረ።

  • መጠበቂያ ግንብ፣ ጥር 1, 1939

    ይሖዋ የሚለው ስም በሽፋኑ ላይ በሁለት ጥቅሶች ላይ ይኸውም በኢሳይያስ 43:12 እና በሕዝቅኤል 35:15 ላይ መውጣት ጀመረ።

  • የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት የመጋቢት 1, 1939 እትም ሽፋን

    መጠበቂያ ግንብ፣ መጋቢት 1, 1939

    ይሖዋ የሚለው ስም በሽፋኑ ላይ ሦስት ቦታዎች ላይ መውጣት ጀመረ፤ በተጨማሪም ከዚህ እትም አንስቶ የመጽሔቱ ሙሉ ስም የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ ተባለ።

ከዚህም በተጨማሪ ከ1920ዎቹ ዓመታት መገባደጃ አካባቢ ጀምሮ ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት በእያንዳንዱ የመጠበቂያ ግንብ እትም የመጀመሪያ ርዕስ፣ የመጀመሪያ አንቀጽ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም እንዲገባ ይደረግ ነበር። ይህ የአምላክ ሕዝቦች፣ የእሱን ስም ከፍ ከፍ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ ግሩም ማስታወሻ ነበር!

13. የአምላክ ቃል ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ምን እንደሆነ የሚገልጸው እንዴት ነው?

13 ሦስተኛ፣ የይሖዋ ሕዝቦች የአምላክ ስም መቀደሱ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ተገነዘቡ። በ1920ዎቹ ዓመታት የአምላክ ሕዝቦች፣ የአምላክ ስም መቀደስ ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ተገነዘቡ። የአምላክ ቃል፣ ይህንን ወሳኝ እውነት የሚገልጸው እንዴት ነው? እስቲ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት። አምላክ፣ እስራኤላውያንን ከግብፅ ነፃ ያወጣበት ዋነኛው ምክንያት ምንድን ነው? ይሖዋ “ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ስል [ነው]” በማለት ተናግሯል። (ዘፀ. 9:16) ይሖዋ፣ እስራኤላውያን በእሱ ላይ ባመፁበት ጊዜ እነሱን ከማጥፋት ይልቅ ምሕረት ያደረገላቸውስ ለምንድን ነው? በዚህ ጊዜም ይሖዋ “እነሱ በሚኖሩባቸው ብሔራት ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስል ስለ ስሜ እርምጃ ወሰድኩ” ብሏል። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ጥቅስ “በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ክብር ተቈጠብሁ” በማለት ያስቀምጠዋል። (ሕዝ. 20:8-10) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከእነዚህና ከሌሎች ጥቅሶች ምን ትምህርት አግኝተዋል?

14. (ሀ) በ1920ዎቹ መገባደጃ አካባቢ የአምላክ ሕዝቦች ምን መረዳት ችለው ነበር? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያገኙት ጥልቅ ማስተዋል በስብከቱ ሥራ ረገድ ምን እንዲያደርጉ አነሳሳቸው? (“ለመስበክ የሚያነሳሳ ጠንካራ ምክንያት” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

14 በ1920ዎቹ መገባደጃ አካባቢ የአምላክ ሕዝቦች ኢሳይያስ ከ2,700 ዓመታት በፊት የተናገረው ሐሳብ ምን ትርጉም እንዳለው መረዳት ቻሉ። ኢሳይያስ ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “ለራስህ የከበረ ስም ለማትረፍ ስትል ሕዝብህን የመራኸው በዚህ መንገድ ነው” ብሎ ነበር። (ኢሳ. 63:14) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የሰዎች መዳን ሳይሆን የአምላክ ስም መቀደስ እንደሆነ ተገነዘቡ። (ኢሳ. 37:20፤ ሕዝ. 38:23) በ1929 ፕሮፌሲ የተባለው መጽሐፍ ይህንን እውነት ጠቅለል አድርጎ ሲገልጽ ‘በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ የይሖዋ ስም ነው’ ብሎ ነበር። የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ረገድ የነበራቸውን አመለካከት ማስተካከላቸው ስለ ይሖዋ እንዲመሠክሩና ስሙን ከነቀፋ ነፃ ለማድረግ እንዲጥሩ አነሳስቷቸዋል።

15. (ሀ) በ1930ዎቹ ዓመታት ወንድሞቻችን ምን ነገሮችን ተገንዝበው ነበር? (ለ) ምን የሚሆንበት ጊዜ ደርሶ ነበር?

15 በ1930ዎቹ መባቻ አካባቢ ወንድሞቻችን፣ የአምላክ ስም ሊሰጠው ስለሚገባው ቦታ ትክክለኛ አመለካከት አዳብረው፣ ከአምላክ የተሰጣቸውን ተልእኮ በተመለከተ ይበልጥ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ አግኝተው እንዲሁም ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ስለሚገባው ነገር ጥልቅ ማስተዋል ማግኘት ችለው ነበር። በመሆኑም ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ በስሙ የመጠራት መብት እንዲያገኙ የሚያደርግበት ጊዜ ደርሶ ነበር። ይህ የሆነው እንዴት እንደሆነ ለመገንዘብ እስቲ ቀደም ባሉት ዘመናት የተከናወኑ አንዳንድ ነገሮችን እንመልከት።

ለመስበክ የሚያነሳሳ ጠንካራ ምክንያት

ሄለን ቦርሸርት

ሄለን ቦርሸርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ከአምላክ ስም መቀደስ ጋር ስለተያያዘው ጉዳይ ግልጽ ግንዛቤ ማግኘታቸው ለስብከቱ ሥራ ባላቸው አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? በ1930 መጠበቂያ ግንብ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “ክርስቲያኖች [ስለ አምላክ ስም መቀደስ የሚገልጸው] ይህ እውነት በደንብ ሲገባቸው የይሖዋ አምላክ ቃልና ስም ምሥክር መሆን ምን ያህል ታላቅ መብት እንደሆነ ተገነዘቡ።” በእርግጥም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ የአምላክ ስም መቀደስ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ መገንዘባቸው ለመስበክ የሚያነሳሳ ጠንካራ ምክንያት ሆኖላቸዋል። (መዝ. 8:1) ሄለን ቦርሸርትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህች እህት በአቅኚነት ማገልገል የጀመረችው ሚያዝያ 1, 1930 ሲሆን ሐምሌ 2003 በ96 ዓመቷ ምድራዊ ሕይወቷን እስካጠናቀቀችበት ጊዜ ድረስ ታማኝ የይሖዋ ምሥክር ነበረች። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በስብከቱ ሥራ እንድትጸና የረዳት ምንድን ነው? ከብዙ ዓመታት በኋላ እንዲህ ብላለች፦ “አቅኚነት ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ዋነኛው ምኞቴ . . . በይሖዋ አምላክ ስምና በቃሉ ላይ የተከመረውን ነቀፋ ማስወገድ ነው።” ዛሬም ቢሆን ለመስበክ የሚያነሳሳን ጠንካራ ምክንያት የአምላክ ስም እንዲቀደስ በማድረጉ ሥራ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ያለን ፍላጎት ነው።

ይሖዋ “ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች” ወሰደ

16. (ሀ) ይሖዋ ስሙን ከፍ ከፍ ከሚያደርግባቸው ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው መንገዶች መካከል አንዱ የትኛው ነው? (ለ) በጥንት ዘመን አምላክ፣ ለስሙ የሚሆኑ ሰዎች እንዲሆኑ መጀመሪያ መብት የሰጠው ለእነማን ነበር?

16 ይሖዋ ስሙን ከፍ ከፍ ከሚያደርግባቸው ጉልህ ስፍራ የሚሰጣቸው መንገዶች መካከል አንዱ በምድር ላይ በስሙ የሚጠራ ሕዝብ እንዲኖር ማድረጉ ነው። ከ1513 ዓ.ዓ. ጀምሮ የእስራኤል ብሔር የይሖዋ ሕዝብ በመሆን እሱን ወክሎ ነበር። (ኢሳ. 43:12) ይሁንና እስራኤላውያን ከአምላክ ጋር የገቡትን ቃል ኪዳን ሳይጠብቁ በመቅረታቸው ከእሱ ጋር የነበራቸውን ልዩ ዝምድና በ33 ዓ.ም. አጡ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ “ከአሕዛብ መካከል ለስሙ የሚሆኑ ሰዎችን ለመውሰድ . . . ለእነሱ ትኩረት [ሰጠ]።” (ሥራ 15:14) ይሖዋ የመረጠው ይህ አዲስ ብሔር ‘የአምላክ እስራኤል’ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ከተለያዩ ብሔራት የተውጣጡ ቅቡዓን የክርስቶስ ተከታዮችን ያቀፈ ነው።—ገላ. 6:16

17. ሰይጣን የጠነሰሰው የትኛው ሴራ ተሳክቶለታል?

17 በ44 ዓ.ም. ገደማ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት “በመለኮታዊ አመራር . . . ‘ክርስቲያኖች’ ተብለው [ተጠሩ]።” (ሥራ 11:26) መጀመሪያ ላይ በዚህ ስም የሚጠሩት እውነተኛ ክርስቲያኖች ብቻ ስለነበሩ ይህ መጠሪያ ማንን እንደሚያመለክት ግልጽ ነበር። (1 ጴጥ. 4:16) ይሁንና ኢየሱስ ስለ ስንዴና እንክርዳድ በተናገረው ምሳሌ ፍጻሜ መሠረት ሰይጣን፣ ክርስቲያን በሚለው ልዩ መጠሪያ አስመሳይ ክርስቲያኖች በሙሉ እንዲጠቀሙበት ለማድረግ የጠነሰሰው ሴራ ተሳካለት። በዚህም የተነሳ ለበርካታ ዘመናት እውነተኛ ክርስቲያኖችን ከአስመሳይ ክርስቲያኖች መለየት አስቸጋሪ ነበር። ይህ ሁኔታ ግን በ1914 ከጀመረው ‘የመከር ወቅት’ አንስቶ መለወጥ ጀመረ። ለምን? መላእክት፣ አስመሳይ ክርስቲያኖችን ከእውነተኞቹ ክርስቲያኖች መለየት ስለጀመሩ ነው።—ማቴ. 13:30, 39-41

18. ወንድሞቻችን አዲስ ስያሜ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲያስተውሉ የረዳቸው ምንድን ነው?

18 በ1919 ታማኙ ባሪያ ከተሾመ በኋላ፣ ይሖዋ ለሕዝቦቹ የሰጣቸው ሥራ ምን እንደሆነ ማስተዋል እንዲችሉ ረዳቸው። ከአስመሳይ ክርስቲያኖች ሁሉ የሚለያቸው ከቤት ወደ ቤት መስበካቸው እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደባቸውም። ይህን ከተገነዘቡ በኋላ “የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች” የሚለው ስያሜ ከሌሎች የተለዩ መሆናቸውን ያን ያህል እንደማይጠቁም አስተዋሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛ ዓላማቸው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ብቻ ሳይሆን ስለ አምላክ መመሥከር እንዲሁም ስሙን ማክበርና ከፍ ከፍ ማድረግ ነው። ታዲያ የሚሠሩትን ሥራ በደንብ የሚገልጸው ስያሜ የትኛው ነው? ይህ ጥያቄ በ1931 መልስ አገኘ።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1931 በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ያደረጉት ትልቅ ስብሰባ ፕሮግራም

የትልቅ ስብሰባ ፕሮግራም፣ 1931

19, 20. (ሀ) በ1931 በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ምን አስደሳች የአቋም መግለጫ ቀርቦ ነበር? (ለ) ወንድሞቻችን አዲስ ስያሜ እንዳገኘን ሲሰሙ ምን ተሰማቸው?

19 ሐምሌ 1931 በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ 15,000 ገደማ የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተገኝተው ነበር። ተሰብሳቢዎቹ በስብሰባው ፕሮግራም የፊት ገጽ ላይ የታተሙት J እና W የሚሉት ሁለት ትላልቅ የእንግሊዝኛ ፊደላት ምን እንደሚያመለክቱ ጥያቄ ተፈጥሮባቸው ነበር። አንዳንዶች ‘ጀስት ዋች’ ሌሎች ደግሞ ‘ጀስት ዌይት’ ማለት እንደሆነ ገመቱ። ከዚያም እሁድ፣ ሐምሌ 26 ወንድም ጆሴፍ ራዘርፎርድ “የይሖዋ ምሥክሮች . . . [በሚለው] ስም ለመታወቅና ለመጠራት እንፈልጋለን” የሚለውን ሐሳብ የያዘ የአቋም መግለጫ አቀረበ። በዚህ ጊዜ፣ በስብሰባው ላይ የተገኙት በሙሉ J እና W የሚሉት የእንግሊዝኛ ፊደላት ጀሆቫስ ዊትነስስ (የይሖዋ ምሥክሮች) የሚሉትን ቃላት እንደሚያመለክቱና ይህም በኢሳይያስ 43:10 ላይ የተመሠረተ ቅዱስ ጽሑፋዊ መጠሪያ እንደሆነ ተገነዘቡ።

20 ተሰብሳቢዎቹ የአቋም መግለጫውን መቀበላቸውን ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የገለጹ ሲሆን ጭብጨባቸውም በአዳራሹ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር አስተጋባ። ፕሮግራሙ በሬዲዮ ይተላለፍ ስለነበር በኮሎምበስ፣ ኦሃዮ የነበሩት ተሰብሳቢዎች ደስታቸውን በጭብጨባ ሲገልጹ በአብዛኞቹ የዓለም ክፍሎች ያሉ ሰዎች መስማት ችለው ነበር! በአውስትራሊያ የነበሩት ኧርነስትና ኔኦሚ ባርበር እንዲህ በማለት ያስታውሳሉ፦ “በአሜሪካ ያሉት ወንድሞች ሲያጨበጭቡ በሜልቦርን ያሉ ወንድሞችም ከመቀመጫቸው ተስፈንጥረው በመነሳት አጨብጭበዋል፤ ያንን ጊዜ መቼም ቢሆን አንረሳውም!”a

የአምላክ ስም በዓለም ዙሪያ ከፍ ከፍ እየተደረገ ነው

21. አዲሱ መጠሪያችን የስብከቱን ሥራ ይበልጥ ያቀጣጠለው እንዴት ነው?

21 የአምላክ አገልጋዮች፣ የይሖዋ ምሥክሮች በሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም መጠራት መጀመራቸው በስብከቱ ሥራ እንዲካፈሉ ተጨማሪ ኃይል ሰጣቸው። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩና በ1931 በኮሎምበስ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የነበሩ ኤድዋርድና ጄሲ ግራይምዝ የተባሉ አቅኚ ባልና ሚስት እንዲህ ብለዋል፦ “ወደ ስብሰባው ስንሄድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነበርን፤ የተመለስነው ግን የይሖዋ ምሥክሮች ሆነን ነው። የአምላካችንን ስም ከፍ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል መጠሪያ ስላገኘን ተደስተን ነበር።” ከስብሰባው በኋላ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን ስም ከፍ ከፍ ለማድረግ የሚያስችል አዲስ ዘዴ መጠቀም ጀመሩ። ከቤት ወደ ቤት በሚያገለግሉበት ወቅት ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ለቤቱ ባለቤት በሚሰጡት ካርድ ላይ “ስለ አምላካችን ስለ ይሖዋ መንግሥት የሚሰብክ የይሖዋ ምሥክር” የሚል ሐሳብ ያሰፍሩ ነበር። በእርግጥም የአምላክ ሕዝቦች በይሖዋ ስም በመጠራታቸው ኩራት ተሰምቷቸው ነበር፤ እንዲሁም ይህ ስም ትልቅ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ከምድር ዳር እስከ ምድር ዳር ለማወጅ ተዘጋጅተው ነበር።—ኢሳ. 12:4

“ወደ ስብሰባው ስንሄድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ነበርን፤ የተመለስነው ግን የይሖዋ ምሥክሮች ሆነን ነው”

22. የይሖዋ ሕዝቦች ከሌሎች ሃይማኖቶች ተለይተው እንደሚታወቁ የሚያሳየው ምንድን ነው?

22 ይሖዋ፣ ቅቡዓን ወንድሞቻችንን ለይቶ በሚያሳውቃቸው ስም እንዲጠሩ ካደረጋቸው በርካታ ዓመታት አልፈዋል። ታዲያ ከ1931 ወዲህ ባሉት ዓመታት ሰይጣን፣ የአምላክ ሕዝቦች ማንነት እንዳይታወቅ ያደረገው ጥረት ተሳክቶለታል? ሰዎች፣ እኛን ከሌሎች ሃይማኖቶች መለየት አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው ማድረግ ችሏል? በፍጹም! እንዲያውም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ የአምላክ ምሥክሮች በመሆናችን ተለይተን እንታወቃለን። (ሚክያስ 4:5⁠ን እና ሚልክያስ 3:18⁠ን አንብብ።) ሰዎች የአምላክን ስም ከእኛ ጋር ስለሚያያይዙት ማንኛውም ሰው፣ ይሖዋ የሚለውን ስም ደጋግሞ የሚጠቀም ከሆነ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነ ያስባሉ። የይሖዋ እውነተኛ አምልኮ እንደ ተራራ ግዙፍ በሆኑት በርካታ የሐሰት ሃይማኖቶች ከመጋረድ ይልቅ “ከተራሮች አናት በላይ ጸንቶ [ቆሟል]።” (ኢሳ. 2:2) በእርግጥም በዛሬው ጊዜ የይሖዋ አምልኮና ቅዱስ ስሙ እጅግ ከፍ ከፍ ብለዋል።

23. በመዝሙር 121:5 መሠረት ስለ ይሖዋ የትኛውን እውነት ማወቃችን ያበረታታናል?

23 ሰይጣን ዛሬም ይሁን ወደፊት ከሚያመጣብን ጥቃት ይሖዋ እንደሚጋርደን ማወቁ ምንኛ የሚያበረታታ ነው! (መዝ. 121:5) “ይሖዋ አምላኩ የሆነ ብሔር፣ የራሱ ንብረት አድርጎ የመረጠው ሕዝብ ደስተኛ ነው” ብሎ የጻፈውን መዝሙራዊ ሐሳብ እኛም እንድናስተጋባ የሚያነሳሳን በቂ ምክንያት አለን።—መዝ. 33:12

a በሬዲዮ ይከናወን ስለነበረው ስብከት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ምዕራፍ 7 ከገጽ 72-74 ተመልከት።

የአምላክ መንግሥት ለአንተ ምን ያህል እውን ነው?

  • የአምላክ መንግሥት ከአምላክ ስም ጋር በተያያዘ ምን አከናውኗል?

  • የአምላክን ስም በመቀደስ ረገድ በግለሰብ ደረጃ ድርሻ ማበርከት የምትችለው እንዴት ነው?

  • በአምላክ ስም በመጠራትህ የምትኮራው ለምንድን ነው? የአምላክ ስም ትልቅ ቦታ ሊሰጠው እንደሚገባ ለሌሎች ለመናገር የምትጓጓውስ ለምንድን ነው?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ