የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w25 መስከረም ገጽ 14-19
  • ለሌሎች አክብሮት አሳዩ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ለሌሎች አክብሮት አሳዩ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሌሎችን ማክበር ሲባል ምን ማለት ነው?
  • ለቤተሰብህ አባላት አክብሮት አሳይ
  • ለእምነት አጋሮችህ አክብሮት አሳይ
  • እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎች አክብሮት ማሳየት
  • አክብሮት ማሳየት ቀረ እንዴ?
    ንቁ!—2024
  • አክብሮት በማሳየት ረገድ ቀዳሚ ነህ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • ለሥልጣን አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው?
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
  • አክብሮት ማሳየት የሚቻለው እንዴት ነው?
    ንቁ!—2016
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
w25 መስከረም ገጽ 14-19

የጥናት ርዕስ 38

መዝሙር 120 እንደ ክርስቶስ ገር መሆን

ለሌሎች አክብሮት አሳዩ

“መከበር ከብርና ከወርቅ ይሻላል።”—ምሳሌ 22:1

ዓላማ

ለሌሎች አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

1. ሰዎች መከበር የሚፈልጉት ለምንድን ነው? (ምሳሌ 22:1)

ሌሎች አክብሮት ሲያሳዩህ ደስ ይልሃል? እንደምትደሰት ጥያቄ የለውም። ሁሉም ሰዎች የመከበር ተፈጥሯዊ ፍላጎት አላቸው። ሰዎች ሲያከብሩን እንደሰታለን። መጽሐፍ ቅዱስ “መከበር ከብርና ከወርቅ ይሻላል” ማለቱ የሚያስገርም አይደለም።—ምሳሌ 22:1⁠ን አንብብ።

2-3. ለሌሎች አክብሮት ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል የማይሆነው ለምንድን ነው? አክብሮት ማሳየት ያለብንስ ለማን ነው?

2 ለሌሎች አክብሮት ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል ላይሆንልን ይችላል። አንደኛው ምክንያት፣ በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ያላቸውን ድክመት ስለምንመለከት ነው። በተጨማሪም የተከበብነው አክብሮት በሌላቸው ሰዎች ነው። እኛ ግን የተለየን መሆን አለብን። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ‘ሁሉንም ዓይነት ሰው እንድናከብር’ ይፈልጋል።—1 ጴጥ. 2:17

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ሌሎችን ማክበር ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚያም (1) ለቤተሰባችን አባላት፣ (2) ለእምነት አጋሮቻችን እንዲሁም (3) ከጉባኤ ውጭ ላሉ ሰዎች አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እናያለን። በተለይ ደግሞ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለሌሎች አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።

ሌሎችን ማክበር ሲባል ምን ማለት ነው?

4. ሌሎችን ማክበር ሲባል ምን ማለት ነው?

4 አክብሮት ምንድን ነው? አክብሮት ሲባል ለሰዎች ያለንን አመለካከትና እነሱን የምንይዝበትን መንገድ ያመለክታል። ለሌሎች አክብሮት ካለን ትኩረትና ቦታ እንደሚገባቸው አድርገን እንመለከታቸዋለን። እንዲህ የምናደርገው በባሕርያቸው፣ ባከናወኑት ሥራ ወይም በሥልጣናቸው የተነሳ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ለሌሎች አክብሮት ካለን፣ ከፍ ያለ ግምት እንደምንሰጣቸውና እንደምናደንቃቸው በሚያሳይ መንገድ እንይዛቸዋለን። ሆኖም አክብሮት የምናሳየው ከልባችን ተነሳስተን መሆን አለበት።—ማቴ. 15:8

5. ለሌሎች አክብሮት ለማሳየት የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

5 ይሖዋ ለሌሎች አክብሮት እንድናሳይ ይፈልጋል። ለምሳሌ ‘የበላይ ባለሥልጣናትን’ እንድናከብር አዞናል። (ሮም 13:1, 7) ሆኖም አንዳንዶች “አንድ ሰው አክብሮት የሚገባው ሆኖ እስከተገኘ ድረስ አከብረዋለሁ” ይሉ ይሆናል። እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ለሰዎች አክብሮት የምናሳየው በእነሱ ድርጊት ላይ ብቻ ተመሥርተን እንዳልሆነ እንገነዘባለን። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ለማድረግ የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ለይሖዋ ያለን ፍቅርና እሱን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት ነው።—ኢያሱ 4:14፤ 1 ጴጥ. 3:15

6. ለማያከብረን ሰው አክብሮት ማሳየት ይቻላል? አብራራ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)

6 አንዳንዶች ‘ለማያከብረን ሰው አክብሮት ማሳየት በእርግጥ ይቻላል?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል። አዎ፣ ይቻላል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። ንጉሥ ሳኦል ልጁን ዮናታንን በሌሎች ፊት አዋርዶት ነበር። (1 ሳሙ. 20:30-34) ያም ቢሆን ዮናታን፣ ሳኦል እስከሞተበት ዕለት ድረስ ከጎኑ ተሰልፎ በመዋጋት አክብሮት አሳይቶታል። (ዘፀ. 20:12፤ 2 ሳሙ. 1:23) ሊቀ ካህናቱ ኤሊ ሐናን እንደሰከረች በመግለጽ ስሟን አጥፍቷል። (1 ሳሙ. 1:12-14) ኤሊ እንደ አባትም ሆነ እንደ ሊቀ ካህናት የሠራቸው ስህተቶች እስራኤል ውስጥ በስፋት የሚታወቁ ቢሆንም ሐና ኤሊን በአክብሮት አነጋግራዋለች። (1 ሳሙ. 1:15-18፤ 2:22-24) ከዚህም ሌላ የአቴንስ ሰዎች ሐዋርያው ጳውሎስን “ለፍላፊ” በማለት ሰድበውታል። (ሥራ 17:18) ነገር ግን ጳውሎስ ያነጋገራቸው በአክብሮት ነው። (ሥራ 17:22) ከዚህ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው፣ ለይሖዋ ያለን ጥልቅ ፍቅርና እሱን ላለማሳዘን ያለን ጤናማ ፍርሃት ቀላል በሚሆንበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ተፈታታኝ በሚሆንበት ጊዜም ጭምር ለሌሎች አክብሮት እንድናሳይ ሊያነሳሳን ይገባል። ከዚህ በመቀጠል፣ አክብሮት ማሳየት ያለብን ለማን እንደሆነና እንዲህ ማድረግ ያለብን ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

ዮናታን፣ ሳኦል እና እስራኤላውያን ወታደሮች ሰይፍ፣ ጦርና ጋሻ ይዘው ሲዋጉ።

ዮናታን አባቱ ቢያዋርደውም እንኳ ከእሱ ጎን ተሰልፎ መዋጋቱንና ንግሥናውን መደገፉን ቀጥሏል (አንቀጽ 6ን ተመልከት)


ለቤተሰብህ አባላት አክብሮት አሳይ

7. የቤተሰባችንን አባላት በአክብሮት መያዝ አስቸጋሪ እንዲሆንብን የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?

7 ተፈታታኙ ነገር። ከቤተሰባችን ጋር ረጅም ጊዜ እናሳልፋለን። በዚህም የተነሳ ጠንካራ ጎናቸውንም ሆነ ድክመታቸውን እናውቃለን። አንዳንዶች ባለባቸው ሕመም የተነሳ እነሱን መንከባከብ አስቸጋሪ ነው፤ ሌሎች ደግሞ ከልክ ያለፈ ጭንቀት ሊኖርባቸው ይችላል። እንዲያውም አንዳንድ የቤተሰባችን አባላት እኛን የሚጎዳ ነገር ሊናገሩ ወይም ሊያደርጉ ይችላሉ። አንዳንዶች ቤታቸውን የእረፍትና የሰላም ቦታ ከማድረግ ይልቅ የቤተሰባቸውን አባላት አክብሮት በጎደለው መንገድ በመያዝ በቤተሰቡ ውስጥ ትርምስ ይፈጥራሉ። በዚህም የተነሳ በቤተሰቡ ውስጥ ስምምነት አይኖርም። የአርትራይተስ በሽታ የሰውነት ክፍሎች ተቀናጅተው እንዳይሠሩ እንቅፋት እንደሚሆነው ሁሉ አክብሮት ማጣትም የቤተሰብ አባላት በአንድነት እንዳይሠሩ እንቅፋት ይሆናል። ልዩነቱ ግን፣ የአርትራይተስ በሽታን በራሳችን ሙሉ በሙሉ ልናድነው ባንችልም አክብሮት ማጣትን አስወግደን የቤተሰባችንን አንድነት ማስጠበቅ እንችላለን።

8. ለቤተሰባችን አባላት አክብሮት ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8)

8 አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? (1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8⁠ን አንብብ።) ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ የቤተሰብ አባላት አንዳቸው ሌላውን መንከባከብ እንዳለባቸው ገልጿል። የቤተሰባችንን አባላት በዚህ መንገድ ለማክበር የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት ግዴታ ስለሆነብን ሳይሆን ‘ለአምላክ የማደርን ባሕርይ ለማንጸባረቅ’ ብለን እንደሆነ ገልጿል። ይህም ሲባል፣ ለቤተሰባችን አባላት አክብሮት የምናሳየው የአምልኳችን ክፍል እንደሆነ አድርገን ስለምንመለከተው ነው ማለት ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የቤተሰብን ዝግጅት ያቋቋመው ይሖዋ ነው። (ኤፌ. 3:14, 15) ስለዚህ የቤተሰባችንን አባላት ስናከብር የቤተሰብ መሥራች የሆነውን ይሖዋን እያከበርነው ነው። ለቤተሰባችን አባላት አክብሮት እንድናሳይ የሚያነሳሳ እንዴት ያለ ጠንካራ ምክንያት ነው!

9. ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

9 አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ሚስቱን የሚያከብር ባል ለብቻቸውም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሲሆኑ ሚስቱን እንደሚወዳት ያሳያል። (ምሳሌ 31:28፤ 1 ጴጥ. 3:7) በፍጹም አይመታትም፣ አያዋርዳትም ወይም ዋጋ ቢስ እንደሆነች እንዲሰማት አያደርግም። በአርጀንቲና የሚኖረው ኤርየልa እንዲህ ብሏል፦ “ሚስቴ ባለባት ሕመም የተነሳ አንዳንድ ጊዜ ስሜቴን የሚጎዳ ነገር ትናገራለች። ይህ በሚሆንበት ጊዜ፣ የተናገረችው ቃል እውነተኛ ስሜቷን የሚያንጸባርቅ እንዳልሆነ ለማስታወስ እሞክራለሁ። በቤተሰባችን ውስጥ ውጥረት የሚፈጥር ነገር ሲከሰት 1 ቆሮንቶስ 13:5⁠ን አስታውሳለሁ። ጥቅሱ ሚስቴን በሚያቃልል መንገድ ሳይሆን በአክብሮት እንዳነጋግራት ያነሳሳኛል።” (ምሳሌ 19:11) አንዲት ሚስት ስለ ባሏ በሌሎች ፊት መልካም ነገር በመናገር ታከብረዋለች። (ኤፌ. 5:33) በአሽሙር አትናገረውም፣ አታሾፍበትም እንዲሁም አትሰድበውም። እንዲህ ያለው ምግባር እንደ ዝገት ትዳራቸውን እንደሚያበላሸው ትገነዘባለች። (ምሳሌ 14:1) በጣሊያን የምትኖር አንዲት እህት ባለቤቷ ከባድ ጭንቀት አለበት። እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጊዜ ባለቤቴ ሳያስፈልግ እንደሚጨነቅ ይሰማኛል። ቀደም ሲል፣ የምናገረው ነገርና ፊቴ ላይ የሚነበበው ስሜት ለእሱ አክብሮት እንደጎደለኝ የሚያሳይ ነበር። ሆኖም ስለ ሌሎች በአክብሮት ከሚናገሩ ሰዎች ጋር ይበልጥ ጊዜ ማሳለፌ ለባለቤቴ ይበልጥ አክብሮት ለማሳየት እንደረዳኝ ይሰማኛል።”

ሥዕሎች፦ አንድ ባልና ሚስት አንዳቸው ለሌላው አክብሮት ሲያሳዩ። 1. ኩሽና ውስጥ ምግብ እያዘጋጁ ባልየው ሚስቱን በደግነት ሲያነጋግራት። 2. ባልየው ለአንድ አረጋዊ ወንድም ምግብ ሲያቀርብ ሚስትየዋ በእንግዶቹ ፊት ባሏን ስታሞግሰው።

ለቤተሰባችን አባላት አክብሮት ስናሳይ የቤተሰባችን ራስ የሆነውን ይሖዋን እናከብረዋለን (አንቀጽ 9ን ተመልከት)


10. ልጆች ለወላጆቻቸው አክብሮት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

10 ልጆች፣ ወላጆቻችሁ ያወጡላችሁን መመሪያ ታዘዙ። (ኤፌ. 6:1-3) ወላጆቻችሁን በአክብሮት አነጋግሯቸው። (ዘፀ. 21:17) ወላጆቻችሁ ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ የእናንተ እርዳታ ይበልጥ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። አቅማችሁ በፈቀደ መጠን ተንከባከቧቸው። የማሪያን ምሳሌ እስቲ እንመልከት፤ አባቷ የይሖዋ ምሥክር አይደለም። አባቷ በታመመ ጊዜ፣ በነበረው ባሕርይ የተነሳ እሱን ማስታመም ከባድ ሆኖባት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ለአባቴ አክብሮት እንዲኖረኝ ብቻ ሳይሆን አክብሮቴን ማሳየት እንድችልም እጸልይ ነበር። ይሖዋ ወላጆቼን እንዳከብር ካዘዘኝ እንዲህ ለማድረግ የሚያስፈልገውን ብርታት ይሰጠኛል የሚል መደምደሚያ ላይ ደረስኩ። አባቴን በአክብሮት ለመያዝ እሱ ባሕሪውን እስኪያስተካክል መጠበቅ እንደሌለብኝ ውሎ አድሮ ተገነዘብኩ።” የቤተሰባችን አባላት ድክመት ቢኖርባቸውም እንኳ አክብሮት ስናሳያቸው የይሖዋን ዝግጅት እንደምናከብር እናሳያለን።

ለእምነት አጋሮችህ አክብሮት አሳይ

11. የእምነት አጋሮቻችንን በአክብሮት መያዝ ሊከብደን የሚችለው ለምንድን ነው?

11 ተፈታታኙ ነገር። የእምነት አጋሮቻችን የሚመሩት በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ነው። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ደግነት በጎደለው መንገድ ሊይዙን፣ በተሳሳተ መንገድ ሊረዱን ወይም ሊያበሳጩን ይችላሉ። አንድ የእምነት አጋራችን ‘ቅር ካሰኘን’ እሱን በአክብሮት መያዝ ሊከብደን ይችላል። (ቆላ. 3:13) ታዲያ በዚህ ረገድ ምን ይረዳናል?

12. ለእምነት አጋሮቻችን አክብሮት ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (2 ጴጥሮስ 2:9-12)

12 አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? (2 ጴጥሮስ 2:9-12⁠ን አንብብ።) ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች “የተከበሩትን” ማለትም ክርስቲያን ሽማግሌዎችን አስመልክቶ አክብሮት የጎደለው ነገር ይናገሩ እንደነበር ጽፏል። ታዲያ ሁኔታውን ይመለከቱ የነበሩ ታማኝ መላእክት ምን ተሰማቸው? “ለይሖዋ ካላቸው አክብሮት የተነሳ” እነዚህን ዓመፀኞች አንድም የስድብ ቃል አልተናገሯቸውም። እስቲ አስበው! ፍጹም የሆኑት መላእክት እነዚህን እብሪተኞች ክፉ ቃል ለመናገር ፈቃደኞች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ እንዲፈርድባቸውና እንዲገሥጻቸው ጉዳዩን ለይሖዋ ትተውታል። (ሮም 14:10-12፤ ከይሁዳ 9 ጋር አወዳድር።) እኛም ከእነዚህ መላእክት ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ተቃዋሚዎቻችንን እንኳ አክብሮት በጎደለው መንገድ መያዝ ከሌለብን የእምነት አጋሮቻችንንማ ምንኛ ልናከብራቸው ይገባል! እንዲያውም እነሱን ለማክበር ‘ቀዳሚ መሆን’ ይኖርብናል። (ሮም 12:10) እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋን እንደምናከብር ያሳያል።

13-14. ለእምነት አጋሮቻችን አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (ሥዕሎቹንም ተመልከት።)

13 አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ሽማግሌዎች፣ ምንጊዜም ጉባኤውን በፍቅር ለማስተማር ጥረት አድርጉ። (ፊልሞና 8, 9) ለአንድ ሰው ምክር መስጠት ካስፈለጋችሁ በደግነት ምከሩት፤ ተበሳጭታችሁ ሳለ ምክር ከመስጠት ተቆጠቡ። እህቶች፣ ከሐሜትና ስም ከማጥፋት በመቆጠብ በጉባኤ ውስጥ አክብሮት እንዲሰፍን ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላላችሁ። (ቲቶ 2:3-5) ሁላችንም ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር በመተባበር ለእነሱ አክብሮት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። በተጨማሪም ስብሰባዎችን በመምራት፣ የስብከቱን ሥራ በማደራጀት እንዲሁም “የተሳሳተ ጎዳና” የተከተሉትን በመርዳት በትጋት ለሚያከናውኑት ሥራ አድናቆታችንን በመግለጽ አክብሮታችንን ማሳየት እንችላለን።—ገላ. 6:1፤ 1 ጢሞ. 5:17

14 ሮሲዮ የተባለች አንዲት እህት ምክር ለሰጣት ሽማግሌ አክብሮት ማሳየት ከብዷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ደግነት በጎደለው መንገድ እንዳነጋገረኝ ስለተሰማኝ ቅር አለኝ። ለቤተሰቦቼ ስለ እሱ አሉታዊ ነገር ተናገርኩ። ይህን ስሜቴን ሌሎች እንዲያውቁብኝ ባልፈልግም፣ ምክር የሰጠኝ ሊረዳኝ ፈልጎ እንደሆነ አልተሰማኝም። በመሆኑም ምክሩን ችላ አልኩት።” ታዲያ ሮሲዮን የረዳት ምንድን ነው? እንዲህ ብላለች፦ “በመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤ ላይ 1 ተሰሎንቄ 5:12, 13⁠ን አነበብኩ። ለዚህ ወንድም አክብሮት እያሳየሁት እንዳልሆነ ስገነዘብ ሕሊናዬ ይረብሸኝ ጀመር። ወደ ይሖዋ ጸለይኩ፤ እንዲሁም አመለካከቴን ለማስተካከል የሚረዳ ሐሳብ ለማግኘት በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር አደረግኩ። ውሎ አድሮ ችግሩ ያለው ወንድም ላይ እንዳልሆነ ተገነዘብኩ፤ ችግሩ እኔ ኩራተኛ መሆኔ ነው። በትሕትናና ሌሎችን በማክበር መካከል ቀጥተኛ ተዛማጅነት እንዳለ አሁን ተገንዝቤያለሁ። አሁንም ቢሆን ማስተካከያ ማድረግ ያስፈልገኛል፤ ሆኖም አክብሮት ለማሳየት ጥረት በማድረጌ ይሖዋ እንደሚደሰትብኝ ይሰማኛል።”

ሥዕሎች፦ አንዲት አረጋዊት እህት መጽሐፍ ቅዱስ እያነበበች ሽማግሌዎች በትጋት የሚሠሩባቸውን የተለያዩ መንገዶች ስታስብ። 1. አንድ ሽማግሌ በጉባኤ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያቀርብ። 2. ዊልቼር የሚጠቀምን ወንድም ሲረዳ። 3. በስብሰባ አዳራሹ ደጅ ላይ ያለውን በረዶ ሲጠርግ።

ሁላችንም ከሽማግሌዎች ጋር በመተባበርና በትጋት ለሚያከናውኑት ሥራ አድናቆታችንን በመግለጽ እንደምናከብራቸው ማሳየት እንችላለን (አንቀጽ 13-14ን ተመልከት)


እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎች አክብሮት ማሳየት

15. እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎች አክብሮት ማሳየት ሊከብደን የሚችለው ለምንድን ነው?

15 ተፈታታኙ ነገር። ብዙውን ጊዜ አገልግሎት ስንወጣ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍቅር የሌላቸው ሰዎች እናገኛለን። (ኤፌ. 4:18) አንዳንዶች ከልጅነታቸው ጀምሮ በተማሩት ነገር የተነሳ መልእክታችንን ለማወቅ እንኳ ፍላጎት የላቸውም። በቀላሉ የማይደሰቱ አሠሪዎች ወይም አስተማሪዎች ይኖሩን ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆች ባሕርያቸው አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ለእነዚህ ሰዎች ያለን አክብሮት ሊቀንስና እነሱን በደግነት መያዝ ሊከብደን ይችላል።

16. ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎችን በአክብሮት መያዛችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (1 ጴጥሮስ 2:12፤ 3:15)

16 አክብሮት ማሳየት ያለብን ለምንድን ነው? ይሖዋ አማኝ ያልሆኑ ሰዎችን የምንይዝበት መንገድ እንደሚያሳስበው አስታውስ። ሐዋርያው ጴጥሮስ በወቅቱ የነበሩትን ክርስቲያኖች መልካም ምግባራቸው አንዳንዶች ‘አምላክን እንዲያከብሩ’ ሊያነሳሳቸው እንደሚችል ገልጾላቸዋል። በዚህም የተነሳ “በገርነት መንፈስና በጥልቅ አክብሮት” ለእምነታቸው ጥብቅና እንዲቆሙ አሳስቧቸዋል። (1 ጴጥሮስ 2:12፤ 3:15⁠ን አንብብ።) ክርስቲያኖች በእምነታቸው ምክንያት ፍርድ ቤት ሲቀርቡም ሆነ በጎረቤቶቻቸው ፊት ለእምነታቸው ጥብቅና ሲቆሙ አማኝ ያልሆኑ ሰዎችን መያዝ የሚኖርባቸው ይሖዋ በሚፈልገው መንገድ ነው። ደግሞም ይሖዋ የምንናገረውን ነገርና የምንናገርበትን መንገድ ልብ ብሎ ይከታተላል። ይህ እምነታችንን የማይጋሩ ሰዎችን በአክብሮት ለመያዝ የሚያነሳሳ አሳማኝ ምክንያት ነው።

17. እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎች አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? አገልግሎት ላይ ስንሆን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት የሌላቸውን ሰዎች እንደምንንቅ የሚያስመስል ነገር ማድረግ ፈጽሞ አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ሰዎቹን በአምላክ ዘንድ የከበሩ እንደሆኑና ከእኛ እንደሚበልጡ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። (ሐጌ 2:7፤ ፊልጵ. 2:3) አንድ ሰው በእምነትህ የተነሳ ከሰደበህ የአሽሙር ንግግር በመናገር አጸፋውን ከመመለስ ተቆጠብ። (1 ጴጥ. 2:23) እንዲጸጽትህ የሚያደርግ ነገር ከተናገርክ ወዲያውኑ ይቅርታ ጠይቅ። በሥራ ቦታ ለምታገኛቸው ሰዎችስ አክብሮት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ታታሪ ሠራተኛ ሁን፤ እንዲሁም ለሥራ ባልደረቦችህና ለአሠሪዎችህ ጥሩ አመለካከት ለማዳበር ጥረት አድርግ። (ቲቶ 2:9, 10) ሐቀኛ፣ ታታሪና ትጉ ሠራተኛ ከሆንክ ሰዎች ይደሰቱብሃል፤ ግን እነሱ ባይደሰቱም እንኳ አምላክን እንደምታስደስት ምንም ጥያቄ የለውም።—ቆላ. 3:22, 23

18. ለሌሎች አክብሮት ማዳበራችንና ማሳየታችን የማያስቆጭ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

18 በእርግጥም ለሌሎች አክብሮት ለማዳበርና ለማሳየት የሚያነሳሳ አጥጋቢ ምክንያት አለን! እስካሁን እንደተመለከትነው፣ ለቤተሰባችን አክብሮት የምናሳይ ከሆነ የቤተሰባችን ራስ የሆነውን ይሖዋን እናከብረዋለን። በተመሳሳይም ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አክብሮት የምናሳይ ከሆነ የሰማዩን አባታችንን እናከብረዋለን። ከዚህም ሌላ፣ እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎች አክብሮት የምናሳይ ከሆነ ታላቁን አምላካችንን ለማክበር እንዲነሳሱ ሁኔታውን እናመቻችላቸዋለን። አንዳንድ ሰዎች በምላሹ አክብሮት ባያሳዩንም እንኳ ለእነሱ አክብሮት ማዳበራችንና ማሳየታችን አያስቆጭም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ይባርከናል። “የሚያከብሩኝን አከብራለሁ” በማለት ቃል ገብቶልናል።—1 ሳሙ. 2:30

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

  • ለቤተሰባችን አባላት አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

  • ለእምነት አጋሮቻችን አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

  • እምነታችንን ለማይጋሩ ሰዎች አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

መዝሙር 129 ጸንተን እንጠብቃለን

a አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ